ርዕሳችንን የተዋስነው ‹‹ለሙስሊሙ ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊው ኮሚቴ›› ከሚጠቀምበት የፌስቡክ ገጽ ስያሜ ነው፡፡ ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› የሚለው ሐረግ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ የሚገልጽ ነፍሰጡር ሐረግ ነው፤ ብዙ ፍቺዎችን ይወልዳል፡፡ ጥያቄ፣ ተማፅኖ እና ትዕዛዝም ሊሆን ይችላል፡፡
ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በርካታ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከል ‹‹መጅሊሱ›› አይወክለንም እና ይቀየር የሚለው አንዱ ነው፡፡ ለዚህ የተገኘው ምላሽ መጅሊሱን የሚተኩ አባላት የመምረጥ መብት ቢሆንም አካሔዱ ሌላ ጥያቄ አጭሯል፤ አባላቱ መመረጥ ያለባቸው በቀበሌ ጽ/ቤቶች በኩል ነው በሚል፡፡ ይህንን ደግሞ አብዛኛው ሙስሊም ሃይማኖታዊ ጉዳይን ከፖለቲካጋ ከመቀላቀል ለይቶ አልተመለከተውም፡፡ ስለዚህ ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ድረስ ተቃውሞውን ለመቀጠል የወሰነ ይመስላል - በሰላማዊ ተቃውሞ፡፡
የሰላማዊውን ተቃውሞ ዑደት (cycle) ብንመለከተው - ይጠይቃሉ፣ መልስ የለም፤ ይማፀናሉ፣ መልስ የለም፤ ያዝዛሉ መልስ የለም፡፡ መጠየቅ ተፈጥሯዊ ግዴታቸው ነው እና አያቆሙም፣ መማፀን ሰብአዊ ልምዳቸው ነውና ይተገብሩታል፣ ማዘዝ ሃይማኖታዊ ነፃነታቸው ከፖለቲካ ተፅዕኖ እንዲወጣ የተሰጣቸው ሕገመንግስታዊ መብታቸው ነውና ያዝዛሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ባሕሪ ነው፡፡ ዕውቁ ቼካዊ ጸሐፊ ፍራንዝ ካፍካ ይህንን በማስመልከት እንዲህ ብሏል፤ ”Believing means liberating the indestructible element in oneself, or, more accurately, liberating oneself, or, more accurately, being indestructible, or, more accurately, being.”
በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄ እና በመንግስት ምላሽ ምሳሌ የምንረዳው ጠቅላላውን የሕዝብና መንግስትን ግንኙነት ነው፡፡
ባለፉት 21 ዓመታት ውስጥ /በተለይም ሕገመንግስቱ ከፀደቀ ወዲህ ባሉት 17 ዓመታት/ ሕዝቦች በድምጻቸው መንግስትን ከመሾምና ከመሻር ጀምሮ ያለው መብት በሙሉ ተሰጥቷቸዋል ይባላል፡፡ እውነት ተሰጥቷቸዋል? እስቲ የኢትዮጵያን የጨዋታ ሕግ እንመለከት፡፡
የምዕራባውያን ሚና እና ድምጻችን
ምዕራባውያን አፍሪካን ወይም ኢትዮጵያን እንደመለስ ዓይነት ባሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመግባባት እና የማሳመን ችሎታ ባላቸው ልሂቃን ዓይን መመልከት እና የአፍሪቃ ቀንድን ከቧታል ከሚሉት አደጋ ይጠብቅልናል ብለው በሚያስቡት መሪ ማስገዛት ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑ ሙስሊም ማኅበረሰብም ሆነ ሌላው በሰላማዊ መንግድ ድምጹን በማሰማት ላይ ያለ ሰው ለትግሉ ምላሽ እርሳቸውን የመሰለ ሰው በማግኘት አለማግኘቱ ላይ የተንጠለጠለ ነው::
ምዕራባውያን በአፍሪካውያን እና በአረብ ላይ ያላቸው አመለካከት በጥቅሉ ጨለምተኛ ነው ማለት ይቻላል፤ አረብን ከእስልምና ጋር በመቀላቀልም ቢሆን ከመታማት አይተርፉም፡፡ ምንም እንኳን በአገራችን ውስጣዊ ጉዳይ ላይ አያገባቸውም ብሎ መዝጋት ቢቻልም፣ በመንገዳችን ላይ የሚጥሉብንን እንቅፋት ግን ከመጋፈጥ አንተርፍም፡፡ ስለዚህ ስለድምጻችን መደመጥ ሲባል እነርሱን የማሳመንም ዕዳ አለብን፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የድምጽ ዋጋ
ምርጫ 97 እና ውጤቱ ገዢው ፓርቲ ለዴሞክራሲ እሴቶች የሚሰጠው ዋጋ ግምት ውሰጥ የወደቀበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነው ማለት ቢቻልም፣ ይህንን ጥያቄ ለማንሳት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ብያኔ ማወቅ እና ከአጀማመሩ ጀምሮ ያለውን ሒደት መመርመር ያስፈልጋል፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይህ ነው የሚል ብያኔ የሚሰጥ ምሁር እስካሁን አልተገኘም፡፡ ምናልባትም ክፍተቱ የተፈጠረው በዘፈቀደ የሚጓዙበት ርዕዮተ-ዓለማዊ መንገድ ከመሆኑ አንጻር ነው ብሎ ለመደምደም ያስችል ይሆናል፡፡ የልማታዊ ጋዜጠኝነት አካዳሚያዊ ፍቺ ተዛብቶ በነባራዊቷ ኢትዮጵያ፣ በመንግስት ይዞታዎች ስር ባሉ ሚዲያዎች ‹‹ይሁንታን ማምረት›› እየሆነ እንደሆነ ከዚህ በፊት በዞን ዘጠኝ ላይ አውርተናል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም፣ ኢሕአዴግ በጥቅሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ መራኄ ጥያቄ ዳቦ እንጂ ዴሞክራሲ አይደለም ከሚለው ፈሊጥ’ጋ የተያያዘ እንደሆነ መገመት ወደተሳሳተ ድምዳሜ አያደርስም፡፡ በዚህ ስሌት ዳቦን (ልማትን) ለማምጣት ሲባል ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች የሚደፈጠጡበት የሚል አንድምታ ላይ ለመድረስ የመንገደድበት ጊዜ ይኖራል፡፡
ድምጽ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች ውስጥ ያለው ዋጋ ከፍተኛ ቢሆንም፣ (መለስ እንደሙጋቤ ‹‹አፍሪካ የሚያስፈልጋት የምዕራባውያኑ ዓይነት ዴሞክራሲ አይደለም›› ማለታቸው ይታወቃል፤) ስለዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ አፍሪካውያንን የሚስማማ ዴሞክራሲ ነው ቢሉን እንኳን ለሕዝባዊ ድምጽ የሚሰጠው ዋጋ እስካሁን ተለይቶ አልታወቀም፡፡
የምርጫ 97ን ውጤት ተከትሎ ‹አሸናፊው እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ› በሚለው የገዢውና ተቃዋሚ ፓርቲዎች እሰጥ አገባ መካከል ‹‹ምርጫው ይደገም›› በሚል ተቃዋሚዎች የጠየቋቸውን ወረዳዎች ባብዛኛው ባለመቀበል፣ ወትሮም ነፃ የመሆኑ ነገር የሚያጠያይቀው የምርጫ ቦርድ - የሕዝቦችን ድምጽ ዋጋ አሳጣው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ይህንን ርምጃ እየተቃወሙ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎችን ድምጽ የሚሰማ ነፃ ወገን ጠፍቶ - ቢያንስ ለ193 ሰዎች ሞት መንስኤ ሆነ፡፡
ይህንን ክፉ ገጠመኝ በወቅቱ ሲዘግቡ የነበሩት አገር በቀል ጋዜጦች በጅምላ ታገዱ፡፡ ይህን ጊዜ ብዙዎች ድምጻቸው በምርጫ ዋጋ እንደሌለው ብቻ ሳይሆን ሌላ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት መንገድ እንደሌላቸውም ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ ደረሱ፡፡ ከዚህ አጋጣሚ በኋላ በተለይም በተቃዋሚው ጎራ ያሉ ወገኖች በደርግ ዘመን አለ ይባል የነበረው የፍርሃት ማስካቸው ውስጥ ገብተው ተሸሸጉ፡፡ ለምርጫ 2002 የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ከምርጫ 97ቱ በእጅጉ ማነሱም የሚናገረው ሕዝቦች ‹‹ድምጻችን ላይሰማ ነገር…›› ብለው ተስፋ መቁረጣቸውን ነው፡፡
በየጊዜው የሚያሻቅበው የኑሮ ውድነት፣ መንግስት ልማትን ከሰብአዊ መብት የማስቀደሙ ውዝግብ፣ የፓርቲ አባልነት በመንግስት ተቋማት የሁለተኛ ዲግሪ የማግኘት ዕድል ከማሰጠት ጀምሮ ላሉ ጉዳዮች እንደዋስትና መታየቱ፣ እጅግ በርካታ መንግስትን የሚነቅፉ ዜጎች ባሉበት አገር በፓርላማው ውስጥ አንድ ብቻ ተቃዋሚ መኖሩ… ወዘተ፣ ወዘተ… እጅግ የሚያስጮሁ ሐቆች ሆነው ሳለ ሕዝቡ ዝምታን መምረጡ ድምጼ ሰሚ የለውም ብሎ ተስፋ ወደመቁረጡ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህንን ዓይነቱን ለመብት ተቆርቋሪነት መቀዛቀዝ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን Political apathy (‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› እንበለው፣) ይሉታል::
‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› የዜጎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት አለመኖር ነው፡፡ እንደምሳሌም፣ ሰበቡ ምንም ይሁን ምን ‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› ውስጥ የገቡ ሕዝቦች አለመምረጥ፣ ሕዝባዊ አስተያየት አለመስጠት፣ ዜግነታዊ ግዴታን ለመወጣት አለመሻት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በርካታ ምሁራን እንደሚስማሙበት ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ‹ፖለቲካዊ ዳተኝነት› የአንድን አገር ዕድገት ባለበት ቆሞ እንዲቀር መንስኤ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ድምጻችን
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዢው ፓርቲ አይወክለንም የሚሉ ድምጾችን ማስተጋባት /አሊያም ቢያንስ ድምጾቹ ወይም ጥያቄዎቹ አግባብ መሆን አለመሆናቸው ላይ አስተያየት መስጠት/ እንዳለባቸው በጥቅሉ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚህ ጽሑፍ እንደምሳሌ (sample case) የያዝነውን የሙስሊሞችን ጉዳይ እንኳን በሚመለከት ያለውን ሁኔታ ብናስተውል ተቃዋሚዎች ያላቸው ድርሻ እጅግ አነስተኛ ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ እስካሁን ድረስ ጥቂቶቹ ተቃዋሚዎች ብቻ ጊዜያዊ መግለጫቸው ላይ ‹‹ጣልቃ ገብነቱን›› እንቃወማለን ከማለት ባሻገር፣ መሬት ላይ ወርዶ ሊተገበር የሚችል የመፍትሄ ሐሳቦችን በመጠቆምና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር፣ ወይም ድምጹን በማጉላት የሠሩት ሥራ አለ ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡
አንዳንዶች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸው ድምጻቸውን የተቀሙ እንደሆኑ ይከራከራሉ፡፡ የሚሰጡትን የአቋም መግለጫም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ከቁብ ቆጥሮ ያዳምጣቸው እንደሆነ እንኳን በጥርጣሪ የሚጠይቁ እልፍ ናቸው፡፡
ከድምጻችን ተቀማ እስከ ድምጻችን ይሰማ?
የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊው ኮሚቴ አባላት በሙሉ እንደታሰሩ ተሰምቷል፣ የገዢው ፓርቲ በርካታ ሙስሊሞችን በየክፍለሃገሩ እያስተባበረ ሰልፍ እያስወጣ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች ‹‹ምርጫውማ በቀበሌ ነው መካሄድ ያለበት›› እያሉ ለትዝብት የሚዳርግ ክርክር ሲከራከሩ በኢቴቪ አይተናል፡፡ ኢቴቪ እነዚህን ሰዎች ሰፊ ሽፋን መስጠቱ ራሱ ምን እየተሰራ እንደሆነ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ድምጽ መስማት ስለማይችል ድምጽ መቀማት ጀምሯል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ድምጽ የማስመለስ ጥረቱ ደግሞ የሚቀጥለው፡፡
በዚህ ዘመነ-መንግስት ድምጽ የመቀማት ወግ የነበረ፣ ያለ እና ኢሕአዴግም እስካለ የሚቀጥል ይመስላል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ይቻል ነበር ቀርቷል፣ በምርጫ 97 መቶ በመቶ የተቃወመ በምርጫ 2002 መቶ በመቶ ደገፈ የሚል ስላቅ ተሰምቷል፣ በየዕለቱ ሁለት ሦስት ጋዜጦች ይወጡ እንዳልነበር አሁን ከሳምንቱ ሦስት ቀናት (ሰኞ፣ ሐሙስ እና አርብ) ምንም ፖለቲካ ነክ ጋዜጦች ማግኘት አይቻልም፡፡ ሐሳብን የመግለጽ መብት በሕግ ሰፍሯል ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የማይጎበኙ ድረገጾች ቁጥር በየቀኑ ያድጋል:: እነዚህ ሁሉ ድምጽ የመቀማት መንግስታዊ ስልት ውጤቶች ናቸው፡፡
ሰላማዊ ትግል እና ‹‹ድምጻችን ይሰማ››
ከቱኒዚያ እና ከግብጽ የፀደይ አብዮት መማር እንደቻልነው፣ ሰላማዊ አብዮታቸው (የነርሱ) ድኅረ ምርጫ 97 ላይ ከነበረው (ከኛ) የተለየ መልክ አለው፡፡ ምንም እንኳን በእኛ አገር፣ ለሕዝባዊ ተቃውሞዎች የመንግስት ሠራዊት የሚወስዳቸው ርምጃዎች ሕዝቡን የሚያስቆጡና ወደአመፅ የሚመሩ ቢሆኑም፣ ያኔ የነበረው ድንጋይ ውርወራ ላይ ያተኮረ አመፅ ከሰላማዊነት ያፈነገጠ ነበር፡፡ አሁን ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄውን የሚያቀርብበት መንገድ ግን አስተያየት ሰጪዎች ‹‹የገዢው ፓርቲ ቅጥሮች›› ናቸው በሚሏቸው ሰዎች ብጥብጥ ለመፍጠር የተሞከረ ቢሆንም በብዙሐኑ ለሰላማዊነት ተገዢነት በተደጋጋሚ ከሽፏል፡፡ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄውን ወይም ተቃውሞውን አመፅ አልባ በሆኑ መንገዶች ብቻ ለማድረግ መወሰኑ እና ከስድስት ወራት በላይ በትግሉ በፅናት መቆየቱ የሚያሳየን፣ በሰላማዊ መንገድ ረዥም ጉዞ መጓዝ እንደሚቻል ቢሆንም መልስ ሳያገኙ እስካሁን መቆየታቸው ግን መንግስትን በቸልተኝነት ከመወንጀል አያተርፈውም፡፡
እንዲያውም የኢትዮጵያ መንግስታዊ ተቋማት ለሰላማዊ ትግል እና ለድምጻችን ይሰማ ጥያቄ ከፍተኛ ደንቃራ ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር ይገባል:: በብዙ ታዳጊ አገራት እንደምናስተውለው፣ የኢትዮጵያ መንግስታዊ ተቋማት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት አንፃር ያላቸው ተወዳዳሪነት አነስተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኗ ኢትዮጵያ፣ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትም ሆነ ማሰራጨት የመንግስታዊ ተቋም ኃላፊነት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ወሳኝ የአገሪቷ ተቋማት (ፖሊስ፣ ፍርድቤት እና ዩንቨርስቲዎች) የስርዓቱን ወይም የገዢው ፓርቲን ለማገልገል የቆሙ የመምሰላቸውን ጉዳይ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ሕገመንግስቱም ቢሆን ከተመሳሳይ ችግር ሰለባ ከመሆን አላመለጠም፡፡ ዴሞክራሲያዊ መርሆችን በንቀጾቹ እንዲያካትት ቢደረግም በዕለት ተዕለት የመንግስት ባለስልጣናት ተግባር ግን ሲጣስ ይውላል፡፡ ስለዚህ የሰላማዊ ትግል ሚና ሕገመንግስቱን ማስጠበቅ ነው ማለትም እንችላለን፡፡
የድምጻችን ይሰማ ተስፋ
የፌስቡኩ ‹ድምጻችን ይሰማ› ገጽ ላይ የሚሰፍሩ ጽሁፎችን ለተመለከተ ሁለት ነገሮችን መረዳት ይችላል፡፡ አንደኛ፤ የዜጎች ጋዜጠኝነት (citizens journalism) ምን ያህል እየተተገበረ እንደሆነ እንደሆነ እና የሌላውን ሕዝብ ስሜት ላለመጉዳት ምን ያህል ጥንቃቄዎች እየተደረጉ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ የገጹ አስተዳዳሪዎች ከተለያዩ ወገኖች የሚገኙ መረጃዎችን ለመላው ሕዝብ እንዲዳረስ የሚያደርጉበት ፍጥነት አስደናቂ ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የተሰነዘሩ የእርምት አስተያየቶችን በሂደት እያስተካከሉ ሲመጡ በጥብቅ የተከታተላቸው የሚረዳላቸው ጥንካሬያቸው ነው፤ የሰላማዊ ትግል ባሕሪም ይኸው ነው፡፡
Nice post...
ReplyDeletedevops training