ለውጥን በምናብ
ይወዱታል እንጂ በተግባር አይዳፈሩትም - ሰዎች፡፡ የሥርዓት ለውጥ ሲሆን ደግሞ ፍርሐቱ ያይላል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ሲሆን
ደግሞ ከማንኛውም ሥርዓት ለውጥ በላይ ያስፈራል፡፡ የፍርሐት ፖለቲካዊ አንድምታ ከታሪክ አንጻር እየተመለከትን ስለራሳችን ለውጥ
እንድናወራ ነው ይህ ጽሑፍ የተጻፈው፡፡
የፍርሐት ዘመን (Reign
of Terror፡ 1793-1794)
የመጀመሪያው
የፈረንሳይ አብዮት መባቻ ላይ ከፍተኛ ፍርሐት ሰፍኖ ነበር፡፡ አምባገነኑ ሉዊስ 16ኛን ገርስሰው ሰብኣዊ መብት እና ሕገ-መንግስታዊ
አስተዳደርን ከአሜሪካ ለመኮረጅ የሞከሩት ፈረንሳውያን እርስ በእርሳቸው ተቀናቃኝነት ባፈሩት የለውጡ መሪዎች ጊሮንዲኖች እና ያቆቢኖች
(Girondins and the Jacobins) አንደኛው ሌላኛውን ‹‹የአብዮቱ ጠላት›› በሚል በደም የታጠበ አብዮት በማድረጋቸው
25 ሺሕ ለሚደርሱ ሰዎች እልቂት መንስኤ ሆኗል፡፡ ያንን ጊዜ የፍርሐት ዘመን (The Reign of Terror) በሚል ታሪክ ጸሐፊያን
ያስታውሱታል፡፡
እኔ የፈረንሳዩ
አቻ ትርጉም ነው ልለው የምለውን ማሕሌት ፋንታሁን የፍርሐት ዘመን በሚል ርዕስ ዞን ዘጠኝ ላይ ከዚህ ቀደም ጽፋዋለች፡፡ ጽሑፏ
ያለንበትን የፍርሐት ወቅት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ለመሆኑ ይሄ ፍርሐታችን የፈረንሳይ አብዮት የወለደው የ‹‹ፍርሐት ዘመን››
ጋር የሚያመሳስለው ነገር ይኖር ይሆን በሚል የሚከተለትን ሁለት ክስተቶች ለማስታወስ እንገደዳለን፡፡
ሀ). ቀይ ሽብር
ምናልባትም
ለአሁኑ ትውልድ አባት የሚባሉት የ‹‹ያ ትውልድ›› አባላት፣ የሚፈልጉት ለውጥ አቅጣጫውን እንዳይስት እና በየግላቸው መቆጣጠር እንዲመቻቸው
ሲባል የሄዱበት መንገድ ሽብር ነበር - ቀይ እና ነጭ ብለው የሰየሙትን ሽብር፡፡
በዚህ መንግሥታዊ
እና መንግሥታዊ ያልሆነ የሽብር ድርጊት ሳቢያ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለው እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች አልቀዋል፡፡
ሌኒን ‹‹ያለ ቀይ ሽብር ማኅበረሰባዊነት አይገነባም›› ብሏል በሚል በአንድ ርዕዮተ ዓለም እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ በሚል እና
ደርግ ጊዜያዊ መንግሥት አቋቁሞ ወደካምፑ ይመለስ የሚሉና ሌሎችም አብዮቱን ያቀጣጠሉ ጥያቄዎችን መልስ በመሻት እና በመነፈግ መካከል
ለመገዳደል ሳይቀር የሶቪየት ኅብረትን ቀይ ሽብር የሚል ስም የተዋሱት ኢሠፓዎች እና ነጭ ሽብር የሚባል ምላሽ የሰጡት ኢሕአፓዎች
ልክ የፈረንሳይ አብዮት ልጆች እንደሆኑት ጊሮንዲኖች እና ያቆቢኖች ‹‹አብዮት ልጆቿን በላች›› ተብሎላቸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ
የቻለው ሲሰደድ የቀረው መፍራት የሚችለውን ያክል የሚፈራበት ታሪክ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ፍርሐት በከፊል የተቀረፈው በኢሕአዴግ አፍላ የሥልጣን ዘመን ነበር፡፡
ለ). ድኅረ ምርጫ 97
ግንቦት 7፤
1997 - የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ከዛን ዕለት ጀምሮ ለ30 ቀናት ምንም ዓይነት
ሕዝባዊ ስብሰባ ማድረግ እንደማይፈቀድ እና ፌዴራል ፖሊሱም ተጠሪነቱ በቀጥታ ለርሳቸው ሆኖ በተጠንቀቅ እንደሚቆም ገለፁ፡፡ ጉዳዩ
አስደንጋጭ ነበር፤ ምክንያቱም የዛን ዕለት የተካሔደው ምርጫ እንጂ ሌላ ምንም ነገር አልነበረም፡፡
ሰኔ ወር ላይ
ኢሕአዴግ ምርጫውን በበላይነት እንዳሸነፈ ምርጫ ቦርድ በማስታወቁ እና ተቃዋሚዎች ምርጫው ይደገም ያሉባቸውን ቦታዎች በአብዛኛው
በመከልከሉ… በየከተማው ሕዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ ያቆሰለውን አቁስሎ፤ የገደለውን ገድሎ ለመደራደር ፈቃደኝነት
በማሳየቱ መጠነኛ መረጋጋት ተከሰተ፡፡ ነገርዬው ግን ብዙም ሳይዘልቅ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት 22/1998 ነገሩ ሁሉ ወደብጥብጥ ተገለባብጦ
ተጠሪነታቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበሩት የፌዴራል ፖሊሶች መንግሥት ባመነው ብቻ 193 ሰዎችን ሕይወት ቀጠፉ፡፡ ከዚያም ፍርሐት
ሆነ፡፡
በቀይ ሽብር
- ነጭ ሽብር ፍጅት ዶ/ር አለማየሁ ረታ እንዳሉት ‹‹እጅ እጁን በእሳት ብረት እየተገረፈ›› አብዮቱን የተነጠቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ
የለውጥ ፍርሐት፣ በኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ዝማሪ ተዘናግቶ በምርጫ ለውጥ ቢጠይቅም የኋለኛው ከፊተኛው የጎላ ለውጥ እንደሌለው በሚያረጋግጥ
መልኩ ዳግም የፍርሐት ዋሻው ውስጥ እንዲሸሸግ በልማት ስም ዴሞክራሲውን መልሶ ተነጥቋል፡፡
“ከማያቁት መላክ የሚያውቁት ሰይጣን”
ሌላኛው በፖለቲካዊ
የሥርዓት ለውጥ ላይ የሚመጡ ተቃውሞዎች ምንጭ ‹‹ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻላል›› የሚለው አባባል ይገልጸዋል፡፡
ይሕ ሕዝብ ይህንን ተረት የፈጠረው ካለፈው ልምዱ በመነሳት ነው፡፡ የሚመጣው ለውጥ በግልጽ የማይታየው ሕዝብ የባሰ ይመጣብኛል ብሎ
መፍራቱ የሚያስገርም አይደለም፤ ይህንን ተረት ለመሻር ለውጥ አምጥቶ የኋለኛው ከፊተኛው እንደሚሻል በተደጋጋሚ ማስመስከር ብቻ ነው
መፍትሔው፡፡ የዚህ ተረት አምላኪዎች ኢሕአዴግ እራሱ እንዲለወጥ እንጂ፣ ፓርቲው በሌላ እንዲተካ አይፈልጉም፡፡ እርግጥ ነው፤ እነዚህ
ሰዎች የዘነጉት ነገር ኢሕአዴግን መለወጥም ራሱ ለውጥ መሆኑን የምናወራበት ጊዜ ይመጣል፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው
አሰፋ ‹‹የቀድሞ አምባገነኖች እልፍ ሀብት ማፍራት ይወዱ ነበር፤ የአሁኖቹ ግን ሕዝብ መግዛት ብቻ ነው የሚያስደስታቸው›› ይላሉ፡፡
ይሄ አባባል ግን የኛዎቹን የሚገልጻቸው አይመስለኝም፡፡ መሪዎቻችን በጣም ሀብታሞች ከመሆናቸው የተነሳ ለመናጢ ድሀ እንኳን የማይበቃ
የወር ደሞዝ እየተቀበሉ አነሰኝ ሲሉ አይደመጡም፣ ልጆቻቸውን ዓለምአቀፍ ት/ቤት ያስተምራሉ፣ ሕንፃ ይገነባሉ፣ ትልልቅ አክሲዮን
ይገዛሉ፡፡ በአጭሩ ልታይ፣ ልታይ አይሉም እንጂ(?) ሀብታሞች ናቸው፡፡ ቁምነገሩ ሀብታም መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን የሀብታቸውን ምስጢርም
ሳይቀር ሕዝቡ ማወቁ ላይ ነው፡፡ እናም አዲስ ተረት ተፈጥሯል፤ ‹‹የጠገበው ይግዛን›› የሚባል! ይህም እንግዲህ ሌላው ለውጥን
የመቃወሚያ (የሚያስፈራ) አንድ ምክንያት ሆኖ ሊመዘገብ ይችላል፡፡
ሰውኛ የለውጥ ፍርሐት
ለውጥን የሚያስፈራን
ቀድመን የጠቃቀስናቸው እሳት የጎረሱ እሳት የለበሱ የለውጥ ገጠመኞች ብቻ አይደሉም፡፡ ጥልቀቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም ሰው አእምሮ
ውስጥ ተፈጥሯዊ የለውጥ ፍርሐት እና መቋቋም (resistance) አለ፡፡
የሥነ-ልቦና
ምሁራን ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት ለውጥ የሚቃወሙባቸውን የተለያዩ ምክንያቶችን ይዘረዝራሉ፡፡ ለምሳሌ ሰዎች የሚሰበክላቸው ለውጥ
ጥቅሙ ላይታያቸው ይችላል ወይም የሚጎዳቸው ዓይነት ይሆናል፤ ለውጦቹ በእርግጥ ይመጣሉ ብለው ማመን ይቸገራሉ ወይም ይመጣበታል የተባለው
መንገድ አያሳምናቸውም፤ ለውጡን አመጣለሁ ወይም እመራለሁ በሚለው አካል እምነት ላይኖራቸው ይችላል፤ ለውጡን ቅድሚያ ላይሰጡት ይችላሉ
ወይም ደግሞ ለውጡ ለነርሱ ዋጋ የሚሰጥ (ወይም ከለውጡ በኋላ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም ያላቸው) አይመስላቸውም፤ ለውጡ የተለየ ክህሎት
ወይም ሌላ መለያ ያላቸውን የሚጠቅም ብቻ ሊታያቸው ይችላል፤ ለውጡ ተጨማሪ ኃላፊነት ወይም ሥራ ይዞባቸው የሚመጣም ሊመስላቸው ይችላል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰዎች ከለመዱት የምቾት ዞን መውጣት ይከብዳቸዋል፡፡
ሰዎች አንድን
ለውጥ የሚቋቋሙት በብዙ መንገድ ነው፤ እነዚህ መንገዶች ለውጡን በሚያመጡ እርምጃዎች ላይ ካለመተባበር እስከ ለውጡን የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች
ማራመድ ሊደርስ ይችላል፡፡
እነዚህን ፍርሐቶች
እና ለውጥን የመቋቋሚያ ምክንያቶች እንኳን መላ አገሪቱን እለውጣለሁ ብሎ ለተነሳ ፓርቲ እና አራማጅ ቀርቶ የአንድን ድርጅት አሠራር
እለውጣለሁ ብሎ ለተነሳ መሪ ከባድ ፈተናዎች ናቸው፡፡
ጥቂት መፍትሔዎች
የለውጥ ፍርሐቱን
ለመስበር የመጀመሪያው ለውጡ እንደሚያስፈልግ የሚያምን፣ ለውጡ የሚመጣበትን መንገድ የሚያመላክት፣ ፍርሐቱን የሚጋፈጥ፣ ችግሩን የሚቋቋም
እና ስሜቱን ማጋባት የሚችል ፈር ቀዳጅ መሪ ወይም የሚችሉ መሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ መሪ የሌለው የለውጥ ሒደት አለ ብሎ ማለት ይቸግራል፡፡
ለውጡ የሚመለከታቸውን
ሰዎች (የኅብረተሰብ አካላት) በለውጡ ሒደት ውስጥ ዋና ተዋናይ ማድረግ፡፡ የስርዓት ለውጥን በተመለከተ ብዙ ከማውራት፣ ከመወያየት
እና መረጃ ከመለዋወጥ በላይ ፋይዳ ያለው ነገር የለም፡፡ የለውጡ ባለቤቶች ስለለውጡ ማወቅ እና በቂ ግንዛቤ ማፍራት የሚችሉበትን
መንገድ በአትኩሮት ማሰብ እና መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ለውጡን የተቀበሉት ቢመስሉም እንኳን ለተግባሩ ላይታዘዙ ይችላሉ፡፡
ለውጥ ሲካሔድ
ለውጡ የሚጎዳቸው አካላት (የኅብረተሰብ ክፍሎች) ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በለውጡ በቀጥተኛ መንገድ የሚታወኩ ሰዎች የለውጡ ሰለባ ሳይሆን
የለውጡ ተጠቃሚ የሚሆኑት እንዴት ነው በሚለው ዙሪያ ላይ ቀድሞ መዘጋጀት፤ መዘጋጀት ብቻም ሳይሆን በለውጡ ምንም ዓይነት ቁስል እና ጠባሳ እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ
ያ የለውጥ ቁስል ሁሌም የታሪክ ማጣቀሻ ሆኖ መቅረቱ የግድ ይሆናል፡፡
ለውጥ ሁሌም
የተለየ ነገር ይፈልጋል - ግን ምን ያህል?... በአንድ ግዜ ብዙ እና ትልቅ ለውጥ ለማምጣት መታገል የሰው ልጅን የልምድ ቀጠና
አፈራርሶ አዲስ ልምድ እንዲገነባ ማድረግ በመሆኑ ከመክበዱም ባሻገር፣ ለግራ መጋባትና ለስህተት መንገድ ይከፍታል፡፡ ስለዚህ ለውጦችን
በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ (በየእርከኑ) እና በበቂ ዝግጅት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡
ለውጡን በአንድ
ጀምበር ለማስኬድ አለመሞከር፤ ይህ በተለይ በፖለቲካዊ ስርዓቶች ላይ የሚከብድ ይመስላል - ነገር ግን የማይቻል ነገር አይደለም፡፡
ሆኖም የስርዓትን ለውጥ አንዱን በአንዱ ለመተካት ከማሰብ ይልቅ ከነባሩ ጎን ለጎን አዲሱን በማስጀመር፣ ነባሩን ስርዓት እየገዱሉ፣
አዲሱን እያጎለበቱ የሚሸጋገሩበትን ጊዜ ማመቻቸት/ማቀድ፡፡
ስጋቶችን አለማጣጣል
ያስፈልጋል፤ ለውጥን መቋቋም ሰውኛ ባሕርይ ነው በሚል ብቻ በቸልተኝነት ማለፍ ተገቢ አይሆንም፡፡ ምናልባትም አንዳንዴ የሚነሱት
ስጋቶች እና ፍርሐቶች እውነትም ተገቢ ስጋቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ስጋቶች፣ ፍርሐቶች እና ጥያቄዎችን ጆሮ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
“ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም”
ለውጥ የግድ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሁሉንም የማይጠቅም ቢሆን እንኳን ለብዙኃኑ ሲባል የግድ
መምጣት አለበት፡፡ የለውጥ ፍርሐትን እና ተቃውሞን እንደችግር ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በቂ ዝግጅት በማድረግ
ግን በተገቢው መንገድ መቀነስ ይቻላል፡፡ የለውጥ ፍርሐትን እና ተቃውሞን ሳይቀንሱ ግን ለውጥን መጨበጥ ዘበት ነው፡፡ የፈረንሳዮቹ
የፍርሐት ዘመን አንድ ዓመት ሳይዘልቅ በሞቀ አብዮት ተገፍፏል፡፡ አብዮት አብዮትን እየወለደ ከአራት አብዮት በኋላ የዛሬዋ ፈረንሳይ
የበለፀገች እና ዴሞክራሲያዊ ሆናለች፤ ለእኛም ይህ የፍርሐት ዘመን ተገፍፎ ብለፅግናና ዴሞክራሲ እንዲመጣ ፍርሐታችንን ለመጋፈጥ
መቁረጥ አለብን፡፡ ‹‹መፍራት ያለብን ፍርሐትን ራሱን ነው›› እንዲሉ ፍራንክሊን ሩዝቬልት፡፡
------
ማስታወሻ፡-
- · ይህ ጽሑፍ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል የሚቀርቡት ጽሑፎች አካል ነው፤
- · ከዚህ ቀደም የተጻፈው ጽሑፍ እዚህ ይገኛል፤
No comments:
Post a Comment