Wednesday, July 25, 2012

ባርነት በዘመን ሲዋጅ?


ፍቃዱ አንዳርጌ
በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ኋላ ቀሩ የአፍሪካ የባርነት ስርዓት በሁለት አፍሪካዊ ባልሆኑ ነገዶች እንደተጀመረ በጉዳዩ ዙሪያ የተፃፉ ፅሁፎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ሁለት የአረብ ሙስሊም እና የአውሮፓ ባሪያ አቅኝዎች በአፍሪካ ዙሪያ አሰፍስፈው በአፍሪካውያን ሰብዓዊነት ላይ ትልቅ ኪሳራ ሲያሳድሩ ከቆዩ በኋላም የአረብ ሙስሊም የባሪያ አቅኝዎች ከመመካከለኛው፣ከምዕራብና ከምስራቅ አፍሪካ የቃረሟቸውን ሰብዓዊ ፍጡሮች እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ሰሜን አሜሪካና ኤዥያ በመላክ የሰው ላብ የገቢ ምንጫቸውን በማሳደግ ሃያልነታቸውን ለማስጠበቅ ሲታትሩ ቆይተዋል፡፡ አውሮፓውያኑም ቢሆኑ ከ15ኛው እሰከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ከምዕራብ፣መካከለኛውና ምስራቅ አፍሪካ በርካሽ የገዟቸውን አፍሪካዊ በትርፍ ወደ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣መካከለኛውና ደቡብ አሜሪካ በመሸጥ የሰብዓዊነትን ልዕልና ተጋፍተዋል፡፡እነዚህ በባርነት ስም ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገሮች የሚጋዙት ምስኪኖች ትንሽ ከሚባል ስራ ጀምሮ እስከ ከባድ የጉልበት ስራ፣ ለጦርነት ፍጆታ ሲያገለግሉ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡

“የምክንያት ዘመን” እየተባለ የሚጠራው ሰብዓዊነትንና ምክንያትን ያማከለው ዘመን እያቆጠቆጠ በመጣበትና ከጨለማ ወደ ብርሃን ጉዞ በሚደረግበት ዘመን (age of enlightenment) እንዲሁም የኢኮኖሚው ስርዓት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪው መሸጋገር ተከትሎ በምእራብ አውሮፓ የባሪያ ንግድ አብሮ እያከተመ ታሪክ ወደ መሆን ተቃረበ፡፡ በዚህን ጊዜ የምዕራቡ ዓለም የባሪያ ስርዓት ገበያው እንደ ጦፈ ነበር፡፡ የማታ ማታ ግን ብሪቴን በ1833 በሁሉም ግዛቶቿ የባርያ ስርዓትን ቀሪ ስታደርግ፣ ፈረሳይ በ1848 ቅኝ ለመግዛት በሰለጠነችባው ሃገሮች የስርዓቱን ቀሪነት በህግ ደንግጋለች፤ የተባበሩት አሜረካም ብትሆን በ13ኛው የህገ መንግስት ማሻሻያ አውግዛ ሰብዓዊነት እንዲልቅ አድርጋለች፡፡ ይህንን ተከትሎም በ1888 የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ላይመለስ ጦሱን ይዞ ቀርቷል፡፡ ቢሆንም ግን ይህ ባርነት ህገ ወጥ በሆነ መልኩ እሰከ 1930 ድረስ ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ሰብዓዊነትን ሲጋፋ እንደቆዬ እሙን ነው፡፡

ይህ የባርነት ዘመን በአፍሪካውያን ላይ ታላቅ የሆነ የስነ ልቦና ኪሳራ ያሳደረ ከማሰብ መብት ጀምሮ እስከ መዘዋወር መብትን የነፈገ፣ የማንነት ቀውስጥ ውስጥ የጣለ፣ የበታችነት ስሜት እንዲዳብር ያደረገ፣ በተፈጥሮ የተሰጠውን ሰብዓዊ መብት የነፈገ “ዘመነ ንፉግ” ሆኖ አልፏል፡፡

የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ!
“ራሳችንን ለማስተዳደር ዕድሉ ቢሰጠን በፍጥነት ምድራዊ ገነት እንደምንፈጥር አስመስለን አወራን፤ በተቃራኒው ያሰፈነው ግን የፍትህ መጓደልና ብሎም ፈላጭ ቆራጭነት ነው”
(ፕሬዘዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ(ታንዛኒያ))

አሁንም አፍሪካውያን የታደልን አይመስልም እንደሚታወቀው በዘመነ ባርነት የነበሩ አፍሪካውያኖች ጉልበታቸውን ገብረዋል፣ማንነታቸውን አጥተው ከባህላቸው፣ ከቋንቋቸው፣ከሃይማኖታቸው ጋር ተፋተው ማቀዋል፡፡ በዘመኑም የነበሩ ባሪያ አሳዳሪዎች የሚፈልጉት ገና ያልተነካውን ትኩስ ጉልበታቸውን ለኢኮኖሚያዊ እድገት ማካበቻ እና ለሃያልነት ማስጠበቂያ ጦርነት ፍጆታ አውለውታል፡፡ ዘመነኞች የሆኑ ገዥዎቻችንም ያገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ ያሉ ይመስል በሃገሬው ላይ ክንዳቸውን አበረትተው በባርነት በትር መውቃታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የማይወቀሱ፣ የማይገሰሱ የሃገሪቱ አርማና ፈላስፋ አድርገው ራሳቸውን የነፃነት ተምሳሌት አድርገው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በህዝባቸው ላይ ግፍ ይፈፅሙና ትዕዛዛቸውና ማስፈራሪያቸው ሲደርሰው በየአደባባዩና ስታዲዬሙ ነቅሎ በመውጣት “ሙሁሩ፣ፈላስፋው ፣ደፋሪው መሪያችን አንተ ለዘላለም ኑርልን አንተን እና መንበርህን የደፈረ ለዘላለም የአሸባሪነት ካባ ከላዩ ላይ አይውለቅ” የመሳሰሉ መፈክሮችና መዝሙሮች ያስፈክራሉ፣ ያዘምራሉ፣ያስደግማሉ፡፡

ዛሬም በእኛ ዘመን በጥቁር ምድር “ባርነት” በዘመን ተዋጅቶ ከዘመኑ ጋር እንዲሄድ በማር የተለወሰ መርዝ ሆኖ ቀርቧል፡፡ የባርነት ስርዓት ማንነትን፣ ትውልድን እንደሚገድል ሁሉ ዛሬ ማንነት እየሞተ ብኩርና በምስር ወጥ እንዲሸጥ አድርጓል፡፡ ይህ ሁኔታም በእኛ ቅኝ ባልተገዛነው ኢትዮጲያውያን ላይ ቀረልን አይስልም፡፡ በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ የተዘረጋው “ዘመናዊ ባሪያ አሳደሪ” ስርዓት በውዴታ ግዴታ ሰንሰለት አንገታችን ተጠፍሮ ወደ ጎን እንዳንመለከትና ከባርነት ሰልፉ እንዳናመልጥ ተደርጓል፡፡ የድሮ አሳዳሪዎች የባሪያውን ጉልበት ለኢኮኖሚና ፖለቲካ ሃያልነታቸው ማስጠበቂያ እንደተጠቀሙበት ሁሉ ዛሬም በሃበሻ ምድር በዘመኑ ዋጅተውት ትውልድን በማድከም ድክመቱን ተጠቅመው የራሳቸውን የፖለቲካ ሃያልነታቸውን እሩቅ ከፍ አድርግው ሰቅለውታል፡፡ ሰንሰለቱን እረዘም አድርገው ዘርግተው ወደ ውዴታ ግዴታ መስመር በማስገባት አንድ ሰው ስራ ለማግኘትም ሆነ ማህበራዊ አገልግሎት ሆነ ሌላ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን አንድ በውዴታ የሚፈፀም ግዴታ ይቀመጥለታል፡፡ የተሰጠውን ኢ-ምክንያታዊ ግዴታ ሲፈጽም የጠየቀው ይሰጠዋልም ይደረግለታልም፡፡ ወጥነት ያለው ሃሳብ እንዲኖርህ ብቻ የስርዓቱን ሰልፍ ልትከተል ግድ ይላል፤ ከሰልፉ ካፈነገጥክ አሁንም በዜግነትህ ብቻ ማግኘት ያለብህን ነገር ልታጣ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ በውዴታ ግዴታ ሰልፉ ውስጥ ገብተህ ትሰለፋለህ፡፡ ሰልፉ ውስጥ ከገባህ በኋላ ግዴታ እንጅ መብት የለህም፣ አወ ማለት እንጅ ለምን ማለት የለም፣ መጎንበስ እንጅ መቃናት አይቻልም፣ እያዩ ማለፍ እንጅ ማስተካከል የለም፣ ሲርብህ መራብ እንጅ ማዛጋት አይቻልም፣ መቀበል እንጅ መጠየቅ አይኖርም፡፡ የባርነትን ጥልቅ ትርጉም በተረዳነው ይህ ራሱ ጉልበትን ያላካተተ ከባርነት አገዛዝ የማይተናነስ መሆኑን ለማወቅ ነጋሪ አያስልገውም፡፡

አንድ ሰው በሃገሩ እየኖረ በታሪኩ ካልኮራ፣ታሪኩን ጮክ ብሎ ሲያወራ ድምፅ ቀንስ እንዲያውስ ማን አባክ አውራ አለህ፣ ሲርበው እራበኝ ብሎ መጠየቁ አሸባሪ የሚያሰኘው ከሆነ፣ ሃሳቡን በነፃነት ሲገልፅ ለምን ተብሎ ወህኒ የሚጋዝ ከሆነ፣ ተበደልኩ ሲል ፀረ ዲሞክራሲ፣ ለምን ሲል ፀረ ልማት የሚባል ከሆነ፣መሪዎቹን በሚደግፍ ሰልፍ ሳይወጣ ሲቀር የሚወገዝ ከሆነ፣ በዲግሪ ማስትሬት ተመርቆ ስራ ብሎ ሲጠይቅ ከግልምጫ ጋር ስራ አትፈጥርም ተብሎ የሚሳለቅበት ከሆነ፣ እድገት የለም ሲል ፀረ- ልማት ፣ የሃይማኖት መብቴ ሲል አክራሪ እየተባለ በሃገሩ እንደሌላ ዜጋ ተቆጥሮ ምን አገባህ እኔ አውቅልሃለው ከተባለ……. እስኪ ተጠየቁ ከዚህ በላይ ባርነት ከወዴት አለ?

በባርነት መኖር ወይስ ወደ ነፃነት እየሄዱ መመሞት?
እስካሁን ከተለያዩ ሰዎች ጋር በግል ካደረኳቸው ውይይቶች ሆነ ሰዎች ሲወያዩ ከታዘብኳቸው አብዛኛዎቹ በዘመናዊ መልኩ የባሪያ አሳዳሪ ስርዓት ሃገሪቱ ውስጥ ሰፍኖ እንዳለና መልኩን ቀይሮ እንደመጣ የሚስማሙ ናቸው፡፡

ባርነቱ ላይ የተስሙት ብዙዎች ተመችቷቸው እንደሆነ፣ አሁን በሃገሪቱ ተዘርግቶ ስላለው ስርአት ሲጠየቁ ግን ሲጠየቁ እረ “የደላው ሙቅ ያኝካል” አሉ የሚል መልስ ሲሰጡ ይሰማል፡፡ታዲያ ስርዓቱ ላይ ቅሬተ ያለው ሰው ካለ ለምን ጥያቄስ አያቀርብም ያልን እንደሆነ አብዛኛው የሚሰጠው መልስ “እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን አይነት ነው፡፡

ይህ የነጻነትን ጣእም በቅጡ ያለመረዳት ችግር የሚቀረፍበትን መንገድ በቀላሉ አግኝተን የምንለውጠውም አይመስልም፡፡የነጻነትን ጣእም ያለመረዳት ችግር ባይሆንም ኖሮ ለዘመናት የባርነትን እና ገዢዎችን እያፈራረቅን አንኖርም ነበር፡፡ ይህ አዙሪት መቼ ይሆን የሚያበቃው?



-----
ፍቃዱ አንዳርጌ ይህንን ጽሁፍ የላኩልን በzone9ners@gmail.com ሲሆን፣ ለዞን ዘጠኝ አንባቢዎች እንዲስማማ መጠነኛ አርትኦት አድርገንበታል፡፡ ጸሐፊውን የሚገኙበት የኢሜይል አድራሻ፡- fekidyiab@gmail.com

No comments:

Post a Comment