Monday, March 21, 2016

የመካከለኛው አውሮጳ ክፉ መንፈስ

(Scepticism and Hope በሚል ርዕስ የተሰበሰቡ 16 መጣጥፎች ውስጥ  The Ghosts of Central Europe የሚል ርዕስ ያለውን በLajos Grendel የተጻፈ ጽሑፍ አቤል ዋበላ እንደሚከተለው ተርጉሞታል።)

ላጆስ ግሬንድል  እንደጸጻጻፈው፣
አቤል ዋበላ እንደተረጎመው

ባንድ ወቅት ስሎቫኪያዊው የክፍሌ ተማሪ  ሀንጋሪያዊ ቢሆን ኖሮ ራሱን በመስኮት እንደሚወረውር ነገረኝ፡፡ በምን ምክንያት እንደዚህ ሞኛሞኝ  ጸባይ እንደሚያሳይ ስጠይቀው ሲያጉተመትም እና ሲያጉረመረርም ቆይቶ በመጨረሻ ሀንጋሪያዊ መሆን የሚያስጠላ ነገር እንደሆነ ከአፉ አመለጠው፡፡ ልክ እንደሆነ ሲገለጥልኝ የጋመው ንዴቴ በድንገት በረደ፡፡ ሀንጋሪያዊ መሆን የሚያስጠላ ነገር ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ቼካዊ፣ ስሎቫካዊ፣ ሩማኒያዊ፣ ጀርመናዊ፣ ይሁድ፣ ሩሲያዊ ወይም ጂፕሲ እንደመሆን የሚደብር ነው፤ ይህን የምለው ኢስቶኒያዊ፣ ላቲቪያዊ ወይም ሉቲኒያዊ ላለማለት ነው፤ ቺቺኒያውያን ወይም በአዘርባጃን የተከበቡትን አርመኒያውያንን ጭራሽ አልጠቀስኩም፡፡

ከራሴ ጋር በሐሳብ ስጫወት . . . ስሎቫኪያዊ ብሆን ምን እሆን ነበር ብዬ አሰብኩኝ፡፡ ስሎቫኪያዊ ብሆን ኖሮ  በታሪክ መስመር ተንከባልዬ እስከ 1993 ጠብቄ  በመጨረሻም  የራሴው ሀገር የሀገርነት ሰርተፊኬት በአንዳንድ የውጪ ሀይሎች መልካም ፈቃድ ላይ እንዳልተመሰረተ  ከመረዳቴ በፊት ሀንጋሪያውያን እና ቼኮችን ይቅር ለማለት አልችልም ነበር፡፡ ቼካዊ ብሆን ኖሮ አባቶቼና አያቶቼ በጣም በሚዘገንን ጭካኔ ጋርደው ከትውልድ መንደራቸው ያካለቧቸውን  ሶስት ሚሊዮን ጀርመናውያንና የእነርሱን ዘር ማንዘር ብቀላ በመፍራት እኖር ነበር፡፡ ፖላንዳዊ ብሆን ኖሮ  እንደስዊዝ አይብ ቤቴን በተደደጋጋሚ ቆርሰው የተካፈሉትን ሁለቱን ሁሉንቻይ ጎረቤቶቼን ሩሲያውያን እና ጀርመናውያን መርሳት አልችልም ነበር፡፡ ይሁድ ብሆን ኖሮ በጀርመን ጦር አብዛኞቹን የምወዳቸውን፣ ዘመዶቼን፣  ጓደኞቼን እስኪሞቱ ድረስ በጭስ የመታፈናቸውን እውነታ እንዴት ይቅር ማለት እችላለው?  ጂፕሲ ብሆን ኖሮ በቀን መቶ ጊዜ ልተወው ብስማማም የቆዳዬ ቀለም ከመገኛዬን ማጋለጡ አልቀረም፡፡ እንግሊዞች አይሪሾች ላይ የሰሩትን፣  ፈረንሳዮች ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ባልሆኑ ዜጎቻቸው ላይ ያደረጉትን እና እነዚህ ሁለቱም በየቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ ያደረጉትን ህልቆ ማሳፍርት (ad infinitum) በመዘርዘር  መቀጠል እችላለው፡፡

ዛሬ ብሔርተኛ፣ ፀረ-ሴማዊ እና ዘረኛ መሆን  በትሁት ማኀበረሰብ ዘንድ ምስጋና ይደረሳቸውና የተለመደ አይደለም ፡፡ ምንም እንኳን አሁንም ይህ የአህጉር ክፍል የሚያንባርቁ እና የሚደሰኩሩ አክራሪ ብሔርተኛነትን የሚያቀነቅኑ ትጉኃንን እያስተናገደ ቢሆንም ይህ እውነታ በሁለቱም በመካከለኛው አውሮጳ እና በባልካን  በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የጨቃላ ትናንሽ ሀገሮች ቀውሶች ኋላቀር ንትርክ  ወይም በምርጥ አገላለጽ የበጥባጭ ህጻናት ተንኮል አዘል ቧልት  የሚመስለው ከምዕራብ ሲታይ  ሊሆን ይችላል፡፡ በተፈጥሮ ስሜታዊ የሆኑት ሀገር በቀል የመካከለኛው አውሮጳ ዜጎች ግን  ምን ያህል ትንሽ ብቻ እንደገባቸው ተረድተው በበቂ ሁኔታ ሊገረሙ አይችሉም፡፡ እርግጥ ነው አልገባቸውም፡፡ ግን እነርሱ እራሳቸው ምዕራቡ ዓለምን በትክክል ስላልተረዱት ብቻ ሳይሆን፣ በነጻነት ከቦታ ቦታ መጓጓዝ ባለመቻላቸው፣ ውስጣዊ ጥልቅ ስሜቶቻቸው ሳይቀር በመንግስት ቁጥጥር ስር በመዋላቸው አሁን አሁን የእነርሱ የትውልድ ሀገር የምድር እምብርት እንደሆነች ወደማመን መጥተዋል፡፡ እናም አሁንም ያ በትክክል የሆነው ነው፡፡


የምድር እምብርት ሁልጊዜ የሚገኘው እኔ እንድቆም የሆንኩበት ስፍራ ነው፡፡ እኔ መሆን የምፈልገው ቦታ ግን እሩቅ ማየት የምችልበትን ስፍራ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መካከለኛው አውሮጳ  ሆነን ማየት የምንችላቸው የምድሪቱ ነገሮች ጥቂት ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች፣ ክስተቶች፣ እውነታዎች እና ግንኙነቶች መካከለኛው አውሮጳውያን ብቻ የሚታዩ ናቸው አንዳንድ ጊዜ ይህን ማየታቸው መረዳታቸውን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ኮሚኒዝም ሲንኮታኮት እና ከዚያም በፊት ባለው ጊዜ በመካከለኛው አውሮጳ ባህር የሚሞሉ መጣጥፎች፣ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ሽንጠ ረጅም ድርሰቶች እና ጽሑፎች ለንባብ በቅተዋል፡፡ ምስጋና ለዚህ የበለጸገ ስነ ጽሑፍ በተጨማሪም በድካሜ ላገኘኹት ልምድ ስለመካከለኛው አውሮጰ የሚከተለውን ዕውቀት አካብቻለው፡፡

  1. መካከለኛው አውሮጳ በማንኛውም ጊዜ፣  በየትኛውም አቅጣጫ ሊወረር የሚችል የአህጉሩ ክፍል ነው፡፡
  2. መካከለኛው አውሮጳ የመካከለኛው አውሮጳ ህዝቦች በነዋሪነት የያዙት ነው፤ ነገር ግን እነዚህ ይዞታዎች በውጭ ጦር ወታደሮች እግር ማረፊያነት በተደጋጋሚ አገልግለዋል፡፡
  3. የመካከለኛው አውሮጳ ሕዝቦች ለአያት ምንጅላታቸው እና ብሔራቸው (nationality) እነዚህ ነገሮች ካላቸው ፋይዳ በሚበልጥ መልኩ ይንሰፈሰፋሉ፡፡
  4. የመካከለኛው አውሮጳ ሕዝቦች በኃይል ተገዝተዋል፡፡ ታሪካዊ የሒሳብ ስሌትን መሰረት በማደረግ በመደበኛ የጊዜ ርቀት ውስጥ በተደጋጋሚ ተደፍረዋል ብሎ የሚናገር ሰውም ሊኖር ይችላል፡፡
  5. በዚህ ምክንያት የመካከለኛው አውሮጳ ህዝቦች ከመካከለኛው አውሮጳ ውጪ ካሉ ህዝቦች በበለጠ የመስጋት እና ሁሉንም በጠላትነት የማየት ዝንባሌ ያታይባቸዋል፡፡
  6. ባንድ ወቅት መካከለኛው አውሮጳ የተዋቀረው በትናንሽ ሀገረ መንግሥቶች ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም በመካከለኛው አውሮጳ ያሉ በርካታ ህዝቦች ከየትኛውም ቦታ በበለጠ በትንሽ ቦታ የመታፍን ፍርሃት አለባቸው፡፡
  7. እነዚህ ሀገረ መንግስቶች ደሃ ናቸው፡፡
  8. የመካከለኛው አውሮጳ ቀደምት ህዝቦች ማንነት ላለፉት ሰባ እና ሰማንያ ዓመታት ቀስ በቀስ ሲሸረሸር ቆይቷል፡፡
  9. እንደማንኛውም ሰው የመካከለኛው አውሮጳ ሕዝቦች ስኬታማ፣ ባለጸጋ፣ ተቀባይነት ያለው እና ደስተኛ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን  በትክክል የሚኖሩበት ስፍራ ሆነው እነዚህን ነገሮች የማግኘት ዕድላቸው በትክክል እጅግ ከሲታ ነው፡፡

ቀጥዬ ከላይ ያነሳናቸውን በየተራ እንድፈትሻቸው እንዲሁም በታሪክም ሆነ በአሁን ጊዜ እውነታ በግልጽ እንደሚተገበሩ ለማሳየት ስዕላዊ መግለጫ እንድጠቀም ፍቀዱልኝ፡፡ ለምሳሌ በካሳ (Kosice) ከተማ ከሚገኙት በርካታ የሽሚት ቤተሰቦች መካከል አንዱን ሽሚት ቤተሰብ እንውሰድ፡፡ በ1991 እ.ኤ.አ. የመጨረሻው የሶቪየት ወታደር የቼኮስላቫኪያን ድንበር ትቶ ሲሄድ ዕድሜው በአመታት ያሻቀበው ሽማግሌው ሽሚት በተመሳሳይ ዕድሜ ክልል ለምትገኘው ለአሮጊቷ እናት ሽሚት “ሩስያውያን ለቀው ሄዱ” ብሎ አበሰራት፡፡ “ታዲያ ማን መጣ?”  ጋዜጦችን አንብባ እና ዜና በቴሌቪዥን ተመልክታ የማታውቀው አሮጊቷ እናት ሽሚት ጠየቀች፡፡“ማንም አልመጣም” ሽማግሌው ሽሚት መለሰ፡፡ “ያ ሊሆን አይችልም እኔ አላምንም፡፡” አሮጊቷ ሽሚት በእርግጠኝነት ደመደመች፡፡ ከዕለታት ባንዱ ቀን በካሳ ታሪክና ባህል የሚኮሩ ገና የተጋቡ ወጣት ጥንዶች ሳሉ፣ ካሳም ጥንታዊት ሀንጋሪ ከነበሯት ቆንጆ ከተሞች አንዷ ሳለች አሮጊቷ እናት ሽሚት በድንጋጤ ለወጣቱ ባሏ ነገረችው “ታምናለህ ቼኮች እዚህ ደርሰዋል፡፡” ሽማግሌው ሽሚት  ያኔ በወጣትነቱም ሆነ ከዚያ በኋላ ባለው ህይወቱ ማንንም ቢያንስ ሁሉንም ቼኮች ለመፍራት ምክንያት ስላልነበረው “ደህና፣ አሁን እንደመጡት በኋላ ደግሞ ይሄዳሉ፡፡”  ብሎ ተናገረ፡፡ ኋላ ላይ ታሪክ እሱ ትክክል እንደነበር አረጋግጧል፡፡ከሀያ አመት በኃላ  በአንደ ቀፋፊ ቀን በመከር ወቅት “ሀንጋሪያውያን መጡ፤ የኛ ሀንጋሪያውያን!” ብሎ ተናገረ፡፡ ከዚያም ሁለተኛው የአለም ጦርነት ተቀሰቀሰ፤ አውደ ውጊያው ወደ ካርፔቲያን (Carpathians) ተቃረበ፤ ጀርመኖችም አንድ ቀን  ደረሱ፡፡ በወቅቱ ሀንጋሪ የናዚ ኢምፓየር የጦርነት ጊዜ አጋር ሆና ሳለ የጀርመናውያን ወረራ ሽሚቶችን ያስቀየመ ነበር፡፡ የአጋር ሀገርን መሬት መያዝ በትልቁ የሚያዋርድ ነው፡፡ ግና ጀርመናውያን ራሳቸውን በከተማዋ የሚያሟሙቀበት ዕድል በቂ ግዜ እንኳን ሳያገኙ በመጡበት በስተምዕራብ እነርሱም መልቀቅ ነበረባቸው፡፡ ጀርመናውያን ለቀው ሄዱ ሩሲያውያን ደግሞ መጡ፡፡ እንደገናም ምንም እንኳን ከሀያ አመት በኋላ ተመልሰው እስኪ መጡ ድረስ ጦራቸው ለሀያ አመታት ተጣብቆ መቆየት ብችልም ሩሲያውያንም ለቀው ሄዱ፡፡

ሽሚቶች እስከ ጥግ ድረስ መካከለኛው አውሮጳውያን ናቸው፡፡ ረጅም በሆነው የህይወታቸው መስመር ለተለያየ የጊዜ ርቀት ሁለት ጊዜ ሀንጋሪያውያን ሁለት ጊዜ ደግሞ የቼኮስላቫኪያ ዜጎች ሁነዋል፡፡

በመጨረሻም ከመሞታቸው ጥቂት አስቀድሞ ደግሞ የስሎቫክ ዜጎች ሆነዋል፡፡ ዴሞክራሲን፣ ፋሽዝምን እና ኮሚንዝምን አጣጥመዋል፡፡ ቀደምት አባቶቻቸው ጀርመናውያን ነበሩ ፡፡ በመካከለኛው ዘመን በአርፓዶች ቤት(Arpad) ወይም በሌሎች መሪዎች እዚህ ሰፍረዋል፡፡ እራሳቸውን እንደ ሀንጋሪያዊ ይቆጥራሉ ነገር ግን ባላቸው የቤተሰብ ሁኔታ እና የጀርመን ዘር እጅግ ይኮራሉ፡፡ በኋላ የኮሚኒዝም ምጽዓትን ተከትሎ እነዚህን ነገሮች እንዲረሱ ተገደዋል፡፡ በኮሚኒስት ቼኮስሎቫኪያ ከቡርዣ መደብ የተገኘ የጀርመን የዘር ግንድ ያለው ሀንጋሪያዊ መሆን የመጨረሻው መጥፎ ሊሆን የሚችል መለያ ነው፡፡ ስለዜግነታቸው በጥያቄዎች ለማጣደፍ የህዝብ ቆጠራ አድራጊዎች  በየአስር አመቱ ይመጣሉ፡፡ ውሎ አድሮ ሽማግሌው ሽሚት በእነዚህ ሁሉ ዘለፋዎች  ተማረረ፡፡ “የስሎቫክ ወይም የሀንጋሪ ዜግነት (Nationality) እንዳለህ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ጭንቅላትህን አሳምን” ትዕግስት ያጣው መኮንን አቻኮለው፡፡“ሁለቱም አይደሉም” ሽማግሌ ሽሚት በቁጣ መለሰ  “ የእኔ ዜግነት ካሳ ነው፡፡” ወዲውኑ ስራውን አጣ እስር ቤት ወስደው ስላልቆለፉበት ግን ራሱን እንደ ዕድለኛ ቆጠረ፡፡

በሀያኛው ክፍለ ዘመን የመካከለኛው አውሮጳ ህዝቦች በማንኛውም ምክንያት ይደፈሩ ነበር፡፡ ድሃ ከሆኑ ምክንያቱ እሱ ነው፤ ሀብታም ከሆኑም እንደዚያው፡፡ ሀንጋሪያዊ፣ ስሎቫካዊ፣  ቼካዊ ወይንም ፖላንዳዊ ከሆኑም በተመሳሳይ ሁኔታ ለዚያው ነው የሚደፈሩት፡፡ ይሁድ ከሆኑም ለዚያው ነው፤  ክርስቲያን ከሆኑም ምክንያቱ እርሱ ነው፡፡ከነዚህ ውስጥ የትኛው፣ ለምን መከራን እንደሚቀበል በየአስራ አምስት እና ሀያ ዓመታት ውስጥ አንዳንዴ ደግሞ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ይቀየራል ፡፡ ማናቸውም ራሳቸውን እንደ የመካከለኛው አውሮጳ ዜጎች በህይወታቸው ለአንድ ጊዜም ቢሆን  ተሳስተው እንኳን ቆጥረው አያውቁም፡፡ ከመጀመሪያው የአለም ጦርነት በኋላ የቼኮስሎቫኪያ ሪፐብሊክ ስትመሰረት መሬቱ በሀንጋሪያውያን ነዋሪዎች ግዛት ውስጥ ተጠቃሎ ነበር፡፡ መሬቱ ግን መሬት ለሌላቸው በዚያው ለነበሩ ሀንጋሪውን ሳይሆን ከሩቅ ሰሜን መጥተው በዚያ ለሰፈሩ ስሎቫኪውያን ነው የተሰጠው፤ ምናልባት ሀብታም ይሆኑና በዚያ አውራጃው ያለውን የሀንጋሪያውያንን የበላይነት ይሰብሩ ይሆናል፡፡ ቀዳሚ የአውራጃው ነዋሪዎች አዲስ መጤዎችን ቅኝ ገዢዎች ብለው የሚጠሩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በ1938 ሀንጋሪያውያን ሲመለሱ አብዛኛው ቅኝ ገዢዎች ከአውራጃው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ በ1945 ደግሞ ቅኝ ገዢዎቹ ተመልሶ ለመምጣት እና  በርካታ ቁጥር ያላቸው ነባር ሀንጋሪያውያንን ለማባረር ተረኞች ነበሩ፡፡ የዚህ የበላይነት መለዋወጥ አደገኛነትን የተረዱት ሽሚቶች ነገሮችን እንደአመጣጡ በመመለስ ራሳቸውን ለመጠበቅ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ አቶ ሽሚት በሚሰራበት ቢሮ ራሱን ስሎቫካዊ ብሎ አውጇል፡፡ በትክክል በቀን ውስጥ ለስምንት ሰዓታት ብቻ ፡፡ በቤት በሚያሳልፈው ቀጣዩ ስምንት ሰዓታት ደግሞ ራሱን ሀንጋሪያዊ ብሎ ይጠራል፡፡

በእንቅልፍ በሚያሳልፋቸው ቀጣይ ስምንት ሰዓታት የምን ሀገር ዜጋ ነኝ ብሎ እንደሚናዘዝ መረጃው የለንም፡፡ ለሁሉም አይነት ሁኔታዎች ራሱን ለማዘጋጀት ትልቁን ወንድ ልጁን ወደ ስሎቫክ ትምህርት ቤት ትንሹን ወንድ ልጁን ደግሞ ወደ ሃንጋሪያውያን ላከ፡፡ በስሎቫካውያን ትምህርት ቤት የተማረው ልጅ የስሎቫክ ኮረዳን ሚስቱ ሲያደርግ በሀንጋሪያውያን ትምህርት ቤት የተመረቀው ደግሞ ሀንጋሪያዊ አገባ፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች የማይታረቅ ጠላትነት ውስጥ እስኪያዳብሩ ብዙ ጊዜ አልወሰደም፡፡ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ታላቅየው ስሙን የስሎቫክ ድምጸት ወዳለው ኮቫልስኪ(Kovalsky) በመቀየር ወደ ስሎቫኪያ  ተሰደደ፤ እናም  ከኮሚኒዝም እና ፋሺዝም  መካከል መምረጥ ካለበት ታናሹን ሰይጣን ኮሚንዝምን በመምረጥ በማእረግ ፓርቲውን ተቀላቀለ፡፡ ሌላኛው ልጅ ሀንጋሪያውያን ድምጸት ያለውን ቫክስፓታኪን (Kovacspataky) በመውሰድ በሀገር ቤት ቆየ፤ እናም በመጨረሻም ፋሺዝም ከሁለቱ ሰይጣኖች ያነሰ መሆኑን በማመን የሀንጋሪያውያን ናዚ ፓርቲ አባላት ቁጥርን በአንድ ጨመረ፡፡ ታላቅየው ምንም እንኳን ምናልባት ሩሲያውያን ኮሚኒስት ቢሆኑም እንኳን ቢያንስ በደረታቸው የሚደልቁ የስሎቫክ ልቦች መያዛቸውን ምክንያት አድርጓል፡፡  በሌላ በኩል ታናሽየው ኮሚኒስት መሆናቸው ብቻ በቂ አይደለም ብሎ ይከራከራል፤ አፍቃሪ ስሎቫክ ኢምፔሪያሊስት መሆናቸውን ጨምሮ ወደ ክርክሩ ያመጣል፡፡

ዴሞክራሲ ደካማ፣ ግብረ ገብነት የጎደለው እና የተበላሸ መሆኑ ሁለቱ ወንድማማቾች የሚስማሙበት ብቸኛ ነገር ነው፡፡ በ1945 ካሳ ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ የቼኮስላቫኪያ ተቀጥያ ስትሆን ትንሹ ልጅ ከነቤተሰቦቹ ወደ ሀንጋሪ አመለጠ፡፡ እዚያ ፋሽስት ለሆነው የቀድሞው ማንነቱ ታማኝ በመሆን እና ከኮሚነስት ሀንጋሪ ስውር ፖሊስ ጋር መተባበር መካከል አንዱን በፍጥነት መምረጥ ነበረበት፡፡ የኋላውን አማራጭ ወሰደ፡፡የ1956ቱን አመጽ ተከትሎ የኮሚኒስት ፓርቲን ተቀላቀለ እናም በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ መጀመሪያ ደግሞ በጣም የተከበረ የለውጥ አራማጅ ኢኮኖሚስት ሆነ፡፡

የኋላው በመጋረጃ ተጋርዶ ነበር፣ ነገር ግን ለውጡ ሲቀዘቅዝ እርሱ ራሱ በሌላ አቅጣጫ ነጎደ፡፡ በውስጣዊ ግጭት እንደተረተረ በአንጻሩ ገና በሚባል ዕድሜው በልብ ድካም ሞተ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ታላቅ ወንድምየው  ለጊዜው ስራው ሽቅብ በተመነደገበት በቼኮስሎቫኪያ ቢቆይም ከአስራ ዘጠኝ ሐምሳዎቹ መጀመሪያ በፊት  ከኮሚኒስት ፓርቲ ተባሮ  በፈጠራ ክስ ወደ ወህኒ ተወረወረ፡፡ ከአስር ዐመታት በኋላ ይቅርታን አግኝቶ ወደፓርቲው ዳግም ተቀላቅሎ ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ በኮሚኒስት ዐሳቦች እምነቱን አሳደረ፡፡ በ1968  ዱቤክ የሩሲያን አገዛዝ ተቃውሞ ሲያደርግ ከኋላ ከደገፉት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እንደገና ከፓርቲ ተባረረ ስራውንም አጣ ልጆቹም ዩኒቨርሲቲ እንዳይገቡ ታገዱ፡፡ በመጨረሻም ከብሔርተኝነት እና ኮሚኒዝም ተፈወሰ፡፡ ከሚስቱ እና ልጆቹ ጋር ስሎቫክ ካረጁት ቤተሰቦቹ ጋር ደግሞ ሀንጋሪኛ ይናገራል፡፡ ታላቁን አብዮት ሳያይ እንደታናሽ ወንድሙ ያለጊዜው አረፈ፡፡

የሁለቱ ወንድማማቾች ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት የሽማግሌው ሽሚት ቀብር ላይ ነበር፡፡ ወላጆቻቸው ምግባር የሌላቸው፣ ደካማ አውራሾች(ለልጆቻቸው ጥቂት ውርስ የሚያስተላለፉ) እና አሳዛኝ ፍጥረቶች እንደሆኑ ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ እነርሱ ቢሆኑ ኖሮ ሁሉንም ነገር በተለየ መንገድ በሰሩት ነበር፡፡ አንዱ ያንዱን አፍ መፍቻ ቋንቋ ባለመናገራቸው እና  ሌላ የውጭ ቋንቋ እንደ ልብ ለመናገር በሚያስችል መልኩ ባለማጥናታቸው ይህን ሁሉ ነገር የተነጋገሩት በአስተርጓሚ በኩል ነበር፡፡ ከመካከለኛው አውሮጳ በመሆናቸው ምንም ኩራት አይሰማቸውም፤ እርግጥ ነው ከብዙ አገዛዞች በኋላ ያላቸውን በሙሉ ሰባራ ሳንቲም ሳትቀር ያጡ ሀገሮች ውስጥ በመኖራቸው ያፍሩ ነበር፡፡  ጥቂት ቀደም ብሎ የቡዳፔስቱ ከዝን(የአጎት ልጅ) ከአይሁድ ልጃገረድ ጋር ተጋብቷል፡፡ ይህ ዜና አሮጊቷ እናት ሽሚት ጋር ሲደርስ ከአስራ ስድተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቤተሰቡ በሙሉ ለማለት ይቻላል ሉተራን በመሆናቸው አቅሏን ልትስት ምንም አልቀራትም ነበር፡፡ “ምንም ችግር የለውም” ሽማግሌው ሽሚት ለማጽናናት ተናገረ፡፡ “ምናልባት ያ እንኳን አንድ ቀን ለሆነ ነገር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ በመጨረሻ ነጻ በመሆናችን እንደሰት፡፡” – “እኮ ለምን?”  አሮጊቷ ሽሚት በቁጣ መለሰች፡፡ “ለማንኛውም በቅርቡ እንሞታለን፡፡”

ከኦጎታማም ልጆቹ አንዱ የአትላንቲክ ውቅያኖስን ያቋረጠ የመጀመሪያ ጎዞውን አድርጎ ከአሜሪካ የተመለሰው በድንጋጤ ነው፡፡ እዚያ መካከለኛው አውሮጳ ብዙም ረብ ከሌላቸው የምድር ጥጎች አንዱ መሆኑ ተገለጠለት፡፡ ራሳቸውን መደገፍ የማይችሉ ሚጠጢ ትንንሽ ሀገሮች፤ ምንም ያህል አንዳች የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው እና ከፊሉ ደግሞ ባህር እንኳን የሌላቸው፡፡ባህሮቹ በትልቅ የውሃ ገንዳ ውስጥ እንዳለ ጠብታ ስለሆኑ የባህር ዳርቻቸው በውሃ የሚታጠቡ እንኳን ብዙም አልጠቀማቸውም፡፡ ተስማሚ ያልሆነው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው ከአውሮጳ ውጭ ያሉ ሀብታትን የመዝረፍ ዕድላቸውን ነፍጓቸዋል፡፡ የተራራቁ ሀገራትን ቅኝ የመግዛት፣ ቀይ ህንዶችን ለመደምሰስ እና የተረፉትን ደግሞ በማከመቻ (reservations) ለመሰብሰብ፣ በግድ ወደ አገራቸው ጥቁር ባሪያዎችን ማምጣት በኋላ ደግሞ ነጻ እንዲሆኑ መልቀቅ፣ በመስፋፋት በሚገኝን ደስታ መቼም ያለመካፈል፣ ሀይል እነርሱ ላይ አላረፈም፡፡ ምርጥ ሊባል የሚችል የሚያደርጉት ነገር ቢኖር በጎረቤታቸው ጉዳት አጠር ወይም ረዘም ለሚል ጊዜ ብርቱ መሆን ነው፡፡ የሽማግሌው ሽሚት የልጅ ልጅ በጥቂቱ ተረድቶ ያሰላሰለው በጎረቤት ያሉ ህዝቦች የእርሱን ዘመዶች በአንድ ወቅት ወይም በሌላ ጊዜ በሚያሳፍር እና ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ የጨቆኗቸው ምክንያቱ ስለሚጠሏቸው ሳይሆን ጨቋኝ የመሆን ሚና የወደቀው እነርሱ ላይ ሳይሆን ጎረቤቶቻቸው ላይ በመሆኑ ነው የሚል ነው፡፡ አንዱን ወይንም ሁሉንም ከዚህ መቀመቅ ማላቀቅ የሚቻለው እያንዳንዱ ሰው አፍ መፍቻ ቋንቋውን ሲረሳ እና መላው መካከለኛው አውሮጳ እንግሊዘኛን ሲናገር እንደሆነ ልብ ብሏል፡፡ ከፊል ምክንያቱ  እንግሊዘኛ አለምአቀፍ ቋንቋ ስለሆነ ሲሆን በከፊል ደግሞ የጀርመኖች አሊያም የሩሲያውያንም አለመሆኑ ነው፡፡  ምናልባትም ህዝቦች ምንም ቋንቋ ባይናገሩ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለማንኛውም በመካከለኛው አውሮጳ ማንም ማንንም ስለማይሰማ በመጨረሻም ሰዎች የሚናገሩትን እየቀነሱ እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ ምናልባትም ንግግር ራሱ ሰዎች እርስ በርስ እንዳይገነዛዘቡ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ቢያንስ በዚህ መንገድ በቃላቶቻችን የተከማቸው ቁጣ እና ጥላቻ ትርጉሙን እና ግቡን ያጣል፡፡
እርግጥ ነው በመካከለኛው አውሮጳ የምናገኘው ሽሚቶችን ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሀንጋሪያዊ ምንጭ ያላቸው እዚህ የሚኖሩ ሀንጋሪያውያን፣ ከስሎቫክ የወጡ ስሎቫኮች፣ ከቼክ የተገኙ ቼኮች እና ከፖላንድ የተገኙ ፖላንዳውያን ማግኘት እንችላለን፡፡ ለእነርሱም  ነገሮች አንድ ስንዝር እንኳ የቀለሉ አይደሉም፡፡ ያን ጊዜ ለጓደኛዬ ስሎቫካዊ ብሆን ኖሮ እኔም ራሴን በመስኮት እወረውር እንደነበር ነገርኩት፡፡ ከዚያም ና አብረን እንዝለል አለኝ፡፡ ከዚህ ከአስራ አንደኛው ፎቅ ግን አይደለም ምናልባትም ከመሬት፡፡ ግን ያን ማድረጉ እርባናው ምንድን ነው?  ከሀያ አምስት ዓመታት በኋላ ከአንዱ አገዛዝ  ወደሌላው አገዛዝ ስንሸጋገር ድብርታችን ቢያድግም ከመስኮቱ ውጭም ሆነ ውስጥ ስፍራን ማግኘት አልቻልንም፡፡ አሁን አሁንማ ማንነታችን ሙሉ በሙሉ አጥተነዋል ወይም ሌሎች ብዙ ማንነቶችንም አግኝተናል፡፡  ይህ በድጋሚ እምብዛም የጤናማ ሀገር ጉዳይ አይደለም፡፡ የሆኑ ሰዎች በምድር የእርሱ የሆነ ስፍራን ፈልገው ካጡ  እነርሱ በዚያ አልነበሩም ወይንም ስፍራው መኖሩ አብቅቶለታል፡፡ ሙሲል ካፍካ ጎመብሮዊች ዳኒሎ ኪስ(Musil, Kafka, Gombrowicz, Danilo Kis) እና ሌሎችም ይህን ግራ የሆነ መካከለኛው አውሮጳ ህያው ስሜት ይረዱታል፡፡ የመካከለኛው አውሮጳ ጸሐፊ ሆኖ ከዚህ ስሜት መራቅ ከባድ ነው፡፡

ዘመን ሳያረጅ በፊት ኤንድሬ አዲይ እንዲህ ጽፎ ነበር

ሁልጊዜም የምናረፍድ ሰዎች እኛው ነን/ከሩቅ የምንመጣ ሰዎች እኛው ነን።
We are the men who are always late/ We are the men who come from far away.

ዛሬም በቀላሉ አንዲሁ በጻፈ ነበር፡፡

No comments:

Post a Comment