Tuesday, May 26, 2015

የጦማርያኑ እና የጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ ከሚገኙት ሰባት የዞን 9 ጦማርያን እና ሶስት ወዳጅ ጋዜጠኞች ስድስቱ ጦማርን እና ሶስቱ ጋዜጠኞች ዛሬ ግንቦት 18/2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛው ፍ/ቤት ቀርበዋል፡፡ መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ሁለት ጉዳዮችን ለማየት ሲሆን፣ አንደኛው አቃቤ ህግ በኤግዚቢትነት አሉኝ ያላቸውን ኤግዚቢቶችና 12 ሲ.ዲዎች መዝገብ ቁጥራቸውን በመጥቀስ አሟልቶ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሰረት ማቅረቡን ለመመልከት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የአቃቤ ህግ ቀሪ የደረጃ ምስክሮችን ለመስማት ነበር፡፡
በዚህ መሰረት አቃቤ ህግ በኤግዚቢትነት የያዛቸውን ላፕቶፕ፣ ሞባይል፣ ሲምካርድ፣ ሃርድ ዲስክ ይዞ ቀርቧል፡፡ ሆኖም ግን ሲ.ዲዎችን በተመለከተ ሲጠየቅ ‹‹ሲ.ዲዎቹ እየመጡ ነው››የሚል ምላሽ በመስጠቱ እና የተከሳሾች ጠበቆች ሲዲዎቹ ሳይመጡ ምስክሮች መሰማት የለባቸውም ብለው በመቃወማቸው ሲዲው ከማእከላዊ ምርመራ እስኪመጣ ምስክሮች አያሰሙም ተብሎ ለከሰአት ተቀጥሮ ነበር ፡፡
ከሰአት በኋላ አቃቤ ህግ ቀሪ ናቸው ካላቸው 16 ምስክሮች መካክል 3ቱን ብቻ ይዞ የቀረበ ሲሆን 13ቱን ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል፡፡ የቀረቡት ሶስቱንም ፍተሻ ሲከናወን ያዩ የደረጃ ምስክሮች ሲሆኑ ፍተሻ ሲከናወን ከማየታቸው በስተቀር ተጨማሪ ነገር መመስከር አልቻሉም ፡፡
የምስክሮች ቃል
19ኛ ምስክር፡- ቸርነት ተፈራ ይባላል፤ 23 አመቱ ነው፡፡ ደንብ በማስከበር ስራ ላይ እንደተሰማራ የገለጸው ይኸው ምስክር አድራሻው አ.አ ጉለሌ ክ/ከተማ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ ላይ ነው ምስክርነቱን አሰምቷል፡፡ "ቤት ሲፈተሽ አይቻለሁ፣ ሲ.ዲ፣ ላፕቶፕ፣ አሮጌ ካሜራ፣ ሚዲያ ኤንድ ኢሌክሽን የሚል ጽሑፍ፣ መጽሐፍ፣ ወረቀቶች፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተገኝተዋል፡፡ የላፕቶፑን አይነት አላስታውስም፡፡ ሲ.ዲዎች ሁለት ናቸው፣ ይዘታቸውን ግን አላውቅም፡፡ እሷ የፈረመችበትን አንዳለ ፈርመናል ብሏል፡፡
ለምስክሩ ‹‹ሲ.ዲው ባዶ ይሁን የተጻፈበት ይሁን ያየኸው ነገር ነበር›› የሚል መስቀለኛ ጥያቄ ሲቀርብለት ‹‹አላየሁም›› ሲል መልሷል፡፡ ሲ.ዲው ላይ ፈርመሃል ሲባልም መፈረሙን አስረድቷል፡፡ በዚህ ጊዜ የፈረመበትን ሲ.ዲ እንዲያሳይ ተጠይቆ አቃቤ ህግ ጣልቃ በመግባት ‹‹ኤዶም ላይ ሲ.ዲ በማስረጃነት አልያዝንም›› የሚል አስገራሚ መልስ ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ምስክሩ 30 ገጽ የእንግሊዝኛ ጽሁፍ የተጻፈበት ወረቀት ላይ መፈረሙን ስለገለጸ ፊርማውን እንዲለይ ሰነዱ ይቅረብላቸው ሲባልም አቃቤ ህግ ‹‹በማስረጃነት አላያያዝንም›› ብሏል፡፡ ምስክሩ ሁለት በማስረጃነት ባልተያዙ ሰነዶች ላይ ነበር ምስክርነቱን የሰጠው ፡፡ በተጨማሪም በፍተሻ ወቅት የተገኘውን ላፕቶፕ እነዲያሳይ የተጠየቀው ምስከሩ የጦማሪ አቤል ዋበላን ላፕቶፕ አሳይተዋል፡፡
20ኛ ምስክር፡- እኒህ ምስክር ደግሞ ቢላል ሙሄ የሱፍ የሚባሉ ሲሆን 38 አመታቸው ነው፡፡ ‹‹ሚያዝያ 2006 ፌደራል ፖሊስ የተስፋለምን ቤት ሲፈትሽ በታዛቢነት አይቻለሁ፡፡ ቤቱን የከፈተው ተስፋለም ነው፡፡ ቤቱ ውስጥ ብዙ መጽሔትና ጋዜጦች፣ መጽሐፎች፣ ወረቀቶች፣ መቅረጸ ድምጽ፣ ላፕቶፕ ተገኝተዋል፡፡›› ተስፋለም ቤት 28 ሲዲዎች ተገኝተዋል ያሉት ምስክሩ ምን አይነት ይዘት አንደነበራቸው ባዶ ይሁኑ ጽሁፍ ያላቸው አላውቅም እነዲሁም ሲዲዎቹ ወጥቶ የታተመ ነገር አላስታውስም ብለዋል፡፡
21ኛ ምስክር፡- ሚሊዮን አሸብር ደግሞ የ31 አመት በንግድ ስራ ላይ የተሰማራ የአ.አ ነዋሪ ነው፡፡ ለምስክርነት መምጣቱን የገለጸው ሚሊዮን በማን ላይ ልትመሰክር ነው የመጣኸው ሲባል በአማኑኤል ፈለቀ ላይ ሲል መልሷል፡፡ ሆኖም ግን ዳኞች ደጋግመው ሲጠይቁት ስሙን አስተካክሎ በናትናኤል ፈለቀ ላይ ሊመሰክር መሆኑን ገልጹዋል፡፡
‹‹ሚያዝያ 17/2006 ቂርቆስ ክ/ከተማ ኮንስትራክሽን ባንክ ፌደራል ፖሊስ የፍርድ ቤት ወረቀት አሳይቶ ፍተሻ ሊያደርግ ስለሆነ እንድታዘብለት ጠይቆኝ ታዝቤያለሁ፡፡ ናትናኤል ፍተሻው እንዲካሄድ ፈቃደኛ ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ተፈትሹዋል፤ ፍተሻውንም አይቻለሁ፡፡ ላፕቶፕ፣ ሲ.ዲዎች (በቁጥር ወደ 16 የሚሆኑ) እና ሰነዶች ተገኝተዋል፡፡ የተገኙት ነገሮች ላይ ፈርሜያለሁ ፡፡ ሲዲም ሆነ ላፕቶፑ ውስጥ ያለውን ነገር ይዘት አላየሁም አላውቅምም ብሏል ፡፡ ላፕቶፑንም ቀርቦ አሳይቷል ፡፡
ሲዲዎቹ
አወዛጋቢዎቹ ሲዲዎች ዛሬም ቀርበዋል ተባለ እነጂ በአቃቤ ህግና በጠበቆች መካከል ያለው ክርክር አልተቋጨም ፡፡ ሲዲዎቹ ኤግዚቢት ስለሆኑ ለተከሳሾች ለማድረስ አልገደድም ሲል የነበረው የአቃቤ ህግ ክርክር ዛሬ ሲዲዎቹ የሰነድ ማስረጃው ላይ የተያያዙትን ሰነዶች ከላፕቶፕ የገለበጥንባቸው ናቸው ብሎ የሰነድ ማስረጃ አካል አድርጓቸዋል ፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች ሲዲዎቹ ማስረጃ ከሆኑ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ አመልክተዋል፡፡ ሲዲዎቹ አንድ ወይም ሁለቱ ናቸው የቪዲዮ ማስረጃ ያላቸው ሌላው ከክሱ ጋር የተያያዘውን ሰነድ የገለበጥንበት ነው፣ ሁሉም በሰነድ የተያየዙ ናቸው ሲል አቃቤ ህግ አዲስ የህግ ፍሬ ነገር አቅርቧል፡፡
የአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበ ማስረጃ
አቃቤ ህግ በዛሬው ውሎው አዲስ ግኝት ይዞ መጥቷል፡፡ የሲዲ ውዝግቡ መሃል ላይ "አንድ ዶክምንተሪ አንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበና ቡድኑ ለቅስቀሳ ይጠቀምበት የነበረ አለንና ፍርድ ቤቱ ሌሎች ማስረጃዎችን አቅርበን ሰንጨርስ ይሄንን ሲዲ እንዲያይልን" ብሏል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ በማስረጃነት አለኝ ያለው ሲዲ መቼ የተገኘ አንደሆነ ምን ይዘት እንዳለው የተጠቀሰ ነገር የለም ፡፡
በመጨረሻም አቃቤ ህግ ቀሪ 13 የደረጃ ምስክሮቹን ፈልጎ ለማቅረብ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ብሏል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆችም ሲዲዎቹ የሰነድ ማስረጃዎች ከሆኑ እንዲሰጣቸው ካልሆነም ኢግዚቢትነታቸው ምዝገባ እንዲለይ ጠይቀዋል፡፡ በሁለቱ ጉዳዬች ላይ ለመወሰን ለነገ ጠዋት ግንቦት19 ከጠዋቱ 3 ሰአት ተቀጥሯል፡፡
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች በከፍተኛ የአካልና የመንፈስ ደህንነት ሆነው የታዬ ሲሆን ቀኑን ሙሉ ፍርድ ቤት ጊቢ ውስጥ አብረው ለመዋል እድል አግኝተዋል፡፡
የዞን ማስታወሻ
ከዚህ በፌት በተደጋጋሚ አንደጠቀስነው ያልተሰራ ወንጀል ማስረጃና ምስክር አይገኝለትምና ተከሰሾችን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ በማሰናበት ፍርድ ቤቱ ሃላፌነቱን በመወጣት ከህግ የበላይነት ጎን መሆኑን አንዲያሳይ በድጋሚ አንጠይቃለን፡፡
 

 

 

No comments:

Post a Comment