አገራችን ወዴት እየሄደች ነው? ቀጣዩስ እጣ ፈንታችንስ ምን ይሆን? ይህ የሰማኒያ ሚሊዮን ሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ ጠቅላያች በእግዜር እጅ ከመያዛቸው በፊት፣ እራሳቸው የሃገሪቱ ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ገዝተውናልና ለኛ ለዜጎች በጊዜያችን የሚመጥነንና የሚገባን ነገሮችን ሳስብ ግን ለብዙዎቹ ጥፋቶች ተጠያቂ አደርጋቸዋለሁ፤ የስልጣን ጥም እና ሕዝብን (ያውም 80 ሚሊዮን) የግል ቤተ ሙከራ ማድረግ፣ ጊዜን እና የሃገርን ንብረት ያላገናዘበ የሙከራ አመራር እና አገዛዝ በፓለቲካውም ሆነ በሞያ ሃላፊነቶች ላይ የፈጀውን ይፍጅ በሚባለልት ሥራና ትክክለኛነቱን ጥናት ያላረጋገጠው እውቀት በመተግበር ለሀገር ሃብት መባከን ምክንያት እንደሆነ ሲያነታርክ ቆይቷል፡፡ ይህ አካሄድ አንዳንዶቹን ባለስልጣኖቻችንን ባለጠጋ አድርጎ እኛን (እና ሃገራችንን) በፀጉራችን ልክ በእዳ ዘፍቆናል፡፡
በፊት በፊት በጎሳዎች መሃከል የሚፈጠሩ ግጭቶች የሚፈቱት በሽማግሌዎች ነበር ዛሬ ዛሬ መፍትሄ የሚያገኙት በፌዴራል ፖሊስ ሆኗል፡፡ (ይህንን የተለመደውን እና ውጤታማውን መፍትሄ በመተው መፍትሄ የሚመስለውን ጊዜያዊ ማደንዘዣ በሂደት እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችን መፍትሄ የምናገኘው በጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ እንዲሆን በማድረግ በመነጋገር ላይ የተመሰረተ የነበረው በአፈሙዝ ፍርሃት ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የአቶ መለስ መገኛ?
አቶ መለስ አልምተዋል፤ አቶ መለስ አጥፍተዋል ቢከፋም ቢለማም እኔ የእርሳቸው አድናቂ ባልሆንም የሚያደንቋቸውን ሰዎች ሐሳብ ግን ማኮስመን አልፈልግም፡፡ ቀጣዩ እጣ ፋንታችን ግን ሁላችንንም ሊያሳስበንና ነገሮችን በጥንቃቄና በማስተዋል ልንመለከት ይገባል፡፡ ሁላችንም እናልፋለን፤ አገራችን ግን አገር ሆና ትቀጥል ዘንድ ሁላችንም ግዴታ አለብን፡፡ ይህቺ አገር የምስኪኑም፣ የቱጃሩም፣ የሆዳሙም፣ የሃቀኛውም፣ የሁሉም ሃገር ነች ነገሮችን ግን ጥሩ ይሆኑ ዘንድ ሁላችንም ግዴታ አለብን፡፡
ብዙ ነገር በምታስቡበት ሰዓት ከኛ በተሻለ መንገዶችን ሊመሩን የሚገቡ አዋቂዎች ፋና ወጊ መሆን ተስኗቸው የእግዜርን እጅ የራሳቸው አስመስለው ወደ አራት ኪሎ እያሳዩን ነው - መለስን ያስታመሙት እነርሱ ይመስል፡፡ ታዝበናል መፍትሄው ምን ይሁን?
በአንድ ሠው ላይ መንጠላጠል (ለሃገርም ሆነ ለድርጅት አዋጭ አይደለም):: መለስን እንደ ብቸኛ አዳኛችን አድርገን እርሳቸውን ብቻ ማሰብ እርሳቸው ራሳቸውን በገነቡበት መንገድ እንደመሸነፍ ነው፤ እንደርሳቸው ያለ ከወዴት ይገኛልም ብሎ መጠየቅ፣ እንደርሳቸው ያለ አምባገነን እንደ መናፈቅ ነው:: አሁንም ስለግለሰቦች ከማሰብ መውጣት መጀመር ያለብን ይመስለኛል፡፡ ማሰብ ያለብን ነጻ መሆን ስለሚገባቸው የፍትህ አካላት፣ ስለ ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ እና በመፈቃቀድና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አገርን እና ሕዝብን እንጂ ግለሰብን አይደለም፡፡ እነዚህ እና የመሳሰሉት ተቋማት ብቃታቸውና ነጻነታቸው ከተረጋገጠ የመምራቱ ጉዳይ ክልሎች በዙር እንኳን ቢያደርጉት መሠረቱ የማይናድ ይሆናል በግለሰብ ላይ ያልተመሰረተ ነውና፡፡
የሰሞኑን ሁኔታ ስታዘበው፣ የሃገራችን ሁኔታ መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ነገሮች እየተከናወኑ ያሉት በሕግ ሳይሆን በጠመንጃ ነው፡፡ ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው የፍትህ ጋዜጣ በሰበብ አስባቡ መታገድና የሙስሊም ኢትየጵያውያን ሰላማዊ እንቅስቃሴ መሪዎች መታሰር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው ጉልበተኛ ጭንቅ ውስጥ ሲገባ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ምን ያህል አስጊ እነደሆኑ ነው፡፡ ያለንበት ሁኔታ ብዙ ባሰብኩበት ቁጥር ፍርሃቴንም ያንረዋል፤ ነገር ግን ይህ አስገራሚ የሆነና ለትንቢት የማይመቸው ሕዝብ ወደ ሚያጠፋን መስመር ባለመሄድ እንደምንድን ሳስብ ተስፋዬ ይለመልማል እንደ ኢህአዴግ ሥራማ ቢሆን ኖሮ?!…
ዜጎች ለውጥን ለመቀበል ፍርሃት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡ በኦክቶበር ወር ላይ በዚሁ ጉዳይ ተደርጎ የነበረው ጥናት እንደሚያሳየው መጠይቁ ከቀረበላቸው 2000 ዜጎች ውስጥ 69 በመቶ የሚሆኑት የአንድን ሰው አስተዳደር (ከዲሞክራሲ አምባገነንትን) መርጠዋል፡፡ በሶሪያም የበሽር ደጋፊዎች ምክንያታቸው የአንድን ሰው አገዛዝ በመደገፋቸው ሳይሆን ግራ የተጋቡና እርስ በርሳቸው እንኳን ያልተግባቡት ተቃዋሚዎች የአሜሪካ ተላላኪ ሆነዋል፡፡ አገሪቷንም ወደ አልተፈለገ እልቂት ይወስዷታል በሚል ነው አሁንም ከበሽር የወገኑት፡፡ እኛም በታሪካችን የማይታለፉ የሚመስሉትን አልፈናል፣ የሚገባንን ለውጥ መሻት ግን ከጊዜያችን ጋር መሄድ ነው፡፡ አለበለዚያ አምባገነኖች በሚቆፍሩልን ጉድጓድ ‹‹ካለነርሱማ ይህች አገር ተስፋ የላትም እያልን›› መፍሰስ ብቻ ነው መጨረሻችን፡፡
ከመለስ ሌላ ማሰብ አለመቻል እንደ ሃገርም እንደ ግለሰብም በራሱ ያሳፍራል፡፡ ኢህአዴግ ምሁራንን እውቅና መንሳትና በፍርሃት ውስጥ ቀብሮ ሃገሪቷን የእርሱ ብቻ ያለበት አስመስሏታል በሚለው የምንስማማው ብዙዎች ነን፡፡ (ሃገሪቷን የተቆጣጠረ ሰሞን ያባረራቸውን ምሁራን አስቡ) ተተኪዎችን ስናስብ በሙያቸውና በብቃታቸው እንጂ በተንኮል፣ በጠመንጃ፣ በ‹‹የፈጀውን ይፍጅ›› በጀትና በ’try and error’ ፕሮፓጋንዳ እንዲሁም ጊዜውና የአለም ባንክ ገፍተው ባመጡት ለውጥ መሆን የለበትም፡፡ ለመሪነትም ባይሆን በቅርብ ከምናውቃቸው ብንነሳ የአዲስ አበባ ባለአደራ ቦርድ ከንቲባ የነበሩት አቶ ብርሃኔ ደሬሳን ማን እንደዛ ይሰራሉ ብሎ ጠብቆ ነበር? አቶ አርከበ ሙሉ ነጻነቱ ቢሰጣቸው ኖሮስ ለሥራው ብቁ አልነበሩምን?፣ በዶ/ር እሌኒ፣ በኤርምያስ አመልጋስ ማን ያልተደመመ አለ? ሌሎችን ኢህአዴግ አዳፍኗቸው ነው እንጂ ሕግ ያለበት ሃገር ቢሆንና ሁሉም በነጻነት መስራት ቢችል ስንት ተአምር ባየን ነበር፡፡ አሁንም ተተኪ ማን አለ በሚል ጥያቄ ማንም አምባገነን እንዲሆንብን መፍቀድ የለብንም፡፡ በ‹ሃገር ፍቅር›ና በ‹ልማት› ስም የተጠቀለልነው ይበቃናል፤ ስለ ነጻ ተቋማት እንጂ ስለግለሰብ ማሰብ ይበቃናል፡፡
ጆሴፍ ስታሊን በጊዜው ራሽያን ከጀርመን ወረራ ታድጓታል፡፡ ከዛም አልፎ በርሊን ድረስ ሄዶ ጀርመንን አደብ አስገዝቷል፡፡ በዚህም ራሺያ የዓለም ሃያልነቷን አስመስክራለች፡፡ ከዛም የተሳካ የተባለውን የኒውክሌር ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል፡፡ እኛ አገር እንደ እድሜ ማራዘሚያ ካርድ እንደ ተመዘዘው GTP ስታሊንም Great Plan for the Transformation of Nature ነበረው፡፡ እርሱም እንደማንኛውም አምባገነን የራሱን ስብዕና አጉልቷል፡፡ አንዳንዶች የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ብቻውን ያሸነፈ እስከማለት ሁሉ ደርሰዋል፡፡ እኛጋስ ‹አባይን የደፈረ› አይደል እያልን ያለነው? አሁን ባለንበት ጊዜ ዓለም ለስታሊን የተደበላለቀ ስሜት አለው፡፡ አንዳንዶች አንባገነንና ነፍሰ ገዳይ ሲሉ ሌሎች በጊዜው ሊኖር የሚገባው መሪ ነበር ይላሉ፤ አንዳንዶች አሁንም ይናፍቋቸዋል፡፡ እኛስ?
ስናጠቃልል የራሽያው Pravda እንዲህ ይል ነበር ‹‹Stalin was the greatest agriculturalist, philologist, geneticist, political scientist and military commander›› እኛ ደግሞ ተውሰንም ቢሆን እንዲህ እንላለን፣
"No matter how experienced leaders are, no matter what knowledge and talents they possess, they cannot succeed in replacing the whole collective. The most important principle is that decisions should be based on the experience of many, should be the fruit of collective creation."
“መሪዎች ምንም ዓይነት ልምድ ቢኖራቸው፣ ምንም ዓይነት ዕውቀት እና ክህሎት ቢኖራቸው፣ ሁሉንም ጠቅለው በመተካት ሊሳካላቸው ግን አይችልም፡፡ እጅግ ጠቃሚው መርኅ፣ ሕዝባዊ ውሳኔዎች የጋራ ልምድን መሰረት ያደረገ እንዲሁም የጋራ ፈጠራ ፍሬዎች መሆን ይገባቸዋል፡፡”
No comments:
Post a Comment