Monday, February 11, 2013

የካምፓስ ተማሪዎች የጎሳ ግጭት፤ ከመነሻው እስከ መድረሻው



ይህ ጽሑፍ ባለፈው ወር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በብሔር ሰበብ በተነሳ ፀብ ላይ ተመስርተው በተከታታይ ድረገጾች ላይ የተጻፉ ጽሑፎች መነሻነት የተጻፈ ማጠናከሪያ ሐተታ ነው፡፡ ስለሆነም እዚህ ውስጥ የተበታተኑት የሰዎቹ ውይይት አጽርኆት (summary) እና ተጨማሪ ሐሳቦች ይንፀባረቃሉ፡፡

ጃዋር መሐመድ (የፖለቲካ ተንታኝ) ነበር ውይይቱን የጀመረው፤ በጽሑፉ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ መንፈስ ተኮትኩቶ የሚያድግባቸው፣ እልፍ ገጽታ ያላቸውን ችግሮቻችን ለመፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ ሐሳቦች የሚፈልቁበት የላቀ እና ገንቢ ውይይቶች የሚካሔዱባቸው ቦታዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተቃራኒው ግን፣ የኢትዮጵያ ኮሌጆች የዘረኝነት፣ ጠባብነት እና አመጽ መፈልፈያ እየሆኑ ነው፡፡›› ይላል፡፡

እኔም በዚህ ጽሑፍ ይህንኑ ጉዳይ ከታሪክ እና ከወቅታዊ ጉዳዮች አንጻር እመላለስበታለሁ፡፡

ለመሆኑ መቼ እና በማን ተጀመረ?

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ዕድሜ አጭር በመሆኑ ብሔር-ነክ ግጭቶች መቼ እንደተጀመሩ የሚዘረዝር መረጃ ማግኘት ቢቸግርም እንኳን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ) እንደሆነ መገመት አይቸግርም፡፡ ሆኖም በቅርቡ በጆን ያንግ የተጻፈ፣ Peasants Revolution of Ethiopia የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ሳገላብጥ ያገኘሁት አንቀጽ አጀማመሩን የሚገልጽ መስሎኝ ወስጄዋለሁ፡፡

“…ዊንጌት ውስጥ … በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመሩ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች በቅርጫት ኳስ ጨዋታ ላይ በተነሳ አለመግባባት ከኦሮሞ ተወላጆች ጋር ተጋጩ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ መለስ በጣም አወዛጋቢ የነበረውን እና በአድዋ ጦርነት ወቅት የትግራይ ተወላጆች ከየትኛውም ብሔረሰብ የበለጠ የሕይወት እና የሰው ኃይል ከፍለዋል፣ ምኒልክንም ለድል አብቅተዋል የሚል የታሪክ ጽሑፍ አቀረቡ…(ገጽ 82) እያለ ይቀጥላል፡፡


ይሁን እንጂ የካምፓስ ውስጥ የዩንቨርስቲ ግጭት ድምፅ አግኝቶ የቀጠለው በኢሕአዴግ ዘመን ነው፡፡ ለዚህ እንደ መንስኤ ሊቆጠር የሚችለው (1). የብሔር ፌዴራሊዝሙ፣ እና (2). ከደርግ አፈና በኋላ የተመለሰው አንጻራዊ የመነጋገር ነጻነት ነው፡፡ በደርግ ዘመን የብሔር (በጥቅሉ የፖለቲካ) ውይይት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የመነሳት ዕድሉ ጠባብ ስለነበር ግጭቱም አይነሳም ነበር፡፡ የወቅቱን ዝምታ ራንዲ ሮኒንግ ባልስቪክ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ባተመላቸው የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናታዊ ጽሑፋቸው (The Quest for Expression: State and The University in Ethiopia Under Three Regimes. 1952-2005) ላይ እንዲህ ገልጸውታል፡፡

‹‹…ከአብዮቱ ፍንዳታ 10 ዓመት በኋላ (የአ.አ.) ዩኒቨርሲቲን እና በጥቅሉ ማኅበረሰቡን ከጠበቅኩት እና በንጉሡም ሆነ በክፍለዘመኑ መጨረሻ - በመለስ ዜናዊ መንግሥታዊ-ስርዓት ካየሁት በላይ በፍርሐት ተሸብቦ ነበር፡፡ ሕይወት ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ የማይጠበቅ እና ደኅንነት የጎደለበት ሆኖ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች ማንኛውንም አስተያየት በአገሪቱ ውስጥ እየተከናወነ ስላለ ጉዳይ ከመስጠት ይቆጠቡ ነበር፡፡ ምክንያቱም ንግግራቸው ሁሉ ፖለቲካዊ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡…››

ጸሐፊው ወደኢሕአዴግ ዘመን ሲመልሱን፣ ‹የዩኒቨርሲቲው ዶርሚተሪዎች በጎሳ ተከፋፍለዋል፤ አማራዎቹ የጎሣ ጽንፈኝነትን ሲቃወሙ ኦሮሞዎቹ ተማሪዎች ደግሞ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን እንደተነጠቁ ይሰማቸዋል፡፡ በትግሬዎቹ እና ቀሪዎቹ መካከል ደግሞ ቀዝቃዛ ጦርነት ተከፍቷል› ይላሉ፡፡ በ1993 የኦሮሞ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ተለቅመው እንዲጠፉላቸው የሚፈልጉትን ቃላት ዝርዝር በፊርማ ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስገብተው ነበር፡፡ ይሄ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ተማሪዎቹ የማይፈልጓቸው ቃላቶች ያሉባቸውን መጽሐፍት ገጾች እየቀደዱ መውጣት ጀመሩ፡፡

ከዚያ በኋላ ብሔር ነክ ጥያቄዎችን በውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ መመለስ፣ በየብሔሩ እየተቧደኑ ማኅበራዊ ግንኙነት መመስረት እና ከማኅበራዊ ግንኙነቱ መስመር ውጪ ያለውን ሁሉ በጠላትነት መፈረጅ፣ አለምግባባቶች ሲኖሩ መደባደብ ‹‹ብዝኃነት (plurality)›ን ዒላማ ያደረገው የዩንቨርስቲ ሕይወት ክሽፈት መለያ ሆነ፡፡

የካምፓስ ተማሪዎች ለምን በብሔር ይጋጫሉ?

ሀ. የመንግሥት ሴራ?

ጃዋር መሐመድ ‹የኢትዮጵያ ካምፓሶች ዓይናውጣ ጦርነት፤ መነሾ ግብ እና ተጽዕኖ› በዳሰሰበት ጽሑፉ መንግሥት ከመነሻ እስከመድረሻው ድረስ ተጠያቂ መሆን እንዳለበት ያትታል፡፡ ለጃዋር ዋና የካምፓስ ተማሪዎች ብሔር ነክ ግጨቶች መንስኤ የሚባሉት ሁለት ናቸው፤ (1). የአካዳሚያዊ ነጻነት አለመኖር (ነጻ ማኅበራት አለመፈቀዳቸው፣ የመወያያ የተማሪዎች ሕትመቶች አለመኖራቸው እና መታገዳቸውን ይጨምራል)፣ (2). የገዢው ፓርቲ የስለላ አባላት ተማሪዎቹ ውስጥ መሰግሰጋቸው እና የመከፋፈል ሚና መጫወታቸው፡፡

ጃዋር በትንታኔው ‹‹ማኅበራት እንዲኖሩ አለመፈቀዱ የባሕል እና ማንነት ልውውጥ እና ትውውቅ ዕድል ስለማይሰጥ፣ የካምፓስ ማኅበራዊ ክበቡ በግምት፣ በተሳሳተ መረጃ፣ እና በጥርጣሬ ስለሚሞላ ለጠባብነት እና አግላይነት መንገዱን ይጠርጋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ካምፓስ ደግሞ ለቡድን አመጽ የተጠመደ የጊዜ ቦምብ ነው፡፡›› በማለት በዩንቨርስቲዎቻችን የሚነሱት ግጭቶች በማኅበራት እና መሰል ውይይቶች ሊፈቱ የሚችሉ ጥያቄዎች በፍራቻ እና አካዳሚያዊ ነጻነት ባለማግኘት ምክንያት የሚፈጠሩ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ እንደጃዋር ገዢው ፓርቲ ይህንን የሚያደርገው ዘመነ ሥልጣኑን ለማስረዘም ‹ከፋፍለህ ግዛ› የተሰኘ ስልት ስለሚጠቀም እንጂ የችግሩ መንስኤ ጠፍቶት አይደለም፡፡

በተመሳሳይ መንገድ በ1990 አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ (ስድስት ኪሎ) በጎሳ ጉዳይ በተነሳ ግጭት ፖሊስ እርምጃ ሲወስድ “ማንኛውም ኦሮሞ ስም ያለው ሰው ወደእስር ይገባል፤ የትግራይ እና አማራ ስም ያላቸው ተማሪዎችን ግን ከሌሎቹ ለይተው ‹እነዚህ የኛ ሰዎች ናቸው›፤ ወይም ‹እነዚህ የኛ ናቸው ተዉኣቸው› ይላሉ፤” በማለት ራንዲ ጽፈዋል፡፡ ይህ ሁለት የፖሊስ ዓይን የሚያንፀባርቀው መንግሥት ጉዳዩን ከላይ የሚመለከትበትን ሁኔታ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ የመንግሥት/የፖሊስ ችግሩን አፈታት የኦሮሞዎቹን ተማሪዎች የመጠቃት ስሜት እንደሚያጋግለው እና ጎሳዊ ጽንፈኝነት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፤ ጃዋርም በዚህ ይስማማል፡፡ የኦሮሞ ተማሪዎች ተለይተው መለቀማቸው ሌላውን በጥርጣሬ እና በአጥቂነት እንዲመለከቱት እና ጥላቻ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል ይላል፡፡

እዚህ ጽሑፍ ላይ ተመስርተው የተሰጡ ምላሾች የዚህን መንስኤ እውነታነት አስረግጠው፣ ነገር ግን ጃዋር ዘነጋቸው የሚሏቸውን ተጨማሪ የግጭት መንስኤዎች ይጠቁማሉ፡፡

ለ. የኦሮሞ ተማሪዎች የመቻቻል ባሕል ማነስ?

ዐብይ ተክለማርያም (የቀድሞዋ አዲስ ነገር ጋዜጠኛ) ለጃዋር ትንታኔ በሰጠው አጭር የምላሽ ማብራሪያ ላይ በጽሑፉ ይዘት እውነትነት ቢስማማም የጥፋተኝነቱን ድርሻ ለመንግሥት ብቻ መስጠቱ ተገቢ አይደለም ይላል፡፡ ዐብይ የምናወራውን ነገር እርግጠኝነቱን ለማወቅ ጥልቅ ጥናት ያስፈልጋል ቢልም፤ ጉዳዩ ግን አሁን እንደምንለው ‹ጥቁር እና ነጭ› ብቻ እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ መንግሥት ብቻ መወቀስ የለበትም የተማሪዎቹ የመቻቻል ባሕል ማነስ ለእሳቱ ነዳጅ አቀብሏል ነው አባባሉ፡፡ እሱ እንደሚለው የኦሮሞ አክቲቪስቶች የፀረ-ነፍጠኛ ትርክት ለዚህ ተጠያቂ ነው፡፡ 

እውነት ነው፤ የኦነግ ትግል የተጧጧፈው በ‹‹ኦሮሞ ኮሎናይዜሽን›› ትርክት ነው፤ ኦነግ እና ብዙዎቹ የኦሮሞ ፖለቲካ አራማጆች የሚያምኑት የኦሮሞ ሕዝብ በብሔሩ ብቻ ሲጨቆን (‹‹ቅኝ ሲገዛ››?) ኖሯል እና አሁን ነጻ መውጣት አለበት ብለው ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ነጻነትን ከመገንጠል አጀንዳ ጋር ማራመዳቸውን አሁን ብዙዎቹ ቀይረውታል፡፡ ያለመገንጠል ‹‹እኩል ነጻ ሆኖ መኖር ይቻላል›› በሚል - ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ጭቆናው አለ ብለው ማሰባቸው ለመቧደን እና ከሌላው ጋር እንዲጋጩ፣ ሌላውን በጥርጣሬም እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል፡፡ አሁንም በዙሪያቸው ያለው ሁሉ የ‹‹ነፍጠኛ›› የበላይነቱን ሊያራምድብን ነው በሚል የመፈረጅ ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ለተደጋጋሚ ግጭቶች መቀስቀስ መንስኤ ይሆናል፤ ከላይ እንደተጠቀሰውም መንግሥትም ሊጠቀምበት ይችላል፡፡

በዚህ መሐል ግን የሚነሳ አንድ ጥያቄ ይኖራል፡፡

ለምን ኦሮሞ ብቻ?

ዘላለም ክብረት (የሕግ መምህር) የጃዋርን እና ዐብይን ምልልስ አስከትሎ ባሰፈረው አስተያየት አዘል ጽሑፉ እሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት የግጭቱ ሰለባ መሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን ባያቸው ግጭቶች ውስጥ ሁሉ የኦሮሞ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡ ተደጋጋሚ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ግጭቶችን የተመለከትን እንደሆነ ግጭቶቹ ሁሉ የኦሮሞ ተማሪዎችን ይነካል፡፡

ራንዲም ከላይ በጠቀስነው ጽሑፍ ላይ ሦስት የካምፓስ የጎሳ ቡድኖች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ኦሮሞዎች፣ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ናቸው በሚል የሚፈረጀት ትግሬዎች እና አማራዎች፡፡ ራንዲ ከደቡብ የመጡት አማራዎቹ ቡድን ውስጥ እንደሚመደቡ ተናግረዋል፡፡ በእርሳቸው መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ግጭቶች ሁሉ ሰለባ የሆኑት፣ የተከሰሱት እና የታሰሩት ኦሮሞዎች መሆናቸው ግጭቱ በአብዛኛው ኦሮሞዎችን በማዕከላዊነት የሚያካትት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

እንግዲህ በዚህ እውነታ ላይ ተመርኩዘን ስንሄድ የኦሮመ ተማሪዎችን አንድም ሆነ ብሎ የሚተነኩሳቸው አለ (የመንግሥት ሴራ እንደተባለው) አለ አሊያም እነርሱ (የመቻቻል ባሕል) ችግር አለባቸው የሚል አጣብቂኝ ጥርጣሬ ውስጥ ይጥለናል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ጋር…?

የኦሮሞ ተማሪዎችን የመቻቻል ባሕል ለመፈተሽ በተቻለን አቅም ወደኋላ መለስ ብለን የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር እንዴት ተቻችሎ ይኖር እንደነበር መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በዚህም የምናገኘው ተማሪዎቹን ከከሰስንበት ተቃራኒውን ነው፡፡ ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን ስለኦሮሞ ሦስት ዓይነት ትርክቶች በሚያውሩበት ጽሑፋቸው የኦሮሞ ሕዝብን የመቻቻል፣ እና ከሌላው ጋር በፍጥነት የመዋሀድ ችሎታ እንዲህ በአድናቆት አስፍረውታል፡፡

‹‹ለመላመድ፣ ለመመሳሰል፣ እና ለእርስበርስ ጋብቻ ያላቸው ፈቃደኝነት ምስጋና ይግባውና፣ የኦሮሞ ሰፋሪዎች በሄዱበት ሁሉ ካለው ሕዝብ ጋር ተዋህደዋል፡፡ የግልጽነት እና ወዳጅነት ባሕሪያቸው አዲስ መጤዎች ማኅበረሰባቸውን እንዲቀላቀል የሚጋብዝ ነው፡፡ በየሰፈሩበት አጎራባች ቦታዎች ካሉ ሰዎች ጋር ጦርነቱ ለጊዜውም ይሁን በዘላቂነት ከመቆሙ የሚዛመዱበት ነገር አያጡም፡፡ ይህ ከሌሎች ጋር የመወዳጀት ችሎታቸው እነርሱ የሌሎችን፣ ሌሎችም የነርሱን ባሕል እንዲወራረሱ አድርጓል፡፡ ኦሮሞዎች በሰሜን ክርስትናን፣ በምስራቅ ደግሞ እስልምናን ተቀብለዋል፤ በደቡብ ምዕራብ ግዛተነገሥት ሲያቋቁሙ በሸዋ ደግሞ እርሻ ጀምረዋል፡፡ ከአማርኛ ተናጋሪዎች ጋር በቀላሉ መቀላቀል መቻላቸው ምስጋና ይግባውና ቀድሞ ሴማዊ የነበረው እና ከግዕዝ፣ ትግርኛ፣ አረቢኛ፣ እና እብራይስጥ የመጣው አማርኛ ቋንቋ አሁን የምስራቃዊ ኩሽ ሰዋሰው፣ ግስ እና ዘዬ ከኦሮምኛ ቋንቋ ወርሶ ወስዷል፡፡

‹‹በደቡብ፣ እነዚህ ቅልቅሎች ሁሉንም ቡድን ያሳትፋሉ፡፡ ስለዚህ፣ በጉራጌ ዞን አካባቢ የሰፈሩ ኦሮሞዎች የእንሰት ባሕልን በመውረሳቸው በኦሮሞዎች ሳይቀር ‹‹ግማሽ ጉራጌ›› በመባል ይቀለድባቸዋል፡፡ የጉጂ ኦሮሞ ኦቱዎች ከሲዳማ ባሕል ጋር በጣም ከመቀላቀላቸው የተነሳ አንዳንዶቹ ሲዳምኛ ብቻ ነው የሚናገሩት፡፡ በሌላ በኩል፣ የጉጂ ኦሮሞዎች የሲዳማ እና ወላይታ ሰዎችን ወደራሳቸው ባሕል ወስደው ቀላቅለዋቸዋል፡፡››

ይህን ስናነብ፤ ይህን ዓይነት የመቻቻል እና የመላመድ ባሕርይ ካለው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ ውስጥ የወጡት ተማሪዎችን የመቻቻል ባሕል ያንሳቸዋል ለማለት ስር የሰደደ መሰረት እናጣለን፡፡ እናም ‹‹የአሁኑ ተማሪዎች ግጭት የኦሮሞ ተማሪዎች የመቻቻል ባሕል ማነስ ከየት መጣ?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ እንግዲህ ለዚህ ጥየቄ የሚቀረን መልስ ጃዋር በጽሑፉ ጠቅሶት እንደነበረው ‹‹የመንግሥት ካድሬዎች ትንኮሳ›› አሊያም ዐብይ እንዳለው ‹‹የፀረ-ነፍጠኛ ትርክት የዘለቃቸው ተማሪዎቹ የመቻቻል ባሕል ማነስ›› ለችግሩ ተጠያቂዎች ሆነው ይቀራሉ፡፡

የግጭቶቹ መነሾዎች

ዘላለም በጽሑፉ ‹‹የሐጎስ እና ገመቹ የግል ፀብ ወደ ትግሬ እና ኦሮሞ ተማሪዎች ያድጋል›› በማለት ግለሰባዊ አስተሳሰብ በቡድን እየተተካ እንደሆነ ያለውን ስጋት ጠቁሟል፡፡

የካምፓስ ውስጥ ፀቦች በግለሰቦች ግጭት ብቻ አይደለም የሚነሱት፤ በቃላት አጠቃቀምም ጭምር ነው፡፡ አንዱ ሌላኛውን ለማብሸቅ፣ ወይም ባለማወቅ በሚጠቀመው የተነወረ ቃል (the “G…” word) ሳቢያ የተነሳ ፀብ… ምናልባትም በውቀቱ ስዩም (ማኅበራዊ ሐያሲ) አስተያየት ሲሰጥ ‹‹ይህን ያለው የምን አገር ተወላጅ ነው ከማለት በፊት ማነው ያለው?›› ለማለት ባለመቻላቸው የሚመጣ ችግር ነው፡፡

ዐብይ የ‹‹ነፍጠኛ›› መጽሐፍትን በማጣቀሳቸው ክፍል ውስጥ በካምፓስ ተማሪ ኦሮሞዎች የተደበደቡ መምህራን ስለመኖራቸው ብዙ ታሪክ መስማቱን ጽፏል፡፡ ዘላለምም የተነወሩ ቃላትን የሚጠቅሱ መጽሐፍት ገጾች በየካምፓሱ ላይብረሪ ተቀድደው አልቀዋል ብሏል፡፡ የሁለቱንም አስተያየት ያደመጠ ሰው መጀመሪያ ሊጠይቅ የሚችለው ጥያቄ ቢኖር ‹‹መጽሐፍቱን በማጥፋት [ያልተወደደውን] ታሪክ ማጥፋት ይቻላል ወይ?›› የሚል ነው፡፡  

‹‹ሰዎች በቋንቋቸው መማር ይገባቸዋል›› ብሎ እንደሚያምን የጠቀሰው ዐብይ ‹‹የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተለያዩ ዓይነት አመለካከቶችን ማወቅ እንዳለባቸውም›› አክሎ ተናግሯል፡፡ ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክረው ደግሞ ዘላለም ክብረት ነው፤ በሁለቱ ተንታኞች ምልልስ ላይ ተመርኩዞ በጻፈው ጽሑፍ ላይ እንዳሰፈረው ጉዳዩን ትቶ በመጽሐፍቱ መኖር/አለመኖር፣ ለመማሪያነት መጠቀስ/አለመጠቀስ ማዕከላዊ ጉዳይ ሆኖ መወሳቱ እና “መጽሐፍቶቹ ከቤተ መጽሐፍቱ እንዲወጡ መጠየቅ መሳቂያነት/ዕብደት ነው” ብሏል፡፡

ከላይ እንዳየናቸው ግጭቶቹ መነሾዋቸው አንድ ወይም ሁለት ግለሰቦች ወይም ደግሞ ቃል ቢሆንም ቅሉ ግን ተጠቂ የሚሆኑት በተለያየ ቡድን/ብሔር ውስጥ የታጠሩ ሰዎች ሁሉ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ዩኒቨርሲቲዎች ከተለያዩ ክልል የመጡ ተማሪዎችን ቀይጠው በማስተናገድ ከነልዩነት አብሮ መኖር እንዲችሉ የማድረጉ ሙከራ ምን ያህል ከስኬት እንደራቀ የሚያሳይ ውጤት መሆኑ ነው፡፡

ለመሆኑ መፍትሔ አለው?

መፍትሔ የሌለው ችግር የለም፤ ምንም እንኳን ካምፓሶች በየብሔሩ ሽምቅ የሚዋጉ ማኅበረሰቦችን ቢያፈሩም ተማሪዎቹ ከዩንቨርስቲ ሲወጡ የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ከተማሪዎቹ እጅግ የላቀ የመቻቻል ባሕል ስላለው እንደዚያ ዓይነቱ ነገር ማኅበረሰቡን የመበጥበጥ ዕድሉ ጠባብ ሆኖ ከርሟል - ቢያንስ እስካሁን ድረስ፡፡ ምክንያቱም ተማሪዎቹ ተመርቀው ሲወጡ የሚኖሩበት ብዝኃ-ብሔሮችን አቅፎ የተቀመጠ ከተማ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነገሮች እየተባባሱ ከሄዱ እና ካሁኑ ፈር ካልተበጀላቸው ነገሩ የተገላቢጦሽ ሊሄድ ይችላል፡፡ ተማሪዎቹ የካምፓስ ውስጥ አግላይ-አቋማቸውን በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊያስተጋቡ እና ማኅበረሰቡም ሊቀበላቸው ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡

ለዚህ ነው ችግሩን ‹‹የካምፓስ ተማሪዎች ዛሬም እንደለመዱት በብሔር ተጋጩ›› ብቻ ብለን እንደዋዛ ማለፍ የማይኖርብን፡፡ ችግሩን እንዳያዳግም አድርጎ ለማባረር የመጀመሪያው መፍትሔ የሚሆኑትን ካሁኑ ማፈላለግ ያሻል፡-

ሀ. ማውራት፣ ማውራት፣ ማውራት

በውቀቱ ስዩም የመጨረሻው የካምፓስ ተማሪዎች ግጭት የተከሰተ ዕለት (በታኅሳስ ወር/2005) በጻፈው አንጀት አርስ ጽሑፉ መደምደሚያ ላይ ‹‹መፍትሄው ምሁራዊ አይናፋርነትን ትቶ መወያየት ነው፤›› ብሎ መክሯል፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ እንደምናየው፣ ባንዱ ኃጢያት ሌላው ይሙት የሚል ብሉያዊ  አስተሳሰብ የካምፓስ ልማድ የሆነ ይመስላል፡፡ ብዙ የተማሩ፣ የተመራመሩ ሰዎችን እንዴት አንድ ተንኳሽ ሊያተራምሳቸው ይችላል?›› ብሎ አንድ በቃላት በሚነሳ ጦርነት እንዴት እንደሚከፋፍለን እና የመወያየት ባሕላችን ማነስ ‹‹ቃላት›› እንኳን መቋቋም እንዳነሰን ታዝቧል፡፡

ጎሣዊ ነውረኛ ቃላት ከመጽሐፍት ውስጥ እና ከመጽሐፍት ገጾች እንዲወገዱ ከመጣር ይልቅ አማራጭ ትርክት ፈጥሮ፣ የትኛው የተሻለ እንደሆነ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ባለማውራት፣ እና አፍን በመለጎም ከዕውቀት መታቀብ እንጂ ለውጥ አይመጣም፡፡ በዝምታ እና በመፈረጅ ፍርሐት ከማለቅ በጫፍ አልባ ሙግት ውስጥ እያለፉ እያደጉ መኖር ይሻላል፡፡

ለ. አራማጆችና ምሁራን በትርክቶቻቸው መቻቻልን አይርሱ

በቀለ ገርባ በ‹‹አሸባሪነት›› ፍርዱ ብያኔ ላይ ማቅለያ ሲጠየቅ ከተናገረው ውስጥ ትግሉን ‹‹…በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ እንደሚገባ ሳልገልጽ ቀርቼ ከሆነና ይህንንም ያደረኩት ለሕዝቦች አብሮ መኖር ከማሰብና ከወንድማማችነት ላነሰ ተግባር ከሆነ የኦሮሞን ሕዝብ[በደሉን] ከሚገባው በላይ አጋንኜው ከሆነና ይህንንም ያደረኩት ለግል ጥቅምና ዝና ከሆነ እግዚአብሔርን ይቅርታ እጠይቃለሁ›› ብሎ ነበር፡፡ ያ የበቀለ ንግግር የብሔር ነጻነት ትግል አጀንዳን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

አሁንም የብሔር ነጻነት አራማጆች የሚታገሉለትን የብሔሮች እኩልነት እና ነጻነት ዒላማ ካልዘነጉ በቀር ሁልጊዜም በግጭት እና ከሌላው ጋር በመቆራቆስ የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ በቅጡ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ትርክቶች ይህንን ሐቅ ዘንግተው አንዱ ከሌላኛው ጋር ጠላትነት በማፍራት የሚመጣ ነጻነት እንደሌለ በማመን መቻቻልን ያገናዘበ ትርክት ይዞ ከአጉል ጽንፍ እና ‹‹ጽንፍ ነው አይደለም›› ሙግት መውጣት እና ለኅብረተሰቡ አብሮ፣ በነጻነት እና እኩልነት መኖር የሚበጅ የመፍትሔ ሐሳብ መቀየስ እና መታገል ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ጉዳዩን ለግል አጀንዳ በማራገብ ችግሩን ማክፋት እንጂ ማቅለል ይከብዳል፡፡

ሐ. መንግሥት የሚበጀውን ይወቅ

ጃዋር ሕዝቦች በምንም ይሁን በምን (በተለይ በብሔር) ከተከፋፈሉ መንግሥት ላይ የማመጽ አቅምም አንድነቱም ስለማይኖራቸው፣ ዕድሜው እንዲረዝምለት ይፈልገዋል ይላል፡፡ ሆኖም፣ ይህ ዓይነቱ የከፋፍለህ ግዛ ጫወታ፣ በእሳት የመጫወት ያክል ነው ይላል የገዛ ሐሳቡን ሲያጠናክር፡፡

መንግሥት የብሔር ፌዴራሊዝም ከ‹‹መለያ-አጀንዳነት›› ይልቅ የአተገባበር እና ሌሎቹም ችግሮች እንከኖቹን ነቅሶ እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል ተጨንቆ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ‹‹የብሔር ጥያቄ ተመልሷል›› ብሎ በደረቅ ዓረፍተነገር ለማሳመን ከመሞከር ይልቅ በየአቅጣጫው የሚነሱ ጥያቄዎችን ማዳመጥ ይበጃል፡፡ የተለዩ የብሔር አባላት የሚመረጡበት፣ የተለዩ የብሔር አባላት የሚገለሉበትን ያልተጻፈ አሠራር የምር መታገል እና የምር የብሔረሰቦችን እኩልነት ለማስፈን ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት፡፡  

ስለዚህ መንግሥት ከጊዜያዊ የሥልጣን ማስቀጠያነት ተሻግሮ የረዥም ዓመት ሕልም ማፍራት አለበት፡፡ የጎሳ ግጭት ለማንም አይበጅም፤ እርስ በእርሱ የሚበጣበጥ ሕዝብ ይዞ መምራት ብሎም ብጥብጡን ሥልጣን ለማስረዘሚያነት እስከመጠቀም ማለም ደግሞ የጅል ብልሐት መሆኑን አውቆ መንግሥታችን መጠንቀቅ እና ወደቀልቡ መመለስ ይኖርበታል፡፡

መ. ከመንደረተኛነትን አስተሳሰብ መላቀቅ

‹‹ጠባብነት›› የሚለው ሐሳብ የሚመጣው ሰዎች ከራሳቸው ዙሪያ ውጪ ሌላ ዓለም እንደሌለ በማሰብ ልዩነትን መረዳት እና ከነልዩነት አብሮ መኖር ሲያቅታቸው ነው፡፡ ይህንን ነው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹‹መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹መንደረተኝነት›› ሲሉ የገለጹት፣ እኔ ልንገላገለው/ልንጠነቀቅለት ይገባል የምለውን አስተሳሰብ ከእርሳቸው በምዋሰው አንቀጽ አብራራዋለሁ፡-

‹‹…መንደረተኛነት ማለት ከመንደር በማይወጣ አስተሳሰብና ከመንደር በማይወጣ ስሜት መመራት ነው፤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለሚኖሩ ሰዎች ዓለማቸው መንደራቸው ነች፤ ከዚያች መንደር ውጪ ሌላ ዓለም የለም፤ ቢኖርም የሚንቁትና የሚጠሉት ነው፤ መንደረተኛነት በግድ ብዙ የአስተሳሰብ ግድፈቶችን ያስከትላል፤ የራስን መንደር የዓለም እምብርት የሆነችና ዓለምንም ኢምንት አስመስሎ በመገመት፣ መንደርዋን ወሰን-የለሽ በማድረግ አስተያየትን ያጠናግራል፤ በአስተሳሰብም ደረጃ መንደረተኛነት ቁሞ-ቀር ያደርጋል፤ የአካል፣ የአእምሮንና የመንፈስን ዕድገትና እርምጃ ያፍናል፤ መንደረተኛነት የታሪክን መሠረትና የታሪክን ትክክኛ አካሄድ ለመረዳትና የታሪክ ባለቤት ለመሆን የሰው ልጅ የአለውን ችሎታ በመቀነስ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል፡፡…››

መደምደሚያ

ጃዋር መሐመድ እና ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በኦነግ ርዕዮተ-ዓለም ላይ በተከራከሩበት የጽሑፍ ምልልስ ላይ ጃዋር የተጠቀመውን ሐረግ ብጠቀም ጥሩ መደምደሚያ ይሆነኛል፡-

‹‹…ኢትዮጵያ ያላለቀች ፕሮጀክት ነች፡፡ በመጨረሻዋ ቅርጹዋ ላይ ሁላችንም የየራሳችን ሚና አለን፡፡ ነገር ግን ይህ እንዲሆን የሚያስፈልገን ትንሹ የባሕሪ ለውጥ አርስበርስ መደማመጥ፣ አንዱ የሌላውን ሕመም መረዳት እና እውነታውን ሳያዛቡ እንዳለ ማቅረብ ነው፡፡ …››

No comments:

Post a Comment