Tuesday, April 9, 2013

#Ethiopia: የአለም ዋንጫው ለኢትዮጵያ ምኗ ነው?


በጌታቸው ሺፈራው

በአሁኑ ወቅት የአገራችን ወጣት  ትኩረት የሚሰጠው ነገር እግር ኳስ ሆኗል፡፡  ወጣቱ ለእግር ኳስ ብቻ የሚሰጠውን ትኩረትም አንዳንዶቹ የስርዓቱ ወጣቱን የማደንዘዣ ስልት ውጤታማነት ማረጋገጫ አድርገው ይወስዱታል፡፡ በአገራችን በአሁኑ ወቅት ከማይታገዱት የውጭ ጣቢያዎች መካከል የቀሩት የእግር ኳስ ማስተላለፊያ ጣቢያዎች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም አሁን አሁን ሥርዓቱ ‹‹ያመነው ፈረስ›› አደጋ ላይ እየጣለው ይመስላል፡፡  ለይስሙላህም ሰንደቅ ዓላማ መከበር ሳይጀምርና ካድሬዎች ሰንደቅ ዓላማ ሲያዩ ይደነግጡ በነበረበት ወቅት  ጀምሮ  ወጣቱ ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ የሚገኘው አዲስ አበባ ስታዲየም ብቻ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም ብዙዎቹ ሥርዓቱ የማይፈልገው ‹‹የአገር ፍቅር ያለው አዲስ አበባ ስታዲም ብቻ ነው›› እስከማለት ደርሰዋል፡፡ 

የአፍሪካ ዋንጫውና የኢትዮጵያውያን  

ኢትዮጵያውያን ለሶስት ዐሥርት ዓመታት ተለይተውት የቆዩትን የአፍሪካ ዋንጫ በተቀላቀሉበት በዚህ አመት ኳስ ወጣቱ ደነዘዘበት ከሚባለው ‹‹እግር ኳስ›› በላይ  ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ የብሔራዊ ቡድናችን ተሳትፎ ኢትዮጵያን በርሃብ ለሚያውቋት አፍሪካዊያንና የዓለም ሕዝብ አዲስ የአጨዋወት ዘይቤ፣ የደጋፊ ስሜትና ድምቀት እንዲሁም ሊረሳ ተቃርቦ የነበረውን ሰንደቃችን አሳይተዋል፡፡ ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያም በደቡብ አፍሪካ የተገኙት ደጋፊዎቻችን ድምፃቸውን ለማሰማት ሞክረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ድምፃችን ታፍኗል ያሉትም ሆነ የአገራችን ፖለቲካ ምኅዳር ተጠርቅሞባቸው በጥገኝነት የሚገኙት ተቃዋሚዎች  ብሔራዊ ቡድናችንን ከመደገፍ ባሻገር ለጊዜው መንግሥት ሊዘጋው ባልፈለገው ዲ ኤስ ቲቪ በኩል የኢትዮጵያውያንን ድምፃቸው ሳይታቀብ አሰምተዋል፡፡ መንግሥት ብሔራዊ ቡድናችን  የአቶ መለስን ቲሸርት ለብሶ  የአፍሪካን ዋንጫ ለአቶ መለስ መታሰቢያ ያደርገዋል  በሚል ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም የእነማንዴላዋ አገር ላይ ከካድሬነት ይልቅ ነጻነትን  ከደጋፊዎቻቸው የተማሩት ተጫዋጮቻችን  የደቡብ አፍሪካ ሜዳ በእብይተኝነታቸው አሸንፈው ተመልሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ ብሔራዊ ቡድናችን በመጀመሪያዋ ጨዋታ ነጥብ አስጥሎ ይዟት የወጣውን የባለፈው ዓመትን ሻምፒዎን ዛምቢያ ያልተናነሰ ሽንፈት ደርሶበታል ለማለት ይቻላል፡፡

የአለም ዋንጫውስ?

ጥቋቁሮቹ አናብስቶች በአፍሪካ የተሻለ የእግር ኳስ ደረጃ ያላትና የዓለም ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫን ያስተናገደችውን ደቡብ አፍሪካን በአገሯ ነጥብ አስጥሎ፣ ቦትስዋናንና ማዕከላዊ አፍሪካን አሸንፎ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያውን  በሁለት ነጥብ ልዩነት እየመራው ነው፡፡ በዚህ አካሄዱ ወደ ብራዚል  የሚጓዝበትን አጋጣሚ እያሰፋ ነው፡፡ ይህ ከመሠረትነው፣ አንዴ ዋንጫውን አንስተን ስንሳተፍበት ከቆየነው የአፍሪካ ዋንጫ በእጅጉ የተለየ መድረክ ነው፡፡ ይህ 20ኛው  የዓለም ዋንጫ 2006 ዓ/ም ከሰኔ መጨረሻ እስከ ሐምሌ መጀመሪያ  በብራዚል ይካሄዳል፡፡ የዓለም ዋንጫው ኢሕአዴግ 100% (ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል) ለማሸነፍ ከሚፈልገው የ2007 ምርጫ የሚቀድመው ለወራት ያህል ብቻ ነው፡፡ 

ብዙ ሳይታሰብበትም ቢሆን በአፍሪካ ዋንጫ የተቃዋሚዎቻችን ድምፅ፣ የሕዝባችንና የእግርኳሳችን ውበት፣ የደጋፊዎቻችን ድምቀት  ለሌሎች ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም አስገራሚና የማይረሳ ትዕይንትና ትዝታ ሆኖ አልፏል፡፡  የዓለም ዋናጫ ዐሥራ አምስት ያህል ወራት ይቀሩታል፡፡ በአፍሪካው ዋንጫ ብዙም ሳያስቡበት ያን ያህል ድምፅ ማሰማት የቻሉት ተቃዋሚዎቻችንና ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዓለም ዋንጫ  ከዚህ የተሻለ ዝግጅት አድርገው ሊጠባበቁት እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ከምንም በላይ ብራዚል ድምፃቸውን ለሚያሰሙት ኢትዮጵያውያን አመች ትመስላለች፡፡ አፍሪካ ውስጥ ከሚኖረውን ወደደቡብ አፍሪካ ካቀናው   ዲያስፖራ ይልቅ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የአገራችን ሕዝብ ወደ ኳሷ አገር ብራዚል ለማቅናት ይቀናዋል፡፡ ዲያስፖራው እስካሁን ገንዘብ ለማሰባሰብ ወይንም ለስብሰባ ተወካዮቹን በእየአህጉሩ ሲልክ ከነበረው በተቃራኒ ራሱ አገሩን ወክሎ ወደ ብራዚል ለመሄድ  የሚያስችለውን ዕድል ብራዚል አዘጋጅታለታለች፡፡  የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ ዋንጫም በላይ ለማየት የሚያጓጓ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከአፍሪካ ዋንጫ የተሻለ እንዲመርጡት ያደርጋል፡፡ በዚህ መድረክም ኦባንግ ሜቶ ወይንም ታማኝ በየነን ሳይጠብቁ ኢትዮጵያውያን  ከደቡብ አፍሪካዎቹ ደጋፊዎቻችን የተማሩትም እና ጊዜ ገዝተው ያጠናከሩትን ሰላማዊ የትግል ስልት ለዓለም ሕዝብ እንደሚያቀርቡ የሚያጠራጠር አይሆንም፡፡ 

የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ  እስከ 500 ሺሕ ደጋፊዎች ሊሳተፉበት እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የዳያስፖራ አባላት እንዳሏት ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በሰሜን አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ የሚኖር ነው፡፡ ከዚህ ዲያስፖራዋ መካከል 0.5 በመቶው እንኳ ወደ ብራዚል ቢያቀና 10 ሺሕ ያህል ደጋፊዎች ይኖሩናል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ  ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችም ወደብራዚል እንደሚያቀኑ አያጠራጥርም፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ ሙስሊም  ለሂጅራ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ከሚሄድ ይልቅ አንዋር መስጊድ የታፈነውን ድምፅ  ብራዚል ላይ ሆኖ ለማሰማት ከብሔራዊ ቡድናችን ጋር ማቅናትን ቅድሚያ የሚሰጠው ይመስለኛል፡፡ ሂጅራው እምነትን በነጻነት ማመን ሲቻል የሚደረግ ነውና በነጻነት ለማመን የሚያስችል ሁኔታን እንደመፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው አይመስልም፡፡ አብዛኛው ኦርቶዶክስም ቢሆን የእምነቱ አባቶች ቅልስ ቤቶች እየፈረሱ ሸንኮራ አገዳ ወደሚተከልባቸው ገዳማት ሄዶ ከመጸለይ ይልቅ ችግሩን ከብራዚል በቀጥታ በሚተላለፈው የዓለም ዋንጫ ሆኖ ቢያሰማ ‹‹ሰመዓት›› የመሆን ዕድል ይኖረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎቻችንም እነ አቶ አየለ ጫሚሶ የፈረሙትን ‹‹ደንብ›› ፈርመው 2007 ምርጫን ከማጀብ ይልቅ ድምፃቸውን ከፍ አድርጎ ሊያስተላልፍላቸው የሚችለውን፣ ከኢቲቪ በእጅጉ በተሻለ ሰዓት የሚሰጣቸውንና ያልተጭበረበረ ውጤት የሚያገኙበትን የብራዚሉን የዓለም ዋንጫ ቢቀላቀሉ  የተሻለ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ በምርጫው ተሳታፊ የሆኑትም ኢትዮጵያ ከሚያደርጉት ይልቅ የብራዚል ሜዳዎች ትልቅ የቅስቀሳ መድረኮች መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡ በእርግጥ ተጫዋቾችችንም ቢሆን ደቡብ አፍሪካ ያሳዩትን እንብይተኝነት ትግል በደቡባዊው አሜሪካ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ ከቻሉ ለቀሪው ትግል ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

በመሆኑም በደቡብ አፍሪካዋ ሞምቤላ ስታዲየም ከነበረው ትግል ይልቅ የብራዚል ቤሌም፣ ቤሎ ሆሪዞንቴ፣ ብራዚላ፣ ካምፖ ግራንዴ፣ኩያባ፣ ኩሪቲባ፣ ማኑስ፣ናታል፣ ፖርተፐአልግሬ፣ሬሲፌ፣ ኦሊንዳ፣ ሪዮብራንኮ፣ሪዮ ዲጀነሮ፣ሳልቫዶርና ሳኦ ፖሎ ለኢትዮጵያውያን አመች ምሽጎች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ በቅርቡ ኢሕአዴግ ባካሄደው  በ9ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ብራዚል በክብር እንግዳነት እንድትሳተፍ  ተጠርታ የነበረች ቢሆንም ‹‹አይመጥነኝም!›› በሚመስል መልኩ ሳትሳተፍ ቀርታለች፡፡ ምናልባት ከዚህ የኢሕአዴግ ጉባኤ በኋላ በተደረገው የ‹‹ብሪክስ (BRICS)›› ስብሰባ የዓለም ዋንጫን በተራ እያስተናገዱ ያሉት የደቡብ አፍሪካና  የብራዚል መሪዎች ስለ ዓለም ዋንጫ፣  ምድባቸውን እየመሩ በመሆናቸው ሊሳተፉ ስለሚችሉ አገራት ሊያወሩ ስለ ኢትዮጵያ ደጋፊዎችም የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካን ምክርና መረጃ ሳትጠብቅም ቢሆን ብራዚል ለአፍሪካ ዋንጫ ድምቀት የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን  አስተውላቸዋለች፡፡ በመሆኑም ብራዚል እራሷ ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫውን ብትቀላቀል የምትቀበላት በደስታ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫው ዓለማቀፋዊ ተደራሽነትምና የኢትዮጵያውያን በዓለም ዋንጫ የሚያደርጉት የሰላማዊ ትግል ተሳትፎ ምናልባትም ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ  ተቃዋሚዎች ጠንካራ ተቃውሞ የሚያደርጉበት ‹‹የትግል ቦታና ድጋፍ›› ያገኙ ያህል የሚታይ ነው፡፡ መቼም የ20ዎቹ ሀብታም አገራት ሰብሰባ ውስጥ በአንድ ጋዜጠኛ  ለሴኮንዶች የሚደረግን ተቃውሞ ትልቅ የሰላማዊ የትግል ስልት መሆኑን ያመነበት፣ ውጤቱንም ያየው ዲያስፖራው ማኅበረሰባችን  በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በቀጥታ በፍቅር የሚታየውን እና ፖሊስ ሳይከለክለው ለ90 ደቂቃዎች ኢሕአዴግን አንገት ማስደፋት የሚችልበትን የብራዚሉን መድረክ እንዲሁ ያልፈዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ብሔራዊ ቡድናችን  ባያልፍስ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምድቡን እየመራ ነው፡፡ ምድቡን መርቶ ሲያጠናቅቅ ወደብራዚል ለማለፍ ከ10ሩ የምድብ አሸናፊ ውስጥ ከአንዱ ጋር በደርሶ መልስ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ቡድኑ እየታየ ያለው መሻሻልና በአፍሪካ ዋንጫ በዛምቢያና ናይጀሪያ ላይ ያሳየው ብቃት ብሔራዊ ቡድኑ ሊያልፍ ተስፋ ሰጭ ነው፡፡ ሆኖም ኳስ ነውና ሊሸነፍም የሚችልነት አጋጣሚ የማይታበል ነው፡፡ የብሔራዊ ቡድናችን በብራዚል መገኘቱ ደጋፊዎችም ለሚያሰሙት ድምፅ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ሆኖም ይህ ስሜቱን ሊያቀዘቅዘው ይችላል እንጂ ያጨናግፈዋል ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ አለፈችም አላለፈችም የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ይካሄዳል፡፡ በመሆኑም ተጫዋቾቹ ባይኖሩም ሜዳው ግን ለኢትዮጵያውያን ክፍት ነው፡፡ ደግሞ አፍሪካ የምትልካቸው አምስት ተወካዮችን እና ሌሎችም በሕዝባችን ዘንድ ተወዳጅ ቡድኖች  ብራዚል ላይ ይቀጥላሉ፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከተሰናበተ በኋላም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው እስከመጨሻው ለማለት በሚቻል መልኩ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ ሰንደቅ ዓላማቸውን አውለብልበዋል፡፡ በመሆኑም የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድናችን ሊያጠናክረው የሚችለው እድል እንጂ በእሱ ብቻ ሊወሰን የሚችል አይመስልም፡፡ በተለይ ኋይት ሀውስና ሌሎቹ ዲያስፖራው ቀድሞ ድምፁን ሲያሰማባቸው የነበሩ ቦታዎችና አጋጣሚዎች አሁን አሁን እየተለመዱ ወይንም እየቀነሱ በመምጣታቸው የሚያሳድሩት ጫና አነስተኛ  መሆኑ ብራዚልን አዲስ ተመራጭ የትግል ቦታ ያደርጋታል፡፡ ምንም እንኳ መሞከሩ የማይቀር ቢሆንም የኢህአዴግ አፀፋም እንቅስቃሴም ቢሆን በብራዚል ቦታ አይኖረውም፡፡ ‹‹ብሪክስ››ን በቀዳሚነት ለምትመራው፣ ለዓለምና ለኢትዮጵያ ሕዝብ 11 በመቶ አደግን፣ ‹‹የመሪ ሌጋሲ››፣ የአባይ ግድብ፣ ‹‹አሸባሪነት››፣ አክራሪነት ድጋፍም ተቃውሞም ሊሆኑ አይችሉም፡፡

ሰንደቁን  እንደ መሳሪያ

ሰንደቅ ዓላማችን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከእኛ ለወሰዱት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ፣ የካሪቢያና ደቡብ አሜሪካ አገራትም መለያ ምልክት ነው፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ ግን ብዙው የዓለም ሕዝብ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያሉትን የሰንደቅ ዓላማ  ከኢትዮጵያ ይልቅ የጋና እና የሌሎቹም የአፍሪካ አገራት ምልክትነቱ ያውቀዋል፡፡ እንኳን ድምፅ ማሰማቱ ተጨምሮበት ኢትዮጵየውያን በብራዚል ሰንደቅ ዓላማችን ማስተዋወቁ በራሱ የሚናቅ ዓላማ አይደለም፡፡ በዓለም ዋንጫ ለዓለም የሚተዋወቁት ሰንደቅ ዓላማዋንና ሌሎች ጉዳዮችን ወደዓለም አቀፍ  የማስታወቂያ ተመን ብንቀይራቸው የማይሞክሩ ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ብራዚል የእኛን ሰንደቅ  በምልክትነት ካነገቡት አገራት ደጋፊዎች ጋር በመሆን ተቃዋሚዎች ሰንደቁን ድምፃቸውን ይበልጡን ለማሰማት ሊጠቀሙበት የሚችሉ መሆናቸው ትግሉን የሰንደቁ ቀለማት ያደመቁትና ጠንካራ ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በምልክትነት የሚጠቀሙት ቤኒን፣ ካሜሮን፣ ማሊ፣ ቶጎ፣ ቡርኪናፋሶና ጋናን የመሳሰሉት አገራት ከእነደጋፊዎቻቸው በደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል ባይገኙም ይህን ዕድለኛ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልበው አያጣም፡፡  ደቡብ አሜሪካ የራስ ተፈሪያን መፍለቂያና መኖሪያ አህጉር ነች፡፡ ጃማይካ፣ ትንዳንድና ቴቤጎ፣ ጉያና፣ ዶሚኒካ፣ ግራናዳ፣ ሀይቲ፣ብረዚል፣ አርጀንቲና፣ ፓናማ፣ ሜክሲኮ፣ ፔሩ፣ ኮሎምቢያ፣ ቺሊ፣ ዩራጋይ፣ ቬንዜየላና አጠቃላይ ደቡብ አሜሪካና ካሪቢያን ከ6 ሚሊዮን በላይ ከሚሆኑት የአለም ራስ ተፈሪያን ተከታዮች መካከል  እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የንቅናቄው ተከታይ መኖሪያ ናቸው፡፡ ዕድሜ ለእነ ማርከስ ጋርቬይና ቦብ ማርሌይ እንጂ ከደቡብ አሜሪካና ካሪቢያን አልፈው ከኮንጎ እስከ ጃፓን ይህን ኢትዮጵያን እንደ ጽዮን የሚቆጥረው  በርካታ የእንቅስቃሴው ተከታዮች ተስፋፍተውበታል፡፡ በሁሉም የደቡብ አሜሪካና የካሪቢያን አገራት የራስ ተፈሪያን ማኅበራት ተመስርተዋል፡፡
አብዛኛዎቹ የደቡብ አሜሪካ የራስ ተፈሪያን ንቅናቄዎች ከቀሪው አለም በተሻለ የተደራጁና ስማቸውም ሆነ እምነታቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ ባለቸው ጥልቅ እምነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ባልተናነሰ አንዳንዴም በተሻለ ስለኢትዮጵያ የሚዘምሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡

በራስ ተፈሪያዊያን ዘንድ ኢትዮጵያ የምታከብረው ልደት፣ የእትጌ መነን የልደት ቀን፣ አፄ ኃይለሥላሴ ጃማይካን የጎበኙበት ቀን፣ የአፄ ኃይለሥላሴ ልደት፣ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፣ ኃይለሥላሴ የነገሱበት ቀን  በድምቀት  ይከበራል፡፡  የራስ ተፈሪያን ንቅናቄ የነጻነት ንቅናቄ አንድ አካልና ለአፍሪካ ነጻነት ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው ነው፡፡ እስከአሁንም ድረስ ለአፍሪካ አንድነት፣ ዕድገትና የጥቁር ነጻነት ትኩረት ሰጥቶ ይታገላል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ደግሞ ከራስ ኮፍያ፣ እስከ ቀለበት፣ቀበቶና የጫማ ማሰሪያ ድረስ የተቀደሰ ምልክታቸው ነውና የሚደግፉት የራሳቸው የሆነ ብሔራዊ ቡድን ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ በቋሚነት የምትደገፍ አገር ነች፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ መሳሪያ በመጠቀም ትኩረት ለመሳብ ብራዚል ትልቅ ዕድል ፈጥራለች፡፡ የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ምልክት ደግሞ ለኢትዮጵያውያን የተሰየመ በሚመስል ሁኔታ ‹‹inspiration›› ወይንም መነቃቃት፣ መነሳሳት የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡

በዓለም ዋንጫ የሚጫወቱት አገራት ዋንጫው  ትርፍና ከመዝናኛ  ያላለፈ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ግን ከዚህም  በላይ ዓላማ ይኖረዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲ ግንባታን ከጀመሩት ጋና፣ ዛምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ብቻ ሳይሆን ከዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ ደጋፊዎችም በተለየ ከእግር ኳሱ በላይ ህልውናቸውን የሚወስነው ፖለቲካ ላይ ድምጻቸውን ማሰማታቸውም ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ብራዚል መሄድ ባይችልም ድምፅን ለማሰማት የሚያስችለው መድረክ በስፋት የተከፈተ መሆኑን  አይተናል፡፡ ቡድናችን ለዓለም ዋንጫው ማለፍ ከቻለ ደግሞ ስሜቱም ሆነ ትግሉ ደማቅና ደማቅ ውጤት የሚያመጣ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሶማሊያና ኤርትራም ሳይቀር ወደውጭ ለመውጣት ሌት ተቀን በምንጥርበት በአሁኑ ወቅት ራስ ተፈሪያኑ ቅድስትና የተስፋይቱ ምድር ወደሚሏት ኢትዮጵያ በመምጣት መሬቷን በጫማ ላለመርገጥ ባዶ እግራቸውን እየኖሩባት ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያልቻሉትን ጨምሮ  በብራዚል የሚገኙት ወይንም የሚሄዱት  ራስታዎች  ለአናብስቶቹንም  ሆነ ለደጋፊዎቻቸው  የሚሰጡት ትርጉም እኛ የዓለም ዋንጫን ከምናይበት በተመሳሳይ ከተራ ኳስ በላይ ነው፡፡ ራስታዎቹ ኢትዮጵያውያንን መቀበል ልክ እየሱስ በነበረበት ወቅት ወይንም በቅርብ እርቀት የሚያውቀውንና ከቅድስቷ ጽዮን የመጣ  ሰው እንደማግኘት ያዩታል፡፡ ለዚህም እንደመንፈሳዊ ዜማ ሁሉ በሬጌ ሙዚቃቸውና በሰንደቅ ዓላማችን እንደሚቀበሏቸው የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡

ደቡብ አሜሪካውያን ሌሎች ጭቁኖችን  በመርዳት የሚታሙ አይደሉም፡፡ አርጀንቲናዊ ቼ ጉቬራ የኩባና ቮልቪያን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት ካደረገው ተጋድሎ ላቲኖቹ ድንበር ዘለል ሰብኣዊነትን ተምረውበታል፡፡ ቼ ደቡብ አሜሪካዎችን ነጻ ከአወጣ በኋላም ቢሆን ወደጭቁኗ አፍሪካ በመምጣት ለነጻነት የቻለውን ያህል ታግሏል፡፡ ይህም ላቲኖቹ የዝሆን ቀንድን በኮንትሮቫንድ ከሚያጋብሱት ተራ ዜጎቿ ጀምሮ ለእርስ በእርስ ጦርነት መሳሪያ ለመሸጥ፣ ርካሽ እቃ ለማራገፍ፣ ነዳጅና አልማዝ ለመመዝበር ወደ አፍሪካ ከምትመጣው ቻይና የተለየ ዓላማ እንዳላቸው አስረጅ ነው፡፡ በቼ ጉቬራ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ንቅናቄ አነስተኛ በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ባያቀናም ነጻ ያወጣት ኩባ ግን በክፉ ቀን ደርሳልናለች፡፡ አሁን ስልጣን ላይ በሚገኙት ገዥዎቻችን መንገድ መሪነት እስከድሬዳዋ  የወረረንን ተስፋፊው የሶማሊያ ጦር  ያሸነፍነው በኩባዎች ረዳትነት ነው፡፡  በአጠቃላይ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ብሔራዊ ቡድናችን፣ ደጋፊዎች፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያነገቡ አገራት፣ ራስ ተፈሪያን ተጠቅሞ ትልቅ ትኩረት መሳብ ይቻላል፡፡ ሰብኣዊነትን መሠረት ያደረገ ድንበር ዘለል ትግል አዲሳቸው ያልሆነው ደቡብ አሜሪካዎች በመልክም ቢሆን ለኢትዮጵያውያን ቅርብ በመሆናቸው  በዚህ የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያውያንን ጥምረት የሚፈራ ኃይል ጠያይምና ቀዮችን ላቲኖች አይቶ ሙሉ ሜዳውን ኢትዮጵያውያን እንደያዙት ሊረዳ ይችላል፡፡ መቼም በታሰበው መልኩ ከተሳካ ኢሕአዴግ የዓለም ዋንጫ በብራዚል እንዲዘጋጅ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እጅ አለበት ማለቱ የማይቀር ነው፡፡ ደግነቱ ብራዚል እንደ ሶማሊያ ወታደር የሚልኩባት ወይንም እንደ ኤርትራ የሚዝቱባት አገር አይደለችም፡፡

ተቃዋሚዎቻችን ምን ያህል ይጠቀሙበታል?

ደቡብ አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ምቹ ናት፡፡ ዋናው አጋጣሚውን የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በሥርዓቱ አፋኝነትም ይሁን በራሳቸው ድክመት አጋጣሚዎችን ሲጠቀሙ አይስተዋሉም፡፡ ለአብነት ያህል የየኔሰው ገብሬን መሰዋት እና ሌሎች አጋጣሚዎችን ተቃዋሚዎች  አንድ አገር ወዳድ ዜጋ ከሚያደርገው በላይ ተጠቅመውበታል ለማለት አያስደፍርም፡፡  አንድ የሰላማዊ ትግልን እከተላለሁ የሚል አካል  እንደ ምርጫ፣ የሰዎች መፈናቀል፣ እስራትና የመሳሰሉትን ትልልቅ ክስተቶች  መጠበቅ ባይኖርበትን  እነዚህ ክስተቶች ሲፈጠሩ ግን ለአገር በሚጠቅም መልኩ ማራገብና አጀንዳ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ለምሳሌ ያህል  በግራዚያኒ ላይ የተደረገውን ተቃውሞ ኢሕአዴግ ለጊዜው በማስቆሙ ብቻ መቆም የለበትም፡፡ ተቃዋሚዎችም ሆኖ ሌሎች አካላት  በተደጋጋሚ ሰልፉ  በመጥራት አጀንዳቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ እስኪወጣ አሊያም በግልጽ ምን አገባኝ እስኪል ድረስና ከዚያም በኋላ ተቃዋሚዎች አጀንዳቸው አድርገው ቢንቀሳቀሱ  ትልቅ  የትግል ስልት መሆን የሚችል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕዝብና መንግሥት በየፊናቸው የሚግባቡበት ወይንም የሚጠረጥሩት ምልክት ማስረጽ አስፈላጊ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡ ይህ ስልት በአንድ ወቅት የጀርመኑን ናዚ ይቃወሙ የነበሩ  ወጣቶች ዋነኛ ስልት ነበር፡፡ ፀረ ናዚ ወጣቶች  ናዚ  የምዕራበዊያን ነው ብሎ የሚቃወመውን የፀጉር አቆራረጥና አሠራር፣ አለባበስ፣ ሙዚቃ ሙሉ በሙሉ ወይንም በሙቀራረብ መልኩ አዘውትረው ተቃውሟቸውን ገልጸውበታል፡፡ የጀርመን ሙዚቃዎችን በአሜሪካ የሙዚቃ ስልት ተጫውተው ሥርዓቱ በግልጽ ለመቃወም እንዳይችል ነገር ግን በጥርጣሬ እንዲሞላ አድርገውታል፡፡ የጀርመን ሕዝብ እንደ ፋሽን መከተል ሲጀምር ሥርዓቱ ሕዝቡን በጥርጣሬ መመልከትና በፍርሐት መራድ ጀምሮ ነበር፡፡ አንዳንዴ በመመሳሰል ብቻ የሚታሰሩ ጀርመናውያን ወጣቶች የሥርዓቱን አስከፊነት ሳይወዱ በግድ በማየታቸው ዋነኛዎቹ የስልቱ አቀንቃኞች ሆነዋል፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግራዚያኒን ለመቃወም በተጠራው ሰልፍ  ሰልፈኞቹ ቀይ ቲሸርት ለብሰው ስለነበር ፖሊስ አላፊ አግዳሚውን ቀይ ለባሽ አስሯል፡፡ ሰልፈኞቹ ከእስር ቤት ሲወጡ እስር ቤት የቀረው  ፖሊሶቹ የፈሩት ቀይ ልብሳቸው ብቻ ነው፡፡ ቀይ ልብስ በበርካታ ሰዎች ዘንድ የሚዘወተር የአዘቦት ልብስ ነው፡፡ ‹‹ቫላንታይን›› እና ሌሎች አንዳንድ አጋጣሚዎች ሲሆኑ ደግሞ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ይለበሳል፡፡ ይህን ተከትሎም ቀይ ልብሶችንም  ለኢሕአዴግ አንድ የመቃወሚያ ምልክት ማድረግ ቢቻል  በቤተ መንግሥት ጥግ የሚያልፉትን ጨምሮ የአገራችን ቀይ ለባሾች በሥርዓቱ ላይ ጥርጣሬን የሚፈጥሩ ይሆናሉ፡፡ በአደባባይ ብሶቱን መግለጽ የማይችለው፣ ሚዲያና ጠንካራ ተቃዋሚ ያጣው ወጣት በቀይ ፋሽን  ኢሕአዴግን ማብገኑ የማይቀር ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ኢሕአዴግ ቀይ ለባሹን ሰው ብቻ ሳይሆን አብዛኛው አካሉ ቀይ የሆነውን የቢሾፍቱውን አውቶውስ ሁሉ በአሉታዊነት  አለመመልከቱን እጠራጠራለሁ፡፡  
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይላቸው getcholink@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment