Sunday, February 7, 2016

እከላከላለሁ!


በበፍቃዱ ኃይሉ

ከ18 ወራት እስር በኋላ ስንፈታ ዐ/ሕግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ በሁለት “ምክንያቶች” በወንጀል ሕጉ (አንቀጽ 257/ሀ) ግዙፍ ያልሆነ “በጽሑፍ ለአመፅ የማነሳሳት” ጥፋት ተከላክዬ ነጻ መሆኔን የማረጋገጥ ሸክሙን ወደ እኔ አዙሮታል፡፡ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው፤

፩) “የግብጽ ዓይነት አብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲነሳ የሚቀሰቅስ ጽሑፍ መጻፉን ለፖሊስ በሰጠው ቃል …‹የእውነት ቃል መስጠቱን› አምኗል” የሚልና፣

፪) ዐ/ሕግ ባቀረባቸው ሰነዶች “በፌዴራሉ ሕገ-መንግሥት የተቋቋመውን ስርዓት ለማፍረስ በጽሑፍ አማካኝነት የቀሰቀሰ ለመሆኑ የተጠቀሱት ማስረጃዎች የሚያስረዱ በመሆኑ” የሚል ናቸው፡፡

የእምነት ወይስ የእውነት ቃል?

ሳይቤሪያ (የማዕከላዊ ጨለማ እስር ቤት) ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ለምርመራ ወጥቶ ሲመለስ ክፍሉ ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች በሙሉ የሚጠይቁት የመጀመሪያው ጥያቄ “አመንክ?” የሚል ነው፡፡ ታሳሪዎቹ ስለምርመራው የሚያውቁት ነገር ስላለ አይደለም ይህንን ጥያቄ የሚጠይቁት፡፡ ነገር ግን የማዕከላዊ ምርመራ በተፈጥሮው፣ በተለይ በሽብር ለተጠረጠረ ሰው “አንዳች ወንጀል እመን” በሚል ስለሆነ ነው፡፡ ሒደቱም፣ በዱላ ነው፡፡ ማዕከላዊ ቆይተው ክስ የተመሰረተባቸው ብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ፍርድቤት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ “ተከላከሉ” የሚባሉት ለፖሊስ የሰጡት የእምነት ቃል ነው፡፡ ፖሊስ በሥነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 27 መሠረት የተጠርጣሪ ቃል የሚቀበልበትን ሰነድ ሲያስፈርም “… ይህንን በነጻ የሰጠሁትን የእምነት ቃሌን አንብቤ ወይም ተነቦልኝ ፈረምኩ” የሚል ዓ/ነገር ከግርጌው ይጨምርበታል፡፡

ማዕከላዊ ውስጥ የተከሳሽን ቃል በነጻ አእምሮው በፈቃደኝነቱ እንዲሰጥ ማድረግ ነውር ነው፡፡ አንድ ሰው ማዕከላዊ ውስጥ ሲመረመር፣ ክብሩ በስድብ ተዋርዶ፣ እየተደበደበ ነው፡፡ የሥነ ስርዓት ሕጉ አንቀጽ 27/2 ‹ማንኛውም ተጠርጣሪ ለፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ በነጻ ፈቃዱ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት፤ ቃል ያለመስጠት መብቱም የተጠበቀ እንደሆነ› ይደነግጋል፡፡ ይህን ግን የማዕከላዊ ፖሊሶች የሚያውቁት አይመስልም፡፡



እኔ ላይ የደረሰው ብቻ ሕግ ለይስሙላ የሚወጣባት እንጂ በሕግ አስከባሪው አካል እንኳን የማይከበርባት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምንኖር ያሳያል፡፡ ማዕከላዊ ውስጥ ቃሌን ለፖሊስ ስሰጥ እንኳን እንደዕቅድ ይዤ ልንቀሳቀስባቸው፣ በመርሕ ደረጃ እንኳን የምቃወማቸውን ነገሮች “አዎ፣ ላደርግ አስቤ ነበር (ማለትም ‹አመፅ ላነሳሳ ጽፌያለሁ›)” ብዬ መርማሪ ፖሊሶች ሲያሻቸው እኔ የተናገርኩትን ወንጀል ሊሆን በሚችልበት መንገድ እየጠመዘዙ፣ ሲያሻቸው ደግሞ ጭራሹኑ እኔ ያላልኩትን ፈጥረው እየጻፉ ያመጡትን የእምነት ቃል አስፈረምውኛል፡፡ ሲደበድቡኝ የከረሙት ሕሊናቸውን በወር ደሞዝ የሸጡ መርማሪዎቼ ያለምንም የሕሊና ወቀሳ የእኔ ቃል ከተባለው ከራሳቸው ቃል ግርጌ “የእውነት ቃሌ ነው” ብለው ጽፈውበታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምንም እንኳን በማዕከላዊ የተጠርጣሪ ቃል በነጻ እንደማይገኝ ከበቂ በላይ በብዙ ተከሳሾችን ጉዳይ በመመልከቱ የሚረዳ ቢሆንም፣ መረዳት ስላልፈለገ “አምኗል” ብሎኛል፡፡ እርግጥ ነው አምኛለሁ፤ በኃይል ፊት ጀግና መሆን ስላልቻልኩ ያላሰብኩ፣ ያላደረግኩትን አምኛለሁ፡፡ እምነቴ ግን እውነቴ አልነበረም፡፡ ወትሮም እኔ የኃይል ትግል ውስጥ አይደለሁምና ኋላም ሆነ ወደፊት በኃይል ፊት የመጀገን ጀብደኛ ሕልም የለኝም፡፡ እስከአቅሜ ጠብታ ድረስ ለፍትሐዊነት የምታገለው ስመታ እየወደቅኩ ነው፤ እረፍት ሳገኝ እየተነሳሁ!

ፍ/ቤቱም ይሁን ከሳሼ መንግሥት ግን መከላከል ሳያስፈልገኝ ቃሉ የኔ አለመሆኑን ሊረዱ የሚችሉባቸው በርካታ ዕድሎች ነበሯቸው፡፡ ጥቂቶቹን ቀጥሎ እንመለከታለን፣

፩) ቃሌን በነጻ ሰጥቼ ቢሆን ኖሮ ፍርድ ቤት ስቀርብ ‹በነጻ ፈቃዴ አልሰጠሁም› ብዬ አልክድም ነበር፣

፪) ቃሌን የሰጠሁበት ሁኔታ፣

ሀ) ጠበቃ እና ቤተሰብ ማግኘት ተከልክዬ ነበር፤
(የግንቦት 3/2006 ሪፖርተር ጋዜጣ እትም “ጠበቆች የታሰሩ ጋዜጠኞችንና ጦማርያንን የማያገኙ ከሆነ ጥብቅና አንቆምም አሉ” የሚል ዜና ይመልከቱ!)

ለ) እየተደበደብኩ ነበር፤
(ይህንንም ሚያዝያ 30/2006 ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀጠሮ ጊዜ ለመጠየቅ አራዳ የመ/ደ/ፍ/ቤት ሲያቀርበኝ ለችሎቱ የገለጽኩ ሲሆን፣ ይህም በተለያዩ ጋዜጦች ተዘግቧል፡፡ በተጨማሪም ፍ/ቤቱም አቤቱታዬን መዝግቦት ይገኛል፡፡)

ሐ) መርማሪዎች እኔ ያላልኳቸውን ጽፈዋል፤
(ይህንንም ሰኔ 22/2006 ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀጠሮ ጊዜ ለመጠየቅ አራዳ የመ/ደ/ፍ/ቤት ሲያቀርበኝ ለችሎቱ ተናግሬያለሁ፡፡ መናገሬንም፣ ሰኔ 25/2006 የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦታል፡፡)
፫) ቃሉ የኔ አለመሆኑን ወይም በመርማሪዎቹ የተጻፈ መሆኑን የሚያስረዱ ሁኔታዎች፣
ሀ) አንድ ተጠርጣሪ ራሱን በማይገልጽበት ሁኔታ ራሴን እንደወነጀልኩ አስመስሎ ማቅረቡ፤ (ለምሳሌ “አመፅ ለማነሳሳት፣… ሁከት ለማነሳሳት…” የሚሉ ቃላት፤ በተጨማሪም “ከ150 እስከ 200 ያሉ ርዕሶችን በመጻፍ ሕዝብን ቀስቅሰናል” (ገጽ 22) የሚሉ ዓ/ነገሮች፤ ብሎም ዞን ዘጠኝን “ሕቡዕ ቡድናችን” (ገጽ 28) እያሉ መጥራት፡፡)

ለ) የቃሉ ይዘት እርስበርስ የሚጋጭ መሆኑ፤ (ለምሳሌ ገጽ 8 ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥቱ በጽሑፍ እንጂ በተግባር አልተተረጎመም” እንዳልኩ ተጽፎ፣ ገጽ 29 ላይ ደግሞ “ሕገ-መንግሥቱ ይከበር ማለቴ ስህተት ነው” እንዳልኩ እርስበርሱ በሚጋጭ መልኩ ተጽፏል፡፡)

ጽሑፎቹ አመፅ ይቀሰቅሳሉ?

በሁለተኝነት ዐ/ሕግ ማስረጃ ብሎ ያያዛቸው ጽሑፎች ለፖሊስ የሰጠሁትን የእምነት ቃል የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል፡፡ እውን ይቀሰቅሳሉ? ጽሑፎቼንስ አንብቦ ለአመፅ የተነሳሳ ሰው ወይም ቡድን አለ? (ለፍርዳችሁ የጽሑፎቹን ሊንክ ከጥቂት ማብራሪያ ጋር አስቀምጬላችኋለሁ፡፡)

በብይኑ ላይ አመፅ እንደምቀሰቅስ ያስረዳሉ ተብለው ከተዘረዘሩት ጽሑፎች መካከል አምስቱ ከርዕሳቸው በስተቀር ዝርዝራቸው አልተያያዘም፡፡ በመጀመሪያ እነርሱን እንመልከት፤ ጽሑፎቹ በጥቅሉ ለውጥ ፈላጊ ዜጋ ከመሆኔ በቀር የሚያስተላልፉት የአመፅ ጥሪ የለም፡፡

(ይህ ጽሑፍ ኢሕአዴግ በምርጫ ሥልጣኑን እንዳይለቅ የሚገዳደሩት ውስጣዊ ችግሮችን የሚተነትን ጽሑፍ ሲሆን፣ የሠላምና ዕርቅ ድርድርን በመፍትሔነት የሚጠቁም ጽሑፍ ነው፡፡ ጽሑፉ እንኳን አመፅ ሊቀሰቅስ የመጨረሻው ዓ/ነገር የሚያወራው ስለሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነው፤ እንዲህ ይነበባል፣ “ […] ኢትዮጵያ በታሪኳ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማየት ትችል ይሆናል፡፡”)

(ይህ ጽሑፍ ለውጥን መቋቋም ሰዋዊ ባሕሪ መሆኑን የሚያትት እና የለውጥ ፍርሐት እና መቋቋምን ለመቅረፍ ነባሩን ስርዓት ከአዲሱ ጎን ለጎን የማስኬድን አስፈላጊነት የሚያስረዳ ነው፡፡)

(ይህ ጽሑፍ ለውጥ በፖለቲካዊ አብዮት ብቻ እንደማይመጣ፤ እንዲያውም አብዮት ለአንዳንዶች መጠቀሚያነት ሊውል እንደሚችል፣ ብሎም ዴሞክራሲ የሚገነባው “የክፍል አለቃ፣ የት/ቤት ዳይሬክተር፣ የቢሮ አለቃ፣ የዕድር ሊቀመንበር፣ የማኅበር ሙሴ የመሳሰሉት…” በሹመት፣ በሞገስ ሲሰየሙ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መመረጥ ሲጀምሩ ነው የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡)

(የጽሑፉ ይዘት ከዚህ ቀደም ማኅበራት ለስርዓት ለውጥ መልካም ሚና ነበራቸው አሁን ግን ነጻ እና ጠንካራ ማኅበራት የሉም የሚል ነው፡፡ የመዝጊያ አንቀጹ እንዲህ ይነበባል “…አሁንም ማኅበራት አሉ፤ ማኅበራቱ ግን እንኳን የስርዓት መሻሻልና ለውጥ ሊጠይቁ ቀርቶ ቢሳሳትም ባይሳሳትም መንግሥትን ከመደገፍ በቀር የተለየ ተግባር የላቸውም፡፡”)

(ይህ ጽሑፍ የሃይማኖቶች (የእምነቶች ነጻነት) መጨቆን ለስርዓት ነውጥ የሚዳርግ ስለሆነ መንግሥት ከእንዲህ ዓይነቱ ተግባር እንዲቆጠብ የሚያስጠነቅቅ ይዘት አለው፡፡)

ከነዚህ በተጨማሪ ዐ/ሕግ ክሱን ያስረዳልኛል ብሎ ያያዛቸው በሦስት የመደብኳቸው ጽሑፎች ይገኛሉ፡፡ አንድ፤ እኔ ጽፌያቸው የዞን ዘጠኝ ወይም የግል ብሎጌ ላይ የታተሙ፣ ሁለት፤ እኔ ጽፌያቸው ነገር ግን ያልታተሙ፣ እና ሦስት፤ እኔ ያልጻፍኳቸው ናቸው፡፡

ሀ) እኔ ጽፌያቸው የታተሙ

(ይህ ጽሑፍ ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ለፖለቲካ ጥቅሙ መገልገያ እያደረገው እንደሆነ የሚገልጽ ጽሑፍ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በፖሊሲ ደረጃ ከሕወሓት ይልቅ አረና ፓርቲ እንደሚሻለው የሚያስረዳ የግል አስተያየት ነው፡፡)

(ይህ ጽሑፍ የኢሕአዴግን ከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ የሚያጣጥልና በኅብረት ስለሰብኣዊ መብታችን እና ዕኩል የዜግነት መብታችን የመታገል ጥያቄ ያዘለ ነው፡፡)

(ይህ ጽሑፍ አምባገነኖች በላያችን ላይ የሚገንኑት እኛ ባለመተባበራችን መሆኑን የሚያስረዳ ይዘት ያለው ነው፡፡)

(ይህ ጽሑፍ በአነስተኛ የኢንተርኔት ላይ ሰርቬይ ላይ ተመሥርቶ የተጻፈ ጽሑፍ ነው፡፡ የሚያስተላልፈው መልዕክትም “ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ዴሞክራሲ የለም፣ አይመጣም የሚል አቋም ይዘዋል” ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ሊወስዷቸው ስለሚገቡ የመፍትሔ እርምጃዎች የሚዘረዝር ይዘት አለው፡፡ በመዝጊያውም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ባለማድረጋቸው ሀገሪቱ ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ ተጠያቂ ይሆናሉ” የሚል ነው፡፡)

(ይህ ጽሑፍ አንደኛ ‹ውርስ ትርጉም ነው› ሁለተኛ ጽሑፉ ላይ ቃል በቃል “መፈንቅለ መንግሥት ወይም አብዮት የማቀጣጠል ዓላማ የለኝም… ራሴን እንደፖለቲካዊ መሪም አልቆጥርም…” ብሎ በመቀጠል “ማንም ሰው የዜግነት ክብሩን ተገፍፎ እንዲጨቆን አልፈልግም፡፡ ይኸው ነው ምኞቴ፡፡” የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡)

(ይህ ጽሑፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ የገጠመው መሆኑን የሚያስረዱ ምልክቶች የተዘረዘሩበት ጽሑፍ ነው፡፡)

(ዞን ዘጠኝ ካደረጋቸው አራት የበይነመረብ ዘመቻዎች የሦስተኛው ጋዜጣዊ መግለጫ)

ለ) እኔ ጽፌው ያልታተመ

፩ኛ) “መሰለፍ እና መሰየፍ”
(ስለሠላማዊ ሰልፍ የሚያወራ ሆኖ አምባገነኖች ሠላማዊ ሰልፈኞችን በሰይፍ መቅጣት ያምራቸዋል የሚል ይዘት አለው፡፡)

ሐ) እኔ ያልጻፍኳቸው

፩ኛ) “ይድረስ ለወጣቱ…” የሚል ደብዳቤ
(ይህ ጽሑፍ የማን እንደሆነ የማላስታውሰው ነገር ግን በኢሜይል ተልኮልኝ፣ አውርጄ ካነበብኩት በኋላ የረሳሁት ደብዳቤ ነው፡፡ ደብዳቤው ሠላማዊ የለውጥ ትግልን የሚሰብክ ነው፡፡ በምክር መልክም፣ “…መብታችሁን ጠይቁ፡፡ ንጠቁ አላልኩም ጠይቁ፡፡” ይላል፡፡

፪ኛ) “መንግሥት የለም ወይ የምንና ምን ዓይነት መንግሥት?”
(ይህ ጽሑፍ የሙስሊሞችን ጉዳይ የሚተነትን በመስፍን ነጋሽ የተጻፈ ጽሑፍ ነው፡፡)

(ይህ ጽሑፍ በማንነት ጥያቄ ላይ በፖለቲካ ባለሙያ የተሰጠ ትንታኔ ላይ የሚያተኩር አሁን በእስር ላይ በሚገኘው አብርሃ ደስታ የተጻፈ ጽሑፍ ነው፡፡)

እኔ የጻፍኳቸውም ይሁኑ፣ ያልጻፍኳቸው (እነዚህ 16 ጽሑፎች) ምንም ዓይነት አመፅ የመቀስቀስ አዝማሚያም ይሁን ፍላጎት የሌላቸው ናቸው፡፡ በአገራችን የተጓደለ ስርዓት ሳይሆን፣ በጠቅላላው የሕግ የበላይነት ላይ ያለኝን እምነት ለማሳየት ስል እስከጥግ ድረስ ስለነጻነቴ የሰውም፣ የሰነድም ማስረጃ እየደረደርኩ ከነገ ጀምሮ እከላከላለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment