Tuesday, July 31, 2012

ፎንቱ ፎኒፍ ሪፈታ ጄናን ኢቲሌን ጂቢቻ ቲ ካቴ ("ስጋ ለስጋ ይደነግጣል ቢባል ጥጃ እንኳ በቁርበት ደነገጠች")


“አገሬ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ነች። እንደ ኢትዮጵያዊ እንከራከራለን። ኢትዮጵያ መኖር አለባት። ሁላችንም የኢትዮጵያ አባል መኾን አለብን ብዬ ነው የማስበው።”

“የኢትዮጵያ አንድነት እና ነፃነት፣ እኩልነት ከተጠበቀ፣ በተፈጥሮ ሃብት የተደላደለች፣ በታሪኳ የገነነች፣ ኢትዮጵያ ሳትከፋፈል እና ሳትቆራረስ ለዘላለም እንድትኖር፣ የጎሳ ልዩነት ሳይደረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ግዴታው እና መብቱም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡”

 “I am so humbled and am forever grateful to our ancestors; no matter what mistakes they committed, they resisted all the colonizing powers in a way that made them create a history and logo that branded Ethiopia as the very idea of the decolonizing imagination.”

የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች [ኢ-መደበኛ] ቡድን አባል መሆኔ በዚህ ዓመት ከተከሰቱልኝ ምርጥ እውነታዎች ውስጥ በጣም ጠቃሚው ነው፡፡ ቡድናችን ‹‹የንባብ ፕሮግራም›› የተሰኘ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ፣ አንድ ጽሑፍ ላይ ተመስርቶ በተወሰነ የጊዜ ዝላይ (Time Interval) መወያየት ጀምሯል፡፡

ይህ ጽሑፍ የዚህ ‹‹የንባብ ፕሮግራም›› ትሩፋት ነው፡፡ በእንዳልክ መራጭነት ‹‹Oromo Narratives›› የዶ/ር ዶናልድ ሌቪን ጥናት ላይ ለመወያየት ተጠራርተን ተገናኘን፡፡ ርዕሰ ጉዳዩ የኦሮሞ ብሔረሰብ የፖለቲካ ጥያቄዎችና አማራጭ መልሶች ላይ በጥቅሉ የሚያጠነጥን ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ የጠለቀ እውቀት ለሌለው ለእንደኔ ዓይነቱ ልብን በብርሃን የሚያጥለቀልቅ (enlights) የንባብና የውይይት ፕሮግራም ነበር፡፡ ይህንን ሳያካፍሉ መቅረት ስስት ነውና፣ ባይሆን እየቆነጠርኩ ላካፍላችሁ፡፡

የብሔረሰቦች ጥያቄ ቢያዳፍኑት የማይጠፋ፣ ቢያቀጣጥሉት የሚፋጅ፣ አይነኬ ጉዳይ ይመስለኝ ነበር፡፡ እርግጥ አላዋቂ አራጋቢ ሲያራግበው - ሰደድ እሳትም ቢሆን ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን የማይነካ ጉዳይ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ ነው፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ ጥያቄዎች ከማንነት እና እሴት እስከ ኤኮኖሚ፣ እስከ አስተዳደራዊ እና አመራር ሚናዎች ድረስ ሁሉንም ያካልላሉ፡፡ እኛም ጨረፍ፣ ጨረፍ እያደረግን እንመለከታቸዋለን፡፡ መጀመሪያ ወደመጀመሪያው!

ከታሪክ በማንኪያ
የገዳ ስርዓት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዘመናዊነት ተቃኝቶ ሊተገበር የሚችል ብቸኛው አገርበቀል ትውፊታዊ የፖለቲካ ስርዓት ነው፡፡ ስርዓቱ ለአምባገነናዊነት በማይመች መልኩ የገዢዎችን መደብ የስልጣን እና ዘመነ ስልጣን የሚገድብበት ደንብ ያለው፣ የወላጆችና ልጆች ትውልድ ክፍተትን የሚያስታርቅበት እና ትውልዶች በየዕድሜያቸው እርከን የአስተዳደር/አመራር ልምድ የሚያዳብሩበት አካሄድ ያለው፣ ከአምልኮጋ ግንኙነት የሌለውና (it indeed has a religious element, the good thing is that the Geddaa system explicitly differentiates the two and the leadership of ritual and the political spheres) ሲያጠፉ የሚከሰሱበት እኩልነትን ማስፍን የሚችል የሕዝባዊ አስተዳደር ስርዓት ነው፡፡ የገዳ ስርዓት በዘር የሚሾሙ (የዕድሜ ልክ ) እና በምርጫ የሚሾሙ (ቢበዛ የ8 ዓመት) መሪዎች ይኖሩታል፡፡ በቀላሉ ሊሻሻሉ ከሚችሉት ድክመቶቹ (ለምሳሌ፤ ሴቶችን አሳታፊ አለመሆኑና ከዘውዳዊነትጋ የሚመሳሰልበት አካሄድ መኖሩ) በስተቀር ራሱን የቻለ ወጥ የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ስርዓት ፍልስፍና ነው፡፡ ለዝርዝሩ ይህንን (አውርዳችሁ) ወይም ይህንን (ባለበት) እንድታነቡት እየጋበዝኩ የኦሮሞን ብሔረሰብ ወደመላው ኢትዮጵያ አካባቢዎች የመሰራጨት ታሪክ በአንድ አንቀጽ እወጣዋለሁ፡፡

ከ16ኛው ክፍለዘመን ወዲህ የኦሮሞ ሕዝቦች ወደሰሜን፣ ምስራቅ እና ምዕራብ በመሰራጨት እንደአሁኑ በመላው የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ለመገኘት በቅተዋል፡፡ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት ባላቸው በቀላሉ የመዋሃድ እና የመወዳጀት ችሎታ ምክንያት በመላው ኢትዮጵያ በሚስፋፉበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ክርስትናን፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ እስልምናን ተቀብለዋል፤ በደቡብ ምዕራብ መንግስት ሲያቋቁሙ፣ በሸዋ ደግሞ አርሶአደር ማኅበረሰብ መስርተዋል፡፡

እዮኣስ (የንጉሥ የበካፋ የልጅ ልጅ) ግማሽ የኦሮሞ ብሔረሰብ አባል የሆነ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው፡፡ ሦስት ሺህ የኦሮሞ ተወላጅ ወታደሮችም ነበሩት፡፡ ከዚያ በኋላም በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪኮች ውስጥ የኦሮሞ ደም ያላቸው የጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ዳግማዊ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና እቴጌ መነንን ጨምሮ በርካታ የንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት ነበሩ፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ ጥያቄዎች
የኦሮሞ ሕዝብ ከሁሉም ብሔረሰቦች ቁጥር በላይ ቢበዛም ‹‹የሁለተኛ ደረጃ ዜጋ›› ሁኗል ብለው የሚከራከሩት ብዙሐን ናቸው፡፡ በአመራር ደርሻ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው አማሮች እና ትግሬዎች (‹‹አቢሲኒያዎች››) ‹‹የመጀመሪያውን ደረጃ›› ይወስዳሉ ነው ምሬቱ፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት ቡና እና አሁን ገቢው እያደገ የመጣው የወርቅ ማዕድንም የኦሮሚያ ምድር ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ኦሮሚያ በኢኮኖሚ የሚገባትን ያህል አልተጠቀመችም የሚል ሌላው የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ዐብይ ጥያቄ ነው፡፡

መፍትሔዎቹስ?
ብዙሐኑ ነጭ በሆነበት አሜሪካ ጥቁር ፕሬዚደንት ሲመረጥ ‹‹ለውጥ መጣ›› ልንል እንችላለን፤ ሌላውን ስርዓቱ ይሰራዋልና፡፡ የኦሮሞ ብሐየረሰብ ተወላጅ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ቢመረጥ ግን እንዲህ በቀላሉ የኦሮሞ ተወላጆች (ወይም በጥቅሉ የብሔረሰቡ) ጥያቄ መልስ አገኘ ብለን መደምደም አንችልም፡፡

ዶ/ር ሌቪን በጠቀስነው ጥናታቸው ውስጥ ሦስት ትርክታዊ አማራጭ መፍትሔዎችን ጠቁመው ነው ጥናታቸውን የሚደመድሙት፡፡

1ኛ. ትውፊታዊው ትርክት
‹‹… sustaining and strengthening whatever can be preserved of the traditional institutions of the Oromo Gadaa system. Toward that end they should maintain a certain distance from the political center of the Ethiopian nation. …›› (…በትውፊታዊው የገዳ ስርዓት ውስጥ አጠናክሮ ማቆየት የሚቻለውን ማስቀጠል፤ በዚያውም ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ማዕከል ጋር ያለውን ርቀት ባለበት ማስጓዝ፡፡…)

2ኛ. የቅኝ ተገዢነት ትርክት
‹‹… a “national liberation struggle [that] will continue between Oromia and Ethiopia until the Oromo nation freely decides its political future by uprooting Ethiopian settler colonialism …›› (…የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ሰፋሪ ቅኝ ገዢዎችን ነቅለው በማስወገድ ስለራሳቸው ዕጣ ፈንታ መወሰን እንዲችሉ/እስኪችሉ ድረስ/ የብሔራዊ ነፃነት ትግል ማድረግ …)


3ኛ. የኢትዮጵያዊነት ትርክት
‹‹… struggling to institutionalize pluralistic democracy and multicultural diversity, Oromo rhetoric and self-understanding should be revised to include appreciation of the many Oromo contributions to building the modern Ethiopian nation, and Oromo customs could be deliberately invoked and adopted to civilize the conduct of members of the national parliament and other deliberative bodies …›› (ብዝሐ ዴሞክራሲያዊነት እና ብዝሐ ባሕላዊነት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን መታገል፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ያለውን እና የነበረውን ሚና ዋጋ ማሰጠት፣ እና የኢትዮጵያ ፓርላማ የኦሮሞን ትውፊታዊ ስርዓትና ወግ ዘመናዊነት በማላበስ ለተግባራዊነት ማብቃት፡፡…)

በግሌ ሦስተኛው የመፍትሔ አማራጭ ውስጥ ራዕይ ይታየኛል፡፡ በመግቢያዬ ላይ ያስቀመጥኳቸው የተቀነጨቡ አባባሎችም የሚያጠናክሩት ‹የኢትዮጵያዊነት ትርክት› መፍትሔዎችን ነው፡፡ ትውፊታዊው የገዳ ስርዓት እጅግ የሚያስደንቁ፣ መቻቻልን የሚያበረታቱ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያሰፍኑ፣ እና ሌሎችም በርካታ ጠንካራ ጎኖች አሉት፡፡ በዶናልድ ጽሑፍ ላይ ተወያይተን ስናበቃ እንዲህ አለምኩ፤

‹‹የኦሮሞ ክልላዊ መንግስት የገዳን ስርዓት ዘመነኝነት አላብሶ በክልላዊ አስተዳደሩ ሲተገብረው፣ የፌዴራል መንግስቱ በስኬቱ ቀንቶ (ከስኬቱ ተምሮ) ስርዓቱን ለብሔራዊ ስርዓትነት ሲያውለው - ለገዛ አገራችን ችግር አገራዊ መፍትሄ… ምኑ ቅጡ!››

ሕልሜ እውን እስኪሆን ድረስ ማለሜን አላቆምም!!!

No comments:

Post a Comment