በዳዊት ተሾመ
ኢትዮጵያ፣ ትግራይ እና ህውሓት ምንና
ምን ናቸው?
በሚል ርዕስ በበፍቃዱ ኃይሉ የቀረበው ጹሑፍ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ የሚያጠነጥነበትን ነገር ግን በአብዛኛው ለግልጽ ውይይትና ክርክር፣ ለመድረክ
ያልበቃ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ነው:: ለመድረክ ያለመብቃቱ ምክንያት በአብዛኛው ግልጽ ውይይት ያላደበርን በመሆናችንና ከብሔር ፖለቲካ
ስስነት ጋር የተያያዘ ይመስለኛል:: በተጨማሪም ብዙዎቹ የሀገራችን ምሁራን በጉዳዩ ላይ የተለያዩ መጽሐፍቶችና ጹሑፎችን ቢጽፉም፤
የጻፉበት ቋንቋ በአብዛኛው በእንግሊዘኛ ስለሆነና የጻፉትም ለውጭ ታዳሚዎቻቸው ስለሆነ የጉዳዩ ባለቤት ባዳ እንዲሆን አድርጎታል::
ይህንን ዝግ ጉዳይ ጸሐፊው ለመስበር መሞከሩ በርታ የሚያስብል ነው:: ጽሑፉ ብዙ የምስማማባቸውን ሐሳቦች ያዘለ ነው:: ሆኖም ግን፣
በዚህ ጽሑፌ ሊታዩ ይገባቸዋል ብዬ ያሰብኳቸውን፣ ጸሐፊው በግልጽ ያላስቀመጣቸውንና በተወሰነ መልኩም አመክኖያዊ ግድፈቶችን ለመጠቆም
ያህል ነው::
(1).
በሳይንሳዊ ምርምር ምልዕ-እውነት (100% truth) የሚባል ነገር የለም:: ምርምር
በራሱ ማስረጃዎች ላይ የተደገፈና በተወሰነ ንድፈ-ሐሳባዊ መሠረት ተመስርቶ
በመከራከር፣ በመቃወም፣ እንዲሁም አዳዲስ ዕሳቤዎችንና ዕይታዎችን በማፍለቅ ወደ እውነት በተቻለ መጠን የመጠጋት ሒደት
ነው:: ስለዚህም እውነት አንጻራዊነትን (relativity) የሚላበስ እንጂ ሁለንተናዊ (absolute) አይደለም:: ስለሆነም፣
ለአንድ ሰው ውይም ቡድን በአብዛኛው እውነት የሆነው ነገር ለሌላው ሰው ውይም ግሩፕ እውነት ሊሆን እንደማይችል ታሳቢ መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው:: በአንድ የተወሰነ
ሐሳብ ውይም ጉዳይ ላይ የተለያዩ ዕይታዎችን (school of thoughts) የምናገኘው ለዚህ ነው::
(2).
ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ሕወሓትን ይደግፋሉ የሚለው ስነ-አመክኖ (logic) ሲገለበጥ ሁሉም የትግራይ
ተወላጆች ተጠቃሚ ናቸው ወደሚለው ጭብጥ ያደርሰናል:: በዚህ ሐሳባዊ ዕይታ ተመስርቶ በጸሐፊው “የሕወሓት/ኢሕአዴግ ደጋፊዎች ቁጥር ከትግራይ ተወላጆች ቁጥር ጋር እኩል ነው“ ወደሚል
ክርክር ይሸጋገራል::
በቅርቡ በታተመውና በኢሕአዴግ ዌብ-ሳይት ላይ የተለቀቀው ሰነድ (EPRDF: In Brief) እንደሚያመለክተው ከሆነ የኢሕአዴግ
የአባላት ቁጥር እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2005 የነበረው 700,000 ሲሆን በ2013 ደግሞ 6.5 ሚሊዮን ነው (ገጽ 3 ይመልከቱ)::
ይህንን ቁጥር ከትግራይ ሕዝብ ቁጥር ጋር ማመሳሰል በመሰረቱ ሁለት ስህተቶች አሉት:: አንደኛው የትግራይ ሕዝብ ብዛት በ2005ዓ.ም
700,000 ብቻ አልነበረም:: ስለዚህም ሁሉም የትግራይ ሕዝብ ሕውሓትን ይደግፋል የሚለው ተጨባጭ እውነታ ሊሆን አይችልም:: ሁለተኛ
ይህ ማመሳሰል የተቀሩትን የግንባሩ አባል ድርጅቶችን ዕውቅና የመንሳት አካሔድ ውጤት ነው:: በመሠረታዊነት ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ
ለድርጅቶቹ ተገቢውን እውቅና ሰጥቶ በማዕከላዊ የስልጣን ድልድሎሽ ላይ ያላቸውን ዝቅተኛ ድርሻ፣ ደካማ ውስጣዊ አቅም እና አነስተኛ
ሕዝባዊ ተቀባይነታቸው ላይ ተንተርሶ መገምገም ይቻላል::
(3).
የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ‹‹ትግራይ የሆነና ትግራይ ያልሆነ›› ብሎ መለየቱ
በኔ አስተሳሰብ የድሮውን አካሄድ መድገም ነው:: ይህም ንደፈ-ሐሳባዊ መሠረቱ በዋነናነት በ1970ዎቹ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አስተሳሰብ
የተጫነው የታሪካዊ ማቴሪያሊዝም ማኅበረሰባዊ አረዳድ ነው:: ከኔ ጋር ያልሆነ ከነሱ ጋር ነው ማለት መሐከል ላይ ያለውን የማኅበረሰብ
ክፍል ማጣጣል ነው:: እንደሚባለውም፣ እውነት ያለቺው መሐከል ላይ ነው እንጂ በግራም ሆነ በቀኝ ጫፎች ላይ አይደለም:: ጆህን
ማረካኪስ የተባለው ጸሐፊም እንዲሁ Ethiopia: The Late Two Frontiers ብሎ በሰየመው መጽሐፉ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ
ማኅበረሰብ በሁለት ከፍሎ ለማሳየት ሞክሯል:: ልዩነቱ ጸሐፊው ሐሳቡን የመሠረተው በብሔርተኝነት ላይ ሲሆን ማረካኪስ ደግሞ ጂኦግራፊክ
አሰፋፈር፣ ሃይማኖትንና ብሔርተኝነት ላይ መመሥረቱ ነው:: ይህ አካሄድ ግን በዋነኛነት የኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል
ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች አቅልሎ የሚመለከት ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል
ያለውን የመተባበር ላይ የተመሠረት ግንኙነት እና በተማሩ በሚባሉት መካከል ያለውን የስልጣን ፉክክርና ትግል ጨፍልቆ የማየትና የኋለኛውን
የማጉላት አካሄድ እየተስፋፋ መምጣቱን የሚያመለክት ነው::
(4).
አረናን በተመለከተ የቀረበው በኔ አስተሳሰብ ቁንጽል ሐሳብ ነው:: በመጀመሪያ
ደረጃ ሦስትም ሰው ሆነ 50 ሰው ከሕውሓት ተገንጥለው ከወጡት ውስጥ አረናን ያቋቋሙት፣ መነሳት የነበረት ሐሳብ እነዚህ ሰዎች ‹ሕውሓትን
ለቀው (“ተባረው”) የወጡት በአካሄድ ደረጃ ባለመስማማታቸው ነው ወይስ በመርሕ፣ ስትራተጂና ግብ ላይ ባለመስማማታቸው?› ነበር::
አረናን የመሠረቱት ሰዎች (ከሕውሓት ተገንጥለው የወጡትም ሆነ ሌሎች) የትግራይን የበላይነት ለማስቀጠል በሚያስችሉ የአካሄድ ጉዳዮች
ላይ ብቻ ከሆነ ከሕውሓት ጋር የሚለያዩት፣ አረና የመድረክ አባልም ሆነ አልሆነ በመሠረታዊነት አሁን ጸሐፊው ያነሳውን ችግር ሊቀርፍ
የሚያስችል ሳይሆን ይበልጡንም ችግሩን የሚያስፋፋና ቅርቃር (deadlock) ውስጥ የሚከት ነው:: በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በፖለቲካ
ታክቲክና ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ትርፍ ሲባል ብዙ የተቋቋሙ ኅብረቶችን፣ ቅንጅቶችንና አንድነቶችን ማየታችንን ታሳቢ በማድረግ የአረና
መድረክን መቀላቀል ይህን ያህል ሊያስገርመን የሚችል ጉዳይ አይደለም:: ይህ ከሆነ በመሠረቱ አረና መድረክን የተቀላቀለው ለፖለቲካዊ
ታክቲክ እና የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚለው መርሕ ላይ በመመሥረት ይሆናል:: ነገር ግን አረና ከሕውሓት የሚለይበት ጉዳይ በመርሕ፣
ስትራተጂና ፖለቲካዊ ግቦች ዙሪያ ከሆነ እውነትም አረና መድክን መቀላቀሉ ጸሐፊው እንደሚለው „ሌላውን በማጥፋት መኖር ሳይሆን ሌላውን በማኖር አብሮ መኖር“ ላይ የተመሠረተ አዲስ ፖለቲካዊ ባሕል
የሚያስተዋውቅና አሁን የተከሰተውን ችግር ሊፈታ የሚያስችል አካሄድ ነው:: ስለዚህም የአረናን ዝርዝር ማኔፌስቶና ፖለቲካዊ ግቦች
ሳያውቁና በትንታኔ ሳይደግፉ እንዲሁ ‹በዘር ፖለቲካ የተለያየውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ማኅበረተስብ መልሶ ማስታረቅ ይቻላል› ማለት
አይቻልም:: የአረናን ዝርዝር ማኔፌስቶና ፖለቲካዊ ግቦች ማወቅና በትንታኔ መደገፍ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፤ የጸሐፊውን ዕሳቤ ለመደገፍም
ሆነ ለመቃወም::
የዘር ፖለቲካን
በተመለከተ:- የዘር ፖለቲካ መሠረታዊ ባሕሪው አዳላጭ መሆኑ ነው:: ብዙ የብሔር ቡድኖች በአንድ አገር ውስጥ መኖራቸው በመሠረታዊ
ደረጃ እንደ ችግር የሚታይ አይደለም:: ችግሩ የሚመነጨው በብሔር ቡድኖች መካከል ያለው ግንኙነት ከትብብርና ከዕኩል ተጠቃሚነት
ወደ የበላይነትና አድሎአዊነት ሲሸጋገር ነው:: የሕውሓትንና የትግራይ ብሔርተኛነትን የፖለቲካ ታሪክ ከዚህ እውነታ የሚወጣ አይደለም::
የዘር ፖለቲካ አዳላጭነቱ የሚመነጨው አመክንዮአዊነትንና ምክንያታዊነትን ሽሮ ‹‹እኛ እና እነርሱ›› ወደሚለው አስተሳሰብ ሲወርድ
ነው:: ይህ እኛ እና እነርሱ አስተሳሰብ በጥርጣሬና ምናባዊ ዕሳቤ አሉ የሚባሉ ልዩነቶችን አስፍቶ የሚያሳይ በተቃራኒው የአንድነትን
ጉዳዮችን ፖለቲካዊ ትርጓሚ በመስጠት የሚያቀጭጭ ነው:: ስለዚህም አንድ ብሔር በጥርጣሬ መታየት ሲጀምር ለኔ ይቀርባል ወደሚለው
የፖለቲካ ቡድን ይበልጥ የሚገፋው ሲሆን በሌሎች የብሔር ቡድኖች ደግሞ ይበልጥ ባይተዋርነትን የሚፈጥር ይሆናል:: ይህ ሁኔታ በደንብ
ከተለጠጠ ደግሞ የደም ዘርን ወደመቁጠር ይወርዳል:: ለምሳሌ ጃዋር መሃመድ በ2010 ባወጣው ጹሑፍ (Tigrean
Nationalism: From Revolutionary Force to Weapon of Repression) ላይ
እንዳመለከተው አሁን ያለው ሕውሓት የትግራይን ብሔርተኝነት የሚወክል አይደለም ምክንያቱም ንፁሕ የትግሬ ተወላጆችን በማባረር ግማሽ
ትግሬ ግማሽ ሌላ ዘር (በአመዛኙ ኤርትራውያን) የሆኑ የተቆጣጠሩት ድርጅት ነው:: በቅርቡም ፕ/ር ተስፋፅዮን መድኃኔ ተመሳሳይ
የሆነ ሐሳብ ኤርትራን በሚመለከት ባወጡት ጽሑፍ ላይ አንፀባርቀዋል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፖለቲካ ልሂቃኖች ደግሞ የዘር ፖለቲካን
ድጋፍ ለማሰባሰቢያና አገዛዛቸውን ቅቡል ለማድረግ ሲሉ አንዱን ያቀረቡና የጠቀሙ በመምስል እና ሌላውን የመግፋት አካሄድ በመጠቀማቸው፤
የዘር ፖለቲካ የግጭትና የጦርነት ምክንያት እንዲመስል አድርጎታል:: አሁንም ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ሕውሓትን ይደግፋሉ፤ ተጠቃሚም
ሆነዋል የሚለው አስተሳሰብ የዘር ፖለቲካ አዳላጭነትን የሚያመላክት ነው::
---
ጸሐፊውን ለማግኘት
የኢሜይል አድራሻቸውን dhabesha@hotmail.com ይጠቀሙ፡፡
Want To Boost Your ClickBank Banner Commissions And Traffic?
ReplyDeleteBannerizer makes it easy for you to promote ClickBank products by banners, simply visit Bannerizer, and grab the banner codes for your chosen ClickBank products or use the Universal ClickBank Banner Rotator to promote all of the ClickBank products.