Tuesday, September 9, 2014

የዞን9 ጦማር "የስጋት" መስመር

ይህ አመት አንደተለመደው አይነት አመት ቢሆን ኖሮ በዚህ ወቅት የዞን9 ጦማርያን በጦማሪት ማህሌት አስተባባሪነት ፣ በአጥናፍ ብርሃኔ እና በጆማኔክስ ካሳዬ ትብብር የአመቱን ታላላቅ ክስተቶች አሰባስበው ከመታተሙ በፊት ለቡድኑ ክለሳ የሚያቀርቡበትና የተረሱ እና ለክስተትነት የማይበቁ የምንላቸውን ሁነቶች የምንለይበትና የአመቱን የጊዜ መስመር የምናወጣበት ወቅት ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ያንን ከማድረግ ይልቅ የዞን9 የጦማርያን ቡድን የጊዜ መስመርን በመስራት ያለፈው አንድ አመት አሁን በስደት እና በእስር የሚገኙት ወዳጆች አንዴት አሳለፉት የሚለውን ለመግለጽ ወደድን፡፡  ይህ የጊዜ መስመር የመጨረሻው የዞን9 ኢትዮጲያዊ ህልም ዘመቻ ከተካሄደ በሁዋላ ባለው የ2006 ዓ/ም በዞን9 ዙሪያ የነበሩ ነገር ግን ለአደባባይ ያልበቁ ክስተቶቸን ይዘግባል፡፡ አላማውም አመቱ አንደቀልድ አለማለፉን እና በአደባባይ ያልተባሉት ጉዳዪች ምን እነደነበሩ ለዞን9 ነዋሪያን ግንዛቤ ያህል ከብዙ በጥቂቱ የቀረበ ነው ፡፡

መስከረም 2006 –አራት የዞን9 ጦማርያን የተሳተፉበት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በኢትዮጲያ ምን ይመስላል የሚል ሪፓርት ዝግጅት ተጠናቀቀ፡፡ በሪፓርቱም ላይ ሃሳብን የነጸነት የመግለጽ መብት ምን ይመስላል የሚለውን ሪፓርት ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በሚያዝያ ኢትዪጵያ መንግሰት ላይ ለሚያደርገው ዩንቨርሳል ፔሪዲክ ሪቪው (UPR)- የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በሰባአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የሀገራት የእርስ በርስ መገማገሚያ ስነ ስርአት  የሚቀርብ  (ለሚዲያ የማይቀርብ ለተባበሩት መንግሰትት ብቻ የሚገባ) ሪፓርት ነበር፡፡
በሪፓርቱ ከተሰራ በሁዋላ ጦማርያን ጓደኞቻቸውን እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ጠንካራ አቋም አላቸው የሚሏቸውን የገዢውን ፓርቲ ደጋፌዎች በመጨመር የሪፓርቱን ውጤት አሳይተው ግብረ መልስ ተቀበሉ፡፡ በወሩ መጨረሻም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስረከቡ፡፡ (በዚህ ሂደት በሁዋላ ለደህንነት አካላት የወዳጆቸን እንቅስቃሴ በመንገር አየር መንገድ ላይ ሲወጡ አንዲጠየቁ ያደረገው የሪፓርተሩ ጋዜጠኛ የማነ ናግሽ የዚህ ሪፓርት ዝግጅትም ንቁ ተሳታፌ ነበር፡፡ )

 በዚሁ ወር የዞን9 ጦማርያን ወዳጅ የሆኑ የተለያዩ አጋር አካላት መንግሰት ጦማርያኑን ከግንቦት ሰባት ጋር በማያያዝ ስማቸውን እያነሳ ነው በሚል ለጦማርያኑ ጉዳዩን ግልጽ አንዲያደርጉላቸው ጠየቁ፡፡ በማስከተልም   የዞን9 ጦማሪ እንዳልካቸው ሃይለሚካኤልን ለትምህርት ከአገር መሄድ አስመልክቶ በተደረገ የምሳ ግብዣ ላይ የቡድን የደህንነት ጉዳይ የውይይት ርእስ ሆኖ ተነሳ ፡፡ በወቅቱ ብዙ የዞን9 ጦማርያን መንግስት አንደ አደጋ አይቆጥረንም የሰራነውም ወንጀል የለም፣ ያለን እንቅስቃሴም ኢንተርኔት ላይ የተገደበ በመሆኑ የደህንነት( እስርም ሆነ የስደት ) ስጋት የለብንም በሚል ተከራከሩ፡፡ በተቃራኒው ቢሆንም አንዲህ አይነት የመንግስት አረዳድ ላይ ችግር ካለ ለጊዜው ለሚቀጥሉት ወራት አንቅስቃሴያችንን በማቀዝቀዝ የመንግሰት ጥርጣሬ አግባብ አለመሆኑን ለማሳየት እንሞክር የሚል ሌላ ክርክር በመምጣቱ ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡ በመሆኑም የበይነ መረብ ዘመቻዎች ለተወሰነ ጊዜ አንዲቆሙ ፣ ወደአፍሪካ ኮሚሽንም ሆነ ወደተባበሩት መንግስታት አንዲሁም የኢንተርኔት አራማጅነትን አስመልክቶ ልምድ ለማካፈል የሚደረጉ ማንኛውም አይነት አለም አቀፍ ጉዞዎች ( በጣም አስፈላጊ እና ቀድመው የታቀዱ ካልሆኑ በስተቀር) አንዲተላለፉ ተወሰነ
በዚሁ ወር አጋማሽ ጦማሪ እነዳልካቸውለፒኤች ዲ ትምህርት ወደአሜሪካን አገር ኦሪጎን ዪንቨርሲቲ አቀና፡፡

በዚሁ ወር መጨረሻ ሁለት የዞን9 ወዳጆች እና አጋሮች ከአዲስ አበባ ኤርፓርት ለመውጣት ሲሞክሩ ኢሜግሬሽን ላይ ካገር አንዳይወጡ ለተወሰነ ሰአት ተይዘው የተለያዩ ጥያቄዎች ቀረበላቸው ፡፡ ሁለቱም ወዳጆች ላይ በተደረገው ድንገተኛ ምርመራ ከዞን9 ጦማርያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት አንዲያስረዱ ተጠየቁ ፡፡

ጥቅምት/ ህዳር 2006 - ጦማርያኑ በዞን9 በኩል የሚጻፉ ጽሁፎችን አቀዝቅዘው በግል የማህበረሰብ ሚዲያው ላይ ወጣ ገባ ሲሉ ቆዩ፡። በዝምታው ቆይታ በጦማርያኑ የታየ ይህ ነው የሚባል የአደባባይ ስራ ቢኖር አሜሪካን አገር ለሚገኘው የኤንፒአር ኮጆ ሾው ኢትዮጲያ ውስጥ በትችት ድምጽ መጦመር ምን ይመስላል የሚለውና የሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በኢትዮጵያ የሚለው አርቲክል 19 በተባለው መንግስታዊ ያልሆነ የሰብአዊ መብት ድርጅት የተሰራው ዶክመንተሪ ፊልም ላይ ተሳትፎ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡


ታህሳስ 2006  - በዚህ ወር በተደረገ ስብሰባ የታየ በቂ ደህንነት ችግር ስለሌለ ስጋታችን የተጋነነ ነውና ወደተለመደው አንቅስቀሴያችን መመለስ አለብን የሚል ውይይት ተካሄደ፡፡ ወደ ሥራ ለመመለስ የጋራ እቅድ ለማውጣት እና የተለመዱ የዞን9 ስራዎችን ይዞ መመለስ ይገባል የሚል ሃሳብ ተነስቶ ለመመለስ የሚያስፈልጉ ዘመቻዎች እቅዶች እና አዳዲስ ጉዳዮቸን የማስተዋወቅ እቅድ አንዲወጣ የስራ ክፍፍል ተደረገ፡፡  ተያይዞም ኢንተርኔት ላይ የዞን9 ህጋዊ ምዝገባን ለማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ባለመኖሩ በተለያየ መልክ በመመዝገብ ይበልጥ ወደ ማህበረሰባዊ ስራ መጠጋትና ተቋማዊ ማድረግ ይገባል ተብሎ ተወሰነ፡፡ በ6 ወር ጊዜ ገደብ ውስጥም ወደሚዲያ/ሲቪል ሶሳይቲ ለማሳደግ ያሉትን እድሎች የማየት እቅድም አብሮ ተያዘ፡፡  በተመሳሳይ ወር አቶ አቤል አባተ አቀናባሪነት በመንግሰት ደህንነትና በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን ድጋፍ የዞን9 ጦማርያን ላይ የተነጣጠረ የቀለም አብዩት የተሰኘው አሳፋሪ ሃሳብን የሚያቀርበው የቴሌቪዥን ዶክምንተሪ ታየ፡፡ (በወቅቱ በጦማርያኑ መካከል በተደረገ ውይይት ከዶክንተሪው በፌት ዞን9ን ይመለከታል የሚል ግምት መጀመሪያም አሳድሮ ነበር፡፡ )  

ጥር 2006 - ጦማሪ ናትናኤል ከአንድ ራሱን ከብሄራዊ ደህንነት አንደመጣ ባስተዋወቀ ሰው በመኖርያ ወረዳው አስተዳደር አማካኝነት ጥያቄ ቀረበለት፡፡ በወቅቱ ጥያቄው ስለጦማሪ ናትናኤል የፓለቲካ ተሳትፎ ስለዞን9 ምስረታ፣ አላማ ፣ እና አባላት የመሳሰሉት ሲሆኑ የደህንነት አባሉ የዞን9 አባላት 10፣000 ናቸው አላማችሁ ምንድነው? የአገር ደህንነትን የሚነካ ነገር እየሰራችሁ እንዳልሆነ በምን እናውቃለን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ያካተተ ነበር፡፡ ናትናኤል የዞን9 አላማ እና የሚሰራቸውን ስራዎች በዝርዝር አስረድቶ አባላቱ 9 አንደሆኑ 10.000 የተባሉት የዞን9 የፌስ ቡክ ገጽ ላይክ ያደረጉት ናቸው በማለት አብራራለት፡፡ የደህንነት አባሉ የቡድን አደረጃጀት ምን ይመስላል? ድጋፍ ታገኛላችሁ ወይ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ናትናኤልን አብረኸን እንድትሰራ አንፈልጋለን የሚል ጥያቄ አቀረበለት፡፡ ናትናኤል በወቅቱ ከደህንነት ጋር የሚያሰራ ምንም ችሎታ አንደሌለው ሌላ ጊዜ ቢጠየቅም ተመሳሳይ መልስ አንደሚመልስለት[JK4]  በማሳወቁ ደህንነቱ ወደፌት እናወራለን በማለት ተለየው፡፡ በዚህም የተነሳ በዚሁ ወር የታቀደው ጽሁፎችን እና ዘመቻዎችን ይዞ የመመለስ ውሳኔ ጉዳይ በድጋሚ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ፡፡ በተመሳሳይ ወር ከታሳሪዎች አንዳቸው ከናትናኤል ጋር ተመሳሳይ የሆነ የደህንነት ጥየቃ አስተናገዱ ፡፡ በወቅቱ ከአሁን ታሳሪዎችን አንዱን ያናገረው ሌላ የደህንነት አባል  የሚሰሩትን ነገር ሪፓርት አድርጉልን እየተከታተላችሁ በመናገር አብራችሁን ስሩ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

የካቲት 2006 - በዚሁ ወር መጨረሻ ጦማሪት ሶልያና ሽመልስ ሰብአዊ መብት አማካሪ ፌሎ በመሆን በቀጣዩ የኢትዮጲያ ሰብአዊ መብት ግምገማ ጋር ተያያዥ የሆኑ ስራዎቸን ለመስራት ለመስራት ተጓዘች፡፡ በጦማሪያኑ በተደጋጋሚ የሚገናኙባቸው ቦታዎች ላይ በግልጽ እና በሚታይ መልኩ የደህንነት ሰዎች አዘውትረው መታየት ጀመሩ፡፡ በተመሳሳይ  ወር ጦማሪ ሶልያና ቀድማ የምትሰራበት መስሪያ ቤቶች ሃላፌዎች ጋር የደህነት ሰዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቀረቡ፡፡ በዚሁ ወር በተመሳሳይ ናትናኤል እና በሌላ አሁን ታሳሪ ላይ ላይ የሚደርሰው ወከባ (በአካልም በስልክም) በረታ ከሚጠየቁት ጥያቄዎችም መካከል አላማችሁ ምንድነው ? ከነማን ጋር ነው የምትሰሩት? በፓርላማ ከታገዱ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላችሁ ወይ ? ባለፉት ወራት ዝም ያላችሁት ለምንድነው ? እየሰራችሁ ያላችሁት ሌላ ስራ አለ ወይ? የሚሉ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የተነሱት ጥያቄዎች አላማችሁ ምንድነው? አባላታችሁ አደጃጀት አላችሁ ወይ የሚሉ ተደጋጋሚ እና አሰልቺ ሲሆኑ ጥያቄ ፣ የደህንነት አባላቶቹ ስለ ኢንተርኔትም ሆነ ስለማህበረሰብ ሚዲያ ያላቸው እውቀት በጣም አነስተኛ በመሆኑ ግማሹ ጊዜ መሰረታዊ የማህበረሰብ ሚዲያን አሰራር በማስረዳት የሚያልቅ ሲሆን በአንድ ወቅት አንዱ የደህንነት አባል ፍሪደም ኦፍ ኤክስፐረሽን ትሰራላችሁ የሚል ክስ በማቅረቡ በተመጣጣኝ ደረጃ መነጋገር አስቸጋሪ እየሆነ ነበር፡፡


መጋቢት 2006-  ከአሁን ታሳሪዎች አንዱ ላይ  አሁን ዝም ያሉት ለምንድነው?  የሚሰሩት ሌላ ነገር ስላለ ነው የሚሉ ጥያቄዎቸን በተደጋጋሚ አስተናገዱ፡፡ ፣ በዚሁ ወር ነገሮች መክፋታቸውን ተከትሎ ለዞን9 ጦማርን ለሌሎች ልምድ እንዲያካፍሉ በተጋበዙበት በታንዛንያ በተደረገው ስብሰባ ውጪ ያሉ የዞን9 ጦማርያን በስካይፕ የተሳተፉበት ሰፋ ያለ ውይይት ተካሄደ፡፡ በዚህ ውይይት ላይም የምንሰራው ወንጀል የለምና ምንም ሊያሰጋን የሚገባ ነገር የለም የሚለው ክርክር አንዳለ ቢሆንም እየበረታ ካለው የደህንነቶች ወከባ አንጻር ተረጋግተው አንዲመለሱ ማድረግ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውሳኔ ተሰጠ፡፡ ፡፡ በዚህም መሰረት ጦማሪ ናትናኤል ደህንነት አባሉ በሚያናግረው ወቅት ስራችንን አንዲያስረዳው (  ደህንንቱ ትዊተር ፌስ ቡክ አጠቃቀም አንዲያሳየው ፣ የተጠረዘውን የዞን9 ስራዎች ስብስብ አንዲሰጠው እና ክትትላቸውም አግባብ አንዳልሆነ እንዲገልጽለት) ተወሰነ፡፡ መንግሰት አዲሱ ስጋት ከ ለምን ተናገራችሁ? ወደ ለምን ዝም አላችሁ? የተቀየረ በመሆኑ ዝምታችን ማቆምና የመመለስ ዝግጅት ማድረግ አንደሚገባ፣ እንዲሁም በደህንነቶች በከፍተኛ ሁኔታ ስማቸው የሚነሳ የቡድኑ አባላት ከፍተኛ የደህንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አንዲመች የደህንነት ስጋት ቅደም ተከተል በማውጣት ጦማሪት ሶልያና እና ጦማሪ በፍቃዱ በአንደኛ ደረጃ በመንግሰት ደህንነቶች አይን በመታየት ጦማሪ አጥናፍ እና ናትናኤል (ናትናኤል በቀጥታ እያናገሩት በመሆኑ እና አጥናፍ ቀድሞ የሚሰራበት መስሪያ ቤት በመሄድም ጭምር የክትትል ሂደቱ ስለጠነከረበት ) በሁለተኛ ደረጃ  በከፍተኛ የደህንነት ግንኙነት መረብ ውስጥ በመሆን  እነዚህ ጦማርያን አስፈላጊውን ጥንቃቄ አንዲያደርጉ እና ወደፊትም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ አንደሚያስፈልግ  ለጊዜው ግን ወደ ተለመደው ኢንተርኔት በመመለስ ምንም እየሰራን አንዳልሆነ ማሳየት አለብን የሚል ውሳኔ ተደረሰ፡፡ ( በወቅቱ ሌሎች ጦማርያን ላይ ያለው ስጋት ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ነው የሚል ድምዳሜ ነበር)

በዚሁ ወር መጨረሻ ጦማሪ አቤል ዋበላ ላይ ከምሽቱ 2 ሰአት 22 አካባቢ በፌዴራል ከሚጠበቅ የመንግስት መስሪያ ቤት አጠገብ ከፍተኛ የአካል ድብደባ ደረሰበት በድብደባው ራሱን የሳተ ሲሆን ሲነቃ ከላፕቶፑና ከስማርት ስልኩ ውጨ የተወሰደ ምንም ንብረት አለመኖሩም ሌላ ከፍተኛ ጥርጣሬን አስነሳ፡፡
በዚያው ወር መጨረሻ ጦማሪ ናትናኤል ለደህንነት አባሉ የዞን9 ስራዎችን የሚያሳይ ጥራዝ በመስጠት የአባላቱን የፌስ ቡክ እና የትዊተር አንቅስቃሴ አንዴት መከታተል አንደሚችል በተወሰነው መሰረት አስረዳው፡፡ ከሚታየው ውጪ የምንሰራው ነገር የለም የዝምታችን ምንጭም የደህንነቶች ወከባ መሆኑን ተናገረ ፡፡ በተደጋጋሚ ህጋዊ መታወቂያ ቢጠይቀውም የደህንነት አባሉ መታወቂያ ለማሳየት ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ በዚሁ ወር ከቀድሞው በተጨማሪ ከአሁን ታሳሪዎች በአንደኛው ላይ ከደህንነቶች ጋር አብሮ የመስራት ጥያቄው ጠነከረ፡፡ አብሮ ካልሰራ የመታሰር አደጋ አንዳለውም ደጋግመው አስጠነቀቁት፡፡ ነገር ግን ማስፈራሪያውን ተከትሎ የሰሩትን ህገ ወጥ ስራ ስለማላውቅ ልተባበር አልችልም ብሎ በአቋም ጸና፡፡


ሚያዝያ 2006  -የቡድኑ የወቅቱ አስተባባሪ ናትናኤል ፈለቀ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቶች ጋዜጠኞች እና ጦማርያን የሚያደርጉበት አመታዊ የልምድ ልውውጥ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስዊድን ተጉዞ ተመለሰ፡፡ በዚሁ ወር መጀመሪያ ከዞን9 ጦማርያን ጋር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ጋር ተያያዥ ስራዎችን በመስራት አጋር ድርጅት የሆነው የአርቲክል 19 ሰራተኛ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ለ36 ሰአታት ተይዞ ከአገር አንዲወጣ ተደረገ፡፡ በወቅቱም መንግሰት ድርጅቱ የሚሰራውን ስራ አንወደውም ከማለት ውጪ ለማባረሩ የሰጠው ሌላ ምክንያት አልነበረም (ይህ ድርጅት ከዚህ ቀደም አቶ ሽመልስ ከማልን ጨምሮ ለሌሎች ባለስልጣናት ስልጠና የሰጠ ሲሆን የሚዲያ ሕጉ በሚወጣበት ወቅት ከመንግስት ጋር አብሮ ይሰራ የነበረ መሆኑ ይታወሳል )
በዚሁ ወር በነበረው በጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሚካሄደው የኢትዮጲያ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በሰባአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የሀገራት የእርስ በርስ መገማገሚያ ስነ ስረአት ቅድመ ግምገማ (Pre UPR) ሊሳተፉ ተጋብዘው የነበሩ ሁለት ጦማርያን የመንግስትን ክትትል ለማረጋጋት በማሰብ ጉዞአቸውን ሰረዙ ፡፡

በመጀመሪያው ሳምንት በጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ፣ በጦማሪ አጥናፍ ላይ የነበረው ክትትል በመጨመሩ እና በጦማሪ አቤል ላይ የደረሰው ድብደባ አጠራጣሪነቱ ከመጨመሩም በተጨማሪ ሌሎች የዞን9 ወዳጆች ከደህንነቶች በተደረገ ተከታታይ የስልክ ጥሪ ጆማኔክስ እና ማሂፋንትሽ የሚባሉ ጦማርያንን አድራሻ አንደሚያውቁና አንዲናገሩ መጠየቃቸውን ተናገሩ፡፡  
በተመሳሳይ ቀን ከደህንነት ቢሮ ጦማሪ ናትናኤል ጋር ተደውሎ የዘጠኙንም አባላት ሙሉ ስም የስልክ አድራሻ እና የሚሰሩበትን መስሪያ ቤት አንዲገልጽ ተጠየቀ፡፡ ( ናትናኤል በወቅቱ ስራቸውን ለመስራት የተሻለ ስልት መጠቀም አንደሚገባቸው በማሳሰብ የማንንም አድራሻ ለመናገር ፍቃደኛ አንዳልሆነ መለሰ)

በእለቱ  ምሽት በጣም አስጊ የሆኑትን ጉዳዪች አስመልክቶ ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበት ውይይት ተካሄደ፡፡ በመሆኑም ዝም በማለት የመንግስት ደህንነቱን ለማረጋጋት የተደረገው ሙከራ አለመሳካቱ አንደውም ለምን ዝም አሉ ወደሚለው መንገድ ማምራቱን ተከትሎ መናገርም ዝም ማለትም ያልተፈቀደልን የቡድኑ አባላት የተለያዩ ምን ማድረግ ይገባል የሚሉ ተከታተይ ውይይቶችን በየቀኑ ማካሄድ ተጀመረ፡፡[በወቅቱ የስጋቱን ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ተከትሎ አውሮፓ ቪዛ ያለው ጦማሪ በፍቃዱ ለጊዜው ከአገር ወጥቶ ዞር አንዲል  የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አደረገው፡፡ ( በወቅቱ በነበረው መረዳት ከፍተኛ አደጋ ላይ አለ ተብሎ የታሰበው በፍቃዱ ነበር)

 ተከታታይ ውይይቶቹ ሲጠናቀቁ ሁለት ሃሳቦች ለውሳኔ ቀረቡ - አንደኛው እየተጠናከረ የመጣውን ጫና በይፋ በመግለጽ ዞን9ን በመበተን ቡድኑ በይፋ እንዲዘጋ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደሞ ወደተለመደው የኢንተርኔት  እንቅስቃሴ በመመለስ እስካሁን ቡድኑ የጠፋበትን ምክንያት መግለጽና ተመሳሳይ የሆኑ ክትትሎችን በተከታታይ ለአአደባባይ ማዋል  በሚል ውይይት ተደረገ፡፡ በዚህ ቀናትን በፈጀ ውይይት ለመጀመሪያም ( ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜም) ውሳኔ ለመስጠት ድምጽ ብልጫ ይደረግ በተባለው መሰረት  በአንድ ተቃውሞ በሁለት አብላጫው በወሰነው እስማማለሁ እና በስድስት ድጋፍ ወደእንቅስቃሴ ለመመለስ ተወሰነ፡፡ ተያይዞም ከደህነት የሚመጡ ጥያቄዎቸን ከዚህ በሁዋላ ማስተናገድ አንደማይገባ ተወሰነ፡፡  

( በዚህ ውሳኔ ወቅት ሁሉም ጦማርያን መንግስት በፍጥነት የእስር እርምጃ ይወስዳል የሚል ግምት ያልነበረን ሲሆን ወደስራ ተመልሰን “ተጽእኖ” እስክንፈጥር ወይም የስራችንን ይዘት አይተው እርምጃ ይወስዳሉ በሚል ግምት ከጥቂት ጊዜያት በሁዋላ ሊመጣ የሚችለውን ነገር አና መደረግ የሚገባቸውን ስራዎች ማዘጋጀት ላይ ከማቀድ ውጨ ያደረግነው ዝግጅት አልነበረም፡፡) 


ሚያዝያ 15 - የዞን9 አባላት ሁሉም በተለመደው ሁኔታ የኢንተርኔት እንቅስቃሴያቸን መመለሳቸውን የሚገልጽ መግለጫ ወጣ፡፡ በወቅቱም ለጊዜው የእስረኞች አያያዝን፣ እየተነቃቃ መጣውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ተከትሎ ታዋቂ የኦሮሞ ፓርቲዎች ፕሮግራምን ማስተዋወቅን( ልዩነቶቻቸው እና አንድነቶቻቸውን)  እና ለመጪው ምርጫ የሚሰሩ ዘመቻዎችን ማዘጋጀት ላይ ማተኮር የመመለሻ ስራዎች አቅጣጫ አንዲሆን ተወሰነ፡፡  ተወሰነ፡፡ በተጨማሪም በመጪው ሳምንት የሚካሄደውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጉባኤ በሰባአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የሀገራት የእርስ በርስ መገማገሚያ ስነ ስረአት አስመልክቶ መረጃዎችን መስጠት ላይ አንድናተኩር እና ቀድመው ታቅደው ነበሩ የዞን9 ስራዎችን መከለስ የመሳሰሉ የስራ ክፍፍሎች ተሰጡ፡፡ 


ሚያዝያ 17 - ሚያዝያ 17 ማምሻውን በተመሳሳይ ሰአት የዞን9 ጦማርን በያሉበት እየተያዙ እነደሆነ መረጃዎች ተሰሙ፡፡ያንን ተከትሎ  እስሩ እየተከናወነ ያለው በተመሳሳይ ሰአት  በመሆኑ መረጃዎች እነደተሰሙ ለሁሉም ጦማርያን ለማስተላለፍ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀረ፡፡ በእለቱ 6 ጦማርያን መያዝ ሲረጋገጥ እስሩ እየተከናወነ እያለ ከመታሰሩ ቀድሞ መረጃ ማድረስ የተቻለው ለጦማሪ ጆማኔከስ በመሆኑ ማምሻውን በአስቸኳይ ነበረበትን ከተማ ቀየረ፡፡


ሚያዝያ 18 - ጦማሪ ጆማኔክስ ካሳየ በተጣደፈ በጣም አጭር የቡድን ውሳኔ ከአገር በፍጥነት ወጣ፡፡ ( ከአገር የወጣው የመጨረሻው ጦማሪ በመሆን ከመንግሰት የተቀናጀ አፈና የተረፈው ብቸኛው የዞኑ ጦማሪ በመሆን ስደትን ተቀላቀለ) በተጨማሪም የዞን 9 ወዳጅ የነበሩ ጋዜጠኞች በተመሳሳይ ክስ መአከላዊ ምርመራ ለእስር አንደተወሰዱ ተሰማ።


 ሚያዝያ 19 - የህግ አማካሪ እና ቤተሰብ ባልተገኘበት እሁድ ቀን አራዳ ፍርድ ቤት ጦማርያኑ ከእስረኛ ጋዜጠኞች ጋር ቀረቡ በወቅቱም ፓሊስ ራሱን የሰብአዊ መብት ተቋም በሚል ከሚጠራ ድርጅት ጋር በመተባበር ህገ መንግሰታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ በማህበረሰብ ሚዲያ አመጽ የመቀስቀስ ዝግጅት በማድረግ ወንጀል መጠርጠራቸውን መግለጹን ከፍርድ ቤት ፋይሉ መረዳት ተቻለ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ክሱን ተከትሎ ከሰብአዊ መብት ተቋማት ጋር መስራትን ወንጀል ማድረግ አደገኛ እና ከአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህጎች ጋር የሚጋጭ መሆኑን በማሳወቅ አስቸኳይ መግለጫ አወጣ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በመቶዎች የሚጠጉ የሰብአዊ መብት ተቋማት እስሩን የሚያወግዙ መግለጫዎችን አወጡ፡። በተመሳሳይ ወር ግሎባል ቮይስስ የመጀመሪያውን አለም አቀፍ የጦማርያኑ እና የጋዜጠኞቹ እስርን የሚቃወም ዘመቻ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በሺዎች  የሚቆጠሩ በመላው አለም ያሉ የሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተሟጋቾች አጋርነታቸውን አሳዩ፡፡ በማህበረሰብ ሚዲያዎችም አበረታች የአጋርነት ድጋፎች  ታዩ፡፡


ሚያዝያ 23 እና 24 - ጦማሪ ጆማኔክስ ካሳየ መኖሪያ እና የስራ ቦታ ከፍተኛ ወከባ እና ተያያዥ ጥያቄዎች ለተለያዪ ሰዎች ቀረቡ፡፡ መንግሰት ደህንነት ሰዎች ባደረጉት በዚህ ከበባ የጦማሪውን አገር ውስጥ አለመኖር ተረዱ፡፡

ሚያዝያ 29 እና 30 - የዞን9 ጦማርን እና ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተሰብ አና በጓደኞቻቸው መታየት ቻሉ፡፡ ሁለት ጦማርያንም ድበደባ እና ኢሰብዓዊ  የሆነ እንግልት እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቀረቡ፡፡ በተመሳሳይ ወር በሁሉም እስረኞች ላይ ከድብደባ ከኢሰብአዊ አያያዝ  የአንቅልፍና የምግብ መክከል አንዲሁም ሌሎች ለአደባባይ የማይገለጹ መንገላታቶች ደረሱባቸው፡፡


 ግንቦት 2006 - በዚህ ወር በአራት የተለያዩ ቀናት በተለያዪ ቡድኖች ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡት ጦማርያን እና ጋዜጠኞቹ ክስ ከሰብአዊ መብት ተቋማት ጋር በመስራት አመጽ ማነሳሳት ከሚለው ወደ ሽብተኛነት ጥርጣሬ ተቀየረ፡፡ አዲስ ወንጀል ለመቀየሩ ማእከላዊ ምርመራ ያሳየው ምንም አይነት ማስረጃ ባይኖርም የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮን እንደፈለገ ማግኘት ቻለ፡፡ በዚሁ ወር በነበረው የመጀመሪያ ቀጠሮ ባለፈው አቤቱታ ካቀረቡት በተጨማሪ ጦማሪ አጥናፍ ብርሃኔ በሌሊት እየተጠራ ምርመራ እንደሚደረግበት እና ድብደባ አንደተፈጸመበት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቀረበ፡፡
በዚሁ ወር ጦማርኑ ከታሰሩ ከአራት ሳምንት በሁዋላ “የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪ” በሆነችው በጦማሪ ሶልያና ሽመልስ ቤት በሌለችበት  በሁለት ዙር የተከፈለ ብርበራ ተካሄደ፡፡ በመጀመያው ዙር ምርመራውን ጨርሶ የሄደው ፓሊስ ያልተፈተሹ ቀሪ ቦታዎች አሉ በማለት ፍሪጅ ጀርባ የግንቦት ሰባት ፕሮግራምን አግኝተናል ሚል የክሱን ፓለቲካዊነትና የደህንንት ተቋሙ የደረሰበትን ቅሌት ደረጃ ያመላከተ ማስረጃ ፈጠራ አካሄደ፡፡ በዚያም በተፈጠረ አታካሮ የጦማሪዋ እናት አልፈርምም በማለት የተቃወሙትን ሰነድ ፓሊስ ራሱ ይዞ ባመጣቸው ምስክሮች አስፈርሞ ሄደ፡፡ ብርበራውን አስከትሎ የክሱ አቅጣጫ የተለመደው የሽብርተኛነት የተመደቡ ድርጅቶች ጋር ማያያዝ መሆኑን ብዙዎች ገመቱ፡፡

ሰኔ 2006 - በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት በመመላለስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ጦማርያን እና ጋዜጠኞች በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ከቤተሰብ ጋር እየተገናኙ ከፍርድ ቤት ቀጠሮ አንድ ቀን ቀድሞ ካልሆነ በስተቀር ከጠበቃ ጋር የመመካከር እድላቸው እነደተከላከለ ማእከላዊ ምርመራ ከረሙ፡፡

ሃምሌ 2006- ወራትን የፈጀው ክስ አሳፋሪ ክስ በልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት ተከፈተ፡፡ በማንኛውም ተራ ግለሰብ ዘንድ የሚታወቀውን ሃቅ በማዛባት ሁሉንም የአንድ አሻባሪ ቡድን አባላት በማስመሰል ቀረበው ክስ ከ20 አመት ጀምሮ እስከ ሞት ድረስ የሚደርስ ቅጣትን የሚመለከት ሆኖ ቀረበ፡፡ ዞን9 የሚለውን የቡድኑን ስም አንድም ቦታ ያልጠቀሰው ይህ ክስ ጦማሪት ሶልያና ሽመልስን አንደኛ ተከሳሽ አድርጎ በመጨመር 10 ሰው ላይ የቀረበ ሲሆን ምን አንደሆነ የማይታወቅ ሽብር ተግባር በመጥቀስ የኢንተርኔት ደህንነት ስልጠናን መውሰድን ዋናው የክሱ ጭብጥ አድርጎ በማቅረብ በተለያዩ የጋዜጠኛነት ፕሮግራሞች ላይ የሚሰጠውን እና አለም አቀፍ ታዋቂነት ያተረፈውን የስልጠና አይነት በሽብር በመፈረጅ ኢትዮጲያን ቀዳሚዋ አገር አደረጋት፡፡ ይህንን ተከትሎም በአገር ውስጥም ሆነ አለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ ግርምት ተስተዋለ፡፡ በዚሁ ወር ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ወደ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ተዘዋወሩ፡፡ ጦማሪት ማህሌት እና ጋዜጠኛ ኤዶም በስተቀር የቀሩት ተከሳሾች በጓደኞቻቸው መጠየቅ ቻሉ፡፡


ነሃሴ 2006 - ዘጠኙም ተከሳሾች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ለጥቅምት 05 2007 አም ተቀጠሩ፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም በሌለችበት ክሷ የሚታየውን ጦማሪት ሶልያና ሽመልስን መጥታ ክሷን አንድትከታተል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ አደረገ፡፡

አዲስ ህልም በማለም የተጀመረው አመትም 6 ጦማርያንን 3 ጋዜጠኞችን በማሰር 3 ሌሎች ጦማርያንን ለስደት በመዳረግ ተጠናቀቀ፡፡

ማስታወሻ (ወዳጅ ጋዜጠኞች ከዞን9 ጦማርያን ጋር በመተዋወቃቸው ብቻ ታሰሩ ሲሆን ከጋዜጠኛ ኤዶም በስተቀር በዞን9 ዘመቻዎችም ላይ ተሳትፈው የማያውቁ ጓደኞች ብቻ ነበሩ፡፡ በነበረው ከፍተኛ ወከባ የመታሰር እጣ ሊኖር አንደሚችል ብንገምትም ሶስቱን ጋዜጠኞች አብረው ይታሰራሉ የሚል ግምት ፈጽሞ አልነበረንም ፡፡)

*************************************************************************************************************
ይህንን ከ24- 31 አመት በሚደርሱ ወጣቶች ያገባናል ብለው ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ የደረሰ ግፍ፣እስር፣ እንግልት፣ ስደት እና ለቁምነገር እና ለአገር ደህነት መዋል የነበረበትን  የመንግሰት ከፍተኛ ሃብት እና የሰው ሃይል ወጣት ዜጎችን በመከታተል ማባከን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳዝነናል፡፡ በዚያው መጠን ለዚህ መስዋእትነት እየከፈሉ ባሉ ጓደኞቻችን እንኮራለን፡፡ ዞን9 መሰረታዊ የሆነው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማግኘት የሚደረግ ትንሽ ሙከራ ነው፡፡ ይህንነ ሙከራ ያለምንም ማቅማማት በፈጠራ ክስ መምታት ሂደቱን ያስተጓጉለው አንደሆነ አንጂ ጨርሶ አይገለውም ፡፡ ታሪክም ምክንያታዊነትም አንደሚያሳው ይህ አይነቱ የመንግሰት ጭፍን እርምጃ ምሬትን ሲጨምር አንጂ ሊያስቀር አይችልም፡፡ በመሰረቱ ዘጠኝ ወጣቶች የሚሸበር መንግስት ለትችት ለመስማት ያለው ትዕግሰት ዜሮ ሊባል በሚችል ሁኔታ መሆኑ ከዞን9 እስር በላይ ምስክር የለም፡፡ እንደዛ ባይሆን ኖሮ “ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ህገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ” የሚል የጥፋተኛነት ቃል በማስፈረም ባልቀለደ ነበር፡፡ 

በመጨረሻም እስር ቤት ለሚገኙ ጓደኞቻችን እና ያልተገደበ አጋርነታቸውን ላሳዩ የዞን9 ነዋሪያን ከልብ የመነጨ የመልካም አዲስ አመት ምኞት እናስተላልፋለን፡፡ጓደኞቻችን እስር ቤት ውስጥ ሆነው የሚቀበሉት አመትም ህልማቸውን የገደበ ቢሆንም በጽናትና በኩራት እነደሚወጡትም ሙሉ እምነታችን ነው ፡፡ በመሰረቱ ወንጀል ያልሰራ እና በፓለቲካ ልዩነት ብቻ የተከሰሰ ህሊና አንገቱን የሚያስደፋው ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ በስደት የምንገኝ ጓደኞቻቸውም እስራቸውንና እንግልታቸውን ልባችንን ቢሰብረውም አንገታችንን በኩራት ቀና የምናደርግበት እና እስራቸው ትርጉም የለሽ የማይሆነበት አመት እንደሚሆን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ሃሳብን መግለጽ የሚደረግ ጥረትና ትግል ከሚመጡበት ተግዳሮቶች በመነሳት አቅጣጫ ይቀይር ይሆናል አንጂ አይቋረጥም የዞን9ኛውያን ጥረትም ከዚያ የተለየ አይሆንም፡፡

ስለሚያገባን እንጦምራለን!
Zone9 Bloggers and Journalists Pic edited by Fractal Element

No comments:

Post a Comment