Saturday, January 5, 2013

ተቃዋሚን በአንድ የመፈረጅ ጣጣ




መቼም ተቃዋሚ ስል የትኛው ዓይነቱን ተቃውሞ ለማለት እንደፈለኩ ሳይገባችሁ የቀረ አይመስለኝም፡፡ በሃገራችን በአሁኑ ሰዓት የኢሕአዴግን አገዛዝ ወይም መንግሥትን የሚቃወሙትን ማለቴ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ እና በተቋም መልክ ያልተደራጁትን ተቃዋሚዎች ትተን (እነርሱ ቢበዙም) ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያገኙ ፓርቲዎችን ብቻ ብንቆጥር 79 ናቸው፡፡ (ምንጭ፤ የምርጫ ቦርድ ድረገጽ)

በተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዛት ደረጃ የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ተቋም ቢኖር ኖሮ በዚህ እንኳን ከመጨረሻ ሳይሆን ከመጀመሪያ አንደኛ እንደምንሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በወቅቱ ያላቸውን የሥራ ብቃት እና ቆራጥነት ማነስ ትተን፤ በቁጥር መብዛታቸው ብቻ በራሱ የፖለቲካ አካሄዳችን ብዙ እንደሚቀረው እና የአመለካከት ችግር እንዳለ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ እንጂ በሰላም ሃገር ለአንዲቷ ሃገር ይሄ ሁሉ ፓርቲ እኔ ነኝ ብቸኛው አማራጭ በሚል የተለየዩ አካሄዶችን እያሳየ ልባችን ባልከፋፈለው ነበር፡፡

የተቃዋሚዎቹ ብዛት ከላይ እንደገለፅኩት ሆኖ ሳለ፤ በኢህአዴግም በተቃዋሚዎችም ዘንድ ተቃዋሚዎችን እንደ አንድ የመቁጠር/የመፈረጅ ችግር በስፋት የሚስተዋል ነገር ነው፡፡

ከኢሕአዴግ ጎራ

የኢሕአዴግ ፓርቲ፣ በፓርቲው ስር የሚገኙ ተቋማት፣ የፓርቲው አድናቂ፣ አፍቃሪ እና ተቆርቋሪ የሆኑ ከዚህ ምድብ ይካተታሉ፡፡ በዚህ ምድብ ያሉ ስለተቃዋሚዎች ሲናገሩ ስትሰሙ ወይም የጻፉትን ስታነቡ በአብዛኛው አስተያየታቸውን የሚሰጡት ሁሉንም እንደ አንድ በመቁጠር መሆኑን መታዘባችሁ ግድ ነው፡፡ እንግዲህ ያሳያችሁ 80 የሚጠጉ ተቃዋሚ ፓርቲ መኖራቸው እየታወቀ፤ ሁሉም ደግሞ የየራሳቸው ልዩነት እና አቋም እንዳላቸው እየታወቀ፤ ለምን ሁሉንም ጨፍልቀው በአንድነት፣ አንድ ዓይነት ስድብ እንደሚሳደቡ (መቼም ‹‹ምስጋና›› አንጠብቅባቸውም) ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቹ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ኢህአዴግን መቃወማቸው እና ተቃዋሚነታቸው ብቻ ነው እንጂ የሚቃወሙበት መስመር፣ ምክንያት፣ የያዙት አጀንዳ፣ ዓላማቸውና እና የሚከተሉት አሰራር ፍፁም የተለያየ ነው፡፡

እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ በዚህ ምድብ ያሉት ግን አንደኛው ተቃዋሚ ያለውን ሐሳብ ‹‹ተቃዋሚዎች እንዲህ አሉ፣ ሊያደርጉ ነው፣ ናቸው›› በሚል የሁሉም እንደሆነ በማስመሰል ተቃውሞን በሙሉ በአንድ በመፈረጅ አስቸጋሪ መልክ አስይዘውታል፡፡

እንግዲህ አስቡት፤ ለምሳሌ እኔ በግሌ /እንደ አንዲት ነጠላ ግለሰብ/ ኢሕአዴግን ተቃውሜ ያነሳሁትን ሐሳብ፤ ‹ተቃዋሚዎች እንዲህ አሉ› ወይም ‹ይላሉ› ተብሎ የኔ የግሌ ብቻ የሆነው ሐሳብ የሁሉም ነው ሲባል፤ ወይንም ደግሞ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ተቃውሞ ያነሳውን ሐሳብ፤ የተቀሩት ተቃዋሚዎች እንዳሉት ተደርጎ ሲወሰድ እና የተቃዋሚዎች የጋራ ሐሳብ እንደሆነ ሲቀቆጠር፡፡

በተጨማሪም እነዚህ ምድቦች  የሚቃወምን ግለሰብ ከተቃዋሚ ፓርቲ ጋር የማስተሳሰር ክኅሎትም አላቸው፡፡ አንድ ግለሰብ ከተቃወም በቅድሚያ በአእምሯቸው የሚመጣው ከጀርባው የትኛው ፓርቲ እንዳለ ነው እንጂ፤ ግለሰብ እራሱን ችሎ መቃወም እንደሚችል አያስቡም ወይም ማሰብ የሚፈልጉም አይመስለኝም፡፡

ከተቃዋሚ ጎራ

በዚህ ምድብ ኢሕአዴግን በተለያየ ደረጃ የሚቃወሙ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎች እና የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው የሚቃወሙትን ይመለከታል፡፡ በዚህ ምድብ የሚገኙት ከላይ እንደተነጋገርነው ብዛታቸውም የትዬለሌ ነው ልዩነትም አላቸው፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው› በሚለው ብሒል መሠረት የተቃኘ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሲብራራ፡ እከሌ የተባለ ግለሰብ ወይም ሚዲያ ወይም ፓርቲ የተቃወመበትን ሐሳብ ሌሎችም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ተቃዋሚ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎች ወይም ፓርቲዎች እንዲቀበሉት/እንዲደግፉት ይጠበቃል ማለት ነው፡፡ ካልሆነ የደጋፊ ብዛት ባለው ተቃዋሚ፤ ከተቃዋሚ ሰፈር የማግለል እና ስም የማጥፋት/ስም የመስጠት ዘመቻ ይካሄዳል፡፡ ገና ለገና በተቃዋሚ ጎራ ስላሉ በሁሉም ጉዳይ መስማማት እና ስምምነትንም መግለፅ ግዴታ መሆን የለበትም፡፡ አንደኛው ተቃዋሚ የሌላውን ሐሳብ ሁሉ (ኢሕአዴግን ስለተቃወመ ብቻ) መቀበል ከቻለማ መከፋፈልን እና ተለያይቶ መሥራትን ምን አመጣው? ለምንስ ያ ሁሉ ፓርቲ ተመሠረተ?

በሁለቱም ጎራ በተደጋጋሚ ተቃዋሚን በአንድ በመፈረጅ የሚሠሩትን ስህተቶች ለማስወገድ፤  በኢሕአዴግ ጎራ ያሉት፣ በተቃወሚው በኩል ያለውን ልዩነት ከግምት ውስጥ ያስገባ  እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን መቃወም ብቻ አንድ እንደማያደርግ በመገንዘብ ለልዩነቶቻቸው ዋጋ በመስጠት እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አካሄድ በመከተል፤ በሁለቱም ምድብ የሚገኙት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
----
የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment