Wednesday, January 16, 2013

ፎቶግራፍ የሌለው የጉዞ ማስታወሻ




የገና ማግስት በቅጡ ሳልዘጋጅ ከቤቴ በመውጣቴ ካሜራ እንደሚያስፈልገኝ የተረዳሁት 200 መቶ ኪሎ ሜትር ከተጓዝኩ በኋላ ነበር - አዋሽን ስንሻገር፡፡ ስለዚህ በዚህ የጉዞ ማስታወሻ ላይ ምስል ከሳች ትረካ እንጂ ምስል የለም፡፡ እየተጓዝኩ ያለሁት ወደአፋር ነው፤ ሰመራ፡፡ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ከአዲስ አበባ ተነስተን፣ የመኪና ጉዞ ምቾትን ትርጉም በሚያሰጠው ላንድክሩዘር ጉዞ ጀመርን፡፡ አዳማ ላይ ቁርጥ እና ጥብስ ለመብላት ሲቆሙ እኔም በሳቅ እና በፈገግታ አጀብኳቸው፡፡

ከአዲስ አበባ በወጣሁ ቁጥር የሚገጥመኝ ችግር ምርጫዬ የሆነ ምግብ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ጥብስ ወይም ቁርጥ መብላት እንደሚያምረው ቁርጤን ስላወቅኩ… እኔም ሽሮ፣ ፓስታ፣ አትክልት የመሳሰሉትን ለብቻዬ እፈልጋለሁ፡፡ አብረውኝ ከሚጓዙት አንዱ ‹‹ቬጅቴርያን ነህ ወይ?›› አለኝ፤ ‹‹አይደለሁም›› አልኩት እንጂ ምንም የምለይበት የለኝም፡፡ እርግጥ ነው ዱለት፣ ክትፎ፣ አሩስቶ ምናምን ከተገኘ አልምርም፡፡ የዛን ዕለት ጠዋት ግን ለነርሱ ከቀረበው ጥብስ ላይ ጥቂት ዛላዎች እያነሳሁ ነካከስኩ፡፡

አዋሽ አርባ የተባለችው ከተማ ከመግባታችን በፊት የአዋሽ ወንዝን ማቋረጥ ነበረብን፡፡ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ድልድዩ አግድርም የተዘረጋ ታንኳ መስሏል፡፡ ስንመለስ ታንኳው (ድልድዩ) በከፊል ሰምጧል፡፡ ስንሄድ ከአዋሽ አርባ ከተማ ወደግራ ታጥፈን ወደሰመራ ከማምራታችን በፊት የድንገቴ ዕቅድ ለውጥ አደረግን፤ ሐረርን አይቻት የማላውቀው እኔ በመሆኔ ለምን በጨረፍታ አናሳየውም ተባባሉ፤ እርግጥ ነው እኔን ሰበብ አርገውኝ ነው እንጂ እነርሱም መሄድ የፈለጉበት ምክንያት አላቸው፡፡

ሐረር - የታጠረች ከተማ?

በካፊያ ታጅበን ወደ12 ሰዓት ገደማ ሐረር ገባን፡፡ የ1000 ዓመቷን እመቤት ሐረር አንድ ቀን ለጉብኝት እንደምሄድባት አውቅ ነበር፤ ግን እንዲህ በድንገቴ ይሆናል ብዬ ስላላሰብኩ ድጋሚ መምጣት እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ በወፍ በረር ጎበኘኋት፡፡ መቼም ጉብኝት ያውም በማታ፣ ያውም  (በእግር መንሸራሸሩ ባይቀና እንኳ) የሕዝብ ትራንስፖርት ሳይጠቀሙ የጉብኝትን ጣዕም ያሳጣል - ስለዚህ አየኋት ለማለት በማያስችል ሁኔታ ቃኘኋት፡፡ ምናልባት በዚያ ፍጥነት ካየሁት የማስታውሰው የአዲስ አበባውን አጤ ምኒልክ ሐውልት መንትያ የሚመስለውን የራስ መኮንን ሐውልት እና ጀጎልን ነው፡፡ ያቺ ጨረፍታ ግን ሐረር - የታጠረች ከተማ ሲባል የነበረኝን ግንዛቤ ለመቀየር በቂ ነበረች፡፡ በዘመኗ ከተማ የነበረችው አሁን ከአንድ የሀብታም ግቢ የምትሰፋ አይደለችም፡፡


ዞሮ፣ ዞሮ በሩ (የሸዋ በር) ውበት እና ሞገሱ እንደጠበቅኩት ነው፡፡ ጊቢው ውስጥ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እና የከተማዋ ሙዚዬም አጥር ላጥር ተዋደው ይታያሉ፡፡ ጅብ የመመገብ ትርኢት የሚታይበትን ቦታም በጣት ጥቆማ አመላክተው በጊዜ አሳብበው አስጎብኚዎቼ ሳያሳዩኝ መልሰውኛል፤ ለነገሩ ከጅብ ጋር ቁራጭ ስጋ ከመናጠቅ ተረፍኩ፡፡

ተመልሰን እራት ቁርጣቸውን ልንበላ ወደአንድ ሆቴል ሄድን፡፡ ሆቴሉ ሰፊ ጊቢ ሲሆን አንድ ትልቅ ክፍል ውስጥ በማይክሮፎን የተደራጀ ቢንጎ ጫወታ ያካሂዳል፡፡ ቢንጎ አጨዋወቱ እንዴት እንደሆነ የማውቀው ጉዳይ የለም፤ ነገር ግን ያ ሁሉ ሰው በዚያ ዓይነት ተመስጦ ሲጫወት ለማየት ጥቂት ተመሰጥኩ፡፡ ራት ተበላ፣ ታደረ፤ ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ የመልስ ጉዞ መገንጠያውን 300 ኪሎ ሜት አልፈነው ወደመጣነው ሰመራ ከተማ፡፡ 

ጉዞ ወደ ሰመራ

የአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ በረሃ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ለጥ እና ቀጥ ባለው መንገዱ ዳር እና ዳር አንዳንዴም ሰማይ እስከሚደፋበት ባለው ርቀት ሙሉ አገሩ ከሰው ቁመት በማይበልጥ፣ ባብዛኛው አረንጓዴ በሆነ ችፍርግ ቁጥቋጦ እና ጫማ ሊውጥ በሚችል ደርቆ (ይመስላል) ቢጫ በሆነ ሳር የተሸፈነ ነው፡፡ አረንጓዴው ቁጥቀጦ እስከገዋኔ ይቀጥላል፡፡ ከገዋኔ በኋላ ግን ቁጥቋጦው ቢኖርም አረንጓዴ ሳይሆን ቅጠሉ የረገፈ እና ግንዱ/ጭራሮውም የደረቀ ይመስላል፡፡

መንገዱ እጅግ በሚያሰለች ሁኔታ ቀጥ ያለ እና ረዥም በመሆኑ አያልቅም፡፡ መደመጨረሻ አካባቢ ላይ እንኳን እኛ ተጓዦቹ መንገዱ ራሱ የሰለቸው ይመስለኛል፡፡ የመቀሌ ጉዞ ማስታወሻዬ ላይ አገሪቱ በተራራ ከመዋጧ የተነሳ ወይ አትታረስ፣ ወይ ከተማ አትሆን ብዬ መማረሬ ትዝ አለኝ፡፡ እዚህ ደግሞ ያልታረሰ እና ምናልባትም ቢታረስበትም በሙቀቱ ምክንያት ፍሬ የማይሰጥ፣ ለከተማ ኑሮም የማይመች ለጥ ያለ ወፍ ዘራሽ የቁጥቋጦዎች ማሳ ይመስላል፡፡ እዚያም ሆነ እዚህ ጥቅም ላይ ያልዋሉ (ሊውሉ የሚችሉ የማይመስሉ) ምድሮችን ነው ያየሁት፤ ባገሬ ገረመኝ፡፡

የመኪናችን ማቀዝቀዣ ፀሐይ መውጣቷን እንጂ ከነልጆቿ መውጣቷን አስረስቶኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሾፌራችን ለሽንት ብሎ መኪናዋን ሲያቆማት በሩን ብርግድ አድርጌ ብቅ ስል እሳት ውስጥ ዘልዬ ብዬ የገባሁ ነው የመሰለኝ፡፡ ነፋስ ቢጤ አለ፤ ነፋሱ ግን የእሳት (የፀሐይ አይመስለኝም) ወላፈን አዝሏል፡፡ መሬቱ ክው ብሎ ደርቆ ውኃ የሚባል አይቶ እንደማያውቅ ያሳብቃል፡፡ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም በሚል ተፈጥሮ የፈቀደችልኝን ያህል ከጓደኞቼ ጎን ተሰልፌ መሬቱን አጠጣሁት፤ ትንሽ እፎይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ተንደርድሬ ወደመኪናው ውስጥ በመግባት ያንን የሚፋጅ ሙቀት መልሼ አመለጥኩት፡፡

በነገራችን ላይ በርቀት እና አልፎ፣ አልፎም በቅርብ ርቀት የሚታዩ ቀጫጭን ቶርኔዶዎች (የሚሾር ነፋስ) አሉ፡፡ እነዚህ ቶርኔዶዎች የመሬቱን አቧራ እየጠቀለሉ ወደላይ ሲያጎኑት በርቀት ተመልክቼ መጀመሪያ ላይ ደንግጬ ነበር፡፡ ይሄ እሳት የሆነ አገር እሳት መትፋት ቢጀምርስ - ‹‹እሳተ ገሞራ ነው እንዴ?›› አልኳቸው፤ ‹‹አይ አቧራ ነው›› ብለው ገላገሉኝ፡፡ ስንመለስ ደግሞ ስንሄድ ያላየናቸውን ዝንጀሮዎች፣ ሚዳቆዎች እና ሰስ አየን፡፡ ለካስ እነርሱም ያንን በርሃ ይዳፈሩታል ያሰኛል፡፡

ሌላው አስገራሚ ገጠመኝ ሰመራ እስከምንደርስ ድረስ የተንቀሳቃሽ ስልካችን ከኔትወርክ ያለመውጣቱ ምስጢር ነው፡፡ ምንም የቴሌ ሞገድ መቀበያ በሌለበት ጭው ባለ በረሃ ውስጥ የአካባቢው ለጥታ ይሁን ሌላ አልገባኝም፤ ኔትዎርክ ግን በሽ ነው፡፡

የውኃ ምጽዋት

በጉዟችን መሐል አንዳንድ የአገሬው ነዋሪዎች ባዶ የውኃ ላስቲክ ከረጢት እየወዘወዙ ያሳዩናል (በነገራችን ላይ እነዚህ ነዋሪዎች ጠቅልለው የሚይዟትን የኬሻ ክብ ጎጇቸውን ተክለው እና በፍየሎቻቸው/ግመሎቻቸው ተከበው አልፎ አልፎ ከመታየታቸው በቀር በአራት መቶ ኪሎ ሜትር ውስጥ የረባ የገጠርም ሆነ የከተማ መንደር የለም ማለት ይቻላል፡፡) እናም እነዚህ የውኃ ላስቲክ የሚወዘውዙት ለምን እንደሆነ ስጠይቅ ውኃ እየለመኑ እንደሆነ ተነገረኝ፡፡ አንዳንዶቹ በጎናቸው በጨርቅ የተጠቀለለች ኮዳ ይዘዋል፤ በኮዳዋ የግመል ወተት እንደሚይዙባት ገመትኩ፡፡ አካባቢው ምንም ውኃ ስለሌለው ወተታቸውን ሲጨርሱ በየመንገዱ ዳር ውኃ እየለመኑ ከመጠጣት በቀር ምንም አማራጭ የላቸውም፡፡ የሚያሳዝነው ግን አብዛኛው መኪና (በመንገዱ የሚበዙት ወደወደብ የሚሄዱና የሚመጡ የጭነት መኪኖች ናቸው) ምንም ሳይሰጣቸው ያልፋል፡፡ የሚያልፈውን መኪና ሁሉ ይለምናሉ፤ እንደእኛ ዓይነቱን (የጭነት ያልሆነ) መኪና ደግሞ አብልጠው ይለምኑታል፡፡ ያለንን ውኃ ከሰጠን በኋላ ግን ቀሪዎቹን ከንፈር በመምጠት በዓይናችን ከመሸኘት በላይ አማራጭ አልነበረንም፡፡ ይህንን ቢመለከቱ ኖሮ፣ ፀጋዬ ገብረመድኅን ‹‹ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?›› የሚለውን ግጥማቸውን ‹‹ውኃ ጥም ስንት ቀን ይፈጃል?›› ብለው እንደገና ይጽፉት ነበር፡፡

በየመንገዱ ዳር እና ዳር ላይ ብዙ የተበጣጠሱ የመኪና ጎማዎች አየሁ፡፡ ግራ ገብቶ ብጠይቅ የፈነዱ የመኪና ጎማዎች እንደሆኑ ተነገረኝ፡፡ ጎማዎቹ የአስፋልቱ እሳት ስለሚለበልባቸው እና ከላይም ጭነቱ ስለሚከብዳቸው ድንገት ይፈነዳሉ፡፡ ለዛም ይመስላል፤ አንዳንድ የአፋር ጊቢ አጥሮች ግማሽ ጎናቸው በተቀበረ ጎማዎች የታጠሩት፡፡ እኔ የመኪናዎች ጎማ መፈንዳት ታሪክን ከሰማሁ በኋላ መረጋጋት አቃተኝ፡፡ ምናልባት የኛ መኪና ጎማ ቢፈነዳስ? (መኪናችን እየበረረች የነበረው በ120 ኪሜ. በሰዓት ፍጥነት ነበር፡፡) ምናልባት አንዱ ኮንቴነር የጫነ ተሳቢ መኪና ጎማ ፈንድቶ ላያችን ላይ ቢወጣስ?... ሁለቱም አልተከሰተም፡፡

ገዋኔ ከተማን ካለፍን በኋላ አሰልቺው ቀጥ ያለ ጉዞ በመጠነኛ አቀበት ላይ የዚግዛግ ጉዞ ጀመረ፡፡ አካባቢው ሆነ ተብሎ የተኮለኮሉ በሚመስሉ ትላልቅ ተፈረካካሽ ዓለቶች (sedimentary rocks) አስገራሚ ውበት የተሰደረ ነው፡፡ ከወዲያ ማዶ የተንጣለለ ውኃ (ሐይቅ መሳይ ታይቶኝ) ተገርሜ ጠየቅኩ፡፡ ለካስ አሸዋ ውስጥ ሰምጦ የሚቀረው አዋሽ ወንዝ ተቀልቦ ግድብ እየተሰራበት ኖሯል?! ግድቡ የሚሰራው ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ እንደሆነም ተነገረኝ፡፡ ያ ግድብ ያቋተው ውኃ ሊዋኙበት ቢሞክሩ እንደፍልውኃ እንደሚፋጅ መገመቴ አልቀረም፡፡ በነገራችን ላይ የአዋሽ ወንዝም ቢሆን አሸዋ ውስጥ ገብቶ ከስሞ የሚቀረው እዚያ ውኃ የጠማው መሬት ውስጥ መሆኑን ስረዳ ከባድ ሳይንስ እንዳልሆነም ጭምር ነው የተረዳሁት፡፡ በዚያ ዓይነት ሙቀት እንኳን መሬቱ እኔም ራሴ አዋሽን ጠጥቶ ለመጨረስ የሚያስችል አቅም የሚያጥረኝ አልመሰለኝም፡፡

ሎጊያ እና ሰመራ

ሎጊያ ከሰመራ 7 ኪሎሜትር ወዲህ የምትገኝ ትንሽዬ ነገር ግን ከሰመራ የተሻለ ሰው፣ ሰው የምትሸት ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ ከአንዲት ባለአንዲት ፎቅ ትንሽዬ ቤት በቀር ጎልቶ የሚታይ እንኳን ቤት የላትም ነገር ግን ሰመራ የመንግሥት ሥራ የሚሠሩት ሳይቀሩ የሚኖሩት ሎጊያ ውስጥ ነው፡፡ በሎጊያ መንገድ ዳርና ዳር ላይ የተደረደሩት መኪናዎች ብዛት ከከተማዋ መኖሪያዎች ብዛት ይበልጣል፡፡ በሰመራ ግን ጥቂት መኪኖች በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶቹ ውስጥ ከመኖራቸው በቀር ጭርታ ያጠቃታል፡፡ በሰመራ ብዙ የመንግሥት ሕንፃዎች እና ጥቂት የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ከመኖራቸው በቀር የሥራ ብቻ ከተማ በመሆን ተወስናለች፡፡

እኛም ሎጊያ የደረስነው በስምነት ሰዓት በመሆኑ ለምሳ አረፍን፡፡ ምግብ ልንበላበት የገባንበት ቤት ግድግዳው ወደጣሪያ አካባቢ ክፍተት አለው፤ በዚያ ላይ ከቆርቆሮው ጣሪያ ስር ሳጣራ ተነጥፏል፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖም ግን ሙቀቱን መቀነስ ስለማይቻለው በግምት 7ሜትር በ10 ሜትር በሚሆነው በዚያ ክፍል ውስጥ ብቻ አምስት ‹ቬንትሌተሮች› ተሰቅለዋል፡፡ ቀና ብዬ ሳየው ቤቷ ድንገት ተነስታ እንደሄሊኮፕተር የምትበር፣ የምትበር መሰለኝ፡፡

የደረስንበት ወቅት አካባቢው ቀዝቀዝ የሚልበት እንደሆነ ቢነግሩንም የውጪውም ሆነ የቤቱ ውስጥ የእሳት ወላፈን ያህል የሚፋጅ ነው፡፡ አንድ የአገሬው ሰው ‹‹የአፋርን ሙቀት ቤት ውስጥ በመግባት ማምለጥ አይቻልም›› ብሎ እንቅጩን ነገረን፡፡ ለአዳር የተከራየነው አልቤርጎ ውስጥ በአጎበር ቦታ ቬንትሌተር ተገጥሞለታል፡፡ ቬንትሌተሩ ሰው ውስጥ ባለበት ሰዓት ሁሉ መሾር አለበት… እንዲያው ለብ ለማድረግ ያህል፡፡ የተከራየነው ክፍል ጣሪያ (ሰገነት) ላይ የክፍት አየር አልጋዎች ተደርደረዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ (በተለይ ግንቦት፣ ሰኔ እና ሐምሌ ላይ) ቤት ውስጥ ማደር እንደማይቻል እና አልቤርጎ የሚከራይ ሰው ሰገነት ላይ የተነጠፉ አልጋዎች ላይ ከላይ እንደሚጋደም ተነገረን፡፡

ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ቀዝቀዛ ሻወሬን ወስጄ ሳበቃ ያለወትሮዬ በቲሸርት ዘንጬ ለእራት ወጣሁ፡፡ የምሽቱ ሙቀት የኔን የቀጭኑን ብላቴና ወዝ ለማፍለቅለቅ ሰከንድ አልፈጀበትም፡፡

‹‹ብር ያለው በርሃ ነው››

ለአገሩ የሚስማማ ሸበጥ ቢጤ መግዛት ፈልጌ ነበርና ሳጠያይቅ ዋጋቸው ውድ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ ‹‹እንዴ ምንድን ነው ነገሩ? ይሄንን ጫማ እኮ ሐረር 200 ብር ተብዬ እምቢ ብያለሁ›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ታዲያ ሐረር እዚህ የለ!›› አለኝ አንዱ፤ አብራው የነበረችው ቆንጅዬ ኮረዳ ደግሞ ‹‹ሐረር ምን ገንዘብ አለ፤ ገንዘብ እኮ ያለው በርሃ ነው›› ብላ ውድ መሆኑ ብር ያለበት አገር ከመሆኑጋ እንደሚያያዝ አረዳችኝ፡፡ ልጅቷ እውነቷን ነበር፤ ኑሮ በአፋር ውድ ነው፡፡ እዚህ ግባ የማይባል ቤት ውስጥ ጥብስ ከ50 ብር በታች፣ ሽሮ ደግሞ ከ30 ብር በታች አታገኙም፡፡ ሰመራ ውስጥ ጥሩ የሚባለው ነገር ግን በአዲስ አበባ ዞር ተብሎ ላይታይ የሚችለው የኤርታሌ ሆቴል አልጋ ድፍን አንድ ሺሕ ብር ያስከፍላችኋል፡፡

የሄድንበትን ጉዳይ ጨርሰን ስንመለስ ያንን አሰልቺ ጉዞ የምናለዝብበት ቴክኒክ እያሰብን ነበር፡፡ ጉዟችንን የጀመርነው ዘጠኝ ሰዓት በመሆኑ በርከት ያለ እሽግ ውኃ ገዝተን መንገድ ላይ ለሚጠይቁን ሰዎችም ለማቀበል ይዘናል፡፡ ለነገሮችም፣ ለእርስ በእርሳችንም ስለተለማመድን ጨዋታችን ደመቅ ብሎ ነበር፡፡ በመንገዳችን መሐል የፌዴራል ፖሊሶች በግምት በየሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ ጥንድ፣ ጥንድ እየሆኑ ቆመው አየን፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ አካባቢ የሾፌራችንን የትውልድ ሐረግ መጥቀስ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ሾፌራችን (ስሙ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል የተሸሸገ ቢሆንም) የቅድም አያቱ ስም ግን ይገለጻል - አቶ አስረስ ይባላሉ፡፡ አቶ አስረስ የመለስ ዜናዊ አስረስ አያት ናቸው፡፡ ሾፌራችን የ25 ዓመት የሹፍርና ልምድ አለው፤ ከመለስ ጋርም ከዝምድናው በተጨማሪ ጥቂት አብረው ተምረዋል፡፡ ሹፌሩ ለመለስ ያለው አድናቆት ከዝምድና ብቻ የመነጨ አይመስልም፡፡ በንግግሩ ቁጥብ ቢሆንም መለስ የአገሪቱን የ40 ዓመት ዕቅድ እንዳቀደላት እና ከዚህ በኋላ መሥራት እንጂ ምንልሥራ ብሎ መጨነቅ እንደማያስፈልግም ነግሮኛል፡፡

በመንገዳችን ላይ የገጠሙንን ፌዴራል ፖሊሶቹን እያየን ሳለን ሁለት ፌዴራል ፖለሲሶች እንድናሳፍራቸው ለመኑን፡፡ ከዚያ በፊት ለአሳፍሩኝ ልመና ብዙም የማይግደረደረው ሾፌራችን በፍጥነት መኪናውን አቆመ እና ተጫኑ:: ዕድሜያቸው ከ25 የማይበልጥ ወንድና ሴት ወታደሮች ናቸው፡፡ እሱ የመጣው ከተንቤን እሷ ደግሞ ከማይጨው እንደመጡ ነገሩን፡፡ ደሞዛቸው ከአንድ ሺሕ ብር እንደማይበልጥ ነገር ግን ምግብ ካምፕ ውስጥ እንደሚዘጋጅላቸው ነገሩን፡፡ እዚያ የመጡት ኢሳዎች እና አፋሮች ከመንገድ ወዲህ ያለው ጎሳ ፍየል፣ ከመንገድ ወዲያ ያለውን ጎሳ ሳር በመጓጣ (ወይም ከዚያ ባልበለጠ ምክንያት) ለሊት ሲታኮሱ ስለሚያድሩ እነርሱን ለመጠበቅ ነው አሉ፡፡ ነገር ግን የዛን ዕለት ወታደሮቹ የበዙት በሌላ ምክንያት መሆኑን ነገሩን፡፡ 

አንድ ሾፌር ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ላይ ሲነዳ በማይታወቁ ሰዎች ታግቶ ነበር፡፡ (ለወትሮው መንገዱ የ24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል፡፡) ወታደሮቹ እንደነገሩን አጋቾቹ ለሚስቱ ደውለው እንዲያናግራት አድርገዋል፡፡ እዚህ ነን እያሉ… ያሉበት ቦታ ሲኬድ አይገኙም፡፡

‹‹ገንዘብ ፈልገው ነው?›› አልናቸው፤

‹‹ኧረ የምን ገንዘብ፤ ነገር ፍለጋ ነው እንጂ›› አለ፡፡ ‹

‹‹ማንን ነው ነገር የሚፈልጉት?›› አልናቸው፡፡

‹‹እኛን ነዋ…!›› አለ፡፡

‹‹ለምን?››

‹‹አሸባሪዎች ናቸው›› አለ፡፡ ሁላችንም ደነገጥን፡፡

እኔ በበኩሌ መንገድ ላይ መታገት አለ የሚባለው ሐሳብ ሲከሰትብኝ ፌዴራል ፖሊሶች አጠገቤ ሲኖሩ ተሰምቶኝ የማያውቅ የደኅንነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ ምነው ባልወረዱ የሚል ስሜትም አደረብኝ፡፡ ሹፌራችን ጥያቄውን ቀጠለ

‹‹ባለሥልጣን ነው

‹‹አይደለም፤››

‹‹ትግሬ ነው?››

‹‹አይደለም፡፡››

‹‹ታዲያ ምን አድርገን ብለው ነው?›› አለን፡፡ ሹፌራችን ትግሬ ነው ወይ ያለበትን ምክንያት አብራራልን፤ አሸባሪዎቹ ትግሬ ሲባል ኢሕአዴግ ይመስላቸዋል በማለት፡፡ ሹፌሩ ቀልድ አዋቂ ነው፤ አሁን ‹‹መለስ ስለሞተ›› ማገት ያለባቸው ‹‹የደቡብ ሰው ነው›› በማለት ሁላችንንም ፈገግ አሰኘን፡፡

እንዲህ እንዲህ እያልን፣ አዋሽ አርባ ከመሸ ደረስን፣ እዚያው አደርን፣ በማግስቱ እኩለ ቀን ላይ አዲስአበባ ደርሰን ተበተንን፡፡ በመጨረሻ ግን ያየሁት ነገር የሰጠኝ ግንዛቤ አፋር ክልል፣ በታዳጊ አገር ውስጥ ያለች ታዳጊ ክልል መሆኗን ነው - ለነገሩ መንግሥትም ታዳጊ ካላቸው ሦስት ክልሎች አንዷ አድርጓት የለ!?

No comments:

Post a Comment