Friday, May 27, 2016

እኩይ ዕኩያዬ፣ ኢሕአዴግ


አገኝሁ አሰግድ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነው፡፡ አገኝሁ ብቻ ሳይሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ አገኝሁ በዚህ ዕድሜው “የዕድሜ እኩይ ዕኩያዬ” ያለውን ኢሕአዴግን “ዴሞክራሲያዊ ሁን ማለት፤ እንደልቡ ይጋልብበት በነበረበት ልጓም ይግባልህ እንደማለት ነው። በጨለማ አድኖ ለሚበላ፣ ጨለማ በረከቱ ነው[ና]” ይለናል፡፡ አንብቡት፡፡

ኢሕአዴግ ተንዶ የማያልቀውን ሕገ መንግሥት ከመጻፉ በፊት፣ ከማርክሲስትነት ወደ ካራቲስትነት
ከመለወጡ በፊት፣ ብሔር ብሔረሰባዊ ሹፈት ከመጀመሩ በፊት… ተወልጃለሁ። በዛው ሥልጣን በያዘበት ዘመን። የፖለቲካ ወሬ እንደ ርዕስ ከጆሮዬ መግባት የጀመረው በአይረሴው ዘጠና ሰባት ወቅት ነው። በገርነታችን ዘመን።

የገር ልብ ናፍቆት

1997 በተለምዶ ሚኒስትሪ የሚባለውን የ8ኛ ክፍል አጠቃላይ ፈተናና የአገር አቀፉን ምርጫ ውጤት የምጠብቅበት ወቅት ነበር። በጊዜው ውስብስብ የፖለቲካ አረዳድ ባይኖረኝም፣ በሰማኋቸው ክርክሮች፣ ባነበቡኳቸው ጋዜጦች… ሞቄያለሁ። ልቤን ‹ቅንጅት› ለተበለው ፓርቲ ‹ልብ ወደ ላይ› አስብዬ አስረከብኩ። አባቴ ያመጣቸው የነበሩ "ነፃነት"፣ "ሚኒልክ"… ጋዜጦች አበጀህ አሉኝ። መረዳቴም ወደ አንድ አቅጣጫ ዘመመ - ኢሕአዴግ ይህቺን ዓመት አይሻገርም! ዛሬ ሳስበው ይገርመኛል። የምርጫው ውጤት በየቀበሌዎቹ ይፋ ሲሆን ብዙ ቀበሌዎች በጊዜ ሄጄ ውጤቱን አይቼ ተመልሻለሁ። በከተማችን ቅንጅትን ወክሎ የተወዳደረው ሰው ማሸነፉን ለቤተሰቦቼ አበሰርኳቸው። ኢሕአዴግን ካለመረዳት የመነጨ ተስፋ ነበረኝ። ምናልባት ይሄን ‹ተስፋ› ከማለት ለ‹ሞኝነት› ይቀርብ ይሆናል። እንደማይደገም ግን እርግጠኛ ነኝ።

ንቦቹ ተናደፉ

በጊዜው የኢሕዴግን ቅፅበታዊ ወደ ጸበኝነት መቀየር፣ አንድ ጋዜጣ ‹ንቦቹ ተናደፉ› ብሎ ዘግቦት ነበር። በወቅቱ ንብም ከታታሪነቷ ተናዳፊነቷ አብዝቶ ታሰበ። ብዙ ወጣቶችም በአግአዚ ጥይት ተነደፉ። የአገሬን ፖለቲካ ከዛን ወቅት ጀምሮ እየጠላሁትም ከምሰማቸው ጉዳዮች አንዱ አደረኩት።

‹ከእኔ ውጪ ለሌላ መንግሥት እንዳትገዙ›

እንኳን ‹ፀሐይ ነኝ› ከሚል ዋሾ መንግስት ጋር ለዓመታት መቆየት፣ በሀሩር ፀሐይ ለሰዓታት መቆየት እንደሚከብድ ግልፅ ነው። ሕይወትን ሕይወት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ለውጥ ነው። ከለውጥም በጎ ለውጥ። ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ አገዛዝ ከምን ወደ ምን ተለወጠች?  የቱ ጨለማ ተገፈፈ፣ የቱ የብርሃን ምሰሶ ቆመላት? ሳያይ የሚያምን ብፁዕ ይኖር ይሆናል። ሳላይ በማመን ለብፁዕነት የምጓጓ ባለመሆኔ፣ መልሴ ‹ምንም› ነው። ከአንድ መንግሥት ጋር አድጌ፣ ከአንድ መንግሥት ጋር መኖሬን በሁለት መንገድ አየዋለሁ።

አንደኛው፣ የብዙ ወጣት ግብ የማይመታ መልካም ሕልም በየጉያው እንዲሟሟ አድርጓል። ሁለተኛው፣ አገሪቷ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር የምታውቅበት ስርዓት ውስጥ የመግቢያ ጊዜውን አንቀራፎታል።

ቴክኖሎጂ በከፈተው በር መንግሥት በምርጫ ካርድ የሚለወጥበትን አገር አይተን፣ ወደ አገር ውስጥ ፊታችንን ስንመልስ፤ እንኳን መንበሩ ልቡ የማይለወጥ መንግሥት ማየት ተስፋን ያጨልማል። ችግሩ ተኝተን በነቃን ቁጥር አንድ መንግሥት ማየታችን ብቻ አይደለም። አብሮም የከፋ መንግሥት መሆኑ ነው። የሚያነክስ ኢኮኖሚ ይዞ ስለማደጉ የሚለፍፍ፣ የታመመ የትምህርት ስርዓት ይዞ ዪንቨርስቲን ስለማስፋፋቱ የሚያወራ፣ የወራት የዝናብ እጥረትን መሻገር ሳይችል “በምግብ ራሳችንን ችለናል” የሚል፣ “መሬት የሕዝብ የሚሆነው በመቃብሬ ላይ ነው” ከሚል እኩይ ድርጅት ከመሆኑ ላይም ነው። እኚህ ሁሉ ተደማሪ ብሶቶች ናቸው። ለአንድ ወጣት ደግሞ ዕድሜውን እንደ ሰሌን በብሶት ወለል ላይ አንጥፎ እንደመኖር ትልቅ እርግማን የለም።

እኩይ(ያ)ዬን ሳውቀው

ኢሕአዴግን ለማወቅ ውስብስብ ጥረት አይፈልግም። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመጠኑ ቀርቦ ያየ ሁሉ ልቦናውን ውጪ ተሰጥቶ ያገኘዋል። እኔ የማውቀው ኢሕአዴግ፣ ‹የፈጀውን ይፍጅ› እንጂ ከሥልጣኑ ምንም የማያስበልጥ ነው። ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ቅንጣት ሳያስብ የዘውግ ፖለቲካን ባደገኛ አያያዝ የሚቆምረውን ነው። እኔ የማውቀው ኢሕአዴግ የአመለካከት ልዩነትን ሕገ መንግሥትን ከማፍረስ አቻ የሚያደርገውን ነው።

በቀረጸው የትምህርት ስርዓት ተምሬያለሁ። አብሬው ድሄ አብሬው ጎርምሻለሁ። ከሹፈቱም ከበትሩም ቀምሻለሁ። እኔ ጋር ያለው ኢሕአዴግ የምናቤ አይደለም፤ የመሬቱ ነው። “ሰልፍ ካለ ዱላ እና እስር አለ” የሚለውን ነው። የጮኸ አምባገነንነቱን ክዶ “ዴሞክራት ነኝ” ብሎ የሚጮኸውን ነው። ገደል ላይ የቆመ ኢኮኖሚውን ይዞ፣ “የዕድገት ሩጫው ላብ በላብ አደረገኝ” የሚለውን ነው።

አሁንስ ተስፋዬ ማነው?  ኢሕአዴግ ሊሆን ይችላልን?

በኢሕአዴግ ተስፋ ማድረግ፣ የበሬ ቆለጥ ካሁን ካሁን ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ መሆኑ ከገባኝ ቆይቻለሁ። ተስፋ በአየር ላይ የሚገነባ የምናብ ቤት አይደለም። ባለፉት ዓመታት በድርጅቱ ተስፋ የነበራቸው ሰዎች ተስፋቸውን እንደጣሉ ወይ እንደሸረሸሩ አምናለሁ። ድርጅቱም ተስፋ የጣሉበትን ሁሉ ተስፋቸውን ለመብላት ወደኋላ አላለም። ከፋ እንጂ ሆዱ አልሰፋም። “የብዕር ቀለም ሳይ፣ የቀለም አብዮት ትዝ ይለኛል” ባይነቱ ብሷል። እና ከዚህ ወንዝ እንደምን የተስፋ ኮዳ ይጠልቃል?!

ዲሞ - Crisis: የግንቦት ሃያ ፍሬ ወይስ የግንቦት ሃያ ፍሬን?

ለአንዳንዶች ትልቁ የተስፋ ዓምድ፣ “ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል” የሚል ነው። እውነት ዲሞክራሲን ከኢሕአዴግ መጠበቅ ይቻላል። ለዛ የሚያበቃ ታሪካዊ እና አመክንዮኣዊ መነሻ አለው?  ጥያቄዎቹን ከድርጅቱ ታሪካዊ መሠረት እና የአሁን ፍላጎት አንፃር ማየት ይቻላል።


የድርጅቱ ከበረሃ ጀምሮ ያለ ታሪክ እንደሚያሳያን ለሐሳብ ነጻነት ቦታ አልነበረውም። የገዛ አባላቱን አስሯል። ገድሏል። በተመሳሳይ አቋም ያሉ የትግል ቡድኖችን በስምምነት በር ገብቶ ረሽኗል። ከመሠረቱም የዴሞክራሲ ሐሳብ በኅሊናው አልነበረም። የዴሞክራሲ አስተሳሰብ መሠረት ያልነበረው ባንድ ጀንበር ከየት ያመጣዋል?  ኢሕአዴግነቱን ይጣ ማለት አይሆንም? ከድርጅቱ አመክኗዊ ፍላጎት አንፃር ካየነው ደሞ፣ ሐቁ ድርጅቱ ዴሞክራሲን አለመፈለጉ ነው። ዴሞክራሲ ለሕዝቡ አልሚ መሆኑ ባያጠራጥርም ለኢሕአዴግ አውዳሚ ነው። እንደልቡ ይጋልብበት በነበረበት ልጓም ይግባልህ እንደማለት ነው። በጨለማ አድኖ ለሚበላ፣ ጨለማ በረከቱ ነው።

አገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ብትሆን አቅማቸው ላሉበት ቦታ የማይመጥን፤ በትምህርትም ሆነ በአመራር አቅም እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። ነገሮች ባሉበት መቆየታቸውን የሚወዱት ለዛ ነው። ቀድሞም ድላቸው የነፍጥ እንጂ የአመለካከት ስላልሆነ፣ ባልለመዱት ሜዳ የመጫወት መልካም ፍቃድ የላቸውም። ዴሞክራሲን ከምላሳቸው እንጂ ከልባቸው አይፈልጉትም። ተነሳሁበት ካለው ዓላማ አንፃር ዛሬም ቢሆን ድርጅቱ ባለ ድል አይደለም። ግንቦት ሃያም ድል ሳይሆን እንደ ድል በዓል መከበሩ፣ ከሌሎች በዓሎች የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል!

No comments:

Post a Comment