የኛ ፕሬስ ጋዜጣ ‹‹የኮንደምኒየም እጣ ውሃ በላው!›› የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡ ‹‹… 128 ሰዎች ሁለትና ከሁለት በላይ የኮንደሚኒየም ቤቶችን ወስደዋል፣ ትክክለኛውን ተመዝጋቢ በመሰረዝና በሌላ በመተካት የሙስናና የዝምድና ሌብነት ተጧጡፏል፡፡…›› የሚሉ ችግሮችን የነቀሰው ዜና ምንጩ የመንግስት መስሪያ ቤት ነው፡፡ ‹‹… የፌዴራል የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ጥናት ያደረገ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ አደረኩት ካለው ጥናት መኖሪያ ቤቶቹን ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ ሂደት ላይ ለሙስና የተጋለጡ ስምንት የሚደርሱ አሰራሮችን አጋልጧል፡፡…››
‹‹ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጪ ያለው ሁሉ የጥፋት መንገድ ነው የሚል አመለካከት ነበረኝ›› ያሉት አቶ ገብሩ አስራት ለየኛ ፕሬስ ጋዜጣ ነው፡፡ አቶ ገብሩ ከጋዜጣው ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ቀነጫጭበን እንመለከታለን፡-
‹‹… እኛና ሌሎች ተቃዋሚዎች የምንሄድበት አቅጣጫ ይለያያል፡፡…››
‹‹… ከኢሕአዴግ ከወጣን በኋላ… ዴሞክራሲ ማለት ራሱ ምንድን ነው? ዴሞክራሲ ያለነፃ ጋዜጦች? ዴሞክራሲ ያለ ሲቪል ማሕበረሰብ? ያለነፃ የፍትሕ ስርዓት ሊኖር ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄዎችን አንስተናል፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሁሉም ተቋማት በአንድ ፓርቲ ስር መግባት አለባቸው የሚል አስተያየት አለ፡፡…››
‹‹…ልማትና ዕድገት ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ዕድገት ከየትም መጥቶ ጥቂት ሚሊየነሮችን ሊያስገኝ ይችላል፡፡ እነዚህ ሰዎች ገንዘብ ዘርፈው ካጠራቀሙም ዕድገት ነው፡፡…››
‹‹… እስቲ ቦሌ ሂዱና ተመልከቱ፡፡ ያ ሁሉ ሕንፃ የማነው? ምን ያህሉ እንዳሉ መቁጠር ትችላላችሁ፡፡ በመንግስት ስር የሚተዳደር ሰው ከ5 ሺህ እና 6 ሺህ በላይ አያገኝም፡፡ በዚህ ገንዘብ ልጆችን እንኳን ማስተማር አይቻልም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ልጆቻቸውን ውጭ አገር ልከው እያስተማሩ ነው፡፡ በመንግስት ሠራተኛ ደሞዝ ይሄ ሁሉ ሀብት ሊገኝ ይችላል ወይ? ...››
‹‹… [የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ሳሉ የግል ጋዜጦችን በተመለከተ ‹ትግራይ የማንም ቆሻሻ ማራገፊያ አትሆንም› ስለማለታቸው] ሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የግል ጋዜጦች ፋይዳ የላቸውም የሚል አቋም በፓርቲ ደረጃ ይዘን ነበር፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው ትክክለኛው አቅጣጫ ከዚያ ውጪ ግን የጥፋት መንገድ ነው የሚል እምነት ነበረን፡፡…››
የኛ ፕሬስ ቴዲ አፍሮ ሁለት ድግሶችን በአንድ ሳምንት መደገሱን ጠቅሶ ባቀረበው ዘገባ ላይ ‹‹... ባለፈው ቅዳሜ በጣይቱ ሆቴል በተከናወነው የምስጋና የምሳ ግብዣ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ በወቅቱ አንድ ትልቅ ስብሰባ አቋርጠው ወደ ግብዣው እንደመጡ ከተናገሩ በኋላ ‹ይህንን ያደረግኩት ከእግዚአብሔር እና ከቴዲ አፍሮ ጥሪ ላይ መቅረት ያስቀስፋል› በሚል የተቀኘ የተጋነነ አድናቆታቸውን እንደሰነዘሩ ለመገንዘብ ተችሏል›› ብሏል፡፡
ምራቂ /ምርቃት/
የኛ ፕሬስ ጋዜጠኞች ከኢትዮ ቻናል ተገንጥለው ነው የራሳቸውን ጋዜጣ የከፈቱት፡፡ ከኢትዮ ቻናል ሲወጡ ‹ሰዓት እላፊ› የተሰኘች ተነባቢ አምዳቸውን ከነካርቱነኛዋ ይዘዋት ወጥተዋል፡፡ ይቺ አምድ የ‹‹ሴተኛ አዳሪዎችን›› ቃለ ምልልስ ይዛ የምትወጣ ሲሆን ከግርጌዋ ‹‹ራስዎንና ቤተሰቦን ከኤችአይቪ ኤድስ ይጠብቁ፤ የዚህ ገፅ ስፖንሰር፡- ሰላም ባርና ሬስቶራንት (ሰበታ)›› የሚለውን ሲያነቡ ፈገግታ ታጭራለች፡፡
* *
‹‹ኢትዮ ቴሌኮም ዌብሳይቶችን የሚገድብ ኔትወርክ እየዘረጋ ነው›› ያለው ደግሞ መሰናዘሪያ ጋዜጣ ነው፡፡ በዝርዝሩም ‹‹በኢትዮጵያ በብቸኝነት የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጠውና በኢትዮጵያ መንግስት የሚተዳደረው ኢትዮ ቴሌኮም ግለሰቦችና ድርጅቶች በኢንተርኔት የሚለዋወጧቸውን መረጃዎች እየለጠፈ የሚመረምርና እንደአስፈላጊነቱ ዌብሳይቶችን የሚገድብ ቶር የተባለ ኔትወርክ እየዘረጋ መሆኑን ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደር የተባለ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን አስታወቀ፡፡…›› (በነገራችን ላይ መሰናዘሪያ ቶር በማለት የገለጸውን ዊኪፔድያ እንዲህ ሲል ይበይነዋል… Tor (short for The onion router) is a system intended to enable online anonymity. Tor client software routes Internet traffic through a worldwide volunteer network of servers to conceal a user's location or usage from anyone conducting network surveillance or traffic analysis. በሌላ በኩል የቶር ፕሮጀክት ድረአምባ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ ታግዷል፡፡)
መሰናዘሪያ በሌላ ዜና ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ ድንበር ተሸጋሪ ጉዲፈቻ በስፋት ከሚካሄድባቸው አስር የአፍሪካ ሃግሮች በሁለተኛ ደረጃ መቀመጧን በመዲናችን በአዲስ አበባ በተካሄደው በአምስተኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ሕፃናት የፖሊሲ ኮንፈረንስ ላይ የቀረቡ መረጃዎች አመለከቱ፡፡…›› ብሎ ዘግቧል፡፡
* * *
ያለዕለቱ ዘግይቶ ረቡዕ የወጣው ፍኖተ ነፃነት ‹‹በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የተደረገው የማደራጀት ሙከራ እስረኞችን አስቆጣ›› የሚል ዜና በፊት ገጹ ይዞ ወጥቷል፡፡ ሲተነትነው ‹‹ቃሊቲ በሚገኘው ማረሚያ ቤት የሚገኙ እስረኞች 1ለ25 እንዲደራጁ ታዘው አብዛኛዎቹ መደራጀት እንደማይፈልጉ አቋም በመያዛቸው አለመግባባት መፍጠሩን የዜና ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡… እስረኞቹ የእያንዳንዱን እስረኛ የ24 ሰዓት ውሎ የሚገመግም አደረጃጀት እንዲታቀፉ ቢጠየቁ እምቢተኛ ሆነዋል፡፡…››
ፍኖተ ነፃነት ‹ቀጣዩ የአዲስ አበባ ምርጫና ከመጋረጃው በስተጀርባ የታፈኑ እውነቶች› በሚል በዳንኤል ተፈራ የተጻፈውን ሰፊ ሐተታ አስነብቦን ሲያበቃ እንዲህ እየታዘበ ይደመድማል፡፡ ‹‹….አሁንም በምርጫው መሳተፍ የሚፈልጉ ተቃዋሚዎች ከመጋረጃው በስተጀርባ ምን ደባ እንዳለ አያውቁም፡፡ ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ አያውቁም፡፡ ግን ይገምታሉ መስከረም ይካሄድ ይሆን? አይ! እንደሱ አይሆንም፡፡ ጥር! ጥር ምን አለ? አዲስ አበባ 126ኛ ዓመቷን በምትይዝበት ይሆን? ይሄ ካልሆነ ያው ምርጫ የሚካሄደው በግንቦት ነው፡፡ አዎ! ግንቦት ግንቦትም ላይሆን ይችላል!... ታድያ መቼ ይሆን?... ግምቱ ይቀጥላል፣ መላ ምቱ ይቀጥላል፣ ከመጋረጃው በስተጀርባም ዳንሱ ይቀጥላል፡፡››
ባለፈው እሁድ በ10 ሰዓት ላይ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ለፖለቲካ እና ሕሊና እስረኞች የሻማ ማብራት ስነስርዓት ተካሄዶ ነበር፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም ሲሆኑ ያደረጉትን ሙሉ ንግግር ፍኖተ ነፃነት አቅርቦት ነበር፡፡ በንግግራቸው መደምደሚያ ላይ ዶ/ር ያዐቆብ ‹‹… አንድ ሕዝብ የሚገባውን መንግሥት ያገኛል በእንግሊዝኛው (a people gets a government it deserves) ይባላል፡፡ እኛም ሕብረት ፈጥረን በአንድነት ቆመን በቆራጥ መንፈስ ኢሕአዴግን ለመተካት እስካልተጋን ድረስ ይህ አሁን በሥልጣን ያለው አምባገነን መንግሥት ይገዛናል፡፡ አመሰግናለሁ ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘላለም ትኑር፡፡››
ፍኖተ ነፃነት ሌላም አለው፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ መምህራንን ለማባረር አዲስ ስልት ቀየሰ›› በሚል ርዕስ ስር በጻፈው ዜና ‹‹… የኢሕአዴግ አባል ሆነው በስራ ማቆም አድማው ያልተሳተፉ መምህራን “A”፣ የኢሕአዴግ አባል ሆነው በስራ ማቆም አድማው የተሳተፉ “B” እንዲሰጣቸው፣ የኢሕአዴግ አባል ሳይሆኑ በስራ ማቆም አድማው ያልተሳተፉ “C” እና የኢሕአዴግ አባል ሳይሆኑ በአድማው የተሳተፉ መምህራን “D” በመስጠት በመጨረሻው ምድብ የተቀመጡትን መምህራን ከስራቸው እንዲባረሩ እንዲደረግ ለየት/ቤቱ ርዕሳነ መ/ራን ትዕዛዝ መተላለፉን ታማኝ ምንጮቻችን ለሪፖርተራችን ገልፀዋል፡፡…››
* * *
ሰንደቅ ጋዜጣ በፊት ገጹ ‹‹ቀጣዩ በጀት የ26.6 ቢሊየን ብር ጉድለት ያሳያል›› ሲል ዜናውን ይጀምራል፡፡ ‹‹ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የ2005 አገራዊ ረቂቅ በጀት ትላንትና ለፓርላማ ያቀረበ ሲሆን ከአጠቃላይ በጀቱ በገቢና ወጪው መካከል የ26 ቢሊየን ብር 634 ሚሊየን 956 ሺህ 84 ብር ጉድለት መታየቱ ታወቋል፡፡›› ለቀጣዩ ዓመት የቀረበው በጀት ከ137 ቢሊየን ብር በላይ ሲሆን የተጠቀሰው ጉድለት ገሚሱ ከውጪ፣ ገሚሱ ደግሞ ከሃገር ውስጥ በሚገኝ በድር ለመሸፈን መታቀዱን ጋዜጣው ገልጧል፡፡
* * *
ሪፖርተር በረቡዕ ዕለት እትሙ ‹‹ሚድሮክ የሚገነባቸውን መንገዶች ሊነጠቅ ነው›› ሲል ዘግቧል፡፡ ‹‹ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የሚገነባቸው ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶች በተገቢው ጊዜ ባለማስረከቡ፣ መንገዶቹን ሊነጠቅ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ በዚህ ምክንትም ሚድሮክ በከተማው የመንገድ ግንባታ ጨረታ እንዳይሳተፍ ተደርጓል፡፡…››
ሪፖርተር የፕሬስ አሳታሚዎች ማኅበር መመስረቱን በዘገበበት ዜና ደግሞ ‹‹…አሳታሚዎቹ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ለማዋጣት ቃል ገብተዋል፡፡ ማኅበሩን በበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ለማስመዝገብ በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡
‹‹አሳታሚዎቹ ማኅበር ከመመስረታቸውም በተጨማሪ ‹የኢትዮጵያ ሚዲያ ዴቨሎፕመንት ፈንድ አክሲዮን ማኅበር› ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ሲመሰረት ማንኛውንም ዓይነት ሕጋዊ የሕትመት ሥራዎችን የሚያከናውንና የሚዲያ ሥራን የሚያቀላጥፍ ኩባንያ እንደሚሆን ታወቋል፡፡›› በማለት ዘግቧል፡፡
‹‹ድምፅ አልባው ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን›› በሚል ርዕስ ጋዜጣው በበኃይሌ ሙሉ ስም ባወጣው ሐተታ ላይ ‹‹…የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በየዓመቱ የሚያወጣውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለተመለከተው ሰው ኢሰመኮ የሰብአዊ መብት ተቋም ሳይሆን የሥልጠና ማዕከል ሊመስለው ይችላል፡፡ በአገሪቱ ተፈጽመዋል ስለተባለ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከመግለጽ ይልቅ ለዚህን ያህል ቀን ከእንዲህ ዓይነት አካላት ጋር አውደ ምክክር ተካሂዷል፣ በዚህን ያህል ጊዜ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፣ በሚሉ ጥቃቅን ጉዳዮች የታጨቀ ሪፖርቶችን ሲያቀርብ ማየት የተለመደ ነገር ነው፡፡…›› የሚል ጽሁፍ አስነብቧል፡፡
* * *
ፍትሕ ጋዜጣ ‹‹ሁለት ጋዜጣ አዟሪዎች ‹ፍትሕ ጋዜጣ ሕገ-ወጥ ነው እንዳትሸጡ› ተብለን ነበር አሉ፤›› ብሎ የፍትሕ ጽ/ቤት ኃላፊዋ መብርሀት ገ/ሚካኤል የፍትሕ ጽ/ቤት ኃላፊ ደግሞ ‹‹ጋዜጣው የተያዘው ሕጋዊ ነው፣ አይደለም በሚል ሳይሆን በእግረኛ መንገድ ላይ ተዘርግቶ ስለተገኘ ነው›› ብለው ማስተባበላቸውን አስነብቧል፡፡
ተመስገን ደሳለኝ ‹‹የጠፋው ትውልድ እና የታህሪር ናፍቆት - ፪›› ባሰኘው እና ከባለፈው ሳምንተ በቀጠለው መጣጥፉ ‹‹…በግሌ [ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ታህሪርን] በእርግጠኝነት ናፍቀዋል ከሚሉት ወገን እሰለፋለሁ፡፡…›› ብሏል፡፡ መለስ ራሳቸው የታህሪሩን ዓይነት አብዮት በኢትዮጵያ እንደሚፈጠር ገብቷቸዋል ሲል ጋዜጠኛ ሪቻርድ ዳውደንን አጣቅሶ የተከራከረው ተመስገን፤ የታህሪር ናፍቆትን ያመላክታሉ ያላቸውን ዘርዝሯል፡፡ እነርሱም፡-
- ፀረ-መጅሊስ እንቅስቃሴ፣
- ማሕበራዊ ድረገጾች ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣
- የፖለቲካ ጋዜጣና መጽሃፍ ተከታታዮች ብዛት፣
- የፍትሕ ጋዜጣ (ከኢሕአዴጉ ‹‹ህዳሴ›› አንፃር) ያለው የስርጭት ብልጫ፣
- ቪኦኤ እና ዶቼ ቬሌ (ከኢትዮጵያ ሬዲዮ አንፃር) ያላቸው የአድማጭ ብልጫ፣
- ‹‹ዳንዲ›› የነጋሶ መንገድ በጥቂት ቀናት ውስጥ 25ሺ ኮፒ ሲሸጥ መለስን አወዳሽ መፅሃፍቶች ግን በዋጋ ቅናሽም የሚገዛቸው መቸገራቸው እና
- የ‹‹ሁለት ምርጫዎች ወግ›› ገዢ ሲያጣ፣ ‹‹የመለስ አምልኮ›› በ10 ቀን ውስጥ 40 ሺ ኮፒ መሸጡ ናቸው፡፡
ሚኪያስ ዲኖ የተባለ ጸሃፊ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹አንዳንድ ሐሳቦች አሉ መፍታታት አቅቷቸው በተኮራመቱበት የሌላ ሐሳብ ሲያርፍባቸው ሙቀት አግኝተው ነፍስ የሚዘሩ፡፡…›› ብሎ ይጀምርና የባለፈው ሳምንት የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ጽሁፍ ሐሳቡን እንዳፍታታለት ነገር ግን ለኤፍኤም ሬዴዮቹ ፕሮግራም መበላሸት የአየር ሰዓቱን ያከራያቸው መንግስት ተጠያቂ መሆኑን ይከራከራል፡፡ ዶ/ር ዋቅጅራም በበኩላቸው ‹ታዲያስ አዲስ› የተሰኘው ፕሮግራም አንዲት የ14 ዓመት ልጅን (በስልክ) ስታድግ ምን መሆን እንደምትፈልግ ከጠየቃት በኋላ ‹‹አስትሮኖት›› ብላ በመመለሷ አዘጋጁ ‹‹አልቀረብሽም›› ብሎ እንደተሳለቀባት ጠቅሰው ‹‹የምዕራባውያንን ፕሮግራሞች ፈጥኖ የሚቀዳ ‹ጋዜጠኛ› እንደምን የሙያውን እውቀትና ስነምግባር አብሮ አይጨልፍም?›› ሲሉ ጠይቀዋል - ካለፈው ሳምንት በቀጠለው ጽሁፋቸው፡፡ ቀናው ገ/ሥላሴ የተባለ ጸሀፊም በዚሁ ጋዜጣ ላይ ‹‹ሚስማሩን የሳተው የበድሉ ዋቅጅራ መዶሻ›› በሚል ርዕስ ትችታቸውን ተችቷል፡፡
* * *
አዲስጉዳይ መጽሄት በየሳምንቱ ለመታተም አሃዱ ባለበት ዕትሙ የሽፋን ገጽ ላይ የአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ጊቢ በር ላይ ያሉትን አንበሶች አፋቸውን፣ ዓይናቸውን እና ጆሯቸውን በያዙ ሦስት ዝንጀሮዎች ተክቶ ‹‹የፍርሃት አገር ‹ኦሜርታ›!›› የሚል ታሪክ አስነብቧል፡፡ ‹‹የማይሰማ፣ የማያይና የማየናገር ሰው አንድ መቶ ዓመታትን በሠላም መኖር ይችላል - ይህ አባባል ‹ኦሜርታ› ተብሎ የሚጠራው የማፊያ የዝምታ ሕግ አስፈሪነትን ለመግለጽ የማፊያ የትውልድ ቦታ በሆነችውና በደቡባዊ ጣሊያን በምትገኘው የሲሲሊ ግዛት ነዋሪዎች ዘንድ የሚነገር ዘወትራዊ ቃል ነው፡፡…›› ብሎ የኦሜርታን ምንነት ካስረዳ በኋላ በሃገራችን ካለው የ‹‹ማወቁንስ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን›› እውነታ ጋር አመሳስሎታል፡፡ አዲስጉዳይ በዚህ ሐተታው ምሁሮቻችንን ‹‹ውሃ ውስጥ ተኝተው የሚያልባቸው›› በማለት ፍሃታቸውን የገለጸው ሲሆን እንደምሳሌም ‹‹…ከፖለቲካ ጋር ፈፅሞ ግንኙነት በሌለውና ማሕበራዊ ጉዳይን በተመለከተ ርዕስ ላይ አስተያየት ተጠይቀው ‹ተዉኝ ልጆቼን ላሳድግበት› ያሉን ምሁር አሉ፡፡ በግልጽ ‹እፈራለሁ› ያሉ ምሁርም አሉ፡፡…›› ብሏል፡፡
* * *
ሎሚ መጽሄት ቅዳሜ ይዞት በወጣው እትሙ የሽፋን ገጽ ላይ ከተነበቡ 13 ርዕሶች ውስጥ ሰባቱ የቴዲ አፍሮን ስምና ጥቁርሰውን ይዘዋል፡፡
* * *
ሪፖርተር ጋዜጣ በእሁድ እትሙ ‹‹አይኤም ኤፍ የመንግስት የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያን አልተቀበለም›› በሚል በሰራው ዜና ላይ ‹‹…[አይኤምኤፍ] የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያን እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡ የዘንድሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት አምስት በመቶ መሆኑን ገልጾ፣ በሚቀጥለው ዓመት ዕድገቱ 5.5 በመቶ ይሆናል የሚለውን ትንበያውን በማሻሻል ሰባት በመቶ እንደሚደርስ አቋሙን ለኢትዮጵያ መንግስት አሳውቋል…›› ብሎ ዘግቧል፡፡ የእንግሊዝኛው ሪፖርተር በበኩሉ ይህንኑ ዜና ሲተነትን ‹‹…IMF has issued a statement praising the macroeconomic and overall growth performance of the country over the past one year….›› ብሎ ጽፏል፡፡
* * *
ፎርቹን ጋዜጣ ስለበጀቱ በሰፊው የተነተነበት ሐተታው ላይ የመጪው ዓመት ዕቅድ ባጀት የሃገር ውስጥ ገንዘብ ስርጭቱ ለዋጋ ግሽበቱ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አምኗል ብሏል፡፡ ዶ/ር እዮብ ተስፋዬ የተባሉ የኢኖሚክስ ባለሙያ አጣቅሶ ‹‹… አስተዳደሩ ይህንን ለማመን አምስት ዓመታት ፈጅቶበታል፤›› ብሏል፡፡
* * *
ካፒታል ጋዜጣ ደግሞ ‹‹New Lease Tariff for Addis/ለአዲስ አበባ አዲስ የሊዝ ታሪፍ›› ወጣላት የሚል ዜና አስነብቧል፡፡ አዲሱ የሊዝ ዋጋ ከ1,686 እስከ 191 ብር በካሬ ሜትር እንደሆነ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ቦታዎች ለሊዙ ዋጋ እንደ ቦታቸው በሦስት ዞኖች ተከፍለዋል፡፡ ‹…ማዕከላዊ የገበያ ክልል ዞን/Central Market District Zone (ከ1,686 ብር እስከ 894 በካሬ የሚከራዩ 5 ደረጃዎች)፣ ተሻጋሪ ዞን/Transitional Zone (ከ1,035 እስከ 555 ብር በካሬ የሚከራዩ 5 ደረጃዎች) እና ተስፋፊ ዞን/Expansion Zone (ከ355 እስከ 191 ብር በካሬ የሚከራዩ 4 ደረጃዎች) ወጥተውለታል…› ሲል ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ ካፒታል ከዚህ በተጨማሪም የክልሎች የበጀት ክፍፍልን ዝርዝር ይዞ ወጥቷል፡፡
ቀልድ
ፍርድ ቤቱ ፍርድ ቤት ተጠራ
ሰሞኑን በአንድ ጋዜታ አንድ ነገር አነበብኩ፡፡ ‹‹አቶ መለስ ዜናዊ ለምስክርነት ፍርድ ቤት ሊቀርቡነው›› ይላል፡፡ እኔ ደነገጥኩኝ፡፡ ምክንያቱም እኔ በ21 ዓመት ክቡር ጠ/ሚኒስትሩን ሳውቃቸው ከፍ/ቤት በላይ ፍርድ ቤት ናቸው፡፡…. ፍኖተ ነፃነት
ሌላም፣ ሌላም
- ፖሊስ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የመመዝገቢያ ፎርም እያስሞላ መሆኑ ነዋሪዎችን አሳስቧል - ፍኖተ ነፃነት
- የኢትዮጵያ መንግስት ከፕሬስ አያያዙ ጋር በተያያዘ ጫና በርትቶበታል (የሲፒጄ እና ኤኤምአይ ተወካዮች አቶ መለስን አነጋግረዋል፣ ድንበርየለሽ የጋዜጠኞ ተመልካች በኢትዮጵያ አዲስ ሳንሱር ተግባራዊ እየሆነ ነው ብሏል፣ ‹‹የሕግ አተገባበር ችግር ካለ ሕጉን ለመከለስ ዝግጁ ነን›› - አቶ በረከት ስምኦን) - ሰንደቅ
- ዓመታዊ ተንከባላይ የምግብ ዋጋ ግሽበቱ ከ44 በመቶ በላይ አሻቀበ - ሰንደቅ
- ከሥራ የታገዱ መምህራን የይቅርታ ደብዳቤ እንዲያስገቡ መጠየቃቸውን ገለፁ - ፍትሕ
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢያቋቁሙስ? - (ኤልያስ) አዲስ አድማስ
- Ethio-Chinese “Romance” at the crossroads – THE Reporter
- አሳይ ትምህርት ቤት ያለወላጆች ፈቃድ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ተቀየረ - ረፖርተር (እሁድ)
- First Smartphone Assembled in Ethiopia Coming to Scene (Hong kong-based Techno Mobile aims for base price of 6,000 Br for Android phone)
የሕትመቶቹ ርዕሰ አንቀጾች
- የኢሕአዴግ እጅ የተነከረበት ሕገ-ወጥ ብልጽግና - የኛ ፕሬስ
- የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማንና ለምን? - መሰናዘሪያ
- ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረጉ ብርበራዎች ይቁሙ - ፍኖተ ነፃነት
- በግብረሰዶማዊነት ችግር ጉዳይ የሃይማኖት አባቶች እርምጃ የሚደገፍ ነው - ሰንደቅ
- የኑሮ ውድነት ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ ‹‹አንከባለለን›› እንደሙቀጫ - ሪፖርተር (ረቡዕ)
- የአልበሽርን ለፍርድ መቅረብ እንደግፋለን! - ፍትሕ
- ሳምንታዊ - ‹‹የማይቻለውን ለማስቻል›› - አዲስጉዳይ
- ‹‹ለመጨነቅም ቢሆን አብረን እንሁን!›› - አዲስ አድማስ
- Standing by the Press – THE Reporter
- ፍትሕና መልካም አስተዳደርን ያየህ ወዲህ በለኝ - ሪፖርተር (እሁድ)
No comments:
Post a Comment