ኢትዮጵያ ድፍን የ25 ብር ኖት የላትም፤ ሆኖም ሊዘጋጅላት ነው ብለን እናስብ:: በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው መሪዎች ምስላቸው በዚህ የብር ኖት ላይ ታትሞ እንዲወጣ ቢፈለግ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያስማሙ መሪዎች አሉን? አቶ መለስስ ለዚህ ማዕረግ በስንቱ ኢትዮጵያዊ ይታጩ ይሆን? ብለን ብንጠይቅ:: መልሱ አዳጋች ነው:: እንደበለፀጉት ሀገሮች ነጻ የሆነ የሕዝብ አስተያየት የሚሰበስብ የሚዲያም ሆነ የህዝብ ግንኙነት ድርጅት በሌለበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር አቶ መለስን አብዛኛው ሕዝብ ‹ይወዳቸዋል› ወይም ‹ይጠላቸዋል› ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይከብዳል:: እንደ አፄ ምንሊክ ወይም እንደ አፄ ኃይለስላሴ የኢትዮጵያዊያንን አስተያየት በተለያየ መስመር እንደማይበታትኑ መናገር ግን አይከብድም:: ከሕዝብ ዕይታ ከተሰወሩ ወዲህ እንኳን፣ ስለጠቅላይ ሚንስትሩ በየማህበራዊ ድረገጾች እና በየጦማሮቹ የሚጻፉት ጽሁፎች የተቃውሞ እና የድጋፍ በማለት ለሁለት መክፈል ይቻላል:: ለመሆኑ አቶ መለስ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን እንዴት ይታያሉ?
ባልደራባዬ አቤል ጠቅላያችን የማን ናቸው? ብሎ በጠየቀበት ጦማሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን እርሳቸውን የኔ ብለው ለመቀበል ይቸገራሉ፤ በግድ አስገድደው ያንተ ነኝ ካላሉት በቀር ሁሉም እርሳቸውን መሪዬ ናቸው ብሎ ለመቀበል አይፈልግም›› ይለናል:: ነገር ግን ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የኢሕአዲግ የፊት ገጽ ሆነው የቆዩት አቶ መለስን ኢትዮጵያውያን እንዴት ያዩዋቸዋል የሚለውን ለመረዳት የኢሕአዲግን የአስተዳደር ስረዓት በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል::
ኢሕአዲግ በቁመናው ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ቢመስልም ሊቀመንበሩ አቶ መለስ ዜናዊ በጠና ታመዋል የሚል ወሬ ሲናፈስ በፓርቲው አባላት መንደር የሚስተዋለው አለመረጋጋት ብሎም የሚወራው የስልጣን ሽኩቻ የኢሕአዴግን ሀገር አቀፍነት ሳይሆን በአቶ መለስ ዜናዊ ሙሉ ቁጥጥር ስር የወደቀ ፓርቲ መሆኑን የተለያዩ ተንታኞች ይናገራሉ:: አቶ መለስ እና ደጋፊዎቻቸው ኢትዮጵያን በአዲስ መንገድ ለመስራት መንገድ ጀምረናል ብለው ቢናገሩም ከተቀናቃኞቻቸው እና ተቃዋሚዎቻቸው ግን ቀድሞ ከነበሩት የኢትዮጵያውያን የአገዛዝ ስርዓቶች ምንም የተለያ ነገር እንዳላመጡ ይባሱንም ሀገሪቱ የነበራትን መልካም እሴቶች እንዲሸረሸሩ ምክንያት ሆነዋል ብለው ይወቅሷቸዋል::
በቅርቡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የአቶ መለስን የሃያ አንድ አመት አስተዳደር ስርዓት በማስመልከት በሰማያዊ ፓርቲ ጋባዥነት ባደረጉትን ንግግር ላይ የአቶ መለስን ስርዓት ከበፊት ስርዓቶች ጋር በማነፃፀር ተናግረዋል:: እንደ ዶክተር ዳኛቸው አገላለፅ የዐፄ ኃይለሥላሴ የፈረስ ስም “ጠቅል” ነበር። ስርዓታቸውና የፈረሳቸው ስም የተዋሃደ ነበር። ፈረሱን ተምሳሌታዊ ያደርጋሉ “ጠቅል” ሲሉ ፍፁማዊ ስርዓት (Absolute State) እየፈጠሩ ነበር። የሰሜኑን ባላባቶች ተራ በተራ በፖለቲካ ካሸነፉ በኋላ “ጠቅል” ነው የሆኑት። እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ “አገር በእጄ” ነው ያሉት። ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቢያንስ ግልፅ ነበሩ። የአቶ መለስ ስርዓት ግን ለየት ያለ “የጠቅልነት”(“Absolutism”) ባህሪ የሚስተዋልበት መሆኑን አስረድተዋል:: ይህ የአቶ መለስ ስርዓት ለየት ያለ “የጠቅልነት”(“Absolutism”) ባህሪ ያለው ሲሆን ምንም ዐይነት ተቀናቃኝ ኃይል የማያስተናግድ እና የተደራጀውንም ሆነ ያልተደራጀውን የማይታገስ ፍፁማዊ ነው። በተጨማሪም የአቶ መለስን የኢሕአዲግ አገዛዝ የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት (Centralized Democracy) የሚተገብር ነው ብለው ገልፀውታል::
የመለስ ፊት ደጋግ ስጦታዎቸ ለኢትዮጵያ
አቶ መለስ ዜናዊ በሰብዓዊ መብት አያያዝ እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሰላ ሂስ ቢሰነዘርባቸውም በደጋፊዎቻውም ሆነ በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ የሚመሰገኑበት ደጋግ ተግባራት አሏቸው:: ከነዚህ በቀዳሚነት የሚነሳው ፍትሐዊ አይደለም ቢባልም የኢኮኖሚ እድገቱ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞዎቹ የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ እና በሴኔጋሉ መሪ አብዱላሂ ዋዴ የአፍሪካ ሕብረትን መቀመጫ ከአዲስ አበባ ወደ ሀገራቸው ለመውሰድ የተለያዩ ማባበያዎችን በመጠቀም ቢሞክሩም በአቶ መለስ አንደበተ ርቱዕነት ተሸንፈው የኅብረቱ መቀመጫ ከታሪካዊ ቦታው ሳይነሳ ቀርቷል:: ነገር ግን ዘግይተዋል አልያም ለፖለቲካ ፍጆታ አውለውታል ተብለው ቢታሙም የታላቁ የአባይ ግድብ ስራ ጅማሮም ሌላው አቶ መለስ ሊታወሱበት የሚችሉበት ደግ ተግባራቸው እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል:: አቶ መለስ በተለያዩ ዓለምአቀፍ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን አልፎም የአፍሪካን ጉዳዮች በማስረዳት የአፍሪካ መሪ የሚል ስያሜ እንዳተረፉ ከተለያዩ ጽሁፎች መረዳት ይቻላል::
መለስ ለኢትዮጵያ ንፍገት እና ክፋት
‹‹አንድ ሺኅ አራት መቶ ማይልስ የሚያህል የውኃ ጠረፍ ካስረከብን በኋላ አራት መቶ ኩንታል ድንች ለማያመርት ቦታ ከ50 እስከ 60 ሺሕ ወጣት በጦርነት ገብረናል›› ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ የኤርትራ መገንጠልን ተከትሎ ሀገሪቱ ወደብ አልባ መሆኗን እና ሁለት ዓመት የቆየውን የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ክስረት በአንድ ላይ ለማውሳት:: ይህ እንግዲህ የአቶ መለስን ንፍገት እና ክፋት ለማውሳት ተችዎቻቸው በቀዳሚነት የሚያነሱት ተግባራቸው ነው:: በስምም ቢሆን ሕገ መንግስታዊ ስርዓት አቋቁመው በሕገ መንግስቱ ላይ የተዘረዘሩትን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሸራርፈዋል፤ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ መብቶችን የሚደፈጥጡ አዋጆችን አውጥተው የዜጎችን መብት ገፈዋል የሚሉ ሂሶችም ከአቶ መለስ ተቃዋሚዎች ተዘውትረው የሚደመጡ ትችቶቻቸው ናቸው::
No comments:
Post a Comment