Friday, June 8, 2012

የሁለት ‘ሚኒስትሮች’ ወግ

ወግን ‹‹ሥርዐት ደንብ ወይም የተደረገውን  ታሪክ ማውጋት መተረክ ፣ ለሹሞች ለአለቃ ለቄስ ገበዝ የሚሰጥ ወይም የነፍስ አባት የሙት ልብስን አልጋን ዋንጫን መግፈፍ።›› ብሎ ከሳቴ ብረሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት ይፈታዋል፡፡

እኛም ከዚህ ትርጉም  ውስጥ ‹‹የተደረገውን ታሪክ ማውጋት መተረክ›› የሚለውን ተከትለን የሁለት መሪዎችን/ጠቅላዮችን ጨዋታ እንጨዋወታለን፡፡

Twitter በተባለው የማህበራዊ ድረ ገፅ አስከ ፈረንጆቹ 2012 ድረስ ከ 140 ሚሊየን በላይ ግለሰቦች ተመዝግበው ስለተለያዩ ጉዳዮች ሃሳባቸውን ያካፍላሉ በተከታዮቻቸውም (Followers) ምላሽ እና አስተያየት ያገኛሉ እነርሱም የፈለጉትን ሰው መከተል (Follow) ይችላሉ፡፡

ከነዚህ መራጆቸ (Twitterati) መካከልም  ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ @MelesZenawi እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ @HailemariamD እንደሚገኙበት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰምተናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ Twitterን የተቀላቀሉት ከ3 ዓመት በፊት ማለትም April 9/2009 እንደሆነ የTwitter ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በመጀመሪያ ያደረጉት Tweetም “Just had some of my favorite Shiro. Thank You Chef” የሚል ሲሆን፡፡ ይህችም Tweet በተለያዩ ግለሰቦችም ዘንድ የተለያየ አንድምታ የምትፈጥር ሆናለች፡፡

- አንዳንዶች ‹‹እንዴ ስለ ምግባቸው ማውራታቸው ከፖለቲከኝነት ይልቅ Holywoodian መሰሉ እኮ›› ሲሉ፣

- ‹‹የለም የለም እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከድሃ ቤተሰብ ተወልደው በድህነት እንደማደጋቸው እርሳቸውም ሽሮ እየበሉ ኑሮን እንደሚገፉት ያመላክታል›› ይላሉ ሌሎች፣

- ከፓርቲው አካባቢ የሚመስሉ ሰዎች ደግሞ ‹‹እኛ በአበል እና በመሳሰሉት ወጭዎች በመደገፍ ቀይ-ከነጭ  እንቆርጣለን እርሳቸው ሽሮ ነው ምግባቸው አቤት መስዋዕትነት!›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህችን አነጋጋሪ Tweet ካደረጉ በኋላ ለሁለት ዓመታት ከTwitter መንደር ጥፍት ብለው ከርመው በ April 2011 ነው ብቅ የሚሉት፡፡ ለመጥፋታቸው ዋነኛው ምክንያት አሁን ካለው የፓርቲያቸው የፓርላማ መቀመጫ ብዛት ጋር ስናስበው ግልፅ ይሆንልናል፡፡ በዛን ወቅት እርሳቸው በምርጫ ዝግጅት እና ወከባ ውስጥ ነበሩ ብለንም መደምደም ያስችለናል፡፡ ፍሬውም 99.6 በመቶ የፓርላማ ወንበር፡፡

የነTwtter ሚና ከፍተኛ እንደነበር የታየበት የአረቡ አለም ፀደይ (The Arab Spring)  ፍሬ ካፈራና ሁሉም በየጓዳው መደንገጥ በያዘበት ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቅ ብለው ጥቅም ላይ ስላልዋለው 3 ሚሊየን ሄክታር መሬታችን፣ ስለ ህዳሴው ግድብ ተስፋና መከራ፣ ስለ የተለያዩ እርዳታዎች፣ ስለውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የግንቦት 20 እንኳን አደረሳችሁ መልእክት ወዘተ tweet ያደርጉና ‘የሆሊውድ’ መንፈሳቸው እንደገና ሲቆሰቆስ፡

I wanted to upload photos of this moments but the twitter app on this iphone is not letting me do it, maybe its [it’s] the network” እንዲሁም “here are some photos I promised…” ብለው ጥያቄ ያጭሩብናል፣ ይሄ ነገር እንዴት ነው? ያስብሉናል፡፡

- የApple ምርት የሆነውን iphone መጠቀማቸው ጠዋት ማታ ከሚከሱት ኒዮ ሊበራሊዝም አቀንቃኞች ጋር የጓዳ ግንኙነት አላቸው እንዴ? ሲያስብለን፣

- “…maybe its [It’s] the network” ሲሉ ደግሞ ‹‹ለካ ቴሌ ቤተሰቦቹንም አሰመርሯል እያልን ብለው ብለው “Ethio Telecom SUCKS” እንዳይሉ እንፈራለን፡፡››

- ለማንኛውም ግን ቆይተውም ቢሆን የለጠፉልንን ፎቶ ስናይ ‹‹ፎቶ አንሽነት ምንኛ መታደል ነው!›› ያስብለናል፡፡

ወደኋላ እንመለስ እና በሜይ 30/ 2011 ፓርቲያቸው ስልጣን የያዘበትን ሀያኛ አመት ካከበረ ከሁለት ቀናት በኋላ  ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ “Welcome to twitter @HailemariamD” በማለት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ወደ Twitter መምጣት ያበስሩናል እንደገናም በሌላ ትዊታቸው “Follow the deputy PM & FM of #Ethiopia” ይላሉ፡፡ ታዲያ ይሄስ ምን ሹክ ይለናል?

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ‹‹ስልጣን ልለቅ ነው፡፡ ኦ ይቅርታ ፓርቲየ ያሳደገህን ድርጅት ጥለህ የት ልትሄድ አርፈህ ተቀመጥ አለኝ›› እያሉ ብዙ ዓመታትን ቆይተዋል፡፡ በቅርብ ደግሞ ‘መተካካት’ በተባለው የፓርቲያቸው ስትራቴጅ አማካኝነት የአሁኑ የምርጫ ወቅት (2002-2007) የመጨረሻቸው እንደሆነ እና ከ2007 ዓ.ም በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደማይቀጥሉ እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

እና እርሳቸውን ማን ይተካቸዋል? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ምላሾች እየተሰጡ ናቸው፡፡ ከቀዳሚዎቹ መልሶች አንዱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ሲሆን ከላይ ከተጠቀሱት ትዊቶችም ወደዚህ ያዘነብላሉ፡፡

“Welcome to twitter @HailemariamD” ሲሉ ‹‹ወደ መንበሩ እንኳን ደህና መጣህ›› እንደማለት ነው፡፡ “Follow the deputy PM & FM of #Ethiopia” ሲሉ ደግሞ ‹‹ህዝቤ ሆይ በስርዓት እንዳኖርኩህ አሁንም ይሀን ስርዓት የሚያስቀጥልልህ የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ ለእርሱም ተገዙ›› ማለታቸው ነው የሚሉ ‘ተንታኞች’ ተበራክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ወደ Twitter አለም ከገቡ ከአንድ ዓመት በላይ የሆናቸው ቢሆንም እስከ አሁን ያደረጓት አንድ እራሷን የቻለች Tweet ብቻ ናት፡፡ እሷም “Happy Birthday @meleszenawi” የምትል ስትሆን ይሄ ምላሻቸውም:
‹‹መልካም ልደት፣ ተቀብያለሁ እርስዋን ያኑርልኝ፣ እናት ሽህ ልጅ ትውለድ ስሙንም መለስ ትበለው የሚል እጅ መንሻ ነው›› የሚል ትርጉም ተሰጥቶት የሽግግሩ ወሬ እየጦፈ ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም በምላሻቸው “Thank You Hailemaram ! I appreciate all the best wishes” ይላሉ፡፡ ይህ የቤተዘመድ ወግ የማያስቀናው ከቶ ማን ነው?

እውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ “Follow the deputy PM & FM of #Ethiopia” እንዳሉት በትረ ስልጣኑን ለተከታያቸው ያስረክቡ ይሆን? መልሳችን አዎ ከሆነ ያሰጀመሩትን ግድብ ሳያስጨርሱ ወዴት ነው? የሚለውም ከባድ ጥያቄ ነው፡፡

1 comment:

  1. [...] ዞን ናይን የተሰኝ በአስር ጀማሪ ጦማሪያን የተጀመረ አዲስ ብሎግ በዚህ ሳምንት በርካታ ጽሁፎች አስነብቦናል:: ሁሉንም ጽሁፎች ወድጃቸዋለሁ መምርጥ ስላለብኝ ግን ሁለቱን ጀባ ልበል:: ዘላለም ማልኮም የሁለት ‘ሚኒስትሮች’ ወግ እና “የቃሊቲው መንግስት” እኔ እንዳነበብኩት በሚል ርእስ የጻፉትን:: በመጀመሪያ ከዘላለም ጽሁፍ አንድ አንቀጽ እንካችሁ: [...]

    ReplyDelete