Monday, April 1, 2013

#Ethiopia: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመደራደር አቅም (ሁለት)


በዳዊት ተ. ዓለሙ*

ባለፈው ሳምንት በወጣው የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል የተቃዋሚ ፓርቲዎች የድርድር አቅም ዋና ዋና አላባዎች የተነሱ ሲሆን ተከታዩ እና የመጨረሻው ክፍል ተከትሎ ይቀርባል፡፡

በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው የቅቡልነት ደረጃ

የተቀዋሚ ፓርቲዎች በማህበሰቡ ውስጥ የሚኖራቸው የቅቡልነት (legetimacy) ደረጃ ፋላጎቶችን የማስታረቅና የማህበረሰቡን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመንቀስ፣ የፖለቲካ አጀንዳ በመቅረጽና ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ላይ የተመሰረተ ነው:: በተለምዶ ፓለቲካ ፓርቲዎች በሚያራምዱት ርዕዮተ አለም ላይ ተመስርተው በሚነድፉት የፖለቲካ ፕሮግራም ላይ የሚወክሉትን የማህበረሰብ ክፍል ፍላጎቶች ያንጸባርቃሉ:: በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን በብሔር ብሔርተኛነት ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደመብዛታቸው፣ በፖለቲካ ፕሮግራማቸው የሚያንጸባርቁት ፍላጎቶች በአንድ የተወሰነ ብሔር ፍላጎት የተገደበና ማህበራዊ መሰረታቸውም እንወክለዋለን የሚሉት ብሔር አባላት ብቻ ናቸው:: ህብረ-ብሄራዊ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች በግልጽ ማህበራዊ መሰረታቸውን ያለዩና በፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው ያስቀመጡት ፍላጎቶች ሃሳባዊነት(utopia) የተላበሰና በሃገሪቱ ካሉ ከማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመነጩ አይደሉም::

ከላይ እንደተመለከተው በሰው ኃይል አመዳደባቸው፣ አደረጃጀትና አሰራራቸው የጥቅመኝነት ግንኙነት የሰፈነበት በመሆኑ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሃከል ያሉ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ሁሉም ፓርቲዎች የሚያንጸባርቁት ማህበራዊ መሰረቶቻቸው እየጠበበ ሂዶ በፓርቲዎች ውስጥ የሚሳተፉትን ሙሁራንparty-based elites’ ሆኗል:: ስለዚህም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረቶቻቸው የጠበበ በመሆኑ ህልውናቸውን የማስጠበቅ ከፍተኛ ፈተና ተጋፍጠዋል፤ ተቋማዊ አቅማቸውን የሚያዳብሩበትን እድል አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፤ የተቃውሞው ፖለቲካ ካለበት  የችግር አዙሪኝ መላቀቅ አቅቶታል:: ይህም ያላቸውን የመደራደር አቅማቸውን እጅግ በጣም የወረደ እንዲሆን አድርጎታል::


ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው ጠባብ የህበረተሰብ መሰረት በመሆኑ የየራሳቸውን ህልውናና ፍግላጎቶች ለማስጠበቅ ሲሉ ሃገራዊውንና ህዝባዊውን ትልቁን ምስል እንዲያጡ አድርጓቸዋል:: ማህበረሰባዊ ፍላጎቶችን ማስታረቅና ልዩነቶችን ማቻቻል ተለምዷዊ ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባራት አንዱ ቢሆንም፣ ይህን ተግባር የመከወን ልምድ ሊዳብር ይቅርና እጅግ በጣም ጠባብ የሆኑ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን የማግዘፉ ልምድ ዛሬም በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ የሚታይ ድርጊት ነው:: የዚህ ችግር ባህሪያዊ መነሻ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ  ሁናቴ ነው:: በአንድ በኩል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማህበረሰቡን ለማነሳሳትና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያላቸውን ልዩነት ፖለቲካዊ ትርጓሚ ለመስጠት የብሔር ብሔርተኝነትን ሲያጎሉ በሌላ በኩል ደግሞ ርዕዮተ አለማዊና መደባዊ ፍላጎቶችን በመጠቀም ከተለያዩ ፓርዎች ጋር አብሮ ለመስራትና ማህበራዊ መሰረታቸውን ለመሳፋት ይጠቀማሉ:: ይህ ሁለትዮሽ አካሄድ ፍላጎቶችን በግልጽ አንጥሮ ለማውጣትና ከሌሎች ፓለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎቶች ጋር ለማስታረቅ፣ ልዩነትን ለማጥበብ ግልጽነትንና መተማመን በመሃከላቸው እንዳይኖር አድርጓል::     

በሌላ በኩል ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቅቡልነት በማህበራዊ ምሕዳር  (Social space) ባላቸው ሚናና አቅም የሚታይ ነው:: ማህበራዊ ምሕዳር የሚገለጽባቸው ቁም ነገሮች አራት ሲሆኑ እነርሱም በማህበራዊ አቅም (Social capital)፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም (Economic capital)፣ ባህላዊ አቅም (Cultural capital) እና ምልክታዊ አቅም (Symbolic capital) ናቸው::

ማህበራዊ አቅም ሲባል በተቃዋሚዎች መካከል ባለ ሰላማዊና ትብብራዊ ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለው የቅቡልነት ሂደት የሚመለከት ነው::  እንደአለመታደል ሆኖ ዶ/ር መራራ ጉዲና Party Politics, Political Polarization and the Future of Ethiopian Democracy ብለው በሰየሙት የጥናት ስራቸው እንዳመለከቱት የፖለቲካ ፓርቲ ባህል የኢትዮጵያን ፖለቲካን ከተዋወቀው ጊዜ ጀምሮ ማለትም ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ያለው የፓለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ የሴራና የጠልፎ መጣል የውድቀት ታሪክ ነው:: እንደ ዶ/ር መራራ አገላለጽ:-

[…] conspiracy and political intrigues have become the hallmark of the Ethiopian political parties and their leaders with the resultant effect of frustration, disillusionment and demobilization of the common folks across the country.     

ይህ አገላለጽ በመሰረቱ ከእውነታው ብዙ የራቀ አይደለም:: ይህ የሴራና የጠልፎ መጣል ታሪክ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ደካማ ከማድረጉም በላይ በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን የቅቡልነት ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው ያለው:: በፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች መካከል ያለውን የጊዜያዊ የመተባበር ፍላጎት እንኳን በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታየው በከፍተኛ ጥርጣሬ ነው:: ይህ ዝቅተኛ የመደራደር አቅም ገዢው ፓርቲ በቀላሉ ፓለቲካዊ ፍላጎቶቹን እዚህ ግባ በማይባል መገዳደር በቀላሉ ሊያስፈጽም የሚችልበትን እድል ከመፍጠሩም በላይ የተቃውሞ ካምፑን በተለያዩ ዘዴዎች በመከፋፈል ውስጣዊ መረጋጋት እንዳይኖራቸውና ህዝቡም በከፍተኛ ጥርጣሬ እንዲመለከታቸው በቀላሉ ፖለቲካዊ ስራዎችን እንዲሰራ አስችሎታል:: እናም ይህ ደካማ ማህበራዊ አቅም  በህዝቡ ውስጥ ዝቅተኛ ቅቡልነት እንዲኖራው ብቻ ሳይሆን ያደረገው የመደራደርና የመገዳደር አቅማቸውን ውስን እንዲሆን ጭምር ነው::

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርዎች ኢኮኖሚያዊ አቅምም ከማህበራዊ አቅማቸው የተለየ አይደለም:: የፓርቲዎች ኢኮኖሚያዊ አቅም ምንጩ በዋናነት መደበኛን ጨምሮ በተለያዩ ዘዴዎች ከአባላትና ደጋፊዎቻቸው የሚያገኙት የፋይናንስ፣ የቁሳቁስና የአገልግሎት ገቢና ድጋፍ ነው:: አንደኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሏቸው አባላት በጣም ጥቂት ስለሆነ ሊያሰባስቡት የሚችሉት መደበኛ ገቢ እጅግ በጣም ውሱን ነው:: ሁለተኛ ከመንግስት የሚያገኙት አመታዊና የምርጫ ድጎማ በጣም አናሳ ከመሆኑም በላይ በአስገዳጅ ሁኔታ ለምሳሌ በታወቀ ድርጅት የኦዲት ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ ጋር የተያያዘ ነው:: ይህም ማለት አንድ የታወቀ ኦዲት የሚሰራ ድርጅት የሚያስከፍለውን የአገልግሎት ክፍያ ታሳቢ ስናደርግ፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት የሚያገኙትን ድጎማ ሙሉ በሙሉ ለፖለቲካዊ ስራቸው ማዋል አይችሉም ማለት ነው:: እንደ ባህል ፖለቲካ ፓርቲዎችን የመደገፍ ልማድ አነስተኛ በሆነባት ሀገርና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መደገፍ መንግስትን እንደመቃወም በሚቆጠርበት ሁኔታ ሊገኝ የሚችለው ድጋፍ አናሳ ነው::

በሀገር ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ባለሃብቶችም አንድም ማህበራዊ ግዴታቸውን ጠንቅቀው የማይረዱ መሆናቸው፣ ሁለትምጎመን በጤናብለው ከፖለቲካዊ ንኪኪ ራሳቸውን የሚያገሉ፣ ሶስትም ከመንግስት ባለስልጣናትና ከገዢው ፓርቲ ጋር የጥቅም ግንኙነት የሚፈጥሩ እንደመሆናቸው መጠን ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በፋይናንስና በዕውቀት የሚደግፉ አይደሉም:: በሌላ በኩል ዲያስፖራው የሚያደርገው ድጋፍ ከፖለቲካ ግለት ጋር የተያያዘ እንጂ ዘላቂነት ያለውና በመርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም:: ከንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከላይ እንደተመለከተው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባላቸው ደካማ ተቋማዊ አቅም የተነሳ ያገኙትን ገቢና ድጋፍ በተሳለጠና ውጤታማ በሆነ መንገድ የመጠቀማቸው አቅም እጅግ ደካማ ነው:: ይህም በመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርምር ላይ የተመሰረቱ፣ የማህበረሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚያስችሉ የጋራ አጀንዳ የመንደፍ ብሎም ማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማህበረሰቡን በነሱ ዙሪያ በማሰባሰብና የቅቡልነታቸውን ደረጃ ከፍ በማድረግ የመደራደርና የመገዳደር አቅማቸውን ገንብተው ገዢውን ፓርቲ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማስገደድ የፖለቲካ ፍላጎታቸውንና አጀንዳቸውን ማስፈጸም የሚችሉበት እድል እጅግ ጠባብ  ሆኗል::  

ባህላዊ አቅም (Cultural capital) የሚለው ዕሳቤ እ.አ.አ በ1973 ቦርዲዎ እና ጃን ክላወዴ "Cultural Reproduction and Social Reproduction" ከተዋወቀ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ትርጓሜዎችን ቢሰጠውም በዚህ ጹሁፍ ግን የገባበት አግባብ ግን ተቋማዊ ፖለቲካል ሶሾሎጂስትስ (Institutional Political Sociologists) በሚጠቀሙት አረዳድ ነው:: ይኸውም <እንዴት አንድ ፖለቲካል ፓርቲ እንደተቋም የማህበረሰቡን ባህልና ወግ ተረድቶ በሚያደርገው ትንታኔ በማህበረሰቡ ውስጥ የጋራ ጠቀሜታ (Common Good) ማስፈን ይችላል?> የሚለውን ነው:: በዚህ አረዳድ መሰረት ምን ያህል የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የማህበረሰቡችን ችግሮች የመረዳት ባህል አዳብረዋል? ምን ያህልስ እርስ በራሳቸው በሚያደርጓቸው ግንኙነቶችና መስተጋብሮች የአጠቃላዩን ማህበረሰብ ማህበራዊ ዕሴቶች ተከትለዋል? ምን ያህልስ ህዝቡ የማህበራዊና ባህላዊ ንቃተ ህሊናው እንዲያድግ እረድተዋል? የሚሉት ጥያቄዎችን ማየት ተገቢ ነው:: በፖለቲካ ፓርዎች መካከል ያለው ቅራኔ በተወሰነ መልኩ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ቅራኔ የሚያንጸባርቅ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ   በፖለቲካ ልሂቃኖች መካከል ያለው የስልጣንና የጥቅም ሽኩቻ በምንም መልኩ ቢሆን በህዝቡ ውስጥ ያለውን አብሮ-የመኖር ዕሴቶች የሚያንጸባርቅ አይደለም:: በብሔር ብሔርተኛነት ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንወክለዋለን የሚሉትን ብሔር የማህበራዊና ባህላዊ ንቃተ-ህሊናው እንዲያድግ አድርገዋል:: ሆኖም ግን እንደመጨረሻ ውጤት የሚታየውን የጋራ ተጠቃሚነት ባህልን ከማዳበርና የጋራ በጎ (Common Good) አጀንዳ ከመንደፍና የህዝቡን ችግሮች በመቅረፍ ቅብሉነታቸውን በማሳደግ የመደራደርና የመገዳደር አቅማቸውን የመገንባት ሂደት ግን ገና ብዙ የሚቀረው ነው:: 

ከላይ ከተጠቀሱት ሶስት አቅሞች አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የተሻለ ደረጃ ያላቸው በምልክታዊ አቅም (Symbolic capital) ነው:: ምንም እንኳን ምልክታዊ አቅም በተለያዩ ሁኔታዎች ሊገለጽ ቢችልም፤የኢትዮጵያ ተቃዋሚ መሪዎች እንደግለሰብ ያላቸው አካዳሚክ ደረጃ እንደ ትልቅ አቅም የሚታይ ነው:: እንደ ተቋም ተቃዋሚ ፓርቲዎች እዚህ ግባ የሚባል ታሪካዊም ሆነ ማህበራዊ ዳራ የላቸውም:: ለምስሌ እንደነጻነት ተምሳሌት ተደርገው ይታዩ የነበሩት በዋናነት ብሔር ተኮሮቹ ሕወሓትና ኦነግ እንዲሁም ህብረ-ብሔሮቹ ኢህአፓና ቅንጅት ነበሩ:: ከነዚህ ውስጥ አሁን ከሕወሓት ውጪ ሁሉም ከመኖር ወደአለመኖር ደረጃ ደርሰዋል:: <የተማረ ይግደለኝ!> በሚል ማህበረሰብ ውስጥ የተቃዋሚ መሪዎች እንደግለሰብ ያላቸው አካዳሚክ ደረጃ በሌሎች አቅሞች ቢታገዝ ኖሮ ሊያስገኝላቸው የሚችለው የቅቡልነትና ሊፍጥርላቸው የሚችለው የመደራደር አቅም እጅግ ከፍተኛ በሆነ ነበር:: ይህ ባለመሆኑ ያላቸውን ምልክታዊ አቅም ከገዢው ፓርቲ አመራሮች ትችት እንኳን ሊያድኑት አልቻሉም:: ለምሳሌ 2002 የምርጫ ውድርር በኢቲቪ በሚተላፈው ፕሮግራም ላይ አቶ ሬዲዋን ሁሴን ይህን አቅማቸውን ሲተች <አቧራ እያራገፉ ብዙ መጽሃፍ ብቻ ማንበቡ ዋጋ የለውም:: የኢትዮጵያን ሁኔቴ መረዳት ጭምር እንጂ!> በማለት ነበር:: ይህ ንግግር አንድም ያላችሁ አካዳሚክ ዕውቀት ከዘመኑ የዕውቀት ደረጃ (state of the art) ጋር አይሄድም፣ ሁለትም ዕውቀታችሁ ጥራዝ ነጠቅ እንጂ የሃገራችንን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አይደለም ማለት ነው:: ምልክታዊ አቅም  በባህሪው ከተጨባጭ ባህላዊና ታሪካዊ ሁኔታዎች ጋር ስለሚያያዝና ምንም አይነት ገደብ ስለሌለው ቀጣይነት ያለው ማህበራዊ ግዴታዎችን የመወጣትና እራስን የማስተዋወቅ ስራ ይጠይቃል:: በዚህም ምክንያት ተቃዋሚ መሪዎች ያላቸውን አቅም የማስጠበቅና በዚህም ማህበረሰባዊ ቅቡልነታቸውን የማሳደግና የመደራደር አቅማቸውን የመገንባት ከፍተኛ የሆነ ውስኑነት ይታይባቸዋል::           

ፖለቲካል ስትራተጂ፣ ታክቲክና  ፖለቲካል ውሳኔ ተተንባይነት


ፖለቲካል ስትራተጂ ማለት  ፖለቲካ ፓርቲዎች የነደፉትን ፖለቲካል ፕሮግራም እንዴት አድረገው ሊያስፈጽም እንደሚችሉ ከሀገራዊና አለማቀፋዊ ተጫባጭ ሁኔታዎች ተነስተው የሚነድፉት አካሄድ ነው:: ፖለቲካል ታክቲክ ደግሞ በተነደፈውን ፖለቲካል ስትራተጂ እንዴት እንደሚፈጸም የሚያመለክት ዝርዝር  የአፈጻጸም ሂደትን የሚያመለከት ነው:: አንድ ፖለቲካ ፓርቲ የመደራደርና የመገዳደር አቅሙን ለመገንባት በዋናነት ፖለቲካል ስትራተጂውንና ታክቲኩን ከማህበረሰባዊው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያገናዘበና በማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማህበረሰቡን ማደራጀትና ማሰባሰብ አለበት:: በዚህ ሂደት ውስጥ አንደኛ ፖለቲካ ፓርቲው በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነትን ያተርፋል:: እንዲሁም ደግሞ በሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም የመደራደር አቅሙን ከፍ ያደርገዋል:: በተያየዘ መልኩም ከሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመደራደር የጋራ ፖለቲካ አጀንዳ ነድፈው የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣሉ::

በኢትዮጵያት ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንጻር ይህ አካሄድ በመሰረቱ ብዙ የተለመደ አይደለም:: በአብዛኛው ፖለቲካ ፓርቲዎች ከነመኖራቸው ራሳቸውን ለማህበረሰቡ የሚያስተዋውቁት ምርጫ የተወሰነ ጊዜ ሲቀረው ብቻ ነው:: ከምርጫ በኋላ እንቅስቃሴ ቢኖር እንኳን መሪዎቹ ጎልተው የሚወጡበትና እንደድርጅት ፖለቲካ ፓርቲዎች የማይታዩበት ነው:: „የምርጫ ፖለቲካ ፓርቲየሚለው አሰያየም በተለያዩ ሙሁራን እየተንጸባረቀ ያለው ለዚህ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ከማህበረሰባዊው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ ፖለቲካል ስትራተጂና ታክቲክ ያላቸው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቁጥር እጅግ አናሳ ናቸው:: ፖለቲካል ስትራተጂና ታክቲክ  ያላቸው እንኳን በማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቀው ስላልገቡ አይደለም በአጠቃላይ ህዝቡ ይቅርና የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናቸው ከፍ ብሏል በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል እንኳን በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ዋና ዋና ልዩነቶች እንኳን አይታወቅም:: ለዚህም ነው የልደቱ ፓርቲ፣ የበየነ ፓርቲ፣ የመራራ ፓርቲ፣ የሃይሉ ሻወል ፓርቲ፣ የቡልቻ ፓርቲ ወዘት እየተባለ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋዜጦች ጭምር የሚዘገበው::   

የተቃዋሚ ፖለቲካል ፓርቲዎች ያላቸው ድርጅታዊ መዋቅራዊ ሁኔታ በራሱ የነደፉትን ፖለቲካል ስትራተጂና ታክቲክ ሊያስፈጽማቸው የሚችል አይደለም:: ምን ይህሉ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተደራጀና በሰው ኃይል የተዋቀረ ቢሮ አላቸው? አብዛኞቹ አዲስ አባባ ከሚገኘው /ቤታቸው ውጭ ሌላ በተለያዩ ክልሎች /ቤት የላቸውም:: በሌላ በኩል በድርጅታዊ መዋቅራቸው ውስጥ ግልጽ የሆነ ከላይ ወደታች (vertical) የተዋረደ የስልጣን ክፍፍል እንዲሁም በተለያዩ ክፍሎች መካከል የጎንዮሽ (horizontal) የስራ ግንኙነት የላቸውም:: ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እስከዛሬ ድረስ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጣዊ መከፋፈል ሲያጋጥማቸው የሚነሱት ሶስት ምክንያቶች ናቸው:: እነርሱም ግለሰባዊ አገዛዝ መስፈን፣ የመተዳደሪያ ደንብ መጣስና የተለመደውን ውስጣዊ አሰራር አለመከተል ናቸው:: የነዚህ ሶስት መሰረታዊ ችግሮች መነሻ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ያለሆነ ከላይ ወደታችና የጎንዮሽ የስልጣንና የስራ ክፍፍሎሽ አለመኖር ነው:: ይህም መዋቅር በራሱ የሚቆም ሳይሆን ፖለቲካል ስትራተጂንና ታክቲክን የሚከተል እንደመሆኑ መጠን በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ውስጣዊ መሰነጣጠቆች የሚያመለክቱት ነገር ቢኖር ግልጽ የሆነና ሁሉም የፓርቲው አመራሮችና አባላት የሚያስተገብሩት ፖለቲካል ስትራተጂና ታክቲክ አለመኖርን ነው::

ይህም በመሆኑ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ግልጽ የሆነና ማህበረሰባዊ መሰረት ያለው የፖለቲካ አጀንዳ መንደፍና በየወቅቱ  ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረጉ ክርክሮችንና ውይይቶችን በበላይነት መምራት አልቻሉም:: ይህም የሆነው አንድም ደካማ ድርጅታዊ አቅም በመኖር ፖለቲካል ስትራተጂን፣ ታክቲክንና የውስጥ ደንብን ተቋማዊ ማድረግ አለመቻሉ፣ ሁለትም ብቃት ባለው የሰው ኃይል አለመደረጃታቸው፣ ሶስትም ድርጅታዊ መዋቅራቸው ወደህዝቡ የቀረበ አለመሆኑና በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው የቅቡልነት ደረጃ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ነው:: በዚህም የተነሳ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር የመደራደር አቅማቸው ውስን ነው:: ገዢው ፓርቲ ከሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታና ከብዙዎቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሮች ውጭ ባይሆንም መንግስታዊ፣ ወታደራዊ፣ የደህንነት መዋቅር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ስልጣን በመያዙ ምክንያት ያሉበትን ውስጣዊ ችግሮች ለመሸፈን ችሏል (ሕወሓት የ1993ቱን ውስጣዊ ክፍፍል የፈታበት መንገድ ልብ ይሏል):: የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖለቲካል ስትራተጂና ታክቲክ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት ከፍ ከማድረግ አንጻርም ሆነ የጋራ አጀንዳ በመንደፍ „አንድ-ለአንድ“ እና „አንድ-ለብዙ“ ከገዢው ፓርቲ ጋር እስካሁን ድረስ በተደረጉ የመደራደር ሂደቶች አቅማቸውን ለመገንባት ያስቻላቸው ሆኖ አይታይም::

ከላይ በተመለከቱት ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወሰዱቸው ፖለቲካዊ አቋሞችና ውሳኔዎች ተተንባይ (predictable) አይደሉም:: ተተንባይ ያልሆኑ የፖለቲካ አቋሞችና ውሳኔዎች መብዛታቸው መንስኤዎቹ በአንድም ሆነ በሌላ አግባብ ከላይ የተጠቀሱት ድክመቶች ናቸው:: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ መለያ ባህሪ እየሆነ የመጣው የሚወስዷቸውን ፖለቲካዊ አቋሞችና ውሳኔዎች ተተንባይ አለመሆኑ ነው:: እስካሁን ውስጣዊ መሰነጣጠቅ የታየባቸው ፓርቲዎች ውስጥ እንደልዩነት ከተነሱት ውስጥ ውስጠ-ፓርቲ ስርአትን የተከተለ ውሳኔ አሰጣጥ መኖሩን ነው:: ነገር ግን ይህ ችግር ገኖ የሚወጣው በፓርቲው ውስጥ በሚኖሩ ቡድኖች መካከል ስምምነት ላይ ሳይደረሰ በሚወሰኑ ፖለቲካ ውሳኔዎች ምክንያት ነው:: ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ መሰንጠቅ ከነ አቶ እስዬና ዶ/ር ነጋሶ ወደ ፓርቲው ለማስገባት በሚደረግ ጥረትና አንድነት መድረክን ለመቀላቀል በመወሰኑ ምክንያት ነው:: ተተንባይ ያልሆኑ የፖለቲካ አቋሞችና ውሳኔዎች ሲበዙ በአባላትና በደጋፊዎች መካከል አደናባሪ ሁኔታን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ የቅቡልነትንና የታአማኒነትን ጥያቄዎች ያስነሳል:: ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሁኔታ በመርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ነድፎ ከሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እና ከመንግስት ጋር የሚደረጉ ድርድሮች ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል:: ይህም የመደራደር አቅምን መልሶ የሚጎዳ ነው:: በመሆኑም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የመደራደር አቅማቸው ውስኑነት በተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የውድቀት አዙሪት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መጥቷል (ውጫዊ ተጽዕኖዎች እንደተጠበቁ ሁነው)::

እንደማጠቃለያ

የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመደራደር አቅም በተለያዩ አላባውያን ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ይህም የዴሞክራሲያዊ ስርአት ለማስፈን የሚደረገውን እንቅስቃሴ በጣም እየጎዳው ይገኛል:: የተቀራረበ የመደራደር አቅም ሲኖር ፖለቲካል ፓርቲዎች በሚገነቡት ዴሞክራሲያዊም ሆነ አስተዳደራዊ ተቋሞች ዙሪያ መግባባት ስለሚደርሱን እኩል ተጠቃሚነት በሚያሰፈን ሁኔታ ተቋሞቹ ስለሚገነቡ ዘላቂነትንና በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት እንዴኖራቸው ያደርጋል:: ይህም በመሆኑ በሀሳብ ልዩነቶች ለይ በሚደረጉ ክርክሮች (arguments) እና ዕውቅና በመሰጣጣት ላይ የሚመሰረት እንጂ የግለሰቦችን ማንንት በማንቋሸሽ (character assassination) ላይ ስለማይመሰረት በመሰረታዊነት ደረጃ የፖለቲካል ባህሉን ሰላማዊ እንዲኖን ያስችላል:: ነገር ግን የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደተቋም ሆነ መሪዎቹ እንደግለሰብ የመደራደር አቅማቸው ውሱን ከመሆኑም በላይ የሚደራደሩባቸው አጀንዳዎችና ያላቸው አቋም የሚመጣጠን ባለመሆኑ ሰላማዊ ፖለቲካል የትግል ባህል እንዳይሰፍን ሆኗል::

ይህን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ቀጥተኛና ቀላል የሆነ ፎርሙላ የለም:: ይህ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በታዳጊ አገሮች የሚታይ ከፓርቲ ፖለቲካና በተነጻጻሪ ሁኔታ ሁሉን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርአት ከመፍጠር አንጻር የልምድ እጥረቶች በሚስተዋልባቸው ሃገሮች ጭምር የሚታይ ነው:: ይህም በባህሪው ችግሩ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር ሂደት ውስጥ ሊታይ የሚችል ነው:: በመሆኑም፣ የፖለቲካ መሪዎችና ወጣቱ ትውልድ ከ1960ዎቹ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተጓዙበትን ሂደት በመገምገም ጠንካራ ጎኖቹን ይዞ በመቀጠል፤ ደካማዎቹን ደግሞ በማረም ወደፊት መጓዝን ይጠይቃል:: የችግሩን ምንጭ በንደፈ-ሃሳባዊ እይታዎች ማድረቅ አይቻልም:: በዋናነት ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስፈልገው የተግባር ምላሽ ነው:: ተግባሮቹን ግን እንደየችግሮቹ ጥልቀትና አንገብጋቢነት እየለዩና ቅደም ተከተል እየሰጡ፣ የማስፈጸሚ ስልቶችን እየቀየሱ፣ ልዩነቶችን ተገቢውን ክብር ሰጥቶ ነገር ግን በጋር በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ ተመስርቶ በጋር ወደ ተግባር መግባትን የሚጠይቁ ናቸው:: ይህም የድሮው የፖለቲካ ልሂቃን ያሌላቸውን አዲስ ባህልን የመገንባት ሂደትን ይጠይቃል::  
-----
*ጸሐፊው አቶ ዳዊት ዓለሙ የUniversity of Passau Governance and Public Policy ድኅረ ምረቃ ተማሪ ናቸው፡፡ ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይላቸው dhabesha@hotmail.com ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment