በዘላለም ክብረት
ረጅም ነው፡፡ ደረቱ ከልክ በላይ ሰፊ ነው፡፡ በደረቱ የጥይት እርሳስ አንጥሮ አንደሚመልስ በጉራ ሳቅ እያለ ይናገራል፡፡ ደረቱ ለምን እንደሰፋ ሲናገር ያለፈበትን ፈተና ያስተጋባል፡፡ ሸካራው እጁ እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ምን ቢሰራ ነው እንዲህ የጠነከረው? ያስብላል፡፡ እድሜውን በትክክል ባያውቀውም 29 ዓመቱ እንደሆነ ግን ይገምታል፡፡ አማርኛ መናገር ስለሚያስቸግረው ‘ተው ባክህ’ የሚል ሐረግ እዚህም እዚያም ጣል ያደርጋል፡፡ ሲናገር ፈገግታ ሁሌም ከፊቱ አይጠፋም፡፡ አፍንጫው በንግግሮቹ መሃል ይነፋል፡፡ የእጅ መሳሪያውና RPGው በአይኑ ላይ ውል ሲሉበት የመሳሪያ ድምፅ በአፉ እያወጣ፣ ጣቶቹን እንደ መሳሪያ ደቅኖ ትዝታውን ያስታምማል - አብዱልከሪም አብዱልሰመድ አብዱልቃድር፡፡
አብዱልከሪም የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ወታደር ነው፡፡ ቤሕነን አብዱልከሪም ደም ውስጥ ይራወጣል፡፡ ለብዙዎች የግንባሩ ስም አዲስ ቢሆንም ቤሕነን ግን ረጅም ታሪክ ያለው ሲሆን፤ ቤሕነንን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡም የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልልን የፖለቲካ ሁኔታ መረዳት አይቻልም፡፡
(ወታደራዊውን አምባገነን የደርግ መንግስት ለመጣል ወጣቶች ወደ ጫካ ገቡ፡፡ በኢሕአዴግ ቋንቋ ወታደራዊው መንግስት በወደቀበት ወቅት አስራ ሰባት የታጠቁ ሐይላት ራሳቸውን አስታጥቀው እየታገሉ ነበር፡፡ እንግዲህ ቤሕነን ከነዚህ አስራ ሰባት ድርጅቶች አንዱ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ስልጣን ይዞ በየክልሉ ስልጣን ለነዚህ አስራ ሰባት ድርጅቶች ማከፋፈል ጀመረ፡፡ ቤሕነንም የቀድሞው ክልል ስድስት፤ የአሁኑ ቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል ደረሰው፡፡)
በ2002 በአንድ ሰበበኛ ቀን አብዱልከሪም ከጓደኞቹ ጋር በተለምዶ ‹የደማዚን እርሻ› እየተባለ ወደሚታወቀው የሱዳን እርሻ በቆሎ ለመሰብሰብ ይሄዳሉ፡፡ አብዱልከሪምና ጓደኞቹ ለጥቂት ቀናት በቆሎ ሲሰበስቡ ከቆዩ በኋላ ግን ሕይወት እንዳሰቡት አላዋለቻቸውም፡፡ ባላሳቡበት ቅጽበት ከየት መጡ ያላሏቸው የታጠቁ ሩጣና ቋንቋ ተናጋሪዎች (ሩጣና የበርታዎች ቋንቋ ነው) እሱንና ጓደኞቹን በመሳሪያ አስገድደው ወደ ሩቅና ወደማያውቁት ሐገር ሊወስዷቸው መኪና ላይ ጫኗቸው፡፡
(የደማዚን እርሻ (Al-Damazin Farms) ከኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚገኝ እርሻ ሲሆን በርታዎች የደማዚን መሬት በሙሉ የበርታ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የደማዚን እርሻ በዓለማቀፍ ደረጃ ታዋቂነትትን ያተረፈ ቦታ ነው፡፡ ሟቹ የዓልቃዒዳ መሪ ኦሳማ ቢንላደን ከ1983 እስከ 1989 ድረስ ሱዳን በነበረበት ወቅት በባለቤትነት ያስተዳድረው የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ ቢንላደን የዓልቃኢዳ አባላትን በእርሻው ቦታ ያሰለጥንበት እንደነበረ ከታወቀ በኋላ የሱዳን መንግስት በደረሰበት ዓለማቀፍ ጫና ምክንያት ቢንላደንን ከሐገር ሲያባርር እርሻውን ደግሞ በመንግስት ቁጥጥር ስር አድርጎት ለረጅም ዓመታት ቆይቷል፡፡ በቅርቡ የግብፅ መንግስት ከዚሁ መሬት ላይ ‘ጥጥና ሱፍ አለማበታለሁ’ በማለት ሰፊ መሬት ወስዷል)
ከሶስት ቀናት አድካሚ ጉዞ በኋላ አብዱልከሪም እና ጓደኞቹ የማያውቁት በተራሮች የተከበበ በርሃማ ቦታ ላይ ወረዱ፡፡ በወቅቱ ግራ የተጋባው አብዱልከሪም ይህ ቦታ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት መኖሪያው እንደሚሆን በወቅቱ መገመት አልቻለም፡፡ ትንሽ እንዳረፉ ግን ስለ ቦታው ምንነትና እነሱ ለምን ወደቦታው እንዲመጡ እንደተደረጉ ገለጻ ተደረገላቸው፡፡ ያሉት በኤርትራ መሬት ላይ ሲሆን አሁን ያሉበት ቦታ ልዩ ስሙ ‘ሀሬና’ እንደሚባልና ከኢትዮጵያና ከሱዳን ድንበር እጅግ ቅርብ በሆነ አቀማመጥ ላይ የሚገኝ ቦታ እንደሆነም በተጨማሪ ተገለጻላቸው፡፡ ወደዚህ ቦታ እንዲመጡ የተደረጉትም የቤኒሻንጉል ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና በመቃወም ዳግም ወደ ጫካ የተመለሰውን የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) እንዲቀላቀሉ ታስቦ መሆኑን ተነገራቸው፡፡ ነገር ግን ከሶስተኛ ክፍል ያልዘለለ መደበኛ ትምሀርት ላልተማረው አብዱልከሪም በወቅቱ የተሰጠው ምክንያት ብዙም የሚገባው አልነበረም፡፡
(ቤሕነን ቤኒሻጉልን ለአምስት ዓመታት ከ1984 – 1988 ካስተዳደረ በኋላ፤ በ1988 ‘የታምራት ላይኔ መፈንቅለ መንግስት’ ብለን ልንጠራው በምንችለው ሂደት ኢሕአዴግ ‘አልተመቸኝም’ ያለውን በበርታዎች የበላይነት ሲመራ የነበረውን የክልሉን መንግስት ‘የአሶሳ ልጆች’ ከ ‘መንጌ ልጆች’፣ ‘የደጃዝማች ሸህ ሆጀሌ ቤተሰቦች’ ከ ‘የደጃዝማች ሙስጠፋ ቤተሰቦች’ በሚል በርታዎችን ከሁለት ከፍሎ አቶ ታምራት ላይኔ በመሩት ስብሰባ የጉምዞች የበላይነት የሰፈነበት መንግስት አቋቋመ፡፡ ፍክክሩንም “በርታዎች ከጉምዞች” የሚል አዲስ መልክ አስያዘው፡፡ ቤሕነንም ከአምስት ዓመታት ረፍት በኋላ በድጋሚ መሳሪያውን አንስቶ ጫካ ገባ፡፡)
ከዛን ጊዜ ጀምሮ አብዱልከሪም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀሬናን ጨምሮ በምዕራብ የኤርትራ በርሃዎች በየቀኑ የፕሮፓጋንዳ ትምህርትና ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየወሰደ ከሌሎች ተዋጊ ቡድኖች ጋር ተቀራርበው እንደኖሩ ፈገግ እያለ ያስታውሳል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ አብዱልከሪም ለምን ታፍኖ ወደ ኤርትራ በርሃ እንደተወሰደ ይረዳል፡፡ አሁን የቤኒሻንጉል ሕዝብ ጥያቄም ለርሱ ግልፅ ነው፡፡ እንዲያውም ጥያቄውን በራሱ ቋንቋ በሩጣንኛና በአረብኛ በደንብ እንደሚተነትን ይናገራል፡፡
ከአምስት ዓመታት የበርሃ ስልጠና በኋላ አብዱልከሪምና ሌሎች ዘጠኝ ጓደኞቹ (ከዘጠኙ መካከል አብዱ ሐሚዝና ኢሳቅ ኢብራሒም የ16 እና የ17 ዓመት ልጆች ናቸው) ወደ ቤኒሻንጉል ተመልስው ገጠር በመግባት ሕዝቡን በፍትህና በዴሞክራሲ ጥያቄዎች ላይ ትምህርት እንዲሰጡ፤ ችግር ካጋጠማቸውም እንዲዋጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው በመጋቢት 2007 ከአድካሚና ረጅም ጉዞ በኋላ የቤኒሻንጉል ምድር ደረሱ፡፡ ነገር ግን ነገሮች እንዳሰቧቸው ቀላል አልሆኑም፡፡ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር በተደረገ አጭር የተኩስ ልውውጥ አንድ ጓደኛቸው ቢሞትባቸውም ከተኩስ ልውውጡ ይልቅ ፈተና የሆነችባቸው ግን ተፈጥሮ ነበረች፡፡ ውሃ ተጠሙ፡፡ ጫካ ውስጥ ያገኙትን ‘ውሃ ነገር’ ሁሉ ቢጠጡም የተፈጥሮ ጥያቄያቸውን መመለስ ግን አልቻሉም፡፡ ለዚህም መፍትሔ ሆኖ የታያቸው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ትጥቃቸውን ሁሉ ጫካ ውስጥ ደብቀው ሱዳን ውስጥ የሚገኝ በአቅራቢያቸው ያለ አንድ መንደር ውስጥ ውሃ ለመጠጣት መሔድ፡፡ ሐሳባቸውን ተግባራዊ አድርገውም ኩርሙክ አጠገብ የምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ውሃ አግኝተው እየጠጡ-እየተጫወቱ እያለ በድንገት ከየት መጡ ያላሏቸው የሱዳን ወታደሮች ከበቧቸው፡፡ ተያዙ፡፡ ወዲያው ለኢትዮጵያ ወታደሮች ተላልፈው ተሰጡ፡፡
(በ1988 ኢትዮጵያና ኤርትራ እፍ ያለ ፍቅር ውስጥ ነበሩ፡፡ ኤርትራ ሎዓላዊነቷ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሱዳን ጋር ፀብ ውስጥ ገባች፡፡ በወቅቱ በፀቡ ላይ ገለልተኝነት እንዲያሳይ በሱዳን መንግስት በጥብቅ ሲጠየቅ የነበረው ኢሕአዴግ በግልፅ የኤርትራ ወገንተኛ መሆኑን በማወጁ የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት እጅጉን ሻክሮ ነበር፡፡ ከዚህ ጋርና በደቡብ ሱዳን ከነበረው ሁኔታ ጋር ተያይዞም በቤኒሻንጉል በኩል በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የድንበር እሰጣ-ገባ ተነሳ፡፡ በወቅቱ በኢሕአዴግ አቋም የተበሳጩት ፕሬዘደንት ኦማር አልበሽር “ሰራዊታችን በሁሉም መልኩ ዝግጅቱን አጠናቆ የትግሬ ወታደሮችን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ እየጠበቀ ይገኛል” በማለት ሕወሃትን ብቻ ነጥለው መዛታቸውም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ አልበሽር በሱዳኑ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው “በአላህ ፈቃድ ዝም አንልም፡፡ አስመራ፣ አዲስ አበባና ካምፓላ ላሉት ተንኳሽ መንግስታት መልስ አንሰጣለን፡፡ ለተቃዋሚዎቻቸውም መሳሪያ እናስታጥቃለን፡፡” ብለውም ነበር፡፡ አሁን አልበሽር ከኢሕአዴግ ጋር ፍቅር በፍቅር ሆነው ያማራቸውን የውጭ ጉዞ ጥማት አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ አሶሳ፣ መቐለ … እየተመላለሱ እየቆረጡ ነው፡፡ እንደ አብዱልከሪም ያሉትን የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎችን ከሃያ ዓመታት በፊት አስታጥቃለው ካሉት ቃላቸው በተቃራኒው ይዘው ለኢሕአዴግ እያስረከቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የኤርትራን ኤርትራ ደግሞ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች እያሰለጠኑ ጸባቸውን አክርረው ቀጥለዋል፡፡)
አብዱልከሪምና ጓደኞቹ በተያዙበት ወቅት መጀመሪያ የተወሰዱት ወደ አሶሳ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ነው፡፡ በማታ ወደ ካምፑ ታስረው የገቡት እነአብዱልከሪም በሰራዊቱ አባላት አሰቃቂ ድብደባ የተፈፀመባቸው ሲሆን፤ በፌሮ ብረት ውሃ ላይ ሲደበደብ እንደቆየ የሚናገረው አብዱልከሪም በተያዙበት እለት ሌሊቱን ሙሉ አብዱልከሪም ብቻ ‘አንተ ነህ መሪው’ በሚል መነሻ በተለምዶ ‘ሒሊኮፍተር’ እየተባለ የሚጠራውን የግርፋት አይነት እንደሚገፈፍ በግ ተሰቅሎ ሲገረፍ እንዳደረ ይናገራል፡፡ ዝናብ ሌሊቱን ሙሉ እየዘነበበት ዛፍ ላይ በሒሊኮፍተር ቅርፅ ተሰቅሎ ሲሽከረከር ያደረው አብዱልከሪም ከስምንት ሰዓታት ስቅላት በኋላ መሬት ሲወርድ እጆቹ ሁሉ መንቀሳቀስ አቅቷቸው እንደነበር ሲያስታውስ ፊቱ ላይ ሐዘን ይታያል፡፡
(‘ሒሊኮፍተር’ የተባለው የማሰቃያ ዘዴ (Torture Method) በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ የገነነ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኤርትራ ዜጎቿን በዚህ አይነት የማሰቃያ ዘዴ እንደምታሰቃይ በተደጋጋሚ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያም በተለይም ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በዚህ የስቃይ አይነት ዜጎችን እንደምታሰቃይ አብዱልከሪምና መሰሎቹ ምስክሮች ናቸው፡፡)
አብዱልከሪምና ጓደኞቹ በግንቦት አጋማሽ 2006 ነበር ወደ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) የመጡት፡፡ በዛን ወቅት አብዱልከሪም እኔ ያለሁበት ክፍል ውስጥ (በተለምዶ ሳይቤሪያ 5 ቁጥር የሚባል ክፍል) ተመድቦ የመጣ ጊዜ በባዶ እግሩ በጣም የተዳከመ ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ የገባ ሰሞን በጣም እንቅልፍ ይተኛ ነበር፡፡ እጅግ በጣም አድካሚ መከራና ስቃይ አልፎ እንደመጣም ያስታውቃል፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ማዕከላዊ ምንም እንኳን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለውን ታሪኩን ደጋግሞ ቢነግራቸውም “የሕዳሴውን ግድብ ልናጠቃ ተልዕኮ ተሰጥቶን ነበር በማለት እመን፤ አመጣጣችሁን ዋሽተኸናል” እያሉ በየቀኑ ‘መርማሪ ፖሊሶቹ’ ይገርፉት ነበር፡፡ አብዱልከሪም ‘ለምርመራ’ ተጠርቶ ተደብድቦ ሲመጣ ድካሙ ስለሚብስበት ይተኛ ነበር፡፡ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነበር በጊዜው የነበረው፡፡ አንድ ቀን ማዕከላዊ ከጓደኞቹ ጋር ተጠርቶ ሲመለስ ‘ምን አሉህ?’ አልነው፤ እሱም ‘መሳሪያችን ከፊታችን አስቀምጠው ፎቶ አነሱን’ አለን፡፡ ለካ በቴሌቪዥን ካሜራ ቀርጸዋቸው በማታው የቴሌቪዥን ዜና ‘አስር አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ’ የሚል ዜና ተላልፎ ነበር፡፡ አብዱልከሪም ‘በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረሃል’ የሚለው ነገር ለረዥም ጊዜ ምን ማለት እንደሆነ አይገባውም ነበር፡፡ ‘ምንድን ነው ሽብርተኝነት?’ ይላል ሁሌ፡፡ ‘አሸባሪ እኔ እሆናለሁ እንዴ?’ እያለም ፈገግ ማለት የዕየለት ደንቡ ነበር፡፡ አያይዞም ‘እኔ ልማት የለም፣ ዴሞክራሲ የለም ብየ ለቤኒሻንጉል የታገልኩ ታጋይ ነኝ እንጅ አሸባሪ አይደለሁም’ ይላል በሚያስቸግረው አማርኛ፡፡ ፍርድ ቤት ቀርበው የሃያ ስምንት ቀን ቀጠሮ ሲሰጥ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት እጅግ ይቸግረው ነበር፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ያለአስተርጓሚ ስለነበር የሚቀርቡት ዳኛዋ ምን ትዕዛዝ እንደሰጠች እንኳን ማወቅ ሳይችሉ ይመለሱ ነበር አብዱልከሪምና ጓደኞቹ፡፡
(የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ከሚታወቁት ሰላማዊ ግለሰቦችን ለማጥቂያ መሳሪያ ከመሆኑ ባሻገር፤ በዋናነት ሰለባ ያደረጋቸው የተለያዩ ብረት ያነሱ ኃይሎችን መሆኑ ክሶቹን ተመልክቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ የሕጉ ሰለባ ግለሰቦች አማርኛ ቋንቋ የማይናገሩ መሆናቸው ሕጉም ሆነ ክሳቸው ምን ማለት እንደሆነ ሳይገነዘቡ ለረጅም ዓመታት እስር መዳረጋቸው ደግሞ አሳዛኙ እውነታ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በአስተርጓሚ እጦት የሚቸገሩ ከመሆናቸውም ባለፈ ባብዛኛው አስተርጓሚ የሚባሉት ራሳቸው ‘መርማሪ ፖሊሶቹ’ ስለሚሆኑ እንደአብዱልከሪም ላሉ ተከሳሾች ጥላቻና ንቀት ያላቸው ናቸው፡፡)
እኔ መደበኛ ክስ ተመስርቶብኝ ወደ አዲስ አበባ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት (ቂሊንጦ) በሔድኩበት ወቅት አብዱልከሪም ምርመራ ጨርሶ የነበረ ቢሆንም ከቤኒሻጉል ተይዘው በመጡ አዲስ ተከሳሾች ምክንያት ዱላውና ድብደባው በአዲስ መልክ በርትቶበት ነበር፡፡ በጥቅምት 2007 ላይ አብዱልከሪም ከጓደኛው ፈተልሙላ አጣሂር ጋር እኔ ወዳለሁበት ቂሊንጦ ዞን አንድ ተመደበ እና በአጋጣሚ አንድ ቤት (ዞን አንድ፣ አንደኛ ቤት) አብረን ሆንን፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ማታ ማታ ሁሌ ብዙ ነገር እናወራ ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን አዝኖ ቤተሰብም ሆነ ጠያቂ ስለሌለው ራሱን በትንሽ ገንዘብ (በወር 60 ብር) ለመደጎም የጀመረውን ለእስረኞች ወጥ የማመላለስ ስራ ፖሊሶች እንደከለከሉት ነገረኝ፡፡ ‘ለምን?’ ብየ ስጠይቀው ‘እነዚህ ጥቋቁር ልጆች ምንም ስራ እንዳይሰሩ፤ አሸባሪዎች ናቸው’ ብሎ አንድ ፖሊስ ከለከለኝ አለኝ፡፡ ልብን ይሰብራል፡፡ ከመከልከሉ ይልቅ የተከለከለበት ምክንያት ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ከዚህ የፖሊሶቹ ተግባር ባለፈ ረዘም ያሉና የቆዳ ቀለማቸው ጠቆር ያሉ ሰዎች ሁሉ የጋምቤላ ተወላጆች ለሚመስሉት አብዛኛው እስረኛ አብዱልከሪምን ‘ኡጁሉ’ እያለ የሚጠራው የነበረ ሲሆን፡፡ ገራገሩ አብዱልከሪም ግን ‘እኔ በርታ ነኝ፤ ምንድነው ኡጁሉ?’ እያለ ፈገግ ከማለት ውጭ አይከፋውም ነበር፡፡
(የቆዳ ቀለምን መሰረት አድርጎ የሚደረገው ፍረጃና ማግለል፤ በተለይም በጋምቤላ እና በቤኒሻጉል ክልሎች ላሉ የፖለቲካ ቡድኖች አንዱ የተቃውሟቸው መሰረት ነው፡፡ ቤሕነን በርታዎችን በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ከምትገፋ ኢትዮጵያ የራሱን ሀገር መመስረት እንደሚመርጥ በፕሮግራሙ የገለጸ ሲሆን፤ ይሄም መጀመሪያ በርታዎች ከቤኒሻንጉል ክልል ተነጥለው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ በሕገ መንግስት አንቀጽ 47 መሰረት የራሳቸውን ክልል ለማቋቋም ከጠየቁት ጥያቄ አንድ ርምጃ ወደፊት የሔደ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት ጥፋተኛ ተብለው ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዘደንት አቶ ኦኬሎ አኳይ ጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋዴን) የተባለ ተገንጣይ (secessionist) ፓርቲ ያቋቋሙበትን ምክንያት ሲያስረዱ “በአኝዋኮች ላይ ከሚደረገው የዘር ማጥፋት በላይ ‘ለማ’ እና ‘አዲስ ጎማ’ እተባልን በቆዳ ቀለማችን ምክንያት የምንገፋበት ሃገር ውስጥ መኖር አስፈላጊ አይደለም” በማለት ይገልጻሉ)
አንድ ቀን አብዱልከሪም አማርኛ ለማንበብ እየሞከረ ነበርና “‘ሕገ መንግስት’ የሚባለውን ‘ኪታብ’ ስጠኝ” ብሎኝ ሰጠሁት፡፡ እሱም ምንነቱን አይቶ ስለቤኒሻንጉል የሚያወራውን አንቀጽ እንዳሳየው ጠይቆኝ አንቀጽ 47/1/6 ላይ ከዘጠኙ ክልሎች አንዱ የቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልል መሆኑን የሚጠቅሰውን ክፍል ሳሳየው ተገርሞ ‘እንዴት ጉሙዝ ይባላል? የቤኒሻንጉል ሕዝብ አንድ ነው እነሱ ለምን ጉሙዝን ለብቻ ሕገ መንግስት ላይ ይጽፋሉ?’ እያለ ተበሳጨ፡፡ እኔ ‘ሁለቱ ይለያያል ብለው ነው ይሄን ያደረጉት’ ብለውም ሊያምን አልቻለም፡፡ በርሃ እያለ የቤኒሻንጉል ሕዝብ ሁሉ አንድ መሆኑን በደንብ ተነግሮታል፡፡ የጉሙዝ ልጆች ከበርታ ልጆች ጋር አንድ ላይ ብረት አንስተውም ተመልክቷል፡፡ ‘ታዲያ ሕገ መንግስቱ ለምን ይለያየናል?’ ማለቱ እንግዲህ ከዚህ የራሱ እውነት የሚመነጭ ነው፡፡
(የቤኒሻንጉል ክልልን ፖለቲካ ያጠኑ ሊቃውንት ይሄ ‘ጉምዝ ከበርታ’ የሚለው ምንታዌ የፖለቲካ አሰላለፍ ኢሕአዴግ የለመደውን ሕዳጣንን በብዙኃን ላይ የማንገስ ዘይቤ ተቀጥላ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም አሰላለፍ ያመች ዘንድ በክልሉ የሚኖሩ አምስቱም ነባር (indigenous) ሕዝቦች (በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮሞ) የየራሳቸውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመሰርቱ ያደረገው ኢሕአዴግ አንዱን የአንዱ አለቃ በማድረግ ክልሉን በሩቅ መቆጣጠር ችሏል፡፡)
አብዱልከሪም የምርጫ 2007 የፓርቲዎች የቴሌቪዥን ክርክርን እያየ ‘ወላሂ ሽማግሌው ጎበዝ’ ነው ይላል ዶ/ር መረራ ጉዲና ሲናገሩ ከት ብሎ እየሳቀ፡፡ መረራ የሕዝቡን ችግር ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ መንገራቸው ነው ለአብዱልከሪምና መሰሎቹ መረራን እንዲወዱ ያደረጋቸው፡፡ ቤኒሻንጉልን የተመለከተ ዜና ሲመለከት ልቡ የሚሰቀለው አብዱልከሪም፤ የሕዳሴው ግድብ ለቤኒሻንጉል ሕዝብ ምን ጥቅም እንደሚሰጠው ብዙም አይገባውም፡፡ ‘ልማት ማፍረስ የቤሕነን አላማ አይደለም’ የሚለው አብዱልከሪም ፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር የሚባለው ነገር አይገባውም፡፡ ‘እውነትን ብቻ መናገር ያስፈልጋል’ የሚለው አብዱልከሪም ‘መከራከር በመሳሪያ ነው’ ብሎ ያምን እንደነበር እየሳቀ ይናገራል፡፡ ‘አዎ እኔ የቤሕነን ወታደር ነኝ፤ ለልማትና ዴሞክራሲ ታግያለሁ፤ ልማት ላጠፋ ግን አልመጣሁም’ ብሎ ውሸት በማያውቀው አንደበቱ ንጽህናው ተናግሯል፡፡ ከሳሹ ግን ‘አይ ግድቡንም ሊያጠቁ ነበር’ ብሎ ከመካከላቸው ያስቀረውን ጓደኛቸውን ለምስክርነት አቅርቦባቸዋል፡፡ ነገር ግን ውሸትን ከሚጸየፉት የበርታ ልጆች አንዱ የሆነው የከሳሽ ምስክር ‘እኛ ግድብ ልናፈርስ አልመጣንም’ በማለት መስክሮ የነአብዱልከሪምን እውነት አረጋግጧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁሉንም ተከሳሾች በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀጽ 7/1 መሰረት ጥፋተኛ በማለት የአራት ዓመታት ጽኑ አስራት በሰኔ ወር 2007 መጀመሪያ ላይ ፈርዶባቸዋል፡፡
አብዱልከሪም ተፈርዶባቸው የተመለሱ እለት አራት ዓመት ማለት ምን እንደሆነ በቅጡ አልተረዳውም፡፡ ሁሌም የማይለየውን ፈገግታው ፊቱ ላይ ብትን አድርጎ ‘አቡሌ አይዞህ’ ይለኛል እኔኑ፡፡ ‘አቡሌ’ ማለት በበርታ ቋንቋ ‘ጓደኛዬ’ ማለት እንደሆነ ስንቴ ነግሮኛል? አብዱልከሪምን ሲፈታ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ በጠየኩት ቁጥር ‘አሁን ረፍት ያስፈልጋል’ ይለኛል፡፡ ቤኒሻንጉል ውስጥ ወደ ትውልድ ቦታው ‘ቁቆ’ ተመልሶ በልጅነቱ ይወዳት የነበረችውን ‘ለይላ’ የምትባል ወዳጁን አግብቶ ማረስ እንደሚፈልግና ከዛ ትምህርት መማር እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ይነግረኝ ነበር፡፡ ከእርሻ ቦታ ታፍኖ ወደ ጦር ካምፕ የተወሰደው አብዱልከሪም እናቱን ከተለያቸው ስምንት ዓመታት እንደሆኑ እየገለጸ በሕይወት መኖራቸውን እንኳን እንደማያውቅና ሲፈታ ግን እንደሚያገኛቸው ተስፋ አለው፡፡ ተወዳጁ ጓደኛዬ አብዱልከሪም ከታሰረ ሁለተኛ ዓመቱ ሲሆን፤ ወደ በርሃማው ‘የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት’ ከሔደ ደግሞ አንደኛ ዓመቱ፡፡
No comments:
Post a Comment