ወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ
ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስልጣን በያዘበት ማግስት ነው፡፡ በጊዜው የነበረው የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና
ቀይ ቀለማትን ብቻ ያዘ ነበር (በርግጥ በሕግ የተደነገገ ባይሆንም በአንዳንድ የደርግ ተቋማት ውስጥ ሰማያዊ መደብ ያለው ሰንደቅ
ዓላማም ይስተዋል ነበር)፡፡ የወቅቱ ባለስልጣናትም አረንጓዴ፣ ቢጫ
እና ቀዩ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የብሄሮችን መፈቃቀድ የሚገልፅ አርማ መኖር አለበት፤ አርማውስ ምን አይነት ይሁን? የሚል ሃሳብ ይቀርባሉ፡፡
የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ላጲሶ ጌ. ዴሌቦም ሀሳባቸውን እንደሚከተለው ሰነዘሩ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ተጨቁኖ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡
ስለዚህም በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው አርማ ይሄን ጭቆናውን የሚገልፅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ደግሞ ‘ከአህያ ምስል’
የተሻለ አርማ የለም፡፡ ሕዝቡ እንደ አህያ ለዘመናት አምባገነንነት ተጭኖበት በጭቆና ውስጥ ነበርና፡፡››
ይህ ከሆነ 17 ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ
የወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/ 2001 በአንቀፅ 4 ላይ እንዳሰፈረው ‹‹ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ መስከረም
ሁለኛ ሳምንት ሰኞ በድምቀት ይከበራል፡፡›› ከአዋጁ መውጥት አስቀድሞ በሰኔ 2000 ዓ.ም በግለሰቦች አነሳሽነት መከበር የጀመረው
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ “ሰንደቃላማችንን ከፍ አድርገን በመለስ ቀያሽነት
የተጀመረውን ህዳሴ እናረጋግጣለን!” እንደሚከበር ተገልጿል፡፡ ነገር ግን የዘንድሮው ክብረ
በዓል በአዋጁ ከተደነገገው ቀን አልፎ ጥቅምት 19/2005 ዓ.ም ነው የሚከበረው፤ ይሄን አስመልክተን በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ዙሪያ ያሉ ሀተታዎችን ለመመልከት ተነሳን፡፡
ሰንደቅ ዓላማ
ከሰንደቅ አላማ ቀለም እና ምልክት
ጀርባ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት እንዲሁም አንዳንዴ አስተሳብን የሚያመለክት መንፈስ አለ፡፡ የካውካሲያን ህዝቦችን (ለምሳሌ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣የሩስያ፣
የአውስትራሊያ ወ.ዘ.ተ) ሰንደቅ አላማዎችን ብንመለከት በአብዛኛው
ነጭ፣ ቀይ እና ሰማያዊ ቀለማትን ለሰንደቅ አላማነት ይጠቀማሉ፡፡ የቀለማቱም ምርጫ በተወሰነም መልኩ የህዝቦቹን አንድ አይነት አመለካከት
ይገልፃሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካዊያንን ሰንደቅ ዓላማ ስንመለከት አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ከፍ ብለው እና በተለያየ
አደራደር ተቀምጠው እናያለን፡፡ ይሄም ተመሳሳይ ምክንያት እንዲሸተን ያደርገናል፡፡
ታሪክ ወ አፈታሪክ
የሀገራችን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ
በሀገሪቱ ውስጥ አነታራኪ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ንትርኩም የሚጀምረው ከታሪካዊ አመጣጡ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም ጉዳይ ታሪክን
ከአፈታሪክ (History from Myth) ለመለየት አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር በዋነኛነት ጎልተው የሚሰሙትን ታሪኮች እና አፈታሪኮችን
አዳቅለን ለማየት እንሞክር፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለውን የኢትዮጵያ
ሰንደቅ ዓላማ ለምን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ሊሆን ቻለ? ለሚለው መልስ የተለያ ወገኖች የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡
ክርስቲያናዊ ትርጉሙም ገዝፎ ይታያል፡፡ እንደ አንዳንድ ፀሃፍት ‹‹የቀድሞ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ወደ ጦር ሜዳ ሲሄዱ የተለያዩ
የዛፍ ዝንጣፊዎችን ይዘው ይዘዋወሩ ነበር፡፡ የሚይዙት ዝንጣፊም አረንጓዴ በመሆኑ በተለያዩ ነገሮች አረንጓዴ ነገርን በማዘጋጀት
እንደ ቀዳሚው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሆነ፡፡›› በማለት አጀማመሩን ይገልፃሉ፡፡
አፈታሪኩ ሲያስከትልም ‹‹ኢትዮጵያ
ከሕገ ልቦና ወደ ሕገ ኦሪት በንግስተ ሳባ አማካኝነት ስትሸጋገር በእግዚአብሄር ተስፋ ማድረግን ለማመላከት ኢትጵያዊያኑ ቀድመው
ይጠቀሙበት የነበረው አረንጓዴ መለያ ላይ ቢጫ ቀለምን በመጨመር አንድ እርምጃ ወደፊት ተሻገ›› በማለት ክልኤቱ ይላል፡፡ ክርስቲያናዊ
አፈታሪኩ ሲቀጥልም ‹‹በንጉስ ባዚን ጊዜ ወደ እየሩሳሌም አቅንቶ ወንጌልን አውቆ የተመለሰው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ክርስትናን ወደ
ኢትዮጵያ ይዞ ከመግባቱ ጋር ተያይዞ፤ ኢትዮጵያዊያን እየሱስ ክርስቶስ በደሙ ቤዛ እንደሆናቸው በማመናቸው ቀድመው ይጠቀሙበት የነበረውን
አረንጓዴ እና ቢጫ መለያ ላይ ቀይ ቀለም በመጨመር አሁን ያለውን ቀለም እንዲይዝ አድርገውታል›› ይላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሰንደቅ
አላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ የሆነው እግዚአብሄር አለምን ዳግም በጥፋት ውሃ ላለመምታት ለኖህ የገባውን ቃልኪዳን የፈፀመው በቀስተዳመና
ነው፤ በቀስተ ዳመናውም ውስጥ ገዝፈው የሚወጡት ቀለሞች አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ በመሆናቸው የነሱን አምሳያነት ነው የሚል አፈታሪክ
ይደመጣል፡፡ ከዚሁ ከኖህ ጋር ተያይዞ ‹‹የጥፋት ውሃው በጎደለ ጊዜ እንደ ብስራት መግለጫ የታየው የወይራ ቅጠል መጀመሪያ አረንጓዴ፣
ሲቆረጥ ወደ ቢጫ በመቀየር መጨረሻ ላይ ቀይ ቀለምን በመያዝ ይደርቃል እናም ሰንደቅ ዓላማችን የወይራው ተምሳሌት በመሆን መልካም
ዜናን ገላጭ ነው›› የሚል አፈታሪክም ይደመጣል፡፡
የቅርብ ጊዜ ታሪኮች ደግሞ የኢትዮጵያ
ሰንደቅ ዓላማ የአሁኑን ቀለም የያዘው ባለፍት 150 ዓመታት በተደረገው ክለሳ ነው፡፡ ከዛ በፊት የነበረው ሰንደቅ ዓላማ ሌሎች
የተለያዩ ቀለማትን የያዙ ነበሩ ይሉናል፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች በአፄ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ጊዜ ነው የአሁኖቹ ቀለማት ጥቅም ላይ
የዋሉት ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ የለም የለም በአፄ ዩሃንስ አራተኛ ዘመነ መንግስት ነው ይላሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አይ በዳግማዊ ምኒልክ
ንግስና ዘመን ነው፤ ይህ የሆነው በማለት ታሪኩን ያወሳስቡታል፡፡ እንግዲህ የቀለማቱ ታሪክ እና ትርጉም ስምምነት ላይ ሳይደረስበት
ሲሰረዝ እና ሲደለዝ አሁን የምንጠቀምበትን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት በሰማያዊ አርማ እና በቢጫ ኮከብ የታጀበ ሰንደቅ ዓላማ
ላይ ደርሰናል፡፡ ውዝግቡ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ እስኪ በአሁኑ ወቅት በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ የሚነሱትን አንዳንድ የውዝግብ
ነጥቦች እያነሳን እንመልከት፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ወይስ ሰንደቅ ዓላማዎች?
ከጣሊያን ወረራ በማስከተል በተፈጠረው
አጋጣሚ ኢትዮጵያ የቀድሞ የግዛት አካሏን እና ለ50 ዓመታት በጣሊያን ቅኝ ግዛት ምክንያት ተነጥሎ የኖረውን የግዛት ክፍሏ ይመለስላት
ዘንድ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመለከተች፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ከረጅም እና አታካች ውይይት እና ግምገማ በኋላ
በአሜሪካን መንግስት አነሳሽነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሃድ ወሰነ፡፡ ኢትዮጵያም በውሳኔው ለጊዜው ግር ብትሰኝም
እንደ አሜሪካን እና ህንድ አይነት ታላላቅ ሀገሮችም በዚሁ የፌደሬሽን ስርዓት እንደሚመሩ መገለፁ ብዥታውን እንዲያለዝበው ሆነ፡፡
ነገር ግን በብዙ ኢትዩጵያውያን
እና በኤርትራ የሚገኝው የአንድነት ማህበር (The Unionist Party) ፤ ኤርትራ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ተለይታ የራሷን
ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለቧ አልተዋጠላቸውም ነበር፡፡ ይሄም ነገር ይቀለበስ ዘንድ አብዝተው በመጎትጎታቸው ለ10 ዓመታት የቆየው ፌደሬሽንም
በንጉሱ ፊርማ ፈረሶ የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማም ጉዳይ አከተመ፡፡
የኢህአዴግን ስልጣን መያዝ ተከትሎ
የኤርትራ መገንጠል ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ያስደነገጠ ጉዳይ ነበር፡፡ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ተረቆ የፀደቀው የኢፌደሪ ሕገ መንግስት
ፌደራሊዝምን እንደ መንግስታዊ መዋቅር መቀበሉ ደግሞ አንዳንድ ወገኖች በተለይም አጥባቂ ኢትዮጵያዊንን (Ultranationalists) ‹‹ይህች ሀገር ተገነጣጥላ ልታልቅ
ነው›› የሚል ሌላ ስጋት ውስጥ ከተታቸው፡፡
ሕገ መንግስቱ የፌደራል ስርዓቱ
በክልልሎች እንደሚዋቀርና እያንዳንዱ ክልሎችም የራሳቸው የሆነ ሰንደቅ ዓላማ እና አርማ እንደሚኖራቸው መደንገጉ፤ ለነዚህ ወገኖች
የኢህአዴግን ፀረ-ኢትዮጵያዊነት መረጋገጫ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ ‹‹ፌደራሊዝሙ እንደዚህ ካልተዋቀረ አብረን መኖራችን ያሰጋናል፤
ክልሎች የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ እና ዓርማ እንዲኖራቸው መፍቀዱ ደግሞ አሜሪካን በሚያክል ትልቅ ሀገር ሳይቀር ተቀባይነት ያለው
የራስን በራስ የማስተዳደር አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በተወሰኑ ቀለማት ብቻ አትገለፅም፡፡›› የሚሉ ምላሾችን በመስጠት ለክልሎች
የራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲመርጡ አስቻላቸው፡፡
ከዛን ጊዜ ወዲህ የሱማሌ ክልል
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ 11 ርዕሰ መስተዳደሮችን የቀያየረ ሲሆን፤ በሰንደቅ ዓላማ መቀየሩስ ለምን ይቅርብኝ?
በሚመስል ምክንያት ሁለት የተለያዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን ቀይሯል፤ ይሄም ድርጊት ብዥታን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በሌላ በኩል የትግራይ
ክልል ሰንደቅ ዓላማ ህወሃት በትግል ወቅት ይጠቀምበት የነበረው ሰንደቅ ዓላማ ለትግራይ ክልልም ማበርከቱ ትክክል አይደለም የሚል ሀሳብ መነሳቱ አልቀረም፡፡
እንግዲህ አንድ ሀገራዊ ሰንደቅ
ዓላማ? ወይስ ሁሉም ክልሎች ከሀገራዊ ሰንደቅ ዓላማው ጎን ለጎን የሚያውለበልቡት የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማዎች? የሚለው ሃሳብ አነታራኪነቱን
ይዞ ቀጥሏል፡፡
‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው ... አንዳንድ
ሀገሮች ከወረቀትም ይሰሩታል››
ባለፉት ዓመታት ሰንደቅ ዓላማ በተነሳ
ቁጥር የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መነሳታቸው አልቀረም፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› ማለታቸው
እንደ አንድ ሀገሩን የማይወድ መሪ እንዲቆጠሩ ያደረጋቸው ሲሆን፤ ከብዙ ኣመታት በኋላ ‹‹ባንዲራ ጨርቅ ነው›› ሲሉ ምን ማለታቸው
እንደሆነ ሲጠየቁ፤ ‹‹አዎ ባንዲራ ትርጉም ከሌለው እንደወረደ ጨርቅ ነው፤ እንዲያውም አንዳንድ ሀገሮች ከወረቀት ይሰሩታል፡፡ ባንዲራ
ትርጉም ይኖረው ዘንድ ዜጎች ሊወዱት እና ትርጉም ሊሰጡት ይገባል፡፡›› በማለት ምክንያታቸውን ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡
ነገር ግን ማሳመኛቸው ያልተዋጠላቸው ሰዎች ‹ምንም ቢሆን እንደ ሀገር መሪ
እንደዚህ ማለት አልነበረባቸውም›› በማለት ሀሳባቸውን ያጣጥሉባቸዋል፤ አቶ መለስንም በፀረ-ኢትዮጵያዊነት ይፈርጇቸው ነበር፡፡ መለስ
ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ባሉ በዓላት ላይ በመገኝት ስማቸውን ለማደስ መጣራቸው አልቀረም ነበር፡፡
The Magic Emblem
ሌላው በአሁኑ ወቅት በሰንደቅ ዓላማ
ጉዳይ ላይ ጎልቶ የሚነሳው ክርክር፤ በአሁኑ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው አርማ ምንነት እና ትርጉም ነው፡፡ ለዛም ይመስላል
ጉራማይሌ የሆነ የሰንደቅ ዓላማ አይነት በየቦታው የምንመለከተው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሰት በአንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ እንዲሁም
ተሻሽሎ የወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 654/2001 በአንቀፅ 8 ላይ እንዳስቀመጡት በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ ሰላምን፣
እኩልነትን አንድነትን እና ተስፋን ገላጭ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ይህ ትርጉም ያልተዋጠላቸው ወገኖች ምልክቱን በብዙ መልኩ በመተርጎም በህገ መንግስቱም ሆነ
በአዋጁ የተጠቀሱት የአርማው ምክንያት ውሸት ነው ይልቅስ ‹‹የአንድ ብሄርን የምግብ አይነት አመላካች ነው›› ፣ አይ ‹‹ምልክቱ
የኢህአዴግ አመራሮች ከሶሻሊዝም ምንጭ እየጠጡ (From Socialism Background) የጎለመሱ በመሆናቸው የሶሻሊዝሟን ኮከብ
በአቋራጭ ሰንደቅ አላማዋ ላይ ማስቀመጣቸው ነው፡፡›› ይላሉ፡፡ ይባስ ብሎም አንዳንዶች ‹‹የጥንቆላ ምልክት ነው፤ እንጅማ የኮከብ
ምስል ከኢትዮጵያ ጋር ምን አገናኝው?››› ይላሉ፡፡
የሆነ ሆኖ የሰንደቅ ዓላማ አዋጁ
በሕገመንግስቱ ከተቀመጠው ዓርማ ውጭ የተሰራ ሰንደቅ ዓላማን መጠቀም እስከ አንድ አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን
የሚደነግግ ሲሆን፤ የኮከቡን አርማ ከያዘው ሰንደቅ አላማ ውጭ ያሉ ታሪካዊ ሰንደቅ ዓላማዎች በቤተ መዘክር እንደሚቀመጡ እና በአረጁ
ጊዜም እንደሚቃጠሉ ይገልፃል፡፡
ዳግማዊ ቦሊቪያን መቅደም
በንጉሱ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያን
ሰንደቅ አላማ በአንዳንድ የትርጉም ምክንያቶች ከአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ወደ ቀይ ቢጫ እና አረንጓዴነት ለመቀየር ኢትዮጵያ ለተባበሩት
መንግስታት ድርጅት አመልክታ ይህ አደራደር በደቡባ አሜሪካዊዋ ሀገር ቦሊቪያ የተያዘ መሆኑን ተገልጾ ጥያቄዋ ውድቅ ተደርጎባታል፡፡
እንደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት
ድርጅት (መኢአድ) ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰማያዊ አርማ የሌለበትን ንፁህ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ትክክለኛው
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በመቁጠር፤ በፓርቲያቸው ፕሮግራም ውስጥ ያካተቱ ሲሆን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትም የቦሊቪያው ታሪክ
እንዳይደገም ይሄን ቀለም የያዘ ሰንደቅ ዓላማ ለሌላ ሀገር እንዳይፈቅድ እስከ መጠየቅ ደርሰዋል፡፡
የሀገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰንደቅ
ዓላማ ጉዳይ ላይ እንኳን ስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡ ለየትኛው ሰንደቅ አላማም ክብር (Allegiance) እንደሚሰጡም አልተስማሙም፡፡
ይህ ልዩነት ህብረተሰባችን ውስጥም አለ፡፡ ብቸኛው መፍትሄ ወደ ውይይት ቀርቦ ሀሳብን መሸጥ እና መግዛት ነው፡፡ ያለዚያ የተለያየ
ሰንደቅ ዓላማ ይዘን የኢትዮጵያን ጥቅም በጋራ ማስጠበቅ እንዴት ይቻለናል?
I don't see any problem with the current flag. The emblem in the middle is nothing but a symbol that shows a promise made by the nations, nationalities and people to live together as one or am I missing something here?
ReplyDelete