Wednesday, April 1, 2015

የዞን ዘጠኝ ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የአቃቤ ሕግ ምስክሮች የመስማት ሂደት

በቀልድ የታጀበው ምስክሮችን የመስማት ውሎ -የዞን9 ጦማርያን እና ወዳጅ ጋዜጠኞች ላይ
የኅሊና እስረኞቹ አጥናፍ፣ ማኅሌት፣ ዘላለም፣ በፍቃዱ፣ ናትናኤል፣ አቤል፣ ኤዶም፣ ተስፋለም እና አስማማው፡፡
ቀን አንድ (መጋቢት 21)
በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው የማስረጃ መስማት ውሎ ዛሬ ምስክሮችን በማስማት ተጀምሯል፡፡ በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ ጉዳዬን ያስረዱልኛል ያላቸውን 17 ምስክሮች ያስመዘገበ ሲሆን 15ቱ በፍርድ ቤቱ ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ አቃቤ ህግ ችሎቱ በዝግ ችሎት አንዲሆን የጠየቀ ሲሆን ምስክሮቼ እና የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ችሎቱ በዝግ ሊሆን ይገባል የሚለውን አቤቱታውን ጠበቆች በከፍተኛ ደረጃ ተቃውመውታል፡፡ ምስክሮቹ የጭብጥ ምስክሮች ሳይሆኑ ፍተሻን የታዘቡ የደረጃ ምስክሮች በመሆናቸው እና ስማቸውም በግልጽ ተከሳሾች ጋር ስለደረሰ ምንም አይነት የደህንነተ ስጋት የለባቸውም ከሚለው የጠበቆች ክርክር በኋላ ፍርድ ቤቱ በጉዳዬ ላይ ተወያይቶ ለመወሰን ረፍት ወስዷል፡፡ በዚህም መሰረት የአቃቤ ህግን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ችሎቱ በግልጽ ሆኖ መስክሮች ምስክርነታቸውን እነዲያሰሙ ታዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክሮች አነማን ላይ አንደሚመሰክሩ እና ምን አንደሚመሰክሩ በተጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱም በጠበቆቹ ስለተነሱት ነጥቦች የአቃቤ ህግን ምላሽ ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግም በዛሬው ዕለት የቀረቡት ምስክሮች በ2ኛ፣ በ3ኛ፣ በ5ኛ፣ በ6ኛ፣ በ7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ( በስድስቱ የዞን9 ጦማርያን ላይ እና በጋዜጠኛ አስማማው ላይ ) ላይ እንደሚመሰክሩ ገልጾ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቡድን በብርበራ ያገኛቸው ማስረጃዎች ከተከሳሾች የተገኙ ስለመሆናቸው ያስረዱልኛል ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በምላሹም መሰረት የአቃቤ ህግ ምስክሮች ምስክርነታቸው ሰጥተዋል፡፡ ምስክርነታቸው ሲሰጡ በነበረበት ወቅት የተከሳሾችን ስም አለማወቅ አንዲሁም የተከሳሾችን መልክ አለመለየት የመሳሰሉት ጉዳዬች የተስተዋሉ ሲሆን ምስክርነታቸውን የሰጡት ሰዎች ስም ዝርዝር እና የምስክርነታቸው ጭብጥ በአጭሩ አንደሚከተለው ነው ፡፡
1.ሙሉጌታ መዝገቡ ለማ - ናዝሬት ነዋሪ ነኝ መአከላዊ ምርመራ ለግል ጉዳይ ሄጄ ፓሊስ ታዛቢ ምስክር አንድሆን ጠይቆኝ በዚያ መሰረት ምስክር ሆኜ ተገኝቻለሁ፡፡ ከአቤል ከኮምፒውተሩ ላይ ጽሁፍ ሲወጣ እና ሲፈርም አይቼ እኔም ፈርሜያለሁ ፡፡ የጽሁፉን ይዘት አላነበብኩም አንዳንድ ቦታ አፍሪካ ሪቪው ኬንያ የሚል ቃል አይቻለሁ የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
2.በለጡ አበበ ዮሴፍ ይባላሉ፡፡ እድሜያቸው 32 ሲሆን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የካ ምድብ ሰራተኛ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆኑ በማን ላይ ለመመስከር እንደመጡ ሲጠየቁ በስም እንደማያስታውሱት ገልጸው በአካል ግን ለይተው አሳይተዋል፡፡ መስካሪዋ በ6ኛ ተከሳሽ ዘላለም ክብረት ላይ የሚመሰክሩ ሲሆን በተለየ ስም ሲጠሩት ተስተውለዋል
"የሽብርተኝነት ጉዳይ የሚያመለክት ይመስለኛል፡፡ ወደ 70 ገጽ አማርኛና 10 ገጽ እንግሊዝኛ ጽሁፍ ተገኝቷል፡፡ ያየሁትን አይቼ ፈርሜያለሁ፡፡" ካሉ በኋላ ተከሳሹስ ፈርሟል ተብለው ሲጠየቁ መጀመሪያ አላስታውስም ቢሉም እንደገና ሲጠየቁ ግን አዎ ፈርሟል ብለዋል፡፡
3.እታፈራሁ ጌታቸው ወልዴ የሚባሉ ሲሆን እድሜያቸው 36 ነው፡፡ በመንግስት ት/ቤት በአስተዳደር ሰራተኛነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ማን ላይ እንደሚመሰክሩ ሲጠየቁ ፍቃዱ እና…..(ስሙ ጠፍቶባቸው ቆይተው) እ…አጥናፉ ብለዋል፡፡ በአካል ደግሞ በፍቃዱን አሳዩ ሲባሉ አጥናፍን አሳይተዋል፡፡ የምስክርነት ቃላቸውም ማእከላዊ ምርመራ ለግል ጉዳይ ሄደው ጽሁፎች ሲታተሙ ማየታቸውንና በፍቃዱ በፍቃደኛነት ሲፈርም ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስለጽሁፎቹ ሲጠየቁ "የአማርኛ ጽሑፎች ናቸው፡፡ 60 ገጽ የሚሆን ‹ወያኔ ይውደም› ምናምን የሚል ጽሑፍ አይቻለሁ፡፡ እንግሊዝኛም አለው 10 ገጽ ይሆናል፡፡ በምስል ከውጭ ሰው ጋር ሆነው የሚነጋገሩትም አይቻለሁ፡፡ ይዘቱ ግን ግር ይለኛል፡፡" ብለዋል፡፡ አጥናፍን አስመልክቶ ደግሞ ‹‹የእሱንም በዚያው መልኩ ነው ያየነው፡፡ ዕለቱም ግንቦት 16/2006 ነው፡፡ ኮምፒውተሩ ላይ የነበሩትን ጽሁፎች እዚያ ለነበሩት ሲያሳይ ነበር፡፡ ጽሑፎችን አይቻቸዋለሁ….‹የጨለማው ቀን….የጨለማው ንጉስ› የሚል አይቻለሁ፡፡ ‹ኢትዮጵያ አንድ ናት› የሚልም አይቻለሁ፡፡ ወደ 30 ገጽ ይሆናል፡፡ ሁሉም ፕሪንት ተደርጎ ሁላችንም ፈርመንበታል፡፡››ብለዋል
ሶስቱ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ጠበቆች በሂደቱ ላይ አስተያየት አለን በማለት፣ ዶክመንቶቹ ፕብሊክ ዶክመንት ናቸው በአደባባይ የተጻፉ ጽሁፎቻቸው እና በማንኛውም ቦታ የሚገኙ ስለሆኑ ዶክመንቶቹን ክደን አልተከራከርንም የእኛ ክርክር ዶክመንቶቹ ለወንጀል ስራ የሚበቁ አይደሉም ነውና በዚህ ጭብጥ ዙሪያ ምስክር መስማቱ ያብቃልን የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡አቃቤ ህግ በበኩሉ ሁሉም ምስክሮች አንዲሰሙልኝ እፈልጋለሁ በማለቱ ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ያስረዱልኛል ካለ ይቀጥል በማለቱ ምስክሮቹ ቀጥለዋል፡፡ ጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄ ሳይጠይቁ ተከታዬቹ ምስክሮች መሰማታቸው ቀጥሏል፡፡
4.አራተኛው ምስክር አፈወርቅ ካሳ ይባላሉ፡፡ የግል ሰራተኛ ሲሆኑ እድሜያቸው 46 ነው፡፡‹‹ቀኑ ሚያዝያ 18/2006 ነው፡፡ የተከሳሹ አስማማው ቤት ጠዋት 3፡00 አካባቢ ሲፈተሸ ታዛቢ ነበርኩ፡፡ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ፓስፖርት…ብዙ ወረቀቶች ላይ ‹‹አዎ የእኔ ናቸው›› እያለ ሲፈርም አይቻለሁ፡፡ እኔም ፈርሜያለሁ፡፡ ቤተሰቦቹም ቤት ውስጥ ነበሩ፡፡ አብዛኛው ያየሁት የግል መጽሄቶችን ነው፡፡ ማህተምም አይቻለሁ፡፡ ደሞ ቢሮው ሄደን ላፕቶፕ፣ ፍላሽ፣ ሲዲ፣ መጽሔቶች አይቻለሁ፡፡ ፖሊስ የሚፈልገውን እየለየ ፈርመናል፡፡ ወደቢሮው የሄድነው በመኪና ነበር፡፡ ከዛ ደግሞ አድራሻችንን ይዘው ስለነበር ሰኔ 4….አይ 14/2006 ነው መሰለኝ ከማዕከላዊ ተጠርተን ላፕቶፕ ላይ የነበረውን ስዕሎችና የእንግሊዝኛ ንግግሮች ሲወጡ አይቻለሁ፡፡ የእኔ ነው ብሎ ሲፈርም እኛ ታዛቢዎችም ፈርመናል፡፡›› ብለው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
5.አምስተኛ ምስክር አጌና አንከና ይባላሉ፡፡ እድሜያቸው 48 ሲሆን ነዋሪነታቸው አ.አ ነው፡፡ የሚመሰክሩት ደግሞ በ3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ላይ ነው፡፡ የምስክርነት ቃላቸው፣ ‹‹ሰኔ 17/2006 ለግል ጉዳይ ማዕከላዊ ነበርኩ፡፡ ከቀኑ 8፡00 ታዛቢ ሁነኝ ብሎ ፖሊስ ጠይቆኝ ታዝቤያለሁ፡፡ ላፕቶፑ ላይ አማርኛ ጽሑፎች አይቻለሁ፡፡ ጽሑፎቹ የተከሳሹ ስለመሆናቸው አምኖ ሲፈርምባቸው ታዛቢዎችም ፈርመናል፡፡ ይዘቱን ግን አላነበብኩትም፤ አልተረዳሁትም፡፡ የገጹን ብዛትም አላስታውስም፡፡›› የሚል የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
6.ስድስተኛ ምስክር ገብረጨርቆስ ገብረመስቀል ይባላሉ፡፡ የ50 ዓመት የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡ ምስክሩ በአስማማው ላይ ለመመስከር እንደመጡ ቢናገሩም በአካል ግን ለይተው አላወቁትም፡፡ እንዲያውም አስማማውን አሳዩ ሲባሉ አቤልን አሳይተዋል፡፡
ከፍርድ ቤቱ ውሎ በኋላ አስተያየታቸው የሰጡት የተከሳሾች ጠበቆች አቃቤ ሀግ ያቀረባቸው ምስክሮች ወረቀት ሲፈረም አየን ከማለት ውጪ ምንም አይነት ለሂደቱ ቁም ነገር ያለው ምስክርነት የሚሰጡ አይደሉም ፡፡ ተከሳሾች ተገኘባቸው የተባለው ጽሁፍ የአደባባይ ዶክመንት ከመሆኑም በላይ አልተገኘብንም ብለን ክደን አልተከራከርንም በይዘቱ ላይ ክርክር ስላልተደረገ መስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብም ብዙ አልጨነቅንም ብለዋል፡፡አቃቤ ሀግ የወንጀሉን የመጀመሪያ ደረጃ ጭብጥ የሚያሳዬ ምስክሮችን ያቅርብ አይቅርብ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የማስረጃ ማሰማት ሂደቱ ነገ ይቀጥላል፡፡
ቀን ሁለት (መጋቢት 22)
በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በ19ኛው ወንጀል ችሎት እየታየ ያለው የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የክስ ጉዳይ ለሁለተኛ ቀን ምስክሮችን አሰምቶ በአወዛጋቢ መልኩ ለሚቀጥለው መጋቢት 30 ቀጠሮ ይዞ ተጠናቋል፡፡
ከእለቱ ዋዜማ ቃለ መሃላ ፈጽመው ሳይሰሙ የቀሩት ምስክሮች የተሰሙ ሲሆን ቃለ መሃላ በቀደመው ቀን በመግባታቸው ቀጥታ ወደ ምስክርነት ቃላቸው ተገብቷል፡፡ በሃያ ስድስተኛው የፍርድ ቤት ውሎ የተሰሙት ምስክሮች
7ተኛ ምስክር -ተስፋዬ መንግስቴ የመሰከሩት አቤል ዋበላ ላይ ሲሆን ከመንገድ ላይ ፓሊስ ሲፈትሹ አንዲታዘቡ ጠይቋቸው ቤቱ እና መስሪያ ቤቱ የተገኘው ሲዲ መጽሄቶች እና መጸሃፍት ላይ ሲገኙ አይቼ ፈርሜያለው አቤልም ፈርሟል ብለዋል፡፡
8ተኛ ምስክር- አቶ በረከት ጌታቸው በተመሳሳይ መንገድ ላይ ፓሊስ ታዘቡልኝ ብሎ የበፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ መታዘባቸውን በፍቃዱ የፈረመባቸው ነገሮች ላይም መፈረማቸውን ተናግረዋል፡፡ ጽሁፎቹ አማርኛ እና አንግሊዘኛ ከመሆናቸው ውጪ የሚያስታውሱት ይዘት አንደሌለ ተናግረዋል፡፡
9ኛ ምስክር - አቶ አንድነት ስሜ ይባለሉ አጥናፍ ብርሃኔ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ቤቱ የተገኙ ወረቀቶች ላይ እሱም ፈርሟል አኔም ፈርሜያለው ብለዋል፡፡ የተገኙት ወረቀቶች አማርኛ እና እንግሊዘኛ ሲሆኑ ሴኩሪቲ ኢን ኤቦክስ የሚል መጽሃፍ አለበት ብለዋል፡፡ በይዘቱ ላይ አቃቤ ህግ አንዲመሰክሩ ቢጠይቅም ጠበቆች በይዘቱ ላይ ለመመስከር ስላልተመዘገቡ አንዳይመሰክሩ ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲመሰክሩ ቢፈቅድም ምስክሩ ምንም ይዘት አንደማያስታውሱ ተናግረዋል፡፡
10ኛ ምስክር -አቶ ታምራት ዓለሙ የሚባሉ ሲሆን አቤል ዋበላ ቤት ሲፈተሽ እንደነበሩ በመግለጽ ምስክርነታቸውን አሰምተዋል፡፡ አቤል የፈረመባቸው ነገሮች ላይ ፈርመናል ያሉ ሲሆን የነጻነት ጎህ ሲቀድ መጽሃፍ እስልምና በኢትዬጲያ የሚል መጽሃፍ አዲስ ጉዳይ መጽኄቶች አና እምነት እና ተስፋ በኢትዬጲያ የሚሊ ጽሁፎች ተገኝተዋል፡፡ ሲዲም ተገኝቷል ብለዋል፡፡ የፍተሻውን ቀን ሚያዝያ 11 ነው ብለዋል፡፡ ( ጦማሪ አቤል የታሰረው ሚያዝያ 17 አንደሆነ ይታወቃል)
11ኛ ምስክር አቶ ፋሲል ግርማ ሲሆኑ በፍቃዱ ሃይሉ ቤት ሲፈተሽ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቤት ውስጥ ተገኙት እቃዎች እና ሰነዶች ላይ ተከሳሹ ሲፈርም እኛም ፈርመናል ብለዋል፡፡ የተገኙትን ሰነዶች ብዛትና ይዘት እንደማያሰታውሱም ተናግረዋል፡፡
12ኛ ምስክር አቶ ደረጀ አበበ የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ ባልደረባ ሲሆኑ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ቢሮ ሲፈተሽ ፓሊስ ታዘቡ ብሏቸው አንደነበሩ እና ተገኙት ወረቀቶች ላይ ፈርመው ቢሮውን ዘግተው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የፈረሙበትን ወረቀት ይዘት የማያስታውሱት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
13ኛ ምስክር አቶ አክሊሉ ሃይለማርያም ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ላይ የመሰከሩ ሲሆን ስሙን ብቻ ነው የማስታውሰው በማለት ያዬትን ተናግረዋል፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዬን አካባቢ ያለው ቤቱ ሲፈተሽ የተገኙ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ጽሁፎች የግል ማስታወሻዎች ሲም ካርድ እና መጽሃፍት የተገኙ ሲሆን ሁሉም ላይ በፍቃዱም ሲፈርም እኔም ፈርሜያለሁ ብለዋል፡፡
በ14ኛ ምስክርነት አቶ የማነ ብርሃኔ የተባሉ ግለሰብ ቀርበው የነበር ቢሆንም አቃቤ ህግ ‹የተለየ ነገር አያስረዱልኝም› በሚል ምስክሩ ሳይደመጡ እንዲመለሱ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ምስክርነታቸው ሳይሰማ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ አጠቃላይ 41 ምስክሮችን እንዳስመዘገበ በመጥቀስ ትናንት ካስመዘገባቸው 17 ምስክሮች ውጭ ሌሎቹን ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳጣቸው በመግለጽ ማቅረብ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን 8ኛ፣ 9ኛ እና 27ኛ ላይ አቃቤ ህግ ያስመዘገባቸው ምስክሮች መጥሪያ ደብዳቤ ደርሷቸው እንዳልተገኙለት ገልጹዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠበቆችን (የተከሳሾችን) አስተያየት ጠይቆ ነበር፡፡ በዚህም ጠበቆቹ አሉ የተባሉትን ምስክሮች ፌደራል ፖሊስ ሌሎችን በአድራሻቸው ፈልጎ ማቅረብ ይገባው እንደነበር፣ እግዚቢት ላይ የተመሰከሩት ቃሎችን ፍ/ቤቱ እንዳይመዘግባቸው ማመልከት፣ እንዲሁም ያልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ምስክር መስማቱ ተገቢ እንዳልሆነ በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም አቃቤ ህግ ቀሪ ምስክሮችን ማሰማት ካለበትም ምስክሮቹን በተሰጠው ቀን ( የማስረጃ መስማት ለሶሰት ተከታታይ ቀናት አንደተቀጠረ ይታወሳል) እንዲያቀርብ በማሳሰብ የደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት በፍርድ ቤቱና በአቃቤ ህግ በኩል እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ በተለይ ባልተካዱ ዶክሜንቶች ላይ ይህን ያህል ጊዜ መውሰዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ጦማሪ ናትናኤል በበኩሉ ‹‹አቃቤ ህግ ያቀረበውን ሰምተናል፤ እኛ ብቻችንን አይደለም የታሰርነው፤ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችንም አብረውን ታስረዋል፡፡ በህሊና እና በኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰብን ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሁሉ ‹ውሳኔው ላይ አብሮ እንዲታይልን እናመለክታለን ብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጠዋት ምስክር መስማቱን ሂደት አጠናቆ ለከሰአት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ ከሰአት በኋላ ሁለት ጉዳዬች ብይን ሰጥቷል፡፡ የመጀመሪያው የምስክሮች ቃል ከመዝገቡ ጋር አንዲያያዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀሩ የተባሉት ሶስት ምስክሮች ታስረው ለመጋቢት 30 አንዲቀርቡ እና አቃቤ ህግ ተጨማሪ ምስክሮች አሉኝ ካለም አንዲያቀርብ ነው፡፡በዚህም መሰረት ለሶስት ቀን የታቀደው ምስክሮችን መስማት በአንድ ቀን ከግማሽ ተጠናቋል፡፡ ጠበቆች አቃቤ ህግ ቀድሞ በተወሰነው ቀን ምስክሮችን ሊያቀርብ ሲገባ ሌላ ቀነ ቀጠሮ መሰጠት የለበትም በማለት ያቀረቡትን ተቃውሞ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምስክሮቹን በፌደራል ፓሊስ እያስፈለኩ ስለሆነ ተከሳሾ ማረሚያ ቤት እንዳሉ ለፍለጋው ጊዜ ይሰጠኝ ብሎ ነበር ፡፡
ጠበቆቹ አቃቤ ህግ የእግዚቢት ሰነዶችን በተመለከተ የመዝገብ ቁጥሩን ገልጾ እንዲቀርብ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ በትዕዛዙ መሰረት አቃቤ ህግ ዛሬ የመዝገብ ቁጥሩን ይዞ መቅረብ የነበረበት ቢሆንም፣ ጠበቆቹ ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት ሲጠይቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልሰጠንም በሚል ክዷል፡፡

የዞን9 ማስታወሻ
አቃቤ ህግ የሌሉትን ምስክሮች ፍለጋ በማለት ለሚያባክነው ጊዜ ፍርድ ቤቱ አንደተለመደው ተባባሪ መሆኑ የፍትህ ስርአቱን በአጠቃላይ እና ይህንን መዝገብ ሂደት ይበልጥ አሳፋሪ አድርጎታል፡፡ አሁንም ቢሆን የተከሳሾች አፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት ተጠብቆ ሁሉም ተከሳሾች ነጻ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ አጥብቀን እንጠይቃለን ፡፡
ያልተሰራ ወንጀል ምስክር አይገኝለትም ፡፡
ዞን9

የዞን ዘጠኞች እና የጋዜጠኞቹን ጠቅላላ የእስካሁኑን የፍርድ ሂደት በእንግሊዘኛ በ Trial Tracker Blog ላይ ያገኙታል፡፡ 

No comments:

Post a Comment