ሃይማኖት ከጊዜ ወደጊዜ ፖለቲካዊ አቅሙን
እያጣ የሚሄድ እና በገለልተኛ አስተሳሰብ የሚተካ እንደሆነ ፖለቲከኞች ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም እውነታው ተቃራኒ መሆኑን
‹ሃይማኖቶች በየጊዜው ያንሰራራሉ› (“Religious resurgence is a cyclical phenomenon”) በማለት
እንደዶናልድ ስሚዝ ያሉ የፖለቲካ እና ሃይማኖትን ግንኙነት በጥልቀት ያጠኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ ከአየናቸው የአረብ አብዮቶች እንኳን
መረዳት እንደምንችለው የቱኒዚያው ኤናህዳ (Ennahda) እና የግብፁ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲዎች በምርጫ ማሸነፋቸው
ምናልባትም እምነት ላይ መሠረታቸውን ያደረጉ የፖለቲካ አጀንዳዎች ወደፊት ተመልሰው ይመጡ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ጆሮ እንዲሰጠው
አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ሃይማኖታዊ በዓላት ከመቼውም ጊዜ በላይ በደማቅ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተከበሩ መምጣታቸው፣
የዶግማ ጦርነቶች በቪዲዮ ካሴቶች መበራከታቸው እና ሌሎችም ምልክቶች የሃይማኖትን ቦታ መልሶ ወደፖለቲካው መድረክ እንደማይመጣ
እርግጠኛ ሆኖ መናገርን እያከበደው ይመስላል፡፡
ምንም እንኳን ሴኩላሪዝም (ከሃይማኖት ነጻ
የሆነ የፖለቲካ ዐውድ መፍጠር) ሙሉ ለሙሉ እውነት ሊሆን የማይችል እንደሆነ ቢታመንም ያደጉ አገራት ከታዳጊዎቹ ይልቅ የሃይማኖትን
ተጽዕኖ ከመንግሥት ጫና ላይ በማላቀቁ ረገድ የተሻለ እየተሳካላቸው ነው፡፡
በድህነት ደረጃቸው ሦስተኛው ዓለም በሚባሉት
እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት የሃይማኖቶች ሚና በፖለቲካው ዕጣ ፈንታ እስከመፍረድ ሊደርስ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ኢኮኖሚያቸው
ዝቅተኛ የሆኑ እና ነጻነታቸውም ውሱን የሆኑ ሰዎች ተስፋ የሚጥሉት ከመንግሥታዊ ሥርዐቱ ይልቅ ‹‹በፈጣሪያቸው›› ላይ መሆኑ
ያፈጠጠ እውነታ ነው፡፡
Religion and Politics in
Arab Transitions በሚል ርዕስ በባራሕ ሚካኤል FRIDE ለተሰኘ አንድ የአውሮፓ የማሰቢያ ቋት (Think Tank)
የተሠራ ጥናት እንደሚተነትነው ‹የአንድ አገር ማኅበረሰብ ሃይማኖተኝነት በአገሪቱ የሥልጣን ሽግግር ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ
ያሳድራል፤ ሆኖም ሃይማኖት በሥልጣን ሽግግር ላይ የጎላ ሚና ከተጫወተ ሽግግሩ ዴሞክራሲያዊ ውጤት ላይኖረው ይችላል› ይለናል -
ጤናማ ዴሞክራሲ በአንድ ወይም ጥቂት የሃይማኖት እሳቤዎች ብቻ የተገደበ እንደማይሆን (ወይም ብዝኃነትን እንደሚያገናዝብ)
እያብራራ፡፡
የሃይማኖት ጉዳዮች ብዙውን ጊዜ የሚያያዙት ከፖለቲካዊ
ሥልጣን ጋር ነው፡፡ ብዙዎች ሃይማኖትን ሥልጣን ለማግኛ (ለጥሩም ይሁን ለክፉ) ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ
በላቲን አሜሪካ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከአምባገነናዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ለመሸጋገር በተደረገው ጥረት ውስጥ የጎላ ሚና
ተጫውታለች፡፡ ቤተክርስቲያኗ በአርጀንቲና የNational Reorganisation Process in Argentinaን ደግፋለች፤
በቺሊ ለPinochet አገዛዝ ተቃውሞዋን ገልፃ በኤል ሳቫዶር ለሚካሄደው ሕዝባዊው የለውጥ እንቅስቃሴ ድጋፍ አሳይታለች፡፡
በቱርክ የጉለን (Gülen) እንቅስቃሴ የተመራው በሱፊ እስላም ወንድማማቾች ነው፡፡ ይህ እና መሰል እንቅስቃሴዎች
የሚያስረግጡልን ፖለቲካዊ ፍላጎት ላላቸው አማኞች ሃይማኖት ጥሩ አብዮታዊ መሣሪያ መሆኑን ነው፡፡
በሌላ በኩል በዓለማችን በዝነኝነታቸው
የሚታወሱት የፈረንሳይ፣ የሜክሲኮ፣ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የኩባ አብዮቶች በሙሉ እና የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የተነሳሱት
በገለልተኛ (ሴኩላር) ርዕዮተ-ዓለሞች ነው፡፡ ሆኖም ተሳክቷል (አንጻራዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር አምጥቷል) የሚባለው የአሜሪካ
አብዮት ደግሞ በተቃራኒው በክርስትና እምነት እሴቶች የተነቃቃ ነው በማለት ሃይማኖት መር የሥርዐት ለውጥ የተሻለ አማራጭነቱን
የሚሰብኩም አይታጡም፡፡ ነገር ግን መጠየቅ የሚገባን ‹ሃይማኖት ለአብዮት (ለሥርዐት ለውጥ) እንቅፋት የሚሆንበትስ ዕድል የለም
ወይ!?› ብለን ነው፡፡
ሃይማኖት ለአብዮት
እንቅፋት ይሆናል?
የተለያዩ ሃይማኖቶች ስለሥልጣን እና ሹመት የተለያየ አቋም አላቸው፡፡ በጥቅሉ ስናስበው ሃይማኖት ዓለምአቀፋዊ ሲሆን
ፖለቲካዊ ሥልጣን ግን ሰዎች በፈጠሩት የጂኦግራፊ ካርታ ላይ የተመሠረተ ሰው ሰራሽ ሥልጣን ቢሆንም ቅዱስ መጽሐፎች ግን
የራሳቸውን አቋም ማንፀባረቃቸው አልቀረም፡፡ ለምሳሌ የክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ወደሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 13፥1-2 እንዲህ
ይላል፡-
ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምንት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ
በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ፣ በባለሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር
ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ፡፡
በእስልምና ሃይማኖት ቅዱስ መጽሐፍ - ቁርኣን ላይም ተቀራራቢ ነገር እናገኛለን፡-
እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፤ መልክተኛውንና ከናንተም የሥልጣን
ባለቤቶችን ታዘዙ፤ በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና
ወደ መልክተኛው መልሱት፤ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡ (ቅዱስ ቁርኣን ምዕራፍ 4፤ አል-ኒሳእ፡፡ ክፍል 5፡፡ ቁጥር
59)
ከላይ እንዳየነው ክርስትና መንግሥት ላይ ማመፅን በፍፁም ቃል ይቃወማል፤ በሌላ በኩል በክርስትና ኢየሱስ ‹‹የቄሳርን
ለቄሳር›› ብሏል ብለው የመንግሥት እና ሃይማኖትን መነጣጠል የሚነግር ነው የሚሉም አይታጡም፡፡ ወደእስልምናም ስንመለከት
ከባለሥልጣናት ጋር ካልተግባባችሁ ወደአላህና መልክተኛው መልሱት እንጂ ምድራዊ መፍትሄ ፈልጉለት አይልም፡፡ እርግጥ ነው
በእስልምናውም ባለሥልጣን የሚለው ቃል የሚወክለው የቤተ ሃይማኖቱን አባቶች እንጂ የመንግሥት ሹማምንትን አይደለም ብለው
የሚከራከሩ አሉ፡፡ በጥቅሉ ግን፣ እኔ በምረዳው እና ከቀደሙት አስተምህሮቶችም ማየት እንደሚቻለው… ሃይማኖተኞች ለመታዘዝ
ቅድሚያ እንዲሰጥ እንደሚወተውቱ ነው፡፡ ችግሩ በጥቅሉ ‹‹መታዘዝ›› የሚለው ቃል ሕዝብን ለሚበድል ባለሥልጣናትም ቢሆን
ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል የተለየ ሐሳብ አላስቀመጡልንም፡፡
እነዚህን የሃይማኖት ኃይለ ቃሎች የሚረ’ዱ መንግሥታትም ሃይማኖትን መጠቀሚያ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ የቀዳማዊ
ኃይለሥላሴ ሕገ መንግሥት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያልሆነች ሚስት ያገባ
ሰው መንገስ እንደማይችል ቃል በቃል ይጠቅስ ነበር፡፡ ንግሥናውም ከእግዚአብሔር የተገኘ እንደሆነ ከላይ የጠቆምነው የመጽሐፍ
ቅዱስ ቃል በሚመስል ሐረግ ያስረዳል፡፡
መንግሥታት ሃይማኖትን በተለያዩ መንገዶች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በርካታ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ Jeff Haynes
የተባሉ ተመራማሪ Religion in Third World Politics በሚለው ጥናታቸው ሃይማኖት በሦስተኛው ዓለም መንግሥታት
እንዴት መጠቀሚያ ሊሆን እንደቻለ ሲጠቁሙ ሥርዐት ለማስቀጠያነት (Regime continuity)፣ ሕዝብ ትዕዛዝ እንዲቀበል
ለማሳመኛነት (Public order maintenance)፣ ሥልጣንን ተቋማዊነት ለማላበስ (Institutionalization of
authority) እና ለዜግነት እንደቅድመሁኔታ በማስቀመጥም (Promotion of citizenship) ጭምር መሆኑን
ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚህ ዘመን አምባገነን መንግሥታት ሃይማኖት እንደመጠቀሚያ የሚሆነው በከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ ነው፡፡
አንደኛው ሃይማኖት ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው እና ለሁለቱም ግን እንደዋስትና መንግሥትን በማስቀመጥ እንዳይተባበሩ እና
መንግሥት ላይ እንዳይነሱ ማድረግ እየተለመደ የመጣ ዘዴ ሆኗል፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ታዲያ፡-
ሃይማኖተኞች በመንግሥት
ላይ ያብያሉ?
ከሃይማኖቶች ዶግማ በመነሳት ሃይማኖተኞች
የሚያብዩት ሃይማኖታቸው የተጠቃ ሲመስላቸው እንጂ እነርሱ እንደሕዝብ የተጨቆኑ ሲመስላቸው አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ
የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሃይማኖትን ከለላ ለማድረግ የሞከሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በአብዮት መውረድ እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡
በንጉሡ ሥርዐት ላይ ለተነሳው አብዮት አንዱ መነሾ የሃይማኖቶች መገለል ነው፡፡ ለምሳሌ “በኢቫንጀሊካል ክርስቲያኖች አመለካከት
በንጉሡ ዘመን [ቤተክርስትየናቸው] ሲደርስባት የነበረው እንግልት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እጅ አለበት ብለው
ማሰባቸው ጽናታቸውን እንዳበረታው እና ሥርዐቱን ለመጣል በሚደረገው ትግል ውስጥም አማራጭ ፍለጋ ተሳትፎ እንዳደረጉ” Revolution
and Religion in Ethiopia በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ Øyvind M. Eide የተባሉ ተመራማሪ አትተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የዶናልድ ስሚዝ
Religion, Politics, and Social Change in the Third World ቅኝ ተገዢዎች ሃይማኖትን በመጠቀም
አብየው (አብዮት አቀጣጥለው) ነጻ የወጡባቸውን አራት መንገዶች ይዘረዝራሉ፡-
1. ሃይማኖት በራሱ የአመራር ዕድል/ተቀባይነት ያጎናፅፋል (ማሕተመ ጋንዲ ስማቸው
በሒንዱ እምነት ‹‹ታላቅ ነፍስ›› የሚልና ከቤተ እምነቱ የተገኘ በመሆኑ በአብዛኛው አማኝ ተቀባይነት አስገኝቶላቸዋል፤)
2. ሃይማኖት ለውጥ ፈላጊዎች እርስ በእርስ የሚተሳሰሩበት ምክንያት በመስጠት ለታጋዮቹ
(ወይም ለውጥ ጠያቂዎቹ) የስሜት ጥንካሬን ያጎናጽፋል፣
3. ሃይማኖት ለትግሉ ወይም ተቃውሞው ጥንካሬ የሚሆን መሠረት ይጥላል፣ (በእስልምና
ቃፊሮች (ያልታመኑ ገዢዎች) ላይ የሚደረግ ጅሃድ (ቅዱስ ጦርነት) ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡)
4. ሃይማኖት የመቃወሚያ መንገድ ይሰጣል (ለምሳሌ ጋንዲ ‹satyagraha› የተሰኘውን
የአመጽ አልባ ሰላማዊ ትግል ፅንሰ ሐሳብ ያገኙት ከሒንዱ እምነታቸው ነበር፡፡)
ከዚህ በተጨማሪም አብዛኛዎቹ ሃይማኖቶች ነጻነት
እና እከሉልነትን እንደመርሕ የሚመለከቱ መሆናቸው በፖለቲካዊ ሥርዐቶች ላይ በቀጥታ ባያምፁም እንኳን የሥርዐቱን ድርጊቶች
በማውገዝ ሃይማኖታዊ አብዮተኞች ከቤተ እምነታቸው ስለሚታገሉለት ለውጥ የማጠናከሪያ ሐሳብ ማግኘት ይችላሉ፡፡ በዚህ መንገድ ነው
የላቲን አሜሪካ አብዮት በክርስትና እና የግብፁ (የ1952/እ.ኤ.አ.) አብዮት በሙስሊም ወንድማማቾች ድጋፍ እና ሃይማኖታዊ
እሳቤ ተነሳስተው ለለውጥ የበቁት፡፡
እነዚህ የታሪክ ዳራዎች ላይ በመመርኮዝ አሁን
የሚታየው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን እና ‹‹የመጅሊሳቸው›› ውዝግብን ተከትሎ ጥያቄ ጥያቄን እየወለደ ቤተ እምነታዊው ጥያቄ ወደፖለቲካዊ እና ሥርዐታዊ
ለውጥ ጥያቄ ያድግ ይሆን፣ ካደገስ ያዋጣ ይሆን የሚሉት ጥያቄዎች ኢትዮጵያውያንን እያወያዩ ነው፡፡
የሙስሊሞች ጥያቄ
ወደአብዮት ያመራ ይሆን?
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በታኅሳስ ወር/2004፣ በአወሊያ ትምህርት ቤት የጀመሩት ‹‹አል አሕባሽ›› የተሰኘ አስተምህሮት
እየተጫነብን ነው ሮሮ - ቀጥሎም ‹መምህራኖቻችን አይባረሩ› እንቅስቃሴ… መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በመምረጥ፣ መጅሊሱ ይቀየርና
ሕገ መንግሥቱ ይከበር እስከማለት ዘልቋል፡፡ ይሄው ጥያቄ የተመለሰበት መንገድ የመጅሊሱ አባላት በቀበሌ እንዲመረጡ ማድረግና
ያንን የተቃወሙትን የኮሚቴ አባላት እና ሌሎችንም ማሰር እና በሽብርተኝነት መክሰስ ሲሆን… ይህ የመንግሥት እርምጃ ሙስሊሙን
ማኅበረሰብ በማስቆጣት ተቃውሞዋቸውን በየሣምንቱ አርብ ከጸሎት በኋላ እየገለጹ ዓመት እንዲደፍኑ አድርጓቸዋል፡፡
በተቃራኒው በየከተማው እነዚህን ብሶተኞች የሚቃወሙ ሙስሊም ሰልፈኞችን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደጋግሞ አሳየ፡፡ ብዙዎች
ሰልፈኞቹን መንግሥት ያስተባበራቸው እንደሆኑ መገመት አልቸገራቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰልፈኞች በሰልፉ ብዙም አልዘለቁበትም፤
በሌላ በኩል ከታሪክ እንደምንረዳው በደርግ ዘመን ‹‹የሃይማኖት መሪዎች የኢምፔሪያሊስቶችን አብዮት የሚያደናቅፍ ሴራ አወገዙ››
የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው እንደነበሩ ሁሉ አሁንም ‹‹የእንትን መስኪድ ኢማሞች ‹አንዳንድ› ድብቅ ሴራ አጀንዳቸውን በሙስሊሙ
ዘንድ ለማራመድ የሚፈልጉ … አወገዙ፡፡›› የሚለውን ዜና ከፕሮፓጋንዳ ለይቶ ማይት ስለማይቻል ነው፡፡
መንግሥት የሙስሊሞቹን ጥያቄ በአጭሩ መልስ የማይሰጠው እንደሚናገረው ‹‹አክራሪነትን›› ለመከላከል ብቻ ነው ማለት
ያስቸግራል፡፡ ይልቁንም የመንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንም የውስጥ ለውስጥ አጀንዳ
በመሆኑ (‹‹የቀድሞውን ጳጳስ የሕወሓት አባል/ደጋፊ ናቸው›› እስከማለት ድረስ) የሙስሊሞቹን ጥያቄ መመለስ ኦርቶዶክስ እምነት
ተከታዮችንና ምናልባትም ሌሎችንም ፊት እንደመስጠት ይሆንብኛል ብሎ ሳይጠረጥር አይቀርም፡፡
የሆነ ሆኖ ምንም እንኳን መንግሥት የሃይማኖተኞችን ጥያቄዎች በጉልበት ቢደፈጥጥም (‹‹ምርጫውን በቀበሌ በማካሄድ››)
ወይም የየሳምንቱን ጥያቄ እንዳልሰማ በማለፍ ‹‹ሰልችቷቸው እንዲተዉት›› ለማድረግ ቢሞክርም፤ እስካሁን ከተለመከትነው መገመት
እንደምንችለው… እነዚህ ሰዎች ስትራቴጂያቸውን እየቀያየሩ ያላቸውን ሁሉ አማራጭ ወደመጠቀም አያመሩም ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡
በቅርቡ እንኳን ያሳዩት የቢጫ ካርድ ተቃውሞ ከእግርኳስ ጨዋታ ሕግ የተወረሰ ሲሆን እንደማስጠንቀቂያ ታይቷል፡፡ ቀጣዩ
ቀይ (የማሰናበቻ) ካርድ እንደሚሆን ቢገመትም መቼ እና እንዴት ለሚለው ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ሙስሊሞቹ
የቀይ ካርድ እርምጃቸውን ከጀመሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከመስኪድና ከጸሎት ስብሰባ ውጪ ሊጠሩ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህ
ዓይነቱ እርምጃ (ከመንግሥት ተገማች ምላሽ ጋር ተደማምሮ) አገሪቱን ወደአብዮት ሊመራት ይችላል ብሎ መጠርጠር ከባድ
አይመስለኝም፡፡
ነገር ግን እንደምናስበው ይህ ዓይነቱ አብዮት በሒደቱም ሆነ በውጤቱ ቀላል አይሆንም፡፡ የሙስሊሞቹ አደባባይ መውጣት
ጥያቄያቸውን ከሃይማኖታዊው ይልቅ ፖለቲካዊው ትርጉሙ ስለሚያመዝን (የመንግሥት አይቀሬ ሥልጣን ፈልገው ነው ፕሮፓጋንዳ ታክሎበት)
ሙስሊም ላልሆነው የኅብረተሰብ አካል የጥርጣሬ መንፈስ ሊፈጥር እና አንዱ በሌላው ላይ የመቃወም አቋም ሊያስይዝና ለፖለቲካውም
ለማኅበረሰቡም የማይበጅ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡
እንደመደምደሚያ
ሃይማኖቶች ለአብዮት የሚያበረክቱት እና ማበርከት የሚችሉት ሚና አሌ የሚባል ባይሆንም፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ
ያገናዘበ አብዮታዊ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ከታሰበ የአገሪቱን ብዝኃ ሃይማኖትነት ማገናዘብ የሚችል ገለልተኛ/ሴኩላር ለውጥ ቢመጣ
እመርጣለሁ፡፡ የሃይማኖተኞች ወይም ሃይማኖትን ግብ ያደረጉ አብዮተኞች ሚናም ሃይማታዊ/አምልኮአዊ ጣልቃ ገብነት ከመቃወም ወይም
የማምለክ/አለማምለክ ነጻነትን (ማለትም በጠቅላላው ሥርዐት ውስጥ የእምነት ነጻነት ሥርዐቱን ለይቶ /ምን ያህል ነጥሎ ማየት
ይቻላል የሚለውን ለውይይት በመተው/ ለማስተካከል) ከመሻት በላይ የተሻገረ መሆን የለበትም፡፡ በጥቅሉ ግን ሃይማኖተኞች
እንደዜግነታቸው የሥርዐት ለውጥን መሻት ብቻ ሳይሆን የለውጡ ዋነኛ ተዋናይ የመሆን መብቱም ግዴታውም አለባቸው፡፡
------
ማስታወሻ፡-
ይህ ጽሑፍ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል የሚቀርቡት ተከታታይ ጽሑፎች አካል ነው፤
-----
ተጓዳኝ ጽሑፎች፤
-----
የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡
No comments:
Post a Comment