Monday, August 6, 2012

የ”ኢሕአዴግ ቀይ እስክሪብቶ”ን እኔ እንደወደድኩት…


የ14 ዓመት እስር ፍርዷ ወደአምስት ዓመት በይግባኝ ዝቅ የተደረገላት ርዕዮ አለሙ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሌላም ድርብ ድል አስመዝግባለች - የመጀመሪያ መጽሐፏን በማስመረቅ!

ርዕስ፡- የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ
የገጽ ብዛት፡- 204
የጽሑፍ ብዛት፡- 19
ዋጋ፡- 40 ብር
የመጀመሪያ እትም፡- ሐምሌ 2004
አርትኦት፡- ስለሺ ሐጎስ
የሽፋን ገጽ ዲዛይን፡- አርኣያ ጌታቸው
የመጽሐፉ ርዕስ ‹የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ› ይሰኛል፡፡ ከሰኔ 2002 እስከ ሰኔ 2003 በአዲስ ፕሬስ ጋዜጣ፣ በቼንጅ መጽሔትና በፍትህ ጋዜጣ ላይ የታተሙ ጽሑፎቿ ስብስብ ነው - መጽሐፉ፡፡

የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ› የሚጀምረው በርዕዮት ምስጋና ነው፡፡ እግዚአብሔር፣ እጮኛዋ፣ ቤተሰቦቿ፣ ወዳጆቿን እና የታሰረችበት (ዞን ስምንት መሆኑ ይታወቃል) ድረስ በመሄድ የጠየቋትን የfacebook ‹‹አሸባሪዎች›› ሳይቀር ያልተመሰገነ የለም፡፡

በመግቢያዋ ላይ ‹‹…[ኢሕአዴግ] ራሱ ላጸደቀው ሕገ መንግስት ታማኝ ቢሆን ኖሮ፤… እኔም ራሴ አርፌ ልማታዊ ጋዜጠኛ እሆን ነበር›› ያለችው ርዕዮት፣ በመጽሐፏ ውስጥ ‹ልማታዊ ጋዜጠኝነትና ልማታዊ ጋዜጠኞቻችን› ባለችው ጽሑፏ (በነገራችን ላይ ይህንን ከሁሉም አስበልጬ ወድጄላታለሁ) - ስለልማታዊ ጋዜጠኝነት ባስቀመጠችው ብያኔ መሰረት በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በሰነዘረቻቸው ገንቢ አስተያየቶች ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኛ›› መባል ነበረባት፤ ትርጉሙ ባይዛባ ኖሮ!

ርዕዮት በጽሑፎቿ ከድህነት አንስቶ እሰከ ድህነትን መጠቀሚያ ስላደረገው የኢሕአዴግ ፖለቲካ፣ ከሃይማኖት አባቶች ‹‹ለሁለት ጌታ ተገዢነት›› እስከ ያለ ፍትሐዊ ውድድር ስለተገኘው አውራ ፓርቲነት፣ ከኢትዮጵያዊነት እስከ እንስታዊነት የሚቀራት ርዕሰ ጉዳይ የለም፡፡

አጻጻፏ ለዛ ያለው ከመሆኑም ባሻገር ትረካዋ ጨዋታ አዋቂ አበው ‹‹ነገር በምሳሌ፣ ጠጅ በብርሌ›› እንዲሉ በአገርኛ ተረቶች የተከሸኑ በመሆናቸው ለማንኛውም አንባቢ ያለችግር የጉዳዩን ዝርዝር ዘልቀው ያስረዱታል፡፡ ከብዙ ተቺ ጸሐፊዎች በተለየ ጽሑፏን በግል አስተያየቶቿ ከመሙላት ይልቅ ማስረጃ ጥናቶችን ማጣቀሷ ደግሞ ለክርክሯ ጭብጥ ጥንካሬን አላብሶታል፡፡ በተጨማሪም ትችቶቹን ብቻ ሰንዝሮ እና የሚኮነነውን ኮንኖ እጅን ከማጣጠፍ ይልቅ መፍትሔ የምትላቸውን በጽሑፎቿ መደምደሚያ ላይ ጠቆም እያደረገች ማለፍን መምረጧ ተጨማሪ እሴት ሆኖላታል፡፡

ከመከራከሪያ ማስረጃዎቿ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የተለያዩ ቦታዎች ላይ መጠቀሟ፣ ጥቅሶቹን ለማይቀበሉ አሳማኝ አለመሆናቸውን እንደችግር አይቼዋለሁ፡፡ ይሁን እንጂ እሷ ግን የምታምንበትን ቤተ ሐይማኖት እና መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ‹‹የማይነኩ›› በማለት ሳትሞግት አላለፈቻቸውም፡፡

‹‹የሐይማኖት አባቶቻችን ማንን እያገለገሉ ነው?›› ባለችው ጽሑፏ ‹ፍቅር እስከ መቃብር› ላይ የፊታውራሪ መሸሻን ፊት እያዩ ሲያዝኑ የሚያዝኑ፣ ሲደሰቱ የሚደሰቱ፣ ሲቆጡ የሚቆጡትን ቄስ ሞገሴን እያጣቀሰች የዘመኑ ጳጳሳትን ብፅዕና ትተቻለች፣  ለሁለት ጌታ መገዛት እንደማይቻል መጽሐፍ ገልጣ ታስረዳለች፡፡ ‹እንስታዊነት እና እኛ› ባለችው ጽሑፏም ጥናት እያጣቀሰች ሴቶችን የወንዶች ረዳት ብቻ አድርገው የሚያቀርቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እና የሸርዐ ሕግጋትን ተችታለች፡፡

ትችቶቿ (ገንቢ አስተያየቶቿ ቢባሉም ያንሳቸዋል፤) በበቂ መረጃ እና መከራከሪያ ሐሳቦች ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፣ እንደአንዳንድ ንዴት የመራቸው ጸሐፊዎች መዘባረቅ ወይም ስድብ አይስተዋልባቸውም፤ ከሐሜት የማያመልጡትን ተቃዋሚዎችንም ቢሆን ያለባቸውን ተፅዕኖ ያገናዘበ ተገቢ ትችት አድርሳቸዋለች፡፡ እንደምሳሌም ስለሰለማዊ ትግል ስታወራ ‹‹ጄን ሻርፕ… ከዘረዘሯቸው 198 የሚደርሱ የአመፅ አልባ ትግል ዓይነቶች ውስጥ በሀገራችን ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አምስቱን እንኳን በትክክል ስለመጠቀማቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡…›› (ገጽ 166) ብላለች፡፡

ርዕዮት በ‹የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ› ውስጥ፣ በአራት ክፍሎች ከተካተቱ 19 ጽሑፎች መካከል ከ6ቱ በቀር በሌሎቹ ውስጥ ምርጫ 1997ን አስታውሳናለች፡፡ ይህም ርዕዮትን እንደብዙዎቻችን ሁሉ ያኔ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ፍሬ ናት ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡

ለማንኛውም መጽሐፉ ከሽፋን ገጹ ጀምሮ እስከ ውስጥ ይዘቱ የሚጠገብ ዓይነት ሁኖ አላገኘሁትም፤ እግረመንገዳችንንም በአገራችን የፍትሕ ስርዓት የመንግስት ክፉ መዝገብ ውስጥ የሚያስገባው ምን ዓይነት ጽሑፍ እንደሆነ ለመታዘብ ስለሚረዳን፣ ሁላችሁም እንድታነቡት ጋብዤያችኋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment