በዘላላም ክብረት
ሁለቱም ሃገራት በይፋ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመሩ መቶ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሁለቱም በተመሳሳይ ወቅት ከኮሚኒስታዊ አስተዳደርና ስርዓት መፋታታቸውን ባወጁ ማግስት ዴሞክራሲን ተግባራዊ የማድረግ ፈተና አጋጥሟቸዋል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በተመሳሳይ ወቅት ባፀደቁት ሕገ መንግስታቸው የምርጫ ዴሞክራሲን (electoral democracy) አውጀዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ሃገራት ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስታቸውን ካፀደቁ ወዲህ ተቃዋሚዎቻቸው ስልጣን ሊይዙ አልቻሉም፤ የመያዝ እድላቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መጥቷል፡፡ ሁለቱም ሃገራት በአሁኑ ወቅት የአንድ ፓርቲ የበላይነት በእጅጉ የጎላባቸው ሃገራት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከምዕራቡ ዓለም ጋር (በተለይም በአለፉት 10 ዓመታት ውስጥ) በዴሞክራሲ ጉዳይ እየተጨቃጨቁ እና ምዕራቡን ዓለምም እያንጓጠጡ ቀጥለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ሃገራት እየመሩ ያሉት መንግስታት ትልቁ ፍርሃታቸው አድርገው የሚያቀርቡትም በምዕራባዊያን የሚደገፍ በእነሱ ቋንቋ ‹የቀለም አብዮትን› ነው፡፡ የሁለቱም ሃገራት የጊዜው ገዥዎች ምዕራቡ ዓለም በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ከስልጣን እነሱን ለማውረድ ቀን ከሌሊት እንደሚሰራና ይሄንም እስከ መጨረሻው እንደሚፋለሙት ይገልፃሉ፡፡ የምዕራቡን ዓለም ጣልቃ ግብነት ለመከላከልም ሕጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸውን ገልፀው፤ ጠበቅ ያሉ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያድ) እና የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጎችን በስራ ላይ ማዋላቸውንም በኩራት ይገልፃሉ፡፡ በተለይም የመያድ ሕጋቸው ‹የውጭ ሐይሎችን› ከፖለቲካዉ ምህዳር ለማራቅ ያደረጉት እንደሆነ ሁለቱም በኩራት ይገልፃሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሩሲያ፡፡
ያለፉትን አስር ዓመታት ምስራቅ
አውሮፓንና የካውካስስ አካባቢን የሚገልፀው የፖለቲካ መገለጫ ‹አብዮት› ነው፡፡ ከአብዮትም ‹የቀለም አብዮት›፡፡ የኢትዮጵያም የፖለቲካ
ምህዳር በተመሳሳይ ጊዜ ባጋጠመው ትኩሳት ምክንያት ከዚህ የአብዮት ተረክ (narrative) ጋር በእጅጉ የሚጋራው ነገር አለ፡፡
አብዮተኞቹ በኬየቭ አደባባይ ሲቆሙና ሲቀመጡ፣ አብዮተኞቹ ቲብሊሲን ሲያጥለቀልቋት ኢሕአዴግ እዚህ ያነጥሳል፤ የአደባባዮቹን ጥበቃ
ያጠናክራል፣ አይናቸው በአብዮት ቀልሟል የሚላቸውን ግለሰቦች ያስራል፣ እጅግ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ስለ ቀለም አብዮት አስከፊነት በመንግስቱ
ሚዲያዎች ይለቀቃሉ፡፡
በሜይ 23፣ 2014 የቀለም አብዮትን ዋና አጀንዳው አድርጎ ከተካሔደው ሶስተኛው የሞስኮ
የዓለማቀፍ ደህንነት ስብሰባ ላይ የሩሲያ ተቀዳሚ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ጀኔራል ቫለሪ ጋሪስሚዮቭ ካቀረቡት መወያያ ላይ የተወሰደ
|
(የዩክሬን ሁለተኛው አብዮት በ2014 ሲከሰት በሚያዚያ ወር ውስጥ ብቻ ከታተሙት ሐያ ስድስት
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እትሞች ውስጥ ‹ዩክሬንን ያየ በእሳት አይጫወትም›፣ ‹ዩክሬን ወደአደገኛ ሁኔታ በመሸጋገር ላይ ናት›፣ ‹ሩሲያ
ዩክሬንን አስጠነቀቀች›፣ ‹አይሲሲ በዩክሬን ጉዳይ ምርመራ ሊጀምር ነው› የሚሉ ፅሁፎችን ጨምሮ በአስራ ሁለቱ እትሞች ለውጡን አጣጥሎ፤
ፑቲንን አጀግኗቸው እናገኛለን)
በእውነትም ያለፉትን አስር ዓመታት
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር ‹የቀለም አብዮት› እንደሚለው ሃረግ የወረረው ፖለቲካዊ መለያ አለ ማለት ከባድ ነው፡፡ ኢሕአዴግ
በየቀኑ የሚጨነቅለት/የሚጨነቅበት፣ ተቃዋሚው በቧልት የሚያየው፤ ነገር ግን ብዙዎቹን ዋጋ እያስከፈለ ያለ ተረክ - ‹የቀለም አብዮት›፡፡
የኢትዮጵያን ፖለቲካ የማቅለም ሒደት
የቀለም አብዮት የሕዝባዊ አመፅ
ቅፅል ስም ነው፡፡ የምስራቅ አውሮፓን የድህረ-ምርጫ ሕዝባዊ አመፆች ተመሳሳይነት ለመግለፅ ልሂቃን ያዳበሩት ስያሜ ነው፡፡ እንደ
ሩሲያ ባሉ ሐገራት ደግሞ ‹ሕዝባዊ አመፅ› የሚለው መጠሪያ ‹ሕዝባዊነት› ስላለው የቀለም አብዮት የሚለውን መጠሪያ መጠቀም ነገስታቱ
ይወዳሉ፡፡ ስያሜው አዎንታዊና አሉታዊ ትርጉም በየሀገራቱ ይሰጠዋል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ‹የቀለም አብዮት› እጅግ የተወገዘ እና
ለከፍተኛ ቅጣት የሚዳርግ ሲሆን - በብዙ ሐገራት ግን የሕዝብ ፍላጎት የሚገለፅበት ኹነት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ስያሜና ወቀሳ
የተጀመረው በባለ ብዙ ታሪኩ ምርጫ ‘97 ወቅት ነው፡፡ ከምርጫ ’97 በፊት ገዥው ፓርቲ ብረት ያነሱትን ፋኖዎች ከሰላማዊ ታጋዮች
ጋር በአንድ ላይ የሚጠራበት ስያሜ ነበረው ማለት አይቻልም፡፡ ‹ፀረ-ሰላም ሐይሎች› ከሚለው ብዙም የማይስብ ስያሜ ያለፈ ሕዝቡን የሚገዛ
መጠሪያ ነበረው ማለትም አይቻልም ነበር፡፡ ገዥው ፓርቲ የቀለም አብዮት የሚለውን መጠሪያ አሉታዊ ትርጉም በመስጠት ነው መሰየሙን
የሚጀምረው፡፡ ገዥው ፓርቲ በተመሳሳይ ወቅት ለቀለም አብዮት የሰጣቸውን ሁለት ትርጉሞች ማየት ምን ያክል አሉታዊነት እንደሚንፀባረቅበት
ያሳያልና እንመልከታቸው፡፡
የቀለም አብዮት በውክልና ወይም በሶስተኛ አካል ፍላጎት በጎዳና ላይ ነውጥ በሕዝብ ድምጽ ስልጣን የያዙ መንግስታትን ከስልጣን የማውረድ ሙከራ ወይም ሴራ ነው፡፡ […] [በሌላ አነጋገር] በውክልና ወይም በሶስተኛ አካል ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚካሔድ መፈንቅለ መንግስት [ነው] […]፡፡
አዲስ ዘመን፡ ዘወርዋራው የቀለም አብዮት መንገድ፣ ሚያዚያ 2006
የቀለም አብዮቶች ሁሉ የሚመሩት በአድህሮት ዓለማቀፍ ሃይላት ራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም በሌሎች ሀገራት ላይ ለማስጠበቅ ምሁራንን እና የግሉን ፕሬስ በቅጥረኝነት በመግዛት የሚቀሰቅሱት አመፅና ሁከት ደም መፋሰስ ሲሆን አብዮት ተብሎ ሊጠራ የማይችል ጸረ ህዝብና ፀረ ሀገር [እንዲሁም] ፀረ አብዮት ክንውን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡ አለን ለማለት አጉል መታከት፣ ሚያዚያ 2006
በረከት ስምኦን ‹የሁለት ምርጫዎች
ወግ› ባሉት የ1997 እና የ2002ን ምርጫ ባነፃፀሩበት በፅሃፋቸው ‹የሰላማዊ ትግል ማኪቬሊ› (The Machiavelli of
non-violence) እየተባሉ የሚጠሩት ጅን ሻርፕ በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር የበርማን ሰላማዊ ትግል ለመርዳት የፃፉት ‹FromDictatorship to Democracy› የተባለ መፅሃፋቸው ወደ አማርኛ ‹ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ› ተብሎ ተተርጎሞ
ገበያ ላይ ስናገኝው ተቃዋሚዎችና የውጭ ሐይሎች ምርጫ ‘97ን ለማደናቀፍ በማሰብ የቀለም አብዮት እንደወጠኑ ደረስንበት ይላሉ፡፡
ይህን የሚሉን በ2003 ሲሆን ወደኋላ መለስ ብለን በ1997 ገዥው ፓርቲ የወሰዳቸውን አንዳንድ ርምጃዎች ስንመለከትም አንዳንድ
እውነታዎችን ማግኝት እንችላለን፡፡
ገዥው
ፓርቲ በምርጫው ወቅት ተቃዋሚዎች ‹በፍኖተ ነገደ› እየተመሩ ምርጫውን ሊያውኩ እየተዘጋጁ ነው በማለት ዶር ነገደ ጎበዜ በ1996 መጨረሻ ያሳተሙትን ‹ሕገ መንግስት ምርጫና ዴሞክራሲ በኢትጵያ፡ ከትላንት ወዲያ እስከ ነገ› የተባለ መፅሃፍ ‹የቦይኮት› ምክር እያጣቀሰ በምርጫው የመጀመሪያ ወራት ይፅፍ ይናገር ነበር፡፡ ተቃዋሚዎችም ምርጫውን ‹ቦይኮት› አላደረጉም፤ የገዥው
ፓርቲም ትንቢት አልሰራም በዚህ በኩል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የካቲት 22/1997 ምርጫውን ለመታዘብ ከአሜሪካ ከመጡ ድርጅቶች መካከል
ሶስቱን ማለትም የአሜሪካው ዴሞክራቲክ ፓርቲ የውጭ ክንፍ የሆነውን እና በቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራውን
National Democratic Institute (NDI)፣ የአሜሪካው የሪፐብሊካን ፓርቲ የውጭ ክንፍ የሆነውንና በ2001 የአሜሪካ
ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ከባራክ ኦባማ ጋር በተወዳደሩት ሴናተር ጆን ማኬን የሚመራውን International
Republican Institute (IRI) እንዲሁም International Foundation for Electoral System
(IFES) ከሀገር በማባረር የወሰደው ርምጃ የቀጣዮቹን አስር ዓመታት ኢሕአዴጋዊ የፖለቲካ ተረክ ግልፅ ያደርገዋል፡፡
በወቅቱ በርምጃው የተበሳጩት ማዳም
ኦልብራይትና ሴናተር ማኬን ለቀድሞው ጠ/ሚ በፃፉት ደብዳቤ በድርጅቶቹ ከ20 ዓመታት
በላይ ባስቆጠረ ስራ ከአንድ ሀገር ሲባረሩ ይህ የመጀመሪያቸው እንደሆነና ውሳኔውም የምርጫውን ሒደት በእጅጉ እንደሚያጠለሸው ገልፀው፤
ድርጅቶቹም በዋናነት የሚረዱት በUSAID እንደሆነም አመልክተው ውሳኔው እንዲቀየር ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ገዥው ፓርቲ እነዚህን
ድርጅቶች ያለፈቃድ ነው ወደሃገር የገቡት በሚል ሰበብ ክልከላውን አፅንቷል፡፡ ነገር ግን በጊዜው የተሰጠው ያለፈቃድ ነው የገቡት
የሚለው ምክንያት እየቆየ በሔደ ቁጥር ሌላ ምክንያት ያለው መሆኑ መገለፁ አልቀረም፡፡ ይሄም የሆነው ምርጫውን ተከትሎ ገዥው ፓርቲ
እስከ 2002 ምርጫ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ አጠናክሮ የጀመረው የቀለም አብዮት ውርጅብኝ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት
ሶስት ድርጅቶች የቀለም አብዮትን ዓለም ላይ ለማስፋፋት ቀንደኞቹ እንደሆኑ ግልፅ አድርጓል፡፡ ዛሬ ኢሕአዴግ ለአባላቱ በሚያሰራጫቸው
ማንኛውም አይነት ፕሮፓጋንዳም ሆነ በመንግስታዊ ሚዲያዎቹ በሚያሰራጫቸው ከቀለም አብዮት ጋር በተያያዙ ፕሮግራሞች እነዚህን ሶስት
ድርጅቶች ሳይጠቀሱ ማግኝት ከባድ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ የቀለም አብዮት ተረክን
በእግሩ ካቆመው በኋላ ለዚህ ተረክ መከራከሪያ ይሆነው ዘንድ በቀለም አብዮት ላይ ያለውን አቋም የሚገልፅና ሕልዮታዊ መሰረት (theoretical
background) ለማስያዝ በ2002 ምርጫ መዳረሻ ላይ የድርጅቱ የርዕዮተ ዓለም መፅሄት እንደሆነች በተነገረችው ‹አዲስ ራዕይ›
መፅሄት ላይ ‹የቀለም አብዮትና አራተኛው አገራዊ ምርጫ› በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ በማቅረብ በወቅቱ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት አባላቱ
እንዲወያዩበት ትዕዛዝ አውርዶ ነበር፡፡ የፅሁፉ ፀሃፊ መፅሄቱ ላይ ባይጠቀስም ሚያዚያ 11/2006 የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ
‘‹የቀለም አብዮት› ለማንም የማይበጅ የጥፋት መንገድ’ ባለው ርዕሰ አንቀፁ ከዚህ ፅሁፍ ላይ በሰፊው ጠቅሶ በስህተት ይሁን በድፍረት
ፅሁፉን የፃፉት የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ናቸው ይለናል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ የቀለም አብዮት
በእያንዳንዱ የገዥው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ፅሁፍ ስር የማይጠፋ አያጅቦ (bogyman) ነው፡፡ ከ2003 አጋማሽ ጀምሮ በሰሜን አፍሪካና
በመካከለኛው ምስራቅ በተነሳው ሕዝባዊ ቁጣ ምክንያት አምባገነኖች ከስልጣናቸው ሲገረሰሱ ኢሕአዴግ የቀለም አብዮት እየታሰበብኝ ነው
ብሎ ካድሬዎቹን በንቃት እንዲከታተሉ ጠቁሞ መስከረም 2004 እነእስክንድር ነጋን ‹የቀለም አብዮት አስባችኋል› በማለት አስሮ ያልሞቀውን
ለማብረድ ሞክሯል፡፡ በ2004 ታሕሳስ አደባባይ የወጣውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄም ለማፈን ይሄን የቀለም አብዮት ካርድ
መምዘዙ አልቀረም፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በሚያዚያ 2006
‹አክራሪነትን ለመዋጋት ዳግም የተገባ ቃል› በሚል ርዕስ በመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በወጣ ፅሁፍ፡
ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነትና ሽብርተኝነት ለማስፋፋት የተካሔደው ሙከራ ዶ/ር ጃሲም ሱልጣን በተባሉና እ.ኤ.አ በ1999 ዓ/ም የከሰመው የኳታር ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባል በነበሩት ግለሰብ በኩል የተከናወነ ነው፡፡ እኒህ ግለሰብ በሙስሊም ብራዘርሁድ ፓርቲ የአክራሪነት አስተምህሮ የተቃኘ የቀለም አብዮትን ለማካሄድ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ የዶ/ር ጃሲም አስተምህሮ ወደ ኢትዮጵያ የዘለቀው በካሚል ሸምሱና አህመድ ሙስጠፋ በተባሉ ሁለት ግለሰቦች ነው፡፡
በማለት የሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ
ኮሚቴ አባል የሆኑትን ሁለት ግለሰቦች በመጥቀስ … በሙስሊም ብራዘርሁድ
ፓርቲ የአክራሪነት አስተምህሮ የተቃኘ የቀለም አብዮትን ለማካሄድ … በሚል ውንጀላ ንቅናቄውን የቀለም አብዮት ያደርገዋል፡፡ በ2006 መጨረሻ በኦሮሚያ ክልል
የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ ደግሞ ገዥው ፓርቲ አሁንም ጣቱን የቀለም አብዮተኞች ወዳላቸው ግለሰቦች/ፓርቲዎች መጠቆሙን አልተወም፡፡
‹በአዲስ አበባ - ኦሮሚያ ሽፋን ስንኩል የሽብር ሴራ› በሚል ርዕስ ሚያዚያ 27/2006
መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በወጣ ፅሁፍ፡
በፖለቲካ ፓርቲ ስም ተደራጅተው በሕግና ሕጋዊ አግባብ መወዳደርም መመረጥም ሲያቅታቸው በቀለም አብዮት ስልጣንን መንጠቅ ሁሌም የሚከጅላቸው ኃይሎች የጥፋት ልሳኖቻቸው ከሆኑ አንዳንድ የስም ጋዜጦች ጋር በፈጠሩት ያልሰመረ ጋብቻ በዩንቨርስቲዎቻችን የታየው ግርግር እንዲወለድ ሆኗል፡፡ሲለን፤ እንዲሁም በዚሁ ጋዜጣ ላይ በግንቦት 2006 ‹ከሁለት ፅንፈኞች ሴራ አገራችንን እንጠብቅ› በሚል ርዕስ በወጣ ፅሁፍ ላይ፡
እንዲሁም ከኦሮሞዎች ፈቃድና ፍላጎት ውጭ ኦሮሚያን ገንጥለው ሕዝቡ ላይ እንዳሻቸው ለመፈንጨት የቋመጡና በቀለም አብዮት ስልጣን ለመንጠቅ የተመኙ የኦሮሞ ፓርቲዎች [ናቸው ሕዝቡን ወደ አመፅ የከተቱት]
በማለት ተቃውሞው የቀለም አብዮተኞች
ሴራ እንደሆነ በመግለፅ ሁሉንም ተቃውሞዎች የቀለም አብዮተኞች ሴራ እንደሆኑ መበየኑን ቀጥሎበታል፡፡ ምርጫ 2007 ከመደረጉ ስድስት ወራት ቀደም ብለው ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ‹ተቃዋሚዎችና ኒዮ ሊብራል ሐይሎች ብሄራዊውን ምርጫ የቀለም አብዮት ለመቀስቀስ እየተጠቀሙበት ነው› በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር፡፡ምርጫው በተቃረበም ወቅት በምርጫ 2007 ‹የቀለም አብዮት ምልክቶች በቅድመ ምርጫው ታይተዋልን?› በማለት የሚጠይቀው ኢሕአዴግ ‹አዎ እየታዩ ነው› በማለት ራሱ ጠይቆ ራሱ ሲመልስ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ያለውን
ተቃውሞ ገና ከጅምሩ ሽብርተኞች የወጠኑት የቀለም አብዮት ሴራ መሆኑን ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ ገልጻል፤ እየገለፀም ነው፡፡ በጉዳዩ
ላይ አወያየዋቸው የሚላቸውን አካላትም ነገሩ ቀለም አብዮት እንደሆነ ሲሰብክ ከርሟል፡፡
በአጠቃላይ በአለፉት አስር ዓመታት
የተካሔዱትን ሶስት ምርጫዎች ‹የቀለም አብዮተኞች ሊበጠብጡብኝ ሞክረዋል› በማለት የሚከሰው ገዥው ፓርቲ፤ በአስር ዓመቱ ውስጥ የተፈጠሩትን
ሁሉንም ታላላቅ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች (የአረቡ ዓለምን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የነበረውን መነቃቃት፣ ከታህሳስ 2004 ጀምሮ እየተካሔደ
ያለውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ እንዲሁም ከሚያዚያ 2006 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል እየተካሔደ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ) የቀለም
አብዮተኞች እኩይ ሴራ ውጤት መሆኑን እየበየነ ቀጥሏል፡፡
‹የቀለም አብዮቱ› የውጭ ክንፍ
ገዥው ፓርቲ ሁሉንም አይነት ተቃውሞዎች
የቀለም አብዮት ብሎ መፈረጁ ከፕሮፓጋንዳ አኳያ ትርፋማ ያደረገው ይመስላል፡፡ በአንድ ድንጋይ የሃገር ውስጡን ተቃዋሚዎች እንዲሁም
በሌላ በኩል የምዕራብ ተችዎቹን ለመምታት ይጠቀምበታልና፡፡ ‹የቀለም አብዮት የምዕራቡ ዓለም የጣልቃ ገብነት ሙከራ ነው› በማለት
መሰረቱን ማስቀመጥ የሚጀምረው ኢሕአዴግ ‹ይሄን ሐይል ከፖለቲካው ውጭ ማድረግ አለብኝ በማለት ነው› ዛቻና ዘመቻውን የሚጀምረው፡፡
ለዚህም ሲባል ከመንግስታዊው ቀጥተኛ ግንኙነት ባለፈ በራሳቸው መንገድ የምዕራቡን ዓለም መንግስታትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን
የተገናኙ ግለሰቦች/ድርጅቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በኢሕአዴግ መነፅር የቀለም አብዮተኞች ቅጥረኞች ናቸው፡፡ ቅጥረኞች ያላቸውንም
ግለሰቦች/ድርጅቶች ለምዕራብ ተላላኪዎቻቸው ሚታዘዙና ቀለብ የሚሰፈርላቸው ናቸው እያለ ‹ተለመደና ዘኬ ባልጫ ፤ ወደ መምሬ ቤት
ሁልጊዜ ሩጫ› ሲል ይታያል፡፡
ለመሆኑ ገዥው ፓርቲ ‹የገበያ አክራሪነትን
ለመጫን በመፈለግ ሩጥ ሲሉት የሚሮጥ፣ ዝለል ሲሉት ምን ያህል ልዝለል የሚል መንግስት በቀለም አብዮት ሊመሰርቱ ይፈልጋሉ› የሚላቸው
የምዕራብ ሐይሎች እነማን ናቸው?
ይሔን መመለስ በጣም ከባድ ነው፡፡
ከባድ የሚሆነው ግን እነዚህን ሐይሎች ማወቅ ስለማንችል አይደለም፡፡ ይልቁንም እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ዘርዝረን መጨረስ የማንችላቸው
በመሆናቸው ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የቀለም አብዮት አቀጣጣዮች የሚላቸውን ድርጅቶች በትንሹ ማየቱ ጉዳዩን የበለጠ ግልፅ ስለሚያደርገው
ቃል በቃል እንጥቀሳቸው፡
የቀለም አብዮቶች በሚነሱበት ሀገራት ሁሉ ከጀርባ መሪዎቹና አስተባባሪዎቹ ምዕራባዊያን መንግስታትና የእነርሱን ዓላማ አስፈፃሚ የሆኑት ዓለማቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ (አዲስ ዘመን፡ በአረንጓዴው አብዮት የሚሰበረው የቀለም አብዮት፣ ሚያዚያ 2006) የቀለም አብዮት ዋነኛ አራማጁ ፋይናንሻል ታይምስ [ሲሆን]፣ የምዕራባዊያኑ የገበያ አክራሪ ኃይሎችን ቀለም አብዮተኖች መፈልፈያ የሆነው [ደግሞ] ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ [ነው]፡፡ (አዲስ ዘመን፡ የቀለም አብዮት ናፋቂዎች፣ ሚያዚያ 10፣ 2006) የዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጠቅላይና የቀለም አብዮት ዋነኛ ዘዋሪ የሆነው ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ [ነው]፡፡ [ይህ] ድርጅ[ት] የመሪነቱን ድርሻ እንዲወጣም ዋነኛው የአሜሪካ መንግስት ፋውንዴሽን ሆኖ በስሩ በርካታ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማቀፍ እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ ከእነዚህ አበይት አለም አቀፍ መያዶች መካከል ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዮት ፎር ኢንተርናሽናል አፌይርስ፣ ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዮት፣ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኤሌክቶሪያል ሲስተም (እነዚህ ሶስቱ በምርጫ 97 ወቅት ምርጫውን እንዳይታዘቡ ከኢትዮጵያ የተባረሩት እንደሆኑ ከላይ አይተናል)፣ ኢንተርናሽናል ሪሰርች ኤንድ ኤክስቼንጅስ ቦርድና ፍሪደም ሃውስ የተሰኙ ተቋማት ይገኙበታል፡፡ ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ የተደራጀው በቀድሞ የሲአይኤ አመራርና አባላት ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ሌላኛው የሲአይኤ ገጽታ ነው ማለት ይቻላል (አዲስ ዘመን፡ የቀለም አብዮት መፍጠሪያ “ማሽኖች” እና ተላላኪዎቻቸው፣ መጋቢት 2006)፡፡ የዲሞክራሲ (sic) ጭንብል ካጠለቁ ዓለም አቀፍ የገበያ አክራሪነት አስፈጻሚ ተቋማት [እና የቀለም አብዮት አቀጣጣዮች] ውስጥ […] ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት በአሜሪካ (USAID) […] እንዲሁም በትውልድ አይሁዳዊ የሆነው ቢሊየነር ጆርጅ ሶሮስ […] [የሚመራው] ግልጽ የማሕበረሰብ ተቋም (the open socity (sic) institute) ይገኙበታል፡፡ ትርምሱን በስተጀርባ [ከ]ሚቀምሩት [መካከል] ደግሞ የአውሮፓ ሕብረት እና […] 'የሰሜን አትላንቲክ የጋራ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (NATO) ይገኙበታል። (በይናገር ታሪኩ፡ ከቀለም አብዮትበስተጀርባ (behind the color revolution) የተደበቁ ቁማርተኞች (ለኢሕአዴግ አባላት ለውይይት የቀረበ ፅሁፍ) 2006)፡፡ [በዩክሬን ከተካሔደው ሁለተኛው የቀለም አብዮት በኋላ] የቀለም አብዮቱ አቀጣጣዮች ቡድን በፕሬዝደንቱ በኩል (የአውሮፓ ሕብረት ፕሬዝደንት) ዩክሬንን አወገዘ፡፡ በሐገራችንም ምርጫ 97 ወቅት የነበረው የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ ቡድን አሁን ድረስ በሃይማኖት ስም አክራሪ ሃይሎችን እያሰረገና ፅንፈኛ ፖለቲከኞችንም እያንቀሳቀሰ መሆኑ ይታወቃል (አዲስ ዘመን፡ ዩክሬንን ያየ በእሳት አይጫወትም ሚያዚያ 03፣ 2006)፡፡ [በሐገራችን ሊካሔድ የታሰበውን ምርጫ 2002ን ወደ ቀለም አብዮትነት ለመቀየር በማሰብ ሰሞኑን] ሒዉማን ራይትስ ዎች፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ… ከየጠቅላይ መምሪያቸው ተመሳሳይ ውንጀላ በማሰማት […] ለወጠኑት የቀለም አብዮት በመሳሪያነት የሚያገለግል እንዲሆን [ተንቀሳቅሰዋል]፡፡ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ፕሬስ ቲቪ፣ ቪኦኤ የመሳሰሉት የውጭ ሚዲያዎች[ም] በግንባር ቀደም የቀለም አብዮት አራጋቢነት ተሰ[ልፈዋል] (አዲስ ራዕይ፡ የቀለም አብዮትና አራተኛው አገራዊ ምርጫ፣ መጋቢት - ሚያዚያ 2002)፡፡ [እንዲሁም] ዘጋርዲያን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒው ዮርክ ታይምስ [ለቀለም አብዮት የተሰለፉ ሐይሎች እንደሆኑ ይታወቃል] (አዲስ ዘመን፡ ዘወርዋራው ቀለም አብዮት መንገድ፣ ሚያዚያ 2006)፡፡ [ከዚህም በተጨማሪ] […] እነ አርቲክል 19 የ2007ን ምርጫ ተከትሎ ለቀለም አብዮት መደላድል ለመፍጠር […] [ሙከራ እያደረጉ ሲሆን፤] እንደሚታወቀው አርቲክል 19 እና መሰል አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት የኋሊት ለመቀልበስ ያልሞከሩት ሴራ የለም። ከሪፖርት ጋጋታ እስከ የቀለም አብዩት ጋሻ ጃግሬዎችን እስከ መመልመል ድረስ ተፍጨርጭረዋል፤ ምናባዊና ተግባራዊ ዳገት ወጥተዋል፤ ቁልቁለት ወርደዋል። (አዲስ ዘመን፡ “አርቲክል 19”— የመብት ተሟጋች ወይስ የቀለም አብዮት አዝማች? ግንቦት፣2006) …
እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡ ዝርዝሩ
አያልቅም፡፡ ገዥው ፓርቲ እነ ሲፒጄ፤ ኦክላንድ ኢንስቲቲዩት እና አልበርት አንስታይን ኢንቲቲውትን ጭምር ዋነኛ የቀለም አብዮት
አቀጣጣይ ብሏቸው እናገኛቸዋለን፡፡ ከበርቴው ጆርጅ ሶሮስን ‹የቀለም
አብዮት አባት›፣ ሶሻሊስቷን ወ/ሮ አና ጎሜዝን ደግሞ ‹የቀለም አብዮት እናት› ብሎ ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡ ስያሜው አያልቅም፡፡
ኢሕአዴግ የሚመራት ኢትዮጵያ በዓመት
ከሚሰፈርላት አጠቃላይ እርዳታ አስር በመቶ ያህሉን የሚሸፍነው የአውሮፓ ሕብረት የቀለም አብዮት አቀጣጣይ ከተባለ፤ ከአመታዊ እርዳታዉ
በUSAID በኩል እስከ አርባ በመቶ የሚሆነውን የምትሸፍነው አሜሪካ እንዲሁም በUSAID በጀት የሚተዳደሩት እነNational Endowment
for Democracy (የNED እርዳታ ለአፍቃሬ ኢሕአዴጎችም እንደሚሰጥ ልብ ይሏል)
የቀለም አብዮት አቀጣጣዮች ከተባሉ፣ በNATO የተለያዩ ወታደራዊ ርዳታዎች የምታገኝው ኢትዮጵያ NATOን የቀለም አብዮቱ አስተባባሪ
ካለችው፣ አርቲክል 19 የገንዘብና የሙያ ድጋፍ በተለያዩ ጊዜያት ስታገኝ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ አርቲክል 19ን ዋነኛ የቀለም
አብዮት አቀጣጣይ ብላ ከፈረጀችው፣ ሶሻሊስቷ አና ጎሜዝ ከከበርቴው ጆርጅ ሶሮስ እኩል የቀለም አብዮት አንኳር ከተባሉ… ማን ቀረ?
በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን ለረሃቡም ሆነ ለችግሩ የሚደርሱት እነሱ ቢሆኑም፤ ገዥው ፓርቲ የቀለም አብዮተኛ ብሎ ያልሰየመው የምዕራብ
አውሮፓ ድርጅትና መንግስት ማግኝት በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህ ሲገርመን የመንግስታቱ ዝምታ ደግሞ የበለጠ እንድንደነግጥ ያደርገናል፡፡
‹የቀለም አብዮቱ› የሀገር ውስጥ ክንፍ
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ገዥው
ፓርቲ ‹የቀለም አብዮት› በሚለው ስያሜ የሚተቹትን የውጭ መንግስታት እንደ ቀጣሪ፤ በሀገር ውስጥ ያለውን ማንኛውንም አይነት ተቃውሞ
እንደተቀጣሪና ተላላኪ በመፈረጅ ሁለቱንም ወደጎን ለማድረግ ረድቶታል፡፡ በሀገር ውስጥ ያለውን ተቃውሞ አንዳንዴ ሕጋዊ ተቃዋሚዎችና
ሕገ ወጡን ከሕጋዊው መንገድ ለመቀላቀል የሚሞክሩ ተቃዋሚዎች ከሚለው ክፍፍል ባለፈ በአብዛኛው ሁሉንም ተቃውሞና የሐሳብ ልዩነት
የሀገር ውስጥ ሕዝባዊ መሰረት የሌለው፣ የውጭ ሐይሎች ቅጥረኛ እና የሀገር ክህደት (ባንዳዊ) ርምጃ እንደሆኑ ይገልፃል፡፡ እኔ
አባል የሆንኩበት ዞን ዘጠኝ ከጓኞቻችን ጋር በመጀመሪያ ‹የቀለም አብዮት ለማቀጣጠል ሲሞክሩ ነበር› ተብለን በታሰርንበት ወቅት
ገዥው ፓርቲ እኛን የሳለበት በመንገድ ለዚህ ጥሩ አብነት ነው፡
ሰሞኑን በድረ ገፆች ላይ በመስራት ለረጅም ጊዜ ዘመቻ ሲያካሂዱ፣ የአገሪቱን እና የመንግስትን ገፅታ ጥላሸት ሲቀቡ የነበሩት [የዞን ዘጠኝ] ግለሰቦች፣ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት እንዲነሳ፣ የጎሳ ጦርነት እንዲቀሰቀስ፣ አገሪቱ ወደ ብጥብጥና ቀውስ ውስጥ እንድትገባ፣ የተጀመረው ልማት እንዲደናቀፍ፣ በዚህም የውጭ ኃይሎችን የግብፅ፣ የሻዕቢያና እንዲሁም የኒዮ ሊብራል ኃይሎችን አጀንዳ ለማሳካት ብዙ ዓመታት ሲሰሩ የነበሩ ቢሆንም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ […] የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሔራዊ ሠላም ክብርና ጥቅም አሳልፈው ለውጭ ኃይሎች በመስጠት በቅጥረኝነት የተሰለፉት እነዚህ ወገኖች ድርጊታቸው በታሪክም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ ይልቁንም ለጠላቶቿ ታላቅ ፈንጠዝያ ለመፍጠር ሲሉ ተገዝተው የተሰለፉበት የጥፋት ጎዳና ለእነሱም ሆነ ለማንም አይበጅም፡፡
አዲስ ዘመን፡ ኢትዮጵያ በአመፅ አትፈርስም፣ ግንቦት 10፣ 2006
ሁኔታውን [የዞን ዘጠኞችን ድርጊት] እንደ ዜጋ ስንመለከተው አሳፋሪው ነገር፣ ትናንት “አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ እናደርጋታለን” ያለውንና ይህ ቀቢፀ-ተስፋው እንደ ጉም ብን ብሎ የጠፋውን የሻዕቢያን ህልም ለማሳካት እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የዘመናት ቁጭት የሆነውን፣ የ‘አይቻልም’ን መንፈስ የሰበረውንና እንደ ዓይኑ ብሌን የሚመለከተውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ በሁከት እንዲቋረጥ ባንዳ ሆኖ መሰለፍ ነው። አባቴ ይሙት! ማንኛውም ዜጋ በእነርሱ [በዞን ዘጠኞች] ቦታ ሆኖ ማፈሩ አይቀርም። ባንዳነት ሀገራችን ውስጥ ‘ወንዜነት’ የሌለው ሀገርን አሳልፎ የመስጠት አሳፋሪ እሳቤ ነውና።
አዲስ ዘመን፡ የ“ዞን 9 አባሎች”—ጦማሪዎች ወይስ ህቡዕ
ተቀጣሪዎች?፣ ሰኔ 2006
በነዚህና በመሳሰሉት ፍረጃዎች ተቀጣሪ የሚላቸውን ሐይሎች ባንዳና እና አቆርቋቋዥ በሚል ስያሜ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲጠሉና
ራሱን የሀገሪቱ ችግሮች መድኃኒት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይህ ከነሱ አስተሳሰብ ውጭ የሉትን ዜጎች ብሄራዊ ስሜት የሌላቸውና ባንዳ
እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ያረጀ አምባገነናዊ ስልት ሲሆን፤ በብዙ ሀገሮች ተቃውሞን ለማጣጣል ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ አሁንም እየዋለ
ያለ ነው፡፡
ሰርቢያዊው ስራዳ ፖፖቪች በጎርጎሮሳዊያኑ 2000 የአምባገነኑን ስሎቦዳን ሚሎሶቪችን ስርዓት በተማሪዎች ተቃውሞ ያስወገደው
የOTPOR የተባለውን ቡድን ያደራጀና የመራ ሲሆን በቅርቡ በLegatum Institute ባቀረበው አንድ ፅሁፉ ላይ ያጋጠመውን
ሲገልፅ:
‹‹ተቃውሟችንን ከጀመርን በኋላ በአንድ ሞቃት የበጋ ቀን ሶስት የመንግስት ሚኒስትሮች በቴሌቪዥን ቀርበው ‹በሲአይኤ
የተቀነባበረና በቅጥረኛ ተማሪዎች እየተካሔደ ያለ እንቅስቃሴ ነው› ሲሉ ሰማሁ፡፡ ወዲያውም…›› ይላል ፖፖቪች ‹‹…የሴት ጓደኛዬ
ደውላ እየሳቀች ‹የኔ የውጭ ቅጥረኛ፣ ወፍራም ቼክ እንደተቆረጠልህ እንዴት አላወኩም፤ ብሩማ ከመጣ ልታዝናናኝ ነው ማለት ነው?›
አለችኝ እያሾፈች›› ይላል፡፡
(አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሚያዚያ 28/2006 ባወጣው
‹ዘወርዋራው ቀለም አብዮት መንገድ› የተባለ ፅሁፍ ‹‹ኦትፖር የተባለው የሰርቢያ የአክቲቪስት ግሩፕ ለሚያደርገው የቀለም አብዮት በዩናይትድ ስቴትስ
መሰረቱን ካደረገው አልበርት አንስታይን ኢንስቲቲውት የስትራቴጅ ስልጠናና የሕትመት [የገንዘብ] ልገሳ ይደረግለት እንደነበር ይታወቃል››
በማለት አስቂኙን ጉዳይ ይደግመዋል፡፡)
‹‹ይህ አይነት ተቃውሞ ሁሉ የውጭ ሐይሎች ሴራ ነው የሚል ተረክ ለአምባገነኖች ሁለት አይነት ጥቅሞችን ይሰጣል›› የሚለው
ፖፖቪች ‹‹አንደኛ ተቃውሞዎችን እና የሐሳብ ልዩነቶች ሁሉ ከውጭ የሚጫኑ ናቸው ከተባለ ተቃዋሚዎች ሁሉ ባንዳዎች እና ሀገር የካዱ
እንደሆኑ ለሕብረተሰቡ ይገልፃል፤ ሁለተኛ ሕብረተሰቡ አይኑን ወደ ውስጣዊ ችግሮች እንዳያዞር በማድረግ ሀሳቡን ሁሉ እነዚህ የውጭ
ሐይሎች የተባሉት ላይ እንዲያደርግ ያስችላቸዋል›› በማለት ይገልፃል፡፡ ይህ የቀለም አብዮት የተባለ ተረክም ተመሳሳይ ውጤት ያለው
ሕብረተሰቡን የማደንዘዣ (the Opium of the Mass) መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡
‹‹በአንድ አገር ውስጥ የቀለም
አብዮት እንዲኖርና አልፎ ተርፎም እንዲሳካ ከማድረግ አኳያ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ጠንካራ አንድነት ያለው የተቃዋሚ ጎራ መኖር
እንዳለበት በመስኩ የተራቀቁት የቀለም አብዮተኞች ይገልፃሉ፡፡›› (አዲስ ራዕይ፡ የቀለም አብዮትና አራተኛው አገራዊ ምርጫ፣ መጋቢት
- ሚያዚያ 2002) የሚለው ገዥው ፓርቲ ሀገሪቱን ያለምንም ተቀናቃኝ ተቆጣጠሯት እንኳን ከቀለም አብዮት ፕሮፓጋንዳው ፈቅ አለማለቱን
ስናይ ፖፖቪች ባለው አንፃር ችግሮችን ሁሉ ከውጭ የመጡ አድርጎ የማቅረብ (externalization) አካሄድና ራሱ ግን ምሉዕ
በኩልሔ እንደሆነ የማሳየት ዓላማ እንደሆነ ለመረዳት ብዙም አያዳግትም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ያወጣችው አዋጅ
እራሷን ከአክራሪ ዓለማቀፍ አክራሪ የገበያ ኃይል ለመከላከልና ከቀለም አብዮት ለመታደግ እንዲቻላት [ነው]፡፡›› (አዲስ ዘመን፡
የቀለም አብዮት ናፋቂዎች፣ ሚያዚያ 10፣ 2006) በማለት በግልፅ የሚናገረው ገዥው ፓርቲ ይህን ካደረገ ከሰባት ዓመታት በላይ
ቢያልፈውም አሁንም ቀለም አብዮተኞች መጡብህ እያለ ቀጥሏል፡፡ የቀለም አብዮት የምዕራብ የገበያ አክራሪዎች ደባ ነው ሲል ቆይቶ
ሲያሻው ደግሞ ‹…በሙስሊም ብራዘርሁድ ፓርቲ የአክራሪነት አስተምህሮ
የተቃኝ የቀለም አብዮት…› እያለ አሁንም የህዝብን ተቃውሞ ሁሉ ማጣጣሉን ተያይዞታል፡፡
ገዥው ፓርቲ ተቃውሞዎችን ሁሉ ‹የውጭ ሐይሎች ደባ›፣ ተቃውመው አደባባይ የወጡትን ዜጎች ሁሉ ‹ቅጥረኞች› እያለ ለጥያቄዎቹም
መልስ መስጠትን እምቢ ብሏል፤ ለጠያቂዎቹም ስብዕና እውቅና እንኳን መስጠት አልፈልግም ብሎ ቀጥሏል፡፡ ከላይ የጠቀስነው ፖፖቪች ‹ከእንደዚህ አይነት መንግስታት የሚመጡትን ‹የውጭ
ሐይሎች ናቸው - የውጭ ቅጥረኞች ናችሁ› ውንጀላዎች እንደቁም ነገር መውሰድ የለብንም፤ ይልቁንም ለእንደዚህ አይነት ውንጀላዎች
ትክክለኛው መልስ ቧልትና ቀልድ ነው› ይላል፡፡ በርግጥም ‹የችግሮቻችን ሁሉ ምንጮች አውሮፓና አሜሪካ ናቸው› በማለት ሀገሩን ሲያምስ
ቆይቶ ሲቸግረው እጁን ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለልመና የሚዘረጋ መንግስት ከቧልት የዘለለ መልስ አይገባውም፡፡
No comments:
Post a Comment