Friday, December 19, 2014

" ህልም አንደሆነ አይታሰርም " ጦማሪ አቤል ዋበላ

‹‹ ስሜ አቤል ዋበላ ነው፡፡ አዲሱ አመት ሲጠባ በአዲስ መንፈስ አዲስ ህልም ለአገሬ ማለም የነበረኝንም ማጠናከር እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያችን የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የሀብት፣ የትምህርት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ሌሎችም ልዩነቶች አብሮነታችንን የማያደናቅፉባት ከነልዩነታችን በጋራ ለታላቅነት የምንጠቀምባት ለሁላችንም ዕኩል ዕድል እና ተጠቃሚነት የሚቀርብባት ሁላችንም እንደየ ችሎታችን ለጋራ ደህንነታችን ነፃነታችን እና ብልፅግናችን የምንሰራባት ብቻ ሳይሆን በጋራ ስኬታማ የምንሆንባት እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕኩል የሚያፈቅራት ኢትዮጵያ እንድትሆን እመኛለው፡፡ ይህ የእኔ ኢትዮጵያዊ ሕልም ነው፡፡››

ከላይ የሰፈረው ጽሁፍ ዞን ዘጠኝ ባዘጋጀው አራተኛው የበይነ መረብ ዘመቻ(Online Campaign) ላይ የተጠቀምንበት ነበር፡፡ የዘመቻው ርዕስ ‹ኑ አብረን ኢትዮጲያዊ ህልም እናልም › ሲሆን የተካሄደውም በ2005ዓ.ም መገባደጃ ወር ጰግሜ ላይ ነው፡፡ በአጋጣሚ ዘመቻው መንግስት የማናውቀውን ‹ወንጀል› እየፈለገብን እንደሆነ ከሁነኛ ምንጮች ከተረዳንበት ወቅት ጋር ገጥሟል፡፡ ለነገሩ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቀደም ፓርላማ ቀርበው ‹‹ኢህአዴግ ሀሳብ የሚፈራ ድርጅት አይደለም››ሊሉ እንደፎከሩት ሳይሆን የሃሳብ ልዩነት እንደሚያስበረግገው ስለምናውቅ መስጋታችን አልቀረም፡፡ ከሌሎች ምንጮችም እርግጠኛ ያልሆኑመረጃዎች ደርሰውን ነበር፡፡ ይሄኛው ግን እርግጥ የሆነ ጅቡ ከበራፍ ላይ እንደቆመ የሚያበስር ነው፡፡

እንደ ሌሎች ዘመቻዎች ሕገ መንግስታዊነት፣ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ..... የመሳሰሉ ለሃገራችን “ቅንጦት” የሚመስሉ ርዕሶችን ማንሳት አልፈለግንም፡፡ አሁን የድራማው ዘመን ተቀይሮ እውናዊ  ሆኗል፡፡ ይህም የኔ የምንለው ትውልድ ምን አይነት ውስብስብ ችግር ውስጥ እንደተዘፈቀ በብርቱ እንድናስብ አደረገን፡፡ ለዚህም ነበር ሁሉን የሚያሳትፍ የትውልድ አቻዎቻችንን የሚጠራ ሰፊ ርዕስ የመረጥነው፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው ውጤቱ አርኪ ነበር፡፡
ስርዓቱ ግን ስለሃገራችን ያገባናልማለታችንን የትውልድ አቻዎቻችንን መፈለጋችንን አልወደደውም፡፡ የዘውጉን እውናዊነት ለማጠናከር ትምህርት ሊሰጠን ወደደ፡፡ መምህራን፣የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ቤተ ሙከራ ተዘጋጀ፡፡ አንደ አጋጣሚ ብቻ ሆኖ ከዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማሪያን ቡድን ስድስታችን እና ሌሎች ሶስት ጋዜጠኞች (ኤዶም ካሳዬ፣ ተስፋለም ወልደየስ እና አስማማው ኃ/ጊዎርጊስ) ለተማሪነት ተመረጥን፡፡ ትምህርቱም ሚያዚያ17/2006 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ውንጀል ምርመራ ዘርፍ (በተለምዶ ማዕከላዊ) ተጀመረ፡፡

ትምህርት አንድ
የመጀመሪያው ትምህርት የሀገራችን ኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ትንታኔ የሚሰጥ ወዳጃችን በዞን ዘጠኝ የሚደረጉ ሙከራዎችን አድንቆ ተጨማሪ መስራት ያለብንን ስራዎች ሊጠቁመን ‹‹ እናንተ ብዙ ጊዜ የምታተኩሩት የከተማ ፖለቲካ ላይ ነው፡፡ እስኪ ወደገጠር ጫንጮ እንኳን ሂዱ ከገበሬው ጋር ጠጅ እየጠጣችሁ ብሶቱን አድምጡና ጻፉ፡፡›› እንዳለን አስታውሳለሁ፡፡
እኛም ይህን ትችት ሙሉ ለሙሉ ተቀብለን በተግባር ባናደርገውም ከከተማ ወጣ ብሎ ለመመለስ ዕቅድ ይዘን ነበር፡፡ ማእከላዊ ግን ይህን ድካማችንን አቅልልሎ ሁሉንም አይነትኢትዮጵያዊ መልኮችን ከየአቅጣጫው አመጣልን፡፡ እነ ኡባንግን ከጋምቤላ፣ እነዚያድን ከደጋሃቡር፣ እነ አብድልከሪምን አቤኒሻንጉል፣እነ አያያዎን ከጎንደር፣እነ ቄስ ብርሃኔ ከአክሱም፣ እነ ሼህ መሀመድን ከጅማ አሰባሰበልን፡፡ የእስር ቤቱን ጨለማ ቀን እና ጨለማ ሌሊቶች ከልብ በሆኑ ወሬዎች አደመቅናቸው፡፡ ፖለቲካዊ ብልጣብልጥነት ያልነካካው ከጭቆናው የመጀመሪያ ረድፍ ገፈት ቀማሾች የሚቀዳ እውነትን አደመጥን፡፡በሰውነት ከመከበር አንስቶ እስከ የምድሪቱን ፍሬ በዕኩልነት መጠቀም ጥሮ ግሮ ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችሉ ዕድሎች ፍትሕአዊነት፣ ሳይፈሩና ሳያፍሩ ሀሳብን መግለጽ በወረዳና ቀበሌ ደረጃ የሚያስከፍለው ዋጋ፣ ከስር ባሉ የቢሮክራሲው አካላት የሚፈፀም ተቋማዊ ግፍ በአጠቃላይ አድርባይነትና አስመሳይነት በመላው ሀገሪቱ እንዴት እንደሰፈነና ብዙሃኑም ኑሮውን በቀቢጸ ተስፋ እንደሚገፋ ተረዳን፡፡ ሁሉም የጎላው ምስል ግን ዛሬም ፌደራሊዝሙ መሰረታዊ የሆኑትን የስልጣንና የሀብት (Power and Resource)ጥያቄዎች እንዳልመለሰ በጉልህ ይናገራል፡፡
ከመታሰሬ በፊት በነበረኝ ግምት በርካታ የኦሮሞዎ ተወላጆችን በማረሚያ ቤት እንደማገኝ ጠብቄ ነበር የመጀመሪያው ሰሞን  ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ከታሰሩ አንዳንድ ሙስሊም ኦሮሞዎችበስተቀር ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች አልነበሩም፡፡ ይሄ ግን ብዙ አልቆየም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ የኦሮሚያ ልዩ ዞንን በሚነካው አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን የተነሳ በተፈጠረው ግርግር በርካታ ኦሮሞ ተማሪዎች ከየዩንቨርስቲው ተለቅመው መጡ፡፡ ያን የስቃይ ቤት በሳቅ ጨዋታቸው አደመቁት፡፡ ውይይታችንም ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ዳሰስን፡፡ እኛም ብዙ ተማርን፡፡ በእነርሱ መሪነት በህብረት የምናዜማቸው የኦሮሚኛ ዘፈኖች የነበርንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስረሱን፡፡
ከሁሉም ከሁሉም biyya Toodhuufen silaala yaa Biyaa Dubro maagala (የጠይም ቆንጆዎች መፍለቂያ ሀገሬ መጥቼ አይሻለሁ) የሚለውን እንጃ የኔን ቀልብ የሳበ ዜማው አንጀቴን ሰርስሮ የገባ ነበር፡፡ አገሬ ጠያይም ቆንጆ ልጆችሽ በነፃነትና በእኩልነት እንዲኖሩብሽ አልማለሁ፡፡ይህ የኔ ኢትዮጵያዊ ሕልም ነው፡፡   
ትምህርት ሁለት
ሁለተኛው ትምህርት በተግባር የተደገፈነው፡፡ በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የተሰሩ የሰብዐዊ መብት አያያዝ ሪፖርቶችን ማንበብ ከጀመርኩኝ ጥቂት አመታት አልፈዋል፡፡ሁሌም እንደተለመደው ኢትዮጵያ የዜጎቻቸውን ሰብዐዊ መብት ከሚጥሱ እና የማሰቃየት ተግባር የሚፈፅሙ በተለይም በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራው የመንግስት ተቋም በዋነኝነትእንደሚጠቀስ ብዙዎቹ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት እስካሁን ድረስ የማሰቃየት ተግባርን (Torture) እኔም ሆነ ጓደኞቼ የምንረዳው እንደማንኛውም የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁ ነበር፡፡በተለይ እኔ በበኩሌ የተለየ ትኩረት እንደማልሰጠው አልሸሽግም፡፡

አሁን እነዚያ የአለማወቅ ወራት አልፈዋል፡፡ በታሪክ መጽሃፍት ላይ በዘመነ ደርግ እንደሚፈጸሙ ያነበብናቸው አስከፊ ተግባራት አሁንም በሃገራችን እንደሚፈፀሙ ህያው ምስክሮች ሆነናል፡፡ ከስነ ልቦናዊ የማሰቃየት ተግባር አንስቶ የተለያዩ የማሰቃያ ቁሳቁስ በመጠቀም እስከሚፈፀሙ ዘግናኝ ተግባሮች በእኛና በሌሎች ላይ ሲፈፀም ተመልክተናል፡፡በከፍተኛ ድብደባ እግሮቹ የሚወላከፉ፣ መራመድ አቅቶት በሸክም ወደ ማረፊያ ቤት የሚመለስ፣ በግርፋት ብዛት ጀርባው ብዙ ሰንበርየተጋደመበት፣ ብልቱ ላይ ሁለት ሌትር ውሃ በመንጠልጠሉ ምክንያት ሽንቱን መሽናት የተቸገረ፣ ጆሮው በጥፊ ደንቁሮና አፍንጫው የሚደማሰው መመልከት የየዕለት ተግባራችን ሆነ፡፡ በኤሌክትሪክ ሾክ የተደረጉና ‹ወፌ ላላ› ተገልብጠው እንደተገረፉ የሚናገሩ ተጠርጣሪዎችም አጋጥመውኛል፡፡ ስድብ፣ ዛቻውና የማዋረዱ ተግባር አእምሮ ሊቆጣጠረው የሚችል አይደለም፡፡ የቀረውን የማሰቃየት ተግባር ሲፈፀም ያዩና በራሳቸው ላይ የተፈፃመባቸው ይናገሩት፡፡   
ይህ ተቋም ባለበት ከተማ ምንም ነገር እንዳልተፈጠሩ ቆጥሬ ስራዬን እየሰራሁ እየበላሁ እና እየጠጣሁ በቆየሁባቸው ዓመታት አፈርኩኝ፡፡ በአገሬ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት እንዲታለፍ ዲሞክራሲያዊነት እንዲጀመር ከዜሮ ትንሽ ከፍ የሚል መፍጨርጨር በማድረጌ ግን ተፅናናሁኝ፡፡ የማሰቃየት ተግባርን በንድፈ ሀሳብ ደረጃ መረዳትና  መረጃዎችን በልብ ማኖር አንድ ነገር ነው፡፡ ዘግናኝ የማሰቃየት ተግባር የተፈፀመበት ተጠቂ ማግኘትና ማናገር ሌላ አንድ ነገር ነው፡፡ የማሰቃየት ተግባርን በራስ ሰውነት ማስተናገድ ግን ከሁሉም ይለያል፡፡ ባለቅኔው ሰው የሚማረው አንድም በሳር 'ሀ' ብሎ አንድም በአሳር '' ብሎ እንዳለ ከዚህ በላይ ትምህርት ከወዴት ይገኛል!?
የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ምርመራ ደግሞ ሳይንስ፡፡ ሀገራችን የምር በሽብርና የሌሎች ወንጀሎች ስጋት ቢኖርባት ተጠርጣሪዎችን መርምሮ ለፍርድ የማቅረብ ዋና ሀላፊነት ያለበትይህ የፍትህ አካል ነው፡፡ በአግባቡ ከተከናወነ ሕጋዊነትን ባህል የሚያደርግ ነገር ግን ተጠርጣሪዎች ላይ የማሰቃየት ተግባር የሚፈፀምበት ከሆነ ደግሞ ሙሉ የፍትህ ስርዓቱን አቀጭጮ የሚያስቀር ነው፡፡ ይህንን የሰው ልጅ ማሰቃያ ስፍራ ለቀን ወደ ማረሚያ ቤት ስንወሰድ አበራ ጀምበሬ Agony in the grand palace ላይ ያሰፈረውን
Commit to the paper the suffering in that dark chamber
Announce to the world all the unbearable torture
የሚለውን ግጥም እያሰብኩኝ አንድ ተጨማሪ ህልም አለምኩኝ፡፡ ይህን ፖለቲካዊ የሀሳብ ልዩነትን መዳመጫና የህሊና እስረኞችን ደም ማፍሰሻ የሆነ ተቋም ወደ ሙዚየም ተቀይሮ ማየት ነው፡፡ ይህ የኔ ኢትየጵያዊ ህልም ነው፡፡
ትምህርት ሶሰት -የትውልድ እዳ
ሶስተኛው ትምህርት የሚገኘው መንግስት ወደ ጦማርያን እጁን እንዲሰድ ያደረገውን ተግባርና እስሩን ተከትሎ የታየውን ምላሽ በመገምገም ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ቮልቴር  If you wish to converse with me define your terms እንዳለው ከዚህ በኋላ ‹‹ትውልድ›› ወይም ‹‹የትውልድ ልሂቃን›› ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ብያኔ ሰጥቼ እቀጥለላሁ፡፡ የነገሩን ውል ለመጨበጥ ትንሽ ወደኋላ መንደርደር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ትውልድ ስንል ተቀራራቢ የእድሜ ክልል ውስጥየሚገኝ መሰረታዊ ለውጥ በሌለውና አንድ ሊባል በሚችል ስርዓተ ትምህርት ያለፈ የአንድ ስርዓት(Regime) ውጤት የሆነ እና የዘመኑን መንፈስ የተሸከመ ማለታችን ነው፡፡ የትውልድ ልሂቃን ስንል ደግሞ ሰፊውን የልህቅነት ትርጓሜ ሊገኝ ከሚችለው ነገር አብላጫውን ያገኙ(those who get the most of what there is to get)የሚለውን እንወስዳለን፡፡ ይህንን ብይን መሰረት በማድረግ አንድ ሰው ያገኘውን የትምህርትና የስራ እድል የገቢ መጠንና በማህበረሰቡ ያለውን ቦታ ከጠቅላላው የሀገሪቱ ዜጋ ጋር በማወዳደር የእርሱ ስፍራ የቱጋ እንደሆነ ይረዳል፡፡
አንድ ትውልድ ዘመኑ የሚጠይቀውን ኃላፊነት በአግባቡ ካልተወጣ በዚያች ሀገር ያሉ ችግሮችን ለማስተካከል ያለው እድል እየጠበበ ይመጣል፡፡ ሳንካ መፍትሄ ሳያገኝ በዘገየ መጠን የበለጠ እየከበደ እና እየተወሳሰበ ስለሚሄድ መፍትሔ ለመስጠት አዳጋችና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል፡፡ 
የሀገራችንን የቅርብ ጊዜ ታሪክ በዚህ አውድ ስናጤን ከጣሊያን ወረራ በኋላ ሀገሪቱን የተረከበው ልሂቅ የፊውዳል ስርዓቱ ዘመኑን እንደማይመጥን እና የሕዝቡን ችግር የመፍታት አላማ እንደሌለው ተገንዝቦ ለመሰረታዊ ለውጥና ማሻሻል ከመስራት ይልቅ ስርዓቱ የፈጠረለትንና የፈቀደለትን የትምህርትና የስራ እድል በመጠቀም ስርዓቱን ማገልገል ምርጫው አድርጓል፡፡ የነዚህ አዳዲስ ምሁራን ዘመኑን ያልዋጀ ጥረት የተመለከተው ማኅበረሰብም ‹‹ከእጅ አይሻል ዶማ›› ብሎ ይጠራቸው ነበር፡፡ በዘመኑ ከነበሩት ስመጥር ቴክኖክራቶች አንዱ የሆኑት የቀድሞውብሔራዊ ባንክ ገዢ  ተፈራ ደግፌ "Minutes of an Ethiopian Century" በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እውነታ በሀዘኔታ ያስታውሱታል፡፡
‹‹The tragedy of our Post-war generationof Ethiopian elite was that we adapted an attitude of public silence and private passivity on this professional level walking away from society instead of confronting its problems››
ልሂቁ ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት በቀር ምንም ሊጠቀስ የሚችል እንቅስቃሴ ሳያደርግ ዝምታን መምረጡ ለሚቀጥለው ትውልድ ግዙፍ ያልተሰሩ የቤት ሥራዎችን እንዳስረከበው መረዳት አያዳግትም፡፡ በክፍሉ ታደሰ ስሌት መሰረት 1930ዎቹ፣ በ1940ዎቹ እና በ1950ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የተወለዱና በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ የነበረውን ልሂቅ ያቀፈው ‹‹ያ ትውልድ›› ከወታደራዊው መንግሥትና እርስ በእርሱ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ትግል አድርጓል፡፡እንደመሬት ላራሹ ያሉ ውጤቶች ቢገኙበትም ሕጋዊነትን ዲሞክራሲያዊነት እንዲጀመር መሰረት ባለመጣሉ በኋላ ለመጡት ሁለት አምባ ገነንሥርዓቶች መነሳት መንስዔ ሆኗል፡፡ 
ወታደራዊ መንግሥት ወድቆ የሽግግር መንግስት የተቋቋመ ሰሞን ስመ ጥሩ ኢኮኖሚስት እሸቱ ጮሌ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ማኅበረሰብ እንዲመሰረት የ1966ቱን አብዮት ለመራው ትውልድ የሰጠው እድል በወታደራዊው ኃይል መጨናገፉን በመጥቀስ ‹‹ታሪክ ሀገራችንን የምንታደግበት እና ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ጎትተን የምናወጣበት ተጨማሪ እድል ሰጥቶናል፡፡ ለአንድ ትውልድ የሚሰጥ ሁለት እድል እንዲሁ በዋዛ የሚገኝ አይደለም፡፡ ሁለቱንም በግዴለሽነትና በሞኝነት ማባከን በቀጣዩ ትውልድ ይቅር የማይባል ወንጀል ነው፡፡››ብለው ቢመክሩም ያ ትውልድ ከራሱ ታሪክ ሳይማር ቀርቶ ዳግም አገሪቱን ወደኋላ የሚጎትት ስህተት ሰርቷል፡፡ 
በስርዓቱ አምባገነንነት የተነሳ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በንቃትመሳተፍ የነበረበት አዲስ ትውልድ (በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ) ምንም ሊጠቀስ የሚችል ነገር ሳይሰራ አልፏል፡፡ ስደተኛው ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ከምርጫ 97 ጋር ከተያያዙ እንቅስቃሴዎች በስተቀር ጉልህ ድርሻ ያልነበረውን ይህንን ትውልድ ‹‹የጠፋ ወይም የባከነ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ምርጫ 97ትም በቅንጅትም ሆነ በሕወሀት ኢኅአዴግ በኩል የመሪነት ሚና የተጫወቱት የያ ትውልድ አባላት በመሆናቸው ለትውልዱ ሙሉ እውቅና ለመስጠት ይከብዳል፡፡
ከዚህ ተስፋ ሰጭ ሙከራ በኋላ ስርዓቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የግል ሚዲያውንና ሲቪል ማኅበረሰቡን አዳዲስ አፋኝ አዋጆች በማውጣት ፣ በማሰር እና በሌሎች እኩይ ተግባራት ማዳከሙ ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ነው ዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማርያን ቡድን  መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ የመጀመሪያዋ ጦማር ‹‹የሚያገባው ትውልድ ፍለጋ›› በሚል ርዕስ የወጣች ሲሆን ይህም ዞኑ ከዚያ በኋላ ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች በሙሉ የቃኘ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ከየትኛውም ብሔር ፣ ሃይማኖትና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ያልወጣና አማራጭ ትርክት በማቅረብ ትውልዱ በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ማነቃቃትን አላማው ያደረገ ነበር፡፡ አቅማችን በፈቀደ መጠን ከአለፉት ትውልዶች በተለይም ከያ ትውልድ ለመማር ሞክረናል፡፡ የሀገሪቱ ችግሮች ውስብስብ መሆናቸውን በመረዳት የትውልድ አቻዎቻችንን እኛም የምንማርበት መድረክ እንዲሆን ምኞታችን ነበር፡፡ ዝምታው ተሰብሮ በኃላፊነት ውይይት እንዲጀመር ተነሳሽነቱን ወሰድን፡፡ 
የውይይቱ መንፈስም ከጽንፈኝነት የፀዳ የሀሳብ ልዩነትን የሚያከብር እና ለአካዳሚያዊ ሀሳቦች ልዕልና የሚሰጥ ለማድረግም ሞክረናል፡፡( ህገ መንግስቱ ይከበር ሰንል የወያኔን ህገ መንግስት እውቅና ሰጡ ብለው ያጣጣሉን ድምጾች ቀላል አልነበሩም) ሀገራችን ያላት ደካማ የውይይት ባህልና ሥርዓቱ በየጊዜው የሚፈጥሯቸው ወደር የለሽ ብሶቶች ዋነኛ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ እኛም የዚህ ማኅበረሰብ ባህልና ታሪክ ውጤቶች በመሆናችን መፈተናችን አልቀረም ፡፡ ነገር ግን ለጫና አልባው ውይይት (endless conversation) በተለይ እርስ በርሳችን በነበረን መስተጋብር ታማኞች ነበርን፡፡
ብዙዎች እንደቂልነት ሊወስዱት ቢችሉም የውይይቱ መድረክ አፍቃሪ ኢኅአዴግ የሆኑ ሰዎችና ራሱን ስርዓቱን የሚጨምርና የማያበሳጭ እንዲሆን በተቻለን መጠን ጥንቃቄ እናደርግ ነበር፡፡ ይህንን ጥረታችንን ብዙ ሰዎች  ትንሽ ሙከራችንን በለጋስነት እንዲወስዱት አደረጋቸው፡፡ ይህ ለጋስነት በሀገር ውስጥ እና በባህር ማዶ የሚገኙ የምናከብራቸው ሰዎችንና ተቋማትን ይጨምራል፡፡ እንደጠበቅነውም ብዙ ያልሆኑ ነገር ግን በቂ ሊባሉ የሚችሉ የትውልድ አቻ ወዳጆችን አፈራልን፡፡ ዞኑም የዘጠኝ ሰዎች ብቻ መሆኑ አከተመ፡፡ ‹‹ይህንን ብታስተካክሉት›› ‹‹ይህቺን ደግሞ እንዲህ ብታደርጓት›› እያሉ ድካማችንን እና ስንፍናችንን ማየት የማይፈልጉ ብዙ ሆኑ፡፡ 
በዚህ ሂደት እኛም ብዙ ተማርን፡፡ የተወሰኑ ኢ-መደበኛ የቡድኑ አባላትም የሕይወት ውሳኔዎችን በመወሰን ስራዎችን በመተው አራማጅነትን እና ጦማሪነት ጋር የተያያዙ ሙያዎች ውስጥ ገቡ፡፡ በፊት የምናከናውናቸውን ትንንሸ ስራዎች መስራት ለእኛ የማያረካ አክባሪዎቻችንንም መናቅ ሆኖ ተሰማን፡፡ ለበለጠ ስራ እራስን ወደ ማዘጋጀት ያሉብንን የአቅምና የቁርጠኝነት ችግሮች ለመፍታት ረዘም ያሉ እቅዶችን ያዝን፡፡ 
እኛ እንዲህ እና እንዲያ እያልን እናስባለን፡፡ መንግስት ደግሞ ስልካችንን ጠልፎ ከዋልንበት እየዋለ በብዙ ጆሮዎችና አይኖች እየሰለለን ወንጀል ሳይሆን ሰበብ ፈልጎ ሊያስረን አድፍጧል፡፡ በመጀመሪያ ‹‹ለራሳችን ትክክል ያልሆነ ትልቅ ግምት ስለሰጠን ነው እንጂ መንግሥት እኛን ምን ሰራችሁ? ምንአጠፋችሁ ብሎ ያስረናል?›› ብለን አጣጣልነው፡፡ የመታሰራችን ምልክቶች ሲገዝፉ ደግሞ ከብዙ ማሰላሰሎችእና ክርክሮች በኋላ እስከአሁን ያደረግነው ‹‹ወንጀል››  ከሆነ ካቴናው በእጃችን እንዲገባ ፈቅደን ጡመራውን እንደምንቀጥል በይፋ አውጀን ተመለስን፡፡ 
ጤናማ ሕዝባዊ ተዋስኦ (Public Discourse) እንዲዳብርና ኃላፊነትየሚሰማው ትውልድ እንዲፈጠር መድከም በእኛ የተጀመረ አይደለም፡፡ ብዙዎች በእስር፣ በግዞት (በስደት) እና በሞት ዋጋ የከፈሉበትነው፡፡ የኛን ትውልድ መንፈስ ለማረቅ ያደረጉት እያንዳንዱ ነገር በህሊናችን የገነነና በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ነው፡፡ ማንም ሊቀይረው በማይችለው የተፈጥሮ ኡደት እኛም ባለተራ ሆነናል፡፡ አገር አገር የምንለው በግልብ ብሔረተኝነትና በአጉል አርበኝነት መንፈስ በመነሳት አይደለም፡፡ የሀገር አመሰራረት ንድፈ ሀሳብና የአለማችን ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታ በመገንዘብ ነው እንጂ፡፡ ሀገራችን ከታሪኳ፣ከራሷና ከአሁኗ ጋር እንድንታረቅ ዋና ፍላጎታችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው የመናገር ነፃነት ሳይገደብ ሁሉም የሀገሪቱ ጉዳዮች የሰለጠነ ጫና አልባ ውይይት ሲደረግባቸው እንደሆነ እናምናለን፡፡
ከትውልድ ጥቂቶችን በማሰር፣ ከሀገር እንዲወጡ በማስገድዶ በማሰደድ እና በመግደል የትውልድ ጥያቄን መቀልበስ ይቻላል ብሎ የሚያስብ ቢኖር እንዳይስት ይጠንቀቅ፡፡ የ1953ቱን መፈንቅለ መንግሥት  መክሸፍን ተመልክቶ ንጉሱ የመፈንቅለ መንግሥቱን ጠንሳሾች በማሰርና በአደባባይ በመስቀል የትውልዱን የለውጥ ጥያቄ ያዳፈኑ መስሏቸው መሰረታዊ ማሻሻል ማድረጉን እንዳይዘነጉ ከመከሩ ሰዎች ውስጥ አንዱ ደራሲ ዶክተር ሀዲስ አለማየሁ ናቸው፡፡ በዚህ ታሪካዊ ምክራቸውን ንጉሱ ከቁብ ባይቆጥሩትም‹‹ለማናቸውም ነገር መነሻ የሆነው ሥሩ እንደተደበቀ ተቀምጦ ከላይ እንደሚታየው ቅርንጫፉን ብቻ ቢጨፈጭፉትና ለጊዜውእንኳ የጠፋ ቢመስል የተመቸ ጊዜ ሲያገኝ የተደበቀው ስር ዳብሮ ተስፋፍቶ ለመጥፋትም እንደሚያስቸግር ሆኖ ይነሳል›› ብለው ተንብየው ነበር፡፡ የዚህ ዘመንም ነገር ጥቂት እድሜ የሰጠው ሰው ሲፈፀም የሚያየው ነው፡፡ 
እስር ሲታሰብ ብዙ ስጋቶች ወደ አዕምሮ ይመጣሉ፡፡ ከሁሉም የሚከብደው ግን ቤተሰብን ማንገላታትና በማረሚያ ቤት ተረስቶ መቅረት ነው፡፡ ቀበቶዬን አስረክቤ ወደማረሚያ ቤት ስወሰድ ይህንን እያወጣሁኝ እያወረድኩኝ ነበር፡፡ ያለፉት ሰባት ወራት የእስር ቆይታዬን ግን በመጠኑም ቢሆን መሳሳቴን ነግሮኛል፡፡ ማዕከላዊ ጨለማ ቤት በነበርኩኝ ጊዜ ጠያቂ ሰው ማግኘት የሚፈቀደው በሳምንት አንድ ቀን ለቤተሰብ አባላት ብቻ ነበር፡፡( እሱም ከሁለት ሳምንት “ምርመራ” በኋላ ከቤተሰብ ውጭ ጠያቂ ሲመጣ እኛን ማግኘት ስለማይፈቀድ የጠያቂው ስም በቁራጭ ወረቀት ላይ ተፅፎ ይመጣ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ለእኔ ብዙ ትርጉም ነበራቸው፡፡ በእስር ቤት አለመረሳቴን እና ስለእኔ እስር የሚጨነቁ ወዳጆች እንዳሉኝ እዚያ ጨለማ ቤት ያለሁት ለግልጉዳዬ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ ጉዳይ(public cause) ይዤ መሆኑ እያስታወሰ መንፈሴ ሳይሰበር ያኖረኝ ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ስንቀርብ ከሩቅ የማያቸው ብዙ ፊቶች መንፈስን የሚያረጋጉና የሚያጽናኑ ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥ እና በባህር ማዶ ያሉ የቅርብ ጓደኞቻችን በአካልነው እንጂ በመንፈስ ከእኛ ጋር አልታሰሩም ማለት ይከብዳል፡፡ ከከንፈር መጠጣ በዘለለ  እስሩ እንዳይከብደን እና በሕግ ፊት (ይፈተን ዘንድ ነው እንጂ የፍትሕ ስርዓቱ ብቻውን ተነጥሎ ጤናማ እንደማይሆን ለቀባሪው ማርዳት ነው) ንጽህናችንን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገውን ከማድረግ አልቦዘኑም፡፡ 
ማንዴላ አንድ ሰው ወህኒ እስኪወርድ ድረስ በእውነት ሀገሩን አያውቃትም(It is said that no one truly knows a nation until one has been inside its jails) ያለው ምንኛ ልክ ነው! እኛም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንደገባ ተማሪ በግርምት እየተማርን ነው፡፡ ከመማር የሚገኝ ደስታ ደግሞ እጅግ ጣፋጭ ነው፡፡
አሁን……..
አሁን በምናብ ወደ አዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኛ ማረፊያ ቤት (ቂሊንጦ)እንሂድ፡፡ የእኛው ቀለብ (Ration) በጎላና በሰፌድ ተደርጎ እየገባ ነው፡፡ ድምጽ ማጉያው ‹‹ሰዓቱ የቆጠራ ስለሆነ ማንኛው ታራሚ በየቤቱ በር ላይ እንዲሰለፍ ›› እያለ ይለፍፋል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎችበኋላ የቤቱ በር ከውጭ ይቆለፋል፡፡ የቤቱ ካቦ የቤቱን በር እየደበደበ ‹ቆጠራ! ቆጠራ!ቆጠራ!..... እያለ ይጮሀል፡፡ በፊት በቀላሉ የማደርጋቸው ማኪያቶ እንደመጠጣትና በአውራ መንገድ ነፋሻ አየር እየተቀበሉ በዝግታ መራመድ የማልችል እስረኛ ሆኛለሁ፡፡ነገር ግን ሰማዩን እያየሁ ስለነገ፣ ስለአገሬ አልማለሁ፡፡ ህልም እንደሆነ አይታሰር!

4 comments:

  1. The article has truly peaked my interest.

    ReplyDelete
  2. I do not know who you are but certainly you’re going to a famous blogger,

    ReplyDelete
  3. You were great and everyone received so much from your experience and knowledge

    ReplyDelete
  4. Absolutely amazing, thank you for sharing your knowledge with me.

    ReplyDelete