ወቅቱ መጽሔቶች እንደአሸን የፈሉበት፣ ጋዜጦች ደግሞ ቁጥራቸው የተመናመነበት ነው፡፡ ብዙዎቹ
[የአማርኛ] መጽሔቶች የሚወጡት በየ15ቀኑ ቅዳሜ ቀን ነው፡፡ ጥቂቶች በወር አንዴ እና አዲስጉዳይ ብቻ በየሳምንቱ ይታተማል፡፡
በመጽሔቶቹ ታሪክ አንጻራዊ ደረጃ ሊሰጠው የሚችለው እና የራሱን ስም (ብራንድ) እየገነባ ነው ሊባል የሚችለው አዲስጉዳይ ነው፡፡
በየሳምንቱ መውጣቱ፣ የመጽሔት ቅርጽ (structure) መያዙ፣ በርካታ ጸሐፊያን እና አምደኛ ያሉት መሆኑ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርጎለታል፡፡
ሌላው ቀርቶ አዲስ ጉዳይ በየ15 ቀኑ፣ ከዚያም በየሳምንቱ መታተም መቻሉ በራሱ ሌሎቹንም ስቧቸዋል፡፡ ባለሙሉ ቀለም ለመሆንም የመጀመሪያ
አርኣያቸው ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ አዲስጉዳይም ቢሆን በተለይ ከይዘት ጥንካሬ ትችት ማምለጥ አይችልም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አዲስ
ጉዳይን እና ሌሎቹን መጽሔቶች በአንድ መስፈርት መመዘኑ ተገቢ ስለማይሆን እሱን ነጥለን ትተን ሌሉቹ /አብዛኛዎቹ መጽሔቶች/ ላይ
ያሉትን ችግሮች እና “ከሽፈዋል”፣ በአዲስ መንገድ ትንሳኤ ያስፈልጋቸዋል ብለን እንከራከራለን፡፡
በማስተዋል አሳታሚ ከተገዛ በኋላ የተለየ ጥንካሬ ያላቸው ፖለቲካዊ ትችቶችን በበርካታ ጸሐፍት
ያስተናግድ የነበረው አዲስ ታይምስ ጋዜጣም ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡ ነገር ግን የአዲስ ታይምስ ሕትመትም ለጊዜው በመቋረጡ በዚህ ጽሑፍ
አንዳስሰውም፡፡
ይዘት
ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ያገላበጥናቸው መጽሔቶች ሁሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከአንድ፣ ሁለት በቀር
ቋሚ አምድ የላቸውም፡፡ ይህም የተዘበራረቀ ሐሳብ ያላቸውን ጽሑፎች እዚህም እዚያም በመሰደር፣ የአንባቢን ሐሳብ በአንድ ማኖር እንዲሳናቸው
አስገድዷል፡፡ ይህ ጉዳይ ተጽዕኖውን የሚያሳድረው በአንባቢዎቻቸው ብቻ ሳይሆን በመጽሔቶቹም በራሳቸው ላይ ነው፡፡ መጽሔቶቹ በየጊዜው
የሚያወጧቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ ሦስት እና አራት ነገሮችን ብቻ ማስተዋል ይችላል፡፡ እነዚህም፡- የቴዲ አፍሮ የግል እና
የግል ያልሆኑ ጉዳዮች፣ የሃይማኖት ልዩነት እና መከፋፈል አጀንዳዎች፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጉዳይ እና አሁን ደግሞ - ገበያው
ይጠይቃልና - የአገር ውስጥ ፖለቲካ ጉዳዮች ናቸው፡፡
መጽሔቶቹ በነዚህ ጉዳዮች ላይ እንደየወቅቱ ወረት ‹‹መንደረተኛ›› ሊባል በሚችል መልኩ ጉዳዮችን
ያራግባሉ፡፡ ነገር ግን በጽሑፎቻቸው አንጽሮተ-ዕይታ ለመጨመር አይሞክሩም፤ ሌላው ቀርቶ አንዱን አጀንዳ እጅግ በሚያሰለች መልኩ
ለረዥም ጊዜ ይዘው ማመንዠክ ይወዳሉ፡፡ እንደምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ስለጤፍ መወደድ መንስኤ ብለው የተናገሩትን ብዙዎቹ
መጽሔቶች እንደርዕስ መዝዘው ይይዙት እና ነገር ግን ምንም ፋይዳ የሌለው ትንተና ከርዕሱ የበለጠ ዋጋ በሌለው ሐተታ ያቀርባሉ፡፡
(ይህ ዜና ማመንዠክ አባዜ የቀድሞው ጠ/ሚኒስተር ሞትን እንዲሁም ተከትለው የመጡ የፓለቲካ ወሬዎችን ይጨምራል፡፡)
የጽሑፎቹ ወጥነት - “ኢቪዲኦን
ወደ ወረቀት?”
መጽሔቶቹ ብዙ ቦታዎች ላይ የጽሑፎቹን ጸሐፊ ስም ሳይጠቅሱ ያልፋሉ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ሁለት
ነው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ጽሑፎቹ ወጥ ሥራዎች (originals) ስላልሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጥቂት አባላት ብቻ ስለሚኖሯቸው
እና እነዚያው ጸሐፍት ሁሉንም ነገር (ፖለቲካውን፣ ፋሽኑንም፣ ኢኮኖሚውንም፣ ማኅበራዊውንም፣ መዝናኛውንም) ብቻቸውን ስለሚጽፉት
እንዳይታወቅ ከመፈለግም ነው፡፡
በሰው ኃይል እጥረትም ይሁን በፈጠራ ማነስ መጽሔቶቹ ወጥ ያልሆኑ ሥራዎችን ሲያትሙ ስም እንኳን
ለመጥቀስ የሚዘነጉበት፣ የዋነኛውን ጸሐፊ ፈቃድ ለማግኘት እንኳን የማይገዱበት እና ኢትዮጵያዊ ካልሆነ እንዲያውም የራሳቸው የፈጠራ
ጽሑፍ እንደሆነ አስመስለው የሚያቀርቡበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡
እዚህ ላይ በምሳሌ ሳይጠቀስ የማይታለፉት የዳንኤል ክብረት እና የአቤ ቶክቻው ጽሑፎች ናቸው፡፡
የዳንኤል ክብረት ጽሑፎች አዲስጉዳይ ላይ ታትመው፣ ከዚያ የግል ድረገጹ ላይ ከወጡ በኋላ ከዚያ ተገልብጠው መልሰው ሌሎች መጽሔቶች
ላይ ማንበብ የተለመደ ድራማ ነው፡፡ አቤ ቶክቻውም በግል ድረገጹ ላይ የሚያትማቸው ፖለቲካዊ ወጎች ከአንድ በላይ በሆኑ መጽሔቶች
ላይ በአንድ ቀን ታትመው የሚወጡበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡
በዚህ እና በሌላም መንገድ መጽሔቶቹ ግፋ ቢል ከ5 እምብዛም በማይበልጡ፣ እንዲያውም ብዙ ጊዜ
የማይጽፉ ነገር ግን ለመጽሔቱ ሞገስ ሲባል ስማቸው ብቻ በሰፈሩ አምደኞች ስም ከለላ በጥቂት ጸሐፊዎች ቁንጽል ሐሳብ በሚስተናገዱ
በርካታ ጽሑፎች እና በይነመረብ እና ማኅበራዊ አውታሮች ላይ በሚገለበጡ ጽሑፎች ጥገኝነት ገንዘብ ብቻ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ይህንን
የመጽሔቶቻንን ነገር ያየ ሰው ኢቪዲኦን ወደ ወረቀት የመቀየር ሥራ ላይ ብቻ መጠመዳቸው በሐፍረት አንገት ሊያስደፋው ይችላል፡፡
እውነታ ማዛባት
የመጽሔቶቻችን ሌላኛው ትልቁ ችግር እውነታ ማዛባት ነው፡፡ ለምሳሌ ቆንጆ መጽሔት በቁጥር
34 እትሙ ‹‹ብርቱኳን ስዬን በነጻ ለቃለች›› የሚል ነገር በጽሑፉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ብርቱኳን አቶ ስዬን በዋስትና የለቀቀች
መሆኑን መረጃ ለሌለው አንባቢ የተለየ እውነት ሰጥቶ ያሰናብተዋል ማለት ነው፡፡
መጽሔቶች እውነታውን የሚያዛቡት በስህተት ብቻም አይደለም፡፡ ገንዘብ የተቀበሉለትን (በተለይ
የጥበብ) ሥራ አዋድዶ በመጻፍም አሳፋሪ ተግባር ውስጥም አይታጡም፡፡ በዚህ መደድ፣ ለምሳሌ ባለፈው ቅዳሜ (ጥር 19/2005) የወጡት
ሎሚ እና ማራኪ መጽሔቶች በከተማዋ ምንም ሊባል በሚችል መንገድ ያልተደመጠውን የብርሀኑ ተዘራ ‹‹ተበቺሳ›› አልበም እንዴት አሞካሽተው
እንዳለፉት ማንበብ ጥርጣሬውን ለማረጋገጥ መንገድ ይሆነናል፡፡ ሎሚ (ቁጥር 40) ‹‹ተበቺሳ ከሚገባው በላይ ነው ተቀባይነቱ››
ሲል፤ ማራኪ (ቁጥር 33) ደግሞ ‹‹ብርሀኑ ተዘራ ገበያውን እየመራ ነው›› ይለናል፡፡ ጽሑፉን ሲያስነብቧችሁ ግን ማስረጃቸው የቃላት
ድርደራ ብቻ ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡
ርዕሰ አንቀጽ
የመጽሔቶቹ ድክመት ጣሪያ የሚነካው በርዕሰ አንቀጾቻቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ መጽሔቶች ለ40 ገጽ
እትማቸው ግማሽ ገጽ ርዕሰ አንቀጽ መጻፍ አይችሉም፡፡ የሚጽፏቸው አንቀጾችም ቢሆኑ ጠንካራ ጉዳዮችን ለመንካት የማይደፍሩ፣ አቋም
ይዘው የማይሞግቱ ናቸው፡፡ ሎሚ መጽሔት ‹‹ማንዴላ በነጻ ወታደራዊ ስልጠና ያገኙባት አገር በመሆኗ፣ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ወደደቡብ
አፍሪካ ለመሄድ ቪዛ ፍለጋ መቸገር የለባቸውም›› የሚል መከራከሪያ ርዕሰ አንቀጹ ላይ አስፍሯል፡፡ ቆንጆ መጽሔት ርዕሰ አንቀጽ
የጻፈለትን ጉዳይ (የውኃ ክፍል፣ ቴሌ እና መንገድ ትራንስፖርት ተስማምተው እንዲሰሩ የሚመክር አንቀጽ) ዋና ትንታኔ ‹ሦስቱ ባዶ
ወንበሮች› በሚል ጽሑፍ አስቀምጧል፡፡ ሆኖም ጽሑፉ የተወሰደው ከኤፍሬም እሸቴ (አደባባይ) የግል ድረገጽ ላይ ነው፡፡ ኤፍሬም በመጽሔቱ
ላይ በአምደኝነትም ሆነ በአዘጋጅነት ስሙ አልሰፈረም፡፡
ባለፈው ቅዳሜ (ጥር 19/2005) ከወጡት መጽሔቶች ሁሉ በአንጻሩ ጥሩ ርዕሰ አንቀጽ ይዞ
ወጥቷል ሊባል የሚችለው ላይፍ መጽሔት ሲሆን ‹‹ኢቲቪ የመንግሥት ሌባ?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ በአንጻሩ የተሻለ ለመሞገት ሞክሯል፡፡፡፡
የሽፋን ገጽ እና የገጽ ቅንብር
የዲዛይን ጉዳይ ሌላኛው የመጽሔቶቻችን አንባቢዎች የራስ ምታት ነው፡፡ የሽፋን ገጽ ዲዛይኖች
ብዙውን ጊዜ በብዙ ምስሎች የታጨቁ ከመሆናቸው የተነሳ የትኛውን አይተን፣ የቱ ላይ ማተኮር እንዳለብን ራሱ ግራ ያጋባሉ፡፡ ሊያ
መጽሔት (በቁጥር 20) በአንዲት የሽፋን ገጹ ላይ ብቻ የቴዲ አፍሮ፣ ኃ/ማርያም ደሳለኝ፣ ሰብለ ተፈራ፣ አማኑኤል በቀለ፣ መኣዛ
መንሥቴ እና ‹ፎርቹን› ጋዜጣ EPRDF Generation በሚል ርዕስ ከረዥም ጊዜ በፊት ለጻፈው ጽሑፉ የተጠቀመበትን ጀርባቸው
ብቻ የሚታዩ 9 ወጣቶች ምስሎች አትሞ ወጥቷል፡፡
ሎሚም (በቁጥር 40) እትሙ ሰባት የውስጥ ታሪኮቹን ርዕስ በምስል አስደግፎ ሽፋን ላይ አትሟቸዋል፤
ላይፍ መጽሔትም (በቁጥር 99) አምስት የውስጥ ታሪኮቹን ምስል ሽፋን ገጹ ላይ አውጥቷል፡፡ መጽሔቶቹ በተጨማሪም በውስጥ ገጾቻቸው
ቋሚ የሚባል የጽሑፍ አቀማመጥ፣ የፎንት መጠን እና ዓይነት አመራረጥ፣ የምስል አደራደር የላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሲታይ የአንባቢን
የማንበብ ፍላጎት ጥርቅም አድርጎ ለመዝጋት ሲባል የተፈጠሩ ያስመስላቸዋል፡፡
ተስፋ ሰጪዎቹ
መጽሔቶቹ በዚህ ሁሉ የመክሸፍ አደጋ ውስጥ ሆነውም እንኳ ተስፋ ሰጪዎች ከውስጣቸው አይታጡባቸውም፡፡
እንደምሳሌ ዕንቁን እና ቁምነገርን መውሰድ ይቻላል፡፡ ዕንቁ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ የሆኑ ጽሑፎችን በበርካታ ቋሚ አምደኞች እና
አዘጋጆች፣ በተወሰነላቸው ርዕሰ ጉዳዮች እና ሙያዊ ዕውቀቱ ባላቸው ሰዎች እያስተናገደ በየ15 ቀኑ የሚታተም መጽሔት ነው፡፡ (የይዘታቸው
ጉዳይ ገደቡ እንዳለ ሆኖ) ቁምነገርም በተለይ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአብዛኛዎቹ መጽሔቶች ተርታ ለመውጣት
የመሻሽል እርምጃዎችን ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ የሚደነቅ ነው
የከሸፉትን ማን አከሸፋቸው?
ጥያቄው በጥናት የተደገፈ መልስ ያስፈልገዋል፡፡ ሆኖም ከአክሻፊዎቻቸው መካከል ፈጣሪያቸው ኢሕአዴግ
እንዳለበት መናገር ቀላል ነው፡፡ ኢሕአዴግ የግል መገናኛ ብዙኃንን ከፈቀደ በኋላ ቀስበቀስ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየገደላቸው
ነው፡፡ ስስ ወይም ፋይዳ የሌላቸውን ጽሑፎች ብቻ የሚነግሡበትን ባሕል የፈጠረውም የቁጥጥር ፍቅሩ ነው፡፡ ጠንካራ እና የተሻለ ይዘት
ያላቸው የሕትመት ውጤቶች በአንባቢ እጦት ሳይሆን በኢሕአዴግ በጎ ፍቃድ እጦት ከገበያ በአጭሩ ይሰናበታሉ፡። አስተዳደራዊ ተግዳሮቶችን
መፍጠርና ሲብስም የሕግን ከለላነት መጠቀሚያ የሚያደርገው መንግሥት መጽሔቶችን “አደጋ ወደሌለበት ማኅበረሰባዊ ለውጥ ወደማያመጣ
ጨዋታ” ገፍቷቸዋል፡፡ ነገር ግን በክሽፈቱ ውስጥ የአሳታሚዎቹ ለሥራ ጥራት ቁርጠኛ አለመሆን እና ትርፍ ተኮር መሆን ትልቅ ሚና
ያለው መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
አሁን ነጻ ጋዜጣ ማሳተም በኢትዮጵያ ‹‹የማይቻል›› ደረጃ እየደረሰ ያለበት ነው፡፡ ብዙዎቹ
የግል ማተሚያ ቤቶች ማተም የሚችሉት መጽሔት በመሆኑ እና ፖለቲካዊ መረጃዎችን ለማግኘት ሕዝቡ ረሀቡን በመጽሔቶች እያሳየ በመሆኑ
መጽሔቶቹ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ተገደዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የመጽሔቶች የአቅርቦት ባሕል መቀየር አለበት፡፡ ስለዚህ
ትልቁ ቁምነገር ግን መጽሔቶቹን ማን አከሸፋቸው ሳይሆን እንዴት ወደትንሳኤ ይምጡ የሚለው ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የመጀመሪያው
ጉዳይ ችግር እንዳለባቸው በማመን ችግራቸውን ለይተው ለማወቅ እና ለማረም ቁርጠኝነት ላይ እንዲደርሱ መምከር ነው፤ ከዚያ ስም ያለው
መጽሔት ለመገንባት መውሰድ የሚገባውን ‹ሪስክ› ሁሉ መውሰድ፡፡
ይህንን ለሚሞክር አንባቢው እንደማያሳፍር በተደጋጋሚ አሳይቷልና፡፡
---
ማስታወሻ፡-
ይህ ጽሑፍ ‹‹መክሸፍ››
በሚል ርዕስ የምናወጣቸው ተከታታይ ጽሑፎች አካል ነው፣
ተጓዳኝ ጽሑፍ፡-
----
የዚህ
ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይበብ በታገደው በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡
No comments:
Post a Comment