Saturday, January 5, 2013

ተቃዋሚን በአንድ የመፈረጅ ጣጣ




መቼም ተቃዋሚ ስል የትኛው ዓይነቱን ተቃውሞ ለማለት እንደፈለኩ ሳይገባችሁ የቀረ አይመስለኝም፡፡ በሃገራችን በአሁኑ ሰዓት የኢሕአዴግን አገዛዝ ወይም መንግሥትን የሚቃወሙትን ማለቴ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ እና በተቋም መልክ ያልተደራጁትን ተቃዋሚዎች ትተን (እነርሱ ቢበዙም) ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያገኙ ፓርቲዎችን ብቻ ብንቆጥር 79 ናቸው፡፡ (ምንጭ፤ የምርጫ ቦርድ ድረገጽ)

በተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዛት ደረጃ የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ተቋም ቢኖር ኖሮ በዚህ እንኳን ከመጨረሻ ሳይሆን ከመጀመሪያ አንደኛ እንደምንሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በወቅቱ ያላቸውን የሥራ ብቃት እና ቆራጥነት ማነስ ትተን፤ በቁጥር መብዛታቸው ብቻ በራሱ የፖለቲካ አካሄዳችን ብዙ እንደሚቀረው እና የአመለካከት ችግር እንዳለ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ እንጂ በሰላም ሃገር ለአንዲቷ ሃገር ይሄ ሁሉ ፓርቲ እኔ ነኝ ብቸኛው አማራጭ በሚል የተለየዩ አካሄዶችን እያሳየ ልባችን ባልከፋፈለው ነበር፡፡

የተቃዋሚዎቹ ብዛት ከላይ እንደገለፅኩት ሆኖ ሳለ፤ በኢህአዴግም በተቃዋሚዎችም ዘንድ ተቃዋሚዎችን እንደ አንድ የመቁጠር/የመፈረጅ ችግር በስፋት የሚስተዋል ነገር ነው፡፡

ከኢሕአዴግ ጎራ

የኢሕአዴግ ፓርቲ፣ በፓርቲው ስር የሚገኙ ተቋማት፣ የፓርቲው አድናቂ፣ አፍቃሪ እና ተቆርቋሪ የሆኑ ከዚህ ምድብ ይካተታሉ፡፡ በዚህ ምድብ ያሉ ስለተቃዋሚዎች ሲናገሩ ስትሰሙ ወይም የጻፉትን ስታነቡ በአብዛኛው አስተያየታቸውን የሚሰጡት ሁሉንም እንደ አንድ በመቁጠር መሆኑን መታዘባችሁ ግድ ነው፡፡ እንግዲህ ያሳያችሁ 80 የሚጠጉ ተቃዋሚ ፓርቲ መኖራቸው እየታወቀ፤ ሁሉም ደግሞ የየራሳቸው ልዩነት እና አቋም እንዳላቸው እየታወቀ፤ ለምን ሁሉንም ጨፍልቀው በአንድነት፣ አንድ ዓይነት ስድብ እንደሚሳደቡ (መቼም ‹‹ምስጋና›› አንጠብቅባቸውም) ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቹ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ኢህአዴግን መቃወማቸው እና ተቃዋሚነታቸው ብቻ ነው እንጂ የሚቃወሙበት መስመር፣ ምክንያት፣ የያዙት አጀንዳ፣ ዓላማቸውና እና የሚከተሉት አሰራር ፍፁም የተለያየ ነው፡፡

እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ በዚህ ምድብ ያሉት ግን አንደኛው ተቃዋሚ ያለውን ሐሳብ ‹‹ተቃዋሚዎች እንዲህ አሉ፣ ሊያደርጉ ነው፣ ናቸው›› በሚል የሁሉም እንደሆነ በማስመሰል ተቃውሞን በሙሉ በአንድ በመፈረጅ አስቸጋሪ መልክ አስይዘውታል፡፡

እንግዲህ አስቡት፤ ለምሳሌ እኔ በግሌ /እንደ አንዲት ነጠላ ግለሰብ/ ኢሕአዴግን ተቃውሜ ያነሳሁትን ሐሳብ፤ ‹ተቃዋሚዎች እንዲህ አሉ› ወይም ‹ይላሉ› ተብሎ የኔ የግሌ ብቻ የሆነው ሐሳብ የሁሉም ነው ሲባል፤ ወይንም ደግሞ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ተቃውሞ ያነሳውን ሐሳብ፤ የተቀሩት ተቃዋሚዎች እንዳሉት ተደርጎ ሲወሰድ እና የተቃዋሚዎች የጋራ ሐሳብ እንደሆነ ሲቀቆጠር፡፡

በተጨማሪም እነዚህ ምድቦች  የሚቃወምን ግለሰብ ከተቃዋሚ ፓርቲ ጋር የማስተሳሰር ክኅሎትም አላቸው፡፡ አንድ ግለሰብ ከተቃወም በቅድሚያ በአእምሯቸው የሚመጣው ከጀርባው የትኛው ፓርቲ እንዳለ ነው እንጂ፤ ግለሰብ እራሱን ችሎ መቃወም እንደሚችል አያስቡም ወይም ማሰብ የሚፈልጉም አይመስለኝም፡፡

ከተቃዋሚ ጎራ

በዚህ ምድብ ኢሕአዴግን በተለያየ ደረጃ የሚቃወሙ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎች እና የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው የሚቃወሙትን ይመለከታል፡፡ በዚህ ምድብ የሚገኙት ከላይ እንደተነጋገርነው ብዛታቸውም የትዬለሌ ነው ልዩነትም አላቸው፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው› በሚለው ብሒል መሠረት የተቃኘ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሲብራራ፡ እከሌ የተባለ ግለሰብ ወይም ሚዲያ ወይም ፓርቲ የተቃወመበትን ሐሳብ ሌሎችም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ተቃዋሚ ግለሰቦች፣ ሚዲያዎች ወይም ፓርቲዎች እንዲቀበሉት/እንዲደግፉት ይጠበቃል ማለት ነው፡፡ ካልሆነ የደጋፊ ብዛት ባለው ተቃዋሚ፤ ከተቃዋሚ ሰፈር የማግለል እና ስም የማጥፋት/ስም የመስጠት ዘመቻ ይካሄዳል፡፡ ገና ለገና በተቃዋሚ ጎራ ስላሉ በሁሉም ጉዳይ መስማማት እና ስምምነትንም መግለፅ ግዴታ መሆን የለበትም፡፡ አንደኛው ተቃዋሚ የሌላውን ሐሳብ ሁሉ (ኢሕአዴግን ስለተቃወመ ብቻ) መቀበል ከቻለማ መከፋፈልን እና ተለያይቶ መሥራትን ምን አመጣው? ለምንስ ያ ሁሉ ፓርቲ ተመሠረተ?

በሁለቱም ጎራ በተደጋጋሚ ተቃዋሚን በአንድ በመፈረጅ የሚሠሩትን ስህተቶች ለማስወገድ፤  በኢሕአዴግ ጎራ ያሉት፣ በተቃወሚው በኩል ያለውን ልዩነት ከግምት ውስጥ ያስገባ  እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን መቃወም ብቻ አንድ እንደማያደርግ በመገንዘብ ለልዩነቶቻቸው ዋጋ በመስጠት እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አካሄድ በመከተል፤ በሁለቱም ምድብ የሚገኙት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
----
የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡

Thursday, January 3, 2013

ምሁርነት እና ምሁር



በተለያዩ የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አንድ የተለመደ አባባልን ማስተዋል የተለመደ ነው፤ ‹በምሑራን* ተሳትፎ የኢትዮጵያን ሕዳሴ እናረጋግጣለን› የሚል ፅሁፍ በሕዳሴው ግድብ ፎቶ ታጅቦ፡፡ ቃላቶቹ ከተሰቀለበት ቦታ አንፃር ስንመለከተው ምሁሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መሽጓል፤ ሕዳሴውንም ‹በምሑሩ› ፊት አውራሪት ይረጋገጣል የሚል አንድምታ እንዳለው መረዳትም ብዙም አይከብድም፡፡

በርግጥ ምሁሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አለን? ኧረ እንዲያውም ምሁር በአጠቃላይ በሀገራችን አሉ ወይ? እያልን እንጠይቅ ዘንድ ፈቀድን፡፡

ምሁር ስንል

በተለያዩ ወቅቶች እና ቦታዎች መታዘብ እንደምንችለው ‹ምሁር› የሚለው ስያሜ በሀገራችን ተለጥጦ ፊደል የቆረን ሁሉ አካትቶ ይዟል፡፡ ኮሌጅ የበጠሰ ሰውማ የሊቀ-ሊቃውንትነት ካባን ይደርባል፡፡ እዚህ ላይ በመጀመሪያ የምናገኝው ችግር ምሁርን (Intellectual) ከባለሙያ (Professional) መደባለቅን ነው፡፡ ባለሙያ የሚለውን ማዕረግ ከሳቴ ብርሃን የአማረኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ሥራን ዐዋቂ መኾን ልዩ ልዩ የትምህርት ሥራን የእጅ ሥራ ጥበብን ማወቅ ወይንም ያንድ ቀን ሥራን ሠርቶ ደመወዝን ማግኘት።›› በማለት የተወሰነ ስራን መስራት እና ምንዳን እንደ ምላሽ ማግኝት (Quid Pro Quo) በማለት ሲያቀርብ፡፡ ምሁር የሚለውን ስያሜ ደግሞከፍተኛ የሆነ የማሰብና የመመራመር ችሎታ ያለው፤ ሊቅ የተማረ በኹሉ ምሉ ትምህርት ያለው ሰው› ብሎ ሰፊ ደርዝ በማስያዝ ምሁርነት ከፍ ያለ ጉዳይ እንደሆነ ያሰረዳል፡፡

Robert Roberts እና Jay Wood ‹Intellectual Virtues› ባሉት መፅሃፋቸው አንድ ምሁር ሊኖረው ስለሚገባው መሰጠቶች (Virtues) አብዝተው ይተነትናሉ እንደ ፀሃፊያኑ ገለፃም ምሁር፤ ምሁር ለመባልም እውቀትን የመሻት (Love of Knowledge) ፀናኢነት (Firmness)፣ ልበ ሙሉነት( Courage)፣ ቀናኢነት (Humility)፣ ነፃነት (Autonomy)፣ ደግነት (Generosity)፣ እና በሳት የፈተነ ጥበብን (Practical Wisdom) መታደል ይኖርበታል በማለት፤ የምሁርነት ተራራ ብዙ ነገሮችን ያቀፈ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

እንግዲህ የአፍላጦኗ (Plato) ሀገረ-መንግሰት (State) በእነዚህ ላቅ ያሉ ስብዕናዎች የምትመራ ነች ማለት ነው፡፡

የእኛዎቹ ወዴት ናቸው?

ምሁር መባል እንዲሁ ቀላል ነገር እንዳልሆነ ከትርጎሞቹ ለማየት ችለናል፡፡ ምሁርነትም መለያ ባህሪውን በራሱ አሳቢ መሆን በማድረግ፤ ምጡቅነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡

እናም በሀገራችን በኢትዮጵያ እነዚህን አሳብያን ከወዴት አሉ? ብለን እንጠይቃለን፡፡ በመጀመሪያ የተማረ ሰው ሁሉ ምሁር እንዳልሆነ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስመርቋቸውም ተማሪዎች ባለሙያዎች እንጅ ምሁራን እንዳልሆኑ ከትርጉሙ እና ማሟላት ካለባቸው መሰጠቶች አንፃር አይተናል፡፡


ከዚህ በመለስስ ኢትዮጵያዊ ምሁርን ወዴት እናገኝዋለን? ቀጣዩ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የምሁር መሰጠቶች ጋር በተያያዘ አሜሪካዊው ሊቅ Noam Chomsky የምሁራን ድርሻ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ምንድነው? ብለው ይጠይቁና ‹It is the responsibility of intellectuals to speak the truth and to expose lies-የምሁር ዋነኛ ግዴታው ለእውነት መኖር እና እውነትን መናገር ነው› ብለው ይመልሳሉ፤ የትኛውን እውነት? ሲባሉም የMartin Heideggerን የእውነት ትርጉም በመዋስ ‹ህብረተሰቡን እርግጠኛ፣ ግልፅ፣ ጠንካራ እና አዋቂ የሚያደርገውን እውነት› ብለው ይመልሳሉ፡፡

እናም ይሄ ኢትዮጵያዊ ምሁር ወዴት አለ? ፍትህ ተጓደለ የሚለው ሊቅ፣ መብት ይከበር ማለት የሚገደው ልበ ብርሃን፣ ደፋሩና ፅኑው ምሁር ኢትዮጵያ ውስጥ ወዴት ነው? 

የምሁር ካባ ለባሹ

የነጠረውን ምሁር ፈልጌ ባጣ ጊዜ፤ እስኪ ከተለመደው ‹የምሑር› ሰፈር ይፈለግ ብየ አሰሳ ገባሁ፡፡ ጂቡቲያዊው የዩኒስኮ ሰራተኛ Ali Moussa Iye በአፍሪካ ቀንድ ያለው የምሁራን ጉዳይ እጅግ አሳስቧቸው ‹The Betrayal of the Intellectuals›  በሚል ርእስ፤ ስለ ቀንዱ ሀገራት የምሁራን ክህደት እና መፍትሄው አጭር ፅሁፍ ፅፈዋል፡፡ ፅሁፋቸውን ሲጀምሩም ‹የቀንዱ ሀገራት ምሁራን አደግዳጊ፣ አቤት ወዴት ባዩችና ሎሌዎች ናቸው› በማለት ነው፡፡ ሲቀጥሉ ‹They have rallied to every flag of convenience raised by powerholders and powerseekers… Intellectuals in the Horn of Africa have failed to fulfill their mission and have betrayed their people.› በማለት ‹ምሑራን› በቀንዱ ሀገራት ከዳተኛ እና ሸክም እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ጋናዊው ፕሮፌሰር ጆርጅ አይቴ እነዚህን ‹ምሑራን› ‘Intellectual Prostitutes’ ይሏቸዋል፡፡ የሀገራችን ‹ምሑራንስ› ከዚህ ይልቃሉን?

‹ግማሽ ወንበዴ፣ ግማሽ መደዴ›

ፊደል የቆጠሩ፣ በዲግሪ ላይ ዲግሪ የደራረቡ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ አይካድም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንባቢ-ማህይማን (Functionally Illiterates) በዝተው ይታያሉ ማለትም ለኔ ስህተት አይደለም፡፡ ሀብት በምን መንገድ ማጋበስ እንደሚቻል ሲያሰላስል የሚውል ዶክተር እና ፕሮፌሰርን ማየት ብርቅ አይደልም፡፡ ሀብትን መፈለግ ሳይሆን ችግሩ የሕዝቡን ሀብት ዘርፌ ካልሄድኩ ብሎ መኳተኑ ነው ትዝብቱ፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ወንበዴው የምሁር ካባ ለባሽ፡፡ በምሁርነት ካባ ለባሹ ሌላኛ ተርታ የሚሰለፈው ደግሞ ‹ሀገሪቱን ወዴት እናስኪድ?› ማለቱን ትቶ፤ ‹እኔ ወዴት ልሂድ?› ማለትን የሚያዘወትረው ነው መደዴው፡፡

የPrinceton ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት Forrest Colburn በወታደራዊው ዘመነ መንግስት ጊዜ በፃፉትና ‹The Tragedy of Ethiopia's Intellectuals› ባሉት ፅሁፋቸው ላይ አንድ ተማሪ እንዲህ አለኝ ይላሉ "Ignorants are more concerned about Ethiopia than are intellectuals." ይህ ነው ኪሳራው፣ ይህ ነው ድቀቱ፡፡

አሸርጋጁ

በሌላ በኩል ደግሞ መንግስታዊ መናን በማሰላሰል መንግስትን አይዞህ በርታ የሚሉ ‹ምሑራን› አሉ፡፡ መንግስትን የሚቃወም ሀሳብም ሲቀርብ ጅራፍ እያነሱ ጀርባ ገራፊዎች ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መንግስትን መቃወም እንደ አንጀራ የያዙ ‹ምሑራን› ተሰልፈዋል፡፡ በመንግስት ተቀጥሮ፤ ለመንግስት ስራ መስራት ስህተት ነው እያልኩ አይደለም፤ መንግስትንም ማማከር ሀጢያት የለውም፡፡ ስህተቱ የሚጀምረው ‹ምሁራን ዋነኛ አላማቸው ለእውነት መኖር ነው› የሚለውን ጥልቅ ሀሳብ ትቢያ ላይ ወርውረው ጥለው. የምሁርነት ካባውን ግን ሲደርቡት ነው፡፡ ወይ ካባውን ማውለቅ ያለዛም ለሀሳበ መኖር ነው ምርጫው መሆን ያለበት፡፡ ግን በምን ወኔ፡፡ ‹ምሑር› ካልተባሉ መናው ይቀራላ፡፡

ምሁር› የለሽ፣ ‹የአደባባይ ምሁር› ትፈልጊያለሽ

እንደ Edward Saïd ያሉ ፀሃፍት ‹[The] ... real or 'true' intellectual is, therefore, always an outsider, living in self-imposed exile, and on the margins of society.› ይላሉ፡፡ ‹ምሁር ከባዕቱ መውጣት የለበትም፤ ራሱን ያሳሰረ የህብረተሰብ ግንጣይ ነው› ይላሉ፡፡ ይህ ‹የጋን መብራት› የሚባለው  ነው፡፡
ገጣሚው ከበደ ሚካኤል በበኩላቸው፡
‹‹የተማረ ሆኖ፣ እውነቱን የማይገልጽ
ባለ ጸጋ ሆኖ፣ ገንዘቡን የማይሰጥ፣
ደሃ ሆኖ፣ መስራት የማይሻ ልቡ፣
ሶስቱም ፍሬ ቢሶች፣
ለምንም አይረቡ።››
ይላሉ፡፡
ዘመናዊ እሳቤው ምሁራን ለህብረተሰቡ ግልጋሎት ይሰጡ ዘንድ ይሰብካል፡፡ ምሁራን ወደ ሕብረተሰቡ ሲወጡም የአደባባይ ምሁራን (Public Intellectuals) ይባላሉ፡፡ እናም በሀገራችን እነዚህ የአደባባይ ምሁራን ያሰፈልጉናል ማለታችን ያስማማን እና ግን የታሉ? ከወዴትስ ይመጣሉ? አሁንም ጥያቄ ነው፡፡ በርግጥ የጓዳውን ምሁር ሳናገኝ የአደባባዩን ምሁር መፈለጋችን ቧልት ይሆን?
ምሁሩ ወይ ወዴት ነህ? ምሁሩን ያገኛችሁ ወይም የት እንደገባ የምታውቁ እስኪ ሀሳባችሁን ወዲህ በሉ፡፡

* በዚህ ፅሁፍ በሀገራችን በተለምዶ ‹ምሑር› የሚባሉትን ለመግልፅ ሐመሩ ‹ሐ›ን መጠቀምን መርጫለሁ፡፡ ለቀሪዎቹ ግን የተለመደውን ‹ምሁርን› ተጠቅሜያለሁ፡፡ 

መጅሊሱን ከውስጥ ስንመለከተው


በመሐመድ ካሊድ

በአንድ የግል ጋዜጣ የዘንድውን አወዛጋቢ የመጅሊስ ምርጫ አስመልክቶ የተመረጡትን ሰዎች ፕሮፋይል እየተመለከትኩ ነበር፡፡ ከጎኔ የነበረ ሰው የሙስሊም ኮፍያዬን ቀና ብሎ ተመልክቶ ከበፊቱ መጅሊስ የተሻለ ዓለማዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ዕውቀት እንዳላቸው ነገረኝ፡፡ በጋዜጣ መሸጫ ዙሪያ “ሲቪሎች” ስለሚበዙ እሱም መረጃ እየሰራ ይሆናል በሚል ግምት በአጭሩ ያለውን መስማማቴን በንቅናቄ ገልጬ ገጹን በመገልበጥ አባረርኩት (አባረረኝ)- ብቻ ያው ነው፡፡ ከዚህ ሰውዬ አስተያየት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያማጥኩትን ለአንባቢያን ላበቃ ዘንድ እነሆ ብእሬን አነሳሁ፡፡ 

ስለ ሰላማዊ ትግል በሚወራበትና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለ 1 ዓመት ሙሉ ሕገ ወጡ መጅሊስ ይወገድ ከማለት ጀምሮ እስከ መሪዎቼ ይፈቱ ከዚያም ምርጫው ውድቅ ይደረግ ጥያቄ በአወሊያ ተጀምሮ እስከ ታላቁ አንዋር መስጂድ በዘለቀው የሰላማዊ ተቃውሞ የአንድ ዓመት ክብረ በዓል እየተከበረ ባለበት ወርሐ ታኅሳስ የመጨረሻ ሳምንት ስለ በግዱ መጅሊስ ማውራት ባይመስጥም ቢያንስ ውስጣዊ አሰራሩን ታነቡት ዘንድ ከትቤዋለሁ፡፡

አዲሱ መጅሊስ

በመጅሊሱ “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” በሚለው ይሁን የእውነት አምነውበትና በአላማው ተመስጠው አሊያም ካድሬነት በሀይማኖት ተቋም ብዙ ተሰላፊ ስለሌለውና ሕወሓቶች ስለማይበዙበት በቀላሉ ትልቅ ካድሬ ሆኖ ለመገኘት ሲሉ አለያም የሀጅ ቢዝነስ አሪፍ ነው ሲባል ሰምተው አላውቅም ብቻ ወንድሞቻቸው አደባባይ እየጮሁ አልፈው ጥቂቶች የተወዳደሩበት በግዴታ ምርጫ ተካሂዶ እነሆ  እንደገና ተዋቅሯል፡፡ (አህመዲን አብዱላሂንም እንደስም ይጠራበት የነበረውንና ጨርቅ ከመሆኑ በቀር የአጼ ምኒሊክን ዘውድ የሚመስለውን ጥምጣሙን ተገላግሎ በኮፍያና በሸሚዝ መሀል ቦሌ ፈታ ብሎ ሲሄድ ልናየው ችለናል፡፡)

አዲሱ መጅሊስ የመጣበትን የምርጫ ሂደት ከቀበሌ መጀመሩ በታሪክ የመጀመሪያ ነው፡፡ ይህን ምርጫ ለማስተባበርም የተሰጠውም የመንግስት ሚዲያ ሽፋን ከመቼውም የተሻለ ነው፡፡ ተቃውሞውም እንዲሁ ታላቅ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል በመጅሊሱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በድግሪና በማስተርስ ድግሪ ደረጃ የተማሩ ሰዎች ለስራ አስፈጻሚነት ደረጃ መድረሳቸው፡፡ ስለነዚህ ጉዶችም ብናወራ የመጅሊሱን ሁኔታ ለመረዳት የሚረዳ ይመስለኛል፡፡

አዲሱ መጅሊስ በሸህ ኪያር ሙሀመድ ፕሬዝዳንትነት ይመራል፡፡ በዋናው የመጅሊስ ስልጣን ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እና ለስላሳው ለውሳኔ የሚቸገሩት ሙሀመድ አሊ እንደ ዋና ጸኀፊ ተወዝተዋል፡፡ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የህዋሃት አባል የሆኑትና የቀድሞ የትግራይ ክልል የሸሪዓ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣የክልሉ እስልምና ጉዳይ ፕሬዝዳንትነትና ሁሉንም ስራ አስፈጻሚ አባረው የሁሉም ዞኖች ተወካይ በመሆን ሁሉን ነገር የራሳቸው ጠቅለው በመያዝ ያላቸውን የአንባገነንነት አቅም ያስመሰከሩት ሼህ ከድር ማህሙድ ተሰይመዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ሌሎቹን ስራ አስፈጻሚዎች በሌላ ጊዜ አስተዋውቃለሁ፡፡ 

Tuesday, January 1, 2013

የሥርዐት ለውጥ እና ሃይማኖቶች




ሃይማኖት ከጊዜ ወደጊዜ ፖለቲካዊ አቅሙን እያጣ የሚሄድ እና በገለልተኛ አስተሳሰብ የሚተካ እንደሆነ ፖለቲከኞች ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም እውነታው ተቃራኒ መሆኑን ‹ሃይማኖቶች በየጊዜው ያንሰራራሉ› (“Religious resurgence is a cyclical phenomenon”) በማለት እንደዶናልድ ስሚዝ ያሉ የፖለቲካ እና ሃይማኖትን ግንኙነት በጥልቀት ያጠኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ ከአየናቸው የአረብ አብዮቶች እንኳን መረዳት እንደምንችለው የቱኒዚያው ኤናህዳ (Ennahda) እና የግብፁ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲዎች በምርጫ ማሸነፋቸው ምናልባትም እምነት ላይ መሠረታቸውን ያደረጉ የፖለቲካ አጀንዳዎች ወደፊት ተመልሰው ይመጡ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ጆሮ እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ሃይማኖታዊ በዓላት ከመቼውም ጊዜ በላይ በደማቅ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተከበሩ መምጣታቸው፣ የዶግማ ጦርነቶች በቪዲዮ ካሴቶች መበራከታቸው እና ሌሎችም ምልክቶች የሃይማኖትን ቦታ መልሶ ወደፖለቲካው መድረክ እንደማይመጣ እርግጠኛ ሆኖ መናገርን እያከበደው ይመስላል፡፡

ምንም እንኳን ሴኩላሪዝም (ከሃይማኖት ነጻ የሆነ የፖለቲካ ዐውድ መፍጠር) ሙሉ ለሙሉ እውነት ሊሆን የማይችል እንደሆነ ቢታመንም ያደጉ አገራት ከታዳጊዎቹ ይልቅ የሃይማኖትን ተጽዕኖ ከመንግሥት ጫና ላይ በማላቀቁ ረገድ የተሻለ እየተሳካላቸው ነው፡፡

በድህነት ደረጃቸው ሦስተኛው ዓለም በሚባሉት እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት የሃይማኖቶች ሚና በፖለቲካው ዕጣ ፈንታ እስከመፍረድ ሊደርስ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ የሆኑ እና ነጻነታቸውም ውሱን የሆኑ ሰዎች ተስፋ የሚጥሉት ከመንግሥታዊ ሥርዐቱ ይልቅ ‹‹በፈጣሪያቸው›› ላይ መሆኑ ያፈጠጠ እውነታ ነው፡፡

Religion and Politics in Arab Transitions በሚል ርዕስ በባራሕ ሚካኤል FRIDE ለተሰኘ አንድ የአውሮፓ የማሰቢያ ቋት (Think Tank) የተሠራ ጥናት እንደሚተነትነው ‹የአንድ አገር ማኅበረሰብ ሃይማኖተኝነት በአገሪቱ የሥልጣን ሽግግር ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ ሆኖም ሃይማኖት በሥልጣን ሽግግር ላይ የጎላ ሚና ከተጫወተ ሽግግሩ ዴሞክራሲያዊ ውጤት ላይኖረው ይችላል› ይለናል - ጤናማ ዴሞክራሲ በአንድ ወይም ጥቂት የሃይማኖት እሳቤዎች ብቻ የተገደበ እንደማይሆን (ወይም ብዝኃነትን እንደሚያገናዝብ) እያብራራ፡፡

የሃይማኖት ጉዳዮች ብዙውን ጊዜ የሚያያዙት ከፖለቲካዊ ሥልጣን ጋር ነው፡፡ ብዙዎች ሃይማኖትን ሥልጣን ለማግኛ (ለጥሩም ይሁን ለክፉ) ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ በላቲን አሜሪካ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከአምባገነናዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ለመሸጋገር በተደረገው ጥረት ውስጥ የጎላ ሚና ተጫውታለች፡፡ ቤተክርስቲያኗ በአርጀንቲና የNational Reorganisation Process in Argentinaን ደግፋለች፤ በቺሊ ለPinochet አገዛዝ ተቃውሞዋን ገልፃ በኤል ሳቫዶር ለሚካሄደው ሕዝባዊው የለውጥ እንቅስቃሴ ድጋፍ አሳይታለች፡፡ በቱርክ የጉለን (Gülen) እንቅስቃሴ የተመራው በሱፊ እስላም ወንድማማቾች ነው፡፡ ይህ እና መሰል እንቅስቃሴዎች የሚያስረግጡልን ፖለቲካዊ ፍላጎት ላላቸው አማኞች ሃይማኖት ጥሩ አብዮታዊ መሣሪያ መሆኑን ነው፡፡

በሌላ በኩል በዓለማችን በዝነኝነታቸው የሚታወሱት የፈረንሳይ፣ የሜክሲኮ፣ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የኩባ አብዮቶች በሙሉ እና የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የተነሳሱት በገለልተኛ (ሴኩላር) ርዕዮተ-ዓለሞች ነው፡፡ ሆኖም ተሳክቷል (አንጻራዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር አምጥቷል) የሚባለው የአሜሪካ አብዮት ደግሞ በተቃራኒው በክርስትና እምነት እሴቶች የተነቃቃ ነው በማለት ሃይማኖት መር የሥርዐት ለውጥ የተሻለ አማራጭነቱን የሚሰብኩም አይታጡም፡፡ ነገር ግን መጠየቅ የሚገባን ‹ሃይማኖት ለአብዮት (ለሥርዐት ለውጥ) እንቅፋት የሚሆንበትስ ዕድል የለም ወይ!?› ብለን ነው፡፡

ሃይማኖት ለአብዮት እንቅፋት ይሆናል?

የተለያዩ ሃይማኖቶች ስለሥልጣን እና ሹመት የተለያየ አቋም አላቸው፡፡ በጥቅሉ ስናስበው ሃይማኖት ዓለምአቀፋዊ ሲሆን ፖለቲካዊ ሥልጣን ግን ሰዎች በፈጠሩት የጂኦግራፊ ካርታ ላይ የተመሠረተ ሰው ሰራሽ ሥልጣን ቢሆንም ቅዱስ መጽሐፎች ግን የራሳቸውን አቋም ማንፀባረቃቸው አልቀረም፡፡ ለምሳሌ የክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ወደሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 13፥1-2 እንዲህ ይላል፡-

ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምንት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ፣ በባለሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ፡፡

በእስልምና ሃይማኖት ቅዱስ መጽሐፍ - ቁርኣን ላይም ተቀራራቢ ነገር እናገኛለን፡-

እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ተገዙ፤ መልክተኛውንና ከናንተም የሥልጣን ባለቤቶችን ታዘዙ፤ በማንኛውም ነገር ብትከራከሩ በአላህና በመጨረሻው ቀን የምታምኑ ብትኾኑ (የተከራከራችሁበትን ነገር) ወደ አላህና ወደ መልክተኛው መልሱት፤ ይህ የተሻለ መጨረሻውም ያማረ ነው፡፡ (ቅዱስ ቁርኣን ምዕራፍ 4፤ አል-ኒሳእ፡፡ ክፍል 5፡፡ ቁጥር 59)

ከላይ እንዳየነው ክርስትና መንግሥት ላይ ማመፅን በፍፁም ቃል ይቃወማል፤ በሌላ በኩል በክርስትና ኢየሱስ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› ብሏል ብለው የመንግሥት እና ሃይማኖትን መነጣጠል የሚነግር ነው የሚሉም አይታጡም፡፡ ወደእስልምናም ስንመለከት ከባለሥልጣናት ጋር ካልተግባባችሁ ወደአላህና መልክተኛው መልሱት እንጂ ምድራዊ መፍትሄ ፈልጉለት አይልም፡፡ እርግጥ ነው በእስልምናውም ባለሥልጣን የሚለው ቃል የሚወክለው የቤተ ሃይማኖቱን አባቶች እንጂ የመንግሥት ሹማምንትን አይደለም ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ በጥቅሉ ግን፣ እኔ በምረዳው እና ከቀደሙት አስተምህሮቶችም ማየት እንደሚቻለው… ሃይማኖተኞች ለመታዘዝ ቅድሚያ እንዲሰጥ እንደሚወተውቱ ነው፡፡ ችግሩ በጥቅሉ ‹‹መታዘዝ›› የሚለው ቃል ሕዝብን ለሚበድል ባለሥልጣናትም ቢሆን ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል የተለየ ሐሳብ አላስቀመጡልንም፡፡  

እነዚህን የሃይማኖት ኃይለ ቃሎች የሚረ’ዱ መንግሥታትም ሃይማኖትን መጠቀሚያ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሕገ መንግሥት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ያልሆነች ሚስት ያገባ ሰው መንገስ እንደማይችል ቃል በቃል ይጠቅስ ነበር፡፡ ንግሥናውም ከእግዚአብሔር የተገኘ እንደሆነ ከላይ የጠቆምነው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በሚመስል ሐረግ ያስረዳል፡፡

መንግሥታት ሃይማኖትን በተለያዩ መንገዶች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በርካታ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ Jeff Haynes የተባሉ ተመራማሪ Religion in Third World Politics በሚለው ጥናታቸው ሃይማኖት በሦስተኛው ዓለም መንግሥታት እንዴት መጠቀሚያ ሊሆን እንደቻለ ሲጠቁሙ ሥርዐት ለማስቀጠያነት (Regime continuity)፣ ሕዝብ ትዕዛዝ እንዲቀበል ለማሳመኛነት (Public order maintenance)፣ ሥልጣንን ተቋማዊነት ለማላበስ (Institutionalization of authority) እና ለዜግነት እንደቅድመሁኔታ በማስቀመጥም (Promotion of citizenship) ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በዚህ ዘመን አምባገነን መንግሥታት ሃይማኖት እንደመጠቀሚያ የሚሆነው በከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ ነው፡፡ አንደኛው ሃይማኖት ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው እና ለሁለቱም ግን እንደዋስትና መንግሥትን በማስቀመጥ እንዳይተባበሩ እና መንግሥት ላይ እንዳይነሱ ማድረግ እየተለመደ የመጣ ዘዴ ሆኗል፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ታዲያ፡-

ሃይማኖተኞች በመንግሥት ላይ ያብያሉ?

ከሃይማኖቶች ዶግማ በመነሳት ሃይማኖተኞች የሚያብዩት ሃይማኖታቸው የተጠቃ ሲመስላቸው እንጂ እነርሱ እንደሕዝብ የተጨቆኑ ሲመስላቸው አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሃይማኖትን ከለላ ለማድረግ የሞከሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በአብዮት መውረድ እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ በንጉሡ ሥርዐት ላይ ለተነሳው አብዮት አንዱ መነሾ የሃይማኖቶች መገለል ነው፡፡ ለምሳሌ “በኢቫንጀሊካል ክርስቲያኖች አመለካከት በንጉሡ ዘመን [ቤተክርስትየናቸው] ሲደርስባት የነበረው እንግልት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን እጅ አለበት ብለው ማሰባቸው ጽናታቸውን እንዳበረታው እና ሥርዐቱን ለመጣል በሚደረገው ትግል ውስጥም አማራጭ ፍለጋ ተሳትፎ እንዳደረጉ” Revolution and Religion in Ethiopia በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ Øyvind M. Eide የተባሉ ተመራማሪ አትተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዶናልድ ስሚዝ Religion, Politics, and Social Change in the Third World ቅኝ ተገዢዎች ሃይማኖትን በመጠቀም አብየው (አብዮት አቀጣጥለው) ነጻ የወጡባቸውን አራት መንገዶች ይዘረዝራሉ፡-
1.   ሃይማኖት በራሱ የአመራር ዕድል/ተቀባይነት ያጎናፅፋል (ማሕተመ ጋንዲ ስማቸው በሒንዱ እምነት ‹‹ታላቅ ነፍስ›› የሚልና ከቤተ እምነቱ የተገኘ በመሆኑ በአብዛኛው አማኝ ተቀባይነት አስገኝቶላቸዋል፤)
2.   ሃይማኖት ለውጥ ፈላጊዎች እርስ በእርስ የሚተሳሰሩበት ምክንያት በመስጠት ለታጋዮቹ (ወይም ለውጥ ጠያቂዎቹ) የስሜት ጥንካሬን ያጎናጽፋል፣
3.   ሃይማኖት ለትግሉ ወይም ተቃውሞው ጥንካሬ የሚሆን መሠረት ይጥላል፣ (በእስልምና ቃፊሮች (ያልታመኑ ገዢዎች) ላይ የሚደረግ ጅሃድ (ቅዱስ ጦርነት) ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡)
4.   ሃይማኖት የመቃወሚያ መንገድ ይሰጣል (ለምሳሌ ጋንዲ ‹satyagraha› የተሰኘውን የአመጽ አልባ ሰላማዊ ትግል ፅንሰ ሐሳብ ያገኙት ከሒንዱ እምነታቸው ነበር፡፡)

ከዚህ በተጨማሪም አብዛኛዎቹ ሃይማኖቶች ነጻነት እና እከሉልነትን እንደመርሕ የሚመለከቱ መሆናቸው በፖለቲካዊ ሥርዐቶች ላይ በቀጥታ ባያምፁም እንኳን የሥርዐቱን ድርጊቶች በማውገዝ ሃይማኖታዊ አብዮተኞች ከቤተ እምነታቸው ስለሚታገሉለት ለውጥ የማጠናከሪያ ሐሳብ ማግኘት ይችላሉ፡፡ በዚህ መንገድ ነው የላቲን አሜሪካ አብዮት በክርስትና እና የግብፁ (የ1952/እ.ኤ.አ.) አብዮት በሙስሊም ወንድማማቾች ድጋፍ እና ሃይማኖታዊ እሳቤ ተነሳስተው ለለውጥ የበቁት፡፡

እነዚህ የታሪክ ዳራዎች ላይ በመመርኮዝ አሁን የሚታየው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን እና ‹‹የመጅሊሳቸው›› ውዝግብን ተከትሎ  ጥያቄ ጥያቄን እየወለደ ቤተ እምነታዊው ጥያቄ ወደፖለቲካዊ እና ሥርዐታዊ ለውጥ ጥያቄ ያድግ ይሆን፣ ካደገስ ያዋጣ ይሆን የሚሉት ጥያቄዎች ኢትዮጵያውያንን እያወያዩ ነው፡፡

የሙስሊሞች ጥያቄ ወደአብዮት ያመራ ይሆን?

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በታኅሳስ ወር/2004፣ በአወሊያ ትምህርት ቤት የጀመሩት ‹‹አል አሕባሽ›› የተሰኘ አስተምህሮት እየተጫነብን ነው ሮሮ - ቀጥሎም ‹መምህራኖቻችን አይባረሩ› እንቅስቃሴ… መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በመምረጥ፣ መጅሊሱ ይቀየርና ሕገ መንግሥቱ ይከበር እስከማለት ዘልቋል፡፡ ይሄው ጥያቄ የተመለሰበት መንገድ የመጅሊሱ አባላት በቀበሌ እንዲመረጡ ማድረግና ያንን የተቃወሙትን የኮሚቴ አባላት እና ሌሎችንም ማሰር እና በሽብርተኝነት መክሰስ ሲሆን… ይህ የመንግሥት እርምጃ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በማስቆጣት ተቃውሞዋቸውን በየሣምንቱ አርብ ከጸሎት በኋላ እየገለጹ ዓመት እንዲደፍኑ አድርጓቸዋል፡፡

በተቃራኒው በየከተማው እነዚህን ብሶተኞች የሚቃወሙ ሙስሊም ሰልፈኞችን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደጋግሞ አሳየ፡፡ ብዙዎች ሰልፈኞቹን መንግሥት ያስተባበራቸው እንደሆኑ መገመት አልቸገራቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰልፈኞች በሰልፉ ብዙም አልዘለቁበትም፤ በሌላ በኩል ከታሪክ እንደምንረዳው በደርግ ዘመን ‹‹የሃይማኖት መሪዎች የኢምፔሪያሊስቶችን አብዮት የሚያደናቅፍ ሴራ አወገዙ›› የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው እንደነበሩ ሁሉ አሁንም ‹‹የእንትን መስኪድ ኢማሞች ‹አንዳንድ› ድብቅ ሴራ አጀንዳቸውን በሙስሊሙ ዘንድ ለማራመድ የሚፈልጉ … አወገዙ፡፡›› የሚለውን ዜና ከፕሮፓጋንዳ ለይቶ ማይት ስለማይቻል ነው፡፡

መንግሥት የሙስሊሞቹን ጥያቄ በአጭሩ መልስ የማይሰጠው እንደሚናገረው ‹‹አክራሪነትን›› ለመከላከል ብቻ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ይልቁንም የመንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንም የውስጥ ለውስጥ አጀንዳ በመሆኑ (‹‹የቀድሞውን ጳጳስ የሕወሓት አባል/ደጋፊ ናቸው›› እስከማለት ድረስ) የሙስሊሞቹን ጥያቄ መመለስ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችንና ምናልባትም ሌሎችንም ፊት እንደመስጠት ይሆንብኛል ብሎ ሳይጠረጥር አይቀርም፡፡

የሆነ ሆኖ ምንም እንኳን መንግሥት የሃይማኖተኞችን ጥያቄዎች በጉልበት ቢደፈጥጥም (‹‹ምርጫውን በቀበሌ በማካሄድ››) ወይም የየሳምንቱን ጥያቄ እንዳልሰማ በማለፍ ‹‹ሰልችቷቸው እንዲተዉት›› ለማድረግ ቢሞክርም፤ እስካሁን ከተለመከትነው መገመት እንደምንችለው… እነዚህ ሰዎች ስትራቴጂያቸውን እየቀያየሩ ያላቸውን ሁሉ አማራጭ ወደመጠቀም አያመሩም ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡

በቅርቡ እንኳን ያሳዩት የቢጫ ካርድ ተቃውሞ ከእግርኳስ ጨዋታ ሕግ የተወረሰ ሲሆን እንደማስጠንቀቂያ ታይቷል፡፡ ቀጣዩ ቀይ (የማሰናበቻ) ካርድ እንደሚሆን ቢገመትም መቼ እና እንዴት ለሚለው ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ሙስሊሞቹ የቀይ ካርድ እርምጃቸውን ከጀመሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከመስኪድና ከጸሎት ስብሰባ ውጪ ሊጠሩ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ እርምጃ (ከመንግሥት ተገማች ምላሽ ጋር ተደማምሮ) አገሪቱን ወደአብዮት ሊመራት ይችላል ብሎ መጠርጠር ከባድ አይመስለኝም፡፡

ነገር ግን እንደምናስበው ይህ ዓይነቱ አብዮት በሒደቱም ሆነ በውጤቱ ቀላል አይሆንም፡፡ የሙስሊሞቹ አደባባይ መውጣት ጥያቄያቸውን ከሃይማኖታዊው ይልቅ ፖለቲካዊው ትርጉሙ ስለሚያመዝን (የመንግሥት አይቀሬ ሥልጣን ፈልገው ነው ፕሮፓጋንዳ ታክሎበት) ሙስሊም ላልሆነው የኅብረተሰብ አካል የጥርጣሬ መንፈስ ሊፈጥር እና አንዱ በሌላው ላይ የመቃወም አቋም ሊያስይዝና ለፖለቲካውም ለማኅበረሰቡም የማይበጅ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡

እንደመደምደሚያ

ሃይማኖቶች ለአብዮት የሚያበረክቱት እና ማበርከት የሚችሉት ሚና አሌ የሚባል ባይሆንም፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አብዮታዊ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ከታሰበ የአገሪቱን ብዝኃ ሃይማኖትነት ማገናዘብ የሚችል ገለልተኛ/ሴኩላር ለውጥ ቢመጣ እመርጣለሁ፡፡ የሃይማኖተኞች ወይም ሃይማኖትን ግብ ያደረጉ አብዮተኞች ሚናም ሃይማታዊ/አምልኮአዊ ጣልቃ ገብነት ከመቃወም ወይም የማምለክ/አለማምለክ ነጻነትን (ማለትም በጠቅላላው ሥርዐት ውስጥ የእምነት ነጻነት ሥርዐቱን ለይቶ /ምን ያህል ነጥሎ ማየት ይቻላል የሚለውን ለውይይት በመተው/ ለማስተካከል) ከመሻት በላይ የተሻገረ መሆን የለበትም፡፡ በጥቅሉ ግን ሃይማኖተኞች እንደዜግነታቸው የሥርዐት ለውጥን መሻት ብቻ ሳይሆን የለውጡ ዋነኛ ተዋናይ የመሆን መብቱም ግዴታውም አለባቸው፡፡
------
ማስታወሻ፡-
ይህ ጽሑፍ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል የሚቀርቡት ተከታታይ ጽሑፎች አካል ነው፤
-----
ተጓዳኝ ጽሑፎች፤
-----
የዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡