Friday, March 8, 2013

#Ethiopia፡ ሴት የመሆን ጥቅሞችና መታደሎች

በሶሊያና ሽመልስ

ሴት መሆን መታደል ነው ብዬ ብጀምር  የሚስቅብኝ አይጠፋም! ሴት የመሆን ጉዳቶች ላይ ተደጋጋሚ ነገር ሲነገር ሰምተናል፡፡ የቤት ውስጥ የሥራ ጫናው፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱ፣ የዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶቹ፣ ከወንድ ይልቅ ለባሕል እና ለማኅበረሰብ የመገዛት ኃላፊነት ላያችን ላይ መጫኑ፣ የሚታየው አካላዊ ጉዳት (አሲዱ፣ አስገድዶ መድፈሩ፣ ድብደባው…) የማይታየው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት (እኔ፣ አንቺ፣ እናቶቻችን ሁላችንም የምናልፍበት የአእምሮኣዊ ጭንቀት ሐሳብ እና ትግል) ሁሉም በተደጋጋሚ ተወርቶላቸዋል፡፡ የሴቶች ቀን ላይ ቆመን ሴት የመሆን ጥቅሞች እና ደስታዎች ላይ ለመጻፍ ብንነሳ ማን ይከለክለናል?

የሴቶች ቀን ሲነሳ ‹‹ሌላው የወንዶች ቀን ነው፤›› የሚል ተራ ክርክርን በዚሁ ነካ አድርጌ ልለፍ፡፡ ማርች 8 የሴቶች ቀን ሲሆን ሌሎቹ የሰዎች ቀናት ናቸው፡፡ የወንድም፣ የሴትም፣ የሕፃንም፣ የሽማግሌም፣ የነጋዴም፣ የወጣትም… - የሁሉም ሰዎች ነው፡፡ የአባቶች ቀን፣ የእናቶች ቀን፣ የበዓላት ቀን ነገር ሲነሳ ይህ ክርክር ትዝ የማይላቸው ሰዎች ለምን ‹‹የሴቶች ቀን›› ላይ ብቻ እንደሚበረቱ አላውቅም?!
ሴት የመሆን መታደሎች

ሴት የመሆን መታደሎቹ አንዱ ኃላፊነትን በሚገባ የመወጣትን ክኅሎት አብሮ ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ አናስተውለው ይሆናል እንጂ ሴት ልጅ ይዛው የማይስተካከል፣ ሴት እንደኃላፊነት ተሰጥቷት የማይፈፀም ነገር የለም፡፡ እንደውም ከወንዶች በተለየ የኃላፊነት ስሜት የሚሰማቸው ሴቶች መሆናቸውን ለማረጋገጥ በተለያዩ የቤት እና ከቤት ውጪ ባሉ ኃላፊነቶች ውስጥ ያሉ ሴቶችን ማየቱ ይበቃል፡፡ የተረሳ ነገርን ማስታወስ፣ ጉዳይን በቁም ነገር መያዝ፣ ነገሮች የሚያመጡትን ውጤት አለማጣጣል እና ችላ አለማለት ሲታይ ኃላፊነትን ለመወጣትማ ሴት ልጅን የመሰለ ነገር የለም ያስብላል፡፡

ለኃላፊነት መብቃት ብቻ አይደለም፤ ውሳኔ መስጠት ሌላው ከሴትነት ጋር አብሮ የተሰጠ ቁርጥ ባህሪይ ነው፡፡ ሴቶች ውሳኔ መስጠት ረገድ ማቅማማት እና እጅ መስጠት አይታይባቸውም፡፡ እስካመኑበት ድረስም ፈራ ተባ አይሉም፡፡ ቆራጥ ውሳኔ የአለቃ ሴቶች፣ የእናቶቻችንም ጭምር ባሕርይ ነው፡፡ ይህ ታዲያ ውሳኔ የመስጠትን ብልሐትና ኃላፊነት አብሮ ይጨምራል፡፡


ውበት ሲነሳ ሴትነትን አለማንሳት የማይቻል ነው፡፡ ውበት በብዙ መልኩ ሊገለጽ ይችላል፤ ሴት ልጅ ላይ የተገለፀውን ያህል ግን የትም የለም፡፡ የውበት መገለጫው የሴት ልጅ ሰውነት ነው፡፡ የማታምር ሴት ልታጋጥም ትችል ይሆናል የውበት አንዱን ክፍል ያልያዘች ግን አትገኝም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ‹እንትንዋ ያምራል፤› የሚል አድናቆትን የምናስከትለው ለሴት ነው፡፡ ውበት ከተነሳ አይቀር ከነምሳሌው፣ ከነመገለጫው እና ከነለዛው ተሟልቶ የሚገኘው ሴት ልጅ ላይ ብቻ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሴት መሆን በራሱ ውበት ነው! እንደው እንደምሳሌ እንኳ ብናነሳው ባለቅኔዎች ስለወንድ ልጅ ፍቅር ይጽፉ ይሆናል እንጂ ስለውበቱ ስንኝ አያባክኑም፡፡ ስለሴት ልጅ ውበት ያልገጠመ ባለቅኔ ግን ባለቅኔ የሆነም አይመስለው፡፡ በውቀቱ ስዩም በኗሪ አልባ ጎጆዎች ውስጥ ‹‹ብታውቂ›› ብሎ የጻፋትን እናስታውስ፡-

ስትሥቂ!
ጠፈርን እንደምታደምቂ
መንፈስን ካዚም እስራት
እንደምታላቅቂ

ብታውቂ!

ስትስሚ!
አጥንት እንደምታለመልሚ
ታማሚ ልብ እንደምታክሚ

ብታውቂ!

ስታወሪ!
ዱዳ እንደምታናግሪ
መነኩሴውን ከሱባኤ፣
ፈላስፋውን ከጉባኤ
እንደምትጠሪ

ብታውቂ!

እንኳንስ በ’ኔ ልትሥቂ
ከራስሽ ጋር ፍቅር ይዞሽ
አይሽ ነበር ስትማቅቂ!!!

ማኅበራዊ ኑሮ እና የሥርዓተ ጾታ አሰላለፍ ቢሸፍነውም ተፈጥሮ ለሴት ልጅ አድልታለች፤ ለዚህ ክርክር አያስፈልገውም፡፡ የሰው ዘርን ወደ ምድር የማምጣት ኃላፊነት እና መንገድ የታደለው ለሴት ነው፡፡ ይህንን ታላቅ ሥራ እና ኃላፊነት ከሴት በቀር መቀበል እና መተግበር የሚችል ሌላ ፍጡር አልተሠራም፡፡ አይሠራምም! ሴት መሆን ይህንን የመውለድ ብቻ ሳይሆን የማሳደግ፣ የተፈጥሮ ምግብ የመመገብ የመሳሰሉትን መታደል አብሮ ይዟል፡፡ ይህ መታደል ማኅበረሰባዊ ጫናና ማጣጣል ቢጨመርበትም ከዚህ በላይ መታደል ምን አለ? ‹‹እናትነት እውነት፤ አባትነት እምነት›› ነው የሚለው አባባልስ የዚህን መታደል ጥቂቷን ያሳይ የለ!?

የሴት ልጅ መታደል ዘጠኝ ወር አርግዞ በመውለድ ፀጋ ብቻ አይወሰንም፤ ሌላው ቀርቶ በሥርዓተ ጾታ የሴት ልጅ በቤት ውስጥ መወሰን በራሱ የራሱ መታደል አለው፡፡ ሴት ልጅ (እናት) በቤት ውስጥ መዋል በመቻሏ ብቻ የታደለችው ምስጢር አለ፡፡ እናት ልጆቿን አቅርባ በምትፈልገው አቅጣጫ ማሳደግ ትችላለች፡፡ መቼም ‹‹ሴትን ማስተማር ማኅበረሰቡን ማስተማር ነው፤›› ሲባል ያልሰማ ሰው አይኖርም፡፡ ይህን ማለት ያስፈለገው ሴት/እናት ለልጆችዋ ያላትን ቅርበት ለማመልከት ነው፡፡ እናት ያፈራችው ዕውቀት ለልጇ መድረሱ አይቀርም የሚል መደምደሚያ ላይ ዓለም በመድረሱ ነው፡፡ ለመሆኑ ‹‹የእናት ፍቅር›› የሚለው ቃል ‹‹የአባት ፍቅር›› ከሚለው የጎላ ጣዕም እና ጉልበት እንዳለውስ አስባችሁት ታውቃላችሁ፡፡ እርግጥ ነው፤ ልጆቻቸውን እጅግ አድርገው የሚወዱ አባቶች ሳይቀሩ ‹‹እናት ናቸው›› የሚል ቁልምጫ ነው የሚሰጣቸው - መታደል ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አገር እንኳን የምትመሰለው በሴት/እናት ነው፡፡

አገር በሴት የምትመሰለው መውደድን ለመግለጽም ጭምር፡፡ ካመጣነው አይቀር ሴት ልጅ ተወዳጅ ብቻ ሳትሆን ተወዳጅ መሆኗንም መጥቀስ አለብን፡፡ ሴት ልጅ አፍቃሪ ናት፡፡ ምናልባት ከልቧ እስክታስገባ የሚፈጅባት ጊዜ ሊኖር ይችላል እንጂ ሴት ለጅ ስታፈቅር እንከን አልባ ፍቅር ነው የምታፈቅረው፡፡ ምንም ለራሷ ሳታስቀር ሁለ ነገሯን ሰጥታ ነው የምታፈቅረው፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ‹‹ሴት ልጅ ስታፈቅር ሙሉ ለሙሉ አይኗን ጨፍና ነው፤ ወንድ ግን አጮልቆም ቢሆን ያያል›› የሚባለው፡፡ ኃይለጊዮርጊስ ማሞ ‹‹ሴት እና ፈጣሪ›› ባሰኘው መድብሉ ላይ ‹‹ተፈጥሮ›› በሚል ርዕስ የጻፈው ግጥም ይህን ባሕሪዋን ከነቆራጥነቷ ደምሮ ያሳያል፡-

ሴት ካፈቀረችህ፥ ከተያዘ ነፍሷ፣
የቤተሰብ ክብር፥ ጨዋታ ነው ለእሷ፣
ከጠላችህ ደግሞ፥ ለዓይኗ ተፀይፋ፣
ፈጣሪንም ብትልክ፥ ትሄዳለች አልፋ፡፡

መሪነትስ ቢሆን?! አመራር የእኛ ነው፡፡ በአደባባይ ወንዶች ወንበሩ ላይ ይቀመጡ እንጂ የወንዶችን የውጪ የታይታ ዓለም፣ ከውስጥ ሴቶች ይቃኙታል፡፡ ቢበዛ መንገዱን ማወቅ ይጠይቅ ይሆናል እንጂ የሚፈለገውን አቅጣጫ የማስያዝ የተደበቀ ሥልጣን የሴቶች ነው፡፡ አልጋ ላይ ፓሊሲ ከማስቀየር ጀምሮ፣ የአልጋ ጨዋታን የመምራት ኃላፊነት የሴቶች ነው፡፡ ጠይቆ እምቢ አለመባል የውበት እና የኃላፊነት እመቤት መሆን ማኅበረሰብን መገንባት እና ሕይወትን ማጣፈጥ የሴቶች መታደሎች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን የተደበቀ የሴቶች በወንዶች ላይ የማዘዝ (ወይም በወንዶች ወኪልነት) የመምራት ሥልጣን ማንነቱን የማላስታውሰው ገጣሚ ጠቃቅሶታል፡፡ በቃሌ እንደማስታውሰው ልውጣላችሁ፡-

አንተ አዳም ራስ ነህ፥ ይላል ቅዱስ ቃሉ፣
አንች ሔዋን አንገት ነሽ፥ ብለው ያወራሉ፣
አንተ ራስ፣ እሷ አንገት
ብታሽከረክርህ ታዲያስ ምን አለበት?

ሌላው እና በብዙ ሰዎች እምብዛም ያልተስተዋለው ነገር ግን አሁንም የሥርዓተ ጾታው የፈጠረው ሌላ ዕድል አለ፤ የፍቅር ግንኙነት የመጀመር ኃላፊነት - ይኼ ኃላፊነት ሴት ላይ አልተጣለም፡፡ ሴት ልጅ እንደ ወንድ የወደደችውን ወንድ ለፍቅር የመጠየቅ እና ነገሮችን የመጀመር ኃላፊነት የለባትም፡፡ ይህንን የማድረግ ባሕላዊ ኃላፊነት ለሴት ልጅ አለመሰጠቱ ጉዳቱ የሚያመዝን የሚመስላቸው ይኖራሉ፤ እውነታው ግን ሴት ለጅ የወደደችውን ወንድ መጥቶ እንዲያነጋግራት የምትጋብዝበት ብዙ መንገድ ሁልጊዜም አላት፡፡ ዞሮ፣ ዞሮ እሷ ለምትፈልገው ግንኙነት ቀድሞ የሚያናግራት፣ ለማስቀጠል የሚጠበቅበትን ሀሉ የሚያደርገው እሱው ነው፡፡ እየፈለገች ተፈላጊ የመሆን ዕድሏ በጇ ነው፡፡
 
በየጊዜው ከሚነሱት ምሬት ብቻ የተሞላባቸው ጉዳዮች አንፃር ስናየው፥ ዛሬን እንኩዋን ሴትነትን እንዲህ ብናከብር ምናለ?!

No comments:

Post a Comment