Monday, April 8, 2013

#Kenya፤ ከነጻነት እስከ ነጻ ምርጫ (#Ethiopia)



ጎረቤት ሀገር ኬንያ እ.አ.አ በ1963 ዓ.ም ነበር ከእንግሊዝ ቀኝ አገዛዝ ነፃ የሆነችው፡፡ በቀጣዩ ዓመት ኬንያ ራስዋን የቻለች ሪፐብሊክ ሆና ስትቋቋም የነፃነት ትግሉን እና የኬንያ አፍሪካ ብሔራዊ ኅብረትን (ካኑ) ይመሩ የነበሩት ጆሞ ኬንያታ* (የአሁኑ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አባት) የኬንያ የመጀመርያ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡ ምክትላቸው ደግሞ የአሁኑ ተሰናባች ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ አባት ኦጊንጋ ኦዲንጋ** ነበሩ፡፡
ኦዲንጋ የኬንያ የመጀመርያ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር ያገለገሉት፡፡ ከፕሬዝዳንት ኬንያታ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ምክንያት ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው የኬንያ ሕዝቦች ሕብረት የተሰኘ የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም የኬንያታን ሥልጣን መገዳደር ጀመሩ፡፡ ጆሞ ኬንያታ ለነፃነት ትግል አጋራቸው ብዙም ክፍተት መስጠት አልፈለጉም፡፡ በሁለቱ አባቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እያደገ ሂዶ እ.አ.አ በ1969 ዓ.ም. በኪሲሙ ግዛት ሕዝብ በተሰበሰበበት የተከሰተ የሁለቱ መሪዎች ‹እንኪያ ሰላምታ›ን ታክኮ በተፈጠረ ሁከት ሰዎች ከሞቱና ከቆሰሉ በኋላ ኦጊንጋ ኦዲንጋ ቀጣዮቹን ሁለት ዓመታት በእስር እንዲያሳልፉ ተገደዱ፡፡
 
እ.አ.አ በ1978 እስኪሞቱ ድረስ ኬንያን ለመምራት የምዕራባውያኑን ድጋፍ ያገኙት ኬንያታ ፊታቸውን ወደ ምስራቅ ያዞሩት ኦዲንጋ ላይ ሙሉ የፖለቲካ እና የሥልጣን የበላይነት ወስደው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከኩኩዩ ቤተሰብ የሆኑት ኬንያታ የ14 ዓመት ሥልጣናቸውን በሞት ሲነጠቁ የተኳቸው ከካለነጂን ጎሳ የሆኑት ዳንኤል አራፍ ሞይ ይሁኑ እንጂ በሕይወት ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት ግን ቤተሰባቸውን በሀብት አንበሻብሸዋል እንዲሁም የኩኩዩ ጎሳን የቁጥር የበላይነት ወደ መንግሥት ተቋማት ሥልጣን የበላይነትም አምጥተዋል ተብለው ይከሰሳሉ፡፡

ሥልጣን በእጃቸው የወደቀላቸው ሞይ ቀስ በቀስ ኬንያታ ሲገነቡ የቆዩትን ሥልጣንን በብቸኝነት መቆጣጠርን እና ተቃዎሚዎቻቸውን የማፈን ልምድ እያዳበሩ ሄደው እ.አ.አ 1982 ኬንያ በአሀዳዊ ፓርቲ (ካኑ) የምትተዳደር ሀገር እንደሆነች በይፋ አሳወጁ፡፡

የሞይ የሥልጣን ዘመን ለኬንያውያን ከቀኝ ግዛት በኋላ የነበረ አስከፊ ወቅት ነበር፡፡ ዜጎች ስለራሳቸው ሀገር መረጃ ለማግኘት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በነበሩትን መገናኛ ብዙኃን ላይ እምነት ስላልነበራቸው ዜናዎችን የሚያገኙት ከቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት እና የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮን ከመሰሉ ምንጮች ነበር፡፡ እ.አ.አ 1978 በተደረገ ምርጫ ሥልጣን የያዙት ሞይ እ.አ.አ በ1983 እና 1988 ሁለት ምርጫዎችን የራሳቸው ፓርቲ ካኑ ካቀረባቸው እጩዎች ጋር ተወዳድረው አሸንፈዋል፡፡ የ1988ቱ ምርጫ መራጮች ድምፅ የሰጡት በሚስጥር ሳይሆን ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪ የተለየ ኮሮጆ ተዘጋጅቶ መራጮች ድምፃቸውን መስጠት ለሚፈልጉት ተወዳዳሪ የተለየ የተራ ሰልፍ ተሰልፈው ነበር፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ዜጋ ለማን ድምፁን መስጠት እንደሚፈልግ ገና ሰልፉን ሲመርጥ ይታወቃል ማለት ነበር፡፡


የ1988ቱን ዓይን ያወጣ ነፃነት እና ፍትሐዊነት የጎደለው ‹‹ምርጫ›› ተከትሎ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከወዳጅ ሀገራት በደረሰባቸው ጫና ሞይ ሕገ መንግስቱን ለማሻሻል ተስማሙ፡፡ የተሻሻለው ሕገ መንግስት የመድብለ ፓርቲ  መኖርን የፈቀደ እና የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ዘመን በሁለት ብቻ የገደበ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት እ.አ.አ በ1992 እና በ1997 ዓ.ም የተካሄዱትን ሁለት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች በማሸነፍ የሞይ የ24 ዓመት የሥልጣን ቆይታ አበቃ፡፡

የ1997ቱን ምርጫ በማሸነፍ የመጨረሻ የሥልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ ሞይ ወዲያው ነበር ተተኪያቸውን ማዘጋጀት የጀመሩት፡፡ በወቅቱ ወጣትነቱን በሚገባ ያላጠናቀቀውን የ36 ዓመቱ የመጀመርያው የኬንያ ፕሬዚዳንት እና የካኑ መሥራች ጆሞ ኬንያታ የበኩር ልጅ ኡሁሩን (ነፃነት ማለት ነው ትርጉሙ) ተተኪያቸው እንዲሆን አስበው የተለያዩ የፓርቲ እና የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ እንዲሠራ ሲያደርጉ ቆይተው በመጨረሻም በይፋ ተተኪ ፕሬዚዳንት እንዲሆን የካኑ ፓርቲን ወክሎ እንዲወዳደር ድጋፋቸውን ሰጡት፡፡ ይህ ክስተት ካኑን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ይሹ የነበሩ እና ኡሁሩ ልምድ እንደሚጎለው በሚያምኑ አንጋፋ የፓርቲው አባላት መካከል ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡

እ.አ.አ በ1982 ዓ.ም ሞይ ላይ በተካሄደ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተሳትፈሃል በሚል (በኋላ ሕይወታቸውን በተባባሪነት በተረኩበት “Raila Odinga: an enigma in Kenyan Politics” ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው የመፈንቅለ መንግሥቱ ሐሳብ ነዳፊ እንደነበሩ አምነዋል፡፡) ለ10 ዓመታት በእስር የቆዩት የኦጊንጋ ኦዲንጋ ልጅ ራይላ ኦዲንጋ በ1997ቱ ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው 4ኛ ሆነው ካጠናቀቁ በኋላ ብዙዎች ባልጠበቁት ሁኔታ ፓርቲያቸውን ከካኑ ጋር ቀላቅለው ነበር፡፡ ኋላ ላይ ሞይ ለ2002ቱ ምርጫ ኡሁሩን ከደገፉ በኋላ እንደገና ከካኑ በመነጠል የለዘብተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን አቋቁመው በኋላም ከሞዋይ ኪባኪ ፓርቲ ብሔራዊ ጥምረት ጋር በመሆን ብሔራዊ የቀስተደመና ቅንጅት (ናርክ) የሚባል ኅብረት ፈጥረው ምርጫውን በማሸነፍ ኪባኪ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን ጨብጡ፡፡

የኪባኪ እና የራይላ ኅብረት ሲመሠረት በተስማሙት መሠረት ለራይላ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ እና ግማሽ የካቢኔ መቀመጫ ለፓርቲያቸው አባላት እንዲሰጥ የተጠበቀ ቢሆንም እውነታው ግን እንደዛ አልሆነም፡፡ ይባስ ብሎም እ.አ.አ 2005 ዓ.ም የሥልጣን ኃይል ከክልል መስተዳድሮች ላይ ቀንሶ ወደ ፕሬዝዳንቱ እንዲያዘምም ያደርጋል የተባለለትን ሕገ-መንግሥት ኪባኪ ለሕዝበ ውሳኔ ሲያቀርቡት ራይላ አጥብቀው ተቃወሙ፡፡ በሕዝበ ውሳኔው ውጤት መሠረት ሕገ-መንግስቱ በ57 በመቶ የድምፅ ብልጫ ውድቅ ከሆነ በኋላ ኪባኪ ራይላን ጨምሮ ከለዘብተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የነበሩትን የካቢኔ አባላት ጠራርገው አባረሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ከሁለት ዓመት በኋላ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሁለቱ ሰዎች ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡

የ2007 ምርጫ

በ2007 በተካሄደው ምርጫ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ኪባኪ ለሁለተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ሲወዳደሩ ከኬኒያ የነፃነት እወጃ አንስቶ ለ44 ዓመታት የተቃውሞውን ሜዳ በመሪነተ የዘለቁት ራይላ ኦዲንጋ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዝዳንትነት ማዕረግ ለማግኝት ወደ ውድድር ገብተዋል፡፡ በ2002ቱ ምርጫ እና በ2005 የሕገ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔ የኬኒያ ምርጫ ቦርድ በውጤታማ ሥራ የተወደሰ ቢሆንም የ2007 ምርጫ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት የጊዜው ፕሬዝዳንት ሞዋይ ኪባኪ በምርጫ ቦርድ ውስጥ ከነበሩ ሃያ ሁለት ባለስልጣናት ዐሥራ ሰባቱን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሳያማክሩ መቀየራቸው ገና ከጅማሮው የቦርዱን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎ ነበር፡፡

ምርጫው በታህሳስ 27 ቀን 2007 ተካሂዶ በማግስቱ ከምርጫ ጣቢያ የሚመጡ ሪፖርቶች የራይላን አሸናፊነት የሚያበስሩ መሆናቸውን ተከትሎ የራይላ ፓርቲ በታኅሳስ 29 አሸናፊነታቸውን በይፋ አበሰረ፡፡ ይሁን እንጂ በዛው ቀን የሚመጡ የምርጫ ውጤቶች የተገላቢጦሽ ሆነው የኪባኪን የበላይነት የሚያሳዩ ሆኑ፡፡ ዘጠና ከመቶ ከተቆጠሩ የምርጫ ጣቢያዎች ከ120ዎቹ 180ዎቹን ኪባኪ እንደሚመሩ ይገልፅ ነበር፡፡

በታኅሳስ 30 ራይላ በጋዜጣዊ መግለጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉና እንደተጭበረበሩ እንዲሁም ኪባኪ ሽንፈትን አምነው መንበራቸውን እንዲለቁ ቢጠይቁም ምርጫ ቦርዱ ግን የኪባኪ አሸናፊነትን አወጀ፡፡ ኪባኪም የሕዝብን ድምፅ እናከብራለን ሲሉ በዛው ቀን የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ ፈፀሙ፡፡ መንግሥት በሚያስተዳድረው የቴሌቨዥን ጣቢያ ማሸነፋቸው ተነግሮላቸው ቃለ መሃላ የፈፅሙትን ሞዋይ ኪባኪን በመቃወም በርካታ የብርቱካናማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ደጋፊዎች የተቃውሞ ሰልፍ ወጡ፡፡ ተቃውሞው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ጎሳ ግጭት ተቀየረ፡፡

የንያንዛ ክልል፣ ናሮክ፣ ናይቫሻ እና ናይሮቢ ግጭቱ  የተባባሰባቸው ቦታዎች ነበሩ፡፡ በኤልዶሬት ከተማ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በተነሳ ግጭት ብቻ 30 ሰዎች ሲሞቱ በአጠቃለይ ቁጥራቸው አንድ ሺሕ ሁለት መቶ  በላይ የሚሆኑ ንፁኃን ዜጎች ምርጫውን ተከትሎ በተነሳው ግጭት ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ 350 ሺህ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ 80 በመቶ የሃገሪቱ የቱሪዝም ገቢ ሲቀንስ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋም በእጥፍ ንሮ ነበር፡፡

እንደብዙ የአፋሪካ አገሮች የኬኒያ መራጮች ድምፃቸውን የሚሰጡት በጎሳ፣ በዘር ሃረግ እንዲሁም በዝምድና ከመሆኑም ባሻገር የፖለቲካ ፓርቲዎችም አመሠራረታቸው ጎሳን ተንተርሰው ነው፡፡ ኩኩዩ የተባለውን ጎሳ በመወከል የመጀመሪያው የኬኒያ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ እና ሦስተኛው ፕሬዝደንት ሞዋይ ኪባኪ በድምሩ ለ25 ዓመታት ኬኒያን መርተዋል፡፡ ሟች ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታን በመተካት ፕሬዝዳንት የሆኑት በአምባገነንነት የሚታሙት ዳንኤል አራፍ ሞይ ካለንጂን ጎሳ በመወከል ለ24 ዓመታት ኬኒያን መርተዋል፡፡

የ2007 ምርጫ ውጤት በኬኒያ የነፃነት ታሪክ ለ44 ዓመታት መንበረ ሥልጣኑን ያልተጋሩት የሃገሪቱን 13 በመቶ የሕዝብ ቁጥር የሚወክሉት ሉዎ ጎሳ አባላት ከእጃቸው ተመንተፎ እንዳመለጣቸው ነበር የተሰማቸው፡፡
በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን አደራዳሪነት የ2007 ምርጫ ከተካሄደ ከሁለት ወር በኋላ ሥልጣን ለመጋራት ኪባኪና ራይላ ተስማሙ፡፡ የመንግሥትን ሥራዎች ማስተባበርና መቆጣጠር ኃላፊነት ያለው አዲስ የጠቅላይ ሚነስተርነት ማዕረግ ለተቃዋሚው ራይላ ተሰጣቸው፡፡ ከሥራቸው ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተርነት ማዕረግ ያላቸው ከሁለቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሆኑ ሲደረግ የኪባኪን ፓርቲ በመወከል ኡሁሩ ሲመረጡ የራይላን ፓርቲ በመወከል ሙዳቫዲ ተመርጠው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የወንጀል ችሎት (አይ.ሲ.ሲ.)

በንፅፅር በወጣትነታቸው የፕሬዝዳንትነት ማዕረግ በማግኘት ወደ ቤተመንግስት የሚገቡት ኡሁሩ ኬኒያታ፣ በኬኒያ ከሚገኙ ቱጃሮች መካከል ቁጥር አንድ ስለመሆናቸው ፎርብስ መጽሔት ያትታል፡፡ ገና ከ29 ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ  የጡት አባታቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፍ ሞይ ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ያለማምዷቸው የነበረ ቢሆንም  በ2002 ምርጫ “የቤተመንግሥት ፕሮጀክት” የሚል ቅፅል ስም ያትርፉ እንጂ በምርጫው አሸናፊ የሆኑት ኪባኪ ነበሩ፡፡

በ2007 ምርጫ ኡሁሩ ኬኒያታ ከኪባኪ ጎን የቆሙ ሲሆን ምርጫውን ተከትሎ የመጣው ግጭት ግን ዘላቂ እርግማን እና ምርቃትን በአንድ ላይ ይዞላቸው መጥቷል፡፡ በግጭቱ ወቅት አንድን ጎሳ ከሌላው ጋር በማጋጨት፣ ግጭቱን በማሴር እና በማባባስ ወንጀል ተከስው ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ የሚገኙት ኡሁሩ በዘንድሮው ምርጫ ወቅት ዓለማቀፉ የወንጀል ችሎት ጥቁር አፍሪካውያን ላይ ብቻ የተነጣጠረ ሴራ ነው በማለት ሕዝባቸው ለሃገር ሉዓላዊነት እንዲነሱ እና ከእጅ አዙር ቀኝ ግዛት እንዲላቀቁ፣ ኬኒያ ነፃ አገር ናት በማለት በምርጫው የተከሰሱበትን ወንጀል ወደጎን በመተው ይባስ ብለው ለራሳቸው ጥቅም ለምርጫ ቅስቀሳ ፍጆታ አውለው የፖለቲካ ትርፍ አግኝተውበታል፡፡

የውጪ ኃይሎች ለሚያሳርፉብን ጫና አንበረከከም ብለው በተደጋጋሚ በምርጫ ቅስቀሳ ውቅት ይናገሩ የነበሩት  ኡሁሩ ሃገራዊ አንድነት ስሜትን በመፍጠር በተቃራኒው ራይላን ለውጪ ኃይሎች ሃገሪቷን አሳልፎ የሰጠ የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርሰ ቅስቀሳቸው ውጤት አስገኝቶላቸዋል፡፡

የዓለማቀፉ የጦር ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ኡሁሩ ወደ ምርጫ ሲገቡ ለምክትል ፕሬዝዳንትነት እጩ ያደረጓቸው ዊሊያም ሩቶ እንደእርሳቸው በችሎቱ ተከሳሽ ናቸው፡፡ የግብርና ሚኒስቴር በነበሩበት ወቅት የግለሰቦችን መሬት በመዝረፍ፣ በሙስና የተከሰሱት ሩቶ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ተደጋጋሚ ችግሮች በዙሪያቸው ቢያንዣብብም በዚህ ዓመት በተደረገው ምርጫ ግን የኬኒያ ሕዝብ ዳግም ድምፅ አልነፈጋቸውም፡፡

በኬኒያ ምርጫ ለማሸነፍ የኩኩዩ ጎሳ አባል መሆን ወይም የኩኩዩዎችን ድምፅ በዋንኝነት መበተን አሊያም  የኩኩዩ ጎሳን ተንተርሰው ከተመሠረቱ ፓርቲዎች ጋር ኅብረት መፍጠር እንደሚያስፈልግ የሚነገር ቢሆንም ራይላ ይህንን ማድረግ ባለመቻላቸው አሳዛኝ ተሸናፊ በመሆን የኬንያ ፕሬዝዳንት የመሆን ተሰፋቸው ለመጨረሻ ጊዜ ከሽፏል፡፡

የተሻሻለው ሕገ መንግሥት

ሁለተኛው የኬኒያ ሕገ መንግሥት እ.ኤ.አ በነሐሴ ወር 2010 ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት በ1969 ከነጻነት በኋላ ነበር የወጣው፡፡ በአዲሱ ሕገ መንግሥት በዋንኛነት ሕግ አስፈፃሚው፣ አውጪውና አስተርጓሚው አካላት እንዲለያዩ ወስኗል፡፡ መንግሥት በክልልና በብሔራዊ ደረጃ እንዲዋቀር ሆኖ፣ የብሔራዊ መንግሥት የክልሎች ኃብት ስብጥር ዕኩል በኩል እንዲያደርግ ደንግጓል፡፡ በሁሉም የመንግሥት ክፍሎች የሚሳተፉ አካላት በሹመት ሳይሆን በብቃት መሆን እንዳለበት ያስቀመጠው አዲሱ ሕገ መንግሥት የጸታ መድሎን ከማስቀረቱም ባሻገር የኬኒያ ዜጎች የሌላ ሃገር ዜግነት ደርበው መያዝ እንደደሚችሉ አስቀምጧል፡፡

የ1969ኙ ሕገ መንግሥት ለፕሬዝዳንቱ የሰጠውን መጠነ ሰፊ ሥልጣን በመገደብ፤ በመንግሥት አስፈፃሚ አካልና ሕግ ተርጓሚ አካል መካከል ልዩነት እንዲኖር ያደረገው አዲሱ ሕገ መንግሥት፣ መንግሥት ለሚፈፅማቸው ማናቸውም ጥፋቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ሕጋዊ መሠረትን አስቀምጧል፡፡ ክልሎች እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት እንዲኖራቸው የሚያዘው አዲሱ ሕገ መንግሥት፣ አዲስ በተቋቋመ የመሬት ኮምሽን በኩል የመሬት የይገባኛል ጥያቄ ያለቸው ዜጎች ምላሽ እንዲያገኙ ፈቅዶ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰብኣዊ መብቶች የማይደፈሩ እና የማይገረሰሱ መሆናቸውን ደንግጓል፡፡

የ2013 ምርጫ አሰላለፍ (ኬንያታ-ሩቶ/ ሙዳቪዲ/ ራይላ)

በ2007 ምርጫ የብርቱካናማ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በመወከል ወደ ፕሬዝዳንትነት መንበር ለመምጣት ያለሙት የያኔው የፓርቲው ጸሐፊ የዛሬው ተመራጭ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ በወቅቱ ከፓርቲው ምርጫ በራይላ እና በሙሳሊያ ሙዳቫዲ የተሸነፉ ቢሆንም የፓርላማ አባል ከመሆን ግን ማንም አላስቀራቸውም፡፡
በኦሬንጅ ፓርቲ ትኬት የፓርላማ አባልነትን ያገኙት ሩቶ በ2007 ራይላ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ድጋፍ የቸሩ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የምርጫውን ውጤት ተከትሎ በተነሳው የርስ በርስ ግጭት፣ የኪባኪ ደጋፊዎች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ግጭቱን በማቀናበርና በማባባስ በዓለም አቀፉ ወንጀል ችሎት ተከሰዋል፡፡

የአሁኑ ተመራጭ ምክትል ፕሬዝዳንት  ከኡሁሩ  ኬኒያታ ጋር በጋራ አብረው ወደ ቤተመንግሥት ለመግባት ተስማምተው መሥራት የጀመሩት በ2012 ሁለቱም በዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ  ሲሆን በ2007 ምርጫ ሁለቱም በተቃራኒ አቅጣጫ የነበሩ ቢሆንም ክሱ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ”  እንዲሉ፣ አብረው እዲሠሩ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡

በሌላ በኩል በዘንድሮው ምርጫ ለራይላ መሸነፍ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ከሚጠቀሱት መካከል ሙሳይላ ሙዳቫዲ ናቸው፡፡ በኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንት ፓርቲ ውስጥ አምባገነንነት ሰፍኗል፣ ከራይላ በቀር ፓርቲውን በመወከል ፕሬዝዳንት ለመሆን ማንም እንዳይሳተፍ ሆን ተብሎ ሴራ ይፈፀማል፣ ለዚህም ተጠያቂው ራይላ ራሳቸው ናቸው በማለት ገና የፓርቲው የውስጥ ምርጫ ሳይካሄድ ፓርቲውን ለቀው የወጡት ሙዳቫዲ፣ ራይላ በምዕራብ ኬኒያ ያላቸው ድጋፍ እንዲሸነሸን አስተዋፅኦ  እንደዳደረጉ ይነገራል፡፡

በተቃራኒው የኪኒያ ምርጫ ከጎሳ ምርጫ  እንደማይለይ የተረዱት ሙዳቫዲ ዩናይትድ ዲሞክራቲክ ፍሮንት ፓርቲን ወክለው  በዘንድሮው ምርጫ ለፕሬዝዳንትንት ሲወዳደሩ በምክትል ፕሬዝዳንትንት የኩኩዩ ጎሳ አባል የሆነውን ጀርሚያ ኮኒን የመረጡ ሲሆን  በምርጫው ግን ስኬት ከእርሳቸው ጋር አልነበረችም፡፡ እንዳውም በብዙ የማኅበረሰብ አውታሮች ኮኒ እንኳን በምርጫው መዳቫዲን ሳይሆን ኬኒያታን ነው የመረጡት ሲሉ መቀለጃ አድርገዋቸዋል፡፡

ሦስቱ አሸናፊዎች

ኡሁሩ - እ.ኤ.አ ማርች 4 ቀን 2013 የተካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በማሸነፍ ቀጣዩ የኬንያ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ የምርጫ እና የድንበር ማካለል ኮሚሽኑ እና የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መስክረውላቸዋል፡፡ ለሚቀጥሉት 5 ዓመታትም ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለማገልገል መሃላ ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ራይላ- ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአርቃቂዎቹ አንዱ ሆነው ያስፀደቁት አዲሱ የኬንያ ሕገ መንግሥት ለሀገሪቱ ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ባስቀመጠው የዕድሜ ገደብ መሠረት ከአሁን በኋላ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም፡፡ እ.አ.አ በ2007 (በኪባኪ) እና በ2013 (በኬንያታ) በተደረጉት ሁለት ተከታታይ ምርጫዎች ተሸንፈዋል፡፡ የማርች 4ቱን ምርጫ እና ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ እደሚያከብሩ እንዲሁም ለተመራጩ ፕሬዝዳንት መልካም ምኞታቸውን በይፋ ማሳወቃቸው ግን የዲሞክራሲ አሸናፊ ያደርጋቸዋል፡፡

ሞዋይ ኪባኪ -  በኬኒያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢኮኖሚ እምርታ እንዳስገኙ የሚነገርላቸው ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት፣ ሕገ መንግሥቱ ለፕሬዝዳንትነት ያስቀመጠውን የሁለት 5 ዓመት አገልግሎት ዘመን ገደብ አክብረው፣ ሕገ መንግሥቱን ላሻሽል የሚል የተለመደ የአፍሪካ መሪዎች ሁካታ ሳይፈጥሩ እሳቸው ያልተወዳደሩበት ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ለብዙ አፍሪካዊያን መሪዎች ምሳሌ አስቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም በጎሳ ፖለቲካ የተተበተቡትን የመንግሥት ተቋማት ታማኝነት እንዲያንሰራራ ቢያንስ የመጀመሪያውን እርምጃ የተራመዱ መሪ ሆነው አልፈዋል፡፡

ከሁሉም በላይ የነጻ ምርጫው ባለቤት - የኬንያ ሕዝብ ነው ትልቁ አሸናፊ፡፡ ኬንያም እንደሀገር ለዲሞክራሲ መዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ተቋማት መጠናከር በአጠቃላይ ለአፍሪቃ በተለይም ደግሞ ለአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት መማርያ መሆን የምትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን አስመስክራለች፡፡

የኬኒያ እና የኢትዮጵያ ምርጫ ምንና ምን?

ኬኒያ ነጻነቷን ከተቀናጀች በተያዘው ዓመት 2013 ኃምሳ ዓመት የሚሞላት ሲሆን በኃምሳ ዓመት ጊዜ ውስጥ አራት ፕሬዝዳንቶችን ቀያይራለች፡፡ ጆሞ ኬኒያታ በሞት ከስልጣን ሲሰናበቱ፣ ሞይና ኪባኪ የስልጣን ጊዜ ገደባቸውን ጨርሰው ለተተኪ ያስረከቡ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ባለፉት ኃምሳ ዓመታት ውስጥ አራት መሪዎችን ስታፈራርቅ ፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ እና መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በግድ ከስልጣናቸው ሲሰናበቱ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስም ሞት ከስልጣን ለይቷቸዋል፡፡ የአሁኑ ጠ/ሚ ኃይለማሪያምንም የሚተካቸው ከራሳቸው ፓርቲ ይሁንታ አግኝቶ ይመጣ እንደሆን እንጂ በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ አሸንፎ  እንደሚመጣ ማሳያ ምንም ተስፋ የለም፡፡

የኬኒያ ዲሞክራሲ ባለፉት ኃምሳ ዓመታት በበርካታ ፈተናዎች ተፈትኖ፣ እየነጠረ ችግሮችን እየቀረፈ ስለመሄዱ የዘንድሮው ምርጫ ማረጋገጫ ሲሆን ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን የማይተካ  ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫው ወቅትና ከምርጫው በኋላ የኬኒያ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ መረጃዎችን ለዜጎች በማድረስ ለዲሞክራሲያዊ ሒደቱ ኃላፊነታቸውን በሚገባ በመወጣታቸው ተወድሰዋል፡፡  በተቃራኒው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዕድገታቸው ቁልቁል እንደ ካሮት ሆኖ ዛሬ ላይ ጠፍተው አማራጭ ሐሳቦች የማይስተናገዱበት ደረጃ ላይ እየደረስን ነው፡፡

ገለልተኛው የኬኒያ ምርጫ ቦርድ  በተለይ በዘንድሮው ምርጫ ከምንግዜውም በላይ ዜጎች በምርጫው አመኔታ እንዲያድርባቸው አስችሏል፡፡ በተገላቢጦሽ ታላቅ አቅም እንዳለው በታዛቢዎች የተነገረለት የኢትዮጵያው ምርጫ ቦርድ፣ አቅሙን በመጠቀም በዘረጋቸው የምርጫ መዋቅሮች ይበልጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫን እንዲሸሹ አደረገ እንጂ  ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫን ማከናወን አልቻለም፡፡ በሕዝብም ዘንድ ያለው ታማኝነትም ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው በተቋማት አለመተማመን በምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል  ነው፡፡

በኬኒያ ምርጫ የሕዝብ ተሳትፎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሮ ፉክክሩ አንገት ለአንገት ደርሶ የዓለምን ሕዝብ በአንድ ላይ ልብ ሲሰቅል፣ ብዙዎች በአገሪቱ የእርስ በእርስ ብጥብጥ ይነሳል ብለው ቢገምቱም የሆነው ግን እንደዛ አልነበረም፡፡ በተለይ ራይላ ኦዲንጋ መሸነፋቸውን በፍርድ ቤት እንደሚሞግቱ ሲናገሩ አገሪቷ በጎሳ ግጭት ትናጣለች ብሎ ያልገመተ አልነበረም፡፡ ራይላ ግን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብለው ኬኒያ ከሁለም እንደምትበልጥ ለዓለም ሲያበስሩ የኬኒያ ፍርድ ቤት ገለልተኛ አቋም እንዳለው ጭምር ዓለም እንዲያውቅ አድርገዋል፡፡ ይህንን መሰል ክስተት በኢትዮጵያ ለማየት የ1997 ምርጫን ተከትሎ ወደእስር ቤት የገቡ መሪዎችን እና የፍርድ ውሳኔን ያስታውሷል፡፡
------
*በዚህ ጽሑፍ ሙሉ ስማቸው ካልተጠቀሰ በስተቀር ኬንያታ ማለት ጆሞ ኬንያታ ለማለት ነው፡፡ ልጅየውን መጥቀስ ስንፈልግ ኡሁሩን ተጠቅመናል፡፡
**በተመሳሳይ ኦዲንጋ ማለት ኦጊንጋ ኦዲንጋ ማለት ሲሆን ልጃቸው ራይላ በሚል ተጠቅሰዋል፡፡

No comments:

Post a Comment