Friday, September 16, 2016

በይነመረብ እና አፋኝ መንግሥታት


ኢንተርኔት ወይም በይነመረብን በየቀጠናው እና በየመተግበሪያው ዓይነት ብልጭ ድርግም በማድረግ የመረጃ ፍሰትን በሚፈልገው መልኩ ለመቆጣጠር ይፋዊ እንቅስቃሴ የጀመረውን የኢትዮጵያ መንግሥት የበይነመረብ ቁጥጥር (censorship) አካሔድ በመታዘብ አጥናፉ ብርሃኔ አገራችን ውስጥ ያለውን የበይነመረብ አፈና ከዓለምዐቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር በዚህ መጣጥፉ ግልጥልጥ አድርጎ ያሳየናል

አፋኝ ወይስ አዳኝ?

በ2014 (እ.ኤ.አ.) በቱርክ አንካራ ከመናገር ነጻነት መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ‹Committee to Protect journalists› (ሲ.ፒ.ጄ.) እና ‹International Press Institute› (አይ.ፒ.አይ.) ጋር ስብሰባ የተቀመጡት ጋዜጠኞችን በማሰርና የተለያዩ ሚድያዎችን በማፈን የሚታወቁት የቱርኩ መሪ ሪሴፕ ጣይብ ኤርዶሃን ለብዙዎች አማራጭ ሚዲያ እየሆነ የመጣውን የማኅበራዊ ሚድያ ወይም ኢንርኔትን (በይነመረብ) አንደሚጠሉ በግልጽ ተናግረው ነበር።

ኤርዶሃን ይህን ከተናገሩ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በገዛ ወታደሮቻቸው መፈንቅለ መንግሥት ተሞከረባቸው። የቱርክ ወታደሮች ከካምፓቸው ወጥተው የቱርክ መንግሥት አፈቀላጤ የሆነውን የቱርክ ራዲዮ ጣብያና ቴለቭዥን ማሰራጫን (TRT) ተቆጣጠረው፣ የመፈንቅለ መንግሥቱን ዜና አወጁ። ኤርዶሃን ይህን እርምጃ አውግዘው ደጋፊዎቻቸውን ለማሰባሰብ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ከሁለት ዓመት በፊት “ጠላቴ” ብለው የፈረጁት በይነመረብ (ኢንተርኔት) ሥልጣናቸውንና ሕይወታቸውን ለማዳን ብቸኛ አማራጫቸው ነበር።

በቱርክ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ወታደሮች የተረሳው የአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ በኤርዶሃን ታማኝ ደጋፊዎች እጅ ስለነበር በይነመረብን ተጠቅመው ሕዝቡ “የቱርክን ዴሞክራሲ” ከመፈንቅለ መንግሥት ለመከላከል አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ከተደበቁበት ቦታ ሆነው ነበር ብሔራዊ ጥሪ ያቀረቡት። የሚድያ ጠላት ተብለው የሚፈረጁት ኤርዶሃን መፈንቅለ መንግሥት እየተደረገ ባለበት ሰዐት ደጋፊዎቻቸውን ለማስሰባሰብ በበይነመረብ ከቲውተር (Twitter) እስከ ፌስታይም (Facetime)  የተጠቀሙ ሲሆን በአንድ ወቅት በቱርክ መንግሥት ከፍተኛ የታክስ ቅጣት የተጣለበት ዶሃን ሚድያ ግሩፕ (Doğan Media Group) እና የታይም ዋርነር (Time Warner) ጥምረት የሆነው ሲ.ኤን.ኤን. ተርክ (CNN Turk) የዜና ተቋም ጋር በቀጥታ በአይፎን ስልክ የሚሠራውን ፌስታይም (Facetime) አፕሊኬሽን በመጠቀም ቃለ ምልልስ አርገው ሕዝባቸው ለመፈንቅለ መንግሥቱ እንቢታውን እንዲገልጽ ብሔራዊ ጥሪ በማድረግ የታንክን አፈሙዝ በበይነመረብ ወይም ኢንተርኔት ጠምዝዘው ሕይወታቸውንም ሥልጣናቸውንም ከአደጋ ታድገዋል።

በይነመረብ ሥልጣን አልለቅ ብለው ወንበር ላይ ዐሥርት ዓመታትን ሙጭጭ ብለው ለተቀመጡ አምባገነን መሪዎች ጠላት ነው። በቅርቡ በኡጋንዳ በተደረገው አገራዊ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት “ምርጫው ሠላማዊና የተረጋጋ ሆኖ እንዲጠናቀቅ” ወይም  በትክክለኛው ትርጉሙ፣ የተቃዋሚ ኃይሎችን ድምፅ ለማፈን የዩጋንዳ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ማኅበራዊ ሚድያዎችንና የአጭር ጽሑፍ መለዋወጫ መተግበሪያዎችን አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ ነው። ይህ ዓይነት እርምጃ በአምባገነን መንግሥታት የሚወሰደው በአገሪቱ ውስጥ በመሪው አካል የሚወሰዱ ሕግን የጣሱ እርምጃዎች ወደ ሚድያ ወጥተው ለዓለም እንዳይደርሱ ነው። የተለያዩ የሰብኣዊ መብት አራማጆችም ምርጫው ይህ ግድፈት ታየበት፣ መንግሥት ይህን አስሯል፣ ምርጫውን አጭበርብሯል እና አደባባይ ወጥተን ደምፃችንን ማሰማት አለብን የሚሉ መልዕክቶች ከማስተላለፍ ይልቅ፣ መንግሥት ይህን ደረገጽ ዘግቷል፣ ይህን ሚድያ አፈነ ከማለት ውጪ ስለምርጫው ወቅታዊ ሁኔታ እንዳይከታተሉ አድርጓቸዋል።


በገዢዎች ፍላጎት የቀጨጨው በይነመረባችን

በበይነመረብ ተጠቃሚ ቁጥር ከዓለም አገራት ግርጌ የምትገኘው አገራችን ይህን አፈና የጀመረችው ገና በቴክኖሎጂም ጅማሬ ማግስት ነው። አንድም አፍሪካዊ አገር ስለ ድረገፅ መዘጋት አንድም ግንዛቤ ባልያዘበት ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ግን ይተቹኛል የሚላቸውን ሚድያዎች በኢትዮጵያ እንዳይታዩ በማድረግ በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ነበር። በአንድ ወቅት እስከ ሦስት መቶ የሚደርሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ድረገጾች በኢትዮጵያ መንግሥት ታፍነው የነበሩ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ መቀመጫቸውን ከአገር ውጪ ያደረጉ የዜና ድረገጾችና በሕጋዊ መንገድ አገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልሳናትም ተዘግተው ነበር። ይህ የበይነመረብ ሚድያን የመዝጋት ዘመቻ ለመንግሥት ቅርበት አላቸው ወይም የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መካሪ ናቸው እየተባሉ በአደባባይ የሚታሙትን እንደ ሪፖርትር ያሉትን ጋዜጣዎች ሳይቀር ለጥቂት ቀናትም ቢሆን አካቶ ነበር።

ዋና መቀመጫውን ሰሜን አሜሪካ ያደረገውና ነጻ ተቋማትን በመደገፍ እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶችንና ሪፖርቶችን በማውጣት የሚታወቀው ፍሪደም ሀውስ (Freedom House) እ.ኤ.አ. በ2015 የኢንተርኔት ነጻነት ሪፖርት (Net Freedom) ኢትዮጵያን የኢንተርኔት ነፃነት የሌለባት አገር ሲል የጠቀሳት ሲሆን የኢንተርኔት ተደራሽነትም በሪፖርቱ ከተጠቀሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት (95 ሚሊዮን) 2.9 በመቶው ብቻ ተጠቃሚ እንደሆነ ይገልጻል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ውሱን የበይነመረብ ተጠቃሚ ፈተና በዚህ ብቻ የበቃ አይደለም። ሐሳብን ለመግለጽ ብቸኛ አማራጭ እየሆነ የመጣው የበይነመረብ ሚድያ “የኮምፒውተር ወንጀሎች” የሚል ሌላ አፋኝ አዋጅ መጥቶበታል። ይህ አዋጅ በግንቦት ወር መጨረሸ ከፀደቀ በኋላ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች “ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማፈን የወጣ ሕግ” ሲሉት ከርመዋል። ሕጉ በዋነኛነት የማኅበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚውን ያሸማቀቀ ሲሆን፤ በኮምፒውተር ወንጀል አዋጁ አንቀፅ 14 ላይ የተጠቀሰው ወንጀል (‹በማንኛውም ሰው ሆነ ብሎ በኅብረተሰቡ መካከል የፍርሐት ስሜት፣ አመፅ፣ ሁከት ወይም ግጭት እንዲፈጠር የሚያነሳሳ ጽሑፍ፣ ተንቀሳቃሽ ምስል፣ ድምፅ ወይም ማንኛውንም ሌላም ምስል በኮምፒዩተር ስርዓት አማካኝነት ያሰራጨ እንደሆነ በእስራት ይቀጣል፡፡) ብዙዎች በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ይጋፋል ሲሉ ተችተውታል።

“No Access #OromoProtests

የኢንተርኔት ሚድያዎችን በማፈን ከአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይና ክልላዊ በሆነ መንገድ ማኅበራዊ ድረገጾችን ማፈን ጀምሯል። ከ7 ወር በፊት በአዲስ አበባ - ኦሮምያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በተነሳውና እስካሁንም እልባት ያላገኘው ሕዝባዊ ተቃውሞን እንቅስቃሴ አደባባይ በማውጣት የማኅበራዊ ሚድያዎች ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም። የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዷቸውን ኢሰብኣዊ ድርጊቶች በአደባባይ ለማጋለጥ ፌስቡክን የመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረገጾች አገልግሎት ላይ ውለዋል፤ እስከ አሁንም እየዋሉ ነው። ሕዝባዊ ጥያቄዎችን የማፈን መጥፎ ሥም ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሕዝባዊ አመፅ በተነሳበት በኦሮምያ ክልል ብቻ ማኅበራዊ ድረገጾችን ለማፈን ጊዜ አልፈጀበትም ነበር። በኦሮምያ ክልል ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቫይበር እና ዋትስአፕ የመሳሰሉ የአንድሮይድ ሞባይል መተግበሪያ (Android Mobile Applications) መሣሪያዎች እንዳይሠሩ ዕቀባ የተጣለባቸው ሲሆን፤ በክልሉ  የነበረውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ባይባልም በቂ ሽፋን እንዳያገኝና የመረጃ ፍሰት እንዲቀንስ አድርጎታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢንተርኔትን ጂኦግራፊያዊ በሆነ መንገድ የማቀብ ወይም የመዝጋት ሥራ በመንግሥት እየተካሔደ ሲሆን፤ ኦሮምያ ክልል ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ተለይቶ የዚህ ሰለባ ከሆነ ወራቶች ተቆጥረዋል። የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ያነጋገራቸው በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል፣ የኢንተርኔት እና ዌብ ባለሙያና መምህር የሆኑት አቶ ወንድማገኝ ደስታ ስለ ማኅበራዊ ድረገጾች ቦታ እየለዩ መዘጋት ሲያብራሩ “ኢትዮጵያ አንድ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ስላላትና የሁሉም ክልሎች እንቅስቃሴ በማዕከላዊነት ስለሚመራ ከአንድ ክልል የሚመጣውን ጥያቄ ዋናው የማዕከሉ ሰርቨር እንዳያስተናግድ ማድረግ እጅግ በጣም ቀላል ነው” ይላሉ፤ ሲቀጥሉም “ከኔትወርክ አስተዳዳሪው ውጩ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያቋርጥ አካል የለም፡፡ የኔትወርክ አስተዳዳሪው (ኢትዮ ቴሌኮም) ኢንተርኔትን ለሟቋረጥ ሦስት መንገዶችን ሊጠቀም ይችላል። አንደኛው፣ አካላዊ በሆነ መንገድ መሣሪያው እንዳይሠራ ማድረግ ሲሆን (no brainer approach) ተብሎ ይጠራል። እንዲህ ዓይነቱ ዕቀባ የኢንተርኔትን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የሚያቋርጥ ሲሆን በ12ኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብሔራዊ ፈታና ወቅት ኢንተርኔትን ለማቋረጥ መንግሥት ይሄን መንገድ አልተጠቀመም ነበር። መንግሥት ለዚህ የተጠቀመው ሦስተኛ ላይ የምገልጸውን መንገድ ነው፡፡ ሁለተኛው መንገድ፣ የአንድ ክልልን ወይም ተቋምን ቦርደር ጌት ዌይ ፐሮቶኮል (Border Getaway Protocol) በመዝጋት ከአንድ አካባቢ የሚመጣውን ጥያቄ  ከመቆጣጠርያ ማዕከሉ እንዳይወጣ እዚያው የሚያስቀር ነው። ሦስተኛውና በአብዛኛው ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውለው ግን (content control software) የኢንተርኔት መቆጣጠሪያ መተግበሪያን በመጠቀም ሲሆን፣ ይሄ መተግበሪያ የተሠራውም የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመገደብ ወይም ጭራሹኑ ለመዝጋት ነው” ይላሉ - አቶ ወንድማገኝ። በምሳሌም ሲያስረዱ “ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ክልሎች ውስጥ በአንዱ ላይ ብቻ ፌስቡክን እንዳይሰራ ለማድረግ ሁሉም ክልሎች ከማዕከላዊው የቴሌኮም ኔትወርክ መቆጣጠሪያ ጋር የተያያዙ ስለሆነ ፌስቡክን ጨምሮ የተመረጡና በአካባቢው ነዋሪ እንዳይጎበኙ የሚፈለጉ ዌብሳይቶችን አድራሻ በማዕከላዊ የኢንተርኔት መቆጣጠሪያ መተግበሪያ (content control software) ላይ ሙሉ አድራሻቸውን በማስቀመጥ የአካባቢው ነዋሪዎች የድረገጹን አገልግሎት እንዳያገኝ ማድረግ ይቻላል ይላሉ። በሞባይል ላይ የሚጫኑ የተለያዩ መተግበሪያዎች (Applications) ማለትም ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቫይበር እና ዋትስአፕ የመሳሰሉት እንዳይሠሩ ለማድረግ የመተግበሪያዎቹን መለያ (signature) በመውሰድና የኢንተርኔት መቆጣጠሪያ መተግበሪያ ላይ በማስቀመጥ እንዳይሠሩ ማድረግ በመንግሥት ቁጥጥር ስርና አንድ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ብቻ ላላት አገር ጥረት የማይጠይቅ ሥራ ነው” ይላሉ - የኢንተርኔትና ዌብ ባለሙያ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ ደስታ።

የማኅበራዊ ሚድያዎች አፈና ይቀጥላል!?

በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት በተለያዩ አፋኝ አዋጆች ምክንያት እየተጣሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሐሳብን እንደፈለጉ መናገር ከምንጊዜውም በላይ አስፈሪ እየሆነ ነው። የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ኦሮምያ ክልል ሕዝባዊ ተቃውሞ በተነሳበት ወቅት በፌስቡክ ገጹ በጻፋቸው ጽሑፎች “በኦሮሚያ የተነሳውን አመፅ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ቀስቅሰሃል” የሚል ክስ ቀርቦበት በሽብር ወንጀል ተከሶ ዘብጥያ ከወረደ ወራቶች ተቆጥረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብት ጉባኤ (United Nation Human Rights council) በይነመረብን መጠቀም እንደ ሰብኣዊ መብት ሊካተት ይገባዋል ብሎ የስምምነት ደንብ (resolution) ያስተላለፈ ሲሆን ይህ የስምምነት ደንብ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በተደጋጋሚ በመጣስ የሚታወቁትን  እንደ ሩሲያንና ኢራንን የመሳሰሉ አገራት ያስኮረፈ ሲሆን ይህ ደንብ ‹አይፅደቅ› ሲሉም ድምፃቸውን በተቃራኒ ሰጥተው ነበር። በጉባኤው የፀደቀው ሕገ ደንብ አባል አገራት ምድር ላይ ያለውን ሰብኣዊ መብት ብቻ ሳይሆን ኢንተርኔት (online) ላይ መጠበቅ አለበት የሚል ሲሆን፤ ይህ ማለት ሐሳባቸውን በተለያዩ የኢንተርኔት ሚድያ ላይ የሚገልጹ ሰዎች መብታቸው እንዲጠበቅ የሚያስገድድ ነው። 

ጋዜጠኖችንና ብሎገሮችን በማሰርና የተለያዩ የሰብኣዊ መብቶችን የመጣስ መጥፎ ሥም ያለው የኢትዮጵያ መንግሥትም ሕገ ደንቡን አልደግፍም ብሎ ድምፀ-ተዐቅቦ ያደረገ ሲሆን፣ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም በአገሪቱ ሙሉ ለሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥ ለተባበሩት መንግሥታት ሰብኣዊ መብት ካውንስል ሕገ ደንብ ተገዢ አለመሆኑን አስመስክሯል። በኢትዮጵያ እየተጠናከረ የመጣው የኢንተርኔት ቁጥጥር ቀን ተቀን እየጨመረ ሲሆን የመሻሻል ተስፋ እየታየበት አይደለም። ከቱርኩ ሪሴፕ ጣይብ ኤርዶሃን እስከ ትንሿ ኢትዮጵያ ያሉ የዓለማችን አምባገነን አገራትና መሪዎች ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ የመረጃ ፍሰትን መገደብ ሁነኛ እርምጃ መሆን እንዳለበት ስለተረዱና የመረጃ ፍሰትን ማቆም የሚቻለው በኢንተርኔትን መቃብር ላይ ስለሆነ ኢንተርኔትን በዓይነቁራኛ እየተከታተሉት ይገኛሉ፡
---
ይህ ጽሑፍ ‹ውይይት› መጽሔት 8ኛ እትም ላይ የወጣ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment