Wednesday, July 18, 2012

የመለስ ዜናዊ ‘ሀሁ’ በስልጣን ጎዳና


መለስ ዜናዊ (የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር)
ልደት፡- ሚያዝያ 30፣ 1947
የኅወሓት ሊቀመንበርነት፡- ከ1981 ጀምሮ
የኢሕአዲግ ሊቀመንበርነት፡- ከ1981 ጀምሮ
የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት፡- ከ1983 – 1987
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር - ከ1987 - አሁን
“ብልቡ ዝሸፈተ ምመልሲ ይብለን” ይባላል በትግርኛ፤ ‘በልቡ የሸፈተን የሚመልሰው የለም’ እንደማለት!

የታሪኩ መጀመሪያ

የሕወኅት ወላጅ ከሆነው ማገብት (ማኅበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) መስራች አባላት አንዱ የሆኑት አረጋዊ በርኸ (ከነፃ አውጪ ታጋይነት ወደምሁርነት የተሸጋገሩ ስደተኛ ምሁር ናቸው፤) The Origin of The Trigray People’s Liberation Front በሚለው ጥናታቸው ላይ እንዳሰፈሩት መጀመሪያ ትግራዋይ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሕብረት ተፈጠረ፡፡ የኅብረቱ አባላት ከሆኑት ውስጥ መለስ ተክሌ እና አባይ ፀሃዬ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ማሕበሩ አርታኢ ቡድንን ይመሩ ነበር፡፡ የኅብረቱ ዋነኛ ዓላማ ለትግራይ ሕዝቦች ፖለቲካዊ ንቃት ማጎናፀፍ ብቻ ስለነበር፣ ከዚያ የተሻለ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲችል በሚል ማገብት ተወለደ፡፡ ማገብት የኅወሓት ወላጅ እናት ነው፡፡

ማገብት ሕወሓትን ከመመስረቱ በፊት ከኅግሓኤ (ሕዝባዊ ግምባር ሓርነት ኤርትራ) ጋር የሥራ ግንኙነት መስርቶ ነበር፤ (ስሙም ከዚያው የተገኘ ይመስላል፡፡) መለስ ከኅወሓት፣ ጥቂት ቀደምት አባላት አንዱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ መጽሐፍት እንደሚተርኩት መለስ ዜናዊ እና አቦይ ስብሓት የኅወሓት መስራች ሳይሆኑ፣ ከተመሰረተ ጥቂት ወራት በኋላ ትግሉን የተቀላቀሉ መሆናቸውን A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia በተሰኘው የዶክትሬት ድግሪ ማሟያ ጽሑፋቸው ላይ አረጋዊ በርኸ ጽፈዋል፡፡ 



መለስ ዜናዊ (የያኔው ለገሠ ዜናዊ) የሕክምና ሳይንስ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሽምቅ ተዋጊነትን የመረጡት በተለይ የትግራይን፣ ብሎም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ነፃነት በመናፈቅ እንደሆነ ድርሳናት ይተርካሉ፡፡ ይሁን እንጂ ገና ትግሉ ከመጀመሩ በፊት መስራቾቹ የተመቻቸ ጊዜ ሲጠብቁ መለስ የደረሱበት ጠፍቶ ነበር፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ግን በኤርትራ፣ የእናታቸው መንደር ከሆነችው አዲ ቋላ ተገኝተዋል፡፡ እንዲህ እያለ፣ እያለ ከዓመታት በኋላ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ሊግ ኦቭ ትግራይ (ማሌሊት) ከኅውሓት ጎን ለጎን ተፈጠረ፤ ይህ ሊግ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊውን ርዕዮተ ዓለም እና የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የምትለዋ ሐረግን በማኒፌስቶው የያዘ ሲሆን በዚህ ግራ ዘመም እና እስካሁንም ድረስ ተፅዕኖው እንዳለ በሚነገርለት የማሌሊት ፖለቲካ ውስጥ የመለስ ዜናዊ ሚና በእጅጉ የጎላ እንደነበር ይነገራል፡፡

የመለስ ዜናዊ ስልጣን የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1979 ኅወሓት የመጀመሪያውን የድርጅት ቻርት ሲያወጣ ነው -የፕሮፓጋንዳ ክፍሉ (ክፍሊ ፖለቲካ)፣ የአባይ ፀሃዬ ምክትል በመሆን፡፡ ይህ ማዕረግ ምናልባትም ብዙ የሚነገርለትን የመለስን አንደበተ ርዕቱነትን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሹመት ነበር፡፡

የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ አመጣጥ
መለስ እስካሁን ድረስ በቅጡ “መፍታት ወይም መበየን” የሚችል ሰው አልተገኘም የሚባልለትን አብዮታዊ ዲሞክራሲን ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ብቸኛው ዲሞክራሲያዊ ርዕዮተ ዓለም ነው ሲሉ የሚከራከሩት ‹የአብዮታዊ ዲሞክራሲ› ሰያሚም ሆነ ፈጣሪ ራሳቸው መለስ ስለሆኑ ነው በሚል በተደጋጋሚ ያሳማቸዋል፡፡ አረጋዊ በርኸ እንደሚተርኩት ‹ሕዳር 1978 መለስ ዜናዊ “አፈላላይጥና ኣብ ግልፂ መድረክ ንክሪብ” (‘ልዩነታችንን በግልፅ መድረክ እንነጋገር’) የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ጻፉ፡፡ ይህንን ሌሎችን በግልጽነት መተቸት ነው የተባለለትን ጽሑፍ ተከትሎ እና የሌኒንን ‘Bourgeois Democracy and the Proletarian Dictatorship’ የተሰኘ ጥናት መሠረት አድርጎ አቢዮታዊ ዴሞክራሲ በራሳቸው በመለስ ዜናዊ ተፈጥሯል፡፡

መለስ ዜናዊ የኅወሓት አመራሮች ኮሚቴ ውስጥ በ1971፣ የሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ውስጥ ደግሞ በ1975 ለመግባት ችለዋል፡፡ ትልቁን ስልጣን ማለትም የኅወሓትን ሊቀመንበርነት ማግኘት የቻሉት የዛሬ 23 ዓመት (በ1981) ከስብሓት ነጋ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ቀድሞም ቢሆን የአመራሮችን የስልጣን ዕድሜ ገደብ የሚገድብ መመሪያ የሌለው ኅወሓት በመለስ ዜናዊ የ21 ዓመታት አመራርም ተተኪ መሪ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ይልቁንም መለስ ዜናዊ ከ10 ዓመት አመራር በኋላ በመልካም ፈቃድ ስልጣናቸውን ካስረከቧቸው አቦይ ስብሓት የተማሩት ነገር እንዳለ በተግባር አላሳዩም፡፡ እንዲያውም በፓርቲው መካከል የተፈጠረው ልዩነት የፈጠረላቸውን ዕድል ተጠቅመው አሁን ፓርቲው ውስጥ ያላቸውን የሁሉ ባለቤትነት መብት እና ስልጣን ስብሓት ነጋ ያኔ ከነበራቸው ስልጣን በእጅጉ የበለጠ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

የሦስት ልጆች አባት ለመሆን የበቁት አቶ መለስ ዜናዊ፣ የኅወሓትም የኢሕአዲግም ሊቀመንበር ሆነው ከ23 ዓመታት በላይ አሳልፈዋል፡፡ እስከዛሬ በ21 ዓመት የኢሕአዴግ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ሥራ ውስጥም ትልቁን ስልጣን የያዙት እርሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ (4 ዓመታት በሽግግር መንግስቱ ፕሬዚደንትነት እና 17 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስቴርነት፡፡)

የመለስ ፈተና እና አስተላለፍ
መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመናቸው አልጋ ባልጋ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ከሁሉም የበለጠ ፈተና ገጥሟቸው የነበረው ግን መለስ እነስዬ የገቡበትን አዘቅት ለማጣጣል ቦናፓርቲዝም ሲሉ የጠሩት የኅወሓት መከፋፈል (ሕንፍሽፍሽ) እና ምርጫ 1997 ሳይጠቀሱ የማይታለፉት ናቸው፡፡ ቦናፓርቲዝም ለኅወሓት የመጀመሪያው የመከፋፈል አደጋ አልነበረም፣ የመጀመሪያው ሕንፍሽፍሽ በሚል የሚታወሰውና በትግሉ ወቅት ተከስቶ የነበረው ገበሬ ታጋዮች፣ ተማሪ መሪዎቻቸውን ለማስወገድ የሞከሩበት መከፋፈል ይቀድመዋል፡፡ ሆኖም በመለስ የስልጣን ሕልውና ላይ በዋናነት ጥላውን ያጠላው የ1993ቱ ሕንፍሽፍሽ ነበር፡፡

በተለይም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት (ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሩቅ ዝምድና አላቸው የሚባሉት) ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ በኤርትራ ላይ ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ ባለመፈለጋቸው ተከስቶ የነበረው ግጭት ተጋግሎ፣ የኅወሓትን ሕልውና እና የመለስ ዜናዊን ስልጣን አደጋ ላይ ከጣለ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቃራኒያቸውን የእነአቶ ተወልደ ቡድን አጀንዳ ተነጥለው የወጡት እንደሚሉት “በመስረቅና የራሳቸው በማስመሰል” ድሉ በእጃቸው እንዲገባ ለማድረግ ችለዋል፡፡ ምንም እንኳን የዚህ ታሪክ አተናተን እስካሁንም ድረስ ሁለቱንም ቡድኖች የሚያግባባ ደረጃ ላይ ባይደርስም እርሱን ተከትሎ በሙስና አቶ ስዬን ማሳሰሩ፣ የአቶ ተወልደ ድምጽ መጥፋቱ መለስ ዜናዊ ለስልጣን ያላቸውን ቀናኢነት ትዝብት ውስጥ የጣለ ነበር፡፡

ከዚህ የኅወሓት መከፋፈል በኋላ፣ መለስን ይፎካከሩ የነበሩት የሕወሓት አባላት እነስዬ፣ ገብሩ አስራት እና አስገደ በመወገዳቸው ያለአንድም ተቀናቃኝ በብቸኝነት የስልጣን መንበሩ ላይ ተደላደሉበት፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን የሌሎቹ የኢሕአዲግ አባል ፓርቲዎች የኅወሓት ተገዢነት የሚታሙ በመሆኑ ከዚያ ውስጥ እርሳቸውን የሚፎካከር ግለሰብ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡

ከዚያ በኋላ፣ በራሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንከን አልባ” እንደሚሆን የተነገረለት ምርጫ 97ትን ተከትሎ የተነሳው አለመግባባት እና ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ ሌላው የመለስን መንበር የነቀነቀ አጋጣሚ ነበር፡፡ ይሁንና መንግስታቸው ባመነው ብቻ በ200 ወጣቶች ሞትና፣ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች (ጋዜጠኞችን ጨምሮ) እስር ተቋጭቷል፡፡ ከዚህ አጋጣሚ በኋላ መለስ እንደግለሰብም ሆነ የሚመሩት ኢሕአዲግ እንደፓርቲ ስልጣን በምርጫ የማስረከባቸውን ነገር በጥያቄ የሚያዩት አልጠፉም፡፡እነዚህ አካላትየአውራ ፓርቲ ኀልዮት እና የ40 ዓመት ዕቅዶቹን የመሳሰሉ የፓርቲ ሰነዶችን በዐብይ ምሳሌነት ያነሳሉ፡፡

መለስ ከኅወሓት መከፋፈል በኋላ ተቀናቃኞቻቸውን በሙሉ በመኮርኮም ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል በሚል የሰብአዊ መብት ተሟጋቶች እና ተቃዋሚዎች ሲወቅሱዋቸው ይደመጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውስጠ ፓርቲ የመቀናቀን አቅም ያላቸውን አባላትንም ቢሆን ዕድል በመንፈግ ይታማሉ፡፡ ለአብነትም የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት ከማንኛውም የኢሕአዲግ/ኅውሓት ባለስልጣን በላይ ተቀባይነት አግኝተው የነበሩትን እና አሁን ፓርቲው የሚኩራራባቸውን ኮንዲሚኒዬም ቤቶችና ጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮጀክቶች ያስጀመሩትን አርከበ ዕቁባይን መጥቀስ ይቻላል፡፡ መለስ የአርከበ ዕቁባይን ሥራ “ቀለም የመቀባት ሥራ” ሲሉ አጣጥለውት ነበር የሚሉ የውስጥ አዋቂ ወጎችም አልጠፉም፡፡

ዊኪሊክስ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ደግሞ፣ የዛሬ ሦስት ዓመት በተካሄደ የኅወሓት የሊቀመንበር ምርጫ መለስ ሳይሆኑ አርከበ ዕቁባይ ተመርጠው እንደነበር ያትታል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መሰሉ ጫና ብዙ ፈተና ያለፉት አርከበ የምርጫውን ውጤት እና የተመረጡበትን ስልጣን አለመቀበላቸውን ጠቅሰው የአሜሪካ አምባሳደር ጽፈዋል፡፡ ‹መለስ ከኃላፊነታቸው ይልቅ ስልጣናቸውን ይወዱ ነበር ወይ?› የሚለው ክርክር ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በተለያየ ወቅቶች በታዩ እርምጃዎቻቸው ለመደምደም ከባድ አይሆንም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ካልተጠቀሱትም ሆነ ጭራሹኑ ካልተነኩት ብዙ ታሪኩች ትዝታ በመነሳት ሊቀናቀኗቸው የሚችሉትን ሁሉ ገለል በማድረግ የፓርቲያቸውን ፖለቲካዊ መሪ የመፍጠር ኃላፊነት ሳይቀር ከንቱ በማስቀረት ‹የማን ይተካቸው እና የአትሄድብን› አጀንዳ የፓርቲው ታላቅ ጉዳይ እንዲሆን ማድረጋቸው ለትዝብት ዳርጓቸዋል፡፡  

በዚህ ስልጣንን ለብቻ የመቆጣጠር ታሪክ ኪሳራ አለ ከተባለ የከሰረው ፓርቲው እና አገሪቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጭምር ይሆናሉ፡፡ ጠ/ሚ መለስ ወጣትነታቸውን የሰዉለት የ17 ዓመት ትግል ሕዝብን የስልጣን ባለቤት የማድረግ ሕልም ነው ቢባልም፣ ከታገሉበት ዓመታት በላይ ስልጣን ላይ በመቆየት እና ለቦታው የሚመጥን ተተኪ ባለማፍራት የታገሉትን አምባገነናዊ ስርዓት በእጅ አዙር አምጥተውታል ብለው የሚሟገቱ ጥቂቶች አይደሉም፡፡፡

አረጋዊ በርኸ በጦርነት እና በትግል ወቅት ጥሩ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የሚያደርግ ሰው (activist) በቀላሉ የእንቅስቃሴው መሪ ተደርጎ የመመረጥ እድል እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የተመረጡ መሪዎችን ለማስወገድ ግን ራሱን የቻለ፣ ሌላ ከፍተኛ ትግል እንደሚጠይቅ ከላይ በተጠቀስው የዶክትሬት ማሟያ ጽሑፋቸው ተናግረዋል፡፡ መለስ ዜናዊ፣ ኢሳያስ አፈወርቂን እና ዮዎሪ ሙሴቪኒን የዚህ ሁነኛ ምሳሌ ሲሉም ጠቅሰዋቸዋል፡፡

እንግዲህ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በጠና እንደታመሙ ከበቂ በላይ ዜናዎች አረጋግጠዋል፡፡ በጽሁፌ መግቢያ ላይ የተዋስኩትን አባባል፣ አረጋዊ በርኸ የተጠቀሙበት የኅወሓትን ከዜሮ ተነስቶ ለድል መብቃትን ለመዘከር ቢሆንም፣ እኔ ግን በተቃራኒው ልዋሳቸው እወደድኩ፡፡ እንደቡድኖች ሁሉ ግለሰቦችም በልባቸው የሚወስኑት ነገር ይኖራቸዋልና መለስም ለዚህ ሁሉ ጠቅላይ ገዢነት  ያበቃቸው በልባቸው የነበረው የመምራት ፍላጎት ነው - እውነትም ‹በልቡ የሸፈተን የሚመልሰው የለም!› እንዲሉ - ለስልጣንም ቢሆን!!!

No comments:

Post a Comment