Sunday, February 3, 2013

“መክሸፍ” እንደተቃዋሚ ፓርቲዎች


በዘንድሮው የሟሟያ ምርጫ 29 ያህል ፓርቲዎች አንወዳደርም የሚል የጋራ አቋም ይዘዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ከምርጫ ቦርድ ጋር ለመደራደር ያወጧቸው ዝርዝር ጥያቄዎች ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ነው ላለመወዳደር የወሰነው ሲሉም አሳውቀዋል፤ እንደነርሱ አባባል ሚዛናዊ ምርጫ በማይካሔድበት እና እራሱ ምርጫ ቦርድም ሚዛናዊ ባልሆነበት መድረክ ተወዳድሮ ማሸነፍ ስለማይቻል፤ ተወዳድሮ ምርጫ አድማቂ ከመሆን አለመወዳደር ይሻላል፡፡ ኢሕአዴግም የእነዚህ ተቃዋሚዎች በምርጫ አለመሳተፍና መሳተፍ ለኢህአዴግ ትርፍም ኪሳራም እንደሌለው በግልጽ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚዎቹን አንድ ጥያቄ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

የፓርቲዎች አባላት ጉዳይ

አንድነት ፓርቲ (በተለይ አንዱአለም ከመታሰሩ በፊት በቋሚነት) ምሁራንን እየጋበዙ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሕዝባዊ ውይይቶችን ለማካሔድ ሞክረዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ይህንኑ ፈለግ በመከተል ጥቂት ውይይቶችን አካሄዷል፡፡ በነዚህ ስብሰባዎች ላይ ግን የሚገኙት ሰዎች ቁጥር በዛ ከተባለ አንድ መቶ ቢደርስ ነው የተለየ የሰዎች ቁጥር መጨመር ይታይበት የነበረው የአንድነት ፓርቲ የየሁለት ሳምንቱ ውይይትም በአጭሩ ቀርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድነት ፓርቲ ለፖለቲካ እና ሕሊና እስረኞች በወር አንድ ጊዜ የሚያደርገው የሻማ ማብራት ፕሮግራም ላይ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር 20 የማይሞላበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ ቁጥርም የታሳሪዎችን  ቤተሰብ ጨምሮ መሆኑንም ማስታወስ ያሻል፡፡ የሻማ ማብራት ፕሮግራም ማዘጋጀታቸው እና በወር አንድ ጊዜ እስረኞች እንዲታወሱ ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ሆኖ በፕሮግራሙ ላይ የሚገኘውን ታዳሚ ቁጥር ማነስ እና ከዕለት ወደ ዕለት እየተመናመነ መሄድ የተሳታፊዎችንም የአዘጋጆችንም ተነሳሽነት እንደሚፈታተነው እሙን ነው፡፡

እነዚህ ፕሮግራሞች ላይ ሕዝቡ የማይገኝባቸውን ሁለት ዐበይት ምክንያቶች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አንደኛ፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ያዘጋጀው ስብሰባ ላይ መገኘት ስለሚያስፈራ፣ ሁለተኛ፤ ስብሰባዎቹ በበቂ ሁኔታ ስለማይተዋወቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ሕዝቡ መካከል ያለው ርቀት ሰፊ ስለሆነ እንዲሁም ማስታወቂያ ስለማይሰራላቸው እና ስለማይሰሙ ነው፡፡ ሁለቱንም ችግሮች መቅረፍ ግን የተቃዋሚዎቹ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡


ፓርቲዎቹ ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ርቀት ለማጥበብ፣ የሕዝቡን የፍርሐት ስሜት በአርኣያነት የመግፈፍ እና ማስታወቂያ በአግባቡ የመሥራት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያዘጋጁዋቸው ስብሰባዎች ላይ ቢያንስ መሐል ከተማ ያሉ አባላቶቻው እንዲገኙ የሚያስገድድ መመሪያ በማኖር፤ የሻማ ማብራት ሥርዐቶቹ ላይ በየክልሉ ባሉት ቢሮዎቻቸውም በተመሳሳይ ሰዐት ሥርዐቱን በማካሔድ አገር አቀፍ ጉዳዩን የማሳሰብ እና ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡

በነዚህ ፕሮግራሞች ላይ የሚሳተፈው ሰው ማነስ በሕዝብ እና በፓርቲዎቹ መካከል ያለው ርቀት ማሳያ ነው፡፡ ሕዝቡን መቅረብ ዓላማቸው ከሆነ (መሆንም አለበት…) ችግሩን በማመን ለመቅረፍ ስትራቴጂ መቅረጽ አለባቸው፡፡ አባላቶቻቸውም ከወር መዋጮ የበለጠ፣ የፋና ወጊነት ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ፕሮግራሞች እና ሌሎች ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ችግሮች ዙሪያ ሞዴል ሁነው ፍርሐት ከመጋፈጥ ተግባራዊ እርምጃ እስከመውሰድ ድረስ መራመድ አለባቸው፡፡

ይህንን ማድረግ ባለመቻላቸው ብቻ የፕሮግራሞቹ ፋይዳም ሆነ ውጤት ጎልቶ አይታይም፤ የታዳሚዎቹ ቁጥርም ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት አሏቸው እንዴ ብለው እስከመጠየቅ እየደረሱ ነው፡፡

የአባሎቻቸው ስብጥር

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለአባሎቻቸው ብዛት እና ስብጥር የሚያወጡት መረጃ በጣም የተገደበ ነው፡፡ እርግጥ ይህ ምስጢራዊነት በአባሎቻቸው ብቻ ሳይሆን በፖሊሲዎቻቸው እና የትግል ስልቶቻቸውም ለሕዝብ ቶሎ ቶሎ ባለማስተዋወቅም ጭምር ነው የሚንጸባረቀው፡፡ የአባላቶቻቸውን ዝርዝር መረጃ ማውጣት ባለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ለአባላቱ የደኅንነት አደጋ አለው ቢባል እንኳን በቁጥር ደረጃ ለምን አያሳውቁም? ግልጽነት የተሞላው አሠራር የሚጀምሩት የመንግሥት ሥልጣን ሲይዙ ብቻ ነው? የአባሎቻቸውን ቁጥር፣ የዕድሜ ሁኔታ፣ በየክልሉ ያላቸውን የአባል ብዛት፣ የሴት አባላቶቻቸውን ብዛት፣ በየወሩ ከአባላት መዋጮ እና በልገሳ የሚሰበስቡትን ገንዘብ እና ሌሎችም ለሕዝብ ይፋ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ማስመስከር እና በሕዝብ ለመገምገም እና ለመመረጥ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ግን ኢሕአዴግ ሕዝብ ላይ በሚያደርሰው በደል ብቻ ተማርሮ ‹‹ተበድሏልና ይምረጠን›› ማለት አሁን ያለው የፖለቲካ ምኅዳር ጥበት ተጨምሮበት የመመረጥን ነገር ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› ያደርገዋል፡፡

ለምሳሌ ‹ተቃዋሚዎቹ ለወጣቱ ምን ዓይነት ቦታ ሰጥተዋል?› የሚለውን ጥያቄ ብናነሳ (ወጣት በኢትዮጵያ ስታትስቲክ ኤጀንሲ መስፈርት መሰረት ከ14 እስከ 29 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ዜጋ ነው፡፡)  በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ስንት አባላት አሏቸው? ከፓለቲካ የራቀውን ወጣት አባል እንዲሆን የሚያደርጉት ምን ማበረታቻ አለ?  የወጣት ክንፍ አላቸው ወይ? ወጣቱን በፓርቲዎቻቸው የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በማስቀመጥ የሥልጣን ሽግግር አድርገዋል ወይ/የሚያደርጉበት አሠራርስ አላቸው ወይ? የሚሉትን ጉዳዮች የሚመልስ አሠራር አይተናል ለማለት ያስቸግራል፡፡

አናሳውን ማሳደግ

የምርጫ 2002 ውጤት ብዙ ችግር ነበረበት፡፡ ከችግሮቹ መካከል ብዙኃኑ ተቃዋሚ ካርድ አለመውሰዱ፣ ከወሰዱት ውስጥም ገሚሱ አለመምረጡ ትክክለኛውን ውጤት አያንፀባርቅም ያስብላል፡፡ ሆኖም የመጨረሻውን ውጤት ብቻ ይዘን ለዚህ ጽሑፍ እንዲመቸን እንነሳ፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባ ብቻ 564,813 (54.2%) ያህሉ መራጮች ለኢሕአዴግ ድምፃቸውን ሲቸሩ 380,355 (36.5%) ደግሞ መድረክን መርጠዋል ይለናል የምርጫ ቦርዱ ውጤት፡፡ እዚህ ጋር ከ380 ሺህ በላይ መራጮች መድረክን ለመምረጥ ከቻሉ ለመድረክ በራቸውን ክፍት አድርገው ነበር ማለት ነው፡፡ መድረክ እነዚህን መራጮቹን ይዞ ከምርጫው ወዲህ ምን ሠራ? እነዚህ ሰዎች መድረክን በመምረጣቸው ምክንያት ፓርላማ ውስጥ ወኪል አላገኙም፤ ይህንን ለማካካስ ፓርቲው የነርሱን ድምጽ ለመሰብሰብ ብሎም ለማስተጋባት ያደረገውስ ጥረት ምንድነው? የሚለውን ስንመለከት በትንንሽ ስኬቶች ላይ መሠረት አድርጎ የማሳደግ ስራን እንደስትራቴጂ መጠቀም የተቃዋሚው ሰፈር ችግር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ዘመኑን መዋጀት

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ አባላት እና አመራሮች የ‹ያ ትውልድ› አባላት ናቸው፡፡ አተኩሮ ለሚመለከታቸው ብዙዎቹ የዘመኑን ችግር እና መፍትሔ የሚያውቁት አይመስሉም፡፡ በዚህ ዘመን ነገሮች የሚቀያየሩት በፍጥነት ነው፡፡ መረጃ በየደቂቃው ከዚያኛው ዓለም ጫፍ ወደዚህኛው ዓለም ጫፍ ይፈሳል፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ግን መረጃ በየወቅቱ እና ከዓለም የመረጃ ፍሰት እኩል በሆነ ፍጥነት ሊያቀብሉ ቀርቶ የማቀበያው መንገድም የላቸውም፡፡ ብዙዎቹ ድረገጽ የላቸውም፣ የሚታተሙ ጋዜጦች የሏቸውም፣ (ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው) ሰዎች ወደነርሱ ሒደው መረጃ እንዲጠይቁ እንጂ እነርሱ መረጃዎቹን ለዜጎች ለመስጠት የሚያስችላቸውን አሠራር አይከተሉም እንጂ ብዙዎቻቸው ቢያንስ የፌስቡክ እና የትዊተር ገጽ ሊኖራቸው ይገባ ነበር፡፡ የፌስቡክ እና የትዊተር ገጽ ያላቸው ጥቂቶቹም ቢሆኑ የወጣቱን ልብ ለማግኘት እና ዘመኑን ለመዋጀት ሲጠቀሙበት እና የተለያዩ መረጃዎችን በፍጥነት እና በተገቢው ሁኔታ ሲያስተላልፉም አይታይም፡፡ የአባላቶቻቸውን መንገላታት መታሰር የተለያዩ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የፓርቲያቸውን ፓሊሲ እና ዕቅድ የአባላቶቻቸውና የአመራሮቻቸውን ሥራዎች የሚያሳይ ምንም ነገር አይታይም፡፡ ቴክኖሎጂው የሰጣቸውን አማራጭ ሐሳብን የማስተላለፊያ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ የተለመደው መንገድ ላይ የሚደርስባቸውን ችግር ያለምንም አማራጭ እርምጃ  ሲያስተጋቡ ይስተዋላል፡፡

‹‹ነጻነት የማያውቁ ነጻ አውጪዎች››

ድረገጽ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድረገጻቸው በኢትዮጵያ እንዳይታይ ታግዶባቸዋል፡፡ አንድነትን (andinet.org) ጥሩ ምሳሌ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንድነት የታገደበት ድረገጹ ብቻ አይደለም፤ በየሣምንቱ ያሳትመው የነበረውም ጋዜጣ ጭምር ነው፡፡ ፓርቲው እንዲህ ዓይነቶቹን ሕጋዊ መብቶቹን ለማስከበር የወሰዳቸው አርምጃዎች ካሉ እነርሱን አላሳወቀም ወይም ምንም እርምጃ አልወሰደም፡።(በፓርላማ የጋዜጣውን ጉዳይበተደጋጋሚ ከማንሳት በስተቀር)  ይህ ያሉትን የሕግ አግባቦች እስከመጨረሻው እንኳን ሳይጠቀሙ ተስፋ አናገኝም በሚል የተስፋ መቁረጥ አዝማሚያ ማሳየት እንዲህ ዓይነት ችግሮችን መፍታት ያቃተው ፓርቲ እንዴት የተወሳሰበውን የኢትዮጵያ ችግር እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ይፈታል ብሎ ማሰብ እንደገና ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› ይመስላል፡፡ ይህ እንግዲህ በሁለት እትም ሙከራ የቀረውን የሰማያዊ ፓርቲ መጽሔት በግል ችግሮቻቸው የሚወዛገቡ እና ፓርቲ ለማፍረስ የሚሮጡ ነጸ አውጪዎችን ሳናጠቅስ ከቀረን ነው፡፡


ተቃውሞን በመግለጫ

ተቃዋሚዎች መንግሥት ስህተት ሰርቷል ወይም ደግሞ የተለየ ነገር አድርጓል ብለው ሲያምኑ ለግል ጋዜጦች ከሚበትኗቸው አጭር፣ ብዙ ጊዜ የታሰበባቸው የማይመስሉ የተቃውሞ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ከመበተን በላይ መታገል ያለ አይመስላቸውም፡፡ ብዙ ጊዜ ለተግባራዊ የሚቀሰቅሱት የኢከኖሚ አቅማቸውን ነው፡፡ ለኢኮኖሚ አቅማቸውም ቢሆን ጠንክረው መሥራት ያለባቸወ እነርሱ ቢሆኑም ኢከኖሚያዊ ፍጆታ የሌላቸውን እንቅስቃዎችን በማካሔድ የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና ለመጨመር እና ትኩረትን ለማግኘት ይረዳቸዋል፡፡ ይህ ታስቦበት ቢሠራ ተቃውሞውን መንገድ ማበርታት ይችላል፡፡

መግለጫ በሚያወጡባቸው ነገር ግን ኢሕአዴግ መልስ እንኳን ሊጽፍባቸው በማይዳዳቸው ጉዳዮች ላይ ተሰሚነትን ለማዳበር ፓርቲዎች እና አባሎቻቸውን ያሳተፉ ሰላማዊ ትኩረት ሳቢ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከተለመዱት (ብዙ ጊዜ ተሞክረው ካልሠሩት) የፓርቲ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ውጪ ሕዝቡን የማግኘት ዕድሎች ይፈጥሩ ነበር፡፡ እነዚህ ለመንግሥትም፣ ለክስ የማይመቹ ነገር ግን የሕዝቡን ሐሳቦች የሚስቡ ተግባራትን ለማከናወን አለመሞከራቸው መኖራቸወን የምርጫ ሰሞን ሆይ ሆይ ብቻ ያስመስለዋል፡፡ ጥረታቸውም ከዕይታ ውጪ እና ውጤት አልባ ይሆናል፡፡ (መሪዎቻቸው አርኣያ የሚሆኑ የቡድን ተግባራትን ማከናወን - እስረኞችን መጠየቅ፣ ደም መስጠት /ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት በምሳሌ ማሳየት/ የብዛት እግር ጉዞ ማድረግ፣ ሕዝብ በብዛት ሊያያቸው የሚችላቸው የአድቮኬሲ እና አራማጅነት ሥራዎች ላይ መሳተፍ…ወዘተ፡፡)  

ዴሞክራሲያዊነታቸውስ?

የስንቶቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላኛው አጀንዳ ዴሞክራሲያዊነት ነው፡፡ ይህ የውስጠ ፓርቲ ዴምክራሲያዊነት ጥያቄ በፓርቲ ደረጃ በግልጽ ለመፈታቱ ማስረጃ ማግኘት ካልቻልን ዴሞክራሲያዊነታቸው በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክርቤቶቻቸው ስንት አባሎች እንዳሏቸው፣ የምክርቤቶቻቸው አባላት ምርጫ መቼ እንደሚካሔድ፣ በኃላፊነት የሚሾሙዋቸው ሰዎች የሥልጣን ዕድሜ ገደብ ቁልጭ ባለ መመሪያ መሠረት ይከናወናል? እድሜ ልካችንን የምናያቸውን በጣት የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ብዙዎቹ አመራሮቻቸው ለዓመታት ሳይቀየሩ አሁንም ይቀየራሉ የሚል ተስፋ ሳይሰጡ ነው የሚኖሩት፡፡ በግልጽ የሚታይ ዴሞክራሲያዊነት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ወሳኝ ጉዳይ የሚሆነው ለሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንድ - ዴሞክራሲያዊነትን የመንግሥት ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ማዳበር ስላለባቸው፡፡ ሁለት - እንደሕዝብ  ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ልዩነት ማየት ስለሚኖርብን፡፡

በምን ምክንያት እንመርጣቸዋለን?

በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው እንደሚስተዋለው ተቃዋሚዎች ዋነኛ ሥራቸው እና አትኩሮታቸው በገዢው ፓርቲ የሚፈፀሙ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን እና ሌሎች ስህተቶችን መተቸት እና አግባብ አለመሆናቸውን በመግለጽ የተቃውሞ መግለጫ ማውጣት ብቻ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም ማለት ባይቻልም እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ግን ከዚህ ያለፈ ሚና የመጫወት ኃላፊነታቸውን መርሳታቸው አግባብ አለመሆኑ ሊሰመርበት የሚገባው ነው፡፡ ኢሕአዴግ የጣሳቸውን ወይም ያጠፋቸውን ጉዳዮች እነሱ እንደማይደግሙት በምን እርግጠኛ ለመሆን እንችላለን - መቃወማቸው ብቻ ማስተማመኛ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ እነርሱ የሚከተሉትን ርዕዮተ ዓለም፣ ፖሊሲ እና ስትራቴጂያቸውን እንድናውቅ እና ከኢሕአዴግ ጋር የሚወዳደሩበት ነጥብ እንዳላቸው ለማሳየት ሲጥሩ አይታይም፡፡ ብዙ ገንዘብ የማይፈጁትን ነገር ግን ርዕዮተ ዓለም፣ ፖሊሲ እና ስትራቴጂያቸውን እንዲሁም ሌሎች እንቅስሴዎቻቸውን ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ ዘመኑ ያመጣቸውን ማኅበራዊ አውታሮች እና ድረገጾች እስካሁን በአግባቡ መጠቀም ለምን አላሰቡም? ይህን እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን መልስ በሌለበት መልኩ የምንመርጣቸው በምን ምክንያት ሊሆን ነው? ምርጫ ወቅትን ጠብቆ የሚመጡ ክርክሮች እና ፓርቲን የማስተዋወቅ ሥራ የመንግስትን ኃላፊነት ለመረከብ በቂ ነውን?
 
በርግጥ እነዚህን ጥያቄዎች ይዞ ፓርቲዎቹ ጽ/ቤት ድረስ የሚሄድ ሰው ምላሾችን አያጣ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው እነዚህን ጉዳዮች ለማወቅ ፓርቲዎቹ ጽ/ቤት ድረስ መሄድ አለበት ወይ? ማነው የተሻለ ኃላፊነት የወሰደው ፓርቲዎች ወይስ ህዝቡ? ይህንንም ለማስወገድ ፓርቲዎች የተለያየ መንገድ ተጠቅመው እንቅስቃሴዎቻቸውን እና አካሄዳቸውን ማኅበረሰቡ በተለይም ወጣቱ ክፍል እንዲውቅ እና እንዲሳተፍ እንዲነሳሳ የማድረግ ሥራ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡

ኢሕአዴግ አገራችንን በምንፈልገው መልኩ እያስተዳደረ ስላልሆነ ብቻ ተቃዋሚን መደገፍ እና ተቃዋሚዎች እንዲያሸንፉ የመፈለግ ነገር በብዛት ይስተዋላል፡፡ ይህ ግን አግባብ እንዳልሆነ፤ ስለተቃወሙ ብቻ ተቃዋሚዎችን መደገፍም አዋጭና ጠቃሚ ስላልሆነ ጠንክረው የተለያዩ ሥራዎችን መሥራትም የታሰበባቸው መንገዶችን መቀየስም ይጠበቅባቸዋል፡፡

‹‹ኧረ እኔም ይቺን ዘዴ ከዛሬ በፊት አላየኋት!››

አንድ ተረት አለች፡፡ አንድ መነኩሴ በጾም ወቅት እንቁላል በሻማ እየጠበሱ ሲበሉ አበምኔቱ (የገዳሙ አስተዳዳሪ) ያገኟቸውና ‹‹እንዴ አባ ምን ነካዎ?›› ቢሏቸው ‹‹ሰይጣን አሳስቶኝ ነው›› ብለው ሲሉ፣ ተደብቆ እያየ የነበረው ሰይጣን ‹‹ኧረ እኔም ይቺን ዘዴ ከዛሬ በፊት አላየኋት!›› ብሏል ይባላል፡፡ ለሆነው ሁሉ ሰይጣንን ከማሳበብ የሰይጣን ሥራን ማቆም ይበጃል ነው አተራረቱ፡፡

ተቃዋሚዎችም ለሁሉም ድክመታቸው ኢሕአዴግን እንደምክንያት ከሚጠቅሱ ቀላል ኃላፊነት አይደለምና  ድክመት እንዳለባቸው በማመን የራሳቸውን ስህተት ለማረም መረባረብ፣ ያልተሞከሩ አዳዲስ መንገዶችን ለመሞከር ማሰብ መጀመር የአቅም እጥረት ካለባቸው ኃላፊነቱን ለሚችሉ መልቀቅ እና ማንኛውንም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚያመጣ መንገድ መሞከር ይኖርባቸዋል፡፡ አለበለዚያ በዚህ አያያዛቸው ኢሕአዴግን ይቀይራሉ  ብሎ ማለት ዘበት!!!
---
ይህ ጽሑፍ ‹‹መክሸፍ*›› በሚል ርዕስ ከዚህ ጀምሮ በተከታታይ የሚወጡ ጽሑፎች አካል ነው፡፡
(*መክሸፍ የሚለው ቃል ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የመጨረሻ መጽሐፍ ላይ ሲጠቀሙበት በተፈጠረ መነሳሳት የተጠቀምንበት ነው፡፡)

No comments:

Post a Comment