ዓለማየሁ
ደንድር የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF
Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነው፡፡ ዓለማየሁ ብቻ ሳይሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ
ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.
ሲገባ የ8 ወር ልጅ የነበረው ዓለማየሁ “ኢሕአዴግ ላይ ያለንን ተስፋ አንጠፍጥፈን ወደ ልኂቃኑ ማንጋጠጥ ጀምረናል” ይለናል፡፡
አንብቡት፡፡
ጥሬ ትርጉሙን (literal meaning) ለመረዳት በኢሕአዴግ የኔታነት ለተማርነው ሊከብደን ይችላል። ጥቅል ሐሳቡ 'ወደድክም ጠላህም ከፖለቲካ አታመልጥም' እንደማለት ይመስለኛል። “አንተ ልጅ ፖለቲካ ማውራት ይቅርብህ ኢሕአዴግ ያስርሃል" ብለው የሚጨነቁልን ወዳጆች፤ በዛው አፋቸው “ተው አንተ የኢሕአዴግ ፖለቲካ... ልጁ ላይ አትድረስ" ማለት ቢችሉ መልካም ነበር። ከፖለቲካ ጋር ያለንን ኑሮ ለመረዳት ጊዜ ይወስዳል፤ ፖለቲካ ሲገነድስ እንጂ ሲሸርፈንና ሲጨርፈን አይታወቅም።
ፖለቲካ ሲጨርፈን
የጨረፈን የጫካ ጓዶች ከተማ ሲጣሉ ነው፤ በአገር ሥም ተዋጉ፣ አብሮ የኖረ ጎረቤት ተላቅሶ ተበታተነ። ልጅ ስለነበርን ፖለቲካ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ ወስዶብናል። ከተማ ሲገቡ የ8 ወር ልጅ ነበርኩ፤ ሳንጎረምስ ተባሉ፤ ከልጅነት የጨዋታ ሚስቴ፤ ዊንታ ለጋስ ጋር እንኳን የጉርምስና መተፋፈር ሳይሆን ፖለቲካ ነው የለየን ብል ማን ያምናል? እንደዛ ለመረዳት ግን ጊዜ ወስዷል። "ዳሕላክ ላይ ልሥራ ቤቴን ... ነጠለኝ ክፉ ዘመን ከምወዳት ባለቤቴ" ተብሎ ሲዘፈን እንኳን ፖለቲካ መሆኑን አልተረዳሁም ነበር።
ከስንት አንዴ ብልጭ ከሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞዎች በኋላ የ97 ምርጫ የማንንም ቀልብ ይዟል፤ የትምህርት ደረጃ ሲባል 'ማንበብና መጻፍ' የሚለው ሁሉ ጋዜጣ ይገዛል፤ እየተቀበልን እናነባለን፡፡ ሙቀቱ እንጂ ጉዳዩ ብዙም አይገባንም፡፡ ያኔ 9ኛ ክፍል ነበርኩ። ሙቀቱ ይስባል፤ እነ ልደቱ “አንከራከርም” ብለው ረግጠው ሲወጡ፤ “እንነጋገርበታለን”፤ “ቅንጅት ፓርላማ አልገባም” ሲል “ልክ ናቸው” እንላለን፤ ፖለቲካው ግን አይገባንም፡ ሙቀቱ ነው ‘ሚስበን። “አዲስ ከተማዎች ቀወጡት” ሲባል “እንዴት እኛስ ተበለጥን?” ይባላል፤ ይቀወጣል፤ ፌዴራል ይመጣል፤ ፀጉሩን ፍሪዝ ያረገ ሲቪል ፖሊስ፣ ፍሪዝ ያረገውንና የጠቆረውን ተማሪ እያንበረከከ በጫማ ጥፊ ይላል፤ እንዲይም ሆኖ ስለ ፖለቲካ መመታታችን ይግባን አይገባን እርግጠኛ አይደለሁም፤ በአዲስ ከተማ ተማሪዎች መበለጣችን እንጂ ምርጫ መጭበርበር ማለት ምን እንደሆነም የምንረዳም አይመስለኝም።
የሥልጣን ዘመኑ የአንድ ጎረምሳ (ሲሞት የሱ የሥልጣን ዘመንና የኔ ዕድሜ ዕኩል ነበር ማለት ይቻላል) ዕድሜ የነበረው መለስ ዜናዊ ሞተ፤ ነብሱን ይማረው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት እሱ ነው የመራን፤ ከቴሌቪዝን በሚታይ ንግግሩ “የታችኞቹ እንጂ መለስማ ጎበዝ ነው” በሚል ማኅበረሰብ አድገን ከሥልጣን ሳይወርድ ታሞ ሞተ፤ አዘንን። “አበበ ገላው እንዴት በአደባባይ ያዋርደዋል?” ሳንልም አልቀረንም። ፖለቲካውን ለመረዳት ሙከራ የጀመርኩት የዚህን ጊዜ ነው፤ ምናልባትም ፅንፍ
የያዘው የሙሾ አውራጁና “እሰይ እንኳን ክልትው አለ” ባዩም ይሆናል ትኩረቴን የሳበው፡፡ የተመስገን ደሳለኝና የፍትሕ ጋዜጣ
ውለታ ሳይዘነጋ፡፡
25ቱን የኢትዮጵያ ሕዝቦች
አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.) የሥልጣን
ዓመታት
ለመረዳት
ለሞከረ
የመጀመሪያው
መረዳት
ኢሕአዴግ
ማለት
መለስ
ማለት እንደነበር
ነው።
“ኢሕአዴግ
ጨቋኝ
ነው፡፡
ያስራል፣
ያሳድዳል፣ ይገድላል”
ስንል
መለስን ማለታችን ነው፡፡
በተለይ
ከ’93
የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) ክፍፍል በኋላ መለስ የኢሕአዴግ የሥጋም የነብስም አባት ነበር። ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ እንኳን 'Meles Zenawi and the Ethiopian
State' ባለው
መለስን
በሚያንቆለጳጵስበት
መጣጥፉ
እንዲህ
ጽፏል፡-
The process of consolidation Right
after the Ethiopia-Eritrea war and the split within his core political party
the TPLF, Meles had concentrated power in his own hands and a tiny group of
advisors. [...] Meles did not only withered away the threat to his power but he
had slowly but steadily worked his way to a supreme position in the Ethiopian
state
ፖለቲካውን በሥመ ‹ብሔር ብሔረሰቦች› ስንረዳው
የአሜሪካና የኢሕአዴግ አለቆች ከ‹ነጻነት› በኋላ ስለብዝኃነት በማውራት ይመሳሰላሉ። የአሜሪካኖቹ አንባገነንነትን ለመንቀል "how we prevent tyranny?" በሚል እሳቦት/ጥያቄ በመነሳት ብዝኃነትን (pluralism) እንደ መፍትሔ ሲያቀርቡ፤ የኢሕአዴግ አለቆች አምባገነንነትን ለመትከል "እንዴት በሥልጣን መሰንበት እንችላለን?" በሚል ጥያቄ በመነሳት፤ አገሪቷ በአጋጣሚ የታደለችውን (መታደል ከሆነ?) የብሔር ብዝኃነት በማስጮህ የከፋፍለህ ግዛ ዓላማቸውን አሳለጡ። እነ ጀምስ ማዲሰን የፍላጎት ግጭት (clash of interest) ለዴሞክራሲ ወሳኝ ነው ሲሉ፤ የኢሕአዴግ የጎበዝ አለቆች የብሔር ግጭትን የሥልጣን ማስጠበቂያ አደረጉት። ሁለቱም (የአሜሪካኖቹም የኢሕአዴጎቹም) ልኂቃን ዓላማቸውን ማስጠበቂያ ያደረጉት መፍትሔ ደሞ ፌደራሊዝም ነው።
ባለመታደል የእኔ ትውልድ የ‹አዲስ ስርዓት› መሞከሪያ ትውልድ ነው። ከዓመት በፊት ያነበብኩት የሌንጮ ለታ መጣጥፍ ላይ "ኢሕአዴግ ለብሔር ፌደራሊዝሙ
(Ethnic Federalism) ሊወቀስም ሊወደስም አይገባም" (ቃል በቃል አልተቀመጠም) ይላሉ። እንደምክንያት ያቀረቡትም ብዙ ብሔሮች ነፍጥ ያነሱበት ዘመን በመሆኑ ከብሔር ፌደራሊዝም ውጪ አማራጭ አልነበረም የሚል ነው። ኦቦ ሌንጮ ልክ ሊሆኑ ይችላሉ። ጥያቄው ግን ‹“የዘውግ ፌደራሊዝም ነፍጥ ላነገቡ መፍትሔ ነው” ያለ ስርዓት፤ በራሱ (በዘውግ ፌዴራሊዝሙ) ላይ ነፍጥ ላነገቡትስ የሚሰጠው መፍትሔ ምን ሊሆን ይችላል?› ነው ። የፌደራሊዝም መሠረቱ የኃይል ክፍፍል (decentralization of power) ሆኖ ሳለ፤ ኢሕአዴግ አገሪቷን በብቸኝነት ፈላጭ ቆራጭ በሆነበት ሁኔታ ሥልጣኑን እነማን እንደሚያከፋፍሉት ግልጽ አይደለም። በዛ ላይ የፓርቲ መዋቅሩ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት (Democratic Centralism) መሠረት
ያደረገ ፓርቲ ራስ ገዝነትን (Autonomous power) ለክልሎች ይሰጣል ማለት የማይታሰብ በመሆኑ “የዘውግ ፌዴራሊዝሙ የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ ጭምብል ነው” ለማለት ያስደፍራል። የፌዴራሊዝም ባሕሪ የሆነው የክልሎች (states) ፉክክር (competitiveness) በኛ አገር በተለያ ዘውጎች መካከል መሆኑም ልብ ይሏል። (እዚህ ላይ የዘውግ ፌደራሊዝም የሚያመጣብን ጣጣ ለማሳየት እንጂ፤ በዚህ ሰዓት ፌደራሊዝሙ ይፍረስ የሚል አቋም እያራመድኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።)
የትውልዳችን ፈተና
ነገሮች ክርር እያሉ ነው፤ የጓደኝነት መሥፈርቱ የ‹ብሔር ተወላጅነት› እየሆነ ነው። በአንድ ወቅት በታሪክ የተከናወኑ ጥፋቶች ጠረጴዛ ላይ ተዘርግፈው የትውልዳችን መካሰሻ ሆነዋል። የ25 ዓመት
ሸክሙ አልበቃ ብሎን የመቶ እና የሁለት መቶ ዓመቱን መደራረቡን መርጠናል፡፡ ስርዓቱም እነዚህን ያለፉ የታሪክ ችግሮች ያጦዛቸዋል። አብዛኞቹ ልኂቃን ጥጋቸውን እንደያዙም ናቸው። ወጣቱ ጫንቃ ላይ ካሉት የኑሮ ብሶቶች የሥራ ማጣት፣ የስርዓቱ ‹ሎሌ› ባለመሆን የሚደርሰው የኢኮኖሚ መገለል፤ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ስደተኝነት በላይ እየላሉ ያሉ የማኅበራዊ አንድነት እሴቶች በዚህ ፅንፍ ቀጥለው የሚበጣጠሱ ከሆነ የትውልዳችንን መከራ የሚያበዛው ይመስላል፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ይሄን ማኅበራዊ እሴት አቅለው የሚያዩ ‹ልኂቃን› ከሁሉም ጥግ አፍጥጠው መውጣታቸው ነው። የታሪክ
ችግሮችና ስህተቶች ተድበስብሰው መታለፍ ባይኖባቸውም በሚያጠፋፋን መልኩ መካሰሱ ማናችንንም አይጠቅመንም፡፡
No comments:
Post a Comment