በእነዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝግብ ተከሰው የነበሩት 4 የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አብርሃም ሰለሞን ነፃ ቢባሉም በይግባኝ ታግደው ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት እየተመላለሱ እንደሆነ ይታወቃል። አሁንም ለቃል ክርክር ሕዳር 29, 2008 ተቀጥረዋል። ቀሪዎቹ፣ ማለትም ዘላለም ወ/አገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ባሕሩ ደጉ፣ ሰለሞን እና ተስፋዬ ከሕዳር 13–16, 2008 ድረስ ከፊል መከላከያዎቻቸውን ያስደመጡ ሲሆን ቀሪውን ዛሬ (ሕዳር 24, 2008) ያስደምጣሉ።
እነዘላለም ተከላከሉ የተባሉት በፀረ–ሽብር ሕጉ አንቀፅ 7/1 መሠረት የግንቦት 7 አባል በመሆን ሠርታችኋል በሚል ነው። በ5ቱም (ዘላለም፣ ዮናታን፣ ባሕሩ፣ ሰለሞን እና ነፃ ተብሎ በይግባኝ የተያዘው አብርሃም ሰለሞን) ላይ የመሰከሩት 3ተኛ የዐ/ሕግ ምስክር አቶ እዮብ ሲሆኑ፣ የምስክርነታቸው ጭብጥ በጥቅሉ ‘ዘላለም ወ/አገኘሁ መልምሏቸው ለግንቦት 7 ወታደርነት 3 ሰዎችን መልምለው ከወሰዱ በኋላ ጎንደር ላይ ባለመስማማታቸው እንደተመለሱ። ከ3ቱ አንዱ እዚሁ መዝገብ ላይ 8ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ሰለሞን መሆናቸውን። አቶ ዘላለም በባሕሩ እና ዮናታን ሥር የተደራጀ ቡድን መኖሩን እንደነገሯቸው’ የሚያስረዳ ነው።
አቶ ሰለሞን፣ ዮናታን እና ዘላለም ከፊል ምስክሮቻቸውን ያስደመጡ ሲሆን አቶ ተስፋዬ (10ኛ ተከሳሽ) ጉዳያቸው ከነዘላለም የተለየ ቢሆንም አንድ መዝገብ በመሆናቸው ምስክሮቻቸውን አስደምጠው ጨርሰዋል።
አቶ ሰለሞን ሁለት ምስክሮችን አቅርበው እዮብ "የተሻለ ሥራ አገናኝሃለሁ በሚል አቶ ሰለሞንን ወደጎንደር ከወሰዷቸው በኋላ ጎንደር ሲደርሱ ለግንቦት ሰባት ወታደርነት እንደሆነ ሲነግሯቸው" መመለሳቸውን አስመስክረዋል። ራሰቸውም በሰጡት ቃል እዮብ እየወሰዳቸው እያለ መቶ አለቃ እያለ ከሚጠራው ሰው ጋር በስልክ ይነጋገር እንደነበርና የዘላለምን ስም ጨርሶ እንዳልሰሙ ተናግረዋል።
ዮናታንም በበኩሉ እስካሁን 4 ምስክሮችን አስደምጧል። የመጀመሪያው አብሮ አደግ ጓደኛው ሲሆን፣ ዮናታን ውጭ አገር ለሚደረግ የሰብኣዊ መብትና ሚዲያ ነክ ሥልጠና ሊሄድ መሆኑን ነግሮት እርሱም ከፈለገ ሲቪውን እንዲሰጠው ጠይቆት መስማማቱን፣ ነገር ግን ሥልጠናው ባልታወቀ ምክንያት መስተጓጎሉን ለችሎቱ አስረድቷል። በሁለተኝነት የቀረበው ምስክር አቶ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ ስለእነዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች ሠላማዊነት እና ሰጪዎቹም ዓለምዐቀፍ ዕውቅና የተቸራቸው ስለመሆኑ የባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል። በሦስተኝነት የቀረበው ምስክር አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ እዮብ ማዕከላዊ እያለ አናግሮት እንደነበር፣ ዮናታንን ፍፁም እንደማያውቀው፣ በኋላ ግን በድብደባ ብዛት እግሩ ተጎድቶ ማንከስ ሲጀምር እና ሥራ የሌላት ሚስቱና ልጁ ዕጣ ሲያሳስበው ተስፋ በመቁረጥ ሌሎቹ ላይ መስክሮ ሊፈታ መሆኑን እንደነገረው ለችሎቱ ነግሯል። በአራተኝነት ዘላለም ወ/አገኘሁ ቀርቦ እዮብ "ዘላለም በዮናታን ሥር ቡድን አለ ብሎ ነግሮኛል ያለው ሐሰት ነው" ብሏል።
ዘላለም ወርቅአገኘሁም ለራሱ እስካሁን 4 መከላከያ ምስክሮችን ያስደመጠ ሲሆን በቀዳሚነት የቀረበው ጥበቡ የተባለው አብሮ አደግ ጓደኛው ነበር። ጥበቡ፣ በክሱ ላይ የግንቦት 7 አመራር ተብሎ የተጠቀሰው ተድላ ደስታ አብሮ አደግ ጓደኛቸው እንደሆነና፣ እንግሊዝ አገር ከሄደ በኋላም ተማሩ እኔ ገንዘብ እልክላችኋለሁ ብሎ ገንዘብ ለሁለቱም እንደላከላቸውና ዘላለም ከመያዙ በፊት ማስተርሱን መማር እንደጀመረ ተናግሯል። የዘላለም እናት ወ/ሮ የኔእናትም በበኩላቸው ተድላ ደስታን ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያውቁት የልጃቸው ጓደኛ በመሆኑ መሆኑን ጠቅሰው በ2005 ብር ልኮለት እሳቸው ጨምረውበት ዘላለም ትምህርት መጀመሩን ለችሎቱ ገልጸዋል። ቀሪዎቹ ሁለት ምስክሮች ሙዘሚል እና አዲሱ የተባሉ በክሱ ላይ በዘላለም ለግንቦት 7 የተመለመሉ እንደሆኑ የተገለጹ ወጣቶች ናቸው። ሁለቱም ወጣቶች በየተራ ከዘላለም ጋር ያላቸው ዕውቂያ በሰፈር ልጅነት እንደሆነና ምንም ዓይነት የሚያውቁት ቡድን እንደሌለ እና በቁም ነገር ቁጭ ብለው ያወሩበት አጀንዳም እንደሌለ ተናግረዋል።
ዘላለምና ዮናታን በሰጡት መከላከያ ቃላቸውም ላይ ወደውጪ ለሰብኣዊ መብትና ሚዲያ ነክ ሥልጠናዎች ለመሄድ ክሱ ላይ የግንቦት ሰባት አመራር ተብሎ የተጠቀሰው እና እነርሱ በጋዜጠኝነቱ እንደሚያውቁት የተናገሩት አርጋው አሽኔ ጋር ከመነጋገራቸው በቀር ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። ዘላለም፣ ሌሎችን ላለማስፈራራት ሲል ዝርዝሩን እንደማይናገር ነገር ግን በሐምሌ ወር፣ በቀዝቃዛ እና ዘጠና ሳንቲሜትር በሆነች ጨለማ ክፍል ውስጥ 41 ቀን መቆየቱንና ጠባሳ የማይተው ነገር ግን የነርቭን ስርዓት በሚያዛባ ምት እየተመታ መመርመሩን ተናግሯል።
በጥቅሉ ዐ/ሕግ ያቀረበው ክስ እና ማስረጃ ጠቅላላ ምስል፣ «ከውጭ አገር ገንዘብ በሚላክለት ዘላለም አማካኝነት የተመለመለው እዮብ ለግንቦት ሰባት ወታደሮችን እየላከ፣ ዘላለምም በሠላማዊ ትግል ሥም ቡድኖችን እያዋቀረ እንደሆነ» ለማሳየት ሲሞክር፣ እነዘላለምም በመከላከያቸው «ከውጭ አገር የተላከው ገንዘብ የዘላለም አብሮ አደግ ጓደኛ ለዘላለም የግል ፍላጎት የላከው መሆኑን፣ እዮብ ለግንቦት ሰባት ወታደርነት [እያታለለ] በወሰዳቸው ሰዎች ውስጥ ዘላለም እጁ እንደሌለበት፣ ቡድን እየተባለ የሚጠራ ነገር እንደሌለ እና ዜጎች ሁሉ ቢወስዱት የሚመከር ሥልጠና ለመውሰድ መጻጻፋቸውን በዚያ መንገድ እንደተተረጎመባቸው» የሚያስረዳ የመከላከያ ምስል ለመፍጠር እየሞከሩ ነው።
Thank you for the good post.
ReplyDeleteThe information is Really very interesting and very easy to understand, I like this!
ReplyDeleteI read your article very impressively I want to write something like this
ReplyDeleteThank you for taking the time to publish this information very useful!
ReplyDeleteI really appreciate reading this blog it is very impressive and informative content.
ReplyDelete