Thursday, September 18, 2014

የቀድሞው “የአብዮት አድናቂ” ኑዛዜ (“Confession of the Ex-Revo” )

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ
 
ርዕሱን  አላስታውሰውም ‘ንጂ እ.ኤ.አ በ2011 Arab Uprising በመባል የሚታወሰውን አብዮትተከትሎ፣ ኢትዮጵያውያን ፌስቡከኞችም (በተለይ ዲያስፖራ የሚገኙ) ግንቦት 20 ላይ (ልክ በኢሕአዴግ የ20ኛ አገዛዝ ዕድሜ)   “Anger day” በሚል በፌስቡክ አብዮትመጥራታቸውን ተቃውሜ አንዲት ጽሑፍ ጽፌ ነበር፡፡ በዓመቱ ደግሞ ‹‹ አብዮት ወረት ነው›› በሚል ርዕስ በፌስቡክ አብዮት ለማስነሳት ፍላጎት ያላቸው በርካቶች እንዳሉ ገልጬ ነገር ግን ይጎድላቸዋል የሚባሉትንነገሮች ዘርዝሬ ጽፌ ነበር፡፡ በነዚህ ሁለት ጽሑፎች ላይ፣ ላዩን አብዮትን የተቃወምኩ ቢመስልም እውነታው ግን ጽሑፎቹ በተጻፉበትወቅት ሕዝቡም፣ ተቃዋሚ ልሂቃኑም፣ ሁኔታዎቹም ለአብዮት ዝግጁ አይደሉም የሚል ዝንባሌ ማሳየቱ ነበር፡፡
ከሌላ ዓመት በኋላደግሞ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል ርዕስ ተከታታይ ጽሑፎችን በ‹‹ዞን 9›› ላይ በግል ተነሳሽነት ማስፈር ጀምሬ ነበር፡፡ ጽሑፉን የጀመርኩት ‹‹ኢሕአዴግ ሥልጣኑን በምርጫ ይለቃል?›› በሚል ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹አይለቅም›› የምልባቸውን ምክንያቶች ካስቀመጥኩ በኋላ የለውጥ አማራጭ የምላቸውን (አብዮት፣ሰላማዊ አለመታዘዝ /civil disobedience/ የመሳሰሉትን) በየዘርፉ እየቀነጫጨብኩ ለማሳየት ነበር ዓላማዬ ከዚያም ‹‹የለውጥ ፍርሃት››፣ ‹‹የሥርዓት ለውጥ እና ሃይማኖት››፣ ‹‹የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት እና የማኅበራት ሚና›› የሚሉ ርዕሶችን በማንሳት በሐሳቦቹ ላይ በሐቀኝነት ለመከራከር ጥረት አድርጌያለሁ (ከዚህ በላይ አልገፋሁበትም እንጂ)፡፡ በበኩሌ ስለአብዮት በደንብ ያነበብኩትም፣ ያሰብኩትም፣ የጻፍኩትም፣ የተረዳሁትም ያኔ ነበር፡፡ ያኔ በአብዮት ላይ የነበረኝ እምነት ተሸርሽሮ ግማሽ ደርሶ ነበር፡፡ ተንጠፍጥፎ ያለቀው ግን አሁንም በዓመቱ (በ2006 አጋማሽ) ነው፡፡ አንባቢ ከአብዮት አድናቂነት ወደ ዝግመተ ለውጥ አራማጅነት (በ ‹‹ያ ትውልድ›› ሰዎች አጠራር ከRevo ወደ Sabo) የተሸጋገርኩበትን የሐሳብ ዳገት (ከፈለጋችሁ ቁልቁለት በሉት) ይረዳ ዘንድ በመጠኑ ዘርዘርአድርጌ ማስረዳት አለብኝ፡፡ (ታዲያ አብዮት አድናቆቱም ቢሆን ከወረቀት እንዳላለፈ ልብ በሉልኝ)፡፡
እነዚያን ተከታታይ ጽሑፎች በጻፍኩበት ሰሞን  ‹አብዮት ‹‹እቆጣጠረዋለሁ›› ብለው ያሰቡትንነገር ግን ድንገት ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችል እሳትን መለኮስ› እንደሆነ እያሰብኩ ባለሁበት ሰሞን ግብጻውያን ሙርሲን ለመጣል ያምጹ ጀመር፡፡ የግብጹ ድጋሚ አመጽ (አብዮት) በጣም የተዘበራረቀ ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ሙርሲ እኔ በግሌ ከማምንባቸውና ቋሚም ከሆኑ የዲሞክራሲ መርሆች እያፈነገጠ ነበር፡፡ ስለዚህ የግብጾች ማበይ ምክንያታዊ ነው ብዬ አምኛለሁ፤ እንዲያውም ሕዝብ አንዴ ‹ከነቃ አይሆንም ዕቃ› ብዬ ነበር፡፡ የግብጽ ሕዝብ የሚፈልገውን ዓይነት ሥርዓት እስከሚያገኝ እያበየ ይቀጥላል የሚል ግምት ነበረኝ- ልክ እንደ ፈረንሳዮቹ ተከታታይ አብዮቶች፡፡  ነገር ግን የግብጽ ሕዝብ እያበየ ቢቀጥልም እንኳን የፈለገውን ላያገኝ እንደሚችል የተረዳሁት ወታደራዊ ክንፍ ቀስ በቀስ አገሪቱን በአብዮቱ ተከልሎ ሲጠቀልላት ስመለከት ነበር ፡፡ ከአገራችን የደርግ አመጣጥ አልለይ ብሎኝ ‹አብዮቶች ሁሉ አንድ ናቸው እንዴ?› እስከሚያስብል ድረስ ተመሳስሎብኝም ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ፕሬሶች በአንዳች ተዋስኦ ይናጡ ጀመር፡፡ ተዋስኦው የተጀመረው የጃዋር መሐመድን ‹ኦሮሞ ቅድሚያ›(Oromo First) የአልጄዚራ ምላሹን ተከትሎ ነበር፡፡ ብዙዎች ይሄን ወቅት የሚያስታውሱት እንደአላስፈላጊ የንትርክ ወቅት ቢሆንም፣በበኩሌ ብዙዎች ቆም ብለው አቋማቸውን እና የአቋማቸውን መሠረት እንዲፈትሹ፣ በታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ኩነቶች ላይ ንባባቸውን እንዲቀጥሉ ያስታወሰ መልካም አጋጣሚ ነው ባይ ነኝ፡፡ ይህ አጋጣሚ በስመ ተቃዋሚ (dissent) የአንድ ኢሕአዴግን ከሥልጣን መውረድ ብቻ እንደ ለውጥ ግብ አድርገን በጋራ ስንንቀሳቀስ የነበርን ተቃዋሚ ግለሰቦች እና ቡድኖች እርስ በርስ ያሉትን ልዩነቶች እና ልዩነቶቻችንን የምናቻችልባቸውን መንገዶች እንድናስተውል መንገድ ፈጥሯል፡፡ ብዙዎቻችን የማንፈልገውን እንጂ የምንፈልገው ምን እንደሆነ በቅጡ እንደማናውቅ፣ትግላችን ከመርሕ ይልቅ በእልሕ እንደሚመራ ያጋለጠ፣ ራሳችንን እንድንገመግም ያስገደደ አጋጣሚ ነበር፡፡
ከዚህ ድንጋጤ ውስጥነው ‹አምባገነን መሪዎቻችን ከሕዝብ ጉያ የወጡ› የአስተሳሰብ ችግር የወለዳቸው የመሆናቸው ሐቅ ዘልቆ የገባኝ (ወይም genuinely comprehend ማድረግ የተቻለኝ) ስለዚህ አብዮት ሲፀነስ ዓላማው ባልተለወጠ ሕዝብ ላይ የተለወጠ መሪ ማስቀመጥ ቢሆንም ሲወለድ ግን አንድም ያልተለወጠ ሕዝብ የተለወጠ መሪ መውለድ ስለማይችል፣ አንድም ደግሞ የተለወጠ መሪ እና ያልተለወጠ ሕዝብ  መዋሐድ ስለማይችሉ፣ አብዮቱ (ዓላማው) ይጨናገፋል፡፡
በዚሁ ጊዜ ነበር የቅርብጊዜ ምሳሌያችንን የአረብ አብዮትን መልሼ በወፍ በረር ለመገምገም የተገደድኩት፡፡ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ…. ከተሳካው የከሸፈው፣ከለማው የወደመው ይበዛል፡፡ የአምባገነን መገርሰስ ብቻውን ለውጥ አያመጣም፤ ከነዚህኞቹ ለውጦች ይልቅ የእኛው ፊውዳሊዝምን ገርስሶ- ወታደራዊ አምባገነንነትን ያመጣው አብዮት የተሻለ ኪሳራ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ (እዚህጋ በኢሕአፓ፣ መኢሶን እና ሌሎችም የደርግ ፓርቲዎች መካከል የተደረገው የድኅረ አብዮት የሥልጣን ሽኩቻ ሳቢያ የጠፋውን ሕይወት ሳንቆጥር መሆኑ ነው፡፡) ከትንሽ ጊዜ በኋላ ደግሞ በብርቱካናማ አብዮቷ የምትደነቀው ዩክሬን አበየች፡፡(‹“የተውኩትን ነገር ተነግሬ፣ ተመክሬ ባገር ምን ጎትቶ አመጣብኝ፣ የአብዮትን ነገር?" Another revolution? ብዬ ትዊት አድርጌም› ነበር) አብዮቷ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የአካሏ ክፋይ የሆነችው ክሬሚያን በማሳጣት ይጀምራል፡፡ ምዕራብ ዩክሬናውያን ሲያብዩ ‹የአገራችን መንግሥት ከምዕብራባውያን ይልቅ ምስራቃውያን (ራሺያ….) አደላ› ብለው ቢሆንም በውጤቱ ግን ጭራሽ ራሺያ ክሬሚያን ጠቅልላ አረፈችው፡፡ልብ በሉ! አብዮቱ ከተነሳበት 360 ዲግሪ ዞሮ ተጠናቀቀ፡፡ ለነገሩ አልተጠናቀቀም፤ አሁን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ተሸጋግሯል፡፡
ይኼኔ ነበር በግል ጦማሬ ላይ ጥር 2006 ‹‹Are revolutions meant to be betrayed?›› ብዬ በመጠየቅ የጻፍኩት፡፡ ዜጎች አብዮትን ሲጀምሩት የማይታዩ ችግሮች ሲጨርሱት የሚስተዋለው ‹ሌባ ሲካፈል እንጂ ሲሰርቅ አይጣላም› ነበር የጽሑፌ አንኳር ሐሳብ፡፡ ‹‹ሌባ›› ያልኳቸው  በሕዝባዊ አብዮት ስም የግል ሕልማቸውን የሚያሳኩ አጀንዳ ያላቸውን ቡድኖች (interest groups) ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ እውነታ ደግሞ እነዚህ ዓይነቶቹ interest groups ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በአብዮት ለውጥ አማጭነት ተስፋ ስቆርጥ የመጀመሪያ ጥያቄዬ ‹‹ሳያብዩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል?›› የሚል ነበር፡፡ የመጀመሪያ መልሴ ‹‹እንግሊዝ›› ነበረች፡፡ የእንግሊዝ ሕዝብና መንግሥት በሕግ የበላይነት ላይ ለማንም ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ የዓለምን ግማሽ በገዙበት ጊዜም አሁንም አብየው አያውቁም- እንግሊዛውያን፡፡ ምክንያቱም ተወያይተው ችግራቸውን መፍታት ይችላሉ፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሲለወጡ ሁሉም በሰላም ይካሄዳል፡፡
ይህንን የመጨረሻ አቋሜን ያውቅ የነበረ ወዳጄ፣ ‹‹እህ አሁንስ?›› አለኝ ‹አብዮት ልታስነሳ አሲረሃል› ተብዬ ተጠርጥሬ ከታሰርኩ በኋላ  ሊጎበኘኝ መጥቶ፡፡ ‹‹አየኸው አይደል፣ ያለአብዮት ለውጥ እንደማይመጣ?›› የሚገርመው፣ የኔና የጓደኞቼ በሕገ-ወጣዊ ማንአለብኝነት መታሰርና፣ የመንግሥት (ፖሊስ) ተጠያቂነት ማጣት ውስጥም ሕዝባዊ አለመለወጥ ነው የሚታየኝ፡፡ መንግሥት አሁንም ቢሆን የሚያስጨንቀው ‹‹የውጭ ኃይሎች ጫጫታ›› እንጂ የውስጥ ሰዎች ጥያቄ አይደለም፡፡ በእኛ ላይ የደረሰው (ሐሳብን በመግለጽ ጦስ መታሰር) በሌሎች ላይ ሲደርስ የነበረ፣ እየደረሰ ያለ ፣ ወደፊትም የሚደርስ መሆኑ ቢታወቀውም ሕዝባችን ግን ‹‹መብቴን ማስጠበቅ አለብኝ›› ከማለት ይልቅ ‹‹ዝም ብል ይሻለኛል›› (ጎመን በጤና) mode ውስጥ ነው፡፡ ሕዝብ ገና አልተለወጠም፤ የለውጥ ጣዕሙም የገባው አይመስልም፡፡ ሌሎች ሰላማዊ የትግል አማራጮችም ገና በኢትዮጵያ አልተሞከሩም፡፡ ሕዝቡ ጣዕሙን የማያውቀውን ለውጥ ከመስጠት በፊት ደግሞ የለውጡን ጣዕም አውቆ ለውጡን ራሱ ጠይቆ፣ ራሱ እንዲያመጣው ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ እንግሊዛውያኑ እንደሚሉት ‹ጋሪው ከፈረሱ ቀድሞ› አይሆንም! ለወዳጄም ይህንኑ ሃሳቤን ነበር የነገርኩት፡፡
ለነገሩ ይህንን ሁሉአልኩ እንጂ ክፍሉ ታደሰ በ‹‹ያ ትውልድ›› (ቅጽ 1) ላይ  ‹ኃይሌፊዳ በ1965 በኢትዮጵያ በ25 ዓመት ጊዜ ውስጥ አብዮት ይነሳል ብዬ አልገምትም ብሎ ነበር› እንዳለው ካልሆንኩ በቀር እኔም በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ይነሳል የሚል ምንም ግምት የለኝም፤ በመጨረሻም በአቤ ቶክቻው ዋዘኛ አባባል ‹‹ካጠፋሁ፣ልጥፋ!››

1 comment:

  1. This is the mind of the new generation, flexible, self assessing and a mind with a working feedback system!! I am so proud of you Lill'le Befekadu, for you to actually asses your position and take us to the journey of self discovering and rediscovering. That is courageous. You know Lill'le brother sometimes what we do unlearn is more important than what we do actually learn.

    This is the kind of mind Ethiopian needs not a fixated mind as it is common with the older generation. We need a mind with a working feedback system, a mind that can actually think, assess, adapt not a mind blinded or pinned by hatred. We don’t need a mind floating in the ‘up there’ utopian imagination... , we need a mind that is not enthralled by imagination, hatred, narrow spanned result, we need a mind that can actually see the reality as it is and adapt!!

    Lill'le brother I am proud of you, I wish you a more inward self look, and an inward look to our collective self.

    ReplyDelete