በፍቃዱ ኃይሉ (ከቂሊንጦ እስር ቤት)
አስታውሳለሁ፣ከአራት ዓመታት በፊት የተሰራ አንድ የETV ‹ዘጋቢ ፊልም› ‹‹የግል ፕሬሱ መርዶ ነጋሪ ወይስ ልማት አብሳሪ?›› የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ‹ዘጋቢ ፊልሙ› የመንግስትን አቋም የሚያንፀባርቅ ስለነበር መንግስት መገናኛ ብዙኃን እንዲሆኑ የማይፈልገውንእና የሚፈልገውን በርዕሱ ቁልጭ አድርጎ ነግሮናል፡፡ እርግጥም ‹‹ልማት አብሳሪነት›› ውስጥ ምንም ስህተት የለም፤ ‹‹መርዶ ነጋሪ›› መሆንም የሚወደድ ነገር አይደለም (የሚቀር ባይሆንም)፡፡ ዛሬ ይህችን ደብዳቤ እንድጽፍላችሁ ያነሳሳኝ ‹‹ልማት አብሳሪነት›› በሚል ሥም ተለብጦ እየተሰራ ያለውን ስህተት (በጊዜ ማጣት) ካልተረዳችሁት ወይም ችላ ካላችሁት ቆም ብላችሁየምታስቡበት አፍታ ላውሳችሁ ብዬ በማሰብ ነው (ጊዜ አለኝና)፡፡
በመጀመሪያግን እንድትረዱልኝ የምፈልገው ነገር አለ፡፡ በስመ የEBC ጋዜጠኝነታችሁ የገዢው ፓርቲ ወገንተኛ ናችሁ የሚል ድምዳሜይዤ አልተነሳሁም፡፡ እንደዚያ ቢሆንማ ኖሮ ይህንን ደብዳቤ ልጽፍላችሁ አልወስንም ነበር፡፡ ይልቁንም፣ ወረድ ብዬ የምገልጸውን‹ስህተት› እየሰራችሁ ያላችሁት አንድም በጫና፣ አንድም በፍርሀት፣ አንድም ‹ትክክል› የሰራችሁ እየመሰላችሁ እንደሆነ በማመንነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ዕድገት ገና ጨቅላ በሆነበት አገራችን ሙያችሁን የምታዳብሩበት ሌላ ሰፊ እና ሴፍ (Safe)ተቋም አጥታችሁም ሊሆን ይችላል፡፡ የስራ አጥነት በተጋነነበት የገዛ አገራችን ወር የሚያደርስ ምንዳ እና አበል የሚከፍል ሌላየሚዲያ ተቋም ማግኘት እንደሚቸግራችሁም አላጣሁትም፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ሁሉ የሚበልጡትን ሙያዊ ስማችሁን (career) እናአገራዊ ኃላፊነታችሁን በነዚህ ሰበብ አስባቦች መጨፍለቃችሁን አልወደድኩምና የመናገር ኃላፊነቴን እነሆ!
‹‹ልማት አብሳሪ›› ወይስ ‹‹ይሁንታ አምራች››?
የዞን9 ጦማሪ እና የጋዜጠኝነት መምህሩ እንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል ዞን 9 ላይ ባሰፈረው አንድ መጣጥፍ ‹የመንግስት ጋዜጠኞች› ‹‹ናችሁ›› የተባሉትን ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኝነት›› እንዳልሆኑት ሲናገር የተጠቀመበት ቋንቋ ‹‹ይሁንታ አምራችነት›› የሚለውንነበር፡፡ ቋንቋው ለኔም ገላጭ ሆኖልኛል፡፡ በሕዝብ በጀት የሚተዳደሩ (የመንግስት) መገናኛ ብዙሃን በስመ ‹‹ልማታዊጋዜጠኝነት›› መንግስት ሊያሳካ የቻላቸውን ሥራዎች ብቻ ነቅሶ በማውጣት ማንቆለጳጰስ ‹‹ልማት አብሳሪነት›› ሊባል አይችልም፤ለገዢው ፓርቲ ሕዝባዊ ይሁንታን ማምረት እንጂ!
ነገሬንላብራራው፡፡ ድኅነትን ያልቀመሰ እና የሚወድ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ድኃ የመሆንን ያህል የድኃ አገር ዜጋ መሆንም ያስጠላል፡፡አገራችን ከድኅነት ለመውጣት የምታደርገው መፍጨርጨር የመንግስት ጉዳይ ከሆነው በላይ የሕዝብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከድኅነትመውጣት የሚቻለው ‹‹ልማት›› የሚለውን ቃል ደጋግሞ በመደስኮር አይደለም፡፡ እየተሰራ ያለውን ነገር መካድ ባይገባም እያልተሰራያለውን ነገር እና በስራው ስም እየጠፋ ያለውን ነገርም አብሮ መንቀስ እና ማጋላጥ ያስፈልጋል፡፡ እንደኔ፣ እንደኔ እውነተኛው‹‹ልማታዊ›› ይህንን አጋልጦ፣ ‹አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት› በሁለቱም ሁኔታዎች የሚያጠፋውን መንግስታችንን ማረምየሚችል ሰው ነው፡፡ አሁን የEBC ጋዜጠኞች እያደረጋችሁ ያላችሁት ግን (ቀደም ብዬ በጠቀስኳቸው ሁኔታዎች ተገዳችሁ እንደሆነብጠረጥርም እንኳ) ‹‹ልማትን መደገፍ ማለት ገዢውን ፓርቲ መደገፍ ማለት ነው›› የማለት ያክል ነው፡፡ ልማታዊነት ሌላ በልማትሥም ለአምባገነኖች ይሁንታን ማምረት ሌላ፡፡
ከድኃሕዝብ መቀነት በተፈታ ወይም በሥሙ በተሰበሰበ ገንዘብ የሚተዳደረው እና ደመወዝ የሚከፍላችሁ EBC (ኢብኮ) እኔ ሞክሩትእያልኩ የምጨቀጭቃችሁን ዓይነት ጋዜጠኝነት እንድትሰሩ የማይፈቅድ መዋቅሮች እንዳሉት ሳልጠረጥር ቀርቼ አይደለምይህንን ምክር የጻፍኩላችሁ፡፡ መዋቅሩንም ቢሆን መታገል፣ ችግሩን መነቅነቅ የሥራችሁ አካል ነው እያልኳችሁ ነው፡፡ በርግጥ፣እንዲህ አይነቱ እርምጃ የመረጣችሁትን safe መንገድ አደገኛ (risky) ያደርገዋል፡፡ ቢሆንም በመርሕ እና ሓቅእስከተመራችሁ ድረስ risk ውስጥ ደስ የሚል ነገር አለው (bitter sweet እንዲሉት ዓይነት) እያልኳችሁ ነው፡፡ሞክሩትና አትከስሩም፡፡
‹‹የእናንተ ገነት››፣ ‹‹የእኛ ገሀነም››
እናንተበልማቷ ወደር የላትም፣ ገነት ሆናለች እያላችሁ የምታወሩልንን ኢትዮጵያ ማን እንደምንላት ታውቃላችሁ? ‹‹እቲቪዮጵያ›› - የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ጸሐፊ ቃልኪዳን ይበልጣል ነው ይህንን ሥም ያወጣላት፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ፡፡ በልማቷ ወደርያልተገኘላት፤ ከተማዋ የመብራትና የውኃ፣ ገጠሯ የማዳበሪያ እጥረት ያልገጠማት፤ መልካም አስተዳደር የሰፈነበት፣ ዴሞክራሲእንደፀበል የምንራጭባት ዓይነቷን ኢትዮጵያ እንኳን ኖሬባት መንገድ ላይ አይቻት አላውቅም፡፡ ትዝብቴን ግልጽ ለማድረግእንዲረዳኝ የዘንድሮውን የምርጫ ድራማ እና የኢብኮን አዘጋገብ ላጣቅስ፡፡
ግንቦትወር ላይ በሚካሄደው እና ብዙዎቻችን (አሸናፊውን ከወዲሁ እናውቀዋለንና) ‹‹የተበላ ዕቁብ›› እያልን የምንጠራውን ምርጫ2007 አስቡት፡፡ መንግስታችንን አስቡት፡፡ ምርጫ ቦርድን አስቡት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስቧቸው፡፡ የኢብኮ ዘገባንአስቡት፡፡ ኢብኮ የኢሕአዴግ ተቀናቃኝ የሆኑትን ፓርቲዎች ደካማ ጎን የሚያብጠለጥልበት፤ የኢሕአዴግ -ግንባር አባላት የሆኑፓርቲዎችን ልደት ወይም አንዳች ሰበብ እየፈለገ የሚያቆለጳጵስበት፤ ምርጫ ቦርድ ሕገ-መንግስታዊ ግዴታውን ንቆ ወገንተኛየሆነበት (በነገራችን ላይ ‹‹ወገንተኛ የሆነበት›› የሚለውን ‹‹ለማን›› እንደሆነ ሳልጠቅስ ገና ገብቷችኋል እና ማስረጃማጣቀስ አያስፈልገኝም፡፡) ብሎም በዜናውም፣ በ ‹‹ዘጋቢ ፊልሞች››ም ሰበብ ለገዢው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የሚደረግበትዴሞክራሲያዊ ስርዓት - እውነት እንነጋገርና ምን ዓይነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው? እውነት የኢትዮጵያ ችግርየመሰረት ድንጋዮች በማስቀመጥ የሚፈታ ነውን? እውነት ኢብኮ የሚያቀርባቸው ሳምንታዊ ፌስቲቫሎች የሕዝብ ገንዘብ በከንቱከማባከን በላይ ፋይዳ አላቸውን?
እናንተ‹‹አሸወይና ነው›› እያላችሁ በእልልታ የምታቀርቡልን ዜና እኛ ‹‹እዬዬ›› የምንልበትን ጉዳይ መሆኑ ‹‹እናንተ››ን እና‹‹እኛ››ን የሁለት አገር ሰው እያስመሰለን ነው፡፡ እናንተ እና እኛ ግን እናንተም እኛን እኛም እናንተን መሆን የነበረብንየአንድ አገር መዳፍ ሁለት ጣቶች ነን፡፡ አንዳችን ጠፍተን አንዳችን መትረፍ የማንችል መንትዬዎች፡፡ ኢትዮጵያችንኢትቪዮጵያን ብትመስልልን አንጠላም፡፡ የምንጠላው በሐሰት የተሸከመችው ስም ከብዷት እንዳትሰበር ነው፡፡
ይህንን ለናንት፣ ለEBC ጋዜጠኞች የጻፍኩትን ግልጽ ደብዳቤ እያነበበ እንዳለመብሰል (naivity) የሚቆጥርብኝ ሰው ጥቂት እንደማይሆንእገምታለሁ፡፡ በናንተ ጉዳይ naive ለመባል የደፈርኩት የEBCን ኩሸት በፍቅር የሚዋሹለት ‹‹ጋዜጠኞች›› ያሉትን ያክልመውጫው እንደመግቢያው አልሰፋ ብሏችሁ የቆያችሁም አላችሁ ብዬ በመገመቴ ነው፡፡ መውጫው ቀላል ነው፡፡ EBCን ከላይ እስከታችየውሸት ቋት ያደረገውን አሰራር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መታገል፤ ከውስጡ፡፡ ዘላለም ለኢፍትሐዊነት ታዛዥ ሁኖ የውሸት ከመኖርአንድ ቀን የእውነት ጀግና ሁኖ መባረር - ቢያንስ አንድ ገጽ የሚወጣው የሕይወት ታሪክ ይወጣዋል፡፡
የዞን9 ማስታወሻ
ይህ ጽሁፍ በጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ተጽፎ በፍቱን መጽሄት ላይ የታተመ ሲሆን ለኢንተርኔት አንባብያን ይበቃ ዘንድ መልሰን አትመነዋል፡፡
ይህ ጽሁፍ በጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ተጽፎ በፍቱን መጽሄት ላይ የታተመ ሲሆን ለኢንተርኔት አንባብያን ይበቃ ዘንድ መልሰን አትመነዋል፡፡
No comments:
Post a Comment