Sunday, December 9, 2012

የሰሞኑ ጋዜጦችና መጽሔቶች




ላይፍ መጽሔት
·         የ‹‹ሰው ለሰው›› ድራማ ቀጣይ ድራማዎች
‹‹ሰዎቹ መካሪ የላቸውም እንዴ›› አስተያየት ሰጭዎች፤
መስፍን ጌታቸው የፍቅር ጥያቄ አቅርቦልኝ  አልተቀበልኩትም›› ተዋናይት ብስራት ገመቹ፤ ‹‹ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ ብትሰሩ ትሩ ይመስለኛል››  ደራሲ መስፍን ጌታቸው፤
·         የአባ ጳውሎስ ተተኪ የመምረጥና የእርቅ ፈተና፤ ማን መንበሩን ሊያገኝ ይችላል?
‹‹ጉባዔ ካህናት ወመምዕናን ለቤተክርስቲን ሠላም›› ትውልድ የሚወርሰው እርቀ ሰላም በሁለቱ ሲኖዶሶች እንዲወርድ ጠየቀ፤
·         ‹‹የስኬትን መንገድ ጀመርኩት እንጂ አልደረስኩበትም›› ተዋናይ ሄኖክ ብርሃኑ
·         የኢትዮጵያ ዘመናዊ የህጻናት የውጭ ንግድ፤ መንግስት ችላ ያለው የሞት መንገድ፣
·         በሕግ የበላይነት እየተሳለቁ እስከመቼ?
o    በድብደባ የስድስት ወር ጽንስ አስወጥቶኛል፣
o    የባለቤቴንና የልጄን ብልት በአጎበር ገመድ ጎትቶታል ተባባሪዎቹ አልተያዙም፣
o    የሰሻለ ህክምና እንዳገኝ ሕዝብ ይተባበረኝ›› ወ/ሮ ወርቅነሽ አድማሱ፣
·         የትራንስፖርት ትርምስ እስከመቼ?
·         ‹‹መድረክ ከኢህአዴግ ጋር ሊያላትመን ይፈልጋል›› በ1997 ኢህአዴግን በመወከል በደብረብርሃን ላይ ተወዳድረው የነበሩት ወ/ሮ የሺ ፈቃደ የኢትዮጵያ ምርቻ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ
·         ሌላም፣ ሌላም…

Friday, December 7, 2012

ሰብኣዊ መብቶች፣ ሕገ-መንግሥቱ እና መንግሥት




ሰሞኑን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማዳመጥ ፍቃደኝነት ካሳያችሁ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከሕገ -መንግሥቱ መጽደቅ ጋር ተያይዞ ለአንድ ሳምንት እየተከበረ ይገኛል፡፡ በትምህርት ቤቶች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ በዓሉ ለቀናት (ለአንድ ሳምንት) እንዲከበር ተወስኗል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን ቀን ተከትሎ ለ7ተኛ ጊዜ የሚከበረው በዓል ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፋቸው መብቶች ብሎ ብዙዎቹ ብሔር ብሔረሰብ ላይ ያተኮሩ መብቶችን ሲያነሳ ሌሎቹን ደሞ ከተግባራዊነታቸው አለያይቶ ለብቻቸው ያስተዋውቃቸዋል፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በሶስተኛው ምእራፍ መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ብሎ በተለምዶ ሰብአዊ እና ሲቪል መብቶች የምንላቸውን ያስቀምጣል፡፡ በክፍል አንድ በ15 አንቀጾች ሰብኣዊ መብቶች የተቀመጡ ሲሆን በዚሁ ምዕራፍ ክፍል ሁለት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስር16 አንቀጾች ተካተዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት መብቶች ከጥቂቶቹ (አንቀጽ 39 ለዚህ ምሳሌ ነው) በስተቀር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕገ መንግሥቱን ሰብኣዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ትኩረት የሰጠ እና የተለየ ያደርጉታል፡፡

ወደ ተግባሩ ሲመጣ ባለፉት 18 ዓመታት  ከጽሑፉ ጋር በፍጹም የማይገናኙ ብዙ የተግባር ጥሰቶችን አንደግለሰብም እንደ አገርም  አስተናግደናል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ግልጽ ጥሰቶች  አስተዳደራዊ ይምሰሉ እንጂ በባሕሪያቸው በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን የሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎች በግልጽ የሚቃረኑ ከመሆናቸውም ባሻገር በተለያዩ የመንግስት አካላት በመጣሳቸው እንደቁምነገር እንደማይቆጠሩ ያሳያል፡፡

የተናቁ አንቀጾች

በምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ በሰብኣዊ መብት ክፍል ከተደነገጉት ዐሥራ አምስት (15) አንቀጾች መካከል ቢያንስ ዐሥራ ሁለቱ በግልጽ በተደጋጋሚ በመንግስት ተጥሰዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ድንጋጌዎች ሊያከብሩዋቸው በሚገቡ የመንግስት አካላት ዘንድ እንደ ቅንጦት ሲቆጠሩ ሌሎቹ ደግሞ በአፈጻጸም ወለምታ ይታሻሉ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን አረጋግጦ በሕግ ካልተደነገገ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ ይናገራል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሕጻናት እና ወጣቶች ሳይቀር በየመንገዱ ሲገደሉ ምስክር የሆንበት ጊዜ ቅርብ ትዝታ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ዜጎች ሕይወታቸውን በሕግ ባልተደነገገ ሁኔታ ማጣት እንደ አንድ ሰብኣዊ መብት ጥሰት ሳይሆን እንደ የአንድ ሰሞን የፓለቲካ አለመረጋጋት ውጤት ብቻ መቆጠሩ፣ የኦጋዴን ጭፍጨፋን ዓይነት የብዙ ሰዎች ሕይወት ያለምንም ሕጋዊ ድንጋጌ የተቀጠፈበትን የመብት ጥሰት በዝምታ መታለፉ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 15 መናቅ ውጤት ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 16 ማንም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ ሕጋዊ ከለላ ቢሰጠውም ይህንን የመብት ጥሰት በዋናነት የሚፈጽሙት ሕግ አስከባሪዎቹ የመንግስት አካላት ናቸው፡፡ ከመንገድ ላይ አንስቶ እስከ ሕጋዊ የፓሊስ ጣቢያዎች ድረስ ያለምንም ማቅማማት እንደሥራም ጭምር ቆጥረው ከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚያደርሱት እነዚሁ የመንግስት አካላት ናቸው፡፡ (ይህ አንግዲህ በደህንነት ነኝ ባይ አባላት እና በስርዓቱ ተጠቃሚዎች የሚፈፀመውን የአካል ጉዳት ሳንጨምር ነው፤) ይህ ከማንኛውም አካላዊ የአካል ጉዳት የመጠበቅ መብት በራሱ በመንግሥት ማረሚያ ቤቶች እንኳን መከበር አቅቷቸው የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ወቅት የሚደርስባቸውን የአካል ጉዳት ለአደባባይ ሲያቀርቡ መስማት ለሕግ አስፈጻሚ አካላት የተለመደ እና እርምጃ ያልተወሰደበት የመብት ጥሰት ነው፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹን የአንዱአለም አራጌን እና ዘሪሁን ገ/እግዜያብሔር በእስረኞች የደረሰባቸውን ከፍተኛ የአካል ጉዳት እና ማረሚያ ቤት ውስጥ ተቀምጠው እንኳን ያጡትን የአንቀጽ 16 ሕጋዊ ከለላ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ዜጎች ክስ ሳይቀርብባቸው እና ሳይፈረድባቸው እንደማይታሰሩ አንቀጽ 17 ቢደነግግም በተቃራኒው ግን ለረዥም አመት ሳይፈረድባቸው ሕይወታቸውን በእስር ቤት የሆኑ ዜጎች ቁጥር መንግሥት የሚታማበት ሰብኣዊ መብት አያያዝ ነው፡፡

Thursday, December 6, 2012

ሕገ መንግስታዊነት


የፈረንሳዩ ንጉስ ልዊ  17ኛ የአምባገነንነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ስልጣኑን ሲያስረግጥም ‘I am the State’ በማለት ነው፡፡ አዎ ልዊ 17ኛ የአምባገነንነትን መጨረሻ ጫፍ አሳውቆናል፡፡ ‹ሀገር የእኔ፤ አኔም ሀገር› ብሎ ማወጁ ‹የፈለኩትን ማድረግ እችላለሁ፣ ፈላጩም ቆራጩም እኔ ነኝ!› እንዲል አደርጎታል፡፡
እንግዲህ በተለየዩ ሀገራት የመንግስት አካላትን ስልጣን በሕግ መገደብ አስፈላጊ የሆነት ዋነኛ ምክንያት እንዲሃ ያለውን ልቅ የስልጣን ምቾት ለማለዘብ ነው፡፡ ሕገ መንግስት ደግሞ ስልጣንን ለመገደብ ተብለው ከሚቀመጡ ገደቦች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ግን ሕገ መንግስት መኖሩ ብቻ ባለስልጣኖችን ስርዓት ለማሲያዝ ይበቃልን?

ሕገ መንግስታዊነት ስንል

ሕገ መንግስታዊነት መነሻውም መድረሻውም ሕገ መንግስቱ ነው፡፡ የሕገ መንግስታዊት ፅንሰ ሀሳብም ከሕገ መንግስት ፅንሰ ሀሳብ ጋር አብሮ የዳበረ ሀሳብ ነው፡፡ Walton Hamilton የተባሉት የህግ ባለሙያ ሕገ መንግስታዊነትን ሲያብራሩ “Constitutionalism is the name given to trust which men to repose in the power of words engrossed on parchment to keep the government in order.” ማለትም ‹‹ሕገ መንግስታዊነት ሰዎች በፅሁፍ ለተቀመጡት እና መንግስትን ስርዓት ለሚያስገቡት ቃላቶች የሚሰጡት እምነት ነው፡፡›› በማለት ነው፡፡ በጥቅሉም ሕገ መንግስታዊነት ስንል ሕገ መንግስቱን ተግባራዊ ማድረገ ማለታችን ነው፡፡ ከዚህ መሰረታዊ ሀሳብም ሁለት አንኳር ጉዳዮችን ማውጣት እንችላለን፡

እምነት (Trust)

እምነት ሰዎች በሕገ መንግስቱ ተማምነው እና ሕገ መንግስቱን እንደ ድጋፍ አድርገው በስርዓቱ ውስጥ የሚኖሩበት ተስፋ ነው፡፡ ሰዎች ሕገ መንግስቱን የሚያከብሩት ሌሎችም እንደኔ ሕገ መንግስቱን ያከብሩታል፤ አናከብርም ቢሉ እንኳን መንግስት ይሄን አመኔታየን ያስከብርልኛል ብለው ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ በሕገ መንግስቱ የተቀመጡት ቃላት በስርዓቱ ያላቸውን አመኔታና በሕግ መንግስቱ ላይ ያላቸውን መመካት ገላጭ ነው፡፡ ተበዳይ ‹ኧረ በሕግ አምላክ› ብሎ መብቱን ሲጠይቅ፤ በዳይ (መንግስትም ሆነ ግለሰብ) ሕግን አስታውሶ እራሱን ከተግባሩ ሲገታ፤ ይሄ ነው ዜጎች በሕጉ ላይ ያላቸው እምነት፡፡ ‹ሕጉን አምኝ› እንዲሉ፡፡

መንግስትን ልክ ማስገባትና መገደብ (Limited and Restrained Government)

ሌላው የሕገ መንግስታዊነት ዋነኛ ግብ እና ዓላማ፤ መንግስትን በሕግ በተሰጠው ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ እና ከተሰተው የስልጣን ገደብ ውጭ ዝንፍ እንዳይል እንደ መቆጣጠሪያነት ማገልገሉ ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መንግስት የዜጎች ይሁንታ ውጤት እንደመሆኑ መጠን፤ ይሄ ይሁንታም በሕገ መንግስቱ የተገለፀ እና በሕገ መንግስታዊነት የሚተረጎም ነው፡፡ ዜጎች መንግሰታቸውን ሲያበጁ ያንተ ስለጣን እስከዚህ ነው፤ ከዚህ በላይ መጓዝ አትችልም ብለው በሕግ ለክተው ስልጣኑን ለመንግስት ይነግሩታል፤ መንግስትም በተሰመረለት ክበብ ውስጥ ይጫወታል፤ ያኔም ሕገ መንግስታዊነት አለ እንላለን፡፡ ስልጣኑ ተገድቦ ሕግን የሚተገብር መንግስትም (Limited Government) የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ዋነኛ ምሰሶ ነው፡፡

ሕገ መንግስቱ ስለ ሕገ መንግስታዊነት

የማንኛውም ሀገር ሕገ መንግስት በመሰረታዊነት ባለ ሁለት ጫፍ (Double Edged) ነው፡፡ በአንድ በኩል ለዜጎች እና ለመንግስት መብት ይሰጣል፣ ግዴታም ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ መብቶች እና ግዴታዎች እንዴት መሬት ይነካሉ፣ በማን ይፈፀማሉ ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ እንግዲህ ሕገ መንግስታዊነትን በዚህ በሁለተኛው ጫፍ ላይ ቆሞ እናየዋለን ማለት ነው፡፡  

ሕገ መንግስት ያለ ሕገ መንግስታዊነት

ሕገ መንግስታዊነት ዘመናት በጨመሩ ቁጥር አብሮ እያደገ  የመጣ ሀሳብ ሲሆን አሁን ባለው መሰረታዊ መግባባትም ሕገ መንገግስታዊነት ማለት መንግስትን እንደ መገደቢያ መሳሪያ፣ የፈላጭ ቆራጭነት ተቃራኒ (The Antithesis of Authoritarianism) እንዲሁም የአሉታዊው አምባገነንነት አዎንታዊ ፀር ተደርጎ የሚወሰድ ሰፊ ሀሳብ ነው፡፡ አዎ ሕገ መንግስት የሕግ የበላይነት ዋነኛ መሰረት ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ መንገስታዊነት በሌለበት ሕገ መንግስት ከወረቀት ላይ ነብርነት አይዘልም፤ አስፈላጊነቱም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህ ጥሩ ማነፃፀሪያ የሚሆኑን የ1923ቱ የኢትዮጵያ ሕገ መንገስት እና የ1947ቱ የተሻሻለው ሕገ መንግስት ናቸው፡፡ የ1923ቱ ሕገ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝው መሬቱም፣ ሕዝቡም ሕጉም የንጉሰ ነገስቱ ነው ብሎ ፍፁማዊ እኔ ሀገር ነኝን (I am the State) ይሰብካል፤ በሕግ መግዛት (Rule By Law) እንጅ ለሕግ መገዛት (Rule of Law) ፈፅሙ ያልተፈቀደ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ይሄ ሕገ መንግስት ወደ መሬት ወረደም አልወረደም ለዜጎች የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡
በሌላ በኩል የተሻሻለው 1947ቱ ሕገ መንግስት ደግሞ 20 የሚበልጡ አንቀፆችን፤ መምረጥ እና መመረጥን መብት ጨምሮ ለዜጎች የተሰጡ መብቶችን ለመደንገግ አውሏቸዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያዊያን ህይወት መሻሻል አለመቻሉ ለንጉሱ ስርዓት ውድቀት ዋነኛ መነሻው ነበር፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሕገ መንግስታዊነት አለመኖሩ ነው፡፡ እናም ሕገ መንግስታዊነት ከሌለ የሕገ መንግስት መኖር በህግ መግዛትን እንጅ ለሕግ መገዛትን አያመጣም፤ ጥቅሙም አይታይም፡፡  

ሕገ መንግስታዊነት ‘በልማታዊት’ ኢትዮጵያ

የአምሰተርዳሙ ነዋሪ እና በኢትዮጵያ ላይ እጅግ ብዙ ጥናቶችን እና ምርምሮችን ያደረጉት ፕሮፌሰር ጆን አብኒክ ‘Ethiopia Ethnicity and Constitutionalism in the Contemporary Ethiopia’ ባሉትና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት (የኢፌድሪ ሕገ መንግስት) ላይ ባተኮረው ፅሁፋቸው  “When reading the constitution it is also notable that how far the proclaimed text s removed from the actual practice of the political culture and social relations in.” በማለት ‹ሕገ መንግስት ወዲያ፤ ተግባር ወዲህን› ያዜሙልናል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ጆን አብኒክ ሁሉ በዛ ያሉ የምዕራብ የሰብዓዊ ተቋማት፣ የተለያዩ መንግስታት እንዲሁም የተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ሕገ መንግስቱና እና መሬት ላይ ያለው እውነታ እጅግ ይለያያል እናም ኢህአዴግ በእጁ ያለውን ሕገ መንግስት ያክብር እያሉ ይማፀናሉ፡፡

ሕገ መንግስቱን ማን ያክብረው?

የኢፌድሪ ሕገ መንግስት አንዳንድ አካላት እንደ አፍራሽ ሰነድ ቢመለከቱም አለም ዓቀፍ የሰብዓዊ ስምምነቶችን ሙሉ ለሙሉ መቀበሉ፤ እንዲሁም ከአጠቃላይ ከአንቀፆቹ ሲሶ (30 አንቀፆች) ያህሉን ለዜጎች መብትን ለመዘርዘር እና ለመስጠት ማዋሉን ስንመለከት፤ ሀገሪቱ ዘመናዊ የሕገ መንግስት ስርዓት ውስጥ ከገባች ጊዜ ጀምሮ የዜጎችን መብት በተሻለ ደረጃ በመለገሱ  ረገድ ትልቅ እምርታን ያሳየ ሕገ መንግስት እንደሆነ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ መብት በሽ የሆነበት ሕገ መንግስት ምነው ተቃውሞ በዛበት; ብለን ስንጠይቅ፤  መልሳችን ‹ሕገ መንግስታዊነት› የሚል ነው፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግስትም ሕገ መንግስታዊነት ወሳኝ እና ዋነኛ የስርዓት አካል አድርጎ በመውሰድ በተለያዩ አንቀፆቹ ሕገ መንግስቱ እንዲከበረና ሕገ መንገስታዊነት እንዲሰፍን ያስገድዳል፡፡
በጥቅሉ በአንቀፅ 9 ንዐስ ቁጥር 3 ላይ ‹‹ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌሎች ማሕበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ መንግስቱን ማስከበርና ለሕግ ተገዥ የመሆን ሀላፊነት አለባቸው፡፡›› በማለት ሁሉም ዜጋ ላይ ግዴታን ይጥላል፡፡

እንዲሁም በተለየ ሁኔታ የተለያዩ አካላትን ሕገ መንግስታዊነት ይስን ዘንድ እንዲሰሩ ያስገድዳል አንቀፅ 13 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ‹‹በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግስትና እና የክልል ህግ አውጭ፣ ሕግ አስፈፃሚና የዳኝነት አካላት በዚህ ምዕራፍ (በሕገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተካተቱትን መብቶች እና ግዴታዎችን ለማለት ነው) ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡››፣  አንቀፅ 51 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ ‹‹የፌደራሉ መንግስት ሕገ መንግስቱን ይከላከላል፣ ይጠብቃል፡፡›› ብሎ ያስቀምጣል፡፡ አንቀፅ 74 ንዑስ ቁጥር  13 ላይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንግስቱን ያከብራል፤ ያስከብራል፡፡›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሕገ መንግስታዊ ግዴታ ተወጭ ያደርገዋል እንዲሁም አንቀፅ 87 ንዑስ ቁጥር 4 ‹‹የመከላከያ ሰራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለሕገ መንግስቱ ተገዥ ይሆናል፡፡›› በማለት የመከላከያ ሰራዊቱ ለሕገ መንግስቱ በመገዛት ሕገ መንግስታዊነትን ያሰፍን ዘንድ ያስገድደዋል፡፡

እንግዲህ ሕገ መንግስታዊነት ይኖር ዘንድ አኒህ ሁሉ ግዴታዎች በሕገ መንግስቱ ተቀምጠው ነው፤ መንግስት ‹የምን ሕገ መንግስት› በማለት የመብት ጥሰቶች እና ኢ-ሕገመንግስዊነት አሰፍኗል ተብሎ እየተነገረ ያለው፡፡

ሕገ መንግስታዊነት እንደ አጀንዳ

ኢሕአዴግ ከምርጫ ዘጠና ሰባት ወዲህ በተቃዋሚው ጎራ ላይ ከለጠፋቸው ታፔላዎች አንዷ ‹የቫይማር ሪፐብሊክ (Weimar Republic) ናፍቆት› ትሰኛለች፡፡ በአጭሩ ሀሳቡ ከአንደኛው የአለም ጦርነት በኋላ የነአዶልፍ ሂትለር The Third Reich እስኪመሰረት ድረስ የነበረችው ጀርመንን ለማመላከት ሲሆን፤ ኢህአዴግ ሀሳቡን ሲያስቀምጥም ‹‹ተቃዎሚዎች እንደ ድህረ የመጀመሪያው የአለም ጦርነቷ የቫይማር ሪፐብሊክ ኢህአዴግን በማድከም ወደ ቫይማር ሪፐብሊክነት ቀይረው፤ በመጨረሻም ሒትለር የየቫይማር ሪፐብሊክን ግሩም ሕገ መንግስት ቀዳዶ እንደጣለው ሁሉ እነዚህ ተቃዋሚዎችም የኢፌድሪ ሕገ መንግስትን ቀዳደው ለመጣል የተዘጋጁ ናቸው›› እያለ በተለያዩ ሰነዶቹ ላይ ትችቶቹን ያቀርባል፡፡

ተቃዋሚው ጎራ ‹የሕገ መንግስት ይሻሻል› ጥያቄውን እንደ ያዘ ሕገ መንግስታዊነት እንዲሰፍን ቢተጋ ኢህአዴግን አጀንዳ ከማሳጣትም አልፎ ‹ሒትለር መጣብህ› ከሚል አለቅጥ የሚጮህ ኢህአዴግዊ ጅራፍ እራሱን ይጠብቃል፡፡ ለዜጎችም ቀላል እና የሕግ ጥልፍፎሽ ውስጥ የማያስገባ የመብት ጥያቄ መሆን ይችላል፤ ሕገ መንግስታዊነት ይስፈን - ሕገ መንግስቱ ይከበር እንደማለት፡፡

Wednesday, December 5, 2012

ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

ጉዳዩ፡- ሕገ መንግሥቱ በመንግሥት እንዲከበር ስለመጠየቅ

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር፣

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 74 ላይ የጠቅላይ ሚኒስትርን ሥልጣን እና ተግባር ሲደነግግ፥ ቁጥር 13 ላይ “[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፣ ያስከብራል” ይላል፡፡ ትንሽ ከፍ ብሎ ደግሞ በቁጥር 8 ላይ “የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብቃት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል” ይላል፡፡

እናም እርስዎ በቅርቡ አመራሩን የተረከቡት መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ሕገ መንግሥቱን በመጣስ የመቃወም፣ የመደራጀትና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንደወንጀለኝነት እንዲፈሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እያደረገ በመሆኑ እና በውጤቱም ብዙ ንጹሐን ዜጎች በሠላማዊ ትግል ተስፋ እየቆረጡ እንዲሳደዱ፣ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርጉ፣ “አሸባሪ” ድርጅቶችን እንዲቀላቀሉ እያስገደደ መሆኑን በመታዘቤ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ልጽፍልዎ ተገድጃለሁ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ ብቻ ያልሆነችውን ያክል እርስዎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበር ላይ እስካሉ ድረስ በእኩልነት እና በቅንነት የሚያገለግሉት የኢሕአዴግ ወዳጆችን ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ ነቃፌዎችንም ጭምር እንደሆነ ይዘነጋዎታል ብዬ ስለማልገምት ላስታውሶት አልደፍርም፤ ነገር ግን በተለያዩ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች የተተበተበች ድሀ አገር ውስጥ የሚኖር ገዢ ፓርቲ ከደጋፊዎቹ ይልቅ ተቃዋሚዎች ሊኖሩት እንደሚችል መገመት ጥልቅ ምርምር ማድረግ አይጠይቅም፡፡ ይህንን የምናገረው ሕዝብ ሆኜ በሕዝብ ውስጥ የሚነገረውንና የሕዝብን ብሶት እየኖርኩኝ በማየቴ ነው፡፡

ከላይ ከጠቀስኩት እውነት በሚጻረር መልኩ ግን ከላይ እስከታች ድረስ በተዘረጋው የመንግሥት ስርዓት ውስጥ በኃላፊነት የተመደቡ ባለሥልጣናት፣ አስፈጻሚዎች እና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በአገሪቱ ተቃዋሚ የሌለ እስከሚመስል ድረስ ከሰብኣዊ እስከ ቡድን መብቶችን በመጣስ እና በማፈራረስ በገዛ አገራችን የሁለተኛ ዜግነት ስሜት እንዲሰማን እያደረጉን ይገኛል፡፡ በግሌ መንግሥት እና ሹመኞቹ መብትን ለማፈን የሚያወጣውን ወጪ ሕገመንግሥቱን ለማክበር ቢያወጡት አገሪቱ እውነተኛ ለውጥ ታስመዘግባለች ብዬ አምናለሁ፡፡

“ሕገ-መንግሥቱ ይከበር” - የበይነመረብ ዘመቻ (ጋዜጣዊ መግለጫ!)


ዞን 9 ኢ-መደበኛ የጦማርያን እና አራማጆች ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ማኅበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተለየ እና ወገናዊ ያልሆነ ተረክ ለመፍጠር እየሠራ የሚገኝ የኢትዮጵያዊያን ስብስብ ነው፡፡ የቡድኑ ዓላማ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገሪቷ ጉዳይ በእኩል ስሜት ያገባኛል ብለው ውይይት የማድረግ ባሕል እንዲያሳድጉ በማድረግ ሀገሪቷን በሁሉም መስኮች ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ ሐሳቦች እንዲወለዱ ማመቻቸት ነው፡፡

ይህንንም ዓላማ ከግብ ለማድረስ የተለያዩ የበይነ-መረብ ዘመቻዎች ለማካኼድ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከዘመቻዎቹም መካከል የመጀመሪያው ‹‹ሕገ-መንግሥቱ ይከበር›› በሚል መርኽ ከኅዳር 27 – 29 ቀን 2005 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
ኅዳር 29 ቀን 2005ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት ከተፈረመ 18 ዓመት ይሆነዋል፡፡ በ1987 ዓ.ም ወደሕልውና የመጣው ሕገ-መንግሥት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ አራተኛው ነው፡፡ ይኸው ሕገ-መንግሥት ከሚቀድሙት ሕገ-መንግሥቶች በተሻለ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ያደረገና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች የተሻለ ትኩረት የሰጠ እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ ሆኖም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶች እና የመልካም አስተዳደር መርኾዎች በተደጋጋሚ ሲጣሱ ይስተዋላል፡፡
በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ከተካተቱት ድንጋጌዎች ጥቂቶቹ አሁንም ድረስ አከራካሪ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ድንጋጌዎች ግን የጋራ መግባባት የተደረሰባቸው ናቸው፡፡ የዚህ ዘመቻ ዓላማ በዋነኝነት የሚሆነውም እነዚህን የጋራ መግባቢያ ላይ የተደረሰባቸውን የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች ማስተዋወቅ እና የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ-መንግሥት ሁሉም የመንግሥት አካላት እና ዜጎች እንዲያከብሩ እና አንዲያስከብሩ መጠየቅ ነው፡፡
ዘመቻው በዋነኛነት የሚካሄደው ‹‹ፌስቡክ›› እና ‹‹ትዊተርን›› በመጠቀም ይሆናል፡፡ ሕገ-መንግሥትን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎች በጦማራችን የሚወጡ ሲሆን በፌስቡክ እና በትዊተርም ላይ ይወጣሉ፡፡ (ለዚህም ‘#RespectTheConstitution’ን ጨምሮ ሌሎችንም የትዊተር ‹ታግ› እንጠቀማለን፤) በሁለቱም የማኅበረሰብ ገጾች ላይ ለዚሁ ዘመቻ ሲባል የተዘጋጁ አጫጭር ጽሑፎች ይሰራጫሉ፡፡ ዘመቻውን የሚመለከቱ ‹ባነሮች› ተዘጋጅተው ዘመቻው በሚቆይባቸው ቀናት የፕሮፋይል ፎቶ ይሆናሉ፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ለመላው የዞን9 ነዋሪዎች እና ሕገ-መንግሥቱ ተከብሮ ማየት ለምትፈልጉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ያላችሁን አመለካከት፣ ሕገ-መንግሥቱ የተጣሰባቸውን ክስተቶች በማካፈል እንዲሁም የፕሮፋይል ፎቷችሁን በመቀየር የዘመቻው ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑ በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ስለሚያገባን እንጦምራለን!!!
ናትናኤል ፈለቀ፤ የዘመቻው አስተባባሪ - “ሕገ-መንግሥቱ ይከበር!”