Sunday, January 13, 2013

ትምህርት… ወዴት ዘመም ዘመም?


ዐፄው ስለትምህርት

በሀገራችን ዘመናዊ ትምርት የተጀመረው በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ቢሆንም ከመስፋፋቱ ጋር ስማቸው በታሪክ መዛግብት በጉልህ የሚነሳው ዐፄ ኃይለሥላሴ ናቸው፡፡ ከሸዋ ፖለቲካ የስልጣን ሽኩቻ በአሸናፊነት ብቅ ያሉት መልከ ቀናው ዐፄ ኃይለሥላሴ ኋላ ላይ ራሳቸው ከሸለሙዋቸው ተማሪዎች ጋር ስልጣናቸውን ያሳጣቸው ግጭት ውስጥ ቢገቡም እስከዛው ድረስ በየጠቅላይ ግዛቱ ያሉትን ልበ ብርሀን ተማሪዎች ሰብስቦ ከማስተማር ቤተመንግሥታቸውን እስከመልቀቅ ደርሰዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ለራሳቸውን የትምህርት ሚኒስትርነት ኃላፊነት በመስጠት ለትምህርት ሟች መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ ጥሩ ውጤት አስመዝጋቢ ተማሪዎችን ከሀገር ዳርቻ ሰብስቦ ማስተማር፤ በአካል ተገኝቶ መሸለምና በቀለም የዘለቁትን ደግሞ ባሕር ማዶ ሄደው እንዲማሩ ማድረጋቸው ለትምህርት ጥራት የሰጡትን ትኩረት ያሳያል፡፡

በልላ በኩል ዐፄው ለመምህርነት የሚታጩ ተማሪዎች ላቅ ያለ ውጤት እንዲኖራቸው ስለሚጠበቅ "በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት"  በተለየ ጥንቃቄ ይሰለጥኑ እንደነበር ጉዳዩን የሚያውቁ የሞያ ባልደረቦቼ አጫውተውኛል፡፡ የእነዚህ የዚያ የትምህርት ስርዓት ውጤት የሆኑት ሰዎች ልዩነት በቀን ተቀን የሥራ እንቅስቃሴያቸው ይታያል፡፡ በዕውቀታቸው ምጡቅ፤ በሥነ ምግባራቸው የተከበሩ እና ለሥራቸው ጠንቃቃ ባለሞያዎች ናቸው፡፡ አሁንስ አስተማሪ ለመሆን የሚሰለጥኑ ዕጩዎች ምን ይመስላሉ? በሌላ ጽሑፍ የምመለስበት ይሆናል፡፡

የፋኖዎቹ ጥንቃቄ

“ያረጀውን ዐፄያዊ ጨቋኝ አገዛዝ በአፍጢሙ ደፍቼ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በሶሻሊዝም መዓዛ ይዤላችሁ መጣሁ” ያለው ደርግ  አገር አንድ የተማረ ሰው ለማፍራት ስንት አመት እንደሚፈጅባት ብዙም ስላልገባቸው "አንድ ጥርስ ቢኖራት በዘነዘና ተነቀሰች" እንዲሉ የነበሩትን በጣም ጥቂት ምሁራን 72 ሰዓት የጥፋት አዋጅ እንደ ገብስ እያጨደ ሬሳውን ቢከምርም የትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ጣልቃ ልግባ ግን አላለም፡፡ የኢሠፓ ካድሬዎችም ቢሆኑ የካቲት 66 ወይም ሩሲያ ሄደው ማርክሲዝምና ሌኒንዝም እንዲጠጡና የገባቸውንም ያልገባቸውንም እንዲያነበንቡ አደረገ እንጂ የሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸውን በቅጥ ዳር ያላደረሱ የመንደር አቢዮት ጠባቂዎችን ባለተደራራቢ ዲግሪ አላደረገም፡፡ እንግዲህደርግ መንግሥት ጥፋቶቹ የትዬለሌ ቢሆኑም በአፈሙዝ ወኔ የትምህርቱን ነገርም ከሆለታ ጦር ትምህርት ቤት  ላስኪደው አላለምና ይህ ያስመሰግነዋል፡፡


ትምህርት ለሁሉም” - በገፍ

ደርጎች ከካምፕ በድንገት ካገኙት ስልጣን ሲባረሩበአንድ ጠመንጃ፣ በአራት ሽጉጥ እና በአንድ ቢላዋ የጀመርነው ትግል እልፍ አድርጎን እልፎችን ነፃ ልናወጣ መጣን” ያሉት የበረሀ ኮብራዎች ግን ልክ እንደ ቤተ መንግሥቱ እና መገናኛ ብዙኃኑ ሁሉ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲንም በፍጥነት መቆጣጠር እንደነበረባቸው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስአንድ ወቅት በቁጭት እንዲህ ብለው ነበር፡፡

"አዲስ አበባ እንደገባን ቤተመንግሥቱን እና መገናኛ ብዙኃኑን ስንቆጣጠር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ረስተነው ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን ዩኒቨርሲቲው የማይዳሰስ ገዳም ነው ማለት አይደለም፡፡"

እኔ ግን አንድ ከጫካ የመጣ ቡድን እንዴት አንድ ትልቅ ዩኒቨርሲቲን ወዲያው መቆጣጠሩ አግባብ ሆኖ እንደተነገረ እስካሁን አልገባኝም፡፡

በዚህ ቁጭት ይመስላልመሪዎቻችን” 1987 . አዲሱ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲን አውጥተው ለይስሙላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ባለሞያዎች አስተያየት እንዲሰጡበት የግማሽ ቀን ስብሰባ ያዘጋጁት፡፡ ፖሊሲው ከሚያነሳቸው ጉዳዮች አንዱ የትምህርትን ተደራሽነት ማረጋገጥ ወይም ቀለል ባለ ቋንቋ የትምህርት መስፋፋት ነው፡፡ ውጤቱም የግል የትምህርት ተቋማትን በጥቂት ዓመት ውስጥ እንደ እንጉዳይ እንዲፈሉ አድርጓል፡፡ ሁለት ክፍል ቤት እና አንድ መጽሐፍ መደርደሪያ ያለው ሁሉ በኮሌጅ እየተሰየመ ማስታወቂያ ማስነገር ጀመረ፡፡ ለድፍን 15 ዓመት እና ከዚያ በላይ ሦስቱን የመ ሕጎች (መመዝገብመክፈል እና መውሰድ) መሟላታቸውን ብቻ እያረጋገጡ ማስመረቁን ተያያዙት፡፡ እንግዲህ የትምህርት ዘመም፣ ዘመም የጀመረው ይሄኔ ነው፡፡

ለዲፕሎማ መርሐ ግብር የተመዘገቡ ሰልጣኞች ዕድሜያቸውንና ገንዘቡን ሰጥተዋቸው መመረቂያ ዓመት ከደረሱ እዛው ኮሌጅ ዲግሪያቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተመረቁ ብዙኃኑ ተመራቂዎች የተመረቁበት መስክ የሚጠይቀውን ዕውቀት በተገቢ ሁኔታ ቀስሞ መውጣት ይቅርና ብዙ ዓመትና ገንዘብ አባክነው "ተምረው" የተመረቁበትን ትምህርት ክፍል (Department) ስም በቅጡ መጥራት የማይችሉ ሆነው አጋጥመውኛል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን " ሕጎች" እያሟሉ ተመርቀው በአገር ዕድገትና መሻሻል ላይ አሉታዊ ጥላቸውን የሚጥሉ "ባለሞያዎች" ቁጥራቸው የሚናቅ አይደለም፡፡

በቅርቡ በጣም ዘግይቶም ቢሆን የግል ትምህርት ተቋማት ከተያያዙት የትምህርት ማስረጃ ንግድ እንዲታቀቡ መለኛው ኢሕአዴግ በቀጥታም ሳይሆን በተዘዋዋሪ እነሱ ያስመረቋቸውን ምሩቃን በተለይ መምህራንን በመንግሥት መሥሪያ ቤት እንደማይቀጥር ግልጽ አደረገ፡፡ ምን ዋጋ አለው ጅብ ከሄደ የሆነው እርምጃ ለረዥም ዘመናት ዘመም ዘመም ሲል የቆየውን የትምህርት ጥራት ከውድቀት አላዳነውም፡፡ ችግሩን ጠቅለል አድርገን ስናየው አቶ መለስ ራሳቸው እንደመሰከሩት ማየትና መስማት የተሳነው የሀገራችን ሲቪል ሰርቪስና የተንቀራፈፈው ሥራ አፈፃፀም የውጤቱ ሕያው ምስክር ነው፡

የረፈደበት ወደ ትምህርት ጥራት ጉዞ

ኢሕአዴግ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ኃያል ክንዱን ለማሳረፍ ዳርዳር ሲል "ባለብሩህ አእምሮው" የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ "ለሳቂታው" ፓርላማችን እንዲህ ብለው ነበር፡፡

"…የግል የትምህርት ተቋማት ዲግሪና ዲፕሎማ መቸብቸቡን ተያይዘውታል፡፡ …ዲፕሎማ ደግሞ የዲግሪ መሰላል አይደለም፡፡ …ዲፕሎማ ያለው ሁሉ ዲግሪ መያዝ አለበት የሚል ሕግ የለም፡፡…"

ንግግሩ ስህተት ባይኖረውም የትምህርት ጥራት ጉዳይ ከረፈደ መነሳቱና ያውም
ለአቶ መለስ ይህን ያህል ዓመት ነገሩ ሳይከሰትላቸው ቆይቷል ብሎ ለማለት ይከብደኛል፡፡

ይህ
የረፈደበት የመንግሥት እርምጃ በትምህርት ጥራት ላይ የተቃጣውን ግዙፍ ጥፋት በምንም መለኪያ የሚመልስ አይደለም፡፡ በድንገት "ነቃሁባችሁ" ብሎ ተቋማቱን በአንድ ጀንበር ከማዳከም ወይም ከማጥፋት መጀመሪያውኑ በቂ ክትትል ማድረግ እና ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚባለው ለትምህርት ጥራት ተገቢው ትኩረት እየተሰጠ ነው ወይ የሚለውንም ጥያቄ ለመመለስ ጥቂት ትዝብቶቼን ላካፍል፡፡

ሽፋን የሸፈነው የጥራት ጉዳይ

ከትምህርት ጥራት ይልቅ ሽፋን ላይ እንደሚያተኩር በተደጋጋሚ የሚደመጠው ኢሕአዴግ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 15 በላይ ዩኒቨርሲቲወችን መገንባቱንና በርካታ "ምሁራንን" ማፍራቱን ሲገልጽ በኩራት ነው፡፡ በርግጥ ኢሕአዴግ ትምህርትን ለማዳረስ ያደረገውን ጥረትና ስኬት ሳይናገሩ ማለፍ ምስጋና ቢስ ያደርጋል፡፡ በርግጥ ጥራትና ሽፋንን አብሮ ማስኬድ ትልቅ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅና በመጠኑም ፈታኝ ቢሆንም አይቻልም ማለት ግን አይደለም፡፡

ምርጫ 97 ያስከተለውን ድንጋጤ ተከትሎ አቶ መለስ ባደረጓቸው ጉዞዎች የተለያዩ ክልልና ዞን ነዋሪዎች "ለእከሌ ጎሳ ዩኒቨርስቲ ተሠርቶ ለኛስ?" የሚለውን ጥያቄ ከባሕል ልብስ ስጦታ ጋር አብረው ያቀርቡ ነበር፡፡ ከማስፋፋቱ ዕቅድም ጋር ተያይዞ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፈቱ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹም ቆጥረው የተረከቧቸውን ተማሪዎች ብዙም ቁጥራቸው ሳይጎድል ማስመረቁን ተያያዙት፡፡

ዋናው
ጥያቄ ግን ተማሪዎቹ በተገቢው መግቢያ መስፈርት ተለክተዋል ወይ? በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ምሩቃኑ ተገቢውን ቀለምና ስነምግባር ቀስመው ይወጣሉ ወይ? በቆይታቸውስ እውን ለቀለም ትምርታቸው ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ይደረጋል ወይ? የሴት ተማሪዎች ሁኔታስ እንዴት ነዉ? የሚለው ነው፡፡
ለሁለት ዓመታት በመሰናዶ የቆዩ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ሰባት የትምህርት ዓይነቶችን መፈተን አለባቸው ይህ ማለት ደግሞ 700 የሚሰላ ዉጤት የኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ እንደዉ አማካይ የማለፊያ መስፈርቱን ብንጠቀምና (ከተፈተኑት ጥያቄ ዉሰጥ 50 እንደመልሱ ቢጠበቅ እንኳን) አንድ መካከለኛ ተማሪ (ጎበዝ አልተባለም) 350 700 የሆነ ዉጤት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ደግሞ በበፊቱ ምዘና 4 ነጥብ 2 ነጥብ ያመጣ ተማሪ ማለት ይሆናል፡፡ በአሁኑ ቅበላ በየዓመቱ ትንሽ ከፍ ወይም ዝቅ የማለት ነገር ቢኖርም 175 ካስመዘገቡት ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ይቻላል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ በጣም ልል የሆነ የመግቢያ መስፈርት በትምህርት ጥራት ላይ የሚያጠላውን መጥፎ ጥላ ማብራራት የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በርካታ የትምህርት ባለሙያዎች አንደሚስማሙበት በማንኛውም የትምህርት ደረጃ የተማሪዎች የቅበላ መስፈርት ለትምህርት ጥራት ያለው ፋይዳ የማይተካ ነው፡፡ እንግዲህ  የባለሙያዎችን ምክርና የትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችን ተሞክሮ ቸል ማለታችን የሚታየውን የትምህርት ጥራት ወደ ውድቀት ዘመም ማለት አብዝቶ ያፋጥናል ማለት ነው፡፡

ዋናው ካርዱ ነው

ከመጀመርያ በሰፊ ወንፊት ተጣርተው የገቡ የዘመናችን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቆይታቸዉ በጥናትመጨናነቅአይመቻቸዉም፡፡ ከዛ ይልቅ በአንድ የኢሕአዴግ አባል ወይም አጋር ድርጅት በአባልነት ተመዝግበው በየዩኒቨርሲቲዎቹ ቅጥር ጊቢ በሚደረጉ የድርጅት ጉባኤዎች ሳያሰልሱ በመገኘት አንዳንድልማታዊቃላትን በመሸምደድ ከቀለም ይልቅ ፖለቲካዊንቃታቸዉንያስመሰክራሉ፡፡ የወደፊት እንጀራቸውን ወፍራም አድርጎ የሚጋግርላቸው በቀለም ትምህርት ችሎታቸወ የሚያገኙት “A” ወይም “B” ሳይሆን በኪሳቸዉ የያዟት ቀይ ካርድ ነች፡፡ ከቅርብ ዓመት ወዲህ በተለይ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ከዐሥራ አንደኛና ዐሥራ ሁለትኛ ክፍል ጀምሮ (ቢቻል ደግሞ ቀድሞ) የአባልነት ካርዷን በጃቸው ካላደረጉ በቀር የታማኝነታቸው መጠን ጥርጣሬ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ተማሪዎች አጫውተውኛል፡፡

ማወቅና አለማወቅ ተደባለቁ

ይህ የተማሪዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሳይንሳዊ ግንኙነት ከሌለው የፓርቲ አባልነት ጋር ተመሳሳይ ማድረግ በማወቅና ባለማወቅ መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት አጥፍቶ ተማሪዎቹ የሚያስለቅስ ውጤት እያመጡ እንዲስቁ ሲያደርግ ተመልክቻለሁ፡፡ የዛሬ አለማወቃቸው የነገ ማንነታቸውን ካልወሰነው ምን ችግር አለው? ያለነው እኮ አላዋቂነት በላዩ ላይ ካድሬነት ከተደረበበት አዋቂዎችን ሳይቀር የሚያሸማቅቅ የክብር ካባ ተደርጎ በሚታሰብበት ግራ የገባው ከባቢ ውስጥ ነው፡፡

የነገሩ
ግራነት የሚጎላው ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ከቤተሰብ ርቆ በዋናነት ለመማርና የተሻለ ዜጋ ለመሆን የመጣ ተማሪ በውጤቱ ዝቅተኛነት ቅንጣት ሐሳብ እንዳያድርበትና ካድሬነቱን ብቻ እንዳያጓድል በግልጽም በስውርም ማበረታታትና እንደ ትክክለኛ ነገር በአደባባይ የሥራና የትምህርት ዕድል የምንሰጠው ቅድሚያ ለአባሎቻችን ነው ተብሎ ሲነገር ስንሰማ ነው፡፡ መንግሥት ያልፋል ሀገርና ትውልድ ግን ቀጣይነት ያላቸው ነገሮች ስለሆኑ ቀጣዩ ትውልድ ለውጤት ቸልተኛ ከሆነ የተለየ ፍላጎትና ዓላማ ያለው መንግሥት ቢመጣ እንኳን የተጣመመውን የትውልድ አስተሳሰብ ማቃናት እንዲህ እንደ ማበላሸቱ የሚቀል አይሆንም፡፡

የዘራነውን ስናጭድ

እንግዲህ አውቆ መገኘት ለወደፊት ስኬታማነት የተሰጠውን ቦታ ከተነጋገርን የዘመኑ ተማሪዎች የማወቅ ጉጉት ባናይባቸውና ከተማረ ሰው የሚገኙትን ትሩፋቶች (ችግር ፈቺነት፣ ሐሳብ አፍላቅነት እና አንባቢነት…) ብናጣባቸው ሊገርመን አይገባም፡፡ እንደውም የሚታየው ተቃራኒው ነው፡፡ በፊት በፊት እከሌ ሰቃይ ናት/ነው እየተባለ በአድናቆት የሚነገርለት የትምህርት ብልጫ በዲጄነትና ሲዲ በማቀያየር ጥበብ አድናቆት ተተክቷል፡፡ በሀገራችን ውስጥ በዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ ወይም በር ላይ miss it not የሚሉ በቀለም ያሸበረቁ የምሽት ጭፈራ ፕሮግራም መኖሩን የሚያበስሩ ማስታወቂያዎችን መለጠፍ ምንም ችግር የሌለው ነገር ነው፡፡

በዚህ
ፓርቲ የሚታደሙ ሴት ተማሪዎች የሴተኛ አዳሪ እህቶቻችንን "የሥራ ልብስ" ዓይነት እራፌ ጨርቅ ጣል አድርገው ታክሲ (ባጃጅ) ሲጠብቁ ማየት ሕሊና ላለው ልብ ይነካል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ስንል ዞሮ ዞሮ የሚወስደን ምንም ባይማሩም እንኳን "ያችን ነገር" ከያዙ መመረቅ ብሎም መቀጠር ካልሆነም መደራጀት ይቻላልና፡፡

ስለ ትምህርት ጥራት መዛመም ተነስቶ ሲቪል ሰርቪስን ዩኒቨርሲቲአለማንሳት "ግንጥል ጌጥ" ይሆንብኛል፡፡ የትምህርት ጥራቱን ዘመም ዘመም በፈረስ ጉልበት ወደ ውድቀት እየገፋ ያለው የኮተቤው ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በዚህ ዝነኝነቱ "የእንትን ማምረቻ" በሚል ቅጽል ስሙም ይታወሳል፡፡ የመግቢያ መስፈርቱ፣ የስልጠና ጊዜው በቅጥ የማይታወቀው ይህ ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ከማደግ አልፎ የመጨረሻውን የትምህርት ደረጃ (ዶክትሬት ዲግሪ) እያሰለጠነ ይገኛል፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ትክክለኛ ሥራው መሆን የነበረበት ሥራ ላይ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችን ጉድለታቸውን ለመሙላት አጫጭር ስልጠና መስጠት ነበር፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ዲግሪ ለመያዝ የቸኮሉ ካድሬዎች ብዙ ሳይጨነቁ ከአዋቂዎች ተርታ ይሰለፋሉ፡፡

ኧረ!... መላመላ…

አብዛኞቹ የሥነ-ትምህርት ጠበብት እንደሚስማሙበት የትምህርት ሽፋንንና ጥራትን ያለ እንከን አብሮ ማስኬድ ያስቸግራል፡፡ በመሆኑም የትምህርት ጥራትን ለመታደግ ተደራሽነቱን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መከወንን እንደ አማራጭ ይመክራሉ፡፡ እንደሚታወቀው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ማግኘት የሁሉም ሰብኣዊ ፍጡር መብት በመሆኑ በዚህ የትምህርት ደረጃ ላይ ለትምህርት ሽፋን /ተደራሽነት/ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው፡፡

ከሁሉ
አስቀድሞ ፖሊሲ የመቅረጽ ሥራ ለባለ ሞያዎቹ መተው ያለበት ሥራ መሆኑን መንግሥት ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ፖለቲከኞች ፖሊሲውን ቀርጸው ባለሞያዎች ሁሉ ነገር ካለቀ በኋላ ለይስሙላ አይተውት ነበር እንዲባል ብቻ የሚደረግ መሆን የለበትም፡፡

የሀገራችን ትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ብዙ ትችቶችን ያስተናገደ ቢሆንም መንግሥት ትችቶችን እንደ መልካም ግብኣት ተቀበቀሎ ከማስተካከል ይልቅ ትክክለኛነቱን በእሰጣ-ገባ መልክ ማስረዳት ይቀናዋል፡፡ የጥራት ችግርን ለመፍታትም ከፖሊሲ ክለሳ ብንነሳ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡

ከፖሊሲ
እርማት በመቀጠል መደረግ ይገባል የምለው ጉዳይ የትምህርት ተቋማት ከፖለቲካ ተፅኖ ማላቀቅ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች (ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ) በግልፅም ሆነ በስውር የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ገዥ አካል ፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሆን የለባቸውም፡፡

የትምህርት አመራሮችን የመሾምና
የመሻር ሥልጣኑም መሰጠት ያለበት አብረዋቸው ለሚሠሩ መምህራን መሆን ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ከላይ ካለው መንግሥታዊ አካል ይልቅ መምህራኑ ማን ከማን የተሻለ የአመራር ሰጭነት ክኅሎት እንዳለው ስለሚያውቁ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛ ቦታ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ በትክክለኛ ሰው የሚመሩ ተቋማት ደግሞ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በተጨማሪም
የተሻለ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎች ከነሱ ያነሰ ቸሎታ ባላቸው ሰዎች እንዲመሩ ማድረግ የሥራ ፍላጎታቸውን የሚቀንስ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ጥሩ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ለመቀጠር ሲያማትሩ ይታያሉ፡፡ ይሄ የባለብዙ ዕውቀትና ልምድ መምህራን ፍልስት በራሱ የዩኒቨርሲቲዎችን የትምህርት ጥራት የሚጎዳ ሆኖ ሳለ በነሱ ምትክ የሚገቡ ሰዎች የነሱን ጫማ ይሞላሉ ወይ የሚለው ሌላ ራስ ምታት ነው፡፡

ከዚህ የትምህርት አመራር ሰጭነት ጋር በተያያዘ ሌላ ዐበይት ጉዳይ የዩኒቨርሲቲዎች በቦርድ የመተዳደር ነገር ነው፡፡ በ1994 . አከባቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት / እሸቱ ወንጨቆ ካቢኔ እና በኢሕአዴግ መካከልአካዳሚክ ፍሪደምዙርያ የተነሳውን አለመግባባት ተከትሎ ኢሕአዴግ እንደ እርምት በወሰደውርምጃ ዩኒቨርሲቲዎችን ገዥው ፓርቲ በዓይነቁራኛ መቆጣጠር ብሎም መምራት ነበር፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት ዩኒቨርሲቲዎች በቦርድ እንዲተዳደሩና የቦርድ ሰብሳቢዎች ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎቹ ላይ አድራጊ ፈጣሪ እንዲሆኑ ተደርገው ተሰየሙ፡፡ የቦርድ ሰብሳቢዎች ዩኒቨርሲቲው የተከፈተበት አካባቢ ተወላጅና የኢሕአዴግ ቱባ ባለሥልጣን መሆናቸው እንደ በቂ ነገር ተደርጎ መወሰድ ደግሞ ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ርዕስ መስተዳድሮች በክልል ዋና ከተማ ላሉ ዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡ በሌሎች አነስተኛ የክልል ከተሞች ላሉ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ሌሎች የክልሉ ተወላጆች ባለሥልጣኖች ተፈልገው የፊት አውራሪነቱ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ የመምህራንን ደረጃን ጨምሮ ሌሎችን አንገብጋቢ ነገሮች የሚወስኑት እነዚህ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ የቦርድ ሰብሳቢ ባለሥልጣናቱ ትምህርት ዝግጅትና ከዩኒቨርሲቲዎች አሠራር ጋር ያላቸው ትውውቅ እና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተሰጣቸው ሥልጣን ትልቅ ልዩነት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡

ለማወቅና ለአዋቂነት እየተሰጠ ያለውን ቦታ ማስተካከል ሌላው የትምህርት ጥራትን ከውድቀት ለመታደግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ማንኛውም ለመማርም ሆነ ተምሮ ወደ ሥራ ለመግባት የተዘጋጀ ሰው ተገቢውን ዕውቀት ቀስሞ ከወጣ በኋላ ወደ ተገቢው ሥራ ሲገባ ምሁራን በተስማሙበት መስፈርት ተለክቶ የመግባት ጉዳይ ድርድር የሌለው ብቸኛ መርህ መሆን አለበት፡፡

ሀገራችን ደሀ እንደ መሆኗ እና የትምህርት መስኩ ደግሞ በተፈጥሮ ገንዘብን የሚወስድ እንጅ እንደ ሌሎች ተቋማት አትራፊ ሆኖ ገንዘብ የሚያመጣ ባለመሆኑ ለትምህርት ሥራው ግብኣት ማሟያና ተያያዥ ወጪዎች የውጭ እርዳታ ማማተሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ እርዳታ የሚሰጡ ሀገራት ደግም ገንዘባቸውን ሲያወጡ የትምህርት ፖሊሲውን አፈፃፀሙን በራሳቸው ፍላጎት እንቃኝ መፈለጋቸው አይቀሬ ነው (ሰባ ሰላሳ ኮታን ያስታውሷል)፡፡ በሀገር ተጨባጭ ሁኔታና በለጋሽ አገራት ፍላጎት መሐል ያለውን ሰፊ ልዩነት የማጣጣምን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ የሚጠይቅ አጣብቂኝም ነው፡፡ ስለዚህም በትምህርት ሚኒስተርና ሚኒስተር ዴኤታነት የሚቀመጡ ሰዎችን ከምን ብሔረሰብ ናቸው ከማለት ይልቅ ምንተመዘገበ አጥጋቢ የዲፕሎማሲ ሥራ ሰርተዋልወደፊትስ ምን ለመሥራት የሚያበቃ የተፈተሸ አቅም አላቸው መባል ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከነባራዊው ሁኔታ የምንረዳው ግን የትምህርት ሚኒስተርነት በአንድ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ የወረደ ዛር ይመስል ለአንድ ብሔር የሚሰጥ ሹመት ነው፡፡ የትምህርት ተደራሽነትን ከማረጋገጥ ተግባር ጋር በሁሉም ደረጃ ያሉ የትምህርት ማት ምን ዓይነት ስብእና ያለው ዜጋ እያፈሩ ነውየሚለው ነገር ላይም ትኩረት አድርጎ መሥራት ተገቢ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment