Monday, August 19, 2013

የሕዝብ ንቀት



በፍቃዱ ኃይሉ

‹ከናንተ መካከል የሕዝብ ንቀት የሌለበት ማነው?›

ከትንሹ እስከ ትልቁ፣ ከመንግሥት እስከ ልሒቁ፣ ከሊቁ እስከ ደቂቁ - ሁሉም መጠኑ ይለያይ እንጂ የሕዝብ ንቀት አለበት፡፡ ‹‹ይሄ ሕዝብ…›› ብሎ የበቀለበትን ሕዝብ የማይተች ግለሰብ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እኔ ራሴ ከዚህ በፊት ሕዝብን በአደባባይ ከተቸሁባቸው ጽሑፎች ውስጥ ‹‹ሁሉም ሕዝብ ገዢው መንግሥት ይመጥነዋል››፣ ‹‹ሕዝቦች ግለሰብን ይጨቁናሉ›› እና ‹‹ሕዝብ ምንድን ነው?›› የሚሉ ርዕሶች የሰጠኋቸው አይዘነጉኝም፤ የተሳሳተ መልዕክት ይዘዋል ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ሕዝብን እንደተራ መንጋ ብቻ መቁጠር በጣም ስህተት መሆኑን እና የእያንዳንዱ ዜጋ ድምር ውጤት መሆኑን እና ማኅበረሰቡን ወካይ መሆኑንም ለመጥቀስ ይህንን መጻፍ ያስፈለገኝ፡፡

ንቀት በያይነቱ

በአንድ መጽሔት ውስጥ ለተወሰኑ እትሞች በኤዲተርነት ተቀጥሬ በመሥራት ውስጣዊ አሠራራቸው ምን እንደሚመስል ለመገምገም እና ከተለያዩ በአገራችን በሚዲያ ሥራ ላይ ለረዥም ጊዜ ከተሰማሩ ሰዎች ጋር ለማውራት ሞክሬ ነበር፡፡ የተረዳሁት ነገር ቢኖር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጠሩ የሕዝብ ንቀቶችን ነው፡፡

ቢያንስ ብዙዎቹ የሚዲያ ሰዎች ‹‹ሕዝቡ የሚወደው እንዲህ ዓይነቱን ነገር ነው…›› የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ በደንብ እንድንግባባ ‹‹ሎሚ›› መጽሔት በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ገቢና ስርጭት ያለው ነገር ግን ከፌስቡክ እና ከተለያዩ ብሎጎች ላይ የተቃረሙ፣ ቢያንስ አንድ ሳምንት ያለፋቸው ታሪኮች ጥርቅም ነው፡፡ ይህ ተሞክሮ ሌሎቹን ሚዲያዎች ሎሚ ሞዴላቸው እንዲሆን እና ሕዝቡ ‹በቅጡ ያልታሰበበት እና ያለፈበት ጽሑፍ በተቀጠሩ ሠራተኞች በጥንቃቄ ከተዘጋጀ እና ከትኩስ መጣጥፎች የበለጠ ይመርጣል› የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡ በሁለት እና በሦስት ሠራተኛ ብቻ ከኢቪዲዮ ላይ በወረዱ ሥራዎች አንዱ ሲከብር ሌላው ሌላው ግን በርከት ያሉ ሠራተኞችን ቀጥሮ፣ ከየትም ቀራርሞ የሚያመጣው መረጃ ገዢ አያገኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ‹‹ተጠያቂው የሕዝቡ ቅሽምና ነው›› ይሏችኋል፡፡ እውነታው ግን ይሄ አይደለም፤ እውነታውን እንመለስበታለን… ከዚያ በፊት ግን ይህ ዓይነቱ ችግር ሚዲያው ላይ ብቻ ሳይሆን በየዘርፉ ያለ ችግር መሆኑን ተጨማሪ ምሳሌዎች መዘርዘር አለብን፡፡

የአገራችንን ፊልሞች ከተከታተልን ‹‹በጣም ብዙዎቹ የአገራችን ፊልሞችን ከድርሰት ጀምሮ እስከ ዝግጅት፣ ከቀረጻ ጀምሮ እስከ ‹ኤዲቲንግ›፣ ከትወና ጀምሮ እስከ ዘውግ ድረስ የሚዘልቁ ችግሮች አሉባቸው፤ የፊልም ባለሙያዎች ራሳቸውን በማሻሻል ሥራቸውን ማሻሻል አለባቸው›› የሚል አስተያየት ሲሰነዘር (በተለይ ከባለሙያዎቹ) የሚቀርበው መልስ አስገራሚ ነው፡፡ የፊልም ሠሪዎቹ የፊልሞቹን ችግሮች ይቀበሉና፤ ነገር ግን ‹‹ሕዝቡ የሚፈልገው እንዲህ ዓይነት ፊልም ነው፤ እኛ ምን እናድርግ? ብዙ ወጪ አውጥተን ጥሩ ፊልም ብንሠራ ማን ያይልናል? ብንከስርስ?›› ይሏችኋል፡፡

በተመሳሳይ መንገድ የአገራችንን የሬዲዮ ፕሮግራሞች ተመልከቱ ‹‹ሆይ፣ ሆይታ›› ያበዛሉ… ሌሎችም፣ ሌሎችም፡፡ እንግዲህ ሚዲያውና የፊልም ‹‹ኢንደስትሪው›› (የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ናቸው ብያለሁ) ሕዝቡን በዚህ መንገድ መመልከታቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳለው አትጠራጠሩ፡፡ ችግሩ ግን በነርሱም አይወሰንም፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሂዱና ‹ለምንድን ነው ሕዝቡ ሰብኣዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ሲጣስ ዝም የምትሉት?›› ሲባሉ ሕዝቡ እንደማይተባበር ይናገራሉ፡፡ በነርሱ አተያይ ሕዝቡ በደሉን ውጦ ዝም የሚል እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እነዚህን ለማስቆም የሚያስችል (ልብ በሉ ለማስቆም የሚያስችል ነው ያልኩት) ዕቅድ ይዘው ቢመጡ የማይተባበራቸውና ዕቅዳቸው በወረቀት ላይ የሚባክን ነው የሚመስላቸው፡፡

ገዢው ፓርቲም የተለየ ሐሳብ የለውም፡፡ ሕዝቡ በራሱ ማገናዘብ የማይችል ይመስል፣ ሕዝቡ ምን ማሰብ እንዳለበት፣ እንዴት ማሰብ እንዳለበት መናገር ይቀናዋል፤ በመሠረቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚያምነው ይህንኑ ነው - ‹ሕዝብ በነጻነት ከተለቀቀ መረን ይወጣል› ብሎ ያስባል፡፡ ለምሳሌ ለሕዝቡ የሚበጀውን የማውቅለት እኔ ነኝ ስለዚህ ‹አዋጅ አጽድቄ ስለጠቀሜታው አስረዳዋለሁ እንጂ በቅድሚያ አላማክረውም› የማለት ዝንባሌ አለው፡፡


ለመሆኑ ሕዝባችንን እናውቀዋለን?

ስለሕዝብ ማንነት እና ምንነት ስናወራ ባብዛኛው እኛ ስለምናውቀው እና ስለበቀልንበት ሕዝብ ማውራታችን አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን እኔና እኔን መሰሎቼ በአንድ ላይ ስንሆን ስለምንሰጠው ትርጉም እያወራን ነው ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ማለት በግርድፉ ግለሰቦች በአንድነት ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ለመሆን እያንዳንዱ ግለሰብ ከሌላውጋ ሊያመሳስለው የሚያስችለውን የነጠላ ማንነት በከፊል መሸራረፍ የግድ ይጠይቀዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሕዝባችንን እናውቀዋለን የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልገናል፡፡

በኔ እምነት ሕዝባችንን አናውቀውም፡፡

ሎሚ መጽሔት በሳምንት 20 ሺሕ ሸማች አለው፡፡ ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወደው እንዲህ ዓይነት መጽሔት ነው…›› የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በ20 ሺሕ አይወከልም፡፡ ሁለተኛ፤ ያ 20 ሺሕ ሸማች የሚወክለውን ‹‹ሎሚ›› መጽሔትን አግኝቶ ከሆነ ያንን ዓይነት ሳይሆን የተሻለ ይዘት እና ደረጃ ያለው ጽሑፍ ያለው መጽሔት የሚፈልጉ ሚሊዮኖች አሉ፡፡ ነገርግን በዘርፉ የተሰማሩት በአሁኑ ገበያ ሚዛን ብዙ የሚሸጠው ‹ሎሚ› ስለሆነ የሎሚን ደምበኞች ለመሳብ ነው፡፡ ስለዚህ በተለየ አቀራረብ የሎሚ ደምበኞችን ለመሳብ ሲሞክሩ ባክነው ይቀራሉ፡፡ ነገር ግን የራሳቸው የደረጃ ጣሪያ እና የጥራት እሴት ይዘው ቢመጡ በሎሚ ዓይነቶቹ መጽሔቶች ተሰላችቶ የተገፋው አንባቢን ልብ እና ቀልብ ማግኘት ይችላሉ፤ ነገር ግን አልሞከሩትም፡፡

የአገርኛ ፊልም ተመልካቾች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ብዙኃኑ የሚያስበው በገንዘብ እና በጊዜ መቀለድ እንደሆነ ነው፡፡ ነገርግን የፊልም ሠሪዎቹ አሁንም የሚደክሙት በተዘረጋው የፊልም ባሕል ውስጥ ያሉትን ጥቂት የፊልም ተመልካቾች ከበፊት ፊልሞች ገበያ አንፃር ‹‹ይወዷቸዋል…›› ብለው የሚገምቷቸውን ታሪኮች እና እንቶ ፈንቶዎች ይዞ መፍጨርጨር ነው እንጂ፣ አዲስ እና የተሻለ ነገር ይዘው ሲመጡ አይታዩም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሴባስቶፖል ሲኒማ የሚያመርታቸው ፊልሞች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየወጣባቸው፣ በሚሊዮኖች ሲያተርፉ በመመልከት ፈንታ… ‹ሕዝባችን ሮማንቲክ ኮሜዲ ካልሆነ በቀር አይወድም› በሚለው አባባላቸው መቁረባቸውን ቀጥለዋል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች… በአብዛኛው የብሶተኞች እና የሥልጣን ጥመኞች ቤቶች ናቸው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ መወዳደር ከጀመሩባቸው ጊዜያት ጀምሮ የተፈጠሩት ችግሮች፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጠራ ፖሊሲ አለመኖር፣ እርስ በእርስ መጋጨት፣ እና ሌሎችም ችግሮች ተደማምረው ሕዝቡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎታል፡፡ ብዙኃኑ ልሒቅ ተቃዋሚዎቹን ጥሎ ሲሸሽ፣ ጥቂት ሕዝባዊ ልዩነቶችን እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ራሱ በቅጡ የማይረዱ ግለሰቦች ፓርቲዎቹን ተቆጣጥረዋቸዋል፡፡ እያንዳንዱን ዝርዝር የማያውቀው ሕዝብ፣ ድምሩን ግን መረዳት ይችላልና በተቃዋሚዎች እምነት ቢያጣ ‹‹ሕዝቡ ጭቆና ተስማምቶት እንደተኛ…›› ሊታሰብ አይገባም፡፡

ከዚህ በፊት አንድ ወዳጄ ከጠቀሳት በኋላ ደጋግሜ እንደተጠቀምኩበት ‹‹አህያ ማር አይጥማትም ሲባል ማን ሰጥቶ ሞከረኝና›› እንዳለችው ሕዝባችንን ማር ሳናቀርብለት ያቀረብኩለትን ሬት ካልተጋተ ብለን ልንንቀው አይገባም፡፡

1 comment: