Thursday, August 6, 2015

አቤላ!

 (በዘላለም ክብረት)

የእስረኛ ፊት ብዙ ነው፡፡ ታሪኩም ብዙ ነው፡፡ ብሶቱም ብዙ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹ዎክ› የሚያደርግበት መንገድ እንኳን ብዙ ነው፡፡ የሆነ በፅሁፍ ለመግለፅ የሚያስቸግር ከአራት እስከ ስድስት የሚሆኑ ርምጃዎችን ተጉዞ መመለስ ከዛ እንደገና መመለስ … ከዛ እንደገና መመለስ …በጣም በተደጋጋሚ … የሚደረገው ‹ደረስ - መለስ› የዎክ አይነት ግን የእስር ቤት መገለጫ ነው፡፡ አብዛኛው እስረኛ ወደ ሰፊው ‹ማረፊያ ቤት› ከመምጣቱ በፊት በፖሊስ ጣቢያዎች ስለሚቆይና ጣቢያዎች ደግሞ ጠባብ በመሆናቸው ምክንያት ወይም በራቸው ተዘግቶ ስለሚውል  እዛው እዛው ‹ደረስ - መለስ› ዎክ ማድረግ እዛ ጣቢያ የተለመደ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የዎክ አይነት በተለየ ደግሞ ማታ ቆጠራ ከመካሔዱና ‹በየበዓታችን› ከመስፈራችን በፊት ባሉት ደቂቃዎች በዛ ያለ ሰው አንድ ላይ ሁኖ ክብ ሰርቶ የሚርመሰመስበት ‹አዙሪት› የዎክ አይነት አለ - በኢትዮጵያ እስር ቤት፡፡ በአብዛኛው እኔና አቤላ የዚህ አዙሪት አካሎች ነበርን፡፡

አንድ ቀን አዙሪቱ መሃል እየተጓዝን እያለ አቤላ ‹ፖሊስ ጣቢያ› በነበርንበት ወቅት መጀመሪያ የተደበደበበትን ምክንያት ሲነግረኝ፤ ‹የሱማሌ ተራ ልጅ ነኝ› በማለቴ ምክንያት ‹አንተ ማነህ ብሔር የለኝም የምትል?› ተብየ ነበር መጀመሪያ የተደበደብኩት፡፡ ዞላ ከ40 እና 50 ዓመታት በፊት ሰዎች ‹ብሔሬ እንትን ነው› በማለታቸው ይሰቃዩ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ‹ዜግነት እንጅ ብሔር የለኝም› ማለት የሚያስገርፍ ሀጢያት ሁኗል›› አለኝ፡፡ ተከዝን፡፡ አቅማችን ‹ሕምምም› ማለት ብቻ ነበርና ‹ሕምምም› ከማለት ውጭ አማራጭ አልነበረንም፡፡ መሬት በፀሃይ ዙሪያ ትሽከረከራለች ማለትም ያስገርፋል፡፡ ፀሃይ በመሬት ዙሪያ ትሽከረከራለች ማለትም ያስገርፋል፡፡ ‹ሕምምም›፡፡ ከአቤላ ጋር ብዙ ትካዜዎችን አሳልፈናል፡፡
ሌላ አንድ ቀን ደግሞ እስር ቤት ካገናኝናቸው በጣም ብዙ ሰዎች አንዱ ወዳጃችን ‹ገ› እኔና አቤላ ወዳለንበት መጣና ‹ክሳችሁ ምንድን ነው› ብሎ ጠየቀን፡፡እኛም ‹ሽብርተኝነት› አልነው፡፡ እሱም ትንሽ ደንገጥ በማለት ‹እንዴ ኢትዮጵያዊያን አይደላችሁም እንዴ› አለን፡፡ ‹ኧረ ኢትዮጵያዊያን  ነን› አልነው እየሳቅን፡፡ ‹አይዋ! ብረት (መሳሪያ ማለቱ ነው) እና ፌፍ - ዎን (የቦምብ አይነት ነው) ተይዞባችኋል ማለት ነው?› አለን፡፡ በፍፁም! እኛ (አቤላም እኔም) የታሰርነው ከቢሯችን ከስራ ላይ ተይዘን እንደሆነ ነገርነው - ለየዋኹ ‹ገ›፡፡ እሱም በጣም ተገርሞ ታዲያ ‹በሽብርተኝነት› እንዴት ተከሰሳችሁ› ሲለን ሳቃችን መቆጣጠር አልቻልንም ነበር፡፡ ሳቅን፡፡ ከአቤላ ጋር በእውነት ብዙ ሳቆችን ተካፍለናል፡፡ በሳቅ ሆዳችን ታሟል፡፡

Frank MacCourtን አንብበን በሳቅ ጠሽ ብለናል፣ Robert Fiskን አንብበን ስለ ዓለም ብዙ አውርተናል፣ Tariq Ramadanን አንበብን በለውጥ ሰባክዎች ቀንተናል…፡፡ ብቻ አብረን ያሳለፍናት እጅግ በጣም አጭር አንድ ዓመት የምታስቀና ነበረች፡፡

ብዙ ጠያቂዎቻችን ሊጠይቁን ይመጡና ጓደኝነት ማለት ‹ታቦት አብሮ ማንገስን› አልያም ‹ሶላት አብሮ መስገድ› ይመስል ሃይማኖት እያነሱ ‹እንዴት ተመቻችታችሁ ትኖራላችሁ› አይነት ነገር ሲሉን ብዙ እንገረም ነበር፡፡ ጓደኝነት እኮ በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከአንድ የመሰሎች ጎራ ወደ ሌላው የሚያሸጋግር ድልድይ!

ሰዎች ያለፍንበት ከአንድ ዓመት የሚበልጥ አስቸጋሪ ጊዜ (እነ አቤል አሁን ያሉበት) ብዙ የሚያበሳጨን ይመስላቸው ይሆናል፣ በፍጹም፡፡ አቤላ ፍ/ቤቱን ተዳፍረሃል ተብሎ ቅጣት በተወሰነበት ጊዜ እየሳቀ መጥቶ ‹3 ዳገት ተለመጥኩ› (በእስር ቤት ቋንቋ ‹3 ዓመት ተፈረደብኝ› እንደማለት ነው) ነበር ያለን፡፡ እኛም ቀልድ መሆኑን ተረድተን ወደ ብስጭትና ቁጭት አልገባንም፣ ይልቁን ስለ Freedom of speech in the court of law እያነሳን ተወያየን እንጂ፡፡ ምንም እንኳን ታላቁ ዳኛ Justice Holmes “The court is not a market of ideas” ቢሉም ከእርሳቸው ተከትለው የመጡት ዳኞች ደግሞ “A judge should show a higher moral character which refuse to be offended in every statements”  እያልን ነበር የምንሳሳቀው፡፡ በጣም የሚገርም ዓመት እኮ ነው አብረን ያሳለፍነው፡፡

አቤላ ወዳንተ ስመጣ፣
ይህችን አጭር ሜሞ ባልተመቻቸ ሁኔታ መንገድ ላይ ሁኜ ነው የምፅፍልህና በማጠሯ አትዘንብኝ እሺ፡፡

እንዲህ ነው፣
እኔም አንተም በማናዉቀው ምክንያት እኔ ተፈትቼ አንተና ወንድሞቻችን አሁንም አበሳችሁን እያያችሁ ነው፡፡ ለዚህ ልቤ ይደማል፡፡ ምን ላድርግ? ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል የተባሉ ሊቅ ስለ  ወዳጅነት ምን አሉ?

“ወዳጅ ‘ማ ማለት አብሮ ባካኝ እንጂ፤
እንደ አይን፣ እንደ ዦሮ፣ እንደ’ግር እንደ’ጅ፡፡

አቤላ እኔ አሁን አይንም፣ ዦሮም፣ እጅም፣ እግርም ላልሆንህ ካንተ ርቄያለሁ፡፡ ያማል፡፡ ግን ቢያንስ ሃሳቤ ውስጥ ትመላለሳለህ፡፡
በመጨረሻ ልደትህን ከአምናው ለየት የሚያደርገው አምና መሬት ላይ “እየተደቦቅን” (እየተኛን) ነበር ያከበርነው ዘንድሮ ግን አልጋ ላይ ሁነህ ማክበርህ ነው፡፡ GTP -2ን ያስታውሷል፡፡

መልካም ልደት አቤላ!

ወንድምህ ዘላለም



No comments:

Post a Comment