Wednesday, December 12, 2012

ዘመቻ ገለአድ



በታምራት ተስፋዬ

ሰከንዶች ደቂቃን፣ ደቂቃ ሰዓትን፣ ሰዓት ቀናትን እየፈጠሩ ይኸው ዛሬ ላይ ደረስን፡፡ 

ዛሬ ትላንት አይደለም፤ ትላንት የዓለምን ሁኔታ  ለመተንበይ የነቢይነትን  ሚና  መጫወት አይጠበቅብንም ነበር፡፡  ትላንት የዓለም  ሁኔታ  በአዝጋሚ   ለውጥ ውስጥ   ከመሆኑም በላይ  ዓለም ለስር ነቀል ለውጥ የተጋለጠች  አልነበረም፡፡ ዛሬ  ሁሉ  ነገር ከመለወጡ የተነሳ ነገን  ለመተንበይ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ   ተደርሷል፡፡ የማትጨበጠውን ዓለም ለመረዳት ሀገራችን ባለፉት  ሦስት  ወራት ያሳለፈውን ሁኔታ  ማሰብ ብቻ   በቂ ነው፡፡  ለዛሬም የሰሞኑ  ዓቢይ  ክስተት  የሆነውን ፖለቲካዊ ለውጥ  እስኪ ትንሽ    አብረን እንየው፡፡

በነገራችን  ላይ  ገለአድ ማለት በመጽሐፍ  ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ  የተራራ ስም ሲሆን  ጌዴዮን ደፋር እና ፈሪ  ወታደሩን የለየበት ቦታ ነው፡፡  እንደሚታወቀው  ጠቅላይ ሚኒስትር  ኃይለማርያም  ከሰሞኑ  ኳታር ደሃ ላይ  ሰንብተው  ተመልሰዋል፡፡  ከዓመታቶች  በፊት ኳታር  ከኤርትራ ጋር  ባላት ቅጥ ያጣ ግንኙነትና  ተዛማጅ  ጉዳዮች ጋር  ተያይዞ   ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ   ግንኙነቷን   ከማቋረጧም በላይ የጐሪጥ መተያየት  ደረጃ  ላይ  ደርሰው እንደነበር የቅርብ ጊዜ  ትዝታ  ነው፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትራችን   ከሦስት  ወር በፊት  ራዕይ ስለማስቀጠል   እና   ራዕይ   ስላለመበረዝ   አበክረው ሲገልጹልን  የነበረ ቢሆንም  ቃላቸውን   ጠብቀው  ለመዝለቅ   ሦስት ወር  እንኳ   ሳይሞላ  መንታ መንገድ ላይ የቆሙ   ይመስላል፡፡   የኳታሩ  ጉዞ  ምን ዓይነት ፖለቲካዉ ተግዳሮት አለው?  እውን  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የገለአድን ተራራ መውጣት  ጀምረው ይሆን? ከጉዞው  በስተጀርባ ሀገራችን ምን ትጠ ብቃለች? እስኪ  ትንሽ   እንየው፡-

ራዕይ  በማስቀጠልና በመበረዝ መሐል

መበረዝና መደለዝ የሚሉ ቃላቶች እንደዛሬው  የካድሬ መዝገበ ቃላቶች  ውስጥ ከመግባታቸው  በፊት  ከጠጅና  ከፈተና ወረቀት ያለፈ  ጥቅም ላይ ለመዋል ዕድል አላገኙም ነበር፡፡ ሟች ጠቅላይ ሚኒስትርን መለስ ተከትሎ  ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹የመለስን ራዕይ ሳይበረዝና ሳይደለዝ እናስፈጽማለን› ካሉ በኋላ  እስከ ታችኛው የእዝ ሰንሰለት ድረስ ዓረፍተ ነገሩን  በየቦታው መናገር  ፋሸን  ከመሆኑም የተነሳ እነዚህን ቃላቶች  ሳያስገቡ አራት ነጥብ ላይ መድረስ እንዳልተቻለ በግልፅ እየታየ ይገኛል፡፡  መለስ የኤርትራ  ተቃዋሚዎችን በማደራጀት ሻእቢያን ለማጥፋት ሲሞክሩ እንጂ በኳታር ትከሻ  ላይ  ከሻእቢያ ጋር የመደራደር ራዕይ እንደነበራቸው   ለመመስከር ምስክር ማስቆጠር አይጠበቅብኝም፡፡ እንግዲህ  እዚያ ጋር አንደጥፋት ሊቆጠር ይችል የነበረው  በነበረው ራእይ እቀጥላለሁ የሚል አስተሳሰብ  ቢኖር  ይመስለኛል፡፡ ዓለም  በፈጣን የለውጥ  ሂደት ውስጥ  ሆና   በትላንት ራዕይ  ዛሬን  አልፋለሁ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ በዚህ  ወቅት  እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ወ/ሮ አዜብም ከራእይ  በራዦች መሐል አንዷ  ቢሆኑ አይገርመኝም፡፡  ዓለምአቀፋዊ ፖለቲካ  ለመተንበይ  የማይቻለበት ሁኔታ ላይ ተደርሰዋል፡፡ ይመስለኛል የላይኛው  አመራር  በቀድሞ  አመራር  ዝግ  የነበሩትን  አንዳንድ ሁኔታዎች  ለማስተካከል እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡  ከነዚህም ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዶሀ  ጉዞ  አንዱ ሊሆን ይችላል፤  የገባው መበረዝና  መሰረዝ ያለበትን ሲሰርዝና ሲበርዝ በሽምደዳ ዕውቀት ላየ የታነፀው የወረዳና የቀበሌ ካድሬ ራዕይ  ስላለመሰረዝና ስላለመደለዝ ይዶሰኩራል ምክንያቱም ይህ ፖለቲካ ነው፡፡ 

ዶሀ ምን ተገኘ?

ጠቅላይ ሚኒስትር  ወደ ኳታር የሁለትዮሽ  ግንኙነቱን በንግድ፣  በኢኮኖሚና  በማኅበራዋ ዘርፎች ለመነጋገር  ከኳታር ባለሥልጣኖች ጋር  ተገናኝተው ተወያዩ የምትለው ዜና ኢቲቪ  ሳጥን ውስጥ  ትቀመጥልንና አንኳር ጉዳይ የሆነው የኤርትራ ጉዳይ  ላይ  መወያየት ይሻላል፡፡ አሁን  ባለንበት ጊዜ  በኢትዮጵያና  በኤርትራ መሐል  ማንኛውንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማድረግ  ከኳታር የተሻለ አማራጭ ገበያው ላይ ማግኘት   አይቻልም፡፡   እንደሚታወቀው ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት በኋላ  ኢትዮጵያ   የማሊያ  ላውጥ  በማድረግ በሯን ለድርድር የከፈተች ይመስላል፡፡  ይህን ሐሳቤን ከሚያጠናክሩልኝ አንዱ በመለስ ጊዜ  በኮብራ  ሀዋሳና  ባሕር ዳር  ሲምነሽንሹ  የነበሩት  ኢትዮጵየ ውስጥ  የሚገኙት  የኤርትራ ተቃዋሚዎች  በአሁን ወቅት ችላ  ከመባላቸውም በላይ ባሕር ዳር ላይ ለተቃዋሚዎቹ  ፕሮፓጋንዳ ይረዳ ዘንድ ሊቋቋም ታስቦ የነበረው የሬዲዮ ጣቢያ  ግንባታ ለጊዜው ቆሟል፡፡ ይህም  ኢትዮጵያ  በኳታር  አማላጅነት ከኤርትራ  ጋር  ሰላም ለማውረድ መፈለጓን ያሳብቅባታል፡፡

ኤርትራ ምን አለ?

ከዐሥራ አምስት ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ጎትጓችነት ለማድረግ የታሰበው ስምምነት ሦስት ነገሮችን ታስቦ የተገባበት ይመስለኛል፡፡

ሀ/ ዘላቂ ሰላም

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከሦስት ዓመት ደም አፍሳሽ ጦርነት በኋላ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም በስተመጨረሻ ባደረጉት የገላጋይ ፍርድ ቤት ክርክር የጦርነቱ መንስኤ የሆኑት ውስጥ ዋነኛዋ የባድመ ቦታ ለኤርትራ በፍርድ ቤቱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ሆኖም መዘዙ ብዙ ዋጋ ስለሚያስከፍል እስከ ዛሬ ድረስ በቦታው ላይ ሰላም ሳይወርድ ቆይቷል፤ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን ኢትዮጵያ የፍርድ ቤቱን ስምምነት ለመቀበል የተዘጋጀች የሚመስል መልእክት ከመንግስት ኮምኒኬሽን ኃላፊ ከሆኑት  ከአቶ በረከት ስምኦን ሰምተናል፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ለኤርትራ ሬድዮ የፍርድ ቤቱን ፍርድ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ከነገሩን አንድ ወር እንኳ አልሞላውም፡፡

መቼም  ሰላም ማውረድ መልካም ሆኖ  ሳለ  ቁምነገሩ ግን  የኤርትራን ጥያቄ  አለማወቅ ላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡  በእውነቱ የኤርትራ ጥያቄ  የመሬት ጥያቄ አይደለም፤ የኢኮኖሚና  የበላይነት ጥያቄ እንጂ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባድሜን   ለኤርትራ ሰጥቼ   ሰላም አመጣለሁ  ብሎ  ካሰበ በእውነት ትክክለኛ ነጥቡን አላገኘውም  ማለት ነው፡፡  አንድ እርግጠኛ  የምሆነው ነገር ቢኖር ኤርትራ  ወደዚህ ጨዋታ በምንም ዓይነት ሁኔታ  እንደማትገባ ነው፡፡  ምክንያቱም በዚህ ጨዋታ  ኢትዮጵያን እንደምታሸንፍ ታውቃለች፡፡  ኢሕአዴግ መሬት በመስጠት  መጥፎ ታሪክ እንደሌለወ  ገና ድሮ ገብቷታል፡፡ ሻእቢያ የኢትዮጵያን ጠላትነተ ለሁለት ከፍሎ ያየዋል፡፡  አንደኛውና  ዋነኛው  ጠላቴ የትግራይ ሹማምንት ብሎ ሲያስብ ቀሪውን የኢትዮጵያን ክፍል በሁለተኛነት ያስቀምጠዋል፡፡ ሻእቢያ ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር አድርጋለሁ ብሎ  ሲያስብ ግብአቶችንና (Input) የሰው ጉልበት (labor) በትግራይ  እንደልቤ እያፈስኩኝ  ያመረትኩትን  እንደ ልቤ ትግራይ ላይና  የተቀረው  ኢትዮጵያ ላይ   አየሸጥኩኝ  ምናምን የሚል እቅድ ይዞ ወደ  ሜደው የገባ ሲሆን ይህን  ኢፍትሐዊ  ንግድ  ያስቀሩብኝ  የትግራይ ሹማምንት ነው ብሎ ቂም ይዞ   እንደነበርና  የመጀመሪየውን የግፍ ፅዋ  በትግራይ ውስጥ  በሀይደር  ትምህርት  ቤት ላይ ያደረገው ግፍ የቅርብ  ጊዜ ትውስታ ነው ፡፡ ሻእቢያ  መቼም ቢሆን  በተረጋጋችው ኢትዮጵያ  ውስጥ የሲንጋፖር ሕልሙን ማሳካት አይቻለውም፡፡  ኤርትራ  ሲንጋፖርን  ለመሆን  ኢትዮጵያ ሩዋንዳን በማድረግ ብቻ ነው ብሎ ገና  ድሮ ደምድሟል፡፡  ስለዚህ  በዚህ   አመለካከት መሠረት  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከዶሀ  መልካም ነገርን ይዘው ተመልሰዋል ለማለት  አይቻልም፡፡

ለ/ እሾህን በእሾህ

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም የዶሀ ጉዞ  ሁለተኛው  ምክንያት እንግዲህ  ከኤርትራ ጋር  በመስማማት የኢትዮጵያ ተቀዋሚዎችን ከጨዋታው በዜሮ ማስወጣት  ይመሰለኛል፡፡ የእሾህን በእሾህ ጨዋታ በሀገራችን ከጥንት ጀምሮ ሲተገበር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኢሕአፓን በመኢሶን፣ ሕወሓትን በኢዲዮ እንዲሉ…. ኢሳትን በኢቢኤስ…  ተስፋዬ ገብረ አብን፣ በመስፍን ነጋሽ እንዲሉ… ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መጠናከራቸውና  አስመራ ላይ መክተማቸውን የጠረጠረ ይመስላል፡፡  በእርግጥ ላለመስማማት ተማምለው የነበሩ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ከሌላ ጊዜ በተለየ ሁኔታ የመተባበር ሁኔታ እየታየባቸው  ይገኛል፡፡  በኢትዮጰያ  ውስጥ በትግል ታሪካችው አንጋፋ  ከሚባሉት ውስጥ  አንዱ የሆነው  ኦነግ አንኳነ የፖሊሲ  ለውጥ  በማድረግ ከሴማውያን ጋር  ለመስራት  በሩን  ክፍት ማድረጉ ለኢሕአዴግ ቁጣዩ ፈተና ምን እንደሚሆን  ከወዲሁ  ለመተንበይ አያስቸግርም፡፡  በዚህም ነጥብ ላይ  ሻእቢያ ለድርድር በሩን አስካልከፈተ ድረስ  የዶሀው  ጉዞ ከወዲሁ   በስኬት እንደማይጠናቀቅ ግልፅ   ያደርገዋል፡፡  ይልቅስ  የእሾህን  በእሾህ   ጨዋታን ወደ ጐን አድርጐ መንግሥት የሀገራችንን ችግር  በሀገራችን  እንፍታው በማለት መቀነቱን ጠበቅ አድርጐ  ብሔራዊ እርቅ ቢያደርግ ይመረጣል፡፡ እሾህን በእሾህ መርሕ ይዞ የገለአድን ተሪራ መውጣት ከባድ ከመሆኑም በላይ  የጌዲዮን ወታደር ለመሆን ትንሽ ያስቸግራል፡፡

ሐ/ የግብፅ  ጉዳይ

ሦስተኛው የዶሀ ጉዞ ከዓባይ ግድብ ጋር ተያየዞ ከግብፅ ጋር የሚገናኝ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ግብፅ የዓባይ ግድብ እውን እንዳይሆን  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትንኮሳ ታደርጋለች ብሎ መንግስታችን የተጨነቀ ይመስለኛል፡፡ ግብፅ   የውክልና ጦርነት (Proxy war)  ኤርትራን ተጠቅማ ታደርጋለች የሚለው መላምት አንዱ ሲሆን   ሁለተኛው  ደግሞ  ግብፅ ግዙፉን አየር ኃይሏን ተጠቅማ  የኤርትራ አየር ላይ እንደልቧ እየተንሳፈፈች  ታጠቃናለች  የሚለው ሌላው   እሳቤ ይመስለኛል፡፡  ይህንንም ለመከላከል ኢትዮጵያ በኳታር አማካኝነት  ከኤርትራ ጋር  ሰላም  ለማውረድ  አስባለች  ማለት ነው፡፡  ይህ  መቼም   መልካም  እሳቤ  ነው፡፡ ነገር ግን  ከዚህ ጉዳይ ጋር  ተያይዞ ቅድመ  ዝግጅት በመከላከያ በኩል ማድረግና የቀጥታ ውይይት ከግብፅ ጋር  ማድረግ  እንደአማራጭ ቢያዝ አይከፋም ባይ ነኝ፡፡   ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት የዓባይን ግድብ አስመልክቶ ከግብፅ  ስለሚሰነዘረው ሁኔታ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ ‹ግብፅ  እኛን   አትደፍረንም፣ ታውቀናለች› የሚል መልስ መስጠታቸው  ትዝ ይለኛል፡፡   በወቅቱ ይህ መልስ ብዙም አልተመቸኝም ነበር፡፡  ከወቅቱ ጋር   የተያያዘ መልስ ነው የሚል ግምትም የለኝም፡፡   ድሮ  ጦርነት በወኔ ማሸነፍ ይቻል ነበር፡፡ ዛሬ ነገሮች  ተለውጠዋል፤ ጦርነት ቴክኖሎጂ ሆኗል፡፡  የላቁ ቴክኖሎጂዎችና  ብዙ ገንዘብ ለጦርነት ያፈሰሰ አካል ነው፡፡ የድል ፅዋ  ሊጨብጥ የሚችለው፡፡   የቹን ዙ መጽሐፍ  ለዛሬ ጦርነት ዋጋ  አይኖረውም፡፡ ግብፅ  በየዓመቱ  ሁለት ቢሊዮን  ዶላር ለመከላከያዋ አሜሪካ እንደምተደጉማት መረሳት የለበትም፡፡  ቴዲ አፍሮ ‹ጋሻው፣  ጐራዴው ቀላ› ሲል   በግብፅኛ   ‹አሞራ  በሰማይ ሲያይሽ  ዋለ› የሚል ትርጉም እንዳለው መረሳት  የለበትም፡፡  በእርግጥም  የግብፅ  አየር ኃይል ግዙፍ ነው፡፡ ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስተራችን አብዝተው  ወደካይሮ  መጓዝና ዳፕሎማሲውን ከግብፅ ጋር  ማጠንከር  ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያኔ ነው ገለአድን   መውጣት የሚቻለው፡፡

የአፍ ወለምታ

ጠቅላይ ሚኒስትራችን  በዶሀ  ካደረጉት  ውስጥ  አንዱ ከቀድሞው ደርቢያችን አልጄዚራ ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ይጠቀሳል፡፡ በቃለ ምልልሱ ላይ ወደ አስመራ ለመሄድና ኢሳያስን በአካል ማግኘት እንደሚፈልጉ ተናግረው ሐሳባቸውን ማጠናከሪያ መለስ 50 ጊዜ  ኢሳያስን ለማናገር እንደሞከሩ ነግረውናል፡፡   የሳቸውን  ፍላጐት በመልካም ባየውም የመለስ ግን የአፍ ወለምታ ትመስለኛለች፡፡ የሀገሬ ሰዎች 1050 ወይም 100 የሚሉ  ቁጥሮችን  አብዝቶ ይወዷቸዋል፡፡  ለምን እንደሆነ ባላውቅም አንድም ቀን ትንታኔዎች 49 ወይም 51 ላይ ሆነው አያውቁም፡፡ ኦ!... ለካ  ኢኮኖሚያችን 11% ነው፡፡…  በ1992ዓ.ም. የጦርነቱ ማብቂያ አካባቢ ዳሬ ሰላም ላይ መለስና ኢሳያስ ተገናኝተው ነበር፡፡ ኢሳያስም  መለስን ለብቻቸው ካላነገርኩዋቸው ሀገር ይያዝልኝ  ቢሉም   መለስ ግን ፈቀደኛ   ሳይሆኑ መቅረታቸውን በዚያ ወቅት  የመንግስት ልሳን  ከሆነችው እፎይታ  መጽሔት ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ መለስ ኢሳያስን ቢያናግሩ ኖሮ አዲስ አበባ ላይ ማርክሲስቱ ተወልደ እና  ስዬ አብርሃ በወቅቱ  በሕወሓት ውስጥ  ተከስቶ ለነበረው ክፍፍል  ይጠቀሙበታል ብለው  መለስ አስበውት   ይሆናል፡፡  ከዚያ በኋላ ግን በተለያየ ወቅት መለስ ኢሳያስን ከመንበረ ስልጣኑ  እንደሚያስወግዱ ሲዝቱ እንጂ   ለድርድር ሲጠይቁ ተሰምተው አይታወቅም፡፡ ስለዚህም  የአቶ ኃይለማርየምን ንግግር ለማመን ያስቸግረኛል፡፡

እንደ ማጠናናቀቂያ

የጠቅላይ ሚኒስትሩን  የዶሀ  ጉዞ  ለሀገራችን  መልካም ነገር  ይዞ  እንዲመጣ ሙሉ ምኞቴ ነው፡፡  የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጅማሮ መልካም ነው ብዬ  አስባለሁ፡፡ ነገር ግን ዲፕሎሲያዊ ጥረቱ  ሀገር  ውስጥም  መቀጠል አለበት ብዬ  አስባሁ፡፡  በተለያዩ  ወቅቶች ከመንግስት ጋር   ተጣልተው ትጥቅ ያነሱትንም ሆነ  በስደት  ያሉትን የሀገሪቱ ልጆችን ማወያየትና   ወደ ሰላማዊ ፖለቲካዉ ውድድር እንዲገቡ  ማሳመን  ቀጣይ  የጠቅላይ ሚኒስትሩ  ዕቅድ እንዲሆን እመኛለሁ፤ መንግሥት ሲተችበት የነበረበትን ቢያስተካክል እና የኢትዮጵያ ልጆች  በአንድ የሚቆሙበትን መንገድ መንግሥታችን ቢያመቻች እመኛለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!
-----
ጸሐፊውን ለማግኘት በዚህ ኢሜይል አድራሻ ይጻፉላቸው:- tamrattesfaye39@yahoo.com

No comments:

Post a Comment