Saturday, February 23, 2013

የቅድመ ምርመራ ቅድመ ምርመራ





ስለ ቅድመ ምርመራ ስናወራ ሃሳቡን በጠንካራ ሁኔታ ተግባራዊ ያደረገው የደርግ መንግስት ሳይጠቀስ አያልፍም፡፡ ከዚያ በፌት በነበረው ጊዜ ‹ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ› የሚለው አስተሳሰብ በስፋት ስለሚታመንበት ንጉሡን ከሚያወድስ እና የንጉሡን ፈቃድ ከሚያሟላ የህትመት እና የብሮድካስት  ስራዎች ውጪ ለመስራት ሃሳብ አልነበረም፡፡ የደርግ መንግስት የንጉሡን ስርዓት ካስወገደ በኋላ ደግሞ የቅድመ ሳንሱር ጉዳይን ጠበቅ ባለ በሕግ ደንግጎ ቀረበ፡፡ ሳንሱር ሳይደረጉ መፅሃፍት አይታተሙም፡፡ ሌሎች የህትመት ውጤቶችም የሚያስተላልፉት መልዕክት ስርዓቱ የሚደግፈውን ርዕዮተ ዓለም ፅንሰ ሃሳብና አስተሳሰብ ብቻ ነበር፡፡ በሃገራችን ባይታተምም ውጭ ሃገር የታተሙ ከስርዓቱ ጋር የሚፃረር ወይም የሚተች መልእክት ያለውን መፅሃፍ/የህትመት ውጤት ለማንበብ እንኳን አይቻልም፤ ወይም እንደ ሰረቀ ሰው ተደብቀው ነበር የሚያነቡት፡፡

ከደርግ ቀጥሎ የመጣው የኢህአዴግ መንግስት ደግሞ የህትመት ነፃነት ያስፈልጋል በሚል ቅድመ ምርመራም ክልክል እንደሆነ አወጀ፡፡

አንቀፅ 29.3 ሀ/ ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን››

ይህን ህግ መሰረት በማድረግም በሬድዬና ቴሌቭዥን ደረጃ የታየ ለውጥ ባይኖርም ብዙ የግል ሃሳብ የሚንፀባረቅባቸው ጋዜጦችና መፅሄቶች ተፈለፈሉ፡፡ ለ97 ሃገራዊ ምርጫም እነዚህ የግል የህትመት ውጤቶች ህብረተሰቡን በማንቃት እና የሃራቸው ፖለቲካ ጉዳይ ያገባኛል ብለው እንዲያስቡ በማድረግ ረገድ አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢህአዴግም በምርጫው ውጤት እና በህዝቡን ስሜት ተደናግጦ ይመስላል ከ97 ምርጫ በኋላ በሰበብ አስባቡ ጋዜጠኖችንና አዘጋጆችን ማሰር እንዲሁም ለራሱ የሚመች ለትርጉም የማይመች እና ከፕሬስ ጋር የተያያዙ ህጎችን ማውጣት እና ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው፡፡


ኢህአዴግ ስለዲሞክራሲያዊ መብቶች ህግ ላይ የማስፈርና የመናገር ችግር የለበትም፡፡ በግልፅ እንደሚታየው በህገመንግስታችን አንቀፅ 29 ላይ ‹የአመለካከት እና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት› በሚል ርእስ በሰባት ንኡስ አንቀፆች ተከፋፍሎ በቂ የሚባል ሽፋን ተደርጎለታል፡፡ ባለስልጣኖቹም ይቺን አንቀፅ ደጋግመው ያነበንቡልናል፡፡ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በተመለከተም የሚመለከታቸው የመንግስት ሰዎች ሲጠየቁ ‹የታሰረ ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ የለም› ይሉናል፡፡ እውነቱን እና በተግባር የምናውቀው ግን በተቃራኒው ነው፡፡

ህገመንግስቱ የሰጣቸውን መብት ተጠቅመው ሃሳባቸውን በነፃ ለመግለፅ የሞከሩት የተለያየ የወንጀል ስያሜ እየተፈጠረላቸው እስር ቤት እንዲገቡ እየተደረገ ነው ተብሎ መንግስትም በተደጋጋሚ ሲታማ ይሰማል፡፡ ከእስሩ ጋር ተያያዥ የሆኑት እንግልት፣ ድብደባ እና ስቃይን የመሳሰሉ ውንጀላዎችን ሳንዘነጋቸው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት ደግሞ ወይም ተሰደዋል ወይም መስራት አቁመዋል፡፡ የተቀሩት ከነገ ዛሬ የጓደኞቻቸው እጣ እንደሚደርሳቸው የስጋት እና የሰቀቀን ኑሮ ውስጥ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ እንግዲ ለሃገራችን ምን ያክል ኪሳራ እንደሚያስከትል ለመገመት ፊደል መቁጠርም አያስፈልግም፡፡

 የቅድሚያ ምርመራ በማኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን የምትገልፀዋ አንቀፅ የምታገለግለው ልክ አይጥ ወጥመድ ላይ እንደሚቀመጥ ምግብ ነው፡፡ አይጧ ምግቡን ብላ ስትመጣ ወጥመዱ እንደሚይዛት ሁሉ በአንቀፅ 29 ላይ የተደነገገውን መብት ተጠቅሞ ሃሳቡን ለመግለፅ የሚሞክርም እንዲሁ በወጥመዱ የመያዝ አደጋ ይገጥመዋል፡፡ ስለዚህ ህጉ ኖረም አልኖረም ልዩነት የለውም ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ኪሳራው ይበዛል፡፡ የፍትሕ ጋዜጣን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ ህትመት በሚገባበት ወቅት ከመታተሙ በፊት ጋዜጣው ላይ ሊወጣ የነበረ ዜና እንዲያስወጡት ለአዘጋጆቹ ከማተሚያ ቤት ተነገራቸው፡፡ አዘጋጆቹ ደግም ይህ የቅድመ ምርመራ እገዳውን እንደሚፃረር ሲነግሯቸው ጋዜጣውን አተሙትና ከታተመ በኋላ (ከስርጭት በፊት) እንዲታገድ ተደረገ፡፡ እንግዲህ በአታሚውም በአሳታሚውም ወገን የሚያስከትለውን ኪሳራ አስቡት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ትዝታችን እንኳን ብንጀምር፤ ባሳለፍነው ሰባት ወር ጌዜ ውስጥ ሦስት ጋዜጦችና አንድ መፅሔት ታግደዋል፡፡ በነዚህ የህትመት ውጤቶች ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩት ፀሃፊያንና ጋዜጠኖችም የስራ አጥነት አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህን የሚያዩ የጋዜጠኝነት እና ስነፅሁፍ ተማሪዎች እንዲሁም የመፃፍ አቅሙና ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶችም ተስፋቸው የመነመነ ይሆናል፡፡ ኪሳራው ብዙ ነው፡፡ ተዘርዝሮ የሚያልቅም አይደለም፡፡

በሕገመንግስቱ የተደነገገልንን ‹የአመለካከት እና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት› እና ‹‹የቅድሚያ ምርመራ በማኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን›› መብት ከመንግስት ባልተናነሰ መልኩ የሚጥሱ አካላት መበራከት ደግሞ ሌላው በቅርቡ እየተስተዋለ ያለ ቀላል የማንለው ችግር ነው፡፡ዋናዎቹ ማተሚያ ቤቶች እና የሆቴል ወይም የአዳራሽ ባለቤቶች ሲሆኑ በአሁን ሰዓት እነዚህ አካላት ህትመቶች ወይም ነፃሃ ሳቦች ለህዝብ እንዳይደርሱ በማድረግ ረገድ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ ማተሚያ ቤቶች በራሳቸው ስልጣን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ወይም መንግስትን የሚተቹ  መፅሃፎችን ለማተም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ የስብሰባ አዳራሽ ያላቸው ሆቴሎች ባለቤቶች እና መሰብሰቢያ አዳራሽ ብቻ ያላቸው ቦታ ባለቤቶች የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወይም ሌሎች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ስብሰባዎችን ለማስተናገድ እንዲሁ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ዋና ዋናዎቹን ጠቀስኩ እንጂ የመንግስት አካል ጋር ሳይደርሱ የሚከሰቱ እገዳዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይህን ነው የቅድመ ሳንሱር ቅድመ ሳንሱር የምለው፡፡ እራሳችን በራሳችን ወይም በቅርብ ጓደኞቻችንም ሳንሱር እንደረጋለን፡፡ ከምናወራው ሰው ጋር ሃሳባችንን ሙሉ በሙሉ ለመናገር የማንደፍር ወይም አይምሯችን ውስጥ እየቆረጥን የምናስቀረው ከሆነ እራሳችንን ሳንሱር አደረግን ማለት ነው፡፡ ፅሁፍም ፅፈን ከሆነ በቅርብ የሚያይልን ሰውም ከመንግስት ሊመጣ የሚችለውን ቅጣት ስጋት ‹ይቺን አስወጣት› የሚል ከሆነ እሱም ሳንሱር እያረገን ነው፡፡ በርግጥ የቅድመ ሳንሱር ቅድመ ሳንሱር መበራከት ከመንግስት ጋር ላለመሳፈጥ፤ ከመንግስት አይን ራቅ ብሎ ሰላማዊ ኑሮ ለመምራት የሚደረግ ጥረት እና የመንግስትን ዱላ ከመፍራት የመጣ ነው፡፡ መንግስትም እንዲህ አይነት አካላት መኖራቸውን አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ ባለፈው ፓርላማ ላይ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ሲናገር እንደሰማነው የማተሚያ ቤትን እና የመሰብሰቢያ አዳራሽን አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ ችግሩን የማተሚያ ቤቱ እና የአዳራሽ ባላቤት እንደሆነ እና ጠያቂውም ከነሱ ጋር እንዲጨርስ እንጂ የመንግስት ጥፋት እንዳይደለ ተነግሯል፡፡

አሁን በሃገራችን እንደምናስተውለው ጥቂት ደፋሮች ወይም ፍርሃታቸውን ያሸነፉ ብቻ ናቸው ሲፅፉ ወይም ሲያወሩ የምንሰማው፡፡ የአብዛኛዎቻችን ስራ ደግሞ ስራዎቻቸውን አይተን/አዳምጠን የገቡበት ገብተን ጎበዝ! ጀግና! በርታ! ማለት፤ ሲታሰሩ ካለንበት ፈቅ ሳንል ዘላቂነት የሌለው አይዞህ! አይዟችሁ! እንላለን-ሄድን ልንጠይቃቸው እንኳን አንፈቅድም ወይም ድፍረቱ የለንም፤ ሲሰደዱ ደግሞ እንሳደባለን፡፡ በቃ ይሄ ነው የአብዛኞቻችን የስራ ድርሻ - ተመልካችና ፈራጅ፡፡ መመልከትና መተወን በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡

ሃሳቤን ለመጠቅለል ያክል ጥቂት ፍርሃታቸውን ያስወገዱትን ብቻ እንዲናገሩ ወይም እንዲፅፉልን ብቻ ከምንጠብቅ እራሳችንም የድርሻችንን በመወጣት፤ እራሳችንን ወይም በቅርብ ያሉትን ጓደኞቻችን ማስፈራራት፣ ተስፋ ማስቆረጥና ሳንሱር ማድረጋችንን ብንተውና ሁላችንም ፍርሃታችንን በተወሰነ መጠን አሰወግደን ሃሳባችንን ያለፍርሃት መግለፅ ብንጀምር እንዲሁም በመጠኑ ህገመንግስቱ ላይ የተፃፈውን መብታችንን እንኳን ለማስከበር ቆርጠን ብንነሳ ለውጥ ማየት የምንችል ይመስለኛል፡፡ 

No comments:

Post a Comment