‹‹2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ተጫኔ ከግንቦት 2004 ዓ.ም የአገር ውስጥ የሽብር ቡድን መመስረት እና በተደራጀ ቡድን ፀሃፊ በመሆን ውስጥ የሥራ ክፍፍል በማድረግ ቡድኑ (sic) ግብና ስትራቴጅ በመንደፍ፤ ለግቡ መሣካት ከተለያዩ የሽብር ኃይሎች ጋር ግንኙነት ሥልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ በማመቻቸት ሀገር ውስጥ ስልጠና በመስጠት እራሱም ለአመፅና ለሽብር ህዝቡን እንዴት ማነሣሣትና ማደራጀት መምራት እንደሚቻል ሥልጠና በመውሰድ በህቡዕ ቡድኑ መካከል የሚደረገውን የመልዕክት ልውውጥ የመንግስት የፀጥታ አካላት እንዳይደርሱባቸው በመደበቅና በስውር በመገናኝት Security in box (sic) የህቡዕ ቡድኑ አመራሮች የሚሰለጥኑትን ስልጠና በመሠልጠን፡ መንግስትን በማናቸውም መንገድ ከስልጣን አስወግዳለሁ ከሚለው የግንቦት ሰባት ሽብር ቡድን ግንኙነት በመፍጠር ተልዕኮ በመቀበል በመንቀሳቀስ እና በሽብር ቡድኑ ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግ ተሣታፊ ሆኗል፤››
ይህ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ‹የህብረተሰቡን ሰላም ወይም ጤና ለመንሳት በማሰብ የሽብርተኝነት ድርጊት ሞከሯል፣ አቅዷል፣ አሲሯል፣ አነሳስቷልና ተዘጋጅቷል› በሚል ስለ ፀረ-ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3(2) እና አንቀፅ 4 ጥሷል በሚል በከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ የቀረበበት ክስ ነው፡፡
ጉዳዩን እያየ ያለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ 19ኛ ወንጀል ችሎትም ከሳሽ ያቀረባቸውን የሰነድ ማስረጃዎች (በነገራችን ላይ ከሳሽ በአጠቃላይ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችን ብቻ ነው፡፡ የቀረቡት የሰው ምስክሮች የሰነድ ማስረጃዎቹን ትክክለኛነት ለማስረዳት ብቻ የቀረቡ ናቸው) መርምሮ በፍቃዱ ኃይሉ መከላከል ሳያስፈልገው በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕግ 141 መሰረት ‹ከክሱ በነፃ መሰናበት አለበት› ወይስ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ 142 መሰረት ‹ክሱን ሊከላከል ይገባዋል› የሚለውን ለመወሰን ቀጠሮ ይዟል፡፡ እኛም በፍቃዱ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች ከቀረበበት ክስ አንፃር መመልከቱ የክሱን ምንነትና ሊጠበቅ የሚችለው/የሚገባው ብይን ምን መሆን አለበት የሚሉትን ጉዳዮች ለመመለስ ይህን ፅሁፍ አቅርበናል፡፡
***
በፍቃዱ ኃይሉን የሚያውቁ ሰዎች ሁሉ የበፍቃዱን ልክፍት በቀላሉ መገንዘብ ይችላሉ - መፃፍ፡፡ በፍቃዱ በመፃፍ የተለከፈ ነው፡፡ የመፃፍ! የመፃፍ! የመፃፍ ሱስ! በፍቃዱ በኢትዮጵያ ምህዳረ ጦማር (Blogsphere) ውስጥ የራሱን ጦማር በመክፈት መፃፍ ከጀመሩት ጥቂት ሰዎች አንዱም ነበር፡፡ የዞን ዘጠኝ የጡመራ መድረክ በግንቦት 2004 (በክሱ ‹ከግንቦት 2004 ዓ.ም የአገር ውስጥ የሽብር ቡድን በመመስረት› የተባለው ነው) ከመመስረቱ አስቀድሞ በራሱ የግል ጦማር ከሃይማኖት እስከ ፖለቲካ እስከ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ያሉትን ጉዳዮች በመዳሰስ የተለያዩ ፅሁፎችን ሲፅፍ የነበረ ሲሆን የዞን ዘጠኝ ጦማር ከተከፈተ በኋላም ቢሆን በግል ጦማሩና በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ የተለያዩ ፅሁፎችን ያለመታከት ይፅፍ ነበር፡፡ በፍቃዱ ይፅፋል! ይፅፋል! ይፅፋል! መፃፉ ‹እዳ› ሆኖ እስኪመጣበት ድረስ፡፡ ከላይ በመግቢያችን የጠቀስነው በፍቃዱ የቀረበ ክስ ‹እውነት› ነው በማለት ከሳሽ በፍቃዱ ላይ ያቀረባቸው ‹ሁሉም› ማስረጃዎች በፍቃዱ በግል ጦማሩና በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ የፃፋቸው ፅሁፎች፤ እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ተፅፈው በፍቃዱ ‹ያነበባቸው› ናቸው፡፡
www.befeqe.com
በፍቃዱ ዘ ኃይሉ |
በፍቃዱ መጦማር የጀመረው www.befeqe.blogspot.com ላይ ሲሆን (በኋላ ይህ ጦማሩ ወደ www.befeqe.com ተቀይሯል) በዚህ ጦማሩ የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳ ከ2003 ጀምሮ እስከታሰረበት ሚያዚያ 2006 ድረስ ይፅፍ ነበር፡፡ ነገር ግን በጦማሩ ላይ ይፅፋቸው የነበሩት ፅሁፎች መንግስትን የሚያስቆጡ (ለምን እንደሚያስቆጡት ባይታወቅም) ሆኑ መሰል ከ2005 አጋማሽ ጀምሮ ጦማሩ በኢትዮጵያ እንዳይታዩ ከታገዱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጦማሮች አንዱ ሁኖ ነበር፡፡ አሁን በፍቃዱ ‹የሕብረተሰቡን ወይም የሕብረተሰቡን ክፍል ደህንነት ወይም ጤና ለመንሳት በማሰብ የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመፈፀም አቅደሃል፣ ተዘጋጅሃል፣ አሲረሃል፣ አነሳስተሃል እንዲሁም ሞክረሃል› ተብሎ በዋናነት ‹በማስረጃነት› የቀረቡበት ሰነዶች (በነገራችን ላይ እንደ ሁሉም ተከሳሾች በብቸኝነት የቀረቡበት የሰነድ ማስረጃዎች ብቻ ናቸው) ደግሞ በዚሁ በግል ጦማሩ ላይ የፃፋቸው ናቸው፡፡
በግል ጦማሩ ከፃፋቸው ፅሁፎች መካከልም፡ ‹‹ትግራይና ሕወሃት ምን እና ምን ናቸው;› በማለት በፃፈው ፅሁፉ ሕወሃትን ስንተች ከትግራይ ሕዝብ ሕወሃትን ነጥለን በማየት መሆን አለበት ማለቱ ጥፋት ነው ተብሎ ፅሁፉ ‹በማስረጃነት› ቀርቦበታል፡፡ ‹‹ሰማንያ ሚሊዮን እስክንሞላ ድረስ እንታገላለን!›› በማለት በሰላማዊ ትግል ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም ማለቱም ሀጢያት ሁኖ ተቆጥሮበት ሸብርተኝነት ነው ተብሎ ይሄም ማስረጃ ሁኖ ቀርቦበታል፡፡ ‹‹ድር ቢያብር ለአምባገነኖች ምናቸው ነው;›› በማለት የመተባበርን ወሳኝነት ገለፀበት ፅሁፍም ‹ማስረ›ጃ ሁኖ ቀርቦበታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ ደባ የሚፈፅምባቸው 10 ነገሮች›› ብሎ የፃፈው ፅሁፍ አስወንጅሎት ‹ማስረጃ› ሁኖ ቀርቦበታል፡፡ እንዲሁም የዳኞቹን ልብ ለመስለብ በሚመስል መልኩ ከሳሽ በፍቃዱ በግል ጦማሩ ላይ ሕገመንግስታዊውን የዳኝነት ነፃነት ጉዳይ እያነሳ የጠየቀበትን ‹‹የኢህአዴግ አባል ያልሆነ ዳኛ አለ ወይ;›› ብሎ የፃፈውን ፅሁፉን ለተከሰሰበት ክስ ‹ማስረጃ ነው› በማለት አቅርቦበታል፡፡ መፃፉ ለበፍቃዱ ሱስም እዳም ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ‹በፃፉት ፅሁፍ አልከሰስናቸውም› በማለት ለክሱ ድጋፍ ሲሰጡ የቆዩ ሲሆን፤ መፃፍ ሱሱ ለሆነው እና መፃፉ በብቸኛ ‹ማስረጃነት› ለቀረበበት በፍቃዱ ይሄን መልስ ደፍረው ይነግሩት ይሆን?
‹ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኑሮ…!?›
በአጠቃላይ በዞን ዘጠኝ ስድስት ጦማርያን እና በሶስት ጋዜጠኞች ላይ (አሁን አምስቱ ተከሳሾች ላይ ቀርቦ የነበረው ክስ ተቋርጦ በፍቃዱን ጨምሮ ቀሪ አምስት ተከሳሾች ላይ ክሱ ቀጥሏል) ለቀረበው ክስ ዋነኛ ማስረጃ በመሆን ከቀረቡት ሰነዶች መካከል በፍቃዱ ኃይሉ የግብጻዊውን ዋኤል ጎኒምን ‹Revolution 2.0› (የበፍቃዱ ‹መርማሪ› የበፍቃዱ ቃል ነው በማለት የፃፈው ቃል ላይ ‹Revolution to point zero› በማለት ነው የፃፈው) የተባለ መፅሃፍ አንብቦ ዋኤል የግብፅ የለውጥ ፀደይ ጊዜ የተለያዩ ግብፃዊያን ሲጠይቁት ለነበሩት ጥያቄዎች የሰጠውን መልስ በውርስ ትርጉም መልኩ ‹ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኑሮ…!?› በሚል ርዕስ በመተርጎም የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ የፃፈው ጦማር ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ በፍቃዱ ይሄን ፅሁፍ ሲዘጋ እንዲህ ይላል፡
‹‹… እውነቱን ለመናገር ቃሉ የወጣው ከልቤ ነው፡፡ ሀገሬን ከልቤ እወዳታለሁ እናም በተሻለ ሁኔታ የምንኖርባት አገር እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡ መፈንቅለ መንግስት ወይም አብዮት የማቀጣጠል ዓላማ የለኝም፤ ራሴን እንደፖለቲካ መሪም አልቆጠርም፡፡ ዋሊያዎቹንና ሉሲዎቹን የሚደግፍ ካፌ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብሎ ተቆራጭ እየበላ ማኪያቶ እየጠጣ ጋዜጣ የሚያነብ ተራ ዜጋ ነኝ፡፡ የሚከፋኝ ብሄራዊ ቡድናችን በሰው ሀገር ሲሸነፍ ነው፡፡ ቁም ነገሩ በኢትዮጵያዊነቴ መኩራት እፈልጋለሁ፡፡ ማንም ሰው የዜግነት ክብሩን ተገፎ እንዲጨቆን አልፈልግም፡፡ ይሄው ነው ምኞት፡፡››
ይሄን የፃፈው በፍቃዱ የዋኤል ጎኔምን መፅሃፍ ለምን አነበብክ ተብሎ ተደብድቧል፡፡ ‹ለምን ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኑሮ
የሚል ፅሁፍስ ፃፍክ› ተብሎ ተገርፏል፡፡ ይህ ‹ማስረጃ› የሚነግረን ብቸኛው ነገር ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኑሮ ‹አሸባሪ› ተብሎ ይታሰር እንደ ነበር ነው፤ ምክንያቱም ‹‹ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኑሮ…!?›› ብሎ ትርጉም በመፃፉ በፍቃዱ ኃይሉ ‹አሸባሪ› ተብሎ ተከሷልና፡፡ ይህም እንግዲህ በፍቃዱ ላይ የቀረበ ‹ማስረጃ› ነው፡፡
በፍቃዱና ‹አሸባሪውን› የረዳውን ‹አሸባሪን› ፅሁፍ ማንበቡ
መስፍን ነጋሽ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በቅድመ ዘጠና ሰባቱ ሪፖርተር ጀምሮ በመዝናኛ ጋዜጣ አልፎ እስከ እጅግ ብዙ አይኖችን ያፈራቸው አዲስ ነገር ድረስ በመፃፍ ብዙ ተወዳጅነትንም አትርፏል፡፡ በድንገት መንግስት መስፍንና ጓደኞችን ‹አልወዳችሁም› አላቸው፤ ሊያስራቸውም ፈለገ - ሞከረ፡፡ አልተሳካለትም፡፡ መስፍን ከሀገሩ ርቆ በሀገራዊ ጉዳዩች ላይ አተኩሮ መፃፉን ሳያቋርጥ ከቀድሞ ጓደኞቹ ጋር በመሆን በሀገሩ ጉዳይ ላይ መፃፉን በድረ ገፅ አማካኝነት ቀጠለ እስከ መስከረም 2004 ድረስ፡፡ በመስከረም 2004 ግን መስፍን ከሌሎች 24 የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን በሌለበት በራስህ በድረ ገፅ የተለያዩ ሰዎችን ፅሁፎች አስተናግደሃል ተብሎ በጉደኛው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ተከሰሰ፡፡ በሐምሌ 2004ም በሌለበት የስምንት ዓመት ፅኑ እስራት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ ፍርዱ ግዞት መሆኑ ነው፡፡ በፍቃዱስ; በፍቃዱ ኃይሉ ደግሞ መስፍን ነጋሽ በአዲስ ነገር ኦንላይን ድረገፅ ላይ ‹‹መንግስት የለም ወይ የማንና ምን አይነት መንግስት;› በሚል ርዕስ የፃፈውን ፅሁፍ ለማንበብ የግል ላፕ ቶፑ ላይ አስቀምጦት ተገኝ፡፡ ‹የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመፈፀም አሲረሃል - ተዘጋጅተሃል› ለሚለው ክስም በማስረጃነት ይሄ ፅሁፍ ቀረበበት፡፡ መስፍን ነጋሽ፤ እስክንድር ነጋ ‹መንግስትንና ሕዝብን በፅሁፍ አሸብረሃል› ተብሎ 18 ዓመት እስራት ተፈረደበት፡፡ መስፍን ነጋሽ ደግሞ ‹የአሸባሪውን› እስክንድር ነጋን ፅሁፍ በድረ ገፅህ አስተናግደሃል ተብሎ በሌለበት ‹አሸባሪ› ተብሎ የ8 ዓመት እስራት ተፈረደበት፡፡ በፍቃዱ ኃይሉ ደግሞ ‹አሸባሪውን› የረዳውን ‹አሸባሪ› ፅሁፍ አንብበሃል ተብሎ ‹በአሸባሪነት› ተከሷል፡፡ የመስፍን ፅሁፍም ‹በማስረጃነት› ቀርቦበታል፡፡ እንግዲህ ቧልቱ ከፍ ያለ ነው፡፡
ቃሉ
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 በተሰጠው አስገዳጅ ትርጉም የመስጠት ስልጣን መሰረት በውሳኔ መዝገብ ቁጥር 77842 እና 77097 ላይ እንዳስረገጠው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 27 (2) መሰረት ለፖሊስ ተሰጠ የተባለ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 35 ለጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል እንዲሁም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 134 መሰረት ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል ‹‹ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ‹ጥፋተኛ ነኝ› ስላለ ብቻ ጥፋተኛ ነው ማለት አይደለም› ይልቁንም ቃሉን የሰጠበት መንገድና ጥፋተኛ ነኝ› ያለበት ጉዳይ ተመርምሮ ነው ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው›› በማለት አመክኖያዊውን ጉዳይ የሕግ መሰረት አስይዞታል፡፡
በፍቃዱ ኃይሉ ላይ ከቀረቡት ማስረጃዎች አንዱ በፍቃዱ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 27 (2) መሰረት ለፖሊስ ተሰጠ የተባለ ቃል ሰነድ ሲሆን፤ በሚታወቀውና በሚያሳዝን ሁኔታ በፍቃዱ እጅግ ከባድ የሆነ ስቃይንና መከራን ተቀብሎ ‹ሕገ መንግስቱ እኮ ምንም ያለመናገር መብት ይሰጠኛል› ብሎ ቢከራከርም፤ ‹ይህ እኮ ሽብር ነው፣ ሕገ መንግስቱን ርሳው› እየተባለ ተገዶ እንዲፈርም የተደረገበት ሰነድ ነው ይህ ሰነድ፡፡ በሃይል የተገኝ ማስረጃ ፍፁም ተቀባይነት የለውም የሚለው የወንጀል ማስረጃ ሕግ መርሆ ይህን ሰነድ ውድቅ በማድረግ የበፍቃዱን ነፃነት የሚያረጋግጥ መሆኑ ግልፅ ቢሆንም፤ እንዲያው ሰነዱ ‹በይዘቱስ› በፍቃዱ ላይ ምን ያስረዳ ይሆን; በፍቃዱ በነፃ ለፖሊስ ሰጠ የተባለው ቃል ላይ ‹ጥፋተኛ ነኝ› ብሎ ተገዶ እንዲፈርም የተደረገባቸው ጥፋቶች በጣም አስገራሚ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በፍቃዱ ላይ የቀረበው ሰነድ እንዲህ ይላል፡
- ‹‹ህገ መንግስቱ ይከበር የሚል ከህዳር 27-29 2005 ድረስ በተደረገው ዘመቻ ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ህገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ፡፡››”- ‹‹የዞን ዘጠኝ የስም ስያሜ ስህተት ነው ፡፡ ምክንያቱም ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውጪ የሚገኝ መላውን የኢትዬጵያ ህዘብ እስረኛ ነው በማለት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች ጋር ማነጻጸሬ ጥፋቴ ነው፡፡››
- ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አላማ በማስተዋወቅ ህዝቡ በምርጫ 2007 ኢህአዴግን አንዳይመርጥ መቀስቀሳችን ጥፋት ነው፡፡››
ይህ ነው እንግዲህ የበፍቃዱ ‹ጥፋት›፡፡ ለዚህም ነው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከላይ በተጠቀሱት ውሳኔዎች ላይ እንደዚህ ያሉ የፖሊስ እብደቶችን ለመከላከል በሚል ሃሳብ ነው ያስተላለፋቸው፡፡ ‹ሕገ መንግስቱ ይከበር! በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ› ያለው በፍቃዱ እንግዲህ ጥፋተኛ ተብሎ ተከላከል ሊባል ነው ማለት ነው!; በፍፁም! ‹ተከላከል› ቢባልስ ምኑን ነው የሚከላከለው; ሕገ መንግስቱ ይከበር ያለው በፍቃዱ ይሄን በማለቴ ‹ጥፋተኛ ነኝ› ብሎ እንዲፈርም ሲደረግ የነበረበትን አሳዛኝ ሁኔታ ከመግለፅ በቀር ንፅህናውን ነው የሚያረጋግጠው፡፡ ይሄን ስንመለከት የሽብርተኝነት ትርጉም እጅግ ላይገባን ከእኛ ይርቅብናል፡፡ በፍቃዱ የተከሰሰበትን ክስ ዓላማም ግልፅ ያደርግልናል፡፡
“ስሜ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ነው፡፡
አዲሱ አመት ሲጠባ በአዲስ መንፈስ አዲስ ህልም ለአገሬ ማለም እና የነበረኝንም ማጠናከር እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዬጵያችን የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የሃብት፣ የትምህርት፣ የፓለቲካ አመለካከት እና ሌሎችም ልዬነቶቻችን አብሮነታችንን የማያደናቅፉባት ከነልዬነታችን በጋራ ለታላቅነት የምንጠቀምባት ፣ ለሁላችንም እኩል እድል እና ተጠቃሚነት የሚቀርብባት፣ ሁላችንም እንደችሎታችን ለጋራ ደህንነታችን ፣ ነጻነታችን እና ብልጽግናችን የምንሰራባት ብቻ ሳይሆን በጋራ ስኬታማ የምንሆንባት ፣ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያፈቅራት ኢትዮጵያ አንድትሆን እመኛለሁ ይህ የእኔ ኢትዬጵያዊ ህልም ነው፡፡››ይህ በፍቃዱ ኃይሉ የዞን ዘጠኝ ጦማርያን ቡድን ከነሃሴ 30/2005 - ጷጉሜ 02/2005 ድረስ ካደረገው ‹ኢትዮጵያዊ ህልም› የበይነ መረብ ዘመቻ ላይ የጻፈው አጭር ምኞት ሲሆን፤ በፍቃዱ ላይ ይህ የምኞት ፅሁፉ የተከሰሰበትን ጉዳይ ያስረዳል ተብሎ ‹በማስረጃነት› ቀርቦበታል፡፡ አንድ ሀገር ሊኖሯት የምትፈልገው መልካም ዜጋ (ideal citizen) ይህን የሚመኝ ከመሆን ውጭ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በአሳዛኝ መልኩ ግን ከጓደኞቹ ጋር ማኪያቶ የመጠጣት ምኞቱ ወንጀል ሁኖበት የተከሰሰው በፍቃዱ በዚህ ‹ማስረጃም› ተከሶበት በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ እና መሰል ፅሁፎች ነፃ ካላወጡት በፍቃዱ ምን ማድረግስ ይችላል? ፍርድ ቤቱስ እነዚህን ‹ማስረጃዎች› ተመልክቶ በፍቃዱን ነፃ ከማለት ውጭ ሌላ ምን ሊለው ይችላል? አዎ! በፍቃዱ ነፃ ሰው ነው!
No comments:
Post a Comment