#Ethiopia #FreeZone9Bloggers
አንድ አመት ከሦስት ወር በእስር ላይ ያሉትና በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን ለ31ኛ ጊዜ ዛሬ ሐምሌ 13/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ለ32ኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ ይከላከሉ ወይስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ይሰናበቱ የሚለውን ለመወሰን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ የደረጃ ምስክሮች ቃል በጽሑፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር አልተያያዘልኝም በሚል መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት እንዳልቻለ በመግለጽ አራቱ ጦማርያን ላይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ እንደገለጸው እስካሁን በ30/07/07 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወቅት የተሰሙት የአቃቤ ህግ የደረጃ ምስክሮች ቃል በጽሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር አልተያያዘም፡፡ በተጨማሪም ሰኔ 8/2007 ዓ.ም በአንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ በቀረበው የአቃቤ ህግ ማስረጃ (ሲ.ዲ) ላይ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን ላይ የተከሳሽ ጠበቆች ያቀረቡት አቤቱታም እንዲሁ በጽሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር እንዳልተያያዘ ተገልጾዋል፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ዛሬ ይሰጠዋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን ብይን በማራዘም የጦማርያኑን ጉዳይ ማጓተቱን ቀጥሏል፡፡ በዚህ መሰረትም ሐምሌ 22/2007 ዓ.ም የተጠቀሱት የምስክሮች ቃል እና የጠበቆች አቤቱታ በጽሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር መያያዙን ‹‹ለመጠባበቅ›› ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዚህም በተከሳሾች ላይ የሚሰጠው ብይን ማራዘሙ ተመልክቷል፡፡ ይህን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ‹‹450 ቀናት በእስር ቆይተናል፤ እኛም ቤተሰቦቻችንም እየተጉላላን ነው፡፡ ይህን ከግምት በማስገባት ብይን ለመስማት አጭር ቀጠሮ ይሰጠን›› ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለብይን ሳይሆን ‹ከመዝገቡ ጋር መያያዙን ለመጠባበቅ› ‹‹አጭር›› ያለውን ቀጠሮ ለሐምሌ 22/2007 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ሐምሌ 1/2007 ዓ.ም ድንገት የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው ሳይደርስ ‹‹ክሳችሁ ተቋርጧል›› በሚል ከእስር የተለቀቁት ጦማርያንና ጋዜጠኞች ዛሬ በቀጠሯቸው መሰረት ችሎት ፊት ቀርበዋል፡፡ ተፈችዎቹ ፍርድ ቤቱ በይፋ እንዳላሰናበታቸው በማሰብ ‹‹በእነ ሶልያና ሽመልስ!›› የሚለው የዳኞቹ ጥሪ ሲሰማ በእስር ላይ ከሚገኙት ጓደኞቻቸው ጋር ከመቀመጫቸው በመነሳት ችሎት ፊት የቀረቡ ሲሆን፣ ዳኞቹ በመካከልም ‹‹የሌሎቻችሁ ክስ ተቋርጧል›› በማለት አልፈዋቸዋል፡፡
ሆኖም ግን አምስቱ ተፈችዎች ለእስር በተዳረጉበት ወቅት ቤታቸው ሲፈተሽ በኤግዚቢትነት እና በሰነድ ማስረጃነት በፖሊስ የተያዙባቸው እቃዎቻቸው እንዲመለሱላቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸው ተገልጾዋል፡፡ ተፈችዎቹ አቤቱታቸውን ቀደም ብለው በጽ/ቤት በኩል አስገብተዋል፣ ፍርድ ቤቱም አቤቱታቸው እንደደረሰው በመግለጽ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት አስረድቷል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ ከቂሊንጦ እስር ቤት የቀረቡት በፍቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና አቤል ዋበላ ያለውን ኢ-ፍትሃዊነት ለመቃወም ጥቁር ቲሸርት ለብሰው ፍርድ ቤት ለመቅረብ ሞክረው የነበር ቢሆንም በእስር ቤቱ አስተዳደር መከልከላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ በርካታ የጦማርያን ወዳጆች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ጋዜጠኞችና ዲፕሎማቶች ተከታትለውታል፡፡ በቅርቡ የእስር ጊዜዋን አጠናቅቃ ከእስር የተፈታችው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙም ችሎቱን ታድማለች፡፡
የዞን9 ማስታወሻ
አራቱ በእስር ላይ የሚገኙት ጦማርያንን እና ቤተሰባቸውን በማጉላላት እና ፍትህ በመንፈግ የሚሰበር ሞራል የላቸውም ፡፡ ሆነ
ተብሎ በሚደረገው በዚህ የፓለቲካ ውሳኔን የመጠበቅ ሂደት የሚባክነው የወጣቶች እድሜ አሁንም ባይሆን አንድ ቀን የህሊና ዋጋ እንደሚያስከፍል ለዳኞች ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ ቀላሉ እርምጃ ቀሪውን የሌለውን ማስረጃ በመመርመር ሰበብ ከማጉላላት ይልቅ አራቱን ጦማርያን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ማሰናበት ነው ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ባለፈው አንድ አመት ከሶስት ወር አጋርነታችሁን ላሳያችሁ በዛሬው ብይን ወቅትም ከፍተኛ ድጋፍ ስትሰጡን ለነበራችሁ የዞን9 ነዋርያን ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
No comments:
Post a Comment