Wednesday, December 5, 2012

“ሕገ-መንግሥቱ ይከበር” - የበይነመረብ ዘመቻ (ጋዜጣዊ መግለጫ!)


ዞን 9 ኢ-መደበኛ የጦማርያን እና አራማጆች ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ማኅበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተለየ እና ወገናዊ ያልሆነ ተረክ ለመፍጠር እየሠራ የሚገኝ የኢትዮጵያዊያን ስብስብ ነው፡፡ የቡድኑ ዓላማ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገሪቷ ጉዳይ በእኩል ስሜት ያገባኛል ብለው ውይይት የማድረግ ባሕል እንዲያሳድጉ በማድረግ ሀገሪቷን በሁሉም መስኮች ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ ሐሳቦች እንዲወለዱ ማመቻቸት ነው፡፡

ይህንንም ዓላማ ከግብ ለማድረስ የተለያዩ የበይነ-መረብ ዘመቻዎች ለማካኼድ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከዘመቻዎቹም መካከል የመጀመሪያው ‹‹ሕገ-መንግሥቱ ይከበር›› በሚል መርኽ ከኅዳር 27 – 29 ቀን 2005 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
ኅዳር 29 ቀን 2005ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ከተፈረመ 18 ዓመት ይሆነዋል፡፡ በ1987 ዓ.ም ወደሕልውና የመጣው ሕገ-መንግሥት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ አራተኛው ነው፡፡ ይኸው ሕገ-መንግሥት ከሚቀድሙት ሕገ-መንግሥቶች በተሻለ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ያደረገና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች የተሻለ ትኩረት የሰጠ እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ሆኖም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶች እና የመልካም አስተዳደር መርኾዎች በተደጋጋሚ ሲጣሱ ይስተዋላል፡፡
በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ከተካተቱት ድንጋጌዎች ጥቂቶቹ አሁንም ድረስ አከራካሪ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ድንጋጌዎች ግን የጋራ መግባባት የተደረሰባቸው ናቸው፡፡ የዚህ ዘመቻ ዓላማ በዋነኝነት የሚሆነውም እነዚህን የጋራ መግባቢያ ላይ የተደረሰባቸውን የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ማስተዋወቅ እና የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ-መንግሥት ሁሉም የመንግሥት አካላት እና ዜጎች እንዲያከብሩ እና አንዲያስከብሩ መጠየቅ ነው፡፡
ዘመቻው በዋነኛነት የሚካሄደው ‹‹ፌስቡክ›› እና ‹‹ትዊተርን›› በመጠቀም ይሆናል፡፡ ሕገ-መንግሥትን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎች በጦማራችን የሚወጡ ሲሆን በፌስቡክ እና በትዊተርም ላይ ይወጣሉ፡፡ (ለዚህም ‘#RespectTheConstitution’ን ጨምሮ ሌሎችንም የትዊተር ‹ታግ› እንጠቀማለን፤) በሁለቱም የማኅበረሰብ ገጾች ላይ ለዚሁ ዘመቻ ሲባል የተዘጋጁ አጫጭር ጽሑፎች ይሰራጫሉ፡፡ ዘመቻውን የሚመለከቱ ‹ባነሮች› ተዘጋጅተው ዘመቻው በሚቆይባቸው ቀናት የፕሮፋይል ፎቶ ይሆናሉ፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ለመላው የዞን9 ነዋሪዎች እና ሕገ-መንግሥቱ ተከብሮ ማየት ለምትፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ያላችሁን አመለካከት፣ ሕገ-መንግሥቱ የተጣሰባቸውን ክስተቶች በማካፈል እንዲሁም የፕሮፋይል ፎቷችሁን በመቀየር የዘመቻው ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑ በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ስለሚያገባን እንጦምራለን!!!
ናትናኤል ፈለቀ፤ የዘመቻው አስተባባሪ - “ሕገ-መንግሥቱ ይከበር!”

No comments:

Post a Comment