Monday, January 21, 2013

አንድ እሁድን በማረሚያ ቤት…



ትላንት እሁድ (ጥር 12/2005) የርዕዮት ዓለሙ ወዳጆች ልደቷን አስመልክተው እንድንጠይቃት በፌስቡክ ሁሉንም ሰው ጋብዘው ነበር፡፡ እኛም ሰብሰብ ብለን ለመሄድ ተቀጣጠርን፤ ሆኖም የእሷ ልደት ላይ ከመገኘታችን በፊት ውብሸት ታዬን ለመጠየቅ ወስነን ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ሳሪስ ተሰባሰብን፡፡ ውብሸት የታሰረው ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ነው፡፡ ቂሊንጦ የሚገኘው አቃቂ ድልድይ አካባቢ ከሚገኘው የጥሩነሽ ሆስፒታል፣ በፒስታ አጭር የታክሲ/ባጃጅ/ጋሪ መንገድ ከተጓዙ በኋላ ነው፡፡

ቂሊንጦ ከቃሊቲ ማረሚያ ቀለል ያለ መንፈስ አለው፡፡ እርግጥ ነው ቀለል የማለቱ ነገር የሚጀምረው መግቢያው ላይ ካለው የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አቀባበል ነው፡፡ ከዚህ በፊት ቃሊቲ ስንመላለስ ባላየነው መልኩ የታራሚዎቹን ጠያቂዎች በአገልግሎቶቻቸው ላይ አወያይተዋል፡፡ አወያዩ ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረው ውይይት ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በወር አንዴም ቢሆን እንደሚቀጥል በመናገር ጀምሮ ጎብኚዎች እየገጠሟቸው ያሉ ችግሮች ካሉ ጠየቀ፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሰዎች እጃቸውን እያወጡ ከማመስገናቸው በቀር የጎላ ይሄ ነው የሚባል ችግር እንዳልገጠማቸው ተናገሩ፤ ይህንንም ከገባን በኋላ ውብሸት ሁሉም ነገር ጥሩ እንደሆነ አረጋግጦልናል፡፡ ይህ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አሠራር ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ርዕዮትስ ስንጠይቅ ከሚገጥመን የፖሊሶች ማመነጫጨቅ፣ ላለማስገባት ሰበብ መፈለግ እና ከመሳሰሉት የሚያበሳጩ እና ተስፋ የሚያቆርጡ ተግባራት ጋር ሲተያይ ፍፁም ተቃራኒ ነው፡፡ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ልምድን ቢወስድ መልካም ነው፡፡

ከውብሸት ጋር የነበረን ቆይታ በሰዓት የተገደበ አልነበረም፤ (ይህ ቃሊቲ ቅዳሜ እና እሁድ ርዕዮትን ለመጠየቅ ስንገባ ከተሰጠን 30 ደቂቃ አንጻር ሲታይ ዓለም ነበር፡፡) ውብሸት በመልካም ጥንካሬ ውስጥ ነው፡፡ ንግግሩ ትህትና የተሞላበት ነበር፡፡ ከገባ ጀምሮ እስካሁን ስላለው ብዙ ጉዳዮች አጫወተን፡፡ ማረሚያ ቤቱ ውስጥ ካሉት ሰዎች ውስጥ በግምት 30 በመቶ የሚሆኑት በፖለቲካ ሰበብ እንደታሰሩ እና ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ከኦነግጋ ንክኪ አላችሁ በሚል እንደተፈረደባቸው አጫውቶናል፡፡ አንዳንዶቹ እስረኞች በጣም አፍላ ወጣቶች ከመሆናቸው የተነሳ ቢያጠፉ እንኳን መክሮ ከመልቀቅ በላይ እርምጃ እንደማይገባቸው አጫወተን፡፡ ውብሸት በአሁኑ ጊዜ ጠዋት ጠዋት በማረሚያ ቤት ውስጥ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምር ሲሆን በተጨማሪም የአረብኛ ቋንቋ ስልጠናም ለታራሚዎቹ በመስጠት ጊዜውን በአግባቡ እንደሚያሳልፍም ነግሮናል፡፡

ውብሸትን በአገር አሸባሪነት በሕግ ከመፈረጁ በተቃራኒው የዋህ እና ቅን ልብ ያለው መሆኑን ሲሰጠን ከነበሩ ማብራሪያዎቹ ለመረዳት አልከበደንም፡፡ በግቢው ውስጥ ላይብረሪ እንዳለ ስንጠይቀው የሰጠን ምላሽ ያልጠበቅነው ስለነበረ አስገርሞናል፡፡ ላይብረሪ እንዳለ ነገር ግን በቂ መጽሐፍት እንደሌሉት እና ይህን ችግር ለመቅረፍ ከዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) ጋር ተጻጽፌ የተወሰነ መጻሕፍት በእርዳታ ላስመጣ የሚል ሐሳብ አቅርቦላቸው እንደነበረ ነገረን፡፡

ሌላው ከጓደኞቹ ወይም ከቤተሰቦቹ የሚገቡለትን መጽሐፍት በተመለከተ የሚመጣለት መጽሐፍ ሁሉ እንደማይገባለት፤ የተመረጡ መጽሐፍቶች ብቻ እንደሚደርሰው ነግሮናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹‹የሎጥ ሽሽት›› የሚል ልብወለድ መጥቶለት እሱጋ ሳይደርስ መመለሱን አጨዋውቶናል፡፡ ይህ ችግር ርዕዮት ጋርም ያለ ችግር ነው፡፡ መጽሐፍ ለሷ እንዲሰጥ የሚመለከተው ክፍል ገብቶ ይዘቱ ተመርምሮ ነው እንዲገባላት የሚደረገው፡፡ ይህም በጣም ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅ እና በአብዛኛውም መጽሐፍቹ እንደማይደርሷት በአንድ ወቅት ነግራናለች፡፡   

ውብሸት ከፍርድ ሒደቱ ጋር በተያያዘ የቀረበበትን ውንጀላ ሲያወራልን በምስክርነት የቀረቡትን የስልክ ንግግሮቹን ሁሉ እራሱ ያደረጋቸው ቢሆንም አተረጓጎማቸው ግን እንዳስወነጀለው ነግሮናል፡፡ ለምሳሌ እርሱ ሚዜ ለመሆን በስልክ ስለሱፍ እና ሸሚዝ ያወራቸው ንግግሮች ተቀርፀው የኮድ ንግግር ናቸው ተብለው ለምስክርነት እንደቀረቡበትም ፊቱ ላይ በግልጽ በሚነበብ ይቅርታ አጫውቶናል፡፡ በሌላ በኩል በእሱ መዝገብ ከገቡ አንዳንድ ታራሚዎች ጋር ሆነው ያስገቡት የይቅርታ ደብዳቤ ስዊዲኖቹ ጋዜጠኞች ከማስገባታቸው አንድ ወር ቀደም ብለው ያስገቡ ቢሆንም፣ ስዊዲኖቹ ከተፈቱ ከአምስት ወር በኋላም እነውብሸት አለመፈታታቸው ‹‹ሁለት ዓይነት አሠራር አለ እንዴ?›› የሚያስብል ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ከውብሸት መልስ ወደቃሊቲ አመራን፣ አንድ ታክሲ ስላላገኘን ተከፋፍለን ነበር የተጓዝነው፡፡ ከፊሎቻችን አብዛኛዎቹ የታራሚ ጎብኚዎች ከሚመጡበት በተቃራኒው መንገድ (ነገር ግን ወደተመሳሳይ በር) በመምጣታችን በሩ ጋር ከደረስን በኋላ በሌላ በኩል ዞረን እንድንመጣ ከጠባቂዎቹ አንዱ ነገረን፡፡ እንደተነገረን ለማድረግ ቢያንስ ከ15 ደቂቃ በላይ ዙሪያ ጥምጥም ለመጓዝ ተገደድን፡፡ ዞረን ስንመጣ ገና ወደዋናው በር ለመድረስ በግምት ከመቶ ሜትር በላይ ሲቀረን መታወቂያ እያሳያን ወደበሩ እንቀርባለን፣ በሩጋርም መታወቂያ እናሳይ እና እንገባለን፣ ከገባንም በኋላ ሌሎቹ ጎብኚዎች እስኪወጡ ጠብቀን በፖለቲካ ነክ ጉዳይ የታሰሩ ሰዎች በሚጠየቁበት ሰዓት ወደውስጥ ለመዝለቅ ጓዛችንን (ስልክ፣ ቁልፍ፣ ፍላሽዲስክ.. የመሳሰሉትን) መታወቂያ አሳይተን ወደውስጥ እንዘልቃለን፤ (ይህ የዘወትር የጉብኝቱ ቅደም ተከተል ነው፡፡)

ቃሊቲ ጊቢ ውስጥ ስንገባ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን፣ ዶ/ር ያዕቆብን ጨምሮ የርዕዮት እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም እና ጓደኞቿን ጨምሮ ሌሎችም በርካቶች ቀድመውን ደርሰው ነበር፡፡ ገና ሰዓቱ እስከሚደርስ ቁጭ ባልንበት ስሜታችን መጋጋል ጀመረ፡፡ ሰዓቱ ደርሶ መግባት ስንጀምር ወደእነርዕዮት ዞን ከመድረሳችን በፊት የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በመባል የሚታወቁት እስረኞች ወጥተው በዘመዶቻቸው ሲጎበኙ አየን፡፡ (በነገራችን ላይ እነዚህን መጎብኘት የሚችለው በቤተሰብ ሊስት ውስጥ ያሉ ውስን ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡) ከዚያም ‹‹እንዴት ናችሁ፣ በርቱ፣ አይዟችሁ›› እያልን ስናልፍ ሲያከላክሉ ከነበሩት የጥበቃ ኃላፊዎች አንዱ አብሮን ርዕዮትን ሊጠይቅ የመጣውን ወዳጃችንን ነጥሎ ያዘው፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊትም ሌላው ወዳጃችን እንዲሁ እነርሱን በማበረታቱ ርዕዮትን የመጠየቅ መብቱን ተገፍፎ ግብግብ ውስጥ ገብቶ ስለነበር፡፡ ታሪክ ራሱን እየደገመ እንደሆነ ገብቶን አንዳንዶቻችን ዝም አልን፡፡ ሙስሊሞቹን እስረኞች ከሚጠይቃቸው ውጪ ሌሎችን ለመጠየቅ መጥቶ ‹‹ማበረታቻ›› አስተያየት ማስተላለፍ ጠባቂዎቹን ያናድዳቸዋል፣ ሆኖም ምክንያታቸው ምን እንደሆነ መረዳት አልቻልንም፡፡ ከብዙ ልምምጥ በኋላ ወዳጃችን ተለቆ ተቀላቀለን፡፡

ወደእነ ርዕዮት መጠየቂያ ቦታ ቀርበን ስናስጠራት ርዕዮት ቀይ በቀይ ለብሳ ከተመለመደው እና ብርታቷን ከሚመሰክረው ፈገግታዋ ጋር ብቅ አለች፡፡ ከመሃከላችን ዶ/ር ያዕቆብ ‹‹ሃፒ በርዝዴይ ቱ..ዩ…›› በሚል ሞቅ ያለ (ከዚህ በፊት ቃሊቲ ውስጥ መደመጡን እንጠራጠራለን) ዜማ የጀመሩትን እኛም ተቀብለነው በሞቀ ዜማ ተቀበልናት፡፡ የዚያን ሰዓት ርዕዮትን ሆኖ ለሚያስበው ሰው ስሜት የሚያሞቅ ከባቤ እንደተፈጠረ አይጠራጠርም፡፡

ቃሊቲ ያለአመሏ ዘና አለች፡፡ ርዕዮት ኬክ እንድትቆርስ ስትጋበዝ ‹‹ፕሮ በኔ ስም ይቁረስልኝ›› ብትልም ሁለት ኬክ በመዘጋጀቱ ፕሮፌሰሩ አንዱን ሌላኛውን ራሷ ቆርሰው ሁላችንም ተቃመስን፡፡ በመስተንግዶው ለወትሮው ታራሚዎቹ እና ጎብኚዎቹ የሚያወሩትን በንቃት የሚከታተሉት ሴት ፖሊሶችም ሳይቀሩ መሳተፋቸው አስደናቂ ነበር፡፡

ርዕዮት ከታጠረው ሽቦ ወዲያ ሆና ወዲያ ወዲህ እያለች የተሰጠችንን አጭር ደቂቃ ለሁላችንም ለማብቃቃት የራሷን ጥረት አደረገች፡፡ ሆኖም ከአበዛዛችን የተነሳ ሁላችንንም ማዳረስ ከባድ ነበር፡፡ ሆኖም ልደቷ፣ ምናልባትም ቤቷ ብትሆን ኖሮ ሊደምቅ ከሚችለው በላይ ደምቆ ታየ፡፡ እርሷም ‹‹ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ፣ አከብራችኋለሁ፡፡ በነበረኝ አቋም እንደምፀናም አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ ጋሽ መስፍንም አንተ በመከርከኝና በአስተማርከኝ መንገድ ተጉዤ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ አመሰግንሃለሁ፡፡›› የሚል አጭር ንግግር አድርጋለች፡፡

ከርዕዮት ጋር (በዚህኛው የሴቶች ዞን) ከታሰሩት መካከል የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤትም ይገኙበታል፡፡ ከርሳቸው በተጨማሪ ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ የታሰሩት ወ/ሮ እማዋይሽና ከርዕዮት ጋር በተያያዘ ክስ የታሰረችው ሒሩትም አብረው ልደቷን አክብረዋል፡፡

ልደቱ በጣም ደማቅ ቢሆንም ከዚያ መውጣት የማችሉ ሰዎች፣ መውጣት የማይችሉት ደግሞ ጥፋት መሆኑን ባላወቁት ሥራ (ባላመኑት ወንጀል መሆኑ) ግን አጥንት የሚሰብር እውነታ ነው፡፡ ሰዓታችን ገደቡ አልቆ ስንወጣ ሙስሊሞቹ ታራሚዎች ዘመዶቻቸውን ተሰናብተው እስኪገቡ ድረስ ለጥቂት ደቂቃዎች ባለንበት እንድንቆም ታገድን፡፡ ብናልፍ የምናደርገው ነገር እነርሱን በእጅ ውልብልቢያ መሰነባበት እና ‹‹አይዟችሁ›› የሚል ማበረታቻ ቃል መጠቀም ቢሆንም የማረሚያ ቤቱን ጠባቂዎች ይህ አላስደሰታቸውም፡፡

ከእገታችን ተለቀን ስንወጣ ከግቢ ውጭ ብቻ የሚፈቀደውን ፎቶ መነሳት ጀመርን፡፡ አንዳንዶቹ ሲሄዱ ጥቂቶቻችን ወደኋላ በመቅረታችን ግን ያልጠበቅነው መዘዝ ተከተለን፡፡ ማረሚያ ቤቱ ጋር ፎቶ መነሳት እንደማይቻል ተነገረን፡፡ ምንም እንኳን እንደዚያ ዓይነት ነገር የሚከለክል ማስታወቂያ ባይኖርም እነርሱ ካሉ/አሉ በመሆኑ ብንለማመጥም አልሆነም፡፡ እንዲያውም የካሜራዋን ባለቤት ከነካሜራው ይዟት ከኛ ነጥሎ ወሰዳት፡፡ ጓደኛችን ‹‹ከቀረሁ ለቤተሰቦቼ ንገሩልኝ›› ብላ በቀልድ ሄደች፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ተመልሳ ስትመጣ ካሜራዋ ውስጥ የነበሩትን ፎቶዎች አስጠፍታ (‹ዲሊት› አስደርጋ) ነበር፡፡

በዚህ መልኩ የዕለቱ በሥራዎቻቸው የምንወዳቸውን ጋዜጠኛ/ታራሚዎች በመጎብኘታችን እራሳችንን በመሸለም ከስዓቱን በመዝናናት አሳለፈን፡፡ እነር ርዕዮትም ቀሪውን ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በመመልከትና ከሌሎች ታራሚዎች ጋር በማውራት ያሳልፉታል፡፡ በዚሁ ይህንን ጽሑፍ ከመደምደማችን በፊት ቀጣዩን የነርዕዮትን ልደት ከአጥር ውጪ የምናከብርበት ቀን እንዲቀርብ መልካም ምኞታችንን እናስተላልፋለን፡፡

No comments:

Post a Comment