የመንግስት ኮምንኬሽን ጉዳዮች በነገሩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ቢሞክርም የአቶ መለስን “ቀላል ህመም” ከማመን ይልቅ አሁንም ኢትዮጵያ በዚሁ ዜና እውነትነት እና ውሸትነት ዙሪያ እየተናጠች ትገኛለች - የሚያሳምን እና የተረጋገጠ መረጃ የሚሰጥ እስካሁን አልተገኘም እንጂ! ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ታመዋል፣ ኧረ እንዲያውም ሞተዋል፣ አይ… መዳከም ነው እንጂ ደህና ናቸው… ወ.ዘ.ተ›› የሚሉ መላምቶች አሁንም በየፊናው ይሰነዘራሉ፡፡ ይህ ዜና እየተናፈሰ ባለበት በዚህ የውጥረት ሰሞን አንድ የመንግስት ኃላፊ ወጥቶ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ረዥም ጊዜ መውሰዱ መንግስትን ትዝብት ላይ ቢጥለውም ከአቶ በረከት መግለጫ በኋላ ደግሞ የመረጃው ትክክለኛነት ለማመን እንኳን ሳይሞክሩ፣ ብዙዎች በተከታዩ የድኅረ መለስ ዘመን ላይ እያወሩ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (እንደ ኮምንኬሽን ሚኒስትሩ ንግግር ቀላሉን ያርግላቸውና) ከዚህ በኋላ አገሪቱን መምራት የማይችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ቀጥሎ ምን ይከሰት ይሆን?›› የሚለው ልብ አንጠልጣይ ጥያቄም በተለያዩ ሰዎች እና አካላት ዘንድ የመወያያ አጀንዳ እየሆነ ይገኛል፡፡
የአቶ መለስ አለመኖር…
የኅወሓት ‹‹የነፍስ አባት›› አቦይ ስብሃት ነጋ በቅርቡ ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ንግግር የአቶ መለስን በጊዜያዊነትም ሆነ በቋሚነት አለመኖር አቃለው ሃገሪቷ በአመራር ደረጃ የሚያጋጥማት ክፍተት እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ከአንድ የበታች አመራር ካድሬ የተሰጠ ሐሳብ ቢሆን ኖሮ ‹‹የፓርቲውን እና የመንግስትን አሠራር ያልተረዳ፣ የዋህ፣ ልማታዊ›› ብለን እናልፈው ነበር፡፡ ጉዳዩን የተናገሩት ግን የፓርቲው ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ እነደመሆናቸው መጠን የመለስ አለመኖርን ክፍተት ለመረዳት የመረጃ እጥረት አለባቸው ተብሎ አይታሰብም፡፡ በሌላ በኩል ክፍተቱ ቢኖርም እንኳን፣ አቦይ ስብሓት ክፍተት አለ ብለው እንዲሉ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡
የአቶ መለስ ስልጣን ለረዥም ዓመታት ተለጥጦ መቆየቱም ብዙም የሚያወያይ እና የሚያከራክር አይደለም፡፡ በተለይ በተለይ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የሚታዩትን የመንግስት ዋና ዋና ዕቅዶች (የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን እና የግድብ ግንባታውን ጨምሮ) አርቃቂ እና ባለቤት እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የዚህ “ከአቅም በላይ የተንጠራራ” ዕቅድ አፈጻጸምን ያለሳቸው ማሰብ ትንሸ አስቸጋሪ ይመስላል፡፡ በተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች አሠራር እና አፈጻጸም ላይ ጠንካራ እጃቸው በተደጋጋሚ ይገባል፣ ለውሳኔም ይቃጣሉ ተብለው የሚታሙት አቶ መለስ ከቤሮክራሲው መጥፋታቸው የሚታይ ክፍተት መፍጠሩም የማይቀር ነው፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ትንታኔው፣ለመንግስት ስህተቶች መከላከሉ፣ ለልማትና ጥፋቱ ማብራሪያ ባለፉት አሥር ዓመታት በብቸኝነት ብቅ የሚሉት መለስ አለመኖራቸው፣ “የፋጡማን አለመኖር” ያህል ነው ብሎ በቀላሉ ማለፍ ለማንም የፖለቲካ ንቃት ላለው ኢትዮጵያዊ የሚዋጥ አይመስልም፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕጋዊው የፍትህ ስርዓት የማይፈቱ የሚመስሉ ጉዳዮችን የመጨረሻ እልባት የመስጠት ድረስ ስልጣን ያላቸው አቶ መለስ መሆናቸው እየታወቀ ይህ ለዓመታት የተገነባን “ሁሉ ያገባኛል” ስብዕና አለመኖር የሚፈጥረው ክፍተት የሚካድ አይደለም፡፡
ታዲያ ይህንን ሁሉ ጫና ጠቅልለው የያዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ድንገት ሳይዘጋጁ እና ሳያዘጋጁ ከመድረኩ ድንገት ድርግም ማለታቸው ከወደፊቱ የአገሪቷ መጻኢ ጊዜ ጋር ቢገናኝ ስህተት ነው ማለት አይቻልም፡፡
ሕገ መንግስታዊው መንገድ
አንዳንዶች የኢፌድሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 75/1/ለ ‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖር ጊዜ ተክቶ ይሠራል፤› የሚለውን እየጠቀሱ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ያስባሉ፤ በዚሁ አንቀጽ መሠረት ሕገ መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሉበት ሁኔታ ሁሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተክተው እንደሚሰሩ ያናገራል፡፡ የዚህን አንቀጽ ተፈጻሚነት ደረጃ በግልጽ በሕገ መንግስቱ ባይቀመጥም ጉዳዩን በተመለከተ የተሻለ የሕግ አግባብ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው የአገሪቱ ሕግም ይህ ብቻ ነው፡፡ በተቃራኒው ይህንን የሕገ መንግስቱን አንቀጽ በሚነካ እና ክፍተቱን መጠቀም በሚመስል መልኩ የኅወሓት “የነፍስ አባት” አቦይ ስብሓት ነጋ በጉዳዩ ዙሪያ ስልጣኑን ለፓርላማው የሰጠ እና አዲስ ምርጫን ያገናዘበ የ“ተረጋጉ!” መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አቦይ በዚሁ የአሜሪካ ድምጽ የሬዲዮ ጣቢያ ንግግራቸው የአቶ መለስ መኖር እና አለመኖር የሚያመጣው ችግር እንደሌለ እና ተተኪ መምረጥ የፓርላማው ኃላፊነት መሆኑን ነው አጽንኦት ሰጥተው ነው የተናገሩት፡፡
ጥቂቶች በተጻፈው (የቀረበ) ሕግ መሰረት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የወደፊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ብለው ቢገምቱም ብዙዎች ግን ይህ የገዢው ፓርቲን ብሎም የኅወሓትን ባሕሪ የማያውቁ እና ያልተረዱ የዋሆች ግምት ነው ብለው ይተቹታል፡፡ እንደ ተቺዎቹ አባባል ከሆነ በቀድሞው የኅወሓት ክፍፍል ወቅት ሚናቸው ከደጋፊነት ባልተሻለ ሁኔታ የነበረው አባል ፓርቲዎች አሁን በአጠቃላይ የኅወሓት የበላይነት የሚታይበትን ሁኔታ ተቀይሮ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ለአቶ ኃይለማርያምም ሆነ ለሌላ አባል ፓርቲ አመራር ይሰጣል ማለት ዘበት ነው፡፡በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ተቺዎች ተከታይ ቦታውንም ሆነ ውስጣዊ ትግሉን ወደ መገመት ሲመጣ ነገሩን ከውጭ በማየት ብቻ ተከታዩ የመሪ ምርጫ ምን እንደሚመስል ለመገመት ይቸገራሉ፡፡
የአቦይ ስብሃት መንገድ
በፓርቲው ውስጥ ባላቸው ቦታ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሚዲያ ቅርብ በመሆን የሚታወቁት አባት ስብሃት ነጋ የስልጣን መተካቱን ነገር አስመልክተው የሰጡት ምላሽ የማይሆን፣ የማይባል እና ሌሎች የአጋር አመራሮችን ገሸሽ ያደረገ የሚመስል አካሄድ ይታይበታል፡፡ አቦይ ከየት እንዳመጡት በማይታወቀው ሕግ ተመስርተው አብላጫ ድምጽ ያለውን ፓርቲ አዲስ እጩ የማቅረብ ስልጣን ሰጥተው ሲያበቁ የተለዩ ሐሳቦች አፍልቆ የማያውቀውን ፓርላማ የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር መራጭ ያደርጉታል፡፡ ነገሩ ጠንካራ የሕግ ድጋፍ ያለው ባይመስልም ከእስከዛሬው የኢህአዴግ/ኅወሓት ህጋዊነት ባህሪይ በመነሳት በዚህ መንገድ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊመጣ የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም ብሎ መደምደምን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በእርግጥ የአቦይ ስብሃት መንገድ ተግባራዊ ለመሆን የውስጠ ፓርቲ ትግሉ እና የእርሳቸው የኃይል ሚዛን ወሳኝ ጉዳዮች ይሆናሉ፡፡
የኅወሓት ምናልባትም የኢህአዴግ መንገድ
ይህ መንገድ ለመገመት የሚከብደው ጉዳዩ የውስጠ ፓርቲ ትግል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን እንደ ከዚህ በፊቶቹ ታውቀው የወጡ ልዩነቶች በፓርቲው በቅርብ ጊዜ ባለመታየቱም ጭምር ነው፡፡ ሁሉም ውሳኔ እና አመራር ከላይ ወደ ታች በሆነበት የኢሕአዲግ አሰራር ግለሰቦች ለአመራር ያላቸውን ፍላጎት እና ዝግጁነት የማሳየት ዕድል አልነበራቸውም፡፡ በተሻለ አፈፃፀም የሚታወቁትም ቢሆኑ “ከአቶ መለስ ጋር መሥራትን መባረክ ነው” እያሉ ወደሰብአዊ አምልኮ በተጠጋ አድንቆት ከማደናነቅ ውጪ ራሳቸውን በተመጣጣኝ ቦታ ያለ ሥራ አስፈጻሚ እና ዕጩ ተተኪ አድርገው ያቀረቡበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህ የአመራር ክፍተት ላይ የውስጠ ፓርቲ ቁርሾ እና “ከእኛ በላይ ለአሳር” አስተሳሰብ ተጨምሮበት የሚቀጥለውን ተተኪ መገመቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
ከቅርብ ሰዎች ተገኙ የተባሉት መረጃዎችም የሚያሳዩት ገና ካሁኑ ለሁለት የተከፈሉ እና ለቦታው ራሳቸውን ያጩ ጎራዎች መኖራቸውን ብቻ ነው፡፡ የተባለው መረጃ እውነት ሆኖ የትኛውም ውስጠ ፓርቲ ቡድን ቢያሸንፍ እንኳን አዲሱ እጩ ወደ ስልጣን የሚመጣበትን መንገድ የፓርቲዎቹ ሕግጋቶች የሚመልሱት ጥያቄ አይመስልም፡፡ የፓርቲ መሪዎቹን የቆይታ ጊዜ የማይገድብ የፓርቲ ሕገ ደንብ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ የሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ምን ዓይነት ስልቶች እንደሚመጡ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ጉዳዩ በተለያየ አተያይ የተወሳሰበ ቢመስልም የትኛውንም ነገር ያስከፍል እንጂ የኅወሓትን የፓርቲ የበላይነት አረጋግጦ የሚጠናቀቅ እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ አዲስ መሪ የማምጣት ትግል የውስጠ ፓርቲ መረጋጋት ላይም የራሱን ተጽዕኖ መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ አቶ መለስ ለዓመታት የገነቡትን እምነት እና በየሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ቢሮ መግለጫ ላይ ሳይቀር የሚከሰት ስብእና ማጣት፣ የአባላትን በራስ መተማመን መጉዳቱ የማይቀር ነው፡፡ በተለይ በተለይ እንደኢሕአዲግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላት ባሉበት ፓርቲ ውስጥ የመረጋጋቱ ሁኔታ ጊዜ የሚወስድ ይሆናል፡፡ ይህ የውስጠ ፓርቲ መረጋጋት እና መለስን የሚተካ አዲስ ምሰሶ የማቆም ሥራ ከፓርቲው ውጪ ለሆኑ የፓለቲካ እንቅስቃሴዎች አዲስ ዕድል ይከፍት ይሆናል የሚሉ ግምቶችንም ፈጥሯል፡፡
የተቃዋሚዎች እና የሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መንገድ
በደካማነቱ እና በተስፋ አስቆራጭነቱ የሚታማው የተቃዋሚው ጎራ በዚህ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ የሚኖረው ሚና ብዙም ከፍተኛ ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይ በተለይ በማኅበረሰብ ደረጃ በምርጫ ዋዜማ ላይ የሚገናኙት (ለዚህ ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም) 91 ፓርቲዎች በእንደዚህ ዓይነት የአመራር ክፍተት ወቅት የሚኖራቸው ሚና ላይ ዝግጅት አላደረጉም ብሎ መደምደም ከባድ አይሆንም፡፡ የፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር በቅጡ አለመገናኘት እና አለመተዋወቅ ለስልጣን ሽግግሩ ከሚታሰቡት አካላት መካከል የመጨረሻዎቹ አድርጎዋቸዋል፡፡ የራሳቸውን ህልውና በማቆየት እና ባለማቆየት ላይ የተጠመዱት እነዚህ አካላት የተሻለ የስልጣን ዕድል ያለው አካል የሚመጸውታቸውን የፖለቲካ ምህዳር ከመጠበቅ ውጪ አማራጭ ያላቸው አይመስሉም፡፡
ይህ የአመራር ክፍተት አሉ እየተባሉ የሚጠሩትን አገር ውስጥ ከሚገኙት ፓርቲዎች ውጪ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችም ቢሆን፣ አሁን ባላቸው በግልፅ የማይታይ እና የማይነገር የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ተመርኩዞ ወደ ላይ ብቅ ይላሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ (ክፍተቱ ለተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተወሰነ ዕድል መስጠቱ የማይቀር ቢሆንም!)
ድኅረ መለስ
አገሪትዋ አሁን ካለችበት የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ተያያዥ አጣብቂኝ ሁኔታዎች ላይ የአቶ መለስ መጥፋት ተጨምሮበት ጉዳዩን ከድጡ ወደማጡ እንዳያሸጋገግረው የሰጉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በቀጣዩ አመራር ወቅት አሁን ትታይ የነበረችውንም የፓለቲካ ምህዳር ጠራርጎ ማጥፋት አዝማሚያ አሁኑኑ እየታየ ነው የሚሉ ክርክሮችም እየበረከቱ ነው፡፡ ቁርጡ ሳይታወቅ ገና፣ ከሰሞኑን በፍትህ ጋዜጣ ላይ የተወሰደው ግራ የሚያጋባ “ሕጋዊ” እርምጃ የድኅረ መለስ ውጤት ተደርጎ መወሰድ ጀምሯል፡፡ በቅርቡ የተወሰደውንም የሙስሊሞችን ጥያቄ በኃይል የመፍታት አዝማሚያ የዚሁ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡
ጠቅልሎ ስልጣንን የማስተዳደር ክህሎት የማጣት ችግር የሚመስለው ይህ እርምጃ ለካ ጠቅላይነት ስልጣን ብቻ ሳይሆን ክህሎትም (የአምባገነንት ክህሎት እንበለው እንዴ?) የሚጠይቅ ነው የሚያስብል ሆኗል፡፡ አዲሱ አመራር ቢያንስ ሁሉን አቀፍ ስልጣን መያዙን እስኪያገጋግጥ እና እስኪለማመድ ድረስ እንኳን ቢሆን ተመሳሳይ እርምጃዎች የማይበረክቱበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
በአቶ መለስ፣ በቋሚነት ያለመኖር ዋና ተግዳሮቱ ወይም ዕድሉ የሚሆነው መጀመሪያ ለፓርቲው ለራሱ ለኢሕአዴግ ነው፡፡ ፓርቲው የአቶ መለስን አለመኖር እንደ ዕድል በመጠቀም ቢያንስ የሚታማበትን የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት እና አመራር ወደ ቡድን አመራር እና እውነተኛ መተካካት ሊቀይረው የሚችልበት እድል አለ፡፡ ይህንን ዕድል በሚገባ ከተጠቀመ ኢሕአዲግ ቀስ በቀስ የቡድን ሐሳቦችን ወደማንሸራሸር እና የሐሳብ ልዩነቶችን ወደሚያስተናግድ ፓርቲነት ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በፓርቲው ውስጥ ታፍነው የቆዩ ሐሳቦችን ለንግግር እና ለትግበራ የማምጣት ዕድል ይኖረዋል፡፡
በተቃራኒው ከፓርቲው የቀድሞ ልምዶች በመነሳት የዴሞክራሲ ባህሉ ዝቅተኛ በመሆኑ ጭራሽ ወደባሰ የውስጠ ፓርቲ ችግር ባይገባም እንኳን ባለበት ሁኔታ የመጨረሻ ውጤቱ የጠቅላዩን መቀየር ብቻ ይሆናል የሚሉ ግምቶች አሉ፡፡ ምናልባት የመለስ ግለሰባዊ ግዙፍነት ከዚህ በባሰ ሁኔታ ተጽዕኖ አሳርፎ ከነበረ ደግሞ ፓርቲውን የተለየ ሐሳብ እያራመዱ፣ በአቶ መለስ ምሰሶነት ጥላ ስር ብቻ የነበሩ አካላት ከአቶ መለስ አለመኖር ጋር ተያይዞ ራሳቸውን በማግለል የአዲስ ቡድኖች የመፈጠር ዕድልም ሊኖር ይችላል የሚሉ መላምቶች በስሱ ይሰማሉ፡፡ (ምንም እንኳን የዚሀ ሁኔታ መፈጠር ዕድል ጠባብ ቢመስልም፡፡) ኢሕአዲግ የአቶ መለስ ስብዕና ብቻ ከፓርቲው ጋር ያጠጋጋቸው መለስን አትንኩብን ፓርቲውን ግን እንደፈለጋችሁ ብለው መለስ ላይ እምነት ያሳደሩ ከፓርቲ ፓለቲካ ውጪ ያሉ አካላትን ይዞ የመቀጠሉ ጉዳይም ሌላው የድኅረ መለስ ጊዜ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙዎቹ እንደሚገምቱት ጉዳዩ በውስጠ ፓርቲ ትግል ጠቅላይን ለጠቅላይ በመተካት ብቻ የኢሕአዲግን ግዙፍነት በመጠበቅ ከተጠናቀቀ የወደፊትዋ ኢትዮጵያ አዝማሚያ ለመሻሻል እድል የሌለው ሊመስል ይችላል፡፡
No comments:
Post a Comment